በዛሬው ጊዜ እየገዛ ያለው መሪያችን
“እሱም ድል እያደረገ ወጣ፤ ድሉንም ለማጠናቀቅ ወደፊት ገሠገሠ።”—ራእይ 6:2
1, 2. (ሀ) ክርስቶስ ከ1914 ወዲህ ንጉሥ ሆኖ ያከናወነው እንቅስቃሴ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተገለጸው እንዴት ነው? (ለ) ክርስቶስ ንጉሥ ሆኖ ከተሾመ በኋላ የትኞቹን እርምጃዎች ወስዷል?
ክርስቶስ በ1914 የይሖዋ መሲሐዊ መንግሥት ንጉሥ ሆኖ ተሹሟል። በአሁኑ ጊዜ ክርስቶስን በዓይነ ሕሊናችን የምንስለው እንዴት አድርገን ነው? በዙፋኑ ላይ ተቀምጦ ጉባኤው በምን ዓይነት ሁኔታ ላይ እንዳለ ለማወቅ አልፎ አልፎ ወደ ምድር በአትኩሮት እንደሚመለከት ንጉሥ አድርገን ነው? ከሆነ አስተሳሰባችንን ማስተካከል ያስፈልገናል። የመዝሙርና የራእይ መጻሕፍት ክርስቶስን የሚገልጹት በፈረስ ላይ ተቀምጦ ‘ድል እያደረገ’ እንዳለና ‘ድሉን እስኪያጠናቅቅ’ ይኸውም የመጨረሻ ‘ድሉን’ እስኪጎናጸፍ ድረስ ወደፊት እንደሚገሰግስ ኃያል ንጉሥ አድርገው ነው።—ራእይ 6:2፤ መዝ. 2:6-9፤ 45:1-4
2 ክርስቶስ ንጉሥ ሆኖ ከተሾመ በኋላ በወሰደው የመጀመሪያ እርምጃ ‘በዘንዶውና በመላእክቱ’ ላይ ድል ተቀዳጅቷል። ክርስቶስ የመላእክት አለቃ ሚካኤል እንደመሆኑ መጠን ሰይጣንንና አጋንንቱን ቅዱስ ስፍራ ከሆነው ከሰማይ በመወርወር በምድር አካባቢ ተወስነው እንዲኖሩ አድርጓቸዋል። (ራእይ 12:7-9) ከዚያም ኢየሱስ የይሖዋ ‘የቃል ኪዳን መልእክተኛ’ በመሆን መንፈሳዊውን ቤተ መቅደስ ለመመርመር ከአባቱ ጋር መጥቷል። (ሚል. 3:1) በዚህ ጊዜ፣ በክፋቷ ተወዳዳሪ የሌላትንና ‘የታላቂቱ ባቢሎን’ ዋነኛ ክፍል የሆነችውን ሕዝበ ክርስትናን ደም ስታፈስ ብሎም ከዚህ ዓለም የፖለቲካ ሥርዓት ጋር መንፈሳዊ ምንዝር ስትፈጽም ስላገኛት ፈርዶባታል።—ራእይ 18:2, 3, 24
በምድር ላይ ያለውን ባሪያውን አነጻው
3, 4. (ሀ) ክርስቶስ የይሖዋ “መልእክተኛ” በመሆን ምን ሥራ አከናውኗል? (ለ) ቤተ መቅደሱ መመርመሩ ምን ነገር ግልጽ እንዲሆን አድርጓል? ኢየሱስ የጉባኤው ራስ እንደመሆኑ መጠን ምን ሹመት ሰጥቷል?
3 በተጨማሪም ይሖዋና ‘መልእክተኛው’ ያደረጉት ምርመራ፣ የሕዝበ ክርስትና ክፍል ያልሆነ የእውነተኛ ክርስቲያኖች ቡድን በመንፈሳዊው ቤተ መቅደስ ምድራዊ አደባባይ ላይ መኖሩን ግልጽ አድርጓል። ይሁን እንጂ እነዚህ የተቀቡ ክርስቲያኖችም ማለትም “ሌዋውያን” መንጻት ይገባቸው ነበር። ነቢዩ ሚልክያስ ይህን ሁኔታ እንደሚከተለው በማለት ገልጾታል፦ “[ይሖዋ] ብርን እንደሚያነጥርና እንደሚያነጻ ሰው ይቀመጣል፤ ሌዋውያንንም አንጽቶ እንደ ወርቅና እንደ ብር ያጠራቸዋል፤ ከዚያም እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] ቍርባንን በጽድቅ የሚያቀርቡ ሰዎች ይኖሩታል።” (ሚል. 3:3) ይሖዋ መንፈሳዊ እስራኤላውያንን ለማንጻት “የቃል ኪዳኑ መልእክተኛ” የሆነውን ክርስቶስ ኢየሱስን ተጠቅሟል።
4 ያም ቢሆን ክርስቶስ ለምርመራ በመጣበት ወቅት እነዚህ ታማኝ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ለእምነት ቤተሰባቸው በጊዜው መንፈሳዊ ምግብ ለማቅረብ የተቻላቸውን ሁሉ ሲያደርጉ ነበር። ከ1879 ጀምሮ እነዚህ ቅቡዓን ክርስቲያኖች በደህናውም ሆነ በአስቸጋሪው ጊዜ፣ ስለ አምላክ መንግሥት የሚናገረውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት በመጠበቂያ ግንብ ላይ ሲያወጡ ቆይተዋል። ኢየሱስ ‘በዚህ ሥርዓት መደምደሚያ’ ላይ ቤተሰቡን ለመመርመር ‘ተመልሶ ሲመጣ’ ለቤተሰቡ “በተገቢው ጊዜ ምግባቸውን” የሚሰጥ ባሪያ እንደሚያገኝ ትንቢት ተናግሮ ነበር። በዚያን ጊዜ ኢየሱስ ለዚህ ባሪያ ደስተኛ መሆኑን የሚገልጽለት ከመሆኑም በላይ በምድር ባለው “ንብረቱ ሁሉ ላይ ይሾመዋል።” (ማቴ. 24:3, 45-47) ክርስቶስ የክርስቲያን ጉባኤ ራስ እንደመሆኑ መጠን ይህን “ታማኝና ልባም ባሪያ” በምድር ላይ የሚገኙትን ከመንግሥቱ ጋር የተያያዙ ነገሮች ለማስተዳደር ይጠቀምበታል። ኢየሱስ ቤተሰቡ ለሆኑት ቅቡዓንና የእነሱ አጋር ለሆኑት “ሌሎች በጎች” በበላይ አካሉ አማካኝነት መመሪያ ሲሰጥ ቆይቷል።—ዮሐንስ 10:16
የምድርን መከር ማጨድ
5. ሐዋርያው ዮሐንስ፣ መሲሐዊው ንጉሥ ምን ሲያደርግ በራእይ ተመልክቷል?
5 ሐዋርያው ዮሐንስ፣ መሲሐዊው ንጉሥ ‘በጌታ ቀን’ ማለትም በ1914 ከተሾመ በኋላ ምን እንደሚያከናውን በራእይ ተመልክቷል። ዮሐንስ እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “እኔም አየሁ፤ እነሆም፣ ነጭ ደመና ነበር፤ በደመናውም ላይ የሰውን ልጅ የሚመስል ተቀምጧል፤ እሱም በራሱ ላይ የወርቅ አክሊል ደፍቷል፣ በእጁም ስለታም ማጭድ ይዟል።” (ራእይ 1:10፤ 14:14) ከይሖዋ የተላከ አንድ መልአክ ‘የምድር መከር ስለደረሰ’ ማጭዱን እንዲሰድ ለዚህ አጫጅ ሲነግረው ዮሐንስ ሰምቷል።—ራእይ 14:15, 16
6. የመከሩ ወቅት ከመድረሱ በፊት በእርሻው ላይ ምን ይከናወናል?
6 ይህ “የምድር መከር” ኢየሱስ ስለ ስንዴውና ስለ እንክርዳዱ የተናገረውን ምሳሌ ያስታውሰናል። ኢየሱስ ጥሩ ስንዴ ለማጨድ አስቦ በእርሻው ላይ ስንዴ ከዘራ ሰው ጋር ራሱን አመሳስሏል፤ ስንዴው ‘የመንግሥቱን ልጆች’ ማለትም ከኢየሱስ ጋር በመንግሥቱ አብረው የሚገዙትን የተቀቡ እውነተኛ ክርስቲያኖች ያመለክታል። ይሁን እንጂ ጠላት የሆነው “ዲያብሎስ” ጨለማን ተገን አድርጎ በእርሻው ላይ እንክርዳድ ማለትም ‘የክፉውን ልጆች’ ዘርቷል። ዘሪው እንክርዳዱና ስንዴው አብረው እንዲያድጉ እስከ መከር ጊዜ ይኸውም ‘እስከዚህ ሥርዓት መደምደሚያ’ ድረስ እንክርዳዱን እንዲተዉት ለሠራተኞቹ ነገራቸው። የመከሩ ጊዜ ሲደርስ ስንዴውን ከእንክርዳዱ እንዲለዩ መላእክቱን ይልካቸዋል።—ማቴ. 13:24-30, 36-41
7. ክርስቶስ ‘የምድርን መከር’ የመሰብሰቡን ሥራ እየመራ ያለው እንዴት ነው?
7 ዮሐንስ በተመለከተው ራእይ ፍጻሜ መሠረት ኢየሱስ ዓለም አቀፉን የመከር ሥራ በበላይነት ሲመራ ቆይቷል። “የምድር መከር” መታጨድ የጀመረው ኢየሱስ በተናገረው ምሳሌ ላይ ‘በስንዴ’ የተመሰሉትንና “የመንግሥቱ ልጆች” የተባሉትን የ144,000 ቀሪ አባላት በመሰብሰብ ነው። ከአንደኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በእውነተኛና በሐሰተኛ ክርስቲያኖች መካከል ያለው ልዩነት ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ግልጽ ከመሆኑ የተነሳ ሰዎች ይህን ልዩነት በቀላሉ ማስተዋል ችለዋል፤ ይህ ደግሞ ‘ለምድር መከር’ ሁለተኛ ክፍል ማለትም ሌሎች በጎችን ለመሰብሰቡ ሥራ አስተዋጽኦ አድርጓል። እነዚህ በጎች “የመንግሥቱ ልጆች” አይደሉም፤ ከዚህ ይልቅ ለዚህ መንግሥት በፈቃደኝነት የሚገዙ “እጅግ ብዙ ሕዝብ” ናቸው። የተሰበሰቡት ‘በልዩ ልዩ ቋንቋ ከሚናገሩ ሰዎች፣ መንግሥታትና [“ብሔሮችና፣” NW] ሕዝቦች’ ነው። እነዚህ ሰዎች፣ ክርስቶስ ኢየሱስንና ከእሱ ጋር በሰማይ አብረው የሚገዙትን 144,000 “ቅዱሳን” ላቀፈው መሲሐዊ መንግሥት በፈቃደኝነት ይገዛሉ።—ራእይ 7:9, 10፤ ዳን. 7:13, 14, 18
ጉባኤዎችን መምራት
8, 9. (ሀ) ክርስቶስ የእያንዳንዱን ጉባኤ አጠቃላይ ሁኔታ ብቻ ሳይሆን የእያንዳንዱን የጉባኤ አባል አኗኗር ጭምር እንደሚመለከት የሚጠቁመው ምንድን ነው? (ለ) በገጽ 26 ላይ ከሚገኘው ሥዕላዊ መግለጫ መመልከት እንደምንችለው ልንርቃቸው የሚገቡ ‘የሰይጣን ጥልቅ ነገሮች’ ምንድን ናቸው?
8 ከዚህ በፊት ባለው የጥናት ርዕስ ላይ ክርስቶስ በአንደኛው መቶ ዘመን የነበረውን የእያንዳንዱን ጉባኤ መንፈሳዊ ሁኔታ በትኩረት ይከታተል እንደነበር ተመልክተናል። በዚህ ዘመንም መሪያችን ክርስቶስ “ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር” የተሰጠው ንጉሥ እንደመሆኑ መጠን በዓለም ዙሪያ ያሉት ጉባኤዎችና የበላይ ተመልካቾቻቸው ራስ ሆኖ እያስተዳደረ ነው። (ማቴ. 28:18፤ ቆላ. 1:18) ይሖዋ ክርስቶስን ከቅቡዓን ‘ጉባኤ ጋር በተያያዘ በሁሉ ነገር ላይ ራስ አድርጎታል።’ (ኤፌ. 1:22) በመሆኑም ከ100,000 በሚበልጡት የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ውስጥ ሁሉ የሚደረገው እያንዳንዱ እንቅስቃሴ ከእሱ የተሰወረ አይደለም።
9 ኢየሱስ ጥንት ለነበረው የትያጥሮን ጉባኤ የሚከተለውን መልእክት ልኮ ነበር፦ “እንደ እሳት ነበልባል የሆኑ ዓይኖች . . . ያሉት የአምላክ ልጅ እንዲህ ይላል፦ ‘ሥራህን [አውቃለሁ።]’” (ራእይ 2:18, 19) ኢየሱስ “እኔ ኩላሊትንና ልብን የምመረምር [ነኝ] . . . ለእናንተም በግለሰብ ደረጃ እንደሥራችሁ እሰጣችኋለሁ” በማለት የሥነ ምግባር ብልግና ይፈጽሙና የራሳቸውን ፍላጎት ያሳድዱ የነበሩትን የዚያ ጉባኤ አባላት አውግዟቸዋል። (ራእይ 2:23) ይህ ጥቅስ ክርስቶስ የእያንዳንዱን ጉባኤ አጠቃላይ ሁኔታ ብቻ ሳይሆን የእያንዳንዱን የጉባኤ አባል አኗኗር ጭምር እንደሚመለከት ይጠቁማል። ኢየሱስ ‘“የሰይጣንን ጥልቅ ነገሮች” የማያውቁትን’ በትያጥሮን የሚኖሩ አንዳንድ ክርስቲያኖችን አመስግኗቸዋል። (ራእይ 2:24) ዛሬም በተመሳሳይ ክርስቶስ ልል አቋም የሚንጸባረቅበት አስተሳሰብ በማዳበር ወይም ደግሞ በኢንተርኔት አሊያም ዓመፅ በሞላባቸው የቪዲዮ ጨዋታዎች አማካኝነት “የሰይጣንን ጥልቅ ነገሮች” ለማወቅ ከመሞከር የሚቆጠቡ ወጣቶችንም ሆነ አዋቂዎችን ያመሰግናቸዋል። በአሁኑ ጊዜ ያሉ በርካታ ክርስቲያኖች በማንኛውም የሕይወታቸው ዘርፍ አቅማቸው በፈቀደላቸው መጠን የእሱን አመራር ለመከተል ሲሉ የሚያደርጉትን ጥረትም ሆነ የሚከፍሉትን መሥዋዕትነት ሲመለከት ምንኛ ይደሰት ይሆን!
10. ክርስቶስ ለጉባኤ ሽማግሌዎች አመራር እንደሚሰጥ የተገለጸው በምን መንገድ ነው? ይሁንና ሽማግሌዎች ምን ነገር መገንዘብ ይኖርባቸዋል?
10 ክርስቶስ በተሾሙ ሽማግሌዎች አማካኝነት በምድር ላይ ለሚገኙ ጉባኤዎቹ ፍቅራዊ አመራር ይሰጣል። (ኤፌ. 4:8, 11, 12) በመጀመሪያው መቶ ዘመን ሁሉም የበላይ ተመልካቾች በመንፈስ የተወለዱ ነበሩ። እነዚህ የበላይ ተመልካቾች በክርስቶስ ቀኝ እጅ እንዳሉ ከዋክብት ተደርገው ተገልጸዋል። (ራእይ 1:16, 20) በዛሬው ጊዜ አብዛኞቹ የጉባኤ ሽማግሌዎች የሌሎች በጎች አባላት ናቸው። እነዚህ ሽማግሌዎች የሚሾሙት በጸሎትና በመንፈስ ቅዱስ አመራር አማካኝነት እንደመሆኑ መጠን እነሱም በክርስቶስ እጅ ውስጥ ማለትም በእሱ አመራር ሥር እንደሆኑ ተደርገው ሊቆጠሩ ይችላሉ። (ሥራ 20:28) ያም ሆኖ እነዚህ ሽማግሌዎች፣ ክርስቶስ በምድር ያሉትን ደቀ መዛሙርቱን ለመምራት በመንፈስ የተቀቡ ጥቂት ወንድሞችን ያቀፈውን የበላይ አካል እየተጠቀመ እንደሆነ ይገነዘባሉ።—የሐዋርያት ሥራ 15:6, 28-30ን አንብብ።
“ጌታ ኢየሱስ፣ ና”
11. መሪያችን ቶሎ እንዲመጣ የምንጓጓው ለምንድን ነው?
11 ሐዋርያው ዮሐንስ በተቀበለው ራእይ ላይ ኢየሱስ ቶሎ እንደሚመጣ ለበርካታ ጊዜያት ተናግሮ ነበር። (ራእይ 2:16፤ 3:11፤ 22:7, 20) ኢየሱስ የሚመጣው በታላቂቱ ባቢሎንና በተቀረው የሰይጣን ክፉ ሥርዓት ላይ የቅጣት ፍርድ ለማስፈጸም እንደሆነ ጥርጥር የለውም። (2 ተሰ. 1:7, 8) አረጋዊው ሐዋርያ ዮሐንስ አስቀድመው የተነገሩትን አስደናቂ ክንውኖች ፍጻሜ ለማየት ከመጓጓቱ የተነሳ “አሜን! ጌታ ኢየሱስ፣ ና” ብሎ ነበር። በዚህ ክፉ ሥርዓት የፍጻሜ ዘመን ላይ የምንኖረው ክርስቲያኖችም መሪያችንና ንጉሣችን የአባቱን ስም ለማስቀደስና ሉዓላዊነቱን ለማረጋገጥ የመንግሥቱን ሥልጣን ይዞ ሲመጣ ለመመልከት እንናፍቃለን።
12. የጥፋት ነፋሳት ከመለቀቃቸው በፊት ክርስቶስ የሚያጠናቅቀው ሥራ ምንድን ነው?
12 ኢየሱስ በዓይን የሚታየውን የሰይጣን ድርጅት ከማጥፋቱ በፊት የ144,000ዎቹ ክፍል የሆኑት የመንፈሳዊ እስራኤላውያን የመጨረሻ አባላት ለመጨረሻ ጊዜ ማኅተም ይደረግባቸዋል። የሰይጣንን ሥርዓት የሚያጠፉት ነፋሳት፣ የ144,000ዎቹ መታተም ሳያበቃ እንደማይለቀቁ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ይናገራል።—ራእይ 7:1-4
13. ክርስቶስ ‘በታላቁ መከራ’ የመጀመሪያ ምዕራፍ ላይ መገኘቱን ይፋ የሚያደርገው እንዴት ነው?
13 አብዛኞቹ የምድር ነዋሪዎች ክርስቶስ ከ1914 ጀምሮ ‘መገኘቱን’ አላስተዋሉም። (2 ጴጥ. 3:3, 4) ይሁንና በቅርቡ የሰይጣን ሥርዓት በተገነባባቸው የተለያዩ ንጥረ ነገሮች ላይ የይሖዋን ፍርድ በማስፈጸም መገኘቱን ይፋ ያደርጋል። “የዓመፅ ሰው” መወገድ ማለትም የሕዝበ ክርስትና የቀሳውስት ቡድን መጥፋት የክርስቶስን “መገኘት” በማያሻማ ሁኔታ ‘ይፋ ያደርጋል።’ (2 ተሰሎንቄ 2:3, 8ን አንብብ።) በተጨማሪም ክርስቶስ በይሖዋ የተሾመ ፈራጅ በመሆን እርምጃ መውሰድ እንደጀመረ ጠንካራ ማስረጃ ይሆናል። (2 ጢሞቴዎስ 4:1ን አንብብ።) በክፋቷ ተወዳዳሪ በሌላትና ‘የታላቂቱ ባቢሎን’ ክፍል በሆነችው ሕዝበ ክርስትና ላይ የሚወሰደው የጥፋት እርምጃ፣ በክፉው ዓለም ሃይማኖታዊ ግዛት ላይ ለሚደርሰው አጠቃላይ ጥፋት ጥርጊያ መንገድ ይከፍታል። ይሖዋ ይህችን መንፈሳዊ ጋለሞታ ከሕልውና ውጪ እንዲያደርጓት የፖለቲካ መሪዎችን ልብ ያነሳሳል። (ራእይ 17:15-18) ይህ ደግሞ ‘የታላቁ መከራ’ የመጀመሪያ ምዕራፍ ይሆናል።—ማቴ. 24:21
14. (ሀ) የታላቁ መከራ የመጀመሪያ ክፍል እንዲያጥር የሚደረገው ለምንድን ነው? (ለ) “የሰው ልጅ ምልክት” ለይሖዋ ሕዝቦች ምን ትርጉም ይኖረዋል?
14 ኢየሱስ የታላቁ መከራ ቀናት “ለተመረጡት” ማለትም በምድር ላይ ለቀሩት ቅቡዓን ክርስቲያኖች ሲባል እንደሚያጥር ተናግሯል። (ማቴ. 24:22) ይሖዋ በሐሰት ሃይማኖት ላይ በሚወስደው የጥፋት እርምጃ ቅቡዓን ክርስቲያኖችም ሆኑ አጋሮቻቸው የሆኑት ሌሎች በጎች እንዲጠፉ አይፈቅድም። አክሎም ኢየሱስ “በእነዚያ ቀናት ከሚኖረው መከራ በኋላ” በፀሐይ፣ በጨረቃ እና በከዋክብት ላይ ምልክት እንደሚታይ ከዚያም “የሰው ልጅ ምልክት በሰማይ” እንደሚታይ ተናግሯል። ይህ ሁኔታ የምድር ብሔራት ‘እያለቀሱ ደረታቸውን እንዲደቁ’ ያደርጋቸዋል። ሰማያዊ ተስፋ ያላቸው ቅቡዓኑም ሆኑ ምድራዊ ተስፋ ያላቸው አጋሮቻቸው እንዲህ ያለው ሁኔታ አይደርስባቸውም። ከዚህ ይልቅ ‘መዳናቸው እየቀረበ ስለሆነ ቀጥ ብለው ይቆማሉ፤ ራሳቸውንም ቀና ያደርጋሉ።’—ማቴ. 24:29, 30፤ ሉቃስ 21:25-28
15. ክርስቶስ ሲመጣ ምን ሥራ ያከናውናል?
15 የሰው ልጅ ድሉን ከማጠናቀቁ በፊት በሌላ መንገድም ይመጣል። እንዲህ በማለት ትንቢት ተናግሯል፦ “የሰው ልጅ ከመላእክቱ ሁሉ ጋር በክብሩ ሲመጣ በክብራማ ዙፋኑ ላይ ይቀመጣል። ሕዝቦችም ሁሉ በፊቱ ይሰበሰባሉ፤ እሱም እረኛ በጎቹን ከፍየሎቹ እንደሚለይ ሰዎችን አንዱን ከሌላው ይለያል። በጎቹን በቀኙ፣ ፍየሎቹን ግን በግራው ያደርጋቸዋል።” (ማቴ. 25:31-33) ይህ ጥቅስ ክርስቶስ ‘ሕዝቦችን ሁሉ’ በሁለት ቡድን ለመለየት ፈራጅ ሆኖ እንደሚመጣ ያሳያል፤ መንፈሳዊ ወንድሞቹን (በምድር ላይ ያሉትን ቅቡዓን ክርስቲያኖች) የሚደግፉትን ሰዎች ‘በጎች’፣ ‘ስለ ጌታችን ኢየሱስ ለሚገልጸው ምሥራች የማይታዘዙትን’ ደግሞ ‘ፍየሎች’ በማለት ይለያቸዋል። (2 ተሰ. 1:7, 8) “ጻድቃን” እንደሆኑ ተደርገው የተገለጹት በጎች በምድር ላይ ‘የዘላለም ሕይወት’ የሚያገኙ ሲሆን ፍየሎቹ ግን “ወደ ዘላለም ጥፋት” ይሄዳሉ።—ማቴ. 25:34, 40, 41, 45, 46
ኢየሱስ ድሉን ያጠናቅቃል
16. መሪያችን ክርስቶስ ድሉን የሚያጠናቅቀው እንዴት ነው?
16 ክርስቶስ ነገሥታትና ካህናት ሆነው ከእሱ ጋር የሚገዙት ቅቡዓን ቁጥራቸው ተሟልቶ ማኅተም ከተደረገባቸው እንዲሁም በጎቹ ተለይተው መዳን እንዲያገኙ በቀኙ ከተደረጉ በኋላ ‘ድሉን ለማጠናቀቅ ወደፊት ይገሠግሣል።’ (ራእይ 5:9, 10፤ 6:2) ኃያላን መላእክትን ያቀፈውን የሰማይ ሠራዊት (ከሞት የተነሱትን ወንድሞቹን እንደሚጨምር ጥርጥር የለውም) በመምራት በምድር ላይ የሚገኘውን መላውን የሰይጣን ፖለቲካዊ፣ ወታደራዊና የንግድ ሥርዓት ድምጥማጡን ያጠፋል። (ራእይ 2:26, 27፤ 19:11-21) ክርስቶስ የሰይጣንን ክፉ ሥርዓት በሚያጠፋበት ጊዜ ድሉ ይጠናቀቃል። ከዚያም ሰይጣንን እና አጋንንቱን በጥልቁ ውስጥ ያስራቸዋል።—ራእይ 20:1-3
17. ክርስቶስ በሺህ ዓመት ግዛቱ ወቅት ሌሎች በጎቹን ወዴት ይመራቸዋል? ቁርጥ ውሳኔያችን ምን ሊሆን ይገባል?
17 ሐዋርያው ዮሐንስ ከታላቁ መከራ በሕይወት የሚተርፉትንና የሌሎች በጎች ክፍል የሆኑትን “እጅግ ብዙ ሕዝብ” በማስመልከት ትንቢት ሲናገር “በዙፋኑ መካከል ያለው በጉ እረኛቸው ይሆናል፤ ወደ ሕይወት ውኃ ምንጭም ይመራቸዋል” ብሏል። (ራእይ 7:9, 17) አዎን፣ ክርስቶስ በሺው ዓመት ግዛቱ ወቅት የእሱን ድምፅ ከልብ የሚሰሙትን ሌሎች በጎች መምራቱን በመቀጠል ወደ ዘላለም ሕይወት ይወስዳቸዋል። (ዮሐንስ 10:16, 26-28ን አንብብ።) እንግዲያው ንጉሥ የሆነውን መሪያችንን በአሁኑ ጊዜም ሆነ ይሖዋ በሚያመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ በታማኝነት ለመከተል ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ!
ለክለሳ ያህል
• ክርስቶስ ንጉሥ ሆኖ ከተሾመ በኋላ የትኞቹን እርምጃዎች ወስዷል?
• ክርስቶስ ጉባኤውን ለመምራት በምድር ላይ የሚጠቀመው ማንን ነው?
• መሪያችን ክርስቶስ ወደፊት የሚመጣው በየትኞቹ መንገዶች ነው?
• ክርስቶስ በአዲሱ ዓለም እኛን መምራቱን የሚቀጥለው እንዴት ነው?
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የሰይጣን ክፉ ሥርዓት መጥፋቱ የክርስቶስ መገኘት ይፋ እንዲሆን ያደርጋል