የይሖዋ ቃል ሕያው ነው
የራእይ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች—ክፍል 2
ይሖዋ አምላክን የሚያመልኩና የማያመልኩ ሰዎች ወደፊት ምን ይጠብቃቸዋል? የሰይጣንና የአጋንንቱ የወደፊት ዕጣ ምንድን ነው? ታዛዥ የሆኑ የሰው ልጆች በክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ወቅት ምን በረከቶች ያገኛሉ? ራእይ 13:1 እስከ 22:21 ለእነዚህና ለሌሎች አስፈላጊ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል።a እነዚህ ምዕራፎች፣ ሐዋርያው ዮሐንስ ከክርስቶስ ልደት በኋላ በመጀመሪያው መቶ ዘመን መገባደጃ አካባቢ ካያቸው 16 ራእዮች መካከል የመጨረሻዎቹን 9 ራእዮች ይዘዋል።
ዮሐንስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “የዚህን ትንቢት ቃል ጮክ ብሎ የሚያነብ እንዲሁም ቃሉን የሚሰሙና በውስጡ የተጻፉትን ነገሮች የሚጠብቁ ደስተኞች ናቸው።” (ራእይ 1:3፤ 22:7) የራእይን መጽሐፍ ማንበባችንና ያገኘናቸውን ትምህርቶች በተግባር ማዋላችን ልባችንን ሊነካው፣ በአምላክና በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ያለንን እምነት ሊያጠናክረው እንዲሁም ስለ ወደፊቱ ጊዜ ብሩኅ ተስፋ እንዲኖረን ሊረዳን ይችላል።b—ዕብ. 4:12
የአምላክን ቁጣ የያዙ ሰባት ሳህኖች ፈሰሱ
ራእይ 11:18 እንዲህ ይላል፦ “ሕዝቦች ተቆጡ፤ [የአምላክ] ቁጣ መጣ፤ ደግሞም . . . ምድርን እያጠፉ ያሉትን የምታጠፋበት የተወሰነው ጊዜ መጣ።” ስምንተኛው ራእይ ‘አሥር ቀንዶችና ሰባት ራሶች ያሉት አውሬ’ ስለሚያከናውናቸው ነገሮች የሚገልጽ ሲሆን ይህም የአምላክ ቁጣ የመጣበትን ምክንያት ለመረዳት ያስችለናል።—ራእይ 13:1
ዮሐንስ በዘጠነኛው ራእይ ላይ “በጉ በጽዮን ተራራ ላይ [ቆሞ]” የተመለከተ ሲሆን ከበጉ ጋር “አንድ መቶ አርባ አራት ሺህ” ሰዎች ነበሩ። አንድ መቶ አርባ አራት ሺዎቹ “ከሰዎች መካከል [የተዋጁ]” ናቸው። (ራእይ 14:1, 4) ከዚያም ዮሐንስ፣ መላእክት አዋጆችን ሲያውጁ ሰማ። በቀጣዩ ራእይ ላይ ደግሞ “ሰባት መቅሰፍቶች የያዙ ሰባት መላእክት” ተመለከተ። ከሁኔታዎቹ ለመረዳት እንደሚቻለው “የአምላክን ቁጣ የያዙትን ሰባቱን ሳህኖች” በሰይጣን ዓለም የተለያዩ ክፍሎች ላይ እንዲያፈሱ እነዚህን መላእክት ያዘዛቸው ይሖዋ ራሱ ነው። ሳህኖቹ አምላክ ስለሚያመጣው ፍርድ የሚገልጹ መልእክቶችንና ማስጠንቀቂያዎችን ይዘዋል። (ራእይ 15:1፤ 16:1) እነዚህ ሁለት ራእዮች ከሦስተኛው ወዮታና ከሰባተኛው መለከት መነፋት ጋር በተያያዘ የአምላክ መንግሥት ስለሚያመጣቸው ፍርዶች የሚገልጹ ተጨማሪ ማብራሪያዎች ይሰጣሉ።—ራእይ 11:14, 15
ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው፦
13:8—‘የበጉ የሕይወት መጽሐፍ ጥቅልል’ ምንድን ነው? ይህ ጥቅልል ምሳሌያዊ ሲሆን በጥቅልሉ ውስጥ የሰፈረው፣ በሰማይ በሚገኘው የኢየሱስ ክርስቶስ መንግሥት ከእሱ ጋር አብረው የሚገዙት ሰዎች ስም ብቻ ነው። በሰማይ የዘላለም ሕይወት የመውረስ ተስፋ ያላቸው በምድር ላይ የሚገኙ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ስምም በዚህ ጥቅልል ውስጥ ይገኛል።
13:11-13—ሁለት ቀንዶች ያሉት አውሬ እንደ ዘንዶ የሚናገረውና ከሰማይ ወደ ምድር እሳት የሚያወርደው እንዴት ነው? ሁለት ቀንዶች ያሉት አውሬ ማለትም የአንግሎ አሜሪካ የዓለም ኃያል መንግሥት እንደ ዘንዶ መናገሩ ሰዎች የእሱን አገዛዝ እንዲቀበሉ ለማድረግ ማስፈራሪያ፣ ተጽዕኖና ኃይል እንደሚጠቀም ያመለክታል። ከሰማይ ወደ ምድር እሳት እንዳወረደ መገለጹ ደግሞ በ20ኛው መቶ ዘመን በተካሄዱት ሁለት የዓለም ጦርነቶች ላይ የክፋት ኃይሎችን ድል እንዳደረገና ኮሚኒዝምን እንዳሸነፈ በመናገር እውነተኛ ነቢይ ለመምሰል መሞከሩን ያሳያል።
16:17—ሰባተኛው ሳህን ውስጥ ያለው ነገር የፈሰሰበት “አየር” ምንድን ነው? እዚህ ላይ የተገለጸው “አየር” የሰይጣንን አስተሳሰብ ማለትም ‘በማይታዘዙት ልጆች ላይ አሁን እየሠራ ያለውን መንፈስ’ ወይም ዝንባሌ ያመለክታል። የሰይጣን ክፉ ሥርዓት ክፍል የሆነ ሰው ሁሉ ይህንን መርዛማ አየር ይተነፍሳል።—ኤፌ. 2:2
ምን ትምህርት እናገኛለን?
13:1-4, 18፦ “ከባሕር” ይኸውም ተነዋዋጭ ከሆነው የሰው ዘር ኅብረተሰብ የወጣው “አውሬ” ሰብዓዊ መንግሥታትን ያመለክታል። (ኢሳ. 17:12, 13፤ ዳን. 7:2-8, 17) ሰይጣን የፈጠረውና ኃይል የሰጠው ይህ አውሬ 666 የሚል ቁጥር ያለው ሲሆን ይህም ምን ያህል ፍጽምና እንደጎደለው የሚያሳይ ነው። የአውሬውን ማንነት መረዳታችን አብዛኛው የሰው ዘር እንደሚያደርገው እሱን በአድናቆት ከመከተል ወይም ከማምለክ እንድንቆጠብ ይረዳናል።—ዮሐ. 12:31፤ 15:19
13:16, 17፦ እንደ “መግዛት ወይም መሸጥ” ያሉ ዕለታዊ እንቅስቃሴዎችን በምናከናውንበት ጊዜ ችግሮች ሊያጋጥሙን ቢችሉም አውሬው በሚያሳድርብን ተጽዕኖ ተሸንፈን ሕይወታችንን እንዲቆጣጠረው መፍቀድ አይኖርብንም። ‘የአውሬው ምልክት በእጃችን ወይም በግምባራችን ላይ እንዲደረግ’ ፈቃደኛ መሆን አውሬው ተግባራችንንም ሆነ አስተሳሰባችንን እንዲቆጣጠረው የመፍቀድ ያህል ነው።
14:6, 7፦ መልአኩ የተናገረው አዋጅ፣ መግዛት ስለጀመረው የአምላክ መንግሥት የሚገልጸውን ምሥራች በጥድፊያ ስሜት መስበክ እንዳለብን ያስተምረናል። መጽሐፍ ቅዱስን የምናስጠናቸው ሰዎች ለአምላክ ጤናማ ፍርሃት እንዲያዳብሩና ለይሖዋ ክብር እንዲሰጡ ልንረዳቸው ይገባል።
14:14-20፦ “የምድር መከር” ማለትም የሚድኑትን ሰዎች የመሰብሰቡ ሥራ ሲጠናቀቅ መልአኩ ‘የምድርን ወይን’ ሰብስቦ “ወደ ታላቁ የአምላክ የቁጣ የወይን መጭመቂያ” ይወረውረዋል። ከዚያም ‘ወይኑ’ ይኸውም በሰይጣን የሚመራው ብልሹ የሆነ ሰብዓዊ የአገዛዝ ሥርዓትም ሆነ ይህ ሥርዓት ያፈራቸው መጥፎ “ዘለላዎች” ድምጥማጣቸው ይጠፋል። እንግዲያው የምድር ወይን ተጽዕኖ እንዳያሳድርብን ቁርጥ ውሳኔ ልናደርግ ይገባል።
16:13-16፦ “በመንፈስ የተነገሩ . . . ርኩሳን ቃላት” የሚያመለክቱት ዲያብሎሳዊ ፕሮፖጋንዳዎችን ሲሆን እንዲህ ያሉት ፕሮፖጋንዳዎች የሚነዙበት ዓላማ የምድር ነገሥታት፣ የአምላክን ቁጣ የያዙት የሰባቱ ሳህኖች መፍሰስ ተጽዕኖ ሳያሳድርባቸው ይሖዋን ለመቃወም እንዲነሳሱ ማድረግ ነው።—ማቴ. 24:42, 44
16:21፦ የዚህ ሥርዓት ፍጻሜ እየተቃረበ ሲሄድ ይሖዋ በሰይጣን ክፉ ሥርዓት ላይ ስለሚወስደው የፍርድ እርምጃ የሚነገረው አዋጅ እንደ ታላቅ የበረዶ ድንጋይ ኃይለኛ የሆኑ መልእክቶችን የያዘ ሊሆን ይችላል። ያም ሆኖ አብዛኞቹ ሰዎች አምላክን መሳደባቸውን ይቀጥላሉ።
ድል አድራጊው ንጉሥ ይገዛል
የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ግዛት የሆነችው “ታላቂቱ ባቢሎን” የሰይጣን ክፉ ዓለም አስጸያፊ ክፍል ናት። በ11ኛው ራእይ ላይ ታላቂቱ ባቢሎን ‘በደማቅ ቀይ አውሬ’ ላይ እንደተቀመጠች ‘ታላቅ ጋለሞታ’ ማለትም ምግባረ ብልሹ እንደሆነች ሴት ተደርጋ ተገልጻለች። የተቀመጠችበት አውሬ “አሥር ቀንዶች” ይህችን ጋለሞታ ድምጥማጧን ያጠፏታል። (ራእይ 17:1, 3, 5, 16) ቀጣዩ ራእይ ይህችን ጋለሞታ ‘ከታላቅ ከተማ’ ጋር አመሳስሏታል፤ ራእዩ ይህቺ ከተማ እንደምትወድቅ ከመግለጹም በላይ የአምላክ ሕዝቦች በአፋጣኝ ‘ከእሷ እንዲወጡ’ ጥሪ ያቀርባል። ብዙዎች በዚህች ከተማ መውደቅ ያዝናሉ። በሰማይ ግን “የበጉ ሠርግ” ስለደረሰ ታላቅ ደስታ ይሆናል። (ራእይ 18:4, 9, 10, 15-19፤ 19:7) ዮሐንስ ‘የነጩ ፈረስ’ ጋላቢ ከብሔራት ጋር እንደሚዋጋ በ13ኛው ራእይ ላይ ተመልክቷል። ይህ ጋላቢ ክፉ የሆነውን የሰይጣን ዓለም ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ያጠፋዋል።—ራእይ 19:11-16
“ዲያብሎስና ሰይጣን የሆነው የመጀመሪያው እባብ” ምን ይደርስበታል? ‘ወደ እሳቱ ሐይቅ የሚወረወረውስ’ መቼ ነው? በ14ኛው ራእይ ላይ ከተገለጹት ጉዳዮች መካከል እነዚህም ይገኙበታል። (ራእይ 20:2, 10) የመጨረሻዎቹ ሁለት ራእዮች በሺው ዓመት ግዛት ውስጥ የሰው ልጆች ሕይወት ምን እንደሚመስል ፍንጭ ይሰጡናል። ‘ራእዩ’ ወደ መደምደሚያው ሲቃረብ ዮሐንስ ‘በአውራ ጎዳና መካከል የሚፈስ የሕይወት ውኃ ወንዝ’ ተመልክቷል፤ ከዚህም ሌላ ‘ለተጠማ ሁሉ’ ግሩም የሆነ ግብዣ ቀርቧል።—ራእይ 1:1፤ 22:1, 2, 17
ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው፦
17:16፤ 18:9, 10—“የምድር ነገሥታት” ታላቂቱ ባቢሎንን ራሳቸው ካጠፏት በኋላ የሚያዝኑት ለምንድን ነው? እነዚህ ነገሥታት የሚያዝኑት ጥቅማቸው ስለተነካባቸው ነው። ታላቂቱ ባቢሎን ከጠፋች በኋላ የምድር ነገሥታት ምን ያህል ትጠቅማቸው እንደነበረ ይገነዘባሉ። ለሚፈጽሙት የጭቆና ድርጊት ሃይማኖታዊ ሽፋን ትሰጣቸው ነበር። ታላቂቱ ባቢሎን ወጣቶችን ለጦርነት በመመልመል ረገድም ታግዛቸው ነበር። ከዚህም በላይ ሕዝቡ እንዲገዛላቸው በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ሚና ትጫወት ነበር።
19:12—በኢየሱስ ላይ የተጻፈውን ስም ከራሱ በቀር ማንም አያውቀውም ሊባል የሚችለው እንዴት ነው? ይህ ስም በኢሳይያስ 9:6 ላይ እንደተገለጹት ያሉ ኢየሱስ በጌታ ቀን የሚያገኛቸውን ልዩ መብቶችና ሥልጣን የሚያመለክት ሳይሆን አይቀርም። ይህን ስም ከእሱ በቀር ማንም አያውቀውም ሊባል የሚችለው የተሰጡት መብቶች ልዩ ስለሆኑና እንዲህ ያለውን ከፍተኛ ሥልጣን መያዝ ምን ትርጉም እንዳለው ሊገባው የሚችለው እሱ ብቻ ስለሆነ ነው። ይሁንና ኢየሱስ ‘አዲሱን ስሙን’ በሙሽራው አባላት ላይ ‘ይጽፍባቸዋል’፤ በሌላ አባባል ከሚያገኛቸው ልዩ መብቶች አንዳንዶቹን ያካፍላቸዋል።—ራእይ 3:12
19:14—በአርማጌዶን ጦርነት ኢየሱስን የሚከተሉት ጋላቢዎች እነማን ናቸው? ከኢየሱስ ጋር ሆኖ በአምላክ ጦርነት በሚካፈለው ‘በሰማይ ባለው ሠራዊት’ ውስጥ መላእክትና ሰማያዊ ሽልማታቸውን ያገኙ ድል የነሱ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ይገኙበታል።—ማቴ. 25:31, 32፤ ራእይ 2:26, 27
20:11-15—‘በሕይወት መጽሐፍ ጥቅልል’ ውስጥ የተጻፈው የእነማን ስም ነው? የዘላለም ሕይወት የሚያገኙ ሰዎች ሁሉ ስማቸው በዚህ ጥቅልል ላይ ተጽፏል፤ እነዚህም ቅቡዓን ክርስቲያኖች፣ የእጅግ ብዙ ሕዝብ አባላት እንዲሁም ‘በጻድቃን ትንሣኤ’ የሚነሱ የአምላክ ታማኝ አገልጋዮች ናቸው። (ሥራ 24:15፤ ራእይ 2:10፤ 7:9) ‘በዓመፀኞች ትንሣኤ’ የሚነሱት ሰዎች ስማቸው ‘በሕይወት መጽሐፍ ጥቅልል’ ላይ የሚጻፈው በሺው ዓመት በሚከፈቱት “[ጥቅልሎች] ውስጥ በተጻፉት” መመሪያዎች መሠረት የሚኖሩ ከሆነ ብቻ ነው። ይሁን እንጂ ስማቸው አንዴ ከተጻፈ ፈጽሞ አይፋቅም ማለት አይደለም። የቅቡዓን ስም በማይደመሰስ ሁኔታ የሚጻፈው እስከ ሞት ድረስ ታማኝ ከሆኑ ነው። (ራእይ 3:5) በምድር ላይ የዘላለም ሕይወት የሚያገኙት ሰዎችም ስማቸው በማይደመሰስ ሁኔታ የሚጻፈው በሺው ዓመት መጨረሻ ላይ የሚያጋጥማቸውን ፈተና ካለፉ ነው።—ራእይ 20:7, 8
ምን ትምህርት እናገኛለን?
17:3, 5, 7, 16፦ “ከላይ የሆነው ጥበብ” “የሴቲቱን እንዲሁም እሷን የተሸከመውን . . . [ደማቅ ቀይ] አውሬ ሚስጥር” እንድንረዳ ያስችለናል። (ያዕ. 3:17) ይህ ምሳሌያዊ አውሬ፣ መጀመሪያ የቃል ኪዳን ማኅበር ይባል የነበረውንና እንደገና ሲቋቋም የተባበሩት መንግሥታት የሚል ስያሜ የተሰጠውን ድርጅት ያመለክታል። የዚህ ሚስጥር መገለጥ የአምላክን መንግሥት የምሥራችና የይሖዋን የፍርድ ቀን በቅንዓት እንድናውጅ ሊያነሳሳን አይገባም?
21:1-6፦ በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ወቅት እንደሚመጡ የተነገሩት በረከቶች እውን እንደሚሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ይሖዋ እነዚህ በረከቶች “ተፈጽመዋል!” በማለት ተናግሯል።
22:1, 17፦ “የሕይወት ውኃ ወንዝ” ይሖዋ ታዛዥ የሆኑ የሰው ልጆችን ከኃጢአትና ከሞት ነፃ ለማውጣት ያደረጋቸውን ዝግጅቶች ያመለክታል። በአሁኑ ጊዜ በተወሰነ መጠን ይህን ውኃ ማግኘት ይቻላል። እኛም “የተጠማም ሁሉ ይምጣ . . . የሕይወትን ውኃ በነፃ ይውሰድ” የሚለውን ግብዣ በአድናቆት በመቀበል ሳንወሰን ሌሎችም እንዲህ እንዲያደርጉ ለመጋበዝ ጥረት እናድርግ!
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በጥር 15, 2009 መጠበቂያ ግንብ ላይ በወጣው “የራእይ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች—ክፍል 1” በሚለው ርዕስ ሥር ከራእይ 1:1 እስከ 12:17 ባሉት ምዕራፎች ላይ የተሰጠውን ማብራሪያ ማግኘት ይቻላል።
b ራእይ ታላቁ መደምደሚያው ደርሷል! በተባለው መጽሐፍ ላይ በራእይ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኘው እያንዳንዱ ምዕራፍና ቁጥር ተብራርቷል።
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ታዛዥ የሆኑ የሰው ልጆች በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር እጅግ አስደናቂ በረከቶች ያገኛሉ!