ምዕራፍ 38
ያህን ስለ ፍርዶቹ አወድሱት!
1. ዮሐንስ ‘በሰማይ እንደ ብዙ ሕዝብ ድምፅ ሲናገር የሰማው’ ምንድን ነው?
ከዚያ በኋላ ታላቂቱ ባቢሎን አትኖርም! እንዲህ ያለው ዜና በጣም ያስደስታል። ዮሐንስም በሰማይ የደስታ ውዳሴ ድምፅ መስማቱ አያስደንቅም። “ከዚህ በኋላ በሰማይ:- ሃሌ ሉያ፣ በዝሙትዋ ምድርን ያጠፋችይቱን ታላቂቱን ጋለሞታ ስለ ፈረደባት፣ የባሪያዎቹንም ደም ከእጅዋ ስለ ተበቀለ፣ ፍርዶቹ እውነትና ጽድቅ ናቸውና ማዳንና ክብር ኃይልም የአምላካችን ነው ብሎ ሲናገር እንደ ብዙ ሕዝብ ታላቅ ድምፅ ያለ ድምፅን ሰማሁ። ደግመውም ሃሌ ሉያ አሉ፤ ጢስዋም ከዘላለም እስከ ዘላለም ይወጣል።”—ራእይ 19:1-3
2. (ሀ) “ሃሌ ሉያ” ማለት ምን ማለት ነው? በዚህ ጊዜ ላይ ዮሐንስ ሁለት ጊዜ ሃሌ ሉያ ሲባል መስማቱ ምን ያመለክታል? (ለ) ታላቂቱ ባቢሎን በመጥፋትዋ ክብር የሚሰጠው ማን ነው? አብራራ።
2 በእውነትም ሃሌ ሉያ! ሃሌ ሉያ ማለት “ያህን አወድሱ” ማለት ነው። “ያህ” ይሖዋ የተባለው መለኮታዊ ስም ምህጻረ ቃል ነው። እዚህ ላይ “እስትንፋስ ያለው ሁሉ እግዚአብሔርን [“ይሖዋን፣” NW] ያመስግን፣ ሃሌ ሉያ” የሚለውን የመዝሙራዊውን ማሳሰቢያ ለማስታወስ እንገደዳለን። (መዝሙር 150:6) ዮሐንስ በዚህ ጊዜ በሰማይ የነበረው የመዘምራን ጓድ “ሃሌ ሉያ” እያለ ሁለት ጊዜ የውዳሴ ዝማሬ ሲያሰማ መስማቱ የመለኮታዊው እውነት መገለጥ ተከታታይነት እንዳለው ያሳያል። የግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች አምላክ ቀደም ካሉት የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች አምላክ የተለየ አይደለም። ስሙም ይሖዋ ነው። የጥንትዋን ባቢሎን እንድትወድቅ ያደረገው አምላክ አሁን ደግሞ በታላቂቱ ባቢሎን ላይ ፈርዶ አጥፍቶአታል። ይህን በማድረጉ ክብር ሁሉ ሊሰጠው ይገባል። ታላቂቱ ባቢሎን የምትወድምበትን ሁኔታ ያመቻቸው ኃይል ከይሖዋ የመጣ ነው እንጂ እርሱ መሣሪያ አድርጎ ከተጠቀመባቸው ብሔራት ብቻ የመጣ አይደለም። ማዳን የሚቻለው ይሖዋ ብቻ ነው።—ኢሳይያስ 12:2፤ ራእይ 4:11፤ 7:10, 12
3. ታላቂቱ ጋለሞታ ሊፈረድባት የሚገባው ለምንድን ነው?
3 ታላቂቱ ባቢሎን ይህን የመሰለ ፍርድ ልትቀበል የሚገባት ለምንድን ነው? ይሖዋ ለኖህና በኖህም በኩል ለሰው ልጅ በሙሉ በሰጠው ሕግ መሠረት ደም አለአግባብ ማፍሰስ በሞት የሚያስቀጣ ወንጀል ነው። ይህ ሕግ ይሖዋ ለእሥራኤላውያን በሰጠው ሕግም በድጋሚ ተጠቅሶአል። (ዘፍጥረት 9:6፤ ዘኍልቁ 35:20, 21) ከዚህም በላይ በሙሴ ሕግ መሠረት ሥጋዊም ሆነ መንፈሳዊ ምንዝር በሞት የሚያስቀጣ በደል ነበር። (ዘሌዋውያን 20:10፤ ዘዳግም 13:1-5) ታላቂቱ ባቢሎን በሺህ ለሚቆጠሩ ዓመታት ደም ስታፈስስ ኖራለች። በተጨማሪም የአመንዝሮች ሁሉ እናት ነች። ለምሳሌ ያህል የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ቀሳውስትዋ እንዳያገቡ መከልከልዋ ብዙዎቹ ቀሳውስት ከባድ የሥነ ምግባር ብልግና እንዲፈጽሙ ምክንያት ሆኖአቸዋል። ከእነዚህም መካከል የኤድስ በሽታ የያዛቸው ጥቂቶች አይደሉም። (1 ቆሮንቶስ 6:9, 10፤ 1 ጢሞቴዎስ 4:1-3) ይሁን እንጂ ‘እስከ ሰማይ እስኪደርስ ድረስ የተከመረባት ኃጢአት’ በመንፈሳዊ አመንዝራነት የፈጸመችው ነው። የሐሰት ትምህርት ስታስተምር ኖራለች፣ ከምግባረ ብልሹ ፖለቲከኞችም ጋር ራስዋን አስተባብራለች። (ራእይ 18:5) ለሠራችው ወንጀል ሁሉ የሚገባትን መቀጫ የምትቀበልበት ጊዜ ስለ ደረሰ በሰማይ የነበሩት እጅግ ብዙ መዘምራን ለሁለተኛ ጊዜ ሃሌ ሉያ በማለት አስተጋቡ።
4. ከታላቂቱ ባቢሎን የሚወጣው ጢስ “ከዘላለም እስከ ዘላለም” መጤሱ ምን ያመለክታል?
4 ታላቂቱ ባቢሎን በጠላት ኃይል እንደተወረረች ከተማ በእሳት ተያይዛለች። ከእርስዋም የሚወጣው ጢስ “ከዘላለም እስከ ዘላለም ይወጣል።” አንድ ከተማ በወራሪ ጠላት እጅ ወድቆ ሲቃጠል የቃጠሎው አመድ ትኩስ እስከሆነ ድረስ ጢስ መውጣቱ አይቀርም። ጢሱ ሳይቆም ከተማውን መልሶ ለመገንባት የሚሞክር ሰው በተዳፈነው ፍም ይቃጠላል። ከታላቂቱ ባቢሎን የሚወጣው ጢስም የተፈጸመባት ፍርድ የመጨረሻና የማያዳግም መሆኑን ለማመልከት “ከዘላለም እስከ ዘላለም” ስለሚወጣ ይህችን ነውረኛ ከተማ መልሶ ሊገነባ የሚችል ማንም አይኖርም። የሐሰት ሃይማኖት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ጠፍቶአል። በእርግጥም፣ ሃሌ ሉያ!—ከኢሳይያስ 34:5, 9, 10 ጋር አወዳድር።
5. (ሀ) 24ቱ ሽማግሌዎች እና አራቱ እንስሳት ምን አደረጉ? ምንስ ተናገሩ? (ለ) የሃሌ ሉያው ዝማሬ በሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት ከሚሰማው ዝማሬ ሁሉ የበለጠ ጣዕም ያለው የሆነው ለምንድን ነው?
5 ዮሐንስ ቀደም ሲል በተመለከተው ራእይ ላይ በዙፋኑ ዙሪያ ታላቅ ክብር የተሰጣቸውን የመንግሥት ወራሾች ከሚያመለክቱት ሃያ አራት ሽማግሌዎች በተጨማሪ አራት ሕያዋን ፍጥረታት ቆመው ተመልክቶ ነበር። (ራእይ 4:8-11) አሁን ደግሞ ታላቂቱ ባቢሎን በመጥፋትዋ ምክንያት ለሦስተኛ ጊዜ ሃሌ ሉያ የሚል የውዳሴ ዝማሬ ሲያስተጋቡ ይመለከታል። “ሃያ አራቱም ሽማግሌዎችና አራቱ እንስሶች በፊታቸው ተደፍተው በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው ለእግዚአብሔር:- አሜን፣ ሃሌ ሉያ እያሉ ሰገዱለት።” (ራእይ 19:4) ስለዚህ ይኸኛው የሃሌ ሉያ ዝማሬ ለበጉ ከቀረበው የውዳሴ ዝማሬ በተጨማሪ የቀረበ “አዲስ ቅኔ” ነው ማለት ነው። (ራእይ 5:8, 9) በአመንዝራይቱ ታላቂቱ ባቢሎን ላይ ወሳኝ ድል ስለተቀዳጀ ክብር ሁሉ ለጽንፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዥ ለይሖዋ እንደሚገባ በመግለጽ ይህን አስደናቂ የድል መዝሙር ዘምረዋል። እነዚህ የሃሌ ሉያ ዝማሬዎች ይሖዋ ወይም ያህ በተናቀባቸው ወይም በተዋረደባቸው የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት ከተዘመሩት የሃሌ ሉያ ዝማሬዎች በሙሉ የበለጠ ለዛና ጣዕም አላቸው። ይህ ይሖዋን የሚያስነቅፈው የአብያተ ክርስቲያናት የግብዝነት ዝማሬ ለዘላለሙ እንዳይሰማ ይደረጋል!
6. የማን “ድምፅ” ተሰማ? ምንስ ምክር ሰጠ? ይህንንስ ምክር በመፈጸም የተካፈሉት እነማን ናቸው?
6 ይሖዋ ‘ስሙን ለሚፈሩ ታላላቆችና ታናናሾች ዋጋቸውን መክፈል’ የጀመረው በ1918 ነበር። ከእነዚህም የመጀመሪያዎቹ የሆኑት ከሙታን አስነስቶ 24ቱ ሽማግሌዎች በተሰጣቸው ሰማያዊ ማዕረግ ያስቀመጣቸው በታማኝነት ሞተው የነበሩት ቅቡዓን ክርስቲያኖች ናቸው። (ራእይ 11:18) ሌሎችም ሃሌ ሉያ እያሉ በመዘመር ከእነዚህ ጋር ይተባበራሉ። ዮሐንስ እንዲህ ሲል ይነግረናል:- “ድምፅም:- ባሪያዎቹ ሁሉ እርሱንም የምትፈሩት ታናናሾችና ታላላቆች ሆይ፣ አምላካችንን አመስግኑ ሲል ከዙፋኑ ወጣ።” (ራእይ 19:5) ይህ የይሖዋ አፈ ንጉሥ የሆነው የልጁ የኢየሱስ ክርስቶስ ድምፅ ነው። እርሱም ‘በዙፋኑ መካከል የሚቆም ነው።’ (ራእይ 5:6) “ባሮቹ ሁሉ” የውዳሴ መዝሙር የሚዘምሩት በሰማይ ብቻ ሳይሆን በምድርም ጭምር ነው። በዚህም በግንባር ቀደምትነት የሚመሩት ቅቡዓን የዮሐንስ ክፍል አባሎች ናቸው። እነዚህም “አምላካችንን አመስግኑ” የሚለውን ትዕዛዝ በታላቅ ደስታ ይፈጽማሉ።
7. ታላቂቱ ባቢሎን ከጠፋች በኋላ ይሖዋን የሚያወድሱት እነማን ናቸው?
7 አዎ፣ እጅግ ብዙ ሰዎችም ከእነዚህ ባሮች የሚቆጠሩ ናቸው። እጅግ ብዙ ሰዎች ከ1935 ጀምሮ ከታላቂቱ ባቢሎን ሲወጡ ቆይተዋል። “እግዚአብሔርን [“ይሖዋን፣” NW] የሚፈሩትን፣ ትንንሾችና ትልልቆችን ይባርካል” የሚለው ቃል ተፈጽሞላቸዋል። (መዝሙር 115:13) በአመንዝራ ሴት የተመሰለችው ታላቂቱ ባቢሎን በምትጠፋበት ጊዜ እነዚህ በሚልዮን የሚቆጠሩ እጅግ ብዙ ሰዎች ከዮሐንስ ክፍል አባሎችና ከሰማይ ሠራዊቶች ጋር በመተባበር ‘አምላካችንን ያወድሳሉ።’ ከሙታን ተነስተው በምድር ላይ የሚኖሩትም ቢሆኑ ከፍተኛ ማዕረግ የነበራቸውም ይሁኑ ያልነበራቸው ታላቂቱ ባቢሎን ለዘላለም እንደጠፋች ሲያውቁ ተጨማሪ የሃሌ ሉያ ዝማሬ ያሰማሉ። (ራእይ 20:12, 15) ይሖዋ ለብዙ ዘመናት በቆየችው አመንዝራ ላይ አንጸባራቂ ድል ስለተጎናጸፈ ምሥጋና ሁሉ ሊሰጠው ይገባል።
8. ዮሐንስ በሰማይ የተመለከተው የመዘምራን ጓድ ታላቂቱ ባቢሎን ከመጥፋትዋ በፊት አሁን ምን እንድናደርግ ሊያነሳሳን ይገባል?
8 ይህ ሁሉ በአሁኑ ጊዜ በአምላክ ሥራ ሙሉ በሙሉ እንድንካፈል የሚቀሰቅሰን እንዴት ያለ ትልቅ ምክንያት ነው! የይሖዋ አገልጋዮች ሁሉ አሁንኑ፣ ታላቂቱ ባቢሎን ከዙፋንዋ ተጥላ ከመጥፋትዋ በፊት ልባቸውንና ነፍሳቸውን ሙሉ በሙሉ የአምላክን ፍርድና ታላቁን የመንግሥት ተስፋ በማወጅ ሥራ ላይ ያውሉ።—ኢሳይያስ 61:1-3፤ 1 ቆሮንቶስ 15:58
‘ሃሌ ሉያ—ይሖዋ ነገሠ!’
9. የመጨረሻው ሃሌ ሉያ በጣም የዳበረና ሙላት ያለው ድምፅ የሆነው ለምንድን ነው?
9 ዮሐንስ ቀጥሎ እንደሚነግረን ሌላም የምንደሰትበት ምክንያት አለን። “እንደ ብዙ ሕዝብም ድምፅ፣ እንደ ብዙ ውኃዎችም ድምፅ፣ እንደ ብርቱም ነጎድጓድ ድምፅ ያለ ድምፅ ሰማሁ እንዲህ ሲል:- ሃሌ ሉያ ሁሉን የሚገዛ ጌታ [“ይሖዋ፣” NW] አምላካችን ነግሦአልና።” (ራእይ 19:6) ይህ በመጨረሻ የተነገረ ሃሌ ሉያ አዋጁን ከአራት አቅጣጫ እንዲሰማና የተመዛዘነ እንዲሆን ያደርገዋል። ይህ ድምፅ ማንኛውም የሰዎች መዘምራን ቡድን ከሚዘምሩት የበለጠ ጉልህ ሆኖ የሚሰማ፣ በምድር ላይ ከሚገኝ ከየትኛውም ወራጅ ወንዝ የበለጠ የሚያስገመግም ድምፅ ያለውና ከማንኛውም የመብረቅ ድምፅ ይበልጥ አስደንጋጭ የሆነ ነው። እልፍ አእላፍ የሆኑት ሰማያዊ ድምፆች “ሁሉን የሚችለው ይሖዋ አምላካችን ንጉሥ ሆኖ መግዛት ጀምሮአል” የሚለውን እውነታ የሚያከብሩ ናቸው።
10. ታላቂቱ ባቢሎን ከጠፋች በኋላ ይሖዋ መንገሥ ጀመረ ሊባል የሚቻለው በምን መንገድ ነው?
10 ይሁን እንጂ ይሖዋ መንገሥ የጀመረው እንዴት ነው? መዝሙራዊው “እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] ግን ከዓለም አስቀድሞ ንጉሥ ነው” ካለ በሺህ የሚቆጠሩ ዓመታት አልፈዋል። (መዝሙር 74:12) በዚያም ጊዜ ቢሆን የይሖዋ ንግሥና ለብዙ ዓመታት የቆየ ነበር። ታዲያ የጽንፈ ዓለሙ ዝማሬ “ይሖዋ ንጉሥ ሆኖ መግዛት ጀምሮአልና” [NW] ያለው ለምንድን ነው? ታላቂቱ ባቢሎን ከጠፋች በኋላ ሰዎች ለይሖዋ ጽንፈ ዓለማዊ ሉዓላዊነት እንዳይገዙ የሚያደርግ ተጻራሪ የሐሰት ሃይማኖት ስለማይኖር ነው። ከዚያ በኋላ የምድር ገዥዎች ይሖዋን ተቃውመው እንዲነሱ የሚቀሰቅስ የሐሰት ሃይማኖት አይኖርም። የጥንትዋ ባቢሎን ከዓለም ኃያልነት ተገልብጣ በወደቀች ጊዜ ጽዮን “እነሆ፣ አምላክሽ ነገሠ” የሚለውን የድል አዋጅ ሰምታ ነበር። (ኢሳይያስ 52:7) በ1914 መንግሥቱ ከተወለደች በኋላ 24ቱ ሽማግሌዎች “ጌታ እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] ሆይ፣ ትልቁን ኃይልህን ስለ ያዝህ ስለ ነገሥህም እናመሰግንሃለን” ብለው ነበር። (ራእይ 11:17) አሁን ደግሞ ታላቂቱ ባቢሎን ከወደመች በኋላ “ይሖዋ ንጉሥ ሆኖ መግዛት ጀመረ” የሚል ጩኸት ተሰምቶአል። የእውነተኛውን አምላክ የይሖዋን ሉዓላዊነት የሚጻረር ሰው ሠራሽ አምላክ ከዚያ በኋላ አይኖርም።
የበጉ ሰርግ ቀርቦአል!
11, 12. (ሀ) የጥንትዋ ኢየሩሳሌም የጥንትዋን ባቢሎን ምን ብላ ጠርታት ነበር? ይህስ በአዲሲቱ ኢየሩሳሌምና በታላቂቱ ባቢሎን መካከል ምን ዓይነት ሁኔታ እንደሚኖር ያመለክታል? (ለ) ታላቂቱ ባቢሎን ድል ከተነሳች በኋላ ሰማያውያን ሠራዊቶች ምን መዝሙር ይዘምራሉ? ምን ማስታወቂያስ ይናገራሉ?
11 የይሖዋ የአምልኮ ቤተ መቅደስ የነበረባት ኢየሩሳሌም ጣዖት አምላኪ የነበረችውን ባቢሎንን “ጠላቴ ሆይ”! ብላ ጠርታት ነበር። (ሚክያስ 7:8) በተመሳሳይም 144,000 አባላት ያሉአት ሙሽራይቱ “ቅድስቲቱ ከተማ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም” ታላቂቱ ባቢሎንን ጠላቴ ብላ የምትጠራበት በቂ ምክንያት ነበራት። (ራእይ 21:2) ይሁን እንጂ አሁን በመጨረሻ በታላቂቱ አመንዝራ ላይ መከራ፣ ውርደትና ጥፋት ደርሶአል። አስማትዋም ሆነ ኮከብ ቆጣሪዎችዋ ሊያድኑአት አልቻሉም። (ከኢሳይያስ 47:1, 11-13 ጋር አወዳድር።) በእርግጥም ይህ ለእውነተኛ አምልኮ ትልቅ ድል ነው።
12 አስጸያፊዋ አመንዝራ፣ ታላቂቱ ባቢሎን ለዝንተ ዓለም ከጠፋች በኋላ ንጽሕት ድንግል በሆነችው በበጉ ሙሽራ ላይ ማተኮር ይቻላል። በዚህም ምክንያት በሰማይ የነበሩት ሠራዊቶች ይሖዋን በማወደስ የሚከተለውን የደስታ መዝሙር አሰምተዋል። “የበጉ ሰርግ ስለ ደረሰ ሚስቱም ራስዋን ስላዘጋጀች ደስ ይበለን ሐሴትም እናድርግ ክብርንም ለእርሱ እናቅርብ። ያጌጠና የተጣራ ቀጭን የተልባ እግር ልብስ እንድትጎናጸፍ ተሰጥቶአታል። ቀጭኑ የተልባ እግር የቅዱሳን ጽድቅ ሥራ ነውና።”—ራእይ 19:7, 8
13. ባለፉት መቶ ዘመናት ለበጉ ሰርግ ምን ዓይነት ዝግጅት ሲደረግ ቆይቶአል?
13 ኢየሱስ ባለፉት መቶ ዘመናት ሁሉ ለዚህ በሰማይ ለሚፈጸመው ሰርግ ፍቅራዊ ዝግጅት ሲያደርግ ቆይቶአል። (ማቴዎስ 28:20፤ 2 ቆሮንቶስ 11:2) 144,000 አባላት ያሉትን መንፈሣዊ እሥራኤል ሲያነፃ ቆይቶአል። ይህንንም ያደረገው ጉባኤው “እድፈት ወይም የፊት መጨማደድ ወይም እንዲህ ያለ ነገር ሳይሆንባት ቅድስትና ያለ ነውር ትሆን ዘንድ” ነው። (ኤፌሶን 5:25-27) እያንዳንዱ የተቀባ ክርስቲያን “የላይኛውን የአምላክ ጥሪ” ለማግኘት አሮጌውን ሰው ከሥራዎቹ ጋር ገፍፎ መጣልና አዲሱን ክርስቲያናዊ ሰው ለብሶ ‘ለይሖዋ እንደሚገባ በሙሉ ልቡ’ የጽድቅ ሥራዎችን መሥራት ነበረበት።—ፊልጵስዩስ 3:8, 13, 14፤ ቈላስይስ 3:9, 10, 23
14. ሰይጣን የበጉ ሚስት አባሎች የሚሆኑትን ሰዎች ለመበከል ምን ዓይነት ጥረት ሲያደርግ ቆይቶአል?
14 ሰይጣን በ33 እዘአ ከዋለው የጰንጠቆስጤ ቀን ጀምሮ ታላቂቱ ባቢሎንን መሣሪያ አድርጎ በመጠቀም የበጉን ሚስት እጩ አባላት ለመበከልና ለማሳደፍ ሲሞክር ቆይቶአል። በአንደኛው መቶ ዘመን መጨረሻ ላይ እንኳን የባቢሎናዊ ሃይማኖትን ዘር በጉባኤው ውስጥ ዘርቶ ነበር። (1 ቆሮንቶስ 15:12፤ 2 ጢሞቴዎስ 2:18፤ ራእይ 2:6, 14, 20) ሐዋርያው ጳውሎስ እምነትን ያጣምሙ ስለነበሩ ሰዎች ሲናገር እንዲህ ብሎ ነበር:- “እንደነዚህ ያሉ ሰዎች የክርስቶስን ሐዋርያት እንዲመስሉ ራሳቸውን እየለወጡ ውሸተኞች ሐዋርያትና ተንኮለኞች ሠራተኞች ናቸውና። ይህም ድንቅ አይደለም ሰይጣን ራሱ የብርሃንን መልአክ እንዲመስል ራሱን ይለውጣልና።” (2 ቆሮንቶስ 11:13, 14) ከዚያ በኋላ በነበሩት ዘመናት ሁሉ ከዳተኛዋ ሕዝበ ክርስትና እንደሌሎቹ የታላቂቱ ባቢሎን ክፍሎች የባለጠግነትና የከበሬታ ልብስ በሆነው “በቀይና በሐምራዊ ልብስ . . . በወርቅና በከበሩ ድንጋዮች በዕንቆችም ተሸልማ ነበር።” (ራእይ 17:4) ቀሳውስትዋና ጳጳሳትዋ እንደ ቆስጠንጢኖስና እንደ ሻርለማኝ ካሉት ደም የተጠሙ ነገሥታት ጋር ተሻርከዋል። “የቅዱሳንን የጽድቅ ሥራ” ተጎናጽፋ አታውቅም። በእርግጥም ሰይጣን ሰዎችን ለማሳት ሲል ያቋቋማት የወጣላት አስመሳይ ሙሽራ ናት። አሁን ግን ለዝንተ ዓለም ጠፍታለች!
የበጉ ሚስት ራስዋን አዘጋጅታለች
15. የማተሙ ሥራ የሚፈጸመው እንዴት ነው? ከአንድ ቅቡዕ ክርስቲያን የሚፈለገው ነገር ምንድን ነው?
15 ስለዚህ አሁን 2,000 ከሚያህሉ ዓመታት በኋላ የሙሽራይቱ ክፍል የሆኑት 144,000ዎች በሙሉ ራሳቸውን አዘጋጅተዋል። ይሁን እንጂ ‘የበጉ ሚስት ራስዋን አዘጋጅታለች’ ሊባል የሚቻለው መቼ ነው? በ33 እዘአ ከዋለው የጰንጠቆስጤ ቀን ጀምሮ ያመኑ ቅቡዓን ሁሉ ‘በቤዛው ነጻነት እስከሚያገኙ ቀን’ ድረስ ቃል በተገባላቸው መንፈስ ቅዱስ በተከታታይ ሲቀቡ ቆይተዋል። ሐዋርያው ጳውሎስ እንደተናገረው “ያተመን የመንፈሱንም መያዣ በልባችን የሰጠን” አምላክ ነው። (ኤፌሶን 1:13፤ 4:30፤ 2 ቆሮንቶስ 1:22) እያንዳንዱ የተቀባ ክርስቲያን “የተጠራና የተመረጠ” ነው። ታማኝ መሆኑንም ያስመሰከረ ነው።—ራእይ 17:14
16. (ሀ) የሐዋርያው ጳውሎስ መታተም የተፈጸመው መቼ ነበር? ይህንንስ እንዴት እናውቃለን? (ለ) የበጉ ሚስት ራስዋን ሙሉ በሙሉ የምታዘጋጀው መቼ ነው?
16 ጳውሎስ ራሱ ለብዙ ዓመታት ከተፈተነ በኋላ እንደሚከተለው ለማለት ችሎ ነበር። “መልካሙን ገድል ተጋድዬአለሁ፣ ሩጫውን ጨርሼአለሁ። ሃይማኖትን ጠብቄአለሁ። ወደፊት የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል። ይህንም ጻድቅ ፈራጅ የሆነው ጌታ ያን ቀን ለእኔ ያስረክባል። ደግሞም መገለጡን ለሚወዱት ሁሉ እንጂ ለእኔ ብቻ አይደለም።” (2 ጢሞቴዎስ 4:7, 8) ሐዋርያው ገና በሥጋ ያለና ወደፊት የሰማዕትነት ሞት የሚጠብቀው ቢሆንም የእርሱ መታተም ሙሉ በሙሉ ተፈጽሞ የነበረ ይመስላል። በተመሳሳይም ከ144,000ዎቹ መካከል በምድር የቀሩት በሙሉ በየግላቸው የይሖዋ ንብረት መሆናቸው ታትሞ የሚያልቅበት ጊዜ ይመጣል። (2 ጢሞቴዎስ 2:19) ይህም የሚሆነው የበጉ ሚስት ራስዋን ሙሉ በሙሉ በምታዘጋጅበት ጊዜ ማለትም አብዛኞቹ የ144,000 ክፍሎች ሰማያዊ ሽልማታቸውን አግኝተው በአሁኑ ጊዜ በምድር የቀሩት አባላት ደግሞ ታማኝ መሆናቸው ተረጋግጦ ሲታተምባቸው ነው።
17. የበጉ ጋብቻ ሊፈጸም የሚችለው መቼ ነው?
17 144,000ዎቹ ታትመው የሚያልቁበት ይህ የይሖዋ የጊዜ ፕሮግራም ሲደርስ መላእክቱ አራቱን የታላቁ መከራ ነፋሳት ይለቃሉ። (ራእይ 7:1-3) በመጀመሪያ በጋለሞታይቱ ታላቂቱ ባቢሎን ላይ የአምላክ ፍርድ ይፈጸማል። ከዚያ ቀጥሎ ድል አድራጊው ክርስቶስ በፍጥነት ወደ አርማጌዶን ይገሰግስና ቀሪውን ምድራዊ የሰይጣን ድርጅት ያጠፋል። በመጨረሻም ሰይጣንንና አጋንንቱን በጥልቁ ውስጥ ያስራል። (ራእይ 19:11 እስከ 20:3) በዚህ ወቅት በምድር ላይ በሕይወት የሚቆዩ ቅቡዓን ካሉ ክርስቶስ ጠላቶቹን ድል እንደነሳ ወደ ሰማያዊ ውርሻቸው እንደሚገቡና ከቀሩት የሙሽራይቱ ክፍል አባሎች ጋር እንደሚተባበሩ አያጠራጥርም። ከዚያ በኋላ አምላክ በወሰነው ጊዜ የበጉ ሰርግ ሊፈጸም ይችላል!
18. በበጉ ሰርግ ረገድ የሚፈጸሙትን ነገሮች ቅደም ተከተል መዝሙር 45 የሚያረጋግጥልን እንዴት ነው?
18 በመዝሙር 45 ላይ የሰፈረው ትንቢታዊ ዘገባ ክንውኖቹ የሚፈጸሙበትን ቅደም ተከተል ያሳያል። በመጀመሪያ ንጉሡ ጠላቶቹን ድል ለመንሳት ይገሰግሳል። (ቁጥር 1-7) ከዚያ በኋላ በዚህ ምድር ላይ ሚዜዎችዋ በሆኑት እጅግ ብዙ ሰዎች ታጅባ የቆየችው የሰማያዊቱ ሙሽራ የጋብቻ ሥርዓት በሰማይ ላይ ይፈጸማል። (ቁጥር 8-15) ከዚያ ቀጥሎ ከሙታን የተነሱት የሰው ልጆች ‘በምድር መሳፍንት’ አመራር ሥር ሆነው ወደ ፍጽምና ደረጃ ስለሚደርሱ ጋብቻው ፍሬ ያስገኛል። (ቁጥር 16, 17) በበጉ ሰርግ ምክንያት በጣም ብዙ በረከት ይገኛል።
የተጠሩት ደስተኞች ናቸው
19. በራእይ መጽሐፍ ውስጥ ከተጠቀሱት ሰባት ደስታዎች መካከል አራተኛው ምንድን ነው? በዚህስ ልዩ ደስታ የሚካፈሉት እነማን ናቸው?
19 ዮሐንስ በራእይ መጽሐፍ ውስጥ ከተመዘገቡት ሰባት ደስታዎች መካከል አሁን አራተኛውን እንደሚከተለው ይጠቅሳል:- “እርሱም (እነዚህን ነገሮች ለዮሐንስ ሲገልጽለት የቆየው መልአክ) ወደ በጉ ሰርግ እራት የተጠሩ ብፁዓን [“ደስተኞች፣” NW] ናቸው ብለህ ጻፍ አለኝ። ደግሞም:- ይህ የእግዚአብሔር እውነተኛ ቃል ነው አለኝ።” (ራእይ 19:9)a “ወደ በጉ ሰርግ እራት” የተጠሩት የሙሽራይቱ ክፍል አባሎች ናቸው። (ከማቴዎስ 22:1-14 ጋር አወዳድር።) መላው የቅቡዓን ሙሽራ ክፍል ይህን ግብዣ የመቀበል ደስታ አግኝቶአል። አብዛኞቹ ተጋባዦች ቀደም ሲሉ የሰርጉ እራት ወደሚደረግበት ወደ ሰማይ ሄደዋል። ገና በምድር ላይ የቀሩትም ቢሆኑ ግብዣ ስለተደረገላቸው ደስተኞች ናቸው። በሰርጉ እራት ላይ የተያዘላቸው ቦታ በማንም አይወሰድባቸውም። (ዮሐንስ 14:1-3፤ 1 ጴጥሮስ 1:3-9) ትንሣኤ አግኝተው ወደ ሰማይ ሲሄዱ መላው የሙሽራ ክፍል በአንድነት በዚህ በጣም አስደሳች በሆነው ጋብቻ ከበጉ ጋር ይካፈላል።
20. (ሀ) “እነዚህ እውነተኛ የአምላክ ቃላት ናቸው” የሚለው አነጋገር ትርጉም ምንድን ነው? (ለ) ዮሐንስ በመልአኩ አነጋገር የተነካው እንዴት ነው? መልአኩስ ምን ብሎ መለሰለት?
20 በተጨማሪም መልአኩ “ይህ የእግዚአብሔር እውነተኛ ቃል ነው” ብሎአል። “እውነተኛ” የሚለው ቃል ከግሪክኛው አሌቲኖስ የተተረጎመ ሲሆን “አስተማማኝ” “ሐቀኛ” የሚል ትርጉም አለው። እነዚህ ቃላት ከይሖዋ የመጡ ስለሆኑ አስተማማኝና ትምክህት የሚጣልባቸው ናቸው። (ከ1 ዮሐንስ 4:1-3፤ ከራእይ 21:5ና ከራእይ 22:6 ጋር አወዳድር።) ዮሐንስ ወደዚህ የሰርግ ድግስ የተጋበዘ ሰው እንደመሆኑ መጠን ይህን ቃል ሲሰማና ለሙሽራይቱ ክፍል የተዘጋጁትን ታላላቅ በረከቶች ሲያሰላስል በጣም ሳይደሰት አልቀረም። እንዲያውም ስሜቱ በጣም ስለተቀሰቀሰ ዮሐንስ ቀጥሎ እንደሚነግረን መልአኩ ምክር ሊሰጠው ተገዶአል። “ልሰግድለትም በእግሩ ሥር ተደፋሁ። እርሱም:- እንዳታደርገው ተጠንቀቅ፤ ከአንተ ጋር የኢየሱስም ምስክር ካላቸው ከወንድሞችህ ጋር አብሬ ባሪያ ነኝ፤ ለእግዚአብሔር ስገድ።”—ራእይ 19:10ሀ
21. (ሀ) የራእይ መጽሐፍ ስለ መላእክት ሁኔታ ምን ይገልጽልናል? (ለ) ክርስቲያኖች ለመላእክት ምን ዓይነት ዝንባሌ ሊኖራቸው ይገባል?
21 በራእይ መጽሐፍ ውስጥ ስለ መላእክት ትጋትና ታማኝነት ብዙ ተመስክሮአል። የእውነት እውቀት አስተላላፊዎች ሆነው አገልግለዋል። (ራእይ 1:1) በምሥራቹ ስብከትና ምሳሌያዊዎቹን መቅሰፍቶች በማፍሰስ ሥራም ከሰዎች ልጆች ጎን ተሰልፈው ሠርተዋል። (ራእይ 14:6, 7፤ 16:1) ሰይጣንንና መላእክቱንም ከሰማይ ለመጣል ከኢየሱስ ጎን ተሰልፈው ተዋግተዋል። ወደፊትም በአርማጌዶን ከእርሱ ጎን ቆመው ይዋጋሉ። (ራእይ 12:7፤ 19:11-14) ወደ ይሖዋ ዙፋን የመቅረብ ነፃነት አላቸው። (ማቴዎስ 18:10፤ ራእይ 15:6) ይሁን እንጂ ትሁታን የአምላክ ባሪያዎች ከመሆን ሊያልፉ አይችሉም። መላእክትን ማምለክ ወይም በአንድ “ቅዱስ” ወይም መልአክ አማካኝነት አምላክን ማምለክ በንጹሕ አምልኮ ውስጥ ምንም ቦታ የለውም። (ቈላስይስ 2:18) ክርስቲያኖች የሚያመልኩት ይሖዋን ብቻ ነው። ልመናቸውንም በኢየሱስ ስም የሚያቀርቡት ለይሖዋ ነው።—ዮሐንስ 14:12, 13
በትንቢት ረገድ ኢየሱስ ያለው ሚና
22. መልአኩ ለዮሐንስ ምን ነገረው? የዚህስ አባባል ትርጉም ምንድን ነው?
22 ከዚህ በኋላ መልአኩ “ትንቢት የሚነገረው ስለ ኢየሱስ ለመመስከር ነው” አለ። (ራእይ 19:10ለ NW) እንዴት እንዲህ ሊሆን ቻለ? በመንፈስ አነሳሽነት የተገለጸ ትንቢት ሁሉ እንዲነገር ምክንያት የሆነው ኢየሱስና እርሱ በይሖዋ ዓላማ ውስጥ የሚጫወተው ሚና ነው። የመጀመሪያው የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት አንድ ዘር እንደሚመጣ ተስፋ ይሰጣል። (ዘፍጥረት 3:15) ይህም ዘር ኢየሱስ ሆኖ ተገኘ። ከዚያ በኋላ የተሰጡት መግለጫዎች ሁሉ የዚህን መሠረታዊ ተስፋ ትንቢታዊ እውነት የሚያዳብሩ ናቸው። ሐዋርያው ጳውሎስ አማኝ ለሆነው አሕዛብ ለቆርኔሌዎስ “ነቢያት ሁሉ [ለኢየሱስ] ይመሰክሩለታል” ብሎአል። (ሥራ 10:43) 20 ከሚያክሉ ዓመታት በኋላ ሐዋርያው ጳውሎስ “እግዚአብሔር ለሰጠው የተስፋ ቃል ሁሉ አዎን ማለት በእርሱ [በኢየሱስ] ነው” ብሎአል። (2 ቆሮንቶስ 1:20) 43 ከሚያክሉ ዓመታት በኋላ ደግሞ ዮሐንስ ራሱ “እውነት ግን በኢየሱስ ክርስቶስ ሆነ” ብሎአል።—ዮሐንስ 1:17
23. ለኢየሱስ ከፍተኛ ማዕረግና ሥልጣን መሰጠቱ ለይሖዋ የሚሰጠውን አምልኮ የማይቀንሰው ለምንድን ነው?
23 ታዲያ እንዲህ መሆኑ ለይሖዋ የምንሰጠውን አምልኮ በአንዳች መንገድ ይቀንሰዋልን? በፍጹም አይቀንሰውም። መልአኩ የተናገረውን የማስጠንቀቂያ ምክር እናስታውስ። “ለእግዚአብሔር ስገድ” ወይም “እግዚአብሔርን አምልክ” አለ። ኢየሱስ ከይሖዋ ጋር ለመተካከል በፍጹም ሞክሮ አያውቅም። (ፊልጵስዩስ 2:6) እርግጥ ነው፣ “የእግዚአብሔር መላእክት ሁሉ [ለኢየሱስ] ይስገዱለት” ተብሎ ተነግሮአል። “ጉልበት ሁሉ ለኢየሱስ ስም ይንበረከክ ዘንድ” ፍጥረት በሙሉ ለኢየሱስ የተሰጠውን ከፍተኛ ማዕረግ ማወቅና መቀበል ይኖርበታል። ይሁን እንጂ ይህን የሚያደርጉት “ለእግዚአብሔር አብ ክብር” እና በይሖዋ ትዕዛዝ እንደሆነ ልብ በሉ። (ዕብራውያን 1:6፤ ፊልጵስዩስ 2:9-11) ይሖዋ ይህን ከፍተኛውን ሥልጣኑን ለኢየሱስ ሰጥቶታል። ይህንን ሥልጣኑን በመቀበላችንና በማወቃችን አምላክን እናከብረዋለን። ለኢየሱስ ሥልጣን ለመገዛት እምቢተኞች ከሆንን ይሖዋን ራሱን ክደነዋል ማለት ነው።—መዝሙር 2:11, 12
24. በጉጉት የምንጠባበቀው የትኞቹን ሁለት አስደናቂ ክንውኖች ነው? በዚህስ ምክንያት የትኞቹን ቃላት ማሰማት ይኖርብናል?
24 ስለዚህ ሁላችንም በኅብረት ከመዝሙር 146 እስከ 150 ላሉት መዝሙሮች መክፈቻ የሆኑትን ቃላት እናሰማ። “ሃሌ ሉያ” ወይም ያህን አወድሱ እንበል። ይሖዋ በባቢሎናዊው የሐሰት ሃይማኖት ግዛት ላይ የሚቀዳጀውን ታላቅ ድል በጉጉት በምንጠባበቅበት ጊዜ ሁሉ ይህ የሃሌ ሉያ ዝማሬ ከዳር እስከ ዳር ያስተጋባ! የበጉ ሰርግ እየተቃረበ በሄደ መጠን ደስታችን ከዕለት ወደ ዕለት ይብዛ!
[የግርጌ ማስታወሻ]
[በገጽ 273 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
“ለሰዶምና ገሞራ የተላከ መልእክት”
የለንደን ዴይሊ ቴሌግራፍ በህዳር 12, 1987 እትሙ ላይ ባወጣው በዚህ ዋነኛ ርዕስ ሥር ለእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን ጠቅላይ ሲኖዶስ ቀርቦ ስለነበረው የውሳኔ አሳብ ዘግቦአል። ይህ ውሳኔ ግብረ ሰዶም የሚፈጽሙ “ክርስቲያኖች” ከቤተ ክርስቲያን እንዲወገዱ የሚጠይቅ ነበር። የርዕሰ አንቀጽ ጸሐፊ የሆኑት ጎድፍሬይ ባርከር “የካንተርበሪው ሊቀ ጳጳስ በትናንትናው ቀን ‘ቅዱስ ጳውሎስ ለእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን ደብዳቤ ቢጽፍ እንዴት ያለ ደብዳቤ ይጽፍ ነበር? ብለን ራሳችንን እንጠይቅ’ በማለት በምሬት ተናግረዋል” ካሉ በኋላ “ለሰዶምና ገሞራ የተላከ መልእክት ብሎ ይጽፍ ነበር” በማለት ሚስተር ባርከር ራሳቸው መልሱን ሰጥተዋል። ቀጥለውም “ዶክተር ራንሲ [ሊቀ ጳጳሱ] ከሮሜ ምዕራፍ 1 የተለየ መልእክት እንደማይሆን ገምተዋል” ብለዋል።
ጸሐፊው በሮሜ 1:26–32 ላይ ጳውሎስ የጻፈውን ቃል እንደሚከተለው ጠቅሰዋል:- “እግዚአብሔር ለማይገባ አስነዋሪ ምኞት አሳልፎ ሰጣቸው። . . . ስለዚህ ወንዶች ከወንዶች ጋር አሳፋሪ ነገር ፈጸሙ። . . . እነዚህን ነገሮች የሚያደርጉ ሁሉ ሞት ይገባቸዋል የሚለውን የእግዚአብሔርን ሕግ እያወቁ ይህን ሁሉ ያደርጋሉ፣ ማድረግ ብቻ ሳይሆን እንዲህ የሚያደርጉትንም ሰዎች ያበረታታሉ።” ጽሑፋቸውን ሲያጠቃልሉ “ቅዱስ ጳውሎስን ያሳሰበው የተራ አማኞች ሁኔታ ነበር። ዶክተር ራንሲ ግን የተቸገሩት በሰባኪዎች ሁኔታ ነው” ብለዋል።
ሊቀ ጳጳሱ ይህን የመሰለ ችግር ያጋጠማቸው ለምንድን ነው? በለንደን ዴይሊ ሜይል ጋዜጣ ላይ ጥቅምት 22 ቀን 1987 የወጣው ርዕስ እንዲህ ብሎ ነበር:- “ከሦስት ቀሳውስት አንዱ ግብረ ሰዶም የሚፈጽም ነው። . . . ግብረ ሰዶማውያንን ለማስወገድ ዘመቻ ቢደረግ የእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን ይዘጋል።” የተጠቀሰው ዘገባ “ብፁዕ” የወንድና የሴት ግብረ ሰዶማውያን ክርስቲያናዊ እንቅስቃሴ ጠቅላይ ጸሐፊ የሚከተለውን እንደተናገሩ ጠቅሶአል:- “ይህ የውሣኔ ሐሳብ ቢጸድቅ ቤተ ክርስቲያን ፈጽማ ትፈራርሳለች። የካንተርበሪው ሊቀ ጳጳስም ይህንን አሳምረው ያውቁታል። ጠቅለል ባለ አነጋገር ከእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን ቀሳውስት ከ30 እስከ 40 በመቶ የሚያክሉት ግብረ ሰዶማውያን ናቸው። እነዚህ ደግሞ ለቤተ ክርስቲያኒቱ አገልግሎት ከፍተኛውን ድርሻ የሚያበረክቱ ናቸው።” የቤተ ክርስቲያን ተሳላሚዎች ቁጥር በጣም እያነሰ መሄዱ ሰዎች ግብረ ሰዶም የሚፈጽሙ ቀሳውስት በመብዛታቸው የተንገሸገሹ መሆናቸውን ያመለክታል።
የቤተ ክርስቲያኒቱ ሲኖዶስ ምን ወሰነ? 388 አባላት (95 ከመቶ የሚያክሉት ማለት ነው) ለስለስ ያለ ውሳኔ እንዲተላለፍ ድምፅ ሰጡ። ስለዚህ ውሳኔ የህዳር 14, 1987 ዘ ኢኮኖሚስት መጽሔት የሚከተለውን ጽፎአል:- “የእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን ግብረ ሰዶምን ይቃወማል። ቢሆንም የተቃውሞው መጠን በቂ አይደለም። የቤተ ክርስቲያኒቱ ሸንጎ የሆነው ጠቅላይ ሲኖዶስ የግብረ ሰዶም ድርጊት የሚፈጽሙ ቄሶችን በማሰብ ግብረ ሰዶም እንደ ዝሙትና እንደ ምንዝር ኃጢአት አይደለም፣ ቋሚ በሆነ የጋብቻ ሰንሰለት ውስጥ ከሚፈጸመው ትክክለኛ የፆታ ግንኙነት በጥቂቱ የሚያንስ ድርጊት ነው የሚል ውሳኔ በዚህ ሳምንት አስተላልፎአል።” ዘ ኢኮኖሚስት ይህንን የካንተርበሪውን ሊቀ ጳጳስ አቋም ሐዋርያው ጳውሎስ በሮሜ 1:26, 27 ላይ ከሰጠው ቀጥተኛ መግለጫ ጋር በማወዳደር ከዋናው ርዕስ ግርጌ “ቅዱስ ጳውሎስ ምን እየተናገረ እንዳለ ያውቅ ነበር” የሚል አጭር መግለጫ አስፍሮ ነበር።
ኢየሱስ ክርስቶስም ምን እየተናገረ እንዳለ ያውቅ ነበር። በጣም ግልጽ በሆነ ሁኔታም ተናግሮአል። የእርሱም መልእክት ከናቁት ሃይማኖታውያን ይልቅ ለሰዶምና ገሞራ ሰዎች በፍርድ ቀን እንደሚቀልላቸው ተናግሮአል። (ማቴዎስ 11:23, 24) እዚህ ላይ ኢየሱስ የአምላክን ልጅና ትምህርቱን ያልተቀበሉት ሃይማኖታዊ መሪዎች ከሰዶም ሰዎች የበለጠ ነውረኞች እንደሆኑ በተነጻጻሪ ሁኔታ መግለጹ ነበር። የሰዶም ሰዎች ‘በዘላለም እሳት’ ወይም በዘላለም ጥፋት እንደተቀጡ ይሁዳ 7 ይናገራል። (ማቴዎስ 25:41, 46) እንግዲያው የታወሩ መንጎቻቸውን ከአምላክ መንግሥት ከፍተኛ የሥነ ምግባር ሕግጋት ዘወር አድርገው ወደዚህ ዓለም ወራዳና ውዳቂ ሥነ ምግባር በጭፍን የሚመሩ ክርስቲያን ነን ባይ ሃይማኖታዊ መሪዎች እንዴት የባሰ ፍርድ ይቀበሉ! (ማቴዎስ 15:14) የሐሰት ሃይማኖት ድርጅት ስለሆነችው ስለ ታላቂቱ ባቢሎን ከሰማይ የተሰማው ድምፅ በአጣዳፊ ሁኔታ እንዲህ ይላል:- “ሕዝቤ ሆይ፣ በኃጢአትዋ እንዳትተባበሩ ከመቅሰፍትዋም እንዳትቀበሉ ከእርስዋ ዘንድ ውጡ።”—ራእይ 18:2, 4
[በገጽ 275 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
በታላቂቱ ባቢሎን ላይ ስላገኘው የመጨረሻ ድል ያህን በማወደስ ሰማይ አራት ጊዜ ሃሌ ሉያ የሚል ድምፅ ያስተጋባል