ንጹሑን ልሳን ተናገርና ለዘላለም ኑር!
“[ይሖዋን (አዓት)] ፈልጉ፣ ጽድቅንም ፈልጉ፣ ትሕትናንም ፈልጉ። ምናልባት [በይሖዋ (አዓት)] ቁጣ ቀን ትሰወሩ ይሆናል።”—ሶፎንያስ 2:3
1. (ሀ) ተማሪዎች የውጭ ቋንቋን ለመማር በምን ዘዴዎች ይጠቀማሉ? (ለ) ንጹሑን ልሣን መናገር ያለብን ለምንድነው?
ተማሪዎች አንድን አዲስ ቋንቋ የሰዋሰውን ሥርዓት በማጥናት ወይም ሰዎች ሲናገሩ በመስማት ሊማሩት ይችላሉ። በሰዋስው ሥርዓት ሲማሩት ባጠቃላይ የመማሪያ መጻሕፍትን በመጠቀም የሰዋሰው ሕጎችን ይማራሉ። በመስማት በሚማሩበት ጊዜም በመምህራቸው የተነገሩ ድምፆችንና የንግግር ፈሊጦችን በመቅዳት ወይም በመኮረጅ ይማራሉ። “ንጹሑን ልሳን” ለመማር ሁለቱም ዘዴዎች ያገለግላሉ። “በይሖዋ የቁጣ ቀን ለመሰወር” የምንሻ ከሆነም ይህን ቋንቋ መናገራችን አስፈላጊ ነው።—ሶፎንያስ 2:1-3፤ 3:8, 9
2. የንጹሑ ቋንቋ የሰዋሰው ሕግ ሊባል የሚችለውን መማር የምንችለው እንዴት ነው?
2 ንጹሑን ልሳን ለመማር አስፈላጊ የሆነው የመማሪያ መጽሐፍ መጽሐፍ ቅዱስ ነው። እሱንና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን በትጋት በማጥናት ለንጹሑ ልሳን የሰዋስው ሕግ የሚባሉትን ልትማሩ ትችላላችሁ። ከይሖዋ ምስክሮች ባንዱ የሚመራ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ጥሩ ጅምር ነው። ከዚህ ቀደም ራሳቸውን ለይሖዋ የወሰኑ ሰዎችም ዘወትር በትጋት ቅዱሳት መጻሕፍትን ማጥናታቸው እጅግ አስፈላጊ ነው። ይሁን እንጂ ንጹሑን ልሳን ለመማር ይበልጥ ውጤታማ የሆኑ የተለዩ መንገዶች አሉን? ንጹሑን ልሳን በመናገርስ ምን ጥቅሞች ይመጣሉ?
ንጹሑን ልሳን እንዴት መማር እንደሚቻል
3. ንጹሑን ልሣን ለመማር ብቸኛው መንገድ ምንድነው?
3 አንድን ቋንቋ በማጥናት ላይ ያለ ሰው ልዩ ልዩ የሰዋሰው ሕጎችን ለማዛመድ እንደሚሞክር ሁሉ ንጹሑን ልሳን ለመማር የሚረዳው አንዱ መንገድ እየተማርክ ያለኸውን እውነት ከዚህ በፊት ከምታውቃቸው ነጥቦች ጋር ማገናዘብ ነው። ለምሳሌ ባንድ ወቅት ኢየሱስ ክርስቶስ የአምላክ ልጅ እንደሆነ አውቀህ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ተግባሮቹን በሚመለከት የምታውቀው ጥቂት ኖሮ ይሆናል። ከዚያን ጊዜ ወዲህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትህ ክርስቶስ ሰማያዊ ንጉሥ በመሆን አሁን እንደሚገዛና በሺህ ዓመት ግዛቱ ወቅትም የሰው ልጆች ወደ ፍጽምና ደረጃ እስኪደርሱ እንደሚረዳቸው አስተምሮሃል። (ራእይ 20:5, 6) አዎን አዲስ ሐሳቦችን ከዚህ በፊት ከምታውቃቸው ጋር ማገናዘብ ንጹሑን ቋንቋ የመረዳት ችሎታህን ያሻሽለዋል።
4. (ሀ) የንጹሑን ልሣን ‘ሰዋሰዋዊ ሕግ’ ለመማር ሌላው መንገድ ምንድነው? ይህንን በምሳሌ ለማስረዳትስ የትኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ተጠቅሷል? (ለ) ጌዴዎንና ከእርሱ ጋር የነበሩት ሦስት መቶ ሰዎች እርምጃ ሲወስዱ ምን ሆነ? የጌዴዎን ታሪክ ምን ትምህርት ያስተምራል?
4 የንጹሕ ልሳንን ‘ሰዋስዋዊ’ ሕጎች ለመማር ሌላው መንገድ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጹ ድርጊቶችን በዓይነት ሕሊና ማየት ነው። ለምሳሌ ያህል በመሳፍንት 7:15-23 ላይ የተመዘገበውን ታሪክ “ለማየትና ለማዳመጥ” ሞክር። ተመልከት። እስራኤላዊው መስፍን ጌዴዎን ሠራዊቱን እያንዳንዱ ሦስት መቶ ጓዶች ያሉት ሦስት ቦታ ከፋፈላቸው። በጨለማ ከጊልቦአ ተራራ ወርደው ተኝተው ያሉትን ምድያማውያን ሠፈር ይከብባሉ። እነዚህ ሦስት መቶ ሰዎች በደንብ የታጠቁ ናቸውን? ወታደራዊ ጦር መሣሪያ አልታጠቁም። ትዕቢተኛ ወታደራዊ ጠበብት እንዴት በሳቁባቸው! እያንዳንዱ ሰው የያዘው መለከት፣ ትልቅ ማሰሮና በማሰሮው ውስጥ ችቦ ብቻ ነው። ይሁን እንጂ እስቲ አዳምጥ! ምልክት ሲሰጣቸው ከጌዴዎን ጋር ያሉት መቶ ሰዎች መለከታቸውን ነፉ፤ ማሰሮዎቻቸውንም ሰባበሩ። ሌሎቹ ሁለት መቶ ወታደሮችም እንደዚያው አደረጉ። ሁሉም የሚንበለበሉ ችቦዎቻቸውን ወደ ላይ ከፍ አድርገው በመያዝ “የይሖዋና የጌዴዎን ሰይፍ!” ብለው ሲጮኹ ትሰማለህ። ይህ ምድያማውያንን እንዴት የሚያሸብር ነው! ከድንኳኖቻቸው እየተንገዳገዱ ሲወጡ በእንቅልፍ የከበዱ ዓይኖቻቸው ደግሞ ፍርሃት የሚያሳድር ጥላ የፈጠሩትን የሚንቦገቦጉ የሚፈነጣጠሩ ችቦዎችን በፍርሃት ፈጥጠው ይመለከታሉ። ምድያማውያን መሸሽ ሲጀምሩ የጌዴዎን ሰዎች መለከቶቻቸውን መንፋታቸውን ይቀጥላሉ። አምላክም ጠላቶቻቸውን አንዱን በሌላው ላይ ያስነሣቸዋል። ይህስ በንጹሑ ልሳን የሚገኝ እንዴት ትልቅ ትምህርት ነው! አምላክ አገልጋዮቹን ያለ ሰብአዊ ጦር ኃይል ሊያድን ወይም ነፃ ሊያወጣ ይችላል። ከዚህም በላይ “ይሖዋ ስለ ታላቅ ስሙ ሲል ሕዝቡን አይተውም።”—1 ሳሙኤል 12:22
5. ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ንግግራችንን ለማጥራት ሊረዱን የሚችሉት እንዴት ነው?
5 ተማሪዎች አንድን የባዕድ ቋንቋ በመስማት ዘዴ በሚማሩበት ጊዜ የመምህሩን ድምፅና አነጋገር በትክክል ለመድገም ወይም ለመኮረጅ ይሞክራሉ። ንጹሑን ልሳን በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ለመናገር እንዴት መልካም አጋጣሚዎች አሉ! እዚያም ሌሎች በዚያ የቅዱስ ጽሑፋዊ እውነት ቋንቋ ሐሳባቸውን ሲገልጹ እንሰማለን፤ እኛም ራሳችን ሐሳባችንን ለመግለጽ መብት እናገኛለን። የተሳሳተ ነገር እንዳንናገር እንፈራለንን? ያ አያሳስበን፤ ምክንያቱም እንደ ሳምንታዊው መጠበቂያ ግንብ በመሳሰሉት ስብሰባዎች ላይ የሚመራው ሽማግሌ በደግነት ሲያርመን ንግግራችንን የተጣራ ሊያደርግልን ይችላል። ስለዚህ አዘውትረህ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ተገኝ፤ ተሳተፍም።—ዕብራውያን 10:24, 25
የቆሸሸ አነጋገር ሰርጎ ገባ
6. በይሖዋ ምሥክሮችና በሕዝበ ክርስትና ሃይማኖታዊ ድርጅቶች መካከል ይህን ያህል ጉልህ ልዩነት ያለው ለምንድነው?
6 የይሖዋን ዓላማ የሚያውጁና ሰማያዊ መንግሥቱንም የሚያስታውቁ ሁሉ ምስክሮቹ በመሆን ንጹሕ ልሳን ይናገራሉ። ስሙን ያስታውቃሉ። “ትከሻ ለትከሻ” ወይም ስምም ሆነውም ያገለግሉታል። (ሶፎንያስ 3:9) የሕዝበ ክርስትና ሃይማኖቶች መጽሐፍ ቅዱስ ቢኖራቸውም ንጹሑን ልሳን አይናገሩም፤ ወይም በእምነት በስሙ አይጠሩም። (ኢዩኤል 2:32) በቅዱሳት መጻሕፍት ላይ የተመሠረተ እርስ በርሱ የሚስማማ መልእክት የላቸውም። ለምን? ምክንያቱም ሃይማኖታዊ ወጎችን፣ ዓለማዊ ፍልስፍናዎችንና ፖለቲካዊ ድጋፍ ሰጭነትን ከአምላክ ቃል በላይ አድርገው ስለያዙ ነው። ዓላማቸው፣ ተስፋቸውም ሆነ ዘዴያቸው ሁሉ የዚህ ክፉ ዓለም ነው።
7. በ1 ዮሐንስ 4:4-6 ላይ በይሖዋ ምሥክሮችና በሐሰት ሃይማኖቶች መካከል ምን ልዩነት እንዳለ ነው የሚያመለክተው?
7 ሕዝበ ክርስትና እንዲያውም ጠቅላላው የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ግዛት የይሖዋ ምስክሮች የሚናገሩትን ዓይነት ቋንቋ አይናገሩም። ለዚህም ነው ሐዋርያው ዮሐንስ ንጹሑን ልሳን ለሚናገሩት እንደሚከተለው የጻፈው፦ “እናንተ ከእግዚአብሔር ናችሁ አሸንፋችሁማል [ምክንያቱም] በዓለም ካለው ይልቅ በእናንተ ያለው ይበልጣልና። እነሱ ከዓለም ናቸው፤ ስለዚህ ከዓለም የሆነውን ይናገራሉ። ዓለሙም ይሰማቸዋል። እኛ ግን ከእግዚአብሔር ነን እግዚአብሔርን የሚያውቅ ይሰማናል። ከእግዚአብሔር ያልሆነ አይሰማንም።” (1 ዮሐንስ 4:4-6) የይሖዋ አገልጋዮች የሐሰት አስተማሪዎችን አሸንፈዋል። ምክንያቱም ከሕዝቡ ጋር የሆነው አምላክ “በዓለም ካለው [ከዓለም ማለትም ከዓመፀኛው ሰብአዊ ኅብረተሰብ ጋር ካለው ከዲያብሎስ] ይበልጣልና።” ከሐዲዎች “ከዓለም ስለሆኑ” እና የሱ ክፉ መንፈስም ስላላቸው “ከዓለም የሆነውን ይናገራሉ፤ ዓለሙም ይሰማቸዋል።” በግ መሰል ግለሰቦች ግን የይሖዋ ሕዝቦች በድርጅቱ በኩል የሚቀርበውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ንጹሕ ልሳን እንደሚናገሩ በመገንዘብ የሚሰሙት ከአምላክ የሆኑትን ነው።
8. የዐመጽ ሰው መታወቂያው ወይም መለያው ምንድነው?
8 ታላቅ ክህደት እንደሚመጣ በትንቢት ተነግሮ ነበር። “የዓመፅ ምሥጢርም” ገና በመጀመሪያው መቶ ዘመን ብቅ ማለት ጀምሮ ነበር። ከጊዜ በኋላ በጉባኤ ውስጥ የማስተማርን ቦታ የተቀበሉ ወይም የያዙ ሰዎች ብዙ የሐሰት መሠረተ ትምህርቶችን አስተማሩ። ቋንቋቸው ንጹሕ ከመሆን በጣም የራቀ ነበር። ስለዚህ ከሐሰት ሃይማኖታዊ ወጎች፣ ከዓለማዊ ፍልስፍናዎችና ቅዱስ ጽሑፋዊ ካልሆኑ ትምህርቶች ጋር የተሳሰረው “የዓመፅ ሰው” የተባለው የሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት ቡድን መጣ።—2 ተሰሎንቄ 2:3, 7
ንጹሑ ልሳን በዓለም ዙሪያ ሲነገር ይሰማል
9. በ19ኛው መቶ ዘመን ምን ሃይማኖታዊ ሁኔታዎች በመከሰት ላይ ነበሩ?
9 “ለቅዱሳን ስለተሰጠ እምነት የሚጋደሉት” በቁጥር አነስተኛ የሆኑ ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ሰዎች ብቻ ናቸው። (ይሁዳ 3) እነዚህ አማኞች ሊገኙ የሚችሉት የት ነው? የሐሰት ሃይማኖት ቁጥር ስፍር የሌላቸውን ሕዝቦች ለብዙ መቶ ዓመታት በመንፈሳዊ ጨለማ አቆይቷቸዋል። ይሁን እንጂ አምላክ የሱ ድጋፍ ወይም ሞገስ ያላቸውን ሰዎች ያውቅ ነበር። (2 ጢሞቴዎስ 2:19) ከዚያም የንግድ፣ የኢንዱስትሪና ማኅበራዊ ለውጦች ይደረጉ በነበረበት በ19ኛው መቶ ዘመን ከአጠቃላዩ የሐሰት ሃይማኖት ዝብርቅ ባቤል የተለዩ ድምፆች መሰማት ጀመሩ። አነስተኛ ቡድኖች የዘመኑን ምልክቶች ለማንበብና የክርስቶስን ዳግማዊ ምፅዓት ለመተንበይ ሞከሩ፤ ይሁን እንጂ ሁሉም ንጹሑን ልሳን ተናጋሪዎቹ አልሆኑም።
10. “ዳግም መምጣትን” ይጠባበቁ ከነበሩት መካከል አምላክ ንጹሑን ልሣን እንዲናገር የመረጠው የትኛውን ቡድን ነው? የይሖዋ እጅ ከእነሱ ጋር እንደነበረ በግልጽ የሚታየውስ እንዴት ነው?
10 ይሁን እንጂ በ1879 ምስክሮቹ በመሆን ንጹሑን ልሳን እንዲናገር በይሖዋ የተመረጠው የትኛው “የዳግም ምፅዓት” ድምፅ እንደሆነ ግልጽ ሆነ። በዚያን ጊዜ በቻርልስ ቴዝ ራስል የሚመራ አንድ ንዑስ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ቡድን በዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ ውስጥ ፒትስበርግ ፔንሲልቫንያ መሰብሰብ ጀምሮ ነበር። እነሱም የኢየሱስ የማይታይ መገኘቱ በዳግም ምፅዓቱ እንደሚጀምር፣ የዓለም የመከራ ዘመን በመምጣት ላይ እንደነበረ፣ ይህንንም ተከታትሎ የሚመጣው ለታዛዥ ሰዎች ከዘላለም ሕይወት ጋር በምድር ላይ ገነትን የሚመልሰው የክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት መሆኑን እርግጠኞች ሆኑ። በ1879 ሐምሌ ወር ላይ እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች አሁን መጠበቂያ ግንብ በመባል የሚታወቀውን መጽሔት ማተም ጀመሩ። ከመጀመሪያው እትም ለሰዎች የታደሉት 6,000 ቅጂዎች ብቻ ነበሩ። ይሁን እንጂ “የይሖዋ እጅ” ከነዚያ ምስክሮቹ ጋር ነበር፤ ምክንያቱም ባሁኑ ጊዜ ይህ መጽሔት በ111 ቋንቋዎች በያንዳንዱ እትም ባማካይ ከ15,000,000 በላይ ቅጂዎች እየታተመ ነው።—ከሥራ 11:19-21 ጋር አወዳድር
11, 12. ንጹሑን ልሣን የሚናገሩት የተረዱአቸው አንዳንድ ቅዱስ ጽሑፋዊ እውነቶች ምንድናቸው?
11 በመጽሐፍ ቅዱስና በይሖዋ ምስክሮች ጽሑፎች አማካኝነት በተለይ ደግሞ እነዚህ ቀናተኛ ክርስቲያኖች ምሥራቹን ለማስታወቅ በሚያደርጉት ጥረት አማካኝነት ንጹሑ ልሳን በምድር ዙሪያ የታወቀ ሆኗል። ንጹሑን ልሳን የሚናገሩትስ እንዴት ያሉ ታላቅ ጥቅሞችን እያገኙ ነው! ምሥጢራዊውን የሥላሴ ቅንብር ተከትለው “እግዚአብሔር እግዚአብሔር ነው፤ ክርስቶስ እግዚአብሔር ነው፤ መንፈስ ቅዱስ እግዚአብሔር ነው” በማለት ፋንታ ይሖዋ ከሁሉ በላይ የሆነ ሉዓላዊ ገዥ፣ ኢየሱስ ደግሞ ከሱ ያነሰ ሆኖ ልጁ መሆኑንና መንፈስ ቅዱስ ደግሞ የአምላክ አስገራሚ አንቀሳቃሽ ኃይል መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ ከሚገልጸው አቋም ጋር ይስማማሉ። (ዘፍጥረት 1:2፤ መዝሙር 83:18፤ ማቴዎስ 3:16, 17) የንጹሑ ልሳን ተናጋሪዎች ሰው ከአነስተኛ የሕይወት ዓይነት ተነስቶ በመሻሻል የመጣ ሳይሆን በአፍቃሪ አምላክ የተፈጠረ መሆኑን ያውቃሉ። (ዘፍጥረት 1:27፤ 2:7) ሙታንን ከመፍራት የሚያድነውን እውነት ይኸውም የነፍስ ሕላዌ በሞት እንደሚያቆም ይገነዘባሉ። (መክብብ 9:5, 10፤ ሕዝቅኤል 18:4) ሲኦልን የተረዱት በአንድ ጨካኝ አምላክ የተፈጠረ የእሳታማ ሥቃይ ቦታ እንደሆነ አድርገው ሳይሆን የሰው ልጆች ሁሉ የጋራ መቃብር እንደሆነ ነው። (ኢዮብ 14:13) እንደዚሁም አምላክ ለሙታን የሰጠው ተስፋ ትንሣኤ መሆኑን ያውቃሉ።—ዮሐንስ 5:28, 29፤ 11:25፤ ሥራ 24:15
12 ንጹሑን ልሳን የሚናገሩት ሁሉ ለደምና ለሕይወት አክብሮት ያሳያሉ። (ዘፍጥረት 9:3, 4፤ ሥራ 15:28, 29) ለታዛዥ ሰዎች የተከፈለው የቤዛ ዋጋ የክርስቶስ ምድራዊ ሕይወት መሆኑን ይገነዘባሉ። (ማቴዎስ 20:28፤ 1 ዮሐንስ 2:1, 2) ጸሎታቸው መቅረብ ያለበት በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ለይሖዋ አምላክ ብቻ መሆኑን ስለሚያውቁ ወደ “ቅዱሳን” አይጸልዩም። (ዮሐንስ 14:6, 13, 14) የአምላክ ቃል ጣዖት ማምለክን ስለሚያወግዝ በአምልኮታቸው በምስሎች አይጠቀሙም። (ዘፀአት 20:4-6፤ 1 ቆሮንቶስ 10:14) ከዚህም ሌላ በመጽሐፍ ቅዱስ የተወገዘውን መናፍስትነትን ስለማይቀበሉ ከአጋንንት ጋር የተያያዘ ማንኛውም ነገር ከሚያመጣው አደጋ ይጠበቃሉ።—ዘዳግም 18:10-12፤ ገላትያ 5:19-21
13. ንጹሑን ልሣን የሚናገሩት ግራ የማይጋቡት ለምንድነው?
13 ንጹሑን ልሳን የሚናገሩ የይሖዋ አገልጋዮች በጊዜ ሂደት ውስጥ የትኛው ነጥብ ላይ ስለመድረሳቸው ግራ አይጋቡም። ኢየሱስ ክብር የተሞላ የማይታይ መንፈስ ሆኖ በተገኘበት “የፍጻሜ ዘመን” ላይ እንደሚኖሩ ይሖዋ አስተምሯቸዋል። (ዳንኤል 12:4፤ ማቴዎስ 24:3-14፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:1-5፤ 1 ጴጥሮስ 3:18) ክርስቶስ ኃያላን ሰማያዊ ሠራዊቶችን ከኋላው አስከትሎ የአምላክን ፍርድ በዚህ የነገሮች ሥርዓት ላይ ለማስፈጸም ወደ ጦርነት ሜዳ ሊገባ ነው። (ዳንኤል 2:44፤ ራእይ 16:14, 16፤ 18:1-8፤ 19:11-21) አዎን፣ ንጹሑን ልሳን የሚናገሩትንም በክርስቶስ የምትመራው የአምላክ መንግሥት በቅርቡ ለታዛዥ የሰው ልጆች በሙሉ በምድራዊ ገነት ታላላቅ በረከቶችን እንደምታመጣ የሚገልጸውን የምሥራች በማወጅ እየተጣደፉ ነው። (ኢሳይያስ 9:6, 7፤ ዳንኤል 7:13, 14፤ ማቴዎስ 6:9, 10፤ 24:14፤ ሉቃስ 23:43) ይህ ሁሉ አለ፤ እንዲያውም ከላይ ከላይ ብቻ ጨረፍ ስናደርግለት ነው። በእርግጥም ንጹሑ ልሳን በምድር ላይ ካሉት ቋንቋዎች ሁሉ ይበልጥ የበለጸገና ውድ የሆነ ቋንቋ ነው!
14. ንጹሑን ልሣን የሚናገሩት ያገኙአቸው ሌሎች ጥቅሞች ምንድናቸው?
14 ንጹሑን ልሳን የሚናገሩ ሰዎች የሚያገኙአቸው ጥቅሞች ልብንና አእምሮን የሚጠብቀውን “የአምላክን ሰላምም” ይጨምራሉ። (ፊልጵስዩስ 4:6, 7) ጤንነትን፣ ደስታንና ይሖዋን ከማስደሰት የሚመጣውን እርካታ የሚያመጡትን የመጽሐፍ ቅዱስን ሕጎች ይታዘዛሉ። (1 ቆሮንቶስ 6:9, 10) አዎን፤ የንጹሑን ልሳን ተናጋሪዎች አምላክ ተስፋ በገባው አዲስ ዓለም ለዘላለም የመኖር ተስፋ አላቸው።—2 ጴጥሮስ 3:13
ተጠቀምበት አለዚያ ትረሳዋለህ
15. ንጹሑን ልሣን በጥሩ ሁኔታ በመረዳትህ ልትጠቀም የምትችለው እንዴት ነው?
15 ወደ አዲሱ ዓለም ገብተህ ንጹሑን ቋንቋ እንድትናገር ከፈለግህ የምታስበውም በዚሁ ቋንቋ እስኪሆን ድረስ በደንብ ልታውቀው ይገባሃል። አንድ ሰው አንድን ቋንቋ በሚማርበት ጊዜ መጀመሪያ ላይ የሚያስበው በትውልድ ቦታው ቋንቋ ሆኖ ሐሳቦቹን ወደ አዲሱ ቋንቋ ይተረጉማል። በአዲሱ ቋንቋ በደንብ እየሠለጠነ በሄደ ቁጥር ግን የመተርጐሙ ሂደት ሳያስፈልገው በሱው ማሰብ ይጀምራል። በተመሳሳይም በትጋት በማጥናት የንጹሑን ልሳን ጥልቅ እውቀት ከማግኘትህ የተነሣ ችግሮችህን ለመፍታትና “በሕይወት መንገድ” ጸንተህ ለመኖር እንዲረዳህ የመጽሐፍ ቅዱስን ሕጎችና ሥርዓቶች በሥራ እንዴት እንደምታውላቸው ታውቃለህ።—መዝሙር 16:11
16. ንጹሑን ልሣን አዘውትረህ ካልተጠቀምክበት ምን ሊደርስብህ ይችላል?
16 በንጹሑ ልሳን አዘውትረህ መጠቀም አለብህ። አለዚያ አጥርተህ የመናገር ችሎታው ይጠፋብሃል። ለማስረዳት ያህል ከአያሌ ዓመታት ቀደም ብሎ አንዳንዶቻችን የውጭ ቋንቋ ተማርን። አሁን የዚያን ቋንቋ አንዳንድ ቃላት እናስታውስ ይሆናል። ግን አዘውትረን ስለማንጠቀምበት የመናገር ችሎታችንን አጥተን ይሆናል። በንጹሑ ልሳን ረገድም ያው ነገር ሊደርስ ይችላል። አዘውትረን የማንጠቀምበት ከሆነ ችሎታችንን ልናጣ እንችላለን። ያ ደግሞ በመንፈሳዊነታችን ላይ አሳዛኝ ውጤት ያስከትላል። ስለዚህ በስብሰባዎችና በመስክ አገልግሎት ንጹሑን ቋንቋ አዘውትረን እንናገረው። እንዲህ ማድረጋችን ከግል ጥናት ጋር ተጣምሮ ነገሮችን በንጹሑ ቋንቋ በትክክል እንድንናገር ያስችለናል። ያስ እንዴት አስፈላጊ ነው!
17. ንግግር ሕይወት አንድን ወይም ሞት የሚያስከትል ሊሆን እንደሚችል ለማስረዳት ምን መጥቀስ ይቻላል?
17 ንግግር ሕይወት አድን ሊሆን ወይም ሞት ሊያስከትል ይችላል። ይህም በእስራኤላዊው በኤፍሬም ነገድና በጊልያዱ መስፍን በዮፍታሔ መካከል ግጭት በተነሣበት ወቅት ታይቷል። የዮርዳኖስን ወንዝ ተሻግረው ይሸሹ የነበሩትን ኤፍሬማውያን ለይቶ ለማወቅ ጊልያዳውያን “ሺቦሌት” የሚለውን የመለያ ቃል ተጠቀሙ። የኤፍሬም ሰዎችም የቃሉን የመጀመሪያ ድምፅ (‘ሽ’) አሳስተው በመጥራት “ሲቦሌት” በማለት በዮርዳኖስ መልካዎች ላይ ለቆሙት የጊልያድ ዘቦች ራሳቸውን አሳልፈው ሰጡ። በዚህም ምክንያት 42,000 ኤፍሬማውያን ታረዱ። (መሳፍንት 12:5, 6) በተመሳሳይም ከመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ጋር በደንብ ለማይተዋወቁ ሰዎች የሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት የሚያስተምሩት ከንጹሑ ልሳን ጋር የሚቀራረብ ድምፅ ያለው ሊመስል ይችላል። ይሁን እንጂ በሐሰት ሃይማኖታዊ መንገድ መናገር በይሖዋ የቁጣ ቀን ሞት የሚያስከትል ይሆናል።
አንድነታችንን እንደጠበቅን እንኖራለን
18, 19. የሶፎንያስ 3:1-5 ትርጉም ምንድነው?
18 የጥንቷን እምነተ ቢስ ኢየሩሳሌምንና የሷን ዘመናዊ እኩያ ሕዝበ ክርስትናን በማስመልከት በሶፎንያስ 3:1-5 ላይ እንዲህ ተብሏል፦ “ለዓመፀኛይቱና ለረከሰች ለአስጨናቂይቱ ከተማ ወዮላት! ድምፅን አልሰማችም። ተግሣጽንም አልተቀበለችም። [በይሖዋም (አዓት)] አልታመነችም። ወደ አምላኳም አልቀረበችም። በውስጧ ያሉ አለቆቿ እንደሚያገሡ አንበሶች ናቸው። ፈራጆቿም እስከ ነገ ድረስ ምንም እንደማያስቀሩ እንደ ማታ ተኩላዎች ናቸው። ነቢያቶቿ ቅሌታሞችና ተንኰለኞች ሰዎች ናቸው። ካህናቶቿም መቅደሱን (ቅዱስ የነበረውን ነገር) አርክሰዋል። በሕግም ላይ ግፍ ሠርተዋል። [ይሖዋ (አዓት)] በውስጧ ጻድቅ ነው። ክፋትን አያደርግም። ፍርዱን በየማለዳው ወደ ብርሃን ያወጣል። ሳያወጣውም አይቀርም። ዓመፀኛው ግን እፍረትን አያውቅም።” የእነዚህ ቃላት ቁም ነገር ምንድን ነው?
19 የጥንቷ ኢየሩሳሌምም ሆነች ዘመናዊቷ ሕዝበ ክርስትና በይሖዋ ላይ ዓምፀዋል። በሐሰት አምልኮ ረክሰዋል። የመሪዎቻቸው መጥፎ ድርጊት ጭቆናን አስከትሏል። አምላክ በተደጋጋሚ ቢያስጠነቅቃቸውም ሰምተው ወደሱ አልቀረቡም። መሳፍንቶቻቸውም በዕብሪት ጽድቅን የሚንቁ እንደሚያደቡ አንበሶች ናቸው። እንደ ነጣቂ ተኩላዎችም በመሆን ፍትሕን ቦጫጭቀው ጥለውታል። ካህናቶቻቸው “ቅዱስ የሆነውን ነገር አርክሰዋል፤ በአምላክ ሕግ ላይም ግፍ (ዓመፅ) ሠርተዋል።” ስለዚህ ይሖዋ “የቁጣውን ትኩሳት ሁሉ ያፈስስባቸው ዘንድ አሕዛብን ሊሰበስብ መንግሥታትንም ሊያከማች” ነው።—ሶፎንያስ 3:8
20. (ሀ) በይሖዋ የቁጣ ቀን ለመዳን ምን መደረግ አለበት? (ለ) ከአምላክ የሚመጡትን ዘላለማዊ በረከቶች ለማግኘት ተስፋ ልታደርግ የምትችለው እንዴት ነው?
20 የይሖዋ የቁጣ ቀን በፍጥነት እየቀረበ ነው። ከዚያ ተርፎ ወደ አምላክ አዲስ ዓለም ለመግባት እንግዲያውስ ሳትዘገይ ንጹሑን ልሳን ተማርና ተናገር። እንዲህ ካደረግህ ብቻ ነው ባሁኑ ጊዜ ከመንፈሳዊ ታላቅ ውድቀትና በፍጥነት እየቀረበ ካለው ዓለም አቀፍ መዓት ጥበቃ ልታገኝ የምትችለው። የይሖዋ ምስክሮች የአምላክን የቁጣ ቀንና ልብን የሚያበረታታውን የመንግሥቱን መልእክት እያወጁ ነው። ስለ መንግሥቱ ክብር መናገር ምን ያህል ያስደስታቸዋል! (መዝሙር 145:10-13) ከነሱ ጋር ተባበርና የንጹሑ ቋንቋ ምንጭ ከሆነው ከልዑል የበላይ ገዥ ከይሖዋ የሚመጡትን የዘላለም ሕይወትና ሌሎች በረከቶችን ለማግኘት ተስፋ ልታደርግ ትችላለህ።
እንዴት ትመልሳለህ?
◻ ንጹሑን ልሳን ለመማር የሚረዱ አንዳንድ መንገዶች ምንድን ናቸው?
◻ ንጹሑን ልሳን መናገር ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው?
◻ ንጹሑን ልሳን አዘውትረህ የማትጠቀምበት ከሆነ ምን ሊያጋጥም ይችላል?
◻ አንድ ሰው የይሖዋን የቁጣ ቀን በሕይወት በማለፍ የዘላለም በረከቶችን ሊያገኝ የሚችለው እንዴት ነው?
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጌዴዎንና ከእርሱ ጋር የነበሩት ሰዎች መለከታቸውን ነፉ፤ ችቦአቸውንም ከፍ አድርገው ያዙት
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ቻርልስ ራስልና ተባባሪዎቹ አምላክ ንጹሑን ልሳን ለማስፋፋት እየተጠቀመባቸው እንዳለ ከ1879 ጀምሮ ግልጽ ሆነ
[በገጽ 20 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ንጹሑን ልሳን በመናገር በኩል ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር አንድ ሆነሃልን?