ምዕራፍ 16
አራት ፈረሰኞች እየጋለቡ ናቸው!
ራእይ 3--ራእይ 6:1-17
ርዕሰ ጉዳይ:- የአራቱ ፈረሰኞች ግልቢያ፣ በመሰዊያው ሥር የተኙት ሰማዕታን ምሥክሮችና ታላቁ የቁጣ ቀን
ራእዩ የሚፈጸምበት ጊዜ:- ከ1914 ጀምሮ ይህ የነገሮች ሥርዓት እስከሚጠፋበት ጊዜ
1. ይሖዋ ጥያቄ አስነስቶ በነበረው ጥቅልል ውስጥ የተጻፉትን ነገሮች ለዮሐንስ የገለጸለት እንዴት ነው?
በዚህ በችግር በተዋጠ ዘመን ውስጥ ስንኖር “ቶሎ ይሆን ዘንድ” ስላለው ነገር ለማወቅ ከፍተኛ ጉጉት ሊያድርብን አይገባምን? በእርግጥ ይገባናል። ምክንያቱም ይህ ጉዳይ የየግል ሕይወታችንን የሚነካ ነገር ነው። ስለዚህ ኢየሱስ ጥያቄ አስነስቶ የነበረውን ጥቅልል ሲከፍት እስቲ ከዮሐንስ ጋር ሆነን እንመልከት። ዮሐንስ የመጽሐፉን ጥቅልል ማንበብ አላስፈለገውም፤ ምክንያቱም በመጽሐፉ ጥቅልል ውስጥ የሰፈሩት ነገሮች የተላለፉለት ‘በምልክቶችና’ በጣም አስደናቂ በሆኑ ተከታታይ ትርዒቶች ነው።—ራእይ 1:1, 10
2. (ሀ) ዮሐንስ ምን ነገር አየ? ምንስ አዳመጠ? የኪሩቤሎቹ መልክ ምን ነገር ያመለክታል? (ለ) የመጀመሪያው ኪሩቤል ትዕዛዝ የሰጠው ለማን ነበር? እንዲህ ብለህ የመለስከው ለምንድን ነው?
2 ኢየሱስ የመጀመሪያውን ማኅተም ሲፈታ ዮሐንስ የተናገረውን እናዳምጥ:- “ከዚህም በኋላ በጉ ከሰባቱ ማኅተሞች የመጀመሪያውን ሲከፍት አየሁ። ከአራቱ እንስሶች አንዱ እንደ ነጎድጓድ በሚያስገመግም ድምፅ “ና” ሲል ሰማሁ።” (ራእይ 6:1 የ1980 ትርጉም) ይህ ድምፅ የመጀመሪያው ኪሩቤል ድምፅ ነው። ይህ ኪሩቤል የአንበሳ መልክ ያለው በመሆኑ የይሖዋ ድርጅት የይሖዋን የጽድቅ ፍርድ ለማስፈጸም በድፍረት እርምጃ እንደሚወስድ ዮሐንስ እንዲረዳ አስችሎታል። ይሁን እንጂ ይህ ትዕዛዝ የተሰጠው ለማን ነው? ዮሐንስ ቀደም ሲል በዚህ ትንቢታዊ ትዕይንት ውስጥ እንዲካፈል ተጋብዞ ስለነበረ ትዕዛዙ የተሰጠው ለዮሐንስ ሊሆን አይችልም። (ራእይ 4:1) ይህ ‘የነጎድጓድ ድምፅ’ የተነገረው ከአራት ተከታታይ ትርዒቶች የመጀመሪያው በሆነው በዚህ ትርዒት ለሚካፈሉት ተዋናዮች ነው።
ነጩ ፈረስና ታላቁ ጋላቢው
3. (ሀ) አሁን ዮሐንስ ምን ነገር ይገልጽልናል? (ለ) በመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎች ትርጉም መሠረት ነጩ ፈረስ የምን ምሳሌ መሆን ይኖርበታል?
3 ዮሐንስና ከዮሐንስም ጋር ቀናተኞቹ የዘመናችን የዮሐንስ ክፍል አባሎችና ተባባሪዎቻቸው በጣም ፈጣን ድራማ የመመልከት መብት አግኝተዋል። ዮሐንስ እንዲህ ብሎአል:- “አየሁም፣ እነሆም፣ አምባላይ (ነጭ) ፈረስ ወጣ፣ በእርሱም ላይ የተቀመጠው ቀስት ነበረው። አክሊልም ተሰጠው፣ ድልም እየነሣ ወጣ ድል ለመንሣት።” (ራእይ 6:2) አዎ፣ “ና” ለሚለው ነጎድጓዳማ ትዕዛዝ ምላሽ በመስጠት አንድ ነጭ ፈረስ ወጣ። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ፈረስ አብዛኛውን ጊዜ የጦርነት ምሳሌ ነው። (መዝሙር 20:7፤ ምሳሌ 21:31፤ ኢሳይያስ 31:1) ይህ የሚያምር ሰንጋ ፈረስ ነውርና እድፍ የሌለበትን ቅድስና በሚያመለክተው ንጣቱ ያንጸባርቅ ነበር። (ከራእይ 1:14፤ 4:4፤ 7:9፤ 20:11 ጋር አወዳድር) ፈረሱ የሚያመለክተው በይሖዋ ቅዱስ ዓይን ንጹሕና ቅዱስ የሆነውን ጦርነት ስለሆነ ይህን የመሰለ መልክ ያለው መሆኑ ምንኛ ተገቢ ነው!—በተጨማሪም ራእይ 19:11, 14ን ተመልከት።
4. የነጩ ፈረስ ጋላቢ ማን ነው? ግለጽ።
4 የዚህ ፈረስ ጋላቢ ማን ነው? ጋላቢው የማጥቂያ የጦር መሣሪያ የሆነውን ቀስት የያዘ ከመሆኑም በተጨማሪ ዘውድ ወይም አክሊል ተሰጥቶታል። በጌታ ቀን አክሊል ወይም ዘውድ ደፍተው የታዩ ጻድቃን ኢየሱስና በ24ቱ ሽማግሌዎች የተወከለው ቡድን ብቻ ናቸው። (ዳንኤል 7:13, 14, 27፤ ሉቃስ 1:31-33፤ ራእይ 4:4, 10፤ 14:14)a ከ24ቱ ሽማግሌዎች መካከል በራሱ የጽድቅ ሥራ ዘውድ የመቀበል መብት ለማግኘት የቻለ ይኖራል ብሎ ማሰብ የማይመስል ነገር ነው። ስለዚህ ይህ ብቸኛ ፈረሰኛ ከኢየሱስ ክርስቶስ በስተቀር ሌላ ማንም ሊሆን አይችልም። ዮሐንስ ኢየሱስን የተመለከተው ይሖዋ “እኔ ግን ንጉሤን ሾምሁ” ባለበትና “አሕዛብን ለርስትህ . . . እሰጥሃለሁ” ያለውን ቃል በፈጸመበት ታሪካዊ ዓመት በ1914 ነበር። (መዝሙር 2:6-8)b ስለዚህ ኢየሱስ የመጀመሪያውን ማኅተም ሲከፍት እርሱ ራሱ አምላክ በቀጠረው ጊዜ አዲስ የተሾመ ንጉሥ እንደመሆኑ ከጠላቶቹ ጋር ለመዋጋት እንዴት ባለ ሁኔታ እንደሚወጣ አሳየ።
5. መዝሙራዊው ከራእይ 6:2 ጋር በሚመሳሰል ሁኔታ ጋላቢውን የገለጸው እንዴት ነው?
5 ይህ ትርዒት በመዝሙር 45:4-7 ላይ ይሖዋ ስለ ሾመው ንጉሥ ከተነገረው ቃል ጋር በጥሩ ሁኔታ ይስማማል:- “ስለ ቅንነትና ስለ የዋህነት ስለ ጽድቅም አቅና ተከናወን ንገሥም። ቀኝህም በክብር ይመራሃል። ኃያል ሆይ ፍላጻዎችህ የተሳሉ ናቸው። እነርሱም በንጉሥ ጠላቶች ልብ ውስጥ ይገባሉ። አሕዛብም በበታችህ ይወድቃሉ። አምላክ ሆይ፣ ዙፋንህ ለዘላለም ነው። የመንግሥትህ በትር የቅንነት በትር ነው። ጽድቅን ወደድህ ዓመፃን ጠላህ፣ ስለዚህ ከባልንጀሮችህ ይልቅ እግዚአብሔር አምላክህ የደስታ ዘይትን ቀባህ።” ዮሐንስ ይህን ትንቢታዊ ቃል አሳምሮ ያውቅ ስለነበረ ኢየሱስ ንጉሥ ሆኖ ስለሚፈጽመው ነገር የሚገልጽ ትንቢት እንደሆነ ለመረዳት ይችል ነበር።—ከዕብራውያን 1:1, 2, 8, 9 ጋር አወዳድር።
ድል እየነሣ ወጣ
6. (ሀ) ጋላቢው ድል መንሳቱን መቀጠል የነበረበት ለምንድን ነው? (ለ) የድል አድራጊነቱ ግልቢያ የሚቀጥለው በየትኞቹ ዓመታት ውስጥ ነው?
6 ይሁን እንጂ አዲሱ ንጉሥ ወደ ጦርነት ለመውጣት የተገደደው ለምንድን ነው? ንግሥናው የተቋቋመው የእርሱን ንግሥና አምርሮ የሚቃወመው የይሖዋ ቀንደኛ ጠላት ሰይጣን ዲያብሎስና አውቀውም ሆነ ሳያውቁ ሰይጣንን የሚያገለግሉ የምድር ሰዎች ባሉበት ጊዜ ላይ በመሆኑ ነው። የመንግሥቱ መወለድ ራሱ በሰማይ ላይ ታላቅ ጦርነት እንዲደረግ የሚያስገድድ ሁኔታ ፈጥሮአል። ኢየሱስ ሚካኤል (“እንደ አምላክ ያለ ማን ነው?” ማለት ነው) በተባለው ስሙ ተዋግቶ ሰይጣንንና አጋንንቱን ድል በማድረግ ወደ ምድር ወርውሮአቸዋል። (ራእይ 12:7-12) የኢየሱስ የድል አድራጊነት ግልቢያ በግ መሰል ሰዎች እየተሰበሰቡ ባሉበት በጌታ ቀን የመክፈቻ አሥርተ ዓመታት ቀጥሎአል። አሁንም መላው ዓለም ገና “በክፉው እንደ ተያዘ” ቢሆንም ኢየሱስ ግን ቅቡዓን ወንድሞቹንና ባልንጀሮቻቸውን የእምነትን ድል እንዲያገኙ በመርዳት በእረኝነት በፍቅር መጠበቁን ቀጥሎአል።—1 ዮሐንስ 5:19
7. በመጀመሪያዎቹ የጌታ ቀን አሥርተ ዓመታት ኢየሱስ በምድር ላይ ምን ዓይነት ድል አግኝቶ ነበር? የእኛስ ቁርጥ ውሳኔ ምን መሆን ይኖርበታል?
7 ባለፉት ከ90 የሚበልጡ የጌታ ቀን ዓመታት ኢየሱስ ምን ሌሎች ድሎችን አግኝቶአል? በዓለም በሙሉ የይሖዋ ሕዝቦች በየግላቸውም ሆነ በጉባኤ ደረጃ ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ አገልግሎቱ ማስረጃ ባቀረበበት ጊዜ የገለጸውን የመሰለ ችግር፣ ተጽእኖ፣ ስደትና መከራ ደርሶባቸዋል። (2 ቆሮንቶስ 11:23-28) የይሖዋ ምሥክሮች ጦርነትና ዓመፅ በሚካሄድባቸው አካባቢዎች ጸንተው ለመኖር ‘ከተለመደው የበለጠ ኃይል’ አስፈልጎአቸዋል። (2 ቆሮንቶስ 4:7) ይሁን እንጂ ታማኞቹ ምሥክሮች ምንም ያህል አስቸጋሪና ፈታኝ ሁኔታ ቢያጋጥማቸውም እንደ ጳውሎስ “የስብከቱ ሥራ በእኔ እንዲፈጸም አሕዛብም ሁሉ እንዲሰሙት ጌታ በእኔ አጠገብ ቆሞ አበረታኝ” ለማለት ችለዋል። (2 ጢሞቴዎስ 4:17) አዎ፣ ኢየሱስ በእነዚህም ተከታዮቹ ረገድ ድል ነስቶአል። ወደፊትም ቢሆን የራሳችንን የእምነት ድል ለመፈጸም ቆርጠን እስከ ተነሳን ድረስ ስለ እኛ ድል በመንሳት ይቀጥላል።—1 ዮሐንስ 5:4
8, 9. (ሀ) ምድር አቀፉ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ እንዴት ባሉ ድሎች ተካፍሎአል? (ለ) የይሖዋ ምሥክሮች ቁጥር ከፍተኛ ዕድገት ያገኘባቸው አገሮች የትኞቹ ናቸው?
8 የይሖዋ ምሥክሮች ምድር አቀፍ ጉባኤ በድል አድራጊው ንጉሥ መሪነት በብዙ ድሎች ተካፍሎአል። እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በሰይጣን የፖለቲካ ሥርዓት ለጊዜው ‘ድል ተነስተው’ በነበረበት በ1918 ፈጽሞ እንዳይጠፉ ጠብቆአቸዋል። ይሁን እንጂ በ1919 የወህኒ ቤት በሮችን ሰብሮ ነፃ ካወጣቸው በኋላ ምሥራቹን “እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ” እንዲያውጁ አዲስ ሕይወት ሰጥቶአቸዋል።—ራእይ 13:7፤ ሥራ 1:8
9 በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅትና ከዚያም በኋላ ሃይማኖታዊ መሪዎች፣ በተለይ የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን መሪዎች ለጨቋኝ አምባገነን ገዥዎች ቀጥተኛም ሆነ ተዘዋዋሪ ድጋፍ በሰጡባቸው አገሮች አምባገነኖቹ ጀርመንና ከጐኗ የተሰለፉት የጦርነት ኃይላት የይሖዋ ምሥክሮችን ጨርሶ ለማጥፋት ጥረት አድርገው ነበር። ቢሆንም ጦርነቱ በጀመረበት ዓመት በ1939 በስብከት ሥራ ተሰማርተው የነበሩት 71,509 የይሖዋ ምሥክሮች ጦርነቱ በ1945 ሲያልቅ 141,606 ደርሰው ነበር። ይህን ያህል ጭማሪ ያገኙት ከ10,000 የሚበልጡ የይሖዋ ምሥክሮች በወህኒ ቤቶችና በማጎሪያ ካምፖች ለብዙ ዓመታት ታስረው በቆዩበትና ሌሎች 2,000 ደግሞ በተገደሉበት ጊዜ ነው። በአሁኑ ጊዜ በዓለም በሙሉ የሚገኙት የይሖዋ ምሥክሮች ቁጥር ከስድስት ሚልዮን በልጦአል። በጣም ከፍተኛ የሆነ እድገት የተገኘው በካቶሊክ አገሮችና እንደ ጀርመን፣ ኢጣልያና ጃፓን በመሰሉት ከባድ ስደት በነበረባቸው አገሮች ነው። በአሁኑ ጊዜ በእነዚህ አገሮች በአጠቃላይ ከ600,000 የሚበልጡ የመስክ አገልጋዮች አሉ።—ኢሳይያስ 54:17፤ ኤርምያስ 1:17-19
10. ድል አድራጊው ንጉሥ ‘ለምሥራቹ በመሟገትና ሕጋዊ እውቅና በማስገኘት’ ረገድ ሕዝቦቹን የባረከው እንዴት ነው?
10 በተጨማሪም ድል አድራጊው ንጉሣችን ለቀናተኛ ሕዝቦቹና ‘ለምሥራቹ በመሟገትና ሕጋዊ እውቅና በማስገኘት’ ረገድ በገዥዎች ፊትና በፍርድ ቤቶች ብዙ ድል አስገኝቶላቸዋል። (ፊልጵስዩስ 1:7፤ ማቴዎስ 10:18፤ 24:9) ይህ ዓይነቱ ድል የተገኘው በዓለም አቀፍ ደረጃ ሲሆን ከእነዚህም መካከል አውስትራሊያ፣ አርጀንቲና፣ ካናዳ፣ ግሪክ፣ ሕንድ፣ ስዋዚላንድ፣ ስዊዘርላንድ፣ ቱርክና ሌሎች አገሮች ይገኛሉ። የይሖዋ ምሥክሮች በዩናይትድ ስቴትስ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ካገኙአቸው 50 ሕጋዊ ድሎች መካከል ምሥራቹን “በአደባባይና ከቤት ወደ ቤት” የማወጅና ጣዖታዊ በሆኑ የአርበኝነት ሥርዓቶች ያለመካፈል ነፃነት የሚያሰጡት ውሣኔዎች ይገኛሉ። (ሥራ 5:42፤ 20:20፤ 1 ቆሮንቶስ 10:14) በዚህም መንገድ በጣም እየተስፋፋ ለመጣው ዓለም አቀፍ ምሥክርነት መንገዱ ተጠረገ።
11. (ሀ) ጋላቢው ‘ድሉን የሚደመድመው’ እንዴት ነው? (ለ) የሁለተኛው፣ የሦስተኛውና የአራተኛው ጥቅልል መፈታት በእኛ ላይ ምን ውጤት ማስከተል ይኖርበታል?
11 ኢየሱስ ‘ድል አድራጊነቱን የሚደመድመው’ እንዴት ነው?c ወደ ፊት እንደምንመለከተው የይሖዋን ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ የሐሰት ሃይማኖትን ካስወገደ በኋላ እያንዳንዱን የሰይጣን ድርጅት ክፍል በምሳሌያዊው እሳት ባሕር ውስጥ ጨምሮ በማጥፋት ነው። ‘ንጉሠ ነገሥታችን’ በጨቋኙ የሰይጣን ፖለቲካዊ ድርጅት ላይ የመጨረሻ ድል የሚቀዳጅበትን የአርማጌዶን ጦርነት በጉጉትና በትምክህት እንጠባበቃለን። (ራእይ 16:16፤ 17:14፤ 19:2, 14-21፤ ሕዝቅኤል 25:17) እስከዚያ ድረስ ግን ተሸንፎ የማያውቀው ድል አድራጊ የነጭ ፈረስ ጋላቢ፣ ይሖዋ በምድር ላይ ባሉት ጻድቅ ሕዝቦቹ ላይ ቅን ልብ ያላቸውን ሰዎች በሚጨምርበት በዚህ ዘመን ግልቢያውን ይቀጥላል። (ኢሳይያስ 26:2፤ 60:22) በዚህ አስደሳች የመንግሥት ማስፋፋት ሥራ ከቅቡዓን የዮሐንስ ክፍሎች ጋር በመካፈል ላይ ነህን? በዚህ ሥራ የምትካፈል ከሆነ የሚቀጥሉት ሦስት ማኅተሞች ሲፈቱ ዮሐንስ የተመለከተው ነገር ይሖዋ በዚህ ዘመን እንዲሠራ ባዘዘው ሥራ የበለጠ ተሳትፎ እንዲኖርህ እንደሚያነሳሳህ አያጠራጥርም።
እነሆ፣ ቀዩ ፈረስ!
12. ኢየሱስ ንጉሥ ሆኖ በማይታይ ሁኔታ መገኘቱ የሚታወቀው እንዴት እንደሆነ ሲገልጽ ምን ተናግሮ ነበር?
12 ኢየሱስ ምድራዊ አገልገሎቱን ሊፈጽም በተቃረበበት ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ብቻቸውን ሆነው “የመገኘትህና የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ ምልክቱ ምንድን ነው?” ብለው ጠይቀውት ነበር። ሲመልስላቸውም “የምጥ ጣር መጀመሪያ” የሚሆኑ ነገሮች እንደሚፈጸሙ ተናገረ። እንዲህ አላቸው:- “ሕዝብ በሕዝብ ላይ፣ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሳል። ታላቅም የምድር መናወጥና በልዩ ልዩ ሥፍራ ቸነፈር ራብም ይሆናል። የሚያስፈራም ነገር ከሰማይም ታላቅ ምልክት ይሆናል።” (ማቴዎስ 24:3, 7, 8 NW፤ ሉቃስ 21:10, 11) የቀሩት የመጽሐፉ ጥቅልል ማኅተሞች ሲፈቱ ዮሐንስ የተመለከታቸው ነገሮች ከዚህ ትንቢት ጋር በአስደናቂ ሁኔታ የሚመሳሰሉ ናቸው። ክብር የተቀዳጀው ኢየሱስ ሁለተኛውን ማኅተም ሲፈታ የሆነውን ነገር እንመልከት።
13. ዮሐንስ ቀጥሎ የተመለከተው ምን ዓይነት ተቃራኒ ሁኔታ ነው?
13 “ሁለተኛውንም ማኅተም በፈታ ጊዜ ሁለተኛው እንስሳ:- ‘መጥተህ እይ’ ሲል ሰማሁ።” (ራእይ 6:3) ይህን ትዕዛዝ ያስተላለፈው ወይፈን የሚመስለው ሁለተኛ ኪሩቤል ነው። እርሱም ምሳሌ የሆነው ለጽድቅ ሥራ ለሚውለው ኃይል ነው። ይሁን እንጂ ዮሐንስ አሁን፣ አሰቃቂና ሞትን የሚያስከትል የኃይል ድርጊት ሲፈጸም ሊመለከት ነው።
14. ዮሐንስ ቀጥሎ ምን ዓይነት ፈረስና ፈረሰኛ ተመለከተ? ይህስ ራእይ ምን ያመለክታል?
14 ታዲያ ይህ “ና” የሚለው ሁለተኛ ትዕዛዝ ምላሽ ያገኘው እንዴት ነው? በዚህ መንገድ ነበር:- “ሌላም ዳማ ፈረስ ወጣ፣ በእርሱም ላይ ለተቀመጠው ሰላምን ከምድር ይወስድ ዘንድ ሰዎችም እርስ በርሳቸው እንዲተራረዱ ሥልጣን ተሰጠው፣ ታላቅም ሰይፍ ተሰጠው።” (ራእይ 6:4) በእርግጥም የሚያስጨንቅ ራእይ ነው። ይህ ራእይ ጦርነትን እንደሚያመለክት ምንም አያጠራጥርም። ሆኖም ይህ ጦርነት ድል አድራጊው በይሖዋ የተሾመ ንጉሥ የሚያደርገው የጽድቅ ጦርነት ሳይሆን የማይፈለግ ደም መፋሰስና ሥቃይ የሚያስከትለው ሰው ሠራሽ የጭካኔ ጦርነት ነው። ይህ ጋላቢ ፍም በሚመስል ቀይ ፈረስ ላይ መጋለቡ እንዴት ተገቢ ነው!
15. ከሁለተኛው ፈረስ ግልቢያ ምንም ዓይነት ተካፋይነት እንዲኖረን የማንፈልገው ለምንድን ነው?
15 ስለ አምላክ ሕዝቦች “ከእንግዲህ ወዲያ ጦርነት አይማሩም” የሚል ትንቢት ስለተነገረ ዮሐንስ ከዚህ ፈረሰኛ ግልቢያ ምንም ዓይነት ተካፋይነት እንዲኖረው እንደማይፈልግ የታወቀ ነው። (ኢሳይያስ 2:4) ዮሐንስም ሆነ የዘመናችን የዮሐንስ ክፍል አባሎችና እጅግ ብዙ ሰዎች በዚህ ዓለም ውስጥ የሚኖሩ ቢሆኑም የዚህ በደም የተበከለው ሥርዓት ክፍል አይደሉም። የጦር መሣሪያዎቻችን ከሥጋዊ ትጥቅ የተለዩና መንፈሣዊ ሲሆኑ እውነትን በትጋት ለማወጅ ‘የአምላክ ኃይል’ አላቸው።—ዮሐንስ 17:11, 14፤ 2 ቆሮንቶስ 10:3, 4
16. የቀዩ ፈረስ ጋላቢ “ትልቅ ሠይፍ” የተሰጠው መቼና እንዴት ነበር?
16 የነጩ ፈረስ ጋላቢ ዘውድ ከተቀበለበት ከ1914 በፊት ብዙ ጦርነቶች ተደርገው ነበር። አሁን ግን የቀዩ ፈረስ ጋላቢ “ታላቅ ሠይፍ” ተሰጥቶታል። ታዲያ ይህ ነገር ምን ያመለክታል? የመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ከፈነዳበት ጊዜ ጀምሮ የሰው ልጆች ጦርነት ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ በጣም አሰቃቂና አጥፊ እየሆነ መጥቶአል። ደም እንደ ውኃ በፈሰሰባቸው ከ1914-1918 በነበሩት ዓመታት ታንኮች፣ የመርዝ ጭስ፣ አይሮፕላኖች፣ ባሕር ሰርጓጅ መርከቦች፣ ትላልቅ መድፎችና አውቶማቲክ መሣሪያዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ወይም ከዚያ በፊት ታይቶ በማያውቅ መጠን ውጊያ ላይ ውለዋል። በ28 አገሮች የውትድርና ሞያተኞች ብቻ ሳይሆኑ የየአገሮቹ ዜጎች በሙሉ በጦርነቱ እንዲካፈሉ ተገድደዋል። የጦር ጉዳተኞች መጠን እጅግ በጣም ብዙ ነበር። ከዘጠኝ ሚልዮን የሚበልጡ ወታደሮች ሲሞቱ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰላማውያን ሰዎች ተገድለዋል። ከዚህ ጦርነት በኋላም እንኳ ቢሆን እውነተኛ ሰላም ወደ ምድር አልተመለሰም። ይህ ጦርነት ከተደረገ ከ50 የሚበልጡ ዓመታት ካለፉ በኋላ የጀርመን ርዕሰ ብሔር የነበሩት ኮንራድ አደናወር “ከ1914 ጀምሮ ከሰው ልጆች ሕይወት አስተማማኝ ኑሮና ጸጥታ ፈጽሞ ጠፍቶአል” ብለዋል። በእርግጥም የቀዩ ወይም የዳማው ፈረስ ጋላቢ ከምድር ላይ ሰላምን እንዲወስድ ተሰጥቶታል።
17. ከአንደኛው የዓለም ጦርነት በኋላም ቢሆን “ትልቁ ሠይፍ” ጥቅም ላይ መዋሉ ያልተቋረጠው እንዴት ነው?
17 የቀዩ ፈረስ ጋላቢ የደም ጥማቱን በዚህ ዓይነት ከቀሰቀሰ በኋላ ወደ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ገባ። የግድያ መሣሪያዎች ይበልጥ ተራቀቁ። በጦርነቱ ያለቁት ሰዎች ቁጥር በመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ካለቁት አራት እጥፍ ሆነ። በ1945 ሁለት የአቶም ቦምቦች ጃፓን ላይ ፈነዱና በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች በቅጽበት አለቁ። የቀዩ ፈረስ ጋላቢ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት 55 ሚልዮን ሰዎችን አጭዶአል። ይሁን እንጂ በዚህም በቃኝ አላለም። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ከ20 ሚልዮን በላይ ነፍሳት ‘በረዥሙ ሠይፍ’ እንደተሰየፉ በአስተማማኝ ምንጮች ተረጋግጦአል።
18, 19. (ሀ) ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ የተፈጸመው መተራረድ የሚመሰክረው የወታደራዊ ቴክኖሎጂን ድል አድራጊነት ሳይሆን ምን ነገርን ነው? (ለ) በሰው ልጆች ሁሉ ላይ ምን ዓይነት አደጋ ተደቅኖአል? ይሁን እንጂ የነጩ ፈረስ ጋላቢ ይህን ለማስወገድ ምን ያደርጋል?
18 ታዲያ ይህን ሁሉ እልቂት የወታደራዊ ቴክኖሎጂ ድል አድራጊነት ነው ልንል እንችላለንን? ከዚህ ይልቅ ምህረት የማያውቀው የቀይ ፈረስ ጋላቢ በከፍተኛ ፍጥነት በመጋለብ ላይ መሆኑን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ነው። ታዲያ ይህ ግልቢያ የሚያቆመው የት ነው? አንዳንድ የሳይንስ ሊቃውንት ታስቦበትና ሆን ተብሎ የሚደረገው የኑክሌር ጦርነት ግምት ውስጥ ሳይገባ፣ ሳይታሰብ በድንገት የኑክሌር ጦርነት ሊፈነዳ እንደሚችል ይናገራሉ። ይሁን እንጂ የነጩ ፈረስ ጋላቢ ስለዚህ ጉዳይ ያሰበው ሌላ ነገር መኖሩ ያስደስተናል።
19 ማኅበረሰቡ በብሔራዊ ኩራትና ጥላቻ ላይ የተመሠረተ እስከሆነ ድረስ ምንም ጊዜ ሊፈነዳ በሚችል የኑክሌር አደጋ ላይ መቀመጡ የማይቀር ነው። ብሔራት ሊደርስባቸው በሚችለው እልቂት ተደናግጠው የኑክሌር መሣሪያዎችን ቢያጠፉም እንኳን መሣሪያዎቹን እንደገና ለመሥራት የሚያስችለው እውቀት ይኖራቸዋል። ባስፈለጋቸው ጊዜ እነዚህን ቀሳፊ የኑክሌር መሣሪያዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ መልሰው ሊሠሩ ይችላሉ። ስለዚህ በተለመዱት ተራ የጦር መሣሪያዎች የተጀመረ ጦርነት በአጭር ጊዜ ውስጥ ተፋፍሞ ከፍተኛ እልቂት ሊያስከትል ይችላል ማለት ነው። የነጩ ፈረስ ጋላቢ የቀዩን ፈረስ የእብደት ግልቢያ ለመግታት አንድ ነገር ካላደረገ በዛሬው ጊዜ ብሔራትን የዋጠው ኩራትና ጥላቻ በሰው ዘሮች ሁሉ ላይ እልቂት ሳያመጣ አይቀርም። ንጉሡ ክርስቶስ ሰይጣን በሚቆጣጠረው ዓለም ላይ የሚያገኘውን ድል እስኪፈጽምና በአምላክና በጎረቤት ፍቅር ላይ የተመሠረተ አዲስ ምድራዊ ማኅበረሰብ እስኪያቋቁም ድረስ ግልቢያውን እንደሚቀጥል እርግጠኞች እንሁን። ይህ ዓይነቱ ፍቅር በዚህ ባበደው ዘመናችን የኑክሌር ጥቃት እንዳይነሳ ይገታሉ ከሚባሉት ደካማ ዘዴዎች ሁሉ በጣም የበለጠ ሰላም የማስጠበቅ ኃይል አለው።—መዝሙር 37:9-11፤ ማርቆስ 12:29-31፤ ራእይ 21:1-5
ጥቁር ፈረስ ግልቢያ ጀመረ
20. የነጩ ፈረስ ጋላቢ ማንኛውንም ዓይነት አጥፊ ሁኔታ እንደሚቋቋም ምን መተማመኛ ተሰጥቶናል?
20 አሁን ኢየሱስ ሦስተኛውን ማኅተም ፈታ። ታዲያ ዮሐንስ ምን ተመለከተ? “ሦስተኛውንም ማኅተም በፈታ ጊዜ ሦስተኛው እንስሳ ‘መጥተህ እይ’ ሲል ሰማሁ።” (ራእይ 6:5ሀ) ይህ ሦስተኛ ኪሩቤል ‘ሰው የሚመስል ፊት’ ያለው መሆኑ በጣም ያስደስታል። ይህም የፍቅርን ባሕርይ ያመለክታል። በመሠረታዊ ሥርዓት የሚመራ ፍቅር በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ ይሰፍናል። በአሁኑም ጊዜ ቢሆን ይህ ዓይነቱ ፍቅር በመላው የይሖዋ ድርጅት ውስጥ ሰፍኖአል። (ራእይ 4:7፤ 1 ዮሐንስ 4:16) “ጠላቶቹን ሁሉ ከእግሩ በታች እስኪያደርግለት ድረስ” በጠላቶቹ መካከል የሚገዛው የነጭ ፈረስ ጋላቢ ቀጥሎ ዮሐንስ እንዲመለከት የተደረገውን መቅሠፍት ያስወግዳል።—1 ቆሮንቶስ 15:25
21. (ሀ) ጥቁሩ ፈረስና ጋላቢው የምን ምሳሌዎች ናቸው? (ለ) ጥቁሩ ፈረስ አሁንም ሕዝቡን ከመፍጀት እንዳልተገታ የሚያረጋግጥልን ምንድን ነው?
21 ታዲያ ዮሐንስ “ና” የሚለው ሦስተኛ ትዕዛዝ ሲፈጸም ምን ነገር ተመለከተ? “አየሁም፣ እነሆም ጉራቻ ፈረስ ወጣ፣ በእርሱም ላይ የተቀመጠው በእጁ ሚዛን ያዘ።” (ራእይ 6:5ለ) ከባድ ረሐብ! የዚህ ትንቢታዊ ትርዒት አስፈሪ መልእክት ይህ ነበር። በጌታ ቀን መጀመሪያ ላይ ምግብ በሚዛን እየተመዘነ በራሽን የተከፋፈለበትን ሁኔታ የሚያመለክት ነው። ከ1914 ጀምሮ ረሐብ ምድር አቀፍ ችግር ሆኖ ቆይቶአል። ረሐብተኞችን ለመመገብ ይውል የነበረው ሀብት በሙሉ የጦር መሣሪያዎችን ለማዘጋጀትና ለማቅረብ ስለሚውል ከዘመናዊው ጦርነት በኋላ ረሐብ መከተሉ የማይቀር ነገር ሆኖአል። የእርሻ ሠራተኞች ለውጊያ ይመለመላሉ። ማሳዎች በጦር መሣሪያዎች ስለሚቆፋፈሩና ቅጥ ያጣው የመሬት አስተዳደር ለምነታቸውን ስለሚያሳጣው በቂ ምርት መስጠት ይሳናቸዋል። ይህ ሁሉ ሁኔታ በመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ጊዜ ታይቶአል። በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በረሐብ እየተሠቃዩ ሞተዋል። ከዚህም በላይ የረሐብ ምሳሌ የሆነው የጥቁሩ ፈረስ ጋላቢ ጦርነቱ ካለቀ በኋላ ግልቢያውን ጋብ አላደረገም። በ1930ዎቹ ዓመታት በዩክሬይን ውስጥ ብቻ አምስት ሚልዮን ሰዎች በረሐብ ምክንያት ሞተዋል። ሁለተኛው የዓለም ጦርነትም ተጨማሪ ረሐብና ችጋር አስከትሎአል። ጥቁሩ ፈረስ ግልቢያውን በመቀጠሉ በ1987 አጋማሽ ላይ የዓለም ምግብ ምክር ቤት 512 ሚልዮን ሰዎች በረሐብ በመሰቃየት ላይ እንዳሉና በየቀኑ 40,000 ሕጻናት ከረሐብ ጋር በተዛመዱ ምክንያቶች የተነሣ እንደሚሞቱ ሪፖርት አድርጎአል።
22. (ሀ) አንድ ድምፅ ምን አለ? ይህስ ምን ነገር አስፈላጊ መሆኑን ያሳያል? (ለ) የአንድ እርቦ ስንዴና የሦስት እርቦ ገብስ ዋጋ መገለጹ ምን ያመለክታል?
22 ዮሐንስ ሌላም የሚነግረን ነገር አለው። “በአራቱም እንስሶች መካከል ድምፅ አንድ እርቦ ስንዴ በዲናር ሦስት እርቦ ገብስም በዲናር ዘይትንና ወይንንም አትጉዳ ሲል ሰማሁ።” (ራእይ 6:6) አራቱም ኪሩቤሎች ምግብ በማከፋፈል ረገድ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተስማምተዋል። ኢየሩሳሌም በ607 ከዘአበ ከመጥፋትዋ አስቀድሞ እሥራኤላውያን እንዳደረጉት “እየፈሩ እንጀራን በሚዛን መብላት” አስፈላጊ ይሆናል። (ሕዝቅኤል 4:16) በዮሐንስ ዘመን አንድ እርቦ ስንዴ የአንድ ወታደር የቀን ቀለብ ነበር። ይህን የሚያክል ስንዴ ምን ያህል ዋጋ ያወጣል? አንድ ዲናር የሚያወጣ ሲሆን አንድ ዲናር ደግሞ የአንድ ሠራተኛ የሙሉ ቀን ደመወዝ ነው። (ማቴዎስ 20:2)d ሰውዬው ቤተሰብ ያለው ከሆነስ? አንድ እርቦ ስንዴ ከመግዛት ይልቅ፤ ሦስት እርቦ ያልተፈተገ ገብስ ለመግዛት ይገደዳል። ይህም ቢሆን ብዙ ቤተሰብ ሊመግብ አይችልም። ገብስ ደግሞ የስንዴን ያህል ተፈላጊነት የነበረው እህል አልነበረም።
23. “ዘይትንና ወይንን አትጉዳ” የሚለው አባባል ምን ያመለክታል?
23 “ዘይትንና ወይንን አትጉዳ” የሚለው አነጋገር ምን ትርጉም አለው? አንዳንዶች ብዙዎቹ የሚበላ ነገር አጥተው በሚራቡበት ጊዜ ሀብታሞች ለቅንጦት የሚያስፈልጉአቸውን ነገሮች እንደማያጡና እንደማይጎዱ ያመለክታል ብለው ተረድተው ነበር። ይሁን እንጂ በመካከለኛው ምሥራቅ ወይንና ዘይት ቅንጦት አልነበሩም። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመናት እንጀራ፣ ዘይትና ወይን ለዕለታዊ ኑሮ የሚያስፈልጉ ነገሮች ነበሩ። (ከዘፍጥረት 14:18ና ከመዝሙር 104:14, 15 ጋር አወዳድር።) አብዛኛውን ጊዜ ጥሩ የመጠጥ ውኃ ስለማይገኝ ለመጠጥ የሚያገለግለው ወይን ጠጅ ነበር። በተጨማሪም ወይን ጠጅ በመድኃኒትነት ያገለግል ነበር። (1 ጢሞቴዎስ 5:23) በዘይት ረገድም ቢሆን በኤልያስ ዘመን በሰራፕታ የነበረችው መበለት በጣም የደኸየች ብትሆንም የቀራትን የመጨረሻ ዱቄት የምትጋግርበት ዘይት አላጣችም ነበር። (1 ነገሥት 17:12) ስለዚህ “ዘይትንና ወይንን አትጉዳ” የሚለው ትዕዛዝ እነዚህን ለሕይወት አስፈላጊ የሆኑ መሠረታዊ ነገሮች በቁጠባ መጠቀም እንደሚያስፈልግ የሚያስገነዝብ ምክር ነው። ሳይቆጥቡ ቢቀሩ ‘ይጎዳሉ’ ወይም የረሐቡ ጊዜ ከማለፉ በፊት ያልቅባቸዋል ማለት ነው።
24. ጥቁሩ ፈረስ ከእንግዲህ ወዲያ ለብዙ ጊዜ ግልቢያውን የማይቀጥለው ለምንድን ነው?
24 ከጥቂት ጊዜ በኋላ የነጩ ፈረስ ጋላቢ ይህን ጥቁር ፈረስ ለጉሞ እንደሚያቆመው በማወቃችን ምንኛ ልንደሰት እንችላለን! የነጩ ፈረስ ጋላቢ ለአዲሱ ዓለም ስላዘጋጀው የፍቅር ዝግጅት የተጻፈውን እንዲህ እናነባለን። “በዘመኑም ጽድቅ ያብባል፣ ጨረቃም እስኪያልፍ ድረስ ሰላም ብዙ ነው። . . . ፍሬውም ከሊባኖስ ይልቅ ከፍ ከፍ ይላል። እንደ ምድር ሣር በከተማ ይበቅላል።”—መዝሙር 72:7, 16፤ በተጨማሪም ኢሳይያስ 25:6-8 ተመልከት።
ግራጫው ፈረስና የፈረሱ ጋላቢ
25. ኢየሱስ አራተኛውን ማህተም በፈታ ጊዜ ዮሐንስ የማንን ድምፅ ሰማ? ይህስ ምን ያመለክታል?
25 ታሪኩ በዚህ ብቻ አላበቃም። ኢየሱስ አራተኛውን ማህተም ሲፈታ የሆነውን ነገር ዮሐንስ ይነግረናል። “አራተኛውንም ማኅተም በፈታ ጊዜ የአራተኛው እንስሳ ድምፅ መጥተህ እይ ሲል ሰማሁ።” (ራእይ 6:7) ይህ ድምፅ ንስር የሚመስለው ኪሩቤል ድምፅ ነው። እርሱም አርቆ ተመልካችነትንና ጥበብን ያመለክታል። በእውነትም ዮሐንስ፣ የዮሐንስ ክፍል አባሎችና ሌሎቹ በምድር የሚኖሩ የአምላክ አገልጋዮች በሙሉ ቀጥሎ በተገለጸው ሁኔታ ምክንያት በአስተዋይነት መመላለስ አስፈልጎአቸዋል። ይህን ካደረግን በዛሬው ጊዜ የሚገኙትን የዚህን ትዕቢተኛና ምግባረ ብልሹ ትውልድ ዓለማዊ ጠቢባን ከሚቀስፈው ቸነፈር ልንጠበቅ እንችላለን።—1 ቆሮንቶስ 1:20, 21
26. (ሀ) አራተኛው ፈረሰኛ ማን ነው? የፈረሱስ ቀለም ተስማሚ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) አራተኛውን ፈረሰኛ የተከተለው ማን ነው? የእርሱ ሰለባ ወይም ተጠቂ የሆኑ ሰዎችስ ምን ይሆናሉ?
26 አራተኛው ፈረሰኛ ለቀረበለት ጥሪ መልስ ሲሰጥ የታየው ምን ዓይነት አሰቃቂ ሁኔታ ነበር? ዮሐንስ ይነግረናል:- “እነሆ ግራጫ ፈረስ አየሁ፤ በፈረሱም ላይ የተቀመጠው ስሙ ሞት ይባል ነበር፤ ሲኦልም ይከተለው ነበር።” (ራእይ 6:8ሀ የ1980 ትርጉም) የመጨረሻው ፈረስ ጋላቢ ሞት የተባለ ስያሜ ተሰጥቶታል። ከአፖካሊፕስ ፈረሰኞች መካከል ማንነቱን በቀጥታ ያሳወቀው ይህ ፈረሰኛ ብቻ ነው። ሞት በግራጫ ፈረስ ላይ መጋለቡ የተገባ ነበር። ምክንያቱም ግራጫ የሚለው ቃል (ግሪክኛ ክሎሮስ) በግሪክኛ ሥነ ጽሑፍ ውስጥ በበሽታ የነጣና የገረጣ ፊት ያመለክታል። በተጨማሪም ከሞት በስተጀርባ ሔድስ (መቃብር) በግልጽ ባልተብራራ ሁኔታ መከተሉ ተገቢ ነው። ምክንያቱም በአራተኛው ፈረስ ከሚጨፈጨፉት ሰዎች መካከል አብዛኞቹን የሚረከበው ሔድስ ስለሆነ ነው። እነዚህ ሔድስ የሚቀበላቸው ሰዎች ‘ሞትና ሲኦል በውስጣቸው ያሉትን ሙታን በሚሰጡበት’ ጊዜ ከሙታን የሚነሡ መሆናቸው በጣም ያስደስታል። (ራእይ 20:13) ይሁን እንጂ ሞት እነዚህን ምርኮኞቹን የሚያጠምድባቸው ዘዴዎች ምንድን ናቸው?
27. (ሀ) ፈረሰኛው ሞት ሰለባዎቹን ወይም የገደላቸውን ሰዎች የሚሰበስበው እንዴት ነው? (ለ) ሞት የሚሰለጥንበት የምድሪቱ አራተኛ ክፍል ምን ማለት ነው?
27 ራእዩ ከዘዴዎቹ አንዳንዶቹን ይዘረዝርልናል:- “በሰይፍና በራብም በሞትም በምድርም አራዊት ይገድሉ ዘንድ ከምድር በአራተኛዋ እጅ ላይ ሥልጣን ተሰጣቸው።” (ራእይ 6:8ለ) በዚህ ፈረስ ግልቢያ የሚነኩት ቃል በቃል ከዓለም ሕዝቦች ውስጥ አንድ አራተኛ የሆኑት ላይሆኑ ቢችሉም ብዙ ሰዎች የሚኖሩባቸውም ሆኑ ጥቂት ሰዎች የሚኖሩባቸው የምድር ክፍሎች በአብዛኛው ይነካሉ። ይህ ፈረሰኛ በሁለተኛው ፈረሰኛ ትልቅ ሠይፍ የተመቱትንና በሦስተኛው ፈረሰኛ ችጋርና ረሐብ የተጎዱትን ሰዎች ሰብስቦ ያከማቻል። በተጨማሪም በሉቃስ 21:10, 11 ላይ እንደተገለጸው በቀሳፊ ቸነፈሮችና በምድር መናወጦች የታጨዱትን ሰዎች ይሰበስባል።
28. (ሀ) ስለ ቀሳፊ ወይም “ገዳይ ቸነፈር” የተነገረው ትንቢት የተፈጸመው እንዴት ነው? (ለ) የይሖዋ ሕዝቦች በጊዜያችን ካሉ ከብዙ በሽታዎች የተጠበቁት እንዴት ነው?
28 አሁን ይበልጥ ትኩረታችንን የሚስበው ‘ገዳይ የሆነው ቸነፈር’ ነው። ከመጀመሪያው የዓለም ጦርነት እልቂት በኋላ ከ1918 እስከ 1919 በነበሩት ጥቂት ወራት ብቻ ስፓኒሽ ፍሉ ወይም የህዳር በሽታ የተባለው ቸነፈር ከ20 ሚልዮን በላይ ሰዎችን አጭዶአል። በምድር ገጽ ላይ ከዚህ ቸነፈር ያመለጠችው ሴይንት ሔሌና የተባለች አነስተኛ ደሴት ብቻ ነበረች። ብዙ ሰዎች በሞቱባቸው አካባቢዎች የሞቱትን ሰዎች አስከሬን መቅበር ስላልተቻለ አንድ ላይ ከምሮ ማቃጠል ግድ ሆኖአል። ዛሬም ቢሆን በአብዛኛው በትንባሆ ጭስ ምክንያት የሚመጣው የልብ በሽታና ካንሰር በአስደንጋጭ ሁኔታ እየተባዛ ሄዶአል። “አስቀያሚ አሥርተ ዓመት” ተብለው በተገለጹት የ1980ዎቹ ዓመታት ከመጽሐፍ ቅዱስ ሕግጋት አንፃር ሲታይ ሕገወጥ በሆነው አኗኗር ምክንያት የኤድስ ‘ገዳይ ቸነፈር’ ወይም መቅሠፍት ተጨማሪ እልቂት የሚያስከትል ቸነፈር ሆኖአል። የዩናይትድ ስቴትስ የጤና ጥበቃ አገልግሎት ከፍተኛ ባለ ሥልጣን በ2000 ስለ ኤድስ ሲናገሩ “በዓለም ላይ እስከ ዛሬ ከተከሰቱት ወረርሽኞች ሁሉ የከፋ ሳይሆን አይቀርም” ብለው እንደገለጹት ሪፖርት ተደርጓል። እኚህ ሰው በዓለም ዙሪያ 52 ሚልዮን ሰዎች በኤች አይ ቪ/ኤድስ እንደተያዙና ከእነዚህም ውስጥ 20 ሚልዮን የሚሆኑት እንደሞቱ ተናግረዋል። የይሖዋ ሕዝቦች ከቃሉ በሚያገኙት የጥበብ ምክር ምክንያት በዛሬው ጊዜ የብዙ በሽታዎች መተላለፊያ ምክንያት ከሆኑት ከምንዝርና ደም ከመውሰድ ስለሚጠበቁ ምን ያህል አመስጋኞች ናቸው!—ሥራ 15:28, 29፤ ከ1 ቆሮንቶስ 6:9-11 ጋር አወዳድር።
29, 30. (ሀ) በሕዝቅኤል 14:21 ላይ የተገለጹት አራት መቅሰፍቶች በዘመናችን የተፈጸሙት እንዴት ነው? (ለ) በራእይ 6:8 ላይ የተገለጹት “አራዊት” ምን ሊሆኑ ይችላሉ? (ሐ) የትንቢታዊው ትርዒት ዋነኛ ትርጉም ምን ሊሆን ይችላል?
29 በተጨማሪም የዮሐንስ ራእይ ሰዎች ሕይወታቸው በአጭሩ እንዲቀጭ ከሚያደርጉባቸው ምክንያቶች አራተኛው የዱር አራዊት እንደሆኑ የዮሐንስ ራእይ ይናገራል። እርግጥ፣ በጥንት ዘመንም ቢሆን ዋነኞቹ አለጊዜ የመሞት ምክንያቶች አራተኛው ማህተም በተፈታ ጊዜ የታዩት ጦርነት፣ ረሐብ፣ በሽታና የዱር አራዊት ናቸው። ስለዚህ እነዚህ ነገሮች ሁሉ በአሁኑ ጊዜ አለጊዜው ለሚመጣ ሞት ምክንያት የሆኑትን ነገሮች ሁሉ ሊወክሉ ይችላሉ። ይህም ይሖዋ እሥራኤላውያንን እንዳስጠነቀቀው ነው። “ሰውንና እንስሳን ከእርስዋ አጠፋ ዘንድ በኢየሩሳሌም ላይ አራቱን ክፉ ፍርዶቼን ሰይፍንና ራብን ክፉዎችንም አውሬዎች ቸነፈርንም” እሰድባቸዋለሁ።—ሕዝቅኤል 14:21
30 ትላልቅ ደኖች በሚገኙባቸው አገሮች አልፎ አልፎ በዱር አራዊት የተገደሉ ብዙ ሰዎች ቢኖሩም በዱር አራዊት መገደል እምብዛም የጋዜጦች ዓምድ አልሆነም። ምናልባት ወደ ፊት ብዙ አካባቢዎች በጦርነቶች ምክንያት ሰው አልባ እየሆኑ ከሄዱና በረሐብ ምክንያት ጠውልገው የተራቡና አራዊትን ለመከላከል የማይችሉ ሰዎች እየበዙ ከሄዱ ብዙ ሰዎች በአራዊት ሊበሉ ይችሉ ይሆናል። ከዚህም በተጨማሪ የማሰብ ችሎታ እንደሌላቸው እንስሳት በኢሳይያስ 11:6-9 ላይ ከተገለጸው ተቃራኒ የሆነ የአውሬነት ባሕርይ የሚታይባቸው ብዙ ሰዎች አሉ። በአሁኑ ጊዜ በዓለም በሙሉ የሚታዩትን ከፆታ ግንኙነት ጋር ዝምድና ያላቸው ወንጀሎች፣ ነፍስ ግድያ፣ አሸባሪነትና የቦምብ ጥቃት ወንጀል በመፈጸማቸው በአብዛኛው ተጠያቂ የሚሆኑት እነዚህ ሰዎች ናቸው። (ከሕዝቅኤል 21:31፤ ከሮሜ 1:28-31ና ከ2 ጴጥሮስ 2:12 ጋር አወዳድር።) አራተኛው ፈረሰኛ የእነዚህንም ግዳዮች ይሰበስባል። የዚህ ትንቢታዊ ትዕይንት ዋነኛ መልእክት የግራጫው ፈረስ ጋላቢ በተለያዩ ምክንያቶች አለጊዜያቸው የሚሞቱትን የሰው ልጆች መሰብሰቡ ነው።
31. የቀዩ፣ የጥቁሩና የግራጫው ፈረስ ጋላቢዎች ብዙ ጥፋት ቢያስከትሉም ተስፋ የመቁረጥ ስሜት ሊሰማን የማይገባው ለምንድን ነው?
31 በመጀመሪያዎቹ አራት ማህተሞች መከፈት ያገኘነው መረጃ በዛሬው ጊዜ ተስፋፍቶ በሚገኘው ጦርነት፣ ረሐብ፣ በሽታና ሰዎችን በአጭሩ በሚቀጩ ሌሎች ምክንያቶች እንዳንሸበር ድፍረትና ትምክህት ይሰጠናል። ሰብዓዊ መሪዎች እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ባለመቻላቸው ተስፋ መቁረጥ አይገባንም። የቀዩ፣ የጥቁሩና የግራጫው ፈረስ ጋላቢዎች መኖራቸውን የሚያረጋግጡ የዓለም ሁኔታዎችን ብንመለከትም ከሁሉም አስቀድሞ መጋለብ የጀመረው የነጩ ፈረስ ባለቤት እንደሆነ መዘንጋት አይገባንም። ኢየሱስ ነግሦአል። እስከ አሁን ድረስም ሰይጣንን ከሰማይ አሽቀንጥሮ እስከ መጣል ድረስ ድል ነስቶአል። ከዚህም በላይ ከመንፈሳዊ እሥራኤል ልጆች የቀሩትንና በሚልዮን የሚቆጠሩትን ከዓለም በሙሉ የተውጣጡ እጅግ ብዙ ሰዎች ስለሰበሰበ ተጨማሪ ድል አግኝቶአል። (ራእይ 7:4, 9, 14) ግልቢያው አጠቃላይ ድል እስከሚያገኝበት ጊዜ ድረስ መቀጠል ይኖርበታል።
32. የመጀመሪያዎቹ አራት ማህተሞች በተፈቱበት ጊዜ ሁሉ ምን ተደርጎ ነበር?
32 እያንዳንዱ ማህተም ከተፈታ በኋላ “ና” የሚል ትዕዛዝ ተሰጥቶአል። ትዕዛዝ በተሰጠበት በእያንዳንዱ ጊዜም ፈረሶች ከነጋላቢዎቻቸው ሲወጡ ታይተዋል። ከአምስተኛው ማህተም ጀምሮ ግን “ና” የሚለውን ጥሪ አንሰማም። ቢሆንም እነዚህ ፈረሰኞች ግልቢያቸውን ገና አላቆሙም። ይህ ሥርዓት እስከሚጠፋበት ጊዜ ድረስ ይጋልባሉ። (ከማቴዎስ 28:20 ጋር አወዳድር።) ኢየሱስ የቀሩትን ሦስት ማኅተሞች ሲፈታ ምን ታላላቅ ሁኔታዎችን ይገልጽልን ይሆን? አንዳንዶቹ ነገሮች ለሰብዓዊ ዓይን ሊታዩ የሚችሉ አይደሉም። ሌሎቹ ደግሞ በዓይን ሊታዩ ቢችሉም ገና ወደ ፊት የሚፈጸሙ ናቸው። ይሁን እንጂ መፈጸማቸው የማይቀር ነው። እስቲ ምን እንደሆኑ እንመልከት።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
b ኢየሱስ በ1914 ወደ መንግሥቱ እንደመጣ ተጨማሪ ማስረጃ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ገጽ 215-218 ተመልከት።
c ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች (ሪቫይዝድ ስታንዳርድ፣ ዘ ኒው ኢንግሊሽ ባይብል፣ ኪንግ ጀምስ ቨርሽን ) ይህን ሐረግ “ድል መንሳት” ወይም (ፊሊፕስ፣ ኒው ኢንተርናሽናል ቨርሽን ) “ድል ለመንሳት መዘጋጀት” ብለው ቢተረጉሙም እዚህ ላይ የተጠቀሰው የግሪክኛ ቃል የፍጻሜ ወይም የመደምደሚያ እርምጃ መሆኑን የሚያመለክት ባሕርይ አለው። በዚህም ምክንያት ወርድ ፒክቸርስ ኢን ዘ ኒው ቴስታመንት የተባለው የሮበርትሰን መጽሐፍ “የግሱ ሰዋስዋዊ አገባብ በመጨረሻው ድል ማግኘቱን ያመለክታል” ብሎአል።
d ባለ ማጣቀሻውን አዲሲቱ ዓለም የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ ተመልከት።
[በገጽ 92 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ንጉሡ በድል አድራጊነት ይጋልባል
በ1930ዎቹና በ1940ዎቹ ዓመታት፣ የይሖዋ ምሥክሮችን ለማጥፋት ቆርጠው የተነሱ ጠላቶች አገልግሎታቸው ሕጋዊ እንዳልሆነ፣ ወንጀል ወይም የመንግሥትን አቋም የሚያናጋ እንደሆነ ለማስመሰል ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል። (መዝሙር 94:20) በ1936 ብቻ በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ 1,149 የይሖዋ ምሥክሮች ታስረው ነበር። የይሖዋ ምሥክሮች ከፍተኛ የፍርድ ቤት ተጋድሎ በማድረግ እስከ ዩናይትድ ስቴትስ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ደርሰዋል። ካገኙአቸው ድሎች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል:-
ግንቦት 3 ቀን 1943 ጠቅላይ ፍርድ ቤት በከሳሽ መርዶክና በተከሳሽ ፔንስልቫንያ ጉዳይ በሰጠው ውሳኔ የይሖዋ ምሥክሮች ጽሑፎችን ለሰዎች ለመስጠትና ለጽሐፎቹም ገንዘብ ለመቀበል ፈቃድ ማውጣት እንደማያስፈልጋቸው በይኖአል። በዚያው ቀን በከሳሽ ማርቲንና በተከሳሽ ስትራዘርስ ከተማ ጉዳይ በሰጠው ውሳኔ የግብዣ ወረቀቶችንና ሌሎች የማስታወቂያ ጽሑፎችን ለማደል ከቤት ወደ ቤት መሄድና የሰዎችን በር ማንኳኳት ወይም ደወል መደወል ሕገወጥ ድርጊት እንዳልሆነ በይኖአል።
ሰኔ 14 ቀን 1943 ጠቅላይ ፍርድ ቤት በከሳሽ ቴይለርና በተከሳሽ ሚሲሲፒ ጉዳይ የይሖዋ ምሥክሮች በስብከታቸው ሰዎች ለመንግሥት ታማኞች እንዳይሆኑ እንደማያደፋፍሩ ወስኖአል። በዚሁ ቀን በከሳሽ የምዕራብ ቨርጂንያ የትምህርት ቦርድና በተከሳሽ ባርኔት ጉዳይ ማንኛውም የትምህርት ቤት ቦርድ የይሖዋ ምሥክሮችን ልጆች ለሰንደቅ ዓለማ ሰላምታ ስላልሰጡ ከትምህርት ቤት ሊያስወጣ እንደማይችል ወስኖአል። በማግስቱ ደግሞ የአውስትራሊያ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በይሖዋ ምሥክሮች ላይ የተጣለው እገዳ “ምክንያተ ቢስ፣ በግብታዊነት የተደረገና ጨቋኝ ነው” በማለት እገዳውን አንስቶአል።
[በገጽ 94 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
“ከምድር ላይ ሰላምን እንዲወስድ ተሰጠው”
ቴክኖሎጂ የሰው ልጆችን ወዴት እየመራቸው ነው? ዘ ግሎብ ኤንድ ሜይል የተባለው የቶሮንቶ ካናዳ መጽሔት ጥር 22 ቀን 1987 የዓለም አቀፍ ልማት ጥናት ማዕከል ፕሬዚደንት የሆኑትን የኢቫን ኤል ሄድን ንግግር አትሞ አውጥቶ ነበር። ከዚህም ውስጥ የሚከተለው ይገኝበታል:-
“በዓለም ውስጥ ከአራት የሳይንስና የቴክኖሎጂ ሊቃውንት መካከል አንዱ የጦር መሣሪያዎችን በመፈልሰፍና በማሻሻል ሥራ የተሠማራ ነው። . . . በ1986 ለዚህ ሥራ የዋለው ጠቅላላ ወጪ በደቂቃ 1.5 ሚልዮን ዶላር ነበር። . . . ለዚህ ዓይነቱ ቴክኖሎጂ ትልቅ ትኩረት በመደረጉ ምክንያት ደህንነታችን ይበልጥ አስተማማኝ ሆኗልን? ልዕለ ኃያላን ያላቸው የኑክሌር መሣሪያ ብዛት በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ዓመታት በሙሉ በጦርነቱ የተካፈሉት አገሮች በሙሉ ከተጠቀሙባቸው መሣሪያዎች 6,000 ጊዜ እጥፍ ይሆናል። ሁለተኛውን የዓለም ጦርነት የሚያክሉ ስድስት ሺህ ጦርነቶችን ሊያዋጋ ይችላል ማለት ነው። ከ1945 ጀምሮ ዓለም ከወታደራዊ እንቅስቃሴዎች ያረፈችው ከሰባት ሳምንታት ለሚያንስ ጊዜ ብቻ ነው። ከ150 የሚበልጡ የእርስ በርስ ወይም የአገር አቀፍ ጦርነቶች ተደርገዋል። እነዚህም ጦርነቶች የ19.3 ሚልዮን ሰዎችን ሕይወት ቀስፈዋል። አብዛኞቹ ሰዎች የሞቱት በዚህ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባለበት አዲስ ዘመን ውስጥ በተፈለሰፉት የአዳዲስ ቴክኖሎጂ ውጤቶች ነው።”
በ2005 በወታደራዊ እንቅስቃሴ ሳቢያ ከ20 ሚልዮን የሚበልጡ ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።
[በገጽ 98, 99 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የራእይ መጽሐፍ አደረጃጀት
በራእይ መጽሐፍ ላይ ባደረግነው ውይይት እስከዚህ ደረጃ ከደረስን የራእይን መጽሐፍ አደረጃጀት ይበልጥ በግልጽ ለመመልከት እንችላለን። ቀስቃሽ ከሆነው መግቢያ ጀምሮ (ራእይ 1:1-9) በ16 ራእዮች የተደራጀ እንደሆነ ከሚከተለው ለመረዳት ይቻላል:-
1ኛ ራእይ (1:10 እስከ 3:22):- ዮሐንስ ለሰባቱ ጉባኤዎች ሞቅ ያለ ምክር አዘል መልእክት የላከላቸውን ክብር የተቀዳጀውን ኢየሱስን በመንፈስ ተመለከተ።
2ኛ ራእይ (4:1 እስከ 5:14):- የይሖዋን ሰማያዊ ዙፋን የሚያሳይ ታላቅ ግርማ ያለው ራእይ። እርሱም ለበጉ የመጽሐፍ ጥቅልል ሰጠው።
3ኛ ራእይ (6:1-17):- በጉ የጥቅልሉን የመጀመሪያ ስድስት ማህተሞች እየከፈተ ደረጃ በደረጃ በጌታ ቀን ውስጥ የሚፈጸሙትን ነገሮች የሚገልጽ ራእይ አሳየ። አራቱ የአፖካሊፕስ ፈረሰኞች ግልቢያቸውን ቀጥለዋል፣ ሰማዕታን ሆነው የሞቱት የአምላክ ባሮች ነጭ ልብስ ተቀብለዋል። ታላቁም የቁጣ ቀን ተገልጾአል።
4ኛ ራእይ (7:1-17):- 144,000ዎቹ መንፈሳዊ እሥራኤላውያን ታትመው እስኪያልቁ ድረስ መላእክት የጥፋቱን ነፋስ አግደው ያዙ። ከብሔራት ሁሉ የተውጣጡ እጅግ ብዙ ሰዎች ማዳን የአምላክና የክርስቶስ መሆኑን ገለጹ። ከታላቁ መከራ በሕይወት ተጠብቀው እንዲያልፉም ተሰበሰቡ።
5ኛ ራእይ (8:1 እስከ 9:21):- ሰባተኛው ማህተም ሲፈታ ሰባት መለከቶች ተነፉ። የመጀመሪያዎቹ ስድስት መለከቶች የአምስተኛው ራእይ ክፍል ናቸው። እነዚህ ስድስት መለከቶች ይሖዋ በሰው ልጆች ላይ ያስተላለፈውን ፍርድ የሚያስታውቁ ናቸው። በተጨማሪም አምስተኛውና ስድስተኛው መለከት የመጀመሪያውንና ሁለተኛውን ወዮታ ያስተዋውቃል።
6ኛ ራእይ (10:1 እስከ 11:19):- አንድ ብርቱ መልአክ ለዮሐንስ አንድ ትንሽ የመጽሐፍ ጥቅልል ሰጠው። ቤተ መቅደሱ ተለካ። ሁለቱ ምሥክሮች ያጋጠማቸውንም ነገር እንመለከታለን። በአምላክ ጠላቶች ላይ የሚመጣ ሦስተኛ ወዮታ የሆነውን የይሖዋንና የክርስቶስን መንግሥት የሚያስተዋውቀው ሰባተኛውና የመጨረሻው መለከት በሚነፋበት ጊዜ መጨረሻ ደረጃ ላይ ይደርሳል።
7ኛ ራእይ (12:1-17):- ይህ ራእይ ሚካኤል እባቡን ሰይጣን ወደ ምድር እንዲወረውር ስላደረገው ስለ መንግሥቱ መወለድ ይገልጻል።
8ኛ ራእይ (13:1-18):- ኃይለኛው አውሬ ከባሕር ወጣ። ሁለት ቀንድ ያለው በግ የሚመስል አውሬ የሰው ልጆች በሙሉ ይህን አውሬ እንዲያመልኩት ጠየቀ።
9ኛ ራእይ (14:1-20):- 144,000ዎቹ በጽዮን ተራራ ላይ ሆነው የሚያሳይ አስደናቂ ራእይ። የመላእክት መልእክት በምድር በሙሉ ተሰማ። የምድር ወይን በሙሉ ተመረተ። የአምላክም የቁጣ ወይን መጭመቂያ ተረገጠ።
10ኛ ራእይ (15:1 እስከ 16:21):- ሰማያዊው ዙፋን በድጋሚ ከታየ በኋላ ሰባቱ የይሖዋ የቁጣ ጽዋዎች በምድር ላይ ፈሰሱ። ይህም ክፍል የተፈጸመው የሰይጣን ሥርዓት እንዴት እንደሚጠፋ በትንቢታዊ ሁኔታ በመግለጽ ነው።
11ኛ ራእይ (17:1-18):- ታላቂቱ ጋለሞታ፣ ታላቂቱ ባቢሎን በአንድ ቀይ አውሬ ላይ ትጋልባለች። ይህም አውሬ ለጥቂት ጊዜ ጥልቅ ውስጥ ገብቶ ከቆየ በኋላ ይወጣና ያጠፋታል።
12ኛ ራእይ (18:1 እስከ 19:10):- የታላቂቱ ባቢሎን ውድቀትና የመጨረሻ ጥፋት ተነገረ። ታላቂቱ ባቢሎን ከጠፋች በኋላ አንዳንዶች ሲያለቅሱላት ሌሎች ደግሞ ይሖዋን አወደሱ። የበጉ ሠርግ እንደ ደረሰም ማስታወቂያ ተነገረ።
13ኛ ራእይ (19:11-21):- ኢየሱስ የአምላክን የቁጣ ፍርድ በሰይጣን ሥርዓት ላይ፣ በሠራዊቶቹና በደጋፊዎቻቸው ላይ ለማውረድ የሰማይን ሠራዊት ይመራል። ሬሣቸውንም የምድር አእዋፍ ይበላሉ።
14ኛ ራእይ (20:1-10):- የሰይጣን ዲያብሎስ ጥልቅ ውስጥ መታሰር፣ የክርስቶስና የነገሥታት ባልንጀሮቹ የሺህ ዓመት ግዛት፣ የሰው ልጅ የመጨረሻ ፈተና፣ የሰይጣንና የአጋንንቱ መጥፋት።
15ኛ ራእይ (20:11 እስከ 21:8):- አጠቃላይ ትንሣኤና ታላቁ የፍርድ ቀን፣ አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር ታዩ፣ ጻድቅ ለሆኑ የሰው ልጆችም የዘላለም በረከት ወረደላቸው።
16ኛ ራእይ (21:9 እስከ 22:5):- የራእይ መጽሐፍ የሚደመደመው ታላቅ ግርማ ባለው የአዲሲቱ ኢየሩሳሌም፣ የበጉ ሚስት ራእይ ነው። የአምላክ የፈውስና የሕይወት ዝግጅት የሚፈሰው ከዚህች ከተማ ነው።
የራእይ መጽሐፍ ከይሖዋ፣ ከኢየሱስ፣ ከመልአኩና ከዮሐንስ ከራሱ የተላለፈውን ሞቅ ያለ የሰላምታና የምክር ቃል በማቅረብ ይጠቃለላል። ለሰው ሁሉ የቀረበው ግብዣ “ና” የሚል ነው።—ራእይ 22:6-21