ምዕራፍ 16
ዲያብሎስንና መሠሪ ዘዴዎቹን ተቃወም
‘ዲያብሎስን ተቃወሙት፤ እሱም ከእናንተ ይሸሻል።—ያዕቆብ 4:7
1, 2. የጥምቀት ሥነ ሥርዓቶች የሚከናወኑባቸው ወቅቶች አስደሳች የሚሆኑት ለእነማን ነው?
ለብዙ ዓመታት ይሖዋን ስታገለግል የቆየህ ክርስቲያን ከሆንክ በትልልቅ ስብሰባዎቻችን ላይ በርካታ የጥምቀት ንግግሮችን እንደሰማህ ጥርጥር የለውም። እንደነዚህ ባሉት አጋጣሚዎች ላይ ብዙ ጊዜ የተገኘህ ብትሆንም እንኳ በፊተኞቹ ወንበሮች ላይ የተቀመጡት ሰዎች ራሳቸውን ለጥምቀት ለማቅረብ ከመቀመጫቸው ሲነሱ ማየትህ በውስጥህ ልዩ ስሜት ይፈጥርብሃል። በዚህ ወቅት በቦታው የተገኙት በሙሉ በደስታ ስሜት የሚዋጡ ሲሆን መሰብሰቢያው ከዳር እስከ ዳር በጭብጨባ ያስተጋባል። ከይሖዋ ጎን ለመሰለፍ የወሰኑ ሌሎች ሰዎች በማየትህ ዓይንህ የደስታ እንባ ሊያቀር ይችላል። እንዲህ ባሉት ወቅቶች የሚሰማን ደስታ በእርግጥም ከፍተኛ ነው!
2 በአካባቢያችን የጥምቀት ሥነ ሥርዓት ሲከናወን የማየት አጋጣሚ የምናገኘው በዓመቱ ውስጥ ጥቂት ጊዜ ብቻ ነው። መላእክት ግን በጣም ብዙ የጥምቀት ሥነ ሥርዓቶች ሲከናወኑ የማየት አጋጣሚ አላቸው። በዓለም ዙሪያ በብዙ ሺህዎች የሚቆጠሩ ግለሰቦች በየሳምንቱ ወደ ይሖዋ ድርጅት መቀላቀላቸው “በሰማይ” ምን ያህል “ታላቅ ደስታ” እንደሚፈጥር መገመት ትችላለህ? (ሉቃስ 15:7, 10) መላእክት በይሖዋ ድርጅት ምድራዊ ክፍል ውስጥ የሚታየውን እድገት ሲመለከቱ በደስታ እንደሚፈነድቁ አያጠራጥርም።—ሐጌ 2:7
ዲያብሎስ “እንደሚያገሳ አንበሳ ይንጎራደዳል”
3. ሰይጣን ‘እንደሚያገሳ አንበሳ የሚንጎራደደው’ ለምንድን ነው? ፍላጎቱስ ምንድን ነው?
3 በአንጻሩ ግን እነዚህን የጥምቀት ሥነ ሥርዓቶች ማየት በጣም የሚያስቆጣቸው መንፈሳዊ ፍጥረታት አሉ። ሰይጣንና አጋንንቱ በሺህ የሚቆጠሩ ግለሰቦች ለዚህ ብልሹ ዓለም ጀርባቸውን ሲሰጡ ማየት ያበሳጫቸዋል። እንደዚህ የሚሰማቸው መሆኑ አያስገርምም። ምክንያቱም ሰይጣን፣ በእውነተኛ ፍቅር ተነሳስቶ ይሖዋን የሚያገለግል አንድም ሰው አይኖርም እንዲሁም ሰዎች ከባድ ፈተና ቢደርስባቸው በታማኝነት አይጸኑም በማለት ፎክሯል። (ኢዮብ 2:4, 5) ራሱን ለይሖዋ በመወሰን እርምጃ የሚወስድ አንድ ሰው በተገኘ ቁጥር ሰይጣን ውሸታም መሆኑ ይረጋገጣል። ሰይጣን በየሳምንቱ በሺህ ለሚቆጠር ጊዜ በጥፊ የተመታ ያህል ነው። ዲያብሎስ ‘የሚውጠውን በመፈለግ እንደሚያገሳ አንበሳ የሚንጎራደድ’ መሆኑ አያስደንቅም። (1 ጴጥሮስ 5:8) ይህ “አንበሳ” በመንፈሳዊ ሊውጠንና ከአምላክ ጋር ያለንን ዝምድና ሊያሻክርብን ወይም ጨርሶ ሊያበላሽብን ይፈልጋል።—መዝሙር 7:1, 2፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:12
አንድ ሰው ራሱን ለይሖዋ ወስኖ በተጠመቀ ቁጥር ሰይጣን ሐሰተኛ መሆኑ ይረጋገጣል
4, 5. (ሀ) ይሖዋ የሰይጣንን ኃይል የገደበው በምን ሁለት መንገዶች ነው? (ለ) አንድ እውነተኛ ክርስቲያን ስለ ምን ነገር እርግጠኛ መሆን ይችላል?
4 ጠላታችን በጣም ጨካኝ ቢሆንም እንኳ በፍርሃት የምንርድበት ምክንያት የለም። ለምን? ምክንያቱም ይሖዋ የዚህን ‘የሚያገሳ አንበሳ’ አቅም በሁለት መንገዶች ገድቦበታል። እነዚህ መንገዶች ምንድን ናቸው? አንደኛ፣ ይሖዋ እውነተኛ ክርስቲያኖች የሆኑት ‘እጅግ ብዙ ሕዝቦች’ ከመጪው ‘ታላቅ መከራ’ በሕይወት እንደሚተርፉ ተንብዮአል። (ራእይ 7:9, 14) አምላክ የተናገራቸው ትንቢቶች ሳይፈጸሙ አይቀሩም። ስለሆነም የአምላክን ሕዝቦች በቡድን ደረጃ ማጥፋት እንደማይችል ሰይጣን ራሱ ያውቀዋል።
5 ይሖዋ የሰይጣንን አቅም የገደበበትን ሁለተኛውን መንገድ በጥንት ጊዜ የኖረ አንድ የአምላክ ታማኝ አገልጋይ ከተናገረው መሠረታዊ እውነት መገንዘብ ይቻላል። ነቢዩ አዛርያስ ለንጉሥ አሳ ‘እናንተ ከይሖዋ ጋር ስትሆኑ፣ እሱም ከእናንተ ጋር ይሆናል’ ብሎት ነበር። (2 ዜና መዋዕል 15:2፤ 1 ቆሮንቶስ 10:13) በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመዘገቡ በርካታ ምሳሌዎች እንደሚያሳዩት፣ ባለፉት ዘመናት ሰይጣን ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ዝምድና የመሠረቱ የአምላክ አገልጋዮችን ለመዋጥ ፈልጎ አንድም ጊዜ አልተሳካለትም። (ዕብራውያን 11:4-40) በዛሬው ጊዜም ከአምላክ ጋር የጠበቀ ዝምድና ያለው አንድ ክርስቲያን ዲያብሎስን መቃወም አልፎ ተርፎም ድል መንሳት ይችላል። እንዲያውም የአምላክ ቃል ‘ዲያብሎስን ተቃወሙት፤ እሱም ከእናንተ ይሸሻል’ የሚል ዋስትና ይሰጠናል።—ያዕቆብ 4:7
“ትግል የምንገጥመው . . . ከክፉ መንፈሳዊ ኃይሎች ጋር ነው”
6. ሰይጣን ክርስቲያኖችን በግለሰብ ደረጃ የሚዋጋው እንዴት ነው?
6 ሰይጣን በጦርነቱ ድል አድራጊ ሊሆን አይችልም። ይሁን እንጂ ከተዘናጋን በግለሰብ ደረጃ የጦርነቱ ሰለባ ሊያደርገን ይችላል። ከይሖዋ ጋር ያለንን ዝምድና ማዳከም ከቻለ በቀላሉ ሊውጠን እንደሚችል ያውቃል። ሰይጣን ይህን ለማድረግ የሚሞክረው እንዴት ነው? የተፋፋመ ጥቃት በመሰንዘር፣ በግለሰብ ደረጃ በማጥቃት እንዲሁም መሠሪ ዘዴ በመጠቀም ነው። እስቲ እነዚህን ዋና ዋና የሰይጣን ዘዴዎች እንመልከት።
7. ሰይጣን በይሖዋ ሕዝቦች ላይ የሚሰነዝረውን ጥቃት ያፋፋመው ለምንድን ነው?
7 የተፋፋመ ጥቃት። ሐዋርያው ዮሐንስ ‘መላው ዓለም በክፉው ኃይል ሥር ነው’ ብሏል። (1 ዮሐንስ 5:19) እነዚህ ቃላት ለሁሉም እውነተኛ ክርስቲያኖች ማስጠንቀቂያ ይዘዋል። ሰይጣን መላውን አምላክ የለሽ ዓለም በቁጥጥሩ ሥር በማድረግ ረገድ ስለተሳካለት፣ በአሁኑ ጊዜ ትኩረቱን መዳፉ ውስጥ ባልገቡት የይሖዋ ሕዝቦች ላይ በማድረግ በእነሱ ላይ የሚያደርሰውን ጥቃት አፋፍሟል። (ሚክያስ 4:1፤ ዮሐንስ 15:19፤ ራእይ 12:12, 17) የቀረው ጊዜ አጭር እንደሆነ ስለሚያውቅ በጣም ተቆጥቷል። ስለሆነም ከበፊቱ በበለጠ ጥቃቱን አፋፍሟል። ከአምላክ ጋር የመሠረትነውን ዝምድና ለማበላሸት በዛሬው ጊዜ ጭካኔ የሞላበት የመጨረሻ ጥቃት በመሰንዘር ላይ ይገኛል። በመሆኑም ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ዛሬ ‘ዘመኑን መረዳትና ምን ማድረግ እንደሚገባን መገንዘብ’ ያስፈልገናል።—1 ዜና መዋዕል 12:32
8. ሐዋርያው ጳውሎስ ከክፉ መናፍስት ጋር “ትግል” አለብን ሲል ምን ማለቱ ነበር?
8 በግለሰብ ደረጃ የሚደረግ ትግል። ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቲያን ባልንጀሮቹን “ትግል የምንገጥመው . . . በሰማያዊ ስፍራዎች ካሉ ከክፉ መንፈሳዊ ኃይሎች ጋር ነው” ሲል አስጠንቅቆ ነበር። (ኤፌሶን 6:12) እዚህ ላይ ጳውሎስ “ትግል” የሚለውን ቃል የተጠቀመው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ቃሉ ቅርብ ለቅርብ ሆኖ አንድ ለአንድ የሚደረግን ግብግብ ስለሚያመለክት ነው። ጳውሎስ ይህን ቃል በመጠቀም እያንዳንዳችን ከክፉ መናፍስት ጋር በግለሰብ ደረጃ ትግል እንደገጠምን አበክሮ ገልጿል። የምንኖረው የክፉ መናፍስት እምነት በተስፋፋበት አካባቢ ሆነም አልሆነ ሕይወታችንን ለይሖዋ በወሰንበት ጊዜ በምሳሌያዊ ሁኔታ ትግል እንደጀመርን ፈጽሞ መዘንጋት አይኖርብንም። እያንዳንዱ ክርስቲያን ራሱን ከወሰነበት ጊዜ አንስቶ በውጊያ ውስጥ ነው። በዚህም ምክንያት ሐዋርያው ጳውሎስ በኤፌሶን የነበሩት ክርስቲያኖች የዲያብሎስን መሠሪ ዘዴዎች ‘እንዲቋቋሙ’ ደጋግሞ ማሳሰብ አስፈላጊ እንደሆነ ተሰምቶታል።—ኤፌሶን 6:11, 13, 14
9. (ሀ) ሰይጣንና አጋንንት የተለያዩ “መሠሪ ዘዴዎች” የሚጠቀሙት ለምንድን ነው? (ለ) ሰይጣን አስተሳሰባችንን ለመበከል የሚሞክረው ለምንድን ነው? ጥረቱ እንዳይሳካ ማድረግ የምንችለውስ እንዴት ነው? (“በሰይጣን መሠሪ ዘዴዎች እንዳትታለል ተጠንቀቅ!” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) (ሐ) አሁን የትኛውን መሠሪ ዘዴ እንመረምራለን?
9 መሠሪ ዘዴዎች። ጳውሎስ ክርስቲያኖች የዲያብሎስን “መሠሪ ዘዴዎች” እንዲቋቋሙ አሳስቧል። (ኤፌሶን 6:11) ጳውሎስ “ዘዴዎች” በማለት ብዙ ቁጥር እንደተጠቀመ ልብ በል። ክፉ መናፍስት አንድ ዘዴ ብቻ ሳይሆን የተለያዩ ዘዴዎችን ይጠቀማሉ። ይህንንም የሚያደርጉበት በቂ ምክንያት አላቸው። አንድን ዓይነት ፈተና ተቋቁመው ያለፉ አንዳንድ ክርስቲያኖች ሌላ ዓይነት ፈተና ሲያጋጥማቸው ተሸንፈዋል። በመሆኑም ዲያብሎስና አጋንንቱ ደካማ ጎናችን ምን እንደሆነ ለማወቅ የእያንዳንዳችንን ጠባይ በቅርብ ይከታተላሉ። ከዚያም ያለንን መንፈሳዊ ድክመት እኛን ለማጥቃት ይጠቀሙበታል። ደስ የሚለው ግን ብዙዎቹ የዲያብሎስ ዘዴዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለተገለጹ ልናውቃቸው እንችላለን። (2 ቆሮንቶስ 2:11) በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ቀደም ባሉት ምዕራፎች ላይ ከእነዚህ ዘዴዎች መካከል የፍቅረ ንዋይን አታላይነት፣ ጎጂ ባልንጀርነትንና የጾታ ብልግናን ተመልክተናል። አሁን ደግሞ ከሰይጣን መሠሪ ዘዴዎች መካከል አንዱን ይኸውም መናፍስታዊ ድርጊትን እንመልከት።
መናፍስታዊ ድርጊቶችን መፈጸም የክህደት ተግባር ነው
10. (ሀ) መናፍስታዊ ድርጊት ምንድን ነው? (ለ) ይሖዋ መናፍስታዊ ድርጊቶችን እንዴት ይመለከታቸዋል? አንተስ እንዴት ትመለከታቸዋለህ?
10 አንድ ሰው መናፍስታዊ ድርጊቶችን ወይም አጋንንታዊ ሥራዎችን ሲፈጽም ከክፉ መናፍስት ጋር በቀጥታ ይገናኛል። ምዋርት፣ ጥንቆላ፣ ድግምትና ሙታንን መጠየቅ ከመናፍስታዊ ድርጊቶች የሚመደቡ ናቸው። ይሖዋ መናፍስታዊ ድርጊቶችን ‘እንደሚጸየፍ’ እናውቃለን። (ዘዳግም 18:10-12፤ ራእይ 21:8) እኛም ‘ክፉ የሆነውን ነገር መጸየፍ’ ስለሚኖርብን ከክፉ መናፍስታዊ ኃይሎች ጋር ግንኙነት መፍጠር ልናስበው እንኳ የማንችለው ነገር ነው። (ሮም 12:9) እንዲህ ባለው ድርጊት መካፈል በሰማይ በሚኖረው አባታችን በይሖዋ ላይ አስጸያፊ ክህደት ከመፈጸም ተለይቶ አይታይም።
11. ሰይጣን መናፍስታዊ ድርጊቶችን እንድንፈጽም ማድረግ ቢችል ትልቅ ድል የሚሆንለት ለምንድን ነው? በምሳሌ አስረዳ።
11 በመናፍስታዊ ድርጊቶች መካፈል በይሖዋ ላይ ከባድ ክህደት እንደመፈጸም ስለሚቆጠር ሰይጣን እንዲህ ባለው ድርጊት እንድንካፈል ለማድረግ ይፈልጋል። ሰይጣን አንድ ክርስቲያን በአጋንንታዊ ተግባር እንዲካፈል ባደረገ ቁጥር አንድ ትልቅ ድል ያስመዘግባል። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? የሚከተለውን ምሳሌ ተመልከት:- አንድ ወታደር ሠራዊቱን ከድቶ ወደ ጠላት ሠራዊት ቢገባ የጠላት ሠራዊቱ አዛዥ በጣም ይደሰታል። እንዲያውም የወታደሩን የቀድሞ አዛዥ ለማዋረድ ሲል ከዳተኛው ወታደር በሕዝብ ፊት እንዲታይ ሊያደርግ ይችላል። በተመሳሳይ አንድ ክርስቲያን መናፍስታዊ ድርጊት ቢፈጽም ሆነ ብሎ ይሖዋን በመካድ ራሱን የሰይጣን ተገዥ ያደርጋል። ሰይጣን ይህን ከዳተኛ ሰው የጦር ምርኮኛው አድርጎ ሲያሳይ ምን ያህል ደስታ ሊሰማው እንደሚችል አስብ! ከመካከላችን ዲያብሎስ እንዲህ ያለውን ድል እንዲያገኝ የሚፈልግ ይኖራል? በፍጹም አይኖርም! እኛ ከሃዲዎች አይደለንም።
ጥያቄዎችን በማንሳት ጥርጣሬ መፍጠር
12. ሰይጣን መናፍስታዊ ድርጊቶችን የምንመለከትበትን መንገድ ለማዛባት የትኛውን ዘዴ ይጠቀማል?
12 መናፍስታዊ ድርጊቶችን እስከተጸየፍን ድረስ ሰይጣን በዚህ ዘዴ ሊያጠምደን አይችልም። በመሆኑም ዓላማውን ለማሳካት ሲል አስተሳሰባችንን ለማዛባት ይሞክራል። እንዴት? ክርስቲያኖችን ግራ አጋብቶ አንዳንዶቹ “ክፉውን መልካም፣ መልካሙን ክፉ” አድርገው እንዲመለከቱ ለማድረግ ይፈልጋል። (ኢሳይያስ 5:20) ይህን ለማሳካት ሰይጣን ለዘመናት ከተጠቀመባቸውና ውጤታማ ሆኖ ካገኛቸው ዘዴዎች መካከል አንዱን ይጠቀማል፤ ይህ ዘዴ ጥያቄዎች በማንሳት ጥርጣሬ መፍጠር ነው።
13. ሰይጣን ጥያቄ በማንሳት ጥርጣሬ ለመፍጠር የሞከረው እንዴት ነው?
13 ሰይጣን ከዚህ ቀደም ይህን ዘዴ እንዴት እንደተጠቀመ ልብ በል። በኤደን ገነት ሔዋንን ‘በእርግጥ አምላክ፣ “በአትክልቱ ስፍራ ካሉ ዛፎች ከማናቸውም እንዳትበሉ” ብሎአልን?’ ሲል ጠይቋታል። በኢዮብ ዘመን መላእክት በሰማይ በተሰበሰቡ ጊዜ፣ ሰይጣን ‘ኢዮብ አምላክን የሚፈራው እንዲሁ ነውን?’ የሚል ጥያቄ አንስቷል። ኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎቱን በጀመረበት ጊዜም፣ ሰይጣን ኢየሱስን “የአምላክ ልጅ ከሆንክ እነዚህ ድንጋዮች ዳቦ እንዲሆኑ እዘዝ” በማለት ተገዳድሮታል። ሰይጣን እንዲህ በማለት፣ ይሖዋ ከስድስት ሳምንታት በፊት “በእሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው” ብሎ በተናገረው ቃል ላይ አሹፏል።—ዘፍጥረት 3:1፤ ኢዮብ 1:9፤ ማቴዎስ 3:17፤ 4:3
14. (ሀ) ሰይጣን ከመናፍስታዊ ድርጊት ጋር በተያያዘ ጥርጣሬ የመፍጠር ዘዴውን የሚጠቀመው እንዴት ነው? (ለ) አሁን ምን እንመረምራለን?
14 ዛሬም ዲያብሎስ መናፍስታዊ ድርጊት መጥፎ ስለመሆኑ ጥርጣሬ ለመፍጠር ተመሳሳይ ዘዴ ይጠቀማል። በአንዳንድ ክርስቲያኖች አእምሮ ውስጥ ጥርጣሬ በመፍጠር ረገድ የተሳካለት መሆኑ ያሳዝናል። እነዚህ ክርስቲያኖች አንዳንድ መናፍስታዊ ድርጊቶች ያን ያህል መጥፎ ስለመሆናቸው መጠራጠር ጀምረዋል። በሌላ አነጋገር ‘በእርግጥ እንዲህ ማድረግ ችግር አለው?’ ብለው ማሰብ ጀምረዋል። (2 ቆሮንቶስ 11:3) እንዲህ ያሉ ሰዎች አስተሳሰባቸውን እንዲያስተካክሉ እንዴት ልንረዳቸው እንችላለን? ሰይጣን በሚጠቀምበት በዚህ ዘዴ እንዳንታለል ምን ማድረግ እንችላለን? የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት ሰይጣን መሠሪ በሆነ መንገድ በመናፍስታዊ ድርጊቶች የበከላቸውን ሁለት ነገሮች እንመልከት። እነዚህም መዝናኛና የሕክምና አገልግሎት ናቸው።
ፍላጎቶቻችንን ይጠቀምባቸዋል
15. (ሀ) በምዕራቡ ዓለም የሚኖሩ ብዙ ሰዎች መናፍስታዊ ድርጊቶችን እንዴት ይመለከቷቸዋል? (ለ) ዓለም ስለ መናፍስታዊ ድርጊቶች ያለው አመለካከት በአንዳንድ ክርስቲያኖች ላይ መጥፎ ተጽዕኖ ያሳደረው እንዴት ነው?
15 በተለይ በምዕራቡ ዓለም አስማት፣ ጥንቆላና ሌሎች መናፍስታዊ ድርጊቶች እንደ ቀላል ነገር እየታዩ መጥተዋል። ፊልሞች፣ መጻሕፍት፣ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችና የኮምፒውተር ጨዋታዎች አጋንንታዊ ድርጊቶችን አስደሳች እንደሆኑና ምንም ጉዳት እንደሌለባቸው ወይም እነዚህን ነገሮች መፈጸም ጉብዝና እንደሆነ አድርገው ያቀርባሉ። በአስማት ላይ የሚያተኩሩ አንዳንድ ፊልሞችና መጻሕፍት ከፍተኛ ተወዳጅነት ከማትረፋቸው የተነሳ አድናቂዎቻቸው ክበብ እስከማቋቋም ደርሰዋል። በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው አጋንንት አስማት ምንም ጉዳት የማያስከትልና ተራ ነገር እንደሆነ ተደርጎ እንዲታይ በማድረግ ረገድ ተሳክቶላቸዋል። ታዲያ ይህ መናፍስታዊ ድርጊትን እንደ ተራ ነገር የመቁጠር ዝንባሌ በክርስቲያኖች ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል? አዎ፣ በአንዳንዶች አስተሳሰብ ላይ መጥፎ ተጽዕኖ አሳድሯል። በምን መንገድ? አንድ ዓይነተኛ ምሳሌ ለመጥቀስ ያህል፣ አንድ ክርስቲያን በአስማት ላይ የሚያተኩር ፊልም ከተመለከተ በኋላ “ፊልሙን ባየውም መናፍስታዊ ድርጊት አልፈጸምኩም” ብሏል። እንዲህ ያለው አስተሳሰብ አደገኛ የሆነው ለምንድን ነው?
16. በመናፍስታዊ ድርጊቶች ዙሪያ የሚያጠነጥን መዝናኛ አደገኛ የሆነው ለምንድን ነው?
16 መናፍስታዊ ድርጊቶችን በመፈጸምና በማየት መካከል ልዩነት ቢኖርም፣ እንዲህ ያሉ ድርጊቶች ሲፈጸሙ መመልከት ምንም ጉዳት የለውም ማለት ግን አይቻልም። ለምን? የአምላክ ቃል፣ ሰይጣንም ሆነ አጋንንቱ በልባችን የምናስበውን የማወቅ ችሎታ እንደሌላቸው ይጠቁማል።a በመሆኑም ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው ክፉ መናፍስት የምናስበውን ለማወቅና ያለንን መንፈሳዊ ድክመት ለማግኘት የመዝናኛ ምርጫችንን ጨምሮ የምናደርጋቸውን ነገሮች በቅርብ ይከታተላሉ። አንድ ክርስቲያን በመናፍስት ጠሪዎች፣ በድግምት፣ በአጋንንት በተያዙ ሰዎች ወይም በሌሎች መናፍስታዊ ድርጊቶች ላይ የሚያጠነጥኑ መጻሕፍትን ወይም ፊልሞችን እንደሚወድ የሚያሳይ ነገር ማድረጉ ለአጋንንት የሚያስተላልፈው መልእክት ይኖራል። ‘ደካማ ጎኔ ይህ ነው’ ብሎ እንደመጠቆም ይሆንበታል። አጋንንትም ይህን ድክመቱን በመጠቀም ድል እስከሚያደርጉት ድረስ ትግላቸውን አፋፍመው ይቀጥላሉ። እንዲያውም አንዳንዶች በመናፍስታዊ ድርጊቶች ዙሪያ የሚያጠነጥኑ መዝናኛዎችን መመልከታቸው ወይም ጽሑፎችን ማንበባቸው ለዚህ ዓይነቱ ተግባር ፍላጎት እንዲያድርባቸው ስላደረጋቸው ውለው አድረው መናፍስታዊ ድርጊት እስከ መፈጸም ደርሰዋል።—ገላትያ 6:7
17. ሰይጣን የጤንነት ችግር ያለባቸውን ሰዎች ለማጥቃት በየትኛው መሠሪ ዘዴ ይጠቀማል?
17 ሰይጣን እኛን ለመርታት የሚጠቀመው ለመዝናናት ባለን ጉጉት ብቻ ሳይሆን የሕክምና አገልግሎት ለማግኘት ባለን ፍላጎት ጭምር ነው። እንዴት? አንድ ክርስቲያን መፍትሔ ለማግኘት ብዙ ቢደክምም የጤንነቱ ሁኔታ እያሽቆለቆለ ሲሄድ የሚያደርገው ጠፍቶት ሊጨነቅ ይችላል። (ማርቆስ 5:25, 26) ይህ ደግሞ ለሰይጣንና ለአጋንንቱ ምቹ አጋጣሚ ይፈጥርላቸዋል። የአምላክ ቃል ‘ከበደለኞች እርዳታ’ መጠየቅን እንደሚያወግዝ አሳምረው ያውቃሉ። (ኢሳይያስ 31:2 NW) አንድ ክርስቲያን ይህን ማስጠንቀቂያ እንዲተላለፍ ለማድረግ አጋንንት ታማሚው የሚያደርገው ጠፍቶት “ሚስጥራዊ ኃይል” የሚጠቀሙ ወይም መናፍስታዊ ድርጊቶች የሚፈጽሙ ሰዎች የሚሰጡትን የሕክምና አገልግሎት ለመሞከር እንዲፈተን ሊያደርጉት ይችላሉ። ይህ ደግሞ በጣም ጎጂ ነው። (ኢሳይያስ 1:13 NW) ይህ የአጋንንት መሠሪ ዘዴ ከተሳካ ታማሚው ከይሖዋ ጋር የመሠረተው ዝምድና ይዳከምበታል። በምን መንገድ?
18. አንድ ክርስቲያን እንዴት ካሉ የምርመራና የሕክምና ዓይነቶች መራቅ አለበት? ለምንስ?
18 ይሖዋ “ሚስጥራዊ ኃይል” የሚጠቀሙ ሰዎችን እርዳታ የፈለጉትን እስራኤላውያን “እጆቻችሁን ለጸሎት ወደ እኔ ስትዘረጉ፣ ዐይኖቼን ከእናንተ እሰውራለሁ፤ አብዝታችሁ ብትጸልዩም እንኳ አልሰማችሁም” በማለት አስጠንቅቋል። (ኢሳይያስ 1:15) እርግጥ ነው፣ በማንኛውም ጊዜ ቢሆን፣ በተለይ ደግሞ በምንታመምበት ጊዜ ጸሎታችንን የሚያግድና ከይሖዋ የምናገኘውን እርዳታ የሚገድብብን አንዳች ነገር ማድረግ አንፈልግም። (መዝሙር 41:3) ስለሆነም አንድ ዓይነት የጤና ምርመራ ወይም ሕክምና ከመናፍስታዊ ኃይል ጋር ግንኙነት እንዳለው የሚጠቁሙ ነገሮች ካሉ አንድ እውነተኛ ክርስቲያን እንዲህ ካለው ሕክምና ሊርቅ ይገባዋል።b (ማቴዎስ 6:13) ይህን ማድረጉ የይሖዋን ድጋፍ እንዳያጣ ያስችለዋል።—“በእርግጥ መናፍስታዊ ድርጊት ነው?” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።
ስለ አጋንንት ብዙ ማውራት ተገቢ ነው?
19. (ሀ) ዲያብሎስ፣ ያለውን ኃይል በተመለከተ ብዙዎች ምን ብለው እንዲያምኑ አድርጓቸዋል? (ለ) እውነተኛ ክርስቲያኖች እንዴት ካሉ ታሪኮች ይርቃሉ?
19 በምዕራቡ ዓለም የሚኖሩ በርካታ ሰዎች የሰይጣንን ኃይል በጣም አቃልለው የሚመለከቱ ሲሆን በሌሎች የዓለም ክፍሎች ያለው ሁኔታ ደግሞ የዚህ ተቃራኒ ነው። በእነዚህ አካባቢዎች ዲያብሎስ፣ በእርግጥ ካለው ኃይል የበለጠ ኃይል እንዳለው አድርገው እንዲያምኑ በማድረግ ብዙዎችን አስቷቸዋል። አንዳንድ ሰዎች የሚበሉት፣ የሚሠሩት፣ የሚተኙትና የሚነሱት ክፉ መናፍስትን እየፈሩ ነው። አጋንንት ከፍተኛ ኃይል እንዳላቸው የሚገልጹ ብዙ ታሪኮች ይወራሉ። እንደነዚህ ያሉ ታሪኮች በአብዛኛው የሚነገሩት በስሜት ሲሆን የሚሰሙትም ተመስጠው ያዳምጣሉ። እኛ እንደነዚህ ያሉትን ታሪኮች ማውራት ይኖርብናል? አይኖርብንም፤ እውነተኛውን አምላክ የሚያመልኩ ሰዎች በሁለት ዋና ዋና ምክንያቶች የተነሳ እንዲህ ከማድረግ ይቆጠባሉ።
20. አንድ ሰው ምናልባትም ሳይታወቀው የሰይጣንን ፕሮፓጋንዳ የሚያሰራጨው እንዴት ነው?
20 አንደኛ፣ አንድ ሰው ስለ አጋንንት ጀብዱ የሚገልጽ ወሬ ሲናገር የሰይጣንን ጥቅምና ፍላጎት ማራመዱ ነው። እንዴት? የአምላክ ቃል ሰይጣን ተአምር የማድረግ ችሎታ እንዳለው የሚናገር ቢሆንም ‘ሐሰተኛ ምልክቶችንና የማታለያ ዘዴዎችን’ እንደሚጠቀም ጭምር ይገልጻል። (2 ተሰሎንቄ 2:9, 10) ሰይጣን ቀንደኛ አታላይ በመሆኑ መናፍስታዊ ድርጊት የሚስባቸውን ሰዎች አእምሮ እንዴት እንደሚማርክና እውነት ያልሆኑ ነገሮችን እንዲያምኑ ለማድረግ ምን ማድረግ እንዳለበት ያውቃል። እንደነዚህ ያሉት ሰዎች አንዳንድ ነገሮችን በእርግጥ እንዳዩና እንደሰሙ አድርገው በቅንነት ሊያምኑና ይህንንም እውነት እንደሆነ አድርገው ሊያወሩ ይችላሉ። ከጊዜ በኋላ ወሬው ከአንዱ ወደ ሌላው ሲተላለፍ በጣም ተጋንኖ ሊወራ ይችላል። አንድ ክርስቲያን እንደነዚህ ያሉትን ወሬዎች ቢያወራ “የውሸት አባት” የሆነውን የዲያብሎስን ፍላጎት መፈጸም አይሆንበትም? የሰይጣንን ፕሮፓጋንዳ ማሰራጨት እንደሚሆንበት ምንም ጥርጥር የለውም።—ዮሐንስ 8:44፤ 2 ጢሞቴዎስ 2:16
21. ጭውውታችን በምን ላይ ማተኮር ይኖርበታል?
21 ሁለተኛ፣ አንድ ክርስቲያን በአንድ ወቅት ከክፉ መናፍስት ጋር ግንኙነት የነበረው ቢሆን እንኳ ለእምነት ባልንጀሮቹ ስለዚህ ነገር ደጋግሞ ማውራት አይኖርበትም። ለምን? ‘የእምነታችን ዋና ወኪልና ፍጹም አድራጊ የሆነውን ኢየሱስን በትኩረት እንድንመለከት’ ምክር ስለተሰጠን ነው። (ዕብራውያን 12:2) አዎ፣ ማተኮር ያለብን በክርስቶስ ላይ እንጂ በሰይጣን ላይ አይደለም። ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ሰይጣን ሊያደርግ ስለሚችላቸውና ስለማይችላቸው ነገሮች ብዙ መናገር ይችል የነበረ ቢሆንም ለደቀ መዛሙርቱ ስለ ክፉ መናፍስት የሚናገሩ ታሪኮችን አላወራላቸውም። ከዚህ ይልቅ ኢየሱስ ያተኮረው በመንግሥቱ መልእክት ላይ ነበር። እኛም የኢየሱስንና የሐዋርያቱን አርዓያ በመከተል ጭውውታችን ‘በአምላክ ታላቅ ሥራ’ ላይ እንዲያተኩር እናደርጋለን።—የሐዋርያት ሥራ 2:11፤ ሉቃስ 8:1፤ ሮም 1:11, 12
22. ‘በሰማይ ለሚኖረው ደስታ’ አስተዋጽኦ ልናደርግ የምንችለው እንዴት ነው?
22 እውነት ነው፣ ሰይጣን ከይሖዋ ጋር ያለንን ዝምድና ለማበላሸት መናፍስታዊ ድርጊቶችን ጨምሮ የተለያዩ መሠሪ ዘዴዎችን ይጠቀማል። ይሁን እንጂ ክፉውን በመጸየፍና ጥሩ ከሆነው ነገር ጋር በመጣበቅ፣ ዲያብሎስ ከማንኛውም ዓይነት መናፍስታዊ ድርጊት ለመራቅ ያደረግነውን ቁርጥ ውሳኔ ለማዳከም የሚያስችል አጋጣሚ እንዳያገኝ እናደርጋለን። (ኤፌሶን 4:27) ዲያብሎስ ጨርሶ እስከሚጠፋበት ጊዜ ድረስ ‘መሠሪ ዘዴዎቹን መቋቋም ከቻልን’ “በሰማይ” እንዴት ያለ “ታላቅ ደስታ” እንደሚሆን አስብ!—ኤፌሶን 6:11
a ለሰይጣን የተሰጡት ቅጽል ስሞች (ተቃዋሚ፣ ስም አጥፊ፣ አሳሳች፣ ፈታኝ፣ ውሸታም) ልባችንንና ሐሳባችንን የማንበብ ችሎታ እንዳለው አያመለክቱም። በአንጻሩ ግን ይሖዋ “ልብን ይመረምራል” ተብሏል፤ ኢየሱስ ደግሞ ‘ኩላሊትንና ልብን የሚመረምር’ ተብሎ ተገልጿል።—ምሳሌ 17:3፤ ራእይ 2:23
b ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በታኅሣሥ 15, 1994 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 19-22 ላይ የወጣውን “የሚደረግልህ የጤና ምርመራ” የሚለውን ርዕስና በጥር 2001 ንቁ! መጽሔት ላይ የወጣውን “የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት—የምትመርጠው የሕክምና ዓይነት ለውጥ ያመጣልን?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።