ምዕራፍ ሰባት
በሞት የተለዩህ የምትወዳቸው ሰዎች ያላቸው እውነተኛ ተስፋ
ትንሣኤ እንደሚፈጸም በእርግጠኝነት ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው?
ይሖዋ ሙታንን ማስነሳት እንደሚፈልግ የሚያሳየው ምንድን ነው?
ትንሣኤ የሚያገኙት እነማን ናቸው?
1-3. ሁላችንንም እያሳደደን ያለው ጠላት ምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ረገድ የሚሰጠውን ትምህርት መመርመራችን እፎይታ የሚያስገኝልን ለምንድን ነው?
ከአንድ ጨካኝ የሆነ ጠላት ሸሽተህ ለማምለጥ እየሮጥክ ነው እንበል። ጠላትህ በጉልበትም ሆነ በፍጥነት ይበልጥሃል። አንዳንድ ጓደኞችህን ሲገድል ስለተመለከትክ ምሕረት የለሽ መሆኑን ታውቃለህ። ሸሽተህ ለማምለጥ የቻልከውን ያህል ብትሮጥም እየቀረበህና እየተጠጋህ ይሄዳል። ሁኔታው ተስፋ አስቆራጭ ይሆንብሃል። ይሁን እንጂ ከዚህ ጠላት ሊያስጥልህ የሚችል አንድ ሰው በድንገት ከተፍ ይላል። ከጠላትህ እጅግ የላቀ ኃይል ያለው ከመሆኑም በላይ እንደሚረዳህ ቃል ይገባልሃል። እንዴት ያለ እፎይታ ይሰማህ ይሆን!
2 በአሁኑ ጊዜ እንዲህ ያለ ጠላት እያሳደደህ ነው ሊባል ይችላል። ይህ ጠላት አንተን ብቻ ሳይሆን ሁላችንንም እያሳደደን ነው። ቀደም ባለው ምዕራፍ ላይ እንደተማርነው መጽሐፍ ቅዱስ ሞትን ጠላት ብሎ ይጠራዋል። ማንኛችንም ብንሆን ይህን ጠላት ሮጠን ልናመልጠውም ሆነ ታግለን ልናሸንፈው አንችልም። አብዛኞቻችን ይህ ጠላት በጣም የምንወዳቸውን ሰዎች ሕይወት ሲቀጥፍ ተመልክተናል። ሆኖም ይሖዋ ከሞት እጅግ የላቀ ኃይል አለው። ይሖዋ አፍቃሪ ታዳጊያችን ከመሆኑም በላይ ሞትን ድል መንሳት እንደሚችል በተግባር አሳይቷል። በተጨማሪም ይህን ጠላት ማለትም ሞትን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንደሚያስወግድ ቃል ገብቷል። መጽሐፍ ቅዱስ “የሚደመሰሰውም የመጨረሻው ጠላት ሞት ነው” ሲል ያስተምራል። (1 ቆሮንቶስ 15:26) ይህ ምሥራች ነው!
3 እስቲ በቅድሚያ፣ የምናውቀው ሰው ሲሞት የሚሰማንን ስሜት እንመልከት። ይህን ማድረጋችን በጣም አስደሳች የሆነን አንድ ተስፋ በሚገባ ማስተዋል እንድንችል ይረዳናል። ይሖዋ ሙታን እንደገና በሕይወት እንደሚኖሩ ቃል ገብቷል። (ኢሳይያስ 26:19) ዳግመኛ ሕያዋን ይሆናሉ። በመሆኑም ሙታን የትንሣኤ ተስፋ አላቸው።
የምትወደው ሰው ሲሞት
4. (ሀ) ኢየሱስ የሚወደው ሰው በሞተ ጊዜ የተሰማው ስሜት ይሖዋ ያለውን ስሜት ያስተምረናል የምንለው ለምንድን ነው? (ለ) ኢየሱስ ምን ልዩ ወዳጅነት መሥርቶ ነበር?
4 የምትወደውን ሰው በሞት ተነጥቀሃል? እንዲህ ያለ ሁኔታ ሲያጋጥምህ የሚሰማህ ጥልቅ ሐዘንና የከንቱነት ስሜት ለመቋቋም የሚከብድ ሊሆን ይችላል። በዚህ ጊዜ ማጽናኛ ለማግኘት የአምላክን ቃል መመርመር ያስፈልገናል። (2 ቆሮንቶስ 1:3, 4) መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋና ኢየሱስ ሞትን በተመለከተ የሚሰማቸውን ስሜት ማስተዋል እንድንችል ይረዳናል። የአባቱ ፍጹም ነጸብራቅ የሆነው ኢየሱስ አንድን ሰው በሞት ማጣት የሚያስከትለውን ሐዘን በሚገባ ያውቃል። (ዮሐንስ 14:9) ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም በሚሄድበት ጊዜ በአቅራቢያ በምትገኘው የቢታንያ ከተማ ይኖሩ የነበሩትን አልዓዛርን እንዲሁም ማርያምና ማርታ የተባሉ እህቶቹን ይጠይቃቸው ነበር። በዚህም የተነሳ የቅርብ ጓደኞች ሆኑ። መጽሐፍ ቅዱስ “ኢየሱስም ማርታን፣ እኅቷንና አልዓዛርን ይወዳቸው ነበር” ይላል። (ዮሐንስ 11:5) ይሁንና ቀደም ባለው ምዕራፍ ላይ እንደተመለከትነው አልዓዛር ሞተ።
5, 6. (ሀ) ኢየሱስ እያለቀሱ የነበሩትን የአልዓዛር ቤተሰቦችና ጓደኞች ሲመለከት ምን ተሰማው? (ለ) ኢየሱስ ማዘኑ እኛን የሚያጽናናን ለምንድን ነው?
5 ኢየሱስ ወዳጁን በሞት በማጣቱ ምን ተሰማው? ኢየሱስ ሐዘን ላይ ወደነበሩት የአልዓዛር ዘመዶችና ጓደኞች ዘንድ እንደሄደ ታሪኩ ይነግረናል። ሲያለቅሱ ሲመለከት ስሜቱ በጣም ተነካ። ‘መንፈሱ በኀዘን ታወከ።’ ታሪኩ “ኢየሱስም እንባውን አፈሰሰ” በማለት ከዚያ በኋላ የሆነውን ሁኔታ ይገልጻል። (ዮሐንስ 11:33, 35) ኢየሱስ ያዘነው ምንም ተስፋ ስላልነበረው ነው? በፍጹም። እንዲያውም ኢየሱስ አንድ ተአምር ሊፈጸም መሆኑን ያውቅ ነበር። (ዮሐንስ 11:3, 4) ያም ሆኖ ሞት የሚያስከትለው ጥልቅ ሐዘን ተሰምቶት ነበር።
6 ይሁንና በአንድ በኩል ሲታይ ኢየሱስ የተሰማው ሐዘን እንድንጽናና ያደርገናል። ኢየሱስም ሆነ አባቱ ሞትን እንደሚጠሉ ያስተምረናል። ይሁን እንጂ ይሖዋ አምላክ ይህን ጠላት መዋጋትና ማሸነፍ ይችላል! አምላክ ኢየሱስን ምን እንዲፈጽም እንዳስቻለው እንመልከት።
“አልዓዛር፣ ና ውጣ!”
7, 8. ከሰብዓዊ አመለካከት አንጻር ሲታይ የአልዓዛር ሁኔታ ተስፋ አስቆራጭ ሊመስል የሚችለው ለምንድን ነው? ሆኖም ኢየሱስ ምን አደረገ?
7 አልዓዛር ዋሻ ውስጥ ተቀብሮ ስለነበር ኢየሱስ የዋሻው መግቢያ የተዘጋበትን ድንጋይ እንዲያነሱ አዘዘ። አልዓዛር ከሞተ አራት ቀን ሆኖት ስለነበር አስከሬኑ መበስበስ ጀምሯል በሚል ማርታ ሐሳቡን ተቃወመች። (ዮሐንስ 11:39) ከሰብዓዊ አመለካከት አንጻር ሲታይ ምንም ተስፋ አልነበረውም።
8 ድንጋዩን አንከባልለው ካነሱት በኋላ ኢየሱስ በታላቅ ድምፅ “አልዓዛር፣ ና ውጣ!” ብሎ ጮኸ። ከዚያስ ምን ሆነ? ‘የሞተው ሰው ወጣ።’ (ዮሐንስ 11:43, 44) በዚያ የነበሩት ሰዎች የተሰማቸውን ደስታ ልትገምት ትችላለህ? አልዓዛር ወንድማቸውም ይሁን ዘመዳቸው አሊያም ጓደኛቸው ወይም ጎረቤታቸው ሞቶ እንደነበረ ያውቃሉ። ሆኖም አሁን፣ ይወዱት የነበረ ያው ሰው ከሞት ተነስቶ ዳግመኛ መካከላቸው ቆሟል። ዓይናቸውን ለማመን ተቸግረው እንደሚሆን መገመት ይቻላል። ብዙዎቹ በደስታ አልዓዛርን አንገቱ ላይ ተጠምጥመው አቅፈውት መሆን አለበት። በሞት ላይ የተገኘ እንዴት ያለ ታላቅ ድል ነው!
9, 10. (ሀ) ኢየሱስ አልዓዛርን ከሞት ለማስነሳት የሚያስችል ኃይል የሰጠው ማን መሆኑን የገለጸው እንዴት ነው? (ለ) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን ስለ ትንሣኤ የሚገልጹ ታሪኮች ማንበብ የሚያስገኛቸው አንዳንድ ጥቅሞች ምንድን ናቸው?
9 ኢየሱስ ይህን ተአምር የፈጸመው በራሱ ኃይል እንደሆነ አድርጎ አልተናገረም። አልዓዛርን ከመጣራቱ በፊት ባቀረበው ጸሎት ላይ ትንሣኤው እንዲከናወን ያደረገው ይሖዋ መሆኑን በግልጽ ተናግሯል። (ዮሐንስ 11:41, 42) ይሖዋ ኃይሉን በዚህ መንገድ የተጠቀመው በዚህ ወቅት ብቻ አልነበረም። የአልዓዛር ትንሣኤ በአምላክ ቃል ውስጥ ከትንሣኤ ጋር በተያያዘ ተመዝግበው ከሚገኙት ዘጠኝ ተአምራዊ ክንውኖች አንዱ ብቻ ነው።a እነዚህን ታሪኮች ማንበቡና ማጥናቱ በጣም አስደሳች ነው። ከሞት ከተነሱት መካከል ወጣቶችና በዕድሜ የገፉ፣ ወንዶችና ሴቶች፣ እስራኤላዊ የሆኑና ያልሆኑ ሰዎች የሚገኙበት በመሆኑ እነዚህ ዘገባዎች አምላክ እንደማያዳላ ያስተምሩናል። በተጨማሪም እነዚህ ታሪኮች ሰዎች በተፈጸሙት ተአምራት ሳቢያ የተሰማቸውን ታላቅ ደስታ ይገልጻሉ! ለምሳሌ ያህል ኢየሱስ አንዲትን ትንሽ ልጃገረድ ከሞት ባስነሳበት ወቅት ወላጆቿ በጣም ተደስተውና ‘ተደንቀው’ ነበር። (ማርቆስ 5:42) አዎን፣ ይሖዋ መቼም የማይረሱት እጅግ የሚያስደስት ተአምር ፈጽሞላቸዋል።
10 እርግጥ ነው፣ ኢየሱስ ከሞት ያስነሳቸው ሰዎች ከጊዜ በኋላ ዳግመኛ ሞተዋል። እንዲህ ሲባል ግን ከሞት መነሳታቸው ትርጉም የለውም ማለት ነው? እንደዚያ ማለት አይደለም። እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች በጣም አስፈላጊ የሆኑ እውነቶችን የሚያረጋግጡልን ከመሆኑም በላይ ተስፋ ይሰጡናል።
ስለ ትንሣኤ ከሚገልጹት ታሪኮች መማር
11. አልዓዛር ከሞት እንደተነሳ የሚገልጸው ታሪክ በመክብብ 9:5 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውን ሐቅ የሚያረጋግጥልን እንዴት ነው?
11 መጽሐፍ ቅዱስ ሙታን “ምንም አያውቁም” ሲል ያስተምራል። ከሕልውና ውጭ በመሆናቸው በሌላ ቦታ ምንም ዓይነት ሕይወት ሊኖራቸው አይችልም። የአልዓዛር ታሪክ ይህን ሐቅ ያረጋግጥልናል። አልዓዛር ከሞት ከተነሳ በኋላ ስለ ሰማይ በመተረክ ሰዎች እንዲደመሙ አድርጓል? ወይም ደግሞ ስለ እሳታማ ሲኦል የሚገልጹ የሚያሳቅቁ ታሪኮችን በማውራት ሰዎችን አሸብሯል? በፍጹም። መጽሐፍ ቅዱስ አልዓዛር እንዲህ ያለ ታሪክ እንዳወራ አይናገርም። ሞቶ በቆየባቸው አራት ቀናት ውስጥ ‘ምንም የሚያውቀው’ ነገር አልነበረም። (መክብብ 9:5) በአጭር አነጋገር በሞት አንቀላፍቶ ነበር።—ዮሐንስ 11:11
12. አልዓዛር በእርግጥ ከሞት እንደተነሳ እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምንድን ነው?
12 በተጨማሪም የአልዓዛር ታሪክ፣ ትንሣኤ የተረጋገጠ ነገር እንጂ ተረት እንዳልሆነ ያስተምረናል። ኢየሱስ አልዓዛርን ከሞት ያስነሳው ብዙ የዓይን ምሥክሮች በተገኙበት ነው። ኢየሱስን ይጠሉ የነበሩት የሃይማኖት መሪዎች እንኳ ይህ ተአምር መፈጸሙን አልካዱም። ከዚህ ይልቅ “ይህ ሰው [ኢየሱስ] ብዙ ታምራዊ ምልክቶችን እያደረገ ስለ ሆነ ምን ብናደርግ ይሻላል?” ብለው ነበር። (ዮሐንስ 11:47) ብዙ ሰዎች ከሞት የተነሳውን አልዓዛርን ለማየት ሄዱ። በዚህም ሳቢያ ሌሎች ተጨማሪ ሰዎች በኢየሱስ አመኑ። አልዓዛር፣ ኢየሱስ በአምላክ የተላከ መሆኑን የሚያረጋግጥ ሕያው ማስረጃ ሆኖላቸዋል። ይህ አሳማኝ ማስረጃ ስለነበረ ርኅራኄ የሚባል ነገር የማያውቁት አንዳንድ የአይሁድ ሃይማኖት መሪዎች ኢየሱስንና አልዓዛርን ለመግደል አሲረው ነበር።—ዮሐንስ 11:53፤ 12:9-11
13. ይሖዋ በእርግጥ ሙታንን ሊያስነሳ ይችላል ብለን የምናምነው የትኛውን መሠረታዊ ሐሳብ ተመርኩዘን ነው?
13 ትንሣኤ የተረጋገጠ ነገር ነው ብሎ ማመን ከእውነታው የራቀ አስተሳሰብ ነው? በፍጹም፤ ኢየሱስ አንድ ቀን “መቃብር ውስጥ ያሉ ሁሉ” ከሞት እንደሚነሱ አስተምሯል። (ዮሐንስ 5:28) የሕይወት ሁሉ ፈጣሪ ይሖዋ ነው። ታዲያ ሕይወትን መልሶ መፍጠር ይችላል ብሎ ማመን የሚከብደው ምኑ ላይ ነው? ይህ በይሖዋ የማስታወስ ችሎታ ላይ በእጅጉ የተመካ እንደሆነ አይካድም። በሞት የተለዩንን የምንወዳቸውን ሰዎች ማስታወስ ይችላል? በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ሥፍር ቁጥር የሌላቸው ከዋክብት ያሉ ቢሆንም አምላክ የእያንዳንዳቸውን ስም ያውቃል! (ኢሳይያስ 40:26) ስለዚህ ይሖዋ አምላክ በሞት የተለዩንን ሰዎች በተመለከተ እያንዳንዷን ዝርዝር መረጃ ሳይቀር ማስታወስ የሚችል ከመሆኑም በላይ እነዚህን ሰዎች ወደ ሕይወት ለመመለስ ፈቃደኛ ነው።
14, 15. ኢዮብ በተናገረው ቃል ላይ እንደተገለጸው ይሖዋ ሙታንን ማስነሳት እንደሚፈልግ የሚጠቁመው ምንድን ነው?
14 መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ ሙታንን ለማስነሳት ከፍተኛ ጉጉት እንዳለው ያስተምራል። ይህን ማረጋገጥ የምንችለው እንዴት ነው? የአምላክ ታማኝ አገልጋይ የነበረው ኢዮብ “ሰው ከሞተ በኋላ ተመልሶ በሕይወት ይኖራል?” ሲል ጠይቋል። ኢዮብ እየተናገረ የነበረው አምላክ እሱን የሚያስታውስበት ጊዜ እስኪደርስ በመቃብር ውስጥ መቆየት ስለሚችልበት ሁኔታ ነበር። ይሖዋን “ትጠራኛለህ፤ እኔም እመልስልሃለሁ፤ የእጅህንም ሥራ ትናፍቃለህ” ብሎታል።—ኢዮብ 14:13-15
15 ይህ ምን ማለት እንደሆነ እስቲ አስበው! ይሖዋ ሙታንን ዳግመኛ ሕያዋን የሚያደርግበትን ጊዜ ይናፍቃል። ይሖዋ እንዲህ ያለ ስሜት የሚሰማው መሆኑን ማወቁ አያስደስትም? ይሁንና ወደፊት ስለሚፈጸመው ትንሣኤ ምን ማለት ይቻላል? የሚነሱት እነማን ናቸው? የሚነሱትስ የት ነው?
“መቃብር ውስጥ ያሉ ሁሉ”
16. ሙታን በሚነሱበት ጊዜ በምን ዓይነት ሁኔታዎች ውስጥ ይኖራሉ?
16 ስለ ትንሣኤ የሚናገሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች ወደፊት ስለሚፈጸመው ትንሣኤ ብዙ ያስተምሩናል። በዚህ ምድር ላይ ዳግመኛ ሕያዋን የሆኑት ሰዎች ከወዳጅ ዘመዶቻቸው ጋር እንደገና ተገናኝተዋል። ወደፊት የሚፈጸመው ትንሣኤም ተመሳሳይ ነው፤ ይሁንና ቀደም ሲል ከተፈጸሙት ትንሣኤዎች በእጅጉ የላቀ ይሆናል። ምዕራፍ 3 ላይ እንደተማርነው የአምላክ ዓላማ መላዋ ምድር ገነት እንድትሆን ነው። ስለዚህ ሙታን የሚነሱት በጦርነት፣ በወንጀልና በበሽታ በተሞላ ዓለም ውስጥ አይደለም። በዚህ ምድር ላይ ሰላምና አስደሳች ሁኔታዎች በሰፈኑበት ዓለም ውስጥ ለዘላለም የመኖር አጋጣሚ ያገኛሉ።
17. ወደፊት የሚከናወነው ትንሣኤ ምን ያህል ስፋት ያለው ነው?
17 የሚነሱት እነማን ናቸው? ኢየሱስ ‘መቃብር ውስጥ ያሉ ሁሉ ድምፁን [የኢየሱስን] ሰምተው ይወጣሉ’ ሲል ተናግሯል። (ዮሐንስ 5:28, 29) በተመሳሳይም ራእይ 20:13 “ባሕርም በውስጡ የነበሩትን ሙታን ሰጠ፤ ሞትና ሲኦልም በእነርሱ ውስጥ የነበሩትን ሙታን ሰጡ” ይላል። “ሲኦል” የሰው ልጆችን የጋራ መቃብር ያመለክታል። (ከገጽ 212-213 ላይ የሚገኘውን ተጨማሪ ክፍል ተመልከት።) ይህ የጋራ መቃብር ባዶ ይሆናል። በዚያ አንቀላፍተው የቆዩ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ዳግመኛ ሕያዋን ይሆናሉ። ሐዋርያው ጳውሎስ “ጻድቃንና ኀጥአን ከሙታን እንደሚነሡ” ተናግሯል። (የሐዋርያት ሥራ 24:15) ይህ ምን ማለት ነው?
18. ከሞት የሚነሱት “ጻድቃን” እነማን ናቸው? ይህ ተስፋ በአንተ ላይ ለውጥ ሊያመጣ የሚችለውስ እንዴት ነው?
18 “ጻድቃን” የሚለው አነጋገር ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት የኖሩትን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ በርካታ ሰዎች ያጠቃልላል። ኖኅን፣ አብርሃምን፣ ሣራን፣ ሙሴን፣ ሩትን፣ አስቴርንና ሌሎች በርካታ ሰዎችን ታስታውስ ይሆናል። በአምላክ ላይ ጠንካራ እምነት ከነበራቸው ከእነዚህ ወንዶችና ሴቶች መካከል አንዳንዶቹ ዕብራውያን ምዕራፍ 11 ላይ ተጠቅሰዋል። ሆኖም “ጻድቃን” የሚለው አነጋገር በዚህ ዘመን የሚሞቱትን የይሖዋ አገልጋዮችም ያጠቃልላል። የትንሣኤ ተስፋ ከማንኛውም ዓይነት የሞት ፍርሃት ነፃ ያደርገናል።—ዕብራውያን 2:15
19. “ኀጥአን” የተባሉት እነማን ናቸው? ይሖዋ በደግነት ተገፋፍቶ ምን አጋጣሚ ይሰጣቸዋል?
19 ይሖዋን ባለማወቃቸው ምክንያት እሱን ሳያገለግሉ ወይም ሳይታዘዙ የሞቱ ሰዎችስ? እነዚህ በቢሊዮን የሚቆጠሩ “ኀጥአን” ተረስተው አይቀሩም። እነሱም ከሞት ተነስተው ስለ እውነተኛው አምላክ መማርና እሱን ማገልገል የሚችሉበት ጊዜ ይሰጣቸዋል። በሺህ ዓመት ጊዜ ውስጥ ሙታን ተነስተው ታማኝ ከሆኑት ሰዎች ጎን በመሰለፍ በምድር ላይ ይሖዋን ማገልገል የሚችሉበት አጋጣሚ ያገኛሉ። ያ ዘመን አስደሳች ጊዜ ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስ ያንን ዘመን የፍርድ ቀን በማለት ይጠራዋል።b
20. ገሃነም ምንድን ነው? እዚያ የሚገቡትስ እነማን ናቸው?
20 እንዲህ ሲባል ግን የሞተ ሰው ሁሉ ይነሳል ማለት ነው? እንደዚያ ማለት አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ ከሞቱ ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ “ገሃነም” ውስጥ እንደሆኑ ይናገራል። (ሉቃስ 12:5) ገሃነም ከጥንቷ ኢየሩሳሌም ውጭ ይገኝ የነበረን አንድ የቆሻሻ መጣያ ሥፍራ ያመለክት የነበረ ስያሜ ነው። በዚያ ሥፍራ አስከሬንና ቆሻሻ ይቃጠል ነበር። አይሁዶች አስከሬናቸው በዚህ ቦታ የሚጣል ሙታንን ቀብርና ትንሣኤ የማይገባቸው እንደሆኑ አድርገው ይቆጥሯቸው ነበር። ስለዚህ ገሃነም ዘላለማዊ ጥፋትን ለማመልከት ተስማሚ ምሳሌ ነው። ምንም እንኳ ኢየሱስ በሕያዋንና በሙታን ላይ በሚካሄደው ፍርድ የራሱ የሆነ ድርሻ ቢኖረውም የመጨረሻው ፈራጅ ይሖዋ ነው። (የሐዋርያት ሥራ 10:42) ክፉና ለመለወጥ ፈቃደኛ ያልሆኑ ብሎ የሚፈርድባቸውን ሰዎች ከሞት አያስነሳም።
ሰማያዊ ትንሣኤ
21, 22. (ሀ) ሌላው ዓይነት ትንሣኤ ምንድን ነው? (ለ) ከሞት ተነስቶ መንፈሳዊ ሕይወት በማግኘት ቀዳሚ የሆነው ማን ነው?
21 በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ሌላ ዓይነት ትንሣኤ እንዳለ የሚገልጽ ሲሆን ይህን ትንሣኤ የሚያገኙ በሰማይ መንፈሳዊ ፍጡር ሆነው ይኖራሉ። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይህን ዓይነቱን ትንሣኤ የሚያሳይ ምሳሌ ተጠቅሶ የሚገኘው አንድ ጊዜ ሲሆን እሱም የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ነው።
22 ኢየሱስ ሰው ሆኖ ከሞተ በኋላ ይሖዋ፣ ታማኝ ልጁ መቃብር ውስጥ እንዲቀር አልፈቀደም። (መዝሙር 16:10፤ የሐዋርያት ሥራ 13:34, 35) አምላክ ኢየሱስን ከሞት አስነስቶታል፤ ሆኖም ኢየሱስ የተነሳው ሰው ሆኖ አይደለም። ሐዋርያው ጴጥሮስ፣ ክርስቶስ “በሥጋ ሞተ፤ በመንፈስ ግን ሕያው ሆነ” ሲል ገልጿል። (1 ጴጥሮስ 3:18) ይህ በእርግጥም ታላቅ ተአምር ነበር። ኢየሱስ ኃያል መንፈሳዊ አካል ሆኖ ዳግመኛ ሕያው ሆነ! (1 ቆሮንቶስ 15:3-6) ይህን ዓይነቱን ታላቅ ትንሣኤ ከማንም በፊት ያገኘው ኢየሱስ ነው። (ዮሐንስ 3:13) ሆኖም ኢየሱስ የመጀመሪያው እንጂ የመጨረሻው አይደለም።
23, 24. የኢየሱስ “ታናሽ መንጋ” አባላት እነማን ናቸው? ቁጥራቸውስ ስንት ነው?
23 ኢየሱስ ብዙም ሳይቆይ ወደ ሰማይ እንደሚመለስ በመገንዘብ ታማኝ ተከታዮቹን በዚያ ‘ስፍራ እንደሚያዘጋጅላቸው’ ነግሯቸው ነበር። (ዮሐንስ 14:2) ኢየሱስ ወደ ሰማይ የሚሄዱትን “ታናሽ መንጋ” ሲል ጠርቷቸዋል። (ሉቃስ 12:32 የ1954 ትርጉም) በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ አነስተኛ በሆነው በዚህ ቡድን ውስጥ የታቀፉት ታማኝ ክርስቲያኖች ስንት ናቸው? ራእይ 14:1 ላይ ሐዋርያው ዮሐንስ “ከዚህ በኋላ አየሁ፤ እነሆ፤ በጉ [ኢየሱስ ክርስቶስ] በጽዮን ተራራ ላይ ቆሞ ነበር፤ ከእርሱም ጋር የእርሱ ስምና የአባቱ ስም በግምባራቸው ላይ የተጻፈባቸው መቶ አርባ አራቱ ሺህ ሰዎች ነበሩ” ሲል ተናግሯል።
24 የኢየሱስን ታማኝ ሐዋርያት ጨምሮ እነዚህ 144,000 ክርስቲያኖች ከሞት ተነስተው ሰማያዊ ሕይወት ያገኛሉ። ይህ ትንሣኤ የሚከናወነው መቼ ነው? ሐዋርያው ጳውሎስ ይህ ትንሣኤ የሚከናወነው ክርስቶስ በሥልጣኑ ላይ በሚገኝበት ጊዜ እንደሆነ ገልጿል። (1 ቆሮንቶስ 15:23 NW) ምዕራፍ 9 ላይ እንደምትማረው በዛሬው ጊዜ የምንኖረው በዚህ ዘመን ውስጥ ነው። ስለዚህ በእኛ ዘመን ያሉት የ144,000 ጥቂት ቀሪዎች በሚሞቱበት ጊዜ በቅጽበት ተነስተው ሰማያዊ ሕይወት ያገኛሉ። (1 ቆሮንቶስ 15:51-55) ይሁን እንጂ አብዛኛው የሰው ዘር ወደፊት ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ትንሣኤ አግኝቶ የመኖር ተስፋ ያለው ነው።
25. በሚቀጥለው ምዕራፍ ላይ የሚብራራው ምንድን ነው?
25 አዎን፣ ይሖዋ ጠላታችን የሆነውን ሞትን ድል በመንሳት ለዘላለም ያስወግደዋል! (ኢሳይያስ 25:8) ይሁንና ‘ሰማያዊ ትንሣኤ የሚያገኙት ሰዎች እዚያ ምን ያደርጋሉ?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። ዕጹብ ድንቅ የሆነው የሰማያዊው መንግሥት መስተዳድር አካል ይሆናሉ። በሚቀጥለው ምዕራፍ ላይ ስለዚህ መስተዳድር ተጨማሪ ትምህርት እናገኛለን።
a ሌሎቹ ታሪኮች በ1 ነገሥት 17:17-24፤ 2 ነገሥት 4:32-37፤ 13:20, 21፤ ማቴዎስ 28:5-7፤ ሉቃስ 7:11-17፤ 8:40-56፤ የሐዋርያት ሥራ 9:36-42 እና 20:7-12 ላይ ተጠቅሰው ይገኛሉ።
b ስለ ፍርድ ቀንና ፍርዱ በምን ላይ የተመሠረተ እንደሆነ የሚገልጽ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት እባክህ ከገጽ 213-215 ላይ የሚገኘውን ተጨማሪ ክፍል ተመልከት።