የጥናት ርዕስ 29
መሪያችንን ኢየሱስን ደግፉ
“ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጥቶኛል።”—ማቴ. 28:18
መዝሙር 13 ምሳሌያችን የሆነው ክርስቶስ
ማስተዋወቂያa
1. በዛሬው ጊዜ የይሖዋ ፈቃድ ምንድን ነው?
በዛሬው ጊዜ የአምላክ ፈቃድ የመንግሥቱ ምሥራች በመላው ምድር እንዲሰበክ ነው። (ማር. 13:10፤ 1 ጢሞ. 2:3, 4) ሥራው የይሖዋ ነው፤ ይህ ሥራ በጣም አስፈላጊ ከመሆኑ የተነሳ ይሖዋ የሥራው ኃላፊ አድርጎ የሾመው የሚወደውን ልጁን ነው። ብቃት ያለው መሪ በሆነው በኢየሱስ አመራር ሥር፣ መጨረሻው ከመምጣቱ በፊት የስብከቱ ሥራ ይሖዋ በሚፈልገው መጠን እንደሚከናወን እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—ማቴ. 24:14
2. በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን?
2 ኢየሱስ መንፈሳዊ ምግብ ለማቅረብና ተከታዮቹን በታሪክ ውስጥ ታይቶ ለማይታወቅ የስብከት ዘመቻ ለማደራጀት ‘ታማኝና ልባም ባሪያን’ እየተጠቀመ ያለው እንዴት እንደሆነ በዚህ ርዕስ ውስጥ እንመለከታለን። (ማቴ. 24:45) በተጨማሪም እያንዳንዳችን ኢየሱስን እና ታማኙን ባሪያ ለመደገፍ ምን ማድረግ እንደምንችል እናያለን።
ኢየሱስ የስብከቱን ሥራ እየመራ ነው
3. ኢየሱስ ምን ሥልጣን ተሰጥቶታል?
3 ኢየሱስ የስብከቱን ሥራ እየመራ ነው። ይህን እንዴት እናውቃለን? ወደ ሰማይ ከማረጉ ከጥቂት ጊዜ በፊት ኢየሱስ በገሊላ በሚገኝ አንድ ተራራ ላይ ከተወሰኑ ታማኝ ተከታዮቹ ጋር ተገናኝቶ ነበር። በዚህ ወቅት “ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጥቶኛል” አላቸው። ቀጥሎ ምን እንዳላቸው ልብ በሉ፦ “ስለዚህ ሂዱና ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን ደቀ መዛሙርት አድርጉ።” (ማቴ. 28:18, 19) ከዚህ መረዳት እንደሚቻለው ኢየሱስ የተሰጠው አንዱ ሥልጣን የስብከቱን ሥራ የመምራት ኃላፊነት ነው።
4. ኢየሱስ በዛሬው ጊዜም የስብከቱን ሥራ እየመራው እንደሆነ እንዴት እናውቃለን?
4 ኢየሱስ የስብከቱና ደቀ መዛሙርት የማድረጉ ሥራ ‘በሁሉም ብሔራት’ እንደሚከናወን እንዲሁም እሱ ‘እስከ ሥርዓቱ መደምደሚያ ድረስ ሁልጊዜ ከተከታዮቹ ጋር እንደሚሆን’ ተናግሯል። (ማቴ. 28:20) እነዚህ አገላለጾች የስብከቱ ሥራ በኢየሱስ አመራር ሥር እስከ ዘመናችን ድረስ እንደሚቀጥል ያሳያሉ።
5. ለመዝሙር 110:3 ፍጻሜ የበኩላችንን አስተዋጽኦ እያበረከትን ያለነው እንዴት ነው?
5 ኢየሱስ በሥርዓቱ መደምደሚያ ላይ የሠራተኞች እጥረት ይኖራል የሚል ስጋት አላደረበትም። ምክንያቱም መዝሙራዊው የተናገረው የሚከተለው ትንቢት እንደሚፈጸም ያውቅ ነበር፦ “ወደ ጦርነት በምትዘምትበት ቀን ሕዝብህ በገዛ ፈቃዱ ራሱን ያቀርባል።” (መዝ. 110:3) በስብከቱ ሥራ የምትካፈል ከሆነ ኢየሱስንና ታማኙን ባሪያ እየደገፍክ እንዲሁም ለዚህ ትንቢት ፍጻሜ የበኩልህን አስተዋጽኦ እያበረከትክ ነው። ሥራው ወደፊት እየገሰገሰ ነው፤ ሆኖም አንዳንድ ተፈታታኝ ሁኔታዎች አሉ።
6. በዛሬው ጊዜ የመንግሥቱ ሰባኪዎች የሚያጋጥማቸው አንዱ ተፈታታኝ ሁኔታ ምንድን ነው?
6 የመንግሥቱ ሰባኪዎች የሚያጋጥማቸው አንዱ ተፈታታኝ ሁኔታ ተቃውሞ ነው። ከሃዲዎች፣ የሃይማኖት መሪዎችና ፖለቲከኞች ብዙ ሰዎች ስለ ሥራችን የተሳሳተ አመለካከት እንዲኖራቸው አድርገዋል። ዘመዶቻችን፣ የምናውቃቸው ሰዎችና የሥራ ባልደረቦቻችን በዚህ ፕሮፓጋንዳ ተታለው ይሖዋን ማገልገላችንን እና መስበካችንን እንድናቆም ጫና ሊያሳድሩብን ይችላሉ። በአንዳንድ አገሮች ውስጥ ጠላቶቻችን ወንድሞቻችንን ያስፈራሯቸዋል፤ ጥቃት ይሰነዝሩባቸዋል፤ አልፎ ተርፎም እስር ቤት ያስገቧቸዋል። ሰዎች እንዲህ ማድረጋቸው አያስገርመንም። ምክንያቱም ኢየሱስ “በስሜ ምክንያት በሕዝቦች ሁሉ ዘንድ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ” በማለት ተንብዮአል። (ማቴ. 24:9) ሰዎች የሚጠሉን መሆኑ ራሱ የይሖዋ ሞገስ እንዳለን የሚያሳይ ማስረጃ ነው። (ማቴ. 5:11, 12) ከዚህ ተቃውሞ በስተ ጀርባ ያለው ዲያብሎስ ነው። ሆኖም የኢየሱስ ኃይል ከዲያብሎስ በእጅጉ ይበልጣል! በኢየሱስ እርዳታ ምሥራቹ ለሁሉም ብሔራት እየተዳረሰ ነው። ይህን የሚያሳዩ ማስረጃዎች አሉ።
7. ራእይ 14:6, 7 እየተፈጸመ እንደሆነ የሚያሳይ ምን ማስረጃ ተመልክተሃል?
7 ምሥራቹን ስንሰብክ የሚያጋጥመን ሌላው ተፈታታኝ ሁኔታ የቋንቋ ልዩነት ነው። ኢየሱስ ለሐዋርያው ዮሐንስ ባሳየው ራእይ ላይ በዘመናችን ምሥራቹ ይህን እንቅፋት እንደሚያሸንፍ ተንብዮአል። (ራእይ 14:6, 7ን አንብብ።) ይህ ትንቢት እየተፈጸመ ያለው እንዴት ነው? በተቻለ መጠን ብዙ ሰዎች የመንግሥቱን መልእክት እንዲሰሙ አጋጣሚ እየሰጠናቸው ነው። በዛሬው ጊዜ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ሰዎች jw.org በተባለው ድረ ገጻችን ላይ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ማንበብ ይችላሉ፤ ምክንያቱም በድረ ገጹ ላይ ከ1,000 በሚበልጡ ቋንቋዎች መረጃ ማግኘት ይቻላል! ደቀ መዛሙርት ለማድረግ የምንጠቀምበት ዋነኛ የማስተማሪያ መሣሪያ የሆነው ለዘላለም በደስታ ኑር! የተባለው መጽሐፍ ከ700 በሚበልጡ ቋንቋዎች እንዲተረጎም ፈቃድ ተሰጥቷል! ከዚህም ሌላ መስማት ለተሳናቸውና ለዓይነ ስውራን በቪዲዮና በብሬይል አማካኝነት መንፈሳዊ ምግብ እየቀረበ ነው። በእርግጥም የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ሲፈጸሙ እየተመለከትን ነው። “ከብሔራት ቋንቋዎች ሁሉ የተውጣጡ” ሰዎች ‘ንጹሑን ቋንቋ’ ማለትም የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት እየተማሩ ነው። (ዘካ. 8:23፤ ሶፎ. 3:9) ይህ ሁሉ እየተከናወነ ያለው ብቃት ያለው መሪ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ እየመራን ስለሆነ ነው።
8. የስብከቱ ሥራችን እስካሁን ምን ውጤት አስገኝቷል?
8 በዛሬው ጊዜ በ240 አገሮች የሚገኙ ከ8,000,000 የሚበልጡ ሰዎች በይሖዋ ድርጅት ውስጥ ታቅፈዋል፤ በየዓመቱ ደግሞ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ይጠመቃሉ! ከቁጥሩ ይበልጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ግን እነዚህ አዳዲስ ደቀ መዛሙርት “አዲሱን ስብዕና” መልበሳቸው ማለትም ግሩም መንፈሳዊ ባሕርያትን ማዳበራቸው ነው። (ቆላ. 3:8-10) ብዙዎች የሥነ ምግባር ብልግናን፣ ዓመፅን፣ ጭፍን ጥላቻንና ብሔራዊ ስሜትን አስወግደዋል። በኢሳይያስ 2:4 ላይ የሚገኘው “ከእንግዲህ ወዲህ ጦርነት አይማሩም” የሚለው ትንቢት እየተፈጸመ ነው። አዲሱን ስብዕና ለመልበስ ጥረት ስናደርግ ሰዎች ወደ አምላክ ድርጅት እንዲሳቡ እናደርጋለን፤ እንዲሁም መሪያችንን ክርስቶስ ኢየሱስን እንደምንከተል እናሳያለን። (ዮሐ. 13:35፤ 1 ጴጥ. 2:12) ይህ ሁሉ የሆነው በአጋጣሚ አይደለም። ኢየሱስ የሚያስፈልገንን እርዳታ ስለሚሰጠን ነው።
ኢየሱስ ባሪያ ሾሟል
9. በማቴዎስ 24:45-47 ላይ ስለ መጨረሻው ዘመን ምን ትንቢት ተነግሯል?
9 ማቴዎስ 24:45-47ን አንብብ። ኢየሱስ በመጨረሻው ዘመን መንፈሳዊ ምግብ የሚያቀርብ “ታማኝና ልባም ባሪያ” እንደሚሾም ትንቢት ተናግሯል። ስለዚህ ይህ ባሪያ በዘመናችን ተግቶ እንደሚሠራ እንጠብቃለን። ደግሞም ይህ እውነት መሆኑ ታይቷል። መሪያችን ለአምላክ ሕዝቦችና ፍላጎት ላላቸው ሰዎች ‘በተገቢው ጊዜ መንፈሳዊ ምግብ’ እንዲሰጣቸው ጥቂት ቅቡዓን ወንዶችን ያቀፈ አንድ ቡድን ሾሟል። እነዚህ ወንዶች በሌሎች እምነት ላይ ለማዘዝ አይሞክሩም። (2 ቆሮ. 1:24) ከዚህ ይልቅ የሕዝቡ “መሪና አዛዥ” ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሆነ ይገነዘባሉ።—ኢሳ. 55:4
10. በሥዕላዊ መግለጫው ላይ ከሚታዩት ጽሑፎች መካከል ወደ ዘላለም ሕይወት በሚወስደው መንገድ ላይ እንድትጓዝ የረዳህ የትኛው ነው?
10 ከ1919 አንስቶ ታማኙ ባሪያ የተለያዩ ጽሑፎችን በማዘጋጀት ለእውነት ፍላጎት ያሳዩ ሰዎች ገንቢ የሆነውን መንፈሳዊ ምግብ ለመጀመሪያ ጊዜ እንዲቀምሱ አድርጓል። በ1921 ታማኙ ባሪያ፣ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች መሠረታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችን እንዲማሩ ለመርዳት የአምላክ በገና (እንግሊዝኛ) የተባለውን መጽሐፍ አዘጋጀ። ዘመኑ ሲለወጥ ደግሞ ሌሎች ጽሑፎች ተዘጋጅተዋል። አንተስ የሰማዩን አባታችንን እንድታውቀውና እንድትወደው የረዳህ የትኛው ጽሑፍ ነው? “እግዚአብሔር እውነተኛ ይሁን፣” ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራው እውነት፣ በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ፣ ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት፣ ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው?፣ መጽሐፍ ቅዱስ ምን ያስተምረናል? ወይስ በቅርቡ የወጣው ለዘላለም በደስታ ኑር! የተባለው መጽሐፍ? እነዚህ ጽሑፎች በሙሉ የተዘጋጁት ሰዎችን ደቀ መዛሙርት ለማድረግ እንዲረዱን ታስበው ነው። ሁሉም በወጡበት ወቅት ጠቃሚ አገልግሎት አበርክተዋል።
11. ሁላችንም መንፈሳዊ ምግብ ማግኘታችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
11 ጠንካራ መንፈሳዊ ምግብ የሚያስፈልጋቸው አዲሶች ብቻ አይደሉም። ሁላችንም ያስፈልገናል። ሐዋርያው ጳውሎስ “ጠንካራ ምግብ [ለጎልማሳ] ሰዎች ነው” በማለት ጽፏል። አክሎም ጳውሎስ ከመጽሐፍ ቅዱስ ያገኘነውን ትምህርት በሥራ ላይ ማዋላችን “ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር መለየት” እንድንችል እንደሚረዳን ገልጿል። (ዕብ. 5:14) የሰዎች ሥነ ምግባር እጅግ ባዘቀጠበት በዚህ ዘመን በይሖዋ መሥፈርቶች መመራት ተፈታታኝ ሊሆን ይችላል። ሆኖም ኢየሱስ ገንቢ የሆነ መንፈሳዊ ምግብ በማቅረብ የሚያስፈልገንን ብርታት እንድናገኝ ያደርጋል። የዚህ ምግብ ምንጭ በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፈው መጽሐፍ ቅዱስ ነው። ታማኙ ባሪያ በኢየሱስ አመራር ሥር ሆኖ ይህን ምግብ ያዘጋጃል እንዲሁም ያከፋፍላል።
12. እንደ ኢየሱስ የአምላክን ስም እንደምናከብር ያሳየነው እንዴት ነው?
12 እንደ ኢየሱስ ሁሉ እኛም ለአምላክ ስም የሚገባውን ክብር እንሰጣለን። (ዮሐ. 17:6, 26) ለምሳሌ በ1931 “የይሖዋ ምሥክሮች” የሚለውን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ስም መጠቀም ጀምረናል፤ በዚህ መንገድ ለአምላክ ስም ትልቅ ቦታ እንደምንሰጥና በእሱ ስም መታወቅ እንደምንፈልግ አሳይተናል። በተጨማሪም ከዚያ ዓመት የጥቅምት ወር አንስቶ መለኮታዊው ስም በእያንዳንዱ የመጠበቂያ ግንብ እትም ሽፋን ላይ መውጣት ጀመረ። ከዚህም ሌላ አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ስም በቃሉ ውስጥ በተገቢው ቦታ ሁሉ እንዲመለስ አድርጓል። እንዲህ በማድረግ፣ የአምላክን ስም ከብዙዎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞቻቸው ካወጡት የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት በእጅጉ የተለየን መሆናችንን አሳይተናል።
ኢየሱስ ተከታዮቹን አደራጅቷል
13. ኢየሱስ በዛሬው ጊዜ ‘በታማኝና ልባም ባሪያ’ እየተጠቀመ እንዳለ የሚያሳምንህ ምንድን ነው? (ዮሐንስ 6:68)
13 ኢየሱስ ‘በታማኝና ልባም ባሪያ’ አማካኝነት በምድር ላይ ንጹሕ አምልኮን የሚያስፋፋ አስደናቂ ድርጅት አቋቁሟል። ስለዚህ ድርጅት ምን ይሰማሃል? ምናልባት እንደ ሐዋርያው ጴጥሮስ ዓይነት ስሜት ይሰማህ ይሆናል፤ ጴጥሮስ ለኢየሱስ “ወደ ማን እንሄዳለን? አንተ የዘላለም ሕይወት ቃል አለህ” ብሎት ነበር። (ዮሐ. 6:68) ማናችንስ ብንሆን ከይሖዋ ድርጅት ጋር ባንተዋወቅ ኖሮ ዛሬ የት እንገኝ ነበር? ክርስቶስ በዚህ ድርጅት አማካኝነት የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ እንድናገኝ ያደርጋል። በተጨማሪም አገልግሎታችንን ውጤታማ በሆነ መንገድ እንድናከናውን ያሠለጥነናል። ከዚህም ሌላ ይሖዋን ለማስደሰት የሚያስችለንን “አዲሱን ስብዕና” እንድንለብስ ይረዳናል።—ኤፌ. 4:24
14. የይሖዋ ድርጅት ክፍል በመሆንህ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት ምን ጥቅም አግኝተሃል?
14 ኢየሱስ በአስቸጋሪ ጊዜ ጥበብ የሚንጸባረቅበት መመሪያ ይሰጠናል። የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በተከሰተበት ወቅት እንዲህ ያለው መመሪያ ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆነ ተመልክተናል። በዓለም ላይ ያሉ ብዙ ሰዎች ምን ማድረግ እንዳለባቸው ግራ በተጋቡበት ወቅት ኢየሱስ ደህንነታችንን ለመጠበቅ የሚረዳን ግልጽ መመሪያ እንድናገኝ አድርጓል። ከቤት ስንወጣ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ እንድናደርግ እንዲሁም አካላዊ ርቀታችንን እንድንጠብቅ ተበረታተን ነበር። ሽማግሌዎች በጉባኤ ውስጥ ካሉ አስፋፊዎች ሁሉ ጋር አዘውትረው እንዲነጋገሩ እንዲሁም ለአስፋፊዎች ቁሳዊና መንፈሳዊ ፍላጎት ትኩረት እንዲሰጡ ማሳሰቢያ ተሰጥቷቸው ነበር። (ኢሳ. 32:1, 2) ከዚህም ሌላ በበላይ አካሉ ሪፖርቶች አማካኝነት ተጨማሪ መመሪያና ማበረታቻ አግኝተናል።
15. በወረርሽኙ ወቅት ስለ ስብሰባዎችና ስለ ስብከቱ ሥራ ምን መመሪያ ተሰጥቶናል? ይህስ ምን ውጤት አስገኝቷል?
15 በወረርሽኙ ወቅት የጉባኤ ስብሰባዎች ማድረግና በስብከቱ ሥራ መካፈል ስለምንችልበት መንገድም ግልጽ መመሪያ አግኝተናል። ወዲያውኑ የጉባኤ፣ የወረዳና የክልል ስብሰባዎችን በኢንተርኔት አማካኝነት ማድረግ ጀመርን። በተጨማሪም አገልግሎታችንን በዋነኝነት በደብዳቤና በስልክ አማካኝነት ማከናወን ጀመርን። ይሖዋም ጥረታችንን ባርኮልናል። በርካታ ቅርንጫፍ ቢሮዎች የአስፋፊዎች ቁጥር በእጅጉ እንደጨመረ ሪፖርት አድርገዋል። እንዲያውም ብዙ ወንድሞችና እህቶች በዚህ ወቅት አበረታች ተሞክሮዎችን አግኝተዋል።—“ይሖዋ የስብከቱን ሥራችንን ባርኮታል” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።
16. ስለ ምን ነገር እርግጠኞች መሆን እንችላለን?
16 አንዳንዶች ድርጅቱ ከወረርሽኙ ጋር በተያያዘ ከልክ በላይ ጥብቅ እንደሆነ ተሰምቷቸው ሊሆን ይችላል። ሆኖም የተሰጠን መመሪያ ጥበብ የሚንጸባረቅበት እንደሆነ በተደጋጋሚ ታይቷል። (ማቴ. 11:19) ኢየሱስ ሕዝቡን ፍቅር በሚንጸባረቅበት መንገድ እየመራ ያለው እንዴት እንደሆነ ስናሰላስል፣ ነገ ምንም ነገር ቢመጣ ይሖዋና የሚወደው ልጁ አብረውን እንደሚሆኑ እርግጠኞች እንድንሆን ያደርገናል።—ዕብራውያን 13:5, 6ን አንብብ።
17. በኢየሱስ አመራር ሥር መሥራት በመቻልህ ምን ይሰማሃል?
17 በኢየሱስ አመራር ሥር መሥራት በመቻላችን ምንኛ ተባርከናል! ባሕል፣ ዜግነትና ቋንቋ በማይገድበው ድርጅት ውስጥ ታቅፈናል። የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ እናገኛለን፤ እንዲሁም የስብከቱን ሥራ ለማከናወን በቂ ሥልጠና ይሰጠናል። በተጨማሪም በግለሰብ ደረጃ አዲሱን ስብዕና እንድንለብስና እርስ በርስ እንድንዋደድ እየተማርን ነው። በእርግጥም በመሪያችን በኢየሱስ የምንኩራራበት በቂ ምክንያት አለን!
መዝሙር 16 ያህ ልጁን ሾሟል አወድሱት
a በዛሬው ጊዜ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ወንዶች፣ ሴቶችና ልጆች ምሥራቹን በቅንዓት እየሰበኩ ነው። አንተስ ከእነሱ መካከል ትገኛለህ? ከሆነ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አመራር ሥር ሆነህ እየሠራህ ነው ማለት ነው። ኢየሱስ በዘመናችን የስብከቱን ሥራ እየመራው መሆኑን የሚያሳዩ ማስረጃዎችን በዚህ ርዕስ ውስጥ እንመለከታለን። በዚህ ሐሳብ ላይ ማሰላሰላችን በክርስቶስ አመራር ሥር ሆነን ይሖዋን ማገልገላችንን ለመቀጠል ያነሳሳናል።