በሕይወት ውስጥ እውነተኛ ስኬት ማግኘት
“ያሰብኸው ይቃናል፤ ይሳካልም።”—ኢያሱ 1:8
1, 2. (ሀ) ብዙ ሰዎች ስኬትን የሚገልጹት እንዴት ነው? (ለ) ለስኬት ያለህን አመለካከት መገምገም የምትችለው እንዴት ነው?
አንድ ሰው በሕይወቱ ውስጥ ስኬታማ ሆኗል ሲባል ምን ማለት ነው? ይህን ጥያቄ የተለያዩ ሰዎችን ብትጠይቅ የምታገኘው መልስ የተለያየ ነው። ለምሳሌ ብዙዎች ስኬት የሚሉት ዳጎስ ያለ ገንዘብ ማግኘትን፣ በተሰማሩበት ሙያ አንቱ መባልን ወይም በትምህርት ላቅ ያለ ውጤት ማስመዝገብን ነው። ሌሎች ደግሞ ከሰዎች ጋር ያላቸውን ግንኙነት ይኸውም ከቤተሰባቸው፣ ከጓደኞቻቸው ወይም ከሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር በጥሩ ሁኔታ መግባባት መቻላቸውን እንደ ስኬት ይቆጥሩታል። አምላክን የሚያገለግል አንድ ሰው ስኬትን በጉባኤ ውስጥ የኃላፊነት ቦታ ከማግኘት ወይም በአገልግሎት ስኬታማ ከመሆን ጋር አያይዞ ይገልጸው ይሆናል።
2 ስለ ስኬት ያለህን አመለካከት ለማወቅ፣ ተሳክቶላቸዋል የምትላቸውን በሌላ አባባል በአድናቆትና በአክብሮት የምትመለከታቸውን የጥቂት ሰዎች ስም ዝርዝር ጻፍ። እነዚህ ሰዎች ጎልቶ የሚታይ ምን የጋራ መለያ አላቸው? ሀብታም ወይም ዝነኛ ናቸው? ትልቅ ቦታ አላቸው? ለእነዚህ ጥያቄዎች የምትሰጠው መልስ በልብህ ውስጥ ምን እንዳለ በግልጽ ያሳያል፤ እንዲሁም በምታደርጋቸው ምርጫዎችና በምትከታተላቸው ግቦች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል።—ሉቃስ 6:45
3. (ሀ) ኢያሱ ስኬታማ እንዲሆን ምን ማድረግ ነበረበት? (ለ) በዚህ የጥናት ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን?
3 ከሁሉ በላይ ትልቅ ግምት ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ ይሖዋ ስኬታማ ሰው እንደሆንኩ አድርጎ ይመለከተኛል? የሚለው ነው፤ ምክንያቱም በሕይወት መኖራችን የተመካው በእሱ ዘንድ ተቀባይነት በማግኘታችን ላይ ነው። ይሖዋ እስራኤላውያንን ወደ ተስፋይቱ ምድር እየመራ የማስገባት ከባድ ኃላፊነት ለኢያሱ በሰጠው ጊዜ የሙሴን ሕግ “ቀንም ሆነ ሌት” እንዲያነብና የተጻፈውን በጥንቃቄ እንዲጠብቅ ነግሮታል። አምላክ “ይህን ካደረግህ ያሰብኸው ይቃናል፤ ይሳካልም” በማለት ዋስትና ሰጥቶታል። (ኢያሱ 1:7, 8) ደግሞም ኢያሱ ተሳክቶለታል። የእኛስ ሁኔታ እንዴት ነው? ስለ ስኬት ያለን አመለካከት አምላክ ካለው አመለካከት ጋር የሚስማማ መሆን አለመሆኑን ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው? መልሱን ለማግኘት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ የሁለት ሰዎችን ሕይወት እንመልከት።
ሰለሞን በሕይወቱ ስኬታማ ነበር?
4. ሰለሞን ስኬታማ ነበር ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው?
4 ሰለሞን በብዙ መንገዶች በዓይነቱ ልዩ የሆነ ስኬት አግኝቷል። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ለበርካታ ዓመታት ይሖዋን ይፈራና ይታዘዝ ነበር፤ እሱም በእጅጉ ባርኮታል። ሰለሞን የፈለገውን እንዲጠይቅ ይሖዋ በነገረው ጊዜ ንጉሡ ሕዝቡን መምራት የሚችልበት ጥበብ እንዲሰጠው መጠየቁን አስታውስ። በዚህ ጊዜ አምላክ ጥበብና ሀብት በመስጠት ባርኮታል። (1 ነገሥት 3:10-14ን አንብብ።) “የሰሎሞን ጥበብ ከምሥራቅ ሰዎች ሁሉ ጥበብ በጣም የላቀ ከግብፅም ጥበብ ሁሉ የበለጠ ነበር።” ዝናውም “በዙሪያው ባሉት አሕዛብ ሁሉ” ዘንድ ለመታወቅ በቅቷል። (1 ነገ. 4:30, 31) ሀብቱን ካነሳን በየዓመቱ የሚገባለት ወርቅ ብቻ 25 ቶን ገደማ ይመዝን ነበር! (2 ዜና 9:13) በዲፕሎማሲ፣ በግንባታና በንግድ ረገድ የላቀ ጥበብ ነበረው። አዎ፣ ሰለሞን በአምላክ ዘንድ ጥሩ አቋም ይዞ በተመላለሰበት ጊዜ ሁሉ ስኬታማ ለመሆን በቅቷል።—2 ዜና 9:22-24
5. ሰለሞን በአምላክ ዘንድ ስኬታማ ስለሆኑ ሰዎች የደረሰበት ድምዳሜ ምንድን ነው?
5 ሰለሞን በመክብብ መጽሐፍ ላይ ያሰፈረው ሐሳብ ጥሩ ውጤትና ደስታ የሚያገኙት፣ ሀብት ወይም ትልቅ ቦታ ያላቸው ሰዎች ብቻ ናቸው የሚል የተሳሳተ አመለካከት እንዳልነበረው ያሳያል። እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ለሰዎች፣ በሕይወት እያሉ ደስ ከመሰኘትና መልካምን ነገር ከማድረግ የተሻለ ነገር እንደሌለ ዐወቅሁ። ሰው ሁሉ ይበላና ይጠጣ ዘንድ፣ በሚደክምበትም ሁሉ ርካታን ያገኝ ዘንድ ይህ የእግዚአብሔር ችሮታ ነው።” (መክ. 3:12, 13) እንዲህ ያሉ ደስታ የሚያስገኙ ነገሮች እውነተኛ ትርጉም የሚኖራቸው አንድ ሰው በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ካገኘ ይኸውም ከአምላክ ጋር ጥሩ ግንኙነት ካለው እንደሆነ ተገንዝቦ ነበር። በእርግጥም ሰለሞን እንዲህ ማለቱ ተገቢ ነው፦ “እነሆ፤ ሁሉ ነገር ከተሰማ ዘንድ፣ የነገሩ ሁሉ ድምዳሜ ይህ ነው፤ እግዚአብሔርን ፍራ፤ ትእዛዛቱንም ጠብቅ፤ ይህ የሰው ሁለንተናዊ ተግባሩ ነውና።”—መክ. 12:13
6. ሰለሞን የተወው ምሳሌ እውነተኛ ስኬትን መለካት የምንችልበት ምን ጠቃሚ ሐሳብ ይዟል?
6 ሰለሞን ለብዙ ዓመታት አምላክን በመፍራት ኖሯል። ቅዱሳን መጻሕፍት ሰለሞን “እግዚአብሔርን ይወድ ነበር፤ በአባቱ በዳዊት ሥርዐትም ይሄድ ነበር” በማለት ይናገራሉ። (1 ነገ. 3:3) በእርግጥ ይህ ስኬት ነው ቢባል አትስማማም? ሰለሞን አምላክ በሰጠው መመሪያ መሠረት ለእውነተኛው አምልኮ የሚያገለግል ዕጹብ ድንቅ ቤተ መቅደስ የገነባ ከመሆኑም በላይ ሦስት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን ጽፏል። እኛም ተመሳሳይ ነገር እናደርጋለን ብለን ባንጠብቅም ሰለሞን ለአምላክ ታማኝ በነበረበት ወቅት የተወው ምሳሌ እውነተኛ ስኬት ምን እንደሆነ ለመመዘን ሊረዳን ይችላል፤ ይህ ደግሞ ስኬታማ እንድንሆን ያስችለናል። በዚህ ረገድ ዛሬ ያሉ አብዛኞቹ ሰዎች የስኬት መለኪያ አድርገው የሚመለከቷቸው ነገሮች ማለትም ሀብት፣ ጥበብ፣ ሥልጣንና ዝና ከንቱ እንደሆኑ ሰለሞን በመንፈስ መሪነት መጻፉን ልብ በል። እነዚህ ነገሮች በእርግጥ ባዶ ስለሆኑ ‘ነፋስን እንደ መከተል’ ይቆጠራሉ። ባለጸጋ ለመሆን የሚቋምጡ በርካታ ሰዎች ተጨማሪ ነገር ለማግኘት ሲፈልጉ አልተመለከትክም? ደግሞም አብዛኛውን ጊዜ ስላሏቸው ነገሮች ይጨነቃሉ። ከዚህም በላይ አንድ ቀን ሀብታቸው ለሌላ ሰው መተላለፉ አይቀርም።—መክብብ 2:8-11, 17፤ 5:10-12ን አንብብ።
7, 8. ሰለሞን ታማኝ ሳይሆን የቀረው እንዴት ነው? ይህስ ምን አስከተለበት?
7 በተጨማሪም ሰለሞን የኋላ ኋላ አምላክን በታማኝነት መታዘዙን አቁሟል። የአምላክ ቃል እንዲህ ይላል፦ “ሰሎሞን በሸመገለ ጊዜ ሚስቶቹ ልቡን ወደ ሌሎች አማልክት መለሱት፤ የአባቱ የዳዊት ልብ እንደ ተገዛ ሁሉ፣ በፍጹም ልቡ ለአምላኩ ለእግዚአብሔር አልተገዛም። . . . ስለዚህ ሰሎሞን በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ድርጊት ፈጸመ።”—1 ነገ. 11:4-6
8 ሰለሞን ተገቢ ያልሆነ ድርጊት በመፈጸሙ ይሖዋ እንዲህ ብሎታል፦ “ያዘዝሁህን ኪዳኔንና ሥርዐቴንም ባለመጠበቅህ፣ መንግሥትህን ከአንተ ወስጄ ከአገልጋዮችህ ለአንዱ እሰጠዋለሁ።” (1 ነገ. 11:11) ይህ እንዴት ያሳዝናል! ሰለሞን በብዙ መንገዶች ስኬታማ የነበረ ቢሆንም ከጊዜ በኋላ ይሖዋን አሳዝኗል። ሰለሞን በአንድ ሰው ሕይወት ውስጥ ትልቅ ቦታ በሚሰጠው ወሳኝ ጉዳይ ማለትም ለአምላክ ታማኝ በመሆን ረገድ ስኬታማ መሆን አልቻለም። ሁላችንም ‘ከሰለሞን ሕይወት የማገኘው ትምህርት ስኬታማ ለመሆን ቁርጥ ውሳኔ እንዳደርግ ያነሳሳኛል?’ ብለን ራሳችንን መጠየቅ እንችላለን።
ስኬታማ ሕይወት የመራ ሰው
9. ከዓለም መለኪያ አንጻር ጳውሎስ ስኬታማ ነበር? አብራራ።
9 የሐዋርያው ጳውሎስ ሕይወት ከንጉሥ ሰለሞን ሕይወት ፈጽሞ የተለየ ነው። ጳውሎስ ከዝሆን ጥርስ የተሠራ ዙፋን አልነበረውም ወይም ነገሥታት ባሉበት ግብዣ ላይ አልተገኘም። ከዚህ ይልቅ የተራበበት፣ የተጠማበት፣ በብርድና በራቁትነት የተቆራመደበት ጊዜ ነበር። (2 ቆሮ. 11:24-27) ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን ከተቀበለ በኋላ ጳውሎስ በአይሁድ ሃይማኖት ውስጥ የነበረውን የክብር ቦታ አጥቷል። ደግሞም የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች ይጠሉት ነበር። ጳውሎስ ታስሯል፣ ተገርፏል፣ በበትር ተደብድቧል እንዲሁም በድንጋይ ተወግሯል። እሱና ክርስቲያን ባልንጀሮቹ እንደተሰደቡ፣ ለስደት እንደተዳረጉና ስማቸው እንደጠፋ ተናግሯል። “እስከ አሁን ድረስ የዓለም ጉድፍና የሁሉ ነገር ጥራጊ እንደሆንን ተደርገን እንታያለን” ብሏል።—1 ቆሮ. 4:11-13
10. ጳውሎስ ስኬታማ መሆን የሚችልበትን አጋጣሚ ሳይጠቀምበት ቀርቷል ሊባል የሚችለው ከምን አንጻር ነው?
10 ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ሳኦል ተብሎ ይጠራ በነበረበት በወጣትነት ዕድሜው በርካታ ጥሩ አጋጣሚዎች ያሉት ይመስል ነበር። ከታወቀ ቤተሰብ የተወለደ ሊሆን የሚችለውና የተከበረ አስተማሪ በሆነው በገማልያል የተማረው ጳውሎስ “በእኔ ዕድሜ ካሉት ከብዙዎቹ የበለጠ በአይሁድ ሃይማኖት የላቀ እድገት እያደረግኩ ነበር” በማለት ጽፏል። (ገላ. 1:14) ሳኦል ዕብራይስጥና ግሪክኛ አቀላጥፎ መናገር ይችል የነበረ ከመሆኑም ሌላ ብዙ ሰዎች የሚመኟቸውን ጥቅሞችና መብቶች የሚያስገኝለት የሮም ዜግነት ነበረው። እንዲህ ያሉትን ዓለም እንደ ስኬት የሚቆጥራቸውን ነገሮች ለመከታተል መርጦ ቢሆን ኖሮ ላቅ ያለ ቦታና ሀብት የማግኘት አጋጣሚ ሊኖረው ይችል ነበር። እሱ ግን በሌሎች ሰዎች ዓይን ምናልባትም በአንዳንድ ዘመዶቹ አመለካከት ፍጹም ሞኝነት የሚመስል የሕይወት ጎዳና መርጧል። ለምን?
11. ጳውሎስ ትልቅ ዋጋ የሰጣቸው ነገሮች ምንድን ናቸው? ግቡ ምን ነበር? እንዲህ ያደረገውስ ለምንድን ነው?
11 ጳውሎስ ከሀብትና በሰዎች ዘንድ ዝናን ከማትረፍ ይልቅ ይሖዋን ይወድና በእሱ ዘንድ ተቀባይነት ማግኘት ይፈልግ ነበር። የእውነትን ትክክለኛ እውቀት ማግኘቱ ዓለም በአብዛኛው በንቀት የሚያያቸውን ነገሮች ማለትም ቤዛው ያለውን ዋጋ፣ ክርስቲያናዊ አገልግሎቱንና በሰማይ ሕይወት የማግኘት ተስፋውን ከፍ አድርጎ እንዲመለከት አስችሎታል። ጳውሎስ ገና ያልተቋጨ አንድ አወዛጋቢ ጉዳይ መኖሩን ተገንዝቧል። ሰይጣን፣ ሰዎች አምላክን እንዳያገለግሉ ማድረግ እችላለሁ ብሎ ተገዳድሯል። (ኢዮብ 1:9-11፤ 2:3-5) ጳውሎስ ምንም ዓይነት ፈተና ቢደርስበት ለአምላክ ታማኝ ለመሆን ይኸውም በእውነተኛው አምልኮ ለመጽናት ቆርጦ ነበር። ስኬትን በተመለከተ የጳውሎስ ግብ ይህ ነበር፤ ዓለም ግን ለዚህ ጉዳይ ምንም ቦታ አይሰጥም።
12. ተስፋህን በአምላክ ላይ ለመጣል የመረጥከው ለምንድን ነው?
12 አንተስ እንደ ጳውሎስ ቁርጥ አቋም አለህ? ታማኝ ሆኖ መኖር ሁልጊዜ ቀላል ባይሆንም እንዲህ ዓይነቱ አካሄድ የይሖዋን በረከትና በእሱ ዘንድ ተቀባይነት እንደሚያስገኝ እናውቃለን፤ ደግሞም አንድን ሰው በእርግጥ ስኬታማ ነው የሚያስብለው ይህ ነው። (ምሳሌ 10:22) እንዲህ ማድረጋችን በአሁኑ ጊዜ ይጠቅመናል፤ ወደፊት ደግሞ በረከት እንደሚያስገኝልን ጥርጥር የለውም። (ማርቆስ 10:29, 30ን አንብብ።) እንግዲያው ተስፋችንን “አስተማማኝነት በሌለው ሀብት ላይ ሳይሆን ለእኛ ደስታ ሲል ሁሉን ነገር አትረፍርፎ በሚሰጠን አምላክ ላይ” እንድንጥል የሚያደርግ በቂ ምክንያት አለን። ‘እውነተኛ የሆነውን ሕይወት አጥብቀን መያዝ እንችል ዘንድ በዚህ መንገድ ለራሳችን ውድ ሀብት እናከማቻለን፤ ይኸውም ለወደፊቱ ጊዜ የሚሆን መልካም መሠረት እንጥላለን።’ (1 ጢሞ. 6:17-19) አዎ ከመቶ፣ ከሺህ ወይም ከዚያ ከሚበልጡ ዓመታት በኋላ ያሳለፍነውን ጊዜ መለስ ብለን ስንመለከት “በእርግጥ ለእውነተኛ ስኬት የሚያበቃ የሕይወት ጎዳና መርጫለሁ!” እንደምንል የተረጋገጠ ነው።
ሀብትህ ባለበት
13. ኢየሱስ ሀብት ማከማቸትን አስመልክቶ ምን ምክር ሰጥቷል?
13 ኢየሱስ ሀብትን አስመልክቶ እንዲህ ብሏል፦ “ብል ሊበላው፣ ዝገት ሊያበላሸውና ሌባ ሰብሮ ገብቶ ሊሰርቀው በሚችልበት በምድር ላይ ለራሳችሁ ሀብት ማከማቸት ተዉ። ከዚህ ይልቅ ብል ሊበላው፣ ዝገት ሊያበላሸውና ሌባ ሰብሮ ገብቶ ሊሰርቀው በማይችልበት በሰማይ ለራሳችሁ ሀብት አከማቹ። ምክንያቱም ሀብትህ ባለበት ልብህም በዚያ ይሆናል።”—ማቴ. 6:19-21
14. በምድር ላይ ሀብት ማካበት ጥበብ የማይሆነው ለምንድን ነው?
14 አንድ ሰው በምድር ላይ ሊያካብት የሚችለው ሀብት በገንዘብ ብቻ አይወሰንም። በሌላ አባባል በሰዎች ዘንድ እንደ ስኬት የሚታዩትን፣ ሰለሞን የጠቀሳቸውን እንደ ክብር፣ ዝና ወይም ሥልጣን የመሳሰሉትን ነገሮች ሊያጠቃልል ይችላል። ኢየሱስ ዓለማዊ ሀብት ዘላቂ እንዳልሆነ በመጥቀስ ሰለሞን በመክብብ መጽሐፍ ላይ ከገለጸው ነጥብ ጋር የሚመሳሰል ሐሳብ ተናግሯል። እንዲህ ያለው ሀብት እንደሚጠፋና በቀላሉ ሊታጣ እንደሚችል በዙሪያህ ባለው ዓለም ሳትመለከት አትቀርም። ፕሮፌሰር ፍሬድሪክ ዴል ብሩነር ዓለም ስለሚሰጠው ሀብት እንዲህ በማለት ጽፈዋል፦ “ዝና አላፊ ጠፊ እንደሆነ የታወቀ ነው። ያለፈው ቅዳሜ እንደ ጀግና የታየው ሰው በቀጣዩ ወቅት ታሪክ ሆኖ ይረሳል። ዘንድሮ የተገኘው ትርፍ በቀጣዩ ዓመት በኪሳራ ይጠፋል። . . . [ኢየሱስ] የሰው ልጆችን ይወዳል። ሰዎች እየከሰመ የሚሄድ ክብር የሚያስከትለው የባዶነት ስሜት እንዳይደርስባቸው አሳስቧል። እንዲህ ዓይነቱ ክብር ዕድሜ የለውም። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ለሐዘን እንዲዳረጉ አይፈልግም። ‘ዓለም ቁንጮ የነበረን ሰው ምንጊዜም ወደታች መጣሉ አይቀርም።’” አብዛኞቹ ሰዎች በዚህ ሐሳብ የሚስማሙ ቢሆንም እውነታውን ለመቀበልና አኗኗራቸውን ለመለወጥ ፈቃደኛ የሚሆኑት ስንቶቹ ናቸው? አንተስ እንዲህ ለማድረግ ፈቃደኛ ነህ?
15. ጥረት ማድረግ ያለብን ምን ዓይነት ስኬት ለማግኘት ነው?
15 አንዳንድ የሃይማኖት መሪዎች ስኬታማ ለመሆን መጣጣር ስህተት እንደሆነና አንድ ሰው እንዲህ ዓይነቱን አካሄድ እርግፍ አድርጎ መተው እንዳለበት ያስተምራሉ። ይሁንና ኢየሱስ ስኬት ለማግኘት ጥረት ማድረግን ሙሉ በሙሉ እንዳላወገዘ ልብ በል። ከዚህ ይልቅ ደቀ መዛሙርቱ የጥረት አቅጣጫቸውን ለውጠው የማይጠፋ ‘ሀብትን በሰማይ ለማከማቸት’ ጥረት እንዲያደርጉ አበረታቷቸዋል። ዋነኛው ፍላጎታችን በይሖዋ ዓይን ስኬታማ ሆነን መገኘት ነው። ኢየሱስ የተናገረው ሐሳብ፣ ግብ አድርገን የምንከታተለውን ነገር የመምረጥ ነፃነት እንዳለን ያስገነዝበናል። እንደ እውነቱ ከሆነ የምንከታተለው በልባችን ውስጥ ያለውን ይኸውም ከፍ አድርገን የምንመለከተውን ነገር ነው።
16. በምን ነገር ላይ ሙሉ እምነት መጣል እንችላለን?
16 ይሖዋን የማስደሰት ልባዊ ፍላጎት ካለን እሱ ይህን እንደሚያይና የሚያስፈልጉንን ነገሮች እንደሚያሟላልን መተማመን እንችላለን። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዳጋጠመው ሁሉ እኛም ለጊዜው እንድንራብ ወይም እንድንጠማ ሊፈቅድ ይችላል። (1 ቆሮ. 4:11) ያም ሆኖ ኢየሱስ በሰጠው ጥበብ የታከለበት ምክር ላይ ሙሉ እምነት ልንጥል እንችላለን፦ “ስለዚህ ‘ምን እንበላለን?’ ወይም ‘ምን እንጠጣለን?’ ወይም ደግሞ ‘ምን እንለብሳለን?’ ብላችሁ ፈጽሞ አትጨነቁ። እነዚህ ነገሮች ሁሉ አሕዛብ አጥብቀው የሚፈልጓቸው ናቸው። በሰማይ የሚኖረው አባታችሁ እነዚህ ሁሉ እንደሚያስፈልጓችሁ ያውቃል። እንግዲያው ከሁሉ አስቀድማችሁ የአምላክን መንግሥትና ጽድቅ መፈለጋችሁን ቀጥሉ፤ እነዚህም ነገሮች ሁሉ ይሰጧችኋል።”—ማቴ. 6:31-33
በአምላክ ዘንድ ስኬታማ ሁኑ
17, 18. (ሀ) እውነተኛ ስኬት በምን ላይ የተመካ ነው? (ለ) ስኬት በምን ላይ የተመካ አይደለም?
17 ወሳኙ ጉዳይ ይህ ነው፦ እውነተኛ ስኬት ማግኘታችን የተመካው ባገኘናቸው ላቅ ያሉ ውጤቶች ወይም በዓለም ዘንድ ባለን ቦታ አይደለም። በተጨማሪም እውነተኛ ስኬት የሚለካው በክርስቲያናዊ ዝግጅት ውስጥ ባለን የኃላፊነት ቦታ አይደለም። ይሁንና እንዲህ ዓይነቱ በረከት ለስኬት መሠረት ከሚሆነው ነገር ጋር ሊዛመድ ይችላል፤ ይህ መሠረት ለአምላክ የምናሳየው ታዛዥነትና ታማኝነት ሲሆን አምላክ “መጋቢዎች ታማኝ ሆነው መገኘት ይጠበቅባቸዋል” በማለት ጉዳዩን ግልጽ አድርጎልናል። (1 ቆሮ. 4:2) ደግሞም በታማኝነት መጽናት አለብን። ኢየሱስ “እስከ መጨረሻው የጸና . . . እሱ ይድናል” ብሏል። (ማቴ. 10:22) መዳናችን ስኬት እንዳገኘን የሚያሳይ ማንም ሊያስተባብለው የማይችል ማስረጃ ነው ቢባል አትስማማም?
18 እስካሁን እንዳየነው ለአምላክ ታማኝ መሆን ትልቅ ቦታ ከማግኘት፣ ከትምህርት፣ ከሀብት ወይም በማኅበረሰቡ ውስጥ ካለን ቦታ ጋር የተያያዘ አይደለም፤ በተጨማሪም ታማኝነት ባለን እውቀት፣ ተሰጥኦ ወይም ችሎታ ላይ የተመካ አይደለም። ያለንበት ሁኔታ ምንም ይሁን ምን ለአምላክ ታማኝ መሆን እንችላለን። በመጀመሪያው መቶ ዘመን በአምላክ ሕዝቦች መካከል ሀብታሞችም ድሆችም ይገኙ ነበር። ጳውሎስ ሀብታም የሆኑትን “መልካም ነገር እንዲያደርጉ፣ በመልካም ሥራዎች ባለጸጋ እንዲሆኑ እንዲሁም ለጋሶችና ለማካፈል ፈቃደኞች እንዲሆኑ” መክሯቸዋል። ሀብታሞችም ሆኑ ድሆች “እውነተኛ የሆነውን ሕይወት አጥብቀው መያዝ” ይችላሉ። (1 ጢሞ. 6:17-19) ይህ ምክር ዛሬም ይሠራል። ሁላችንም ተመሳሳይ አጋጣሚ ተከፍቶልናል እንዲሁም ተመሳሳይ ኃላፊነት ተጥሎብናል፤ በታማኝነት መቀጠልና “በመልካም ሥራዎች ባለጸጋ” መሆን ይገባናል። እንዲህ ካደረግን በፈጣሪያችን ዘንድ ስኬታማ እንሆናለን፤ እንዲሁም እሱን እያስደሰትን እንዳለን ማወቃችን ደስታ ያስገኝልናል።—ምሳሌ 27:11
19. ስኬትን በተመለከተ ቁርጥ ውሳኔህ ምንድን ነው?
19 የሚያጋጥሙህን ሁኔታዎች ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር አትችል ይሆናል፤ ሆኖም ሁኔታዎቹን መወጣት የምትችልበትን መንገድ መቆጣጠር ትችላለህ። ያለህበት ሁኔታ ምንም ይሁን ምን ታማኝ ለመሆን ጥረት አድርግ። ደግሞም እንዲህ ያለ ጥረት ማድረግህ አያስቆጭም። ይሖዋ አሁንም ሆነ ለዘላለም አትረፍርፎ እንደሚባርክህ እርግጠኛ ሁን። ኢየሱስ ለቅቡዓን ክርስቲያኖች “እስከ ሞት ድረስም እንኳ ታማኝነትህን አስመሥክር፤ እኔም የሕይወትን አክሊል እሰጥሃለሁ” በማለት የተናገረውን ሐሳብ ፈጽሞ አትዘንጋ። (ራእይ 2:10) በእርግጥም ይህ እውነተኛ ስኬት ነው!