መሳፍንት
10 ከአቢሜሌክ በኋላ የዶዶ ልጅ፣ የፑሃ ልጅ የይሳኮር ሰው የሆነው ቶላ እስራኤልን ለማዳን ተነሳ።+ እሱም በኤፍሬም ተራራማ አካባቢዎች በምትገኘው በሻሚር ይኖር ነበር። 2 በእስራኤልም ውስጥ ለ23 ዓመት ፈራጅ ሆኖ አገለገለ። ከዚያም ሞተ፤ በሻሚርም ተቀበረ።
3 ከእሱም በኋላ ጊልያዳዊው ያኢር ተነሳ፤ በእስራኤልም ውስጥ ለ22 ዓመት ፈራጅ ሆኖ አገለገለ። 4 ያኢር በ30 አህዮች የሚጋልቡ 30 ወንዶች ልጆች ነበሩት፤ እነሱም እስከ ዛሬ ድረስ ሃዎትያኢር+ ተብለው የሚጠሩ 30 ከተሞች ነበሯቸው፤ ከተሞቹም የሚገኙት በጊልያድ ምድር ነው። 5 ከዚያም ያኢር ሞተ፤ በቃሞንም ተቀበረ።
6 እስራኤላውያንም በይሖዋ ፊት እንደገና መጥፎ ነገር አደረጉ፤+ ባአልን፣+ የአስታሮትን ምስሎች፣ የአራምን* አማልክት፣ የሲዶናን አማልክት፣ የሞዓብን አማልክት፣+ የአሞናውያንን አማልክትና+ የፍልስጤማውያንን አማልክት+ ማገልገል ጀመሩ። ይሖዋን ተዉት፤ እሱንም አላገለገሉም። 7 የይሖዋም ቁጣ በእስራኤል ላይ ነደደ፤ እነሱንም ለፍልስጤማውያንና ለአሞናውያን ሸጣቸው።+ 8 ስለሆነም በዚያ ዓመት እስራኤላውያንን አደቀቋቸው፤ ክፉኛም ጨቆኗቸው፤ ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ በጊልያድ በሚገኘው በአሞራውያን ምድር የነበሩትን እስራኤላውያን በሙሉ ለ18 ዓመት ጨቆኗቸው። 9 በተጨማሪም አሞናውያን ይሁዳን፣ ቢንያምንና የኤፍሬምን ቤት ለመውጋት ዮርዳኖስን ይሻገሩ ነበር፤ እስራኤላውያንም እጅግ ተጨንቀው ነበር። 10 ከዚያም እስራኤላውያን “አንተን አምላካችንን ትተን ባአልን በማገልገላችን+ በአንተ ላይ ኃጢአት ሠርተናል” በማለት ይሖዋ እንዲረዳቸው ጮኹ።+
11 ሆኖም ይሖዋ እስራኤላውያንን እንዲህ አላቸው፦ “ግብፃውያን፣+ አሞራውያን፣+ አሞናውያን፣ ፍልስጤማውያን፣+ 12 ሲዶናውያን፣ አማሌቃውያንና ምድያማውያን በጨቆኗችሁ ጊዜ አላዳንኳችሁም? ወደ እኔ ስትጮኹ ከእጃቸው ታደግኳችሁ። 13 እናንተ ግን እኔን ትታችሁ ሌሎች አማልክትን አገለገላችሁ።+ ዳግመኛ የማላድናችሁም በዚህ የተነሳ ነው።+ 14 ወደመረጣችኋቸው አማልክት ሂዱና እንዲረዷችሁ ጠይቋቸው።+ በጭንቀታችሁ ጊዜ እነሱ ያድኗችሁ።”+ 15 እስራኤላውያን ግን ይሖዋን “ኃጢአት ሠርተናል። መልካም መስሎ የታየህን ማንኛውንም ነገር አድርግብን። እባክህ፣ የዛሬን ብቻ አድነን” አሉት። 16 እነሱም ከመካከላቸው ባዕዳን አማልክትን አስወግደው ይሖዋን አገለገሉ፤+ በመሆኑም በእስራኤል ላይ እየደረሰ የነበረውን መከራ ሊታገሥ አልቻለም።* +
17 ከጊዜ በኋላም አሞናውያን+ ተሰባስበው በጊልያድ ሰፈሩ። በመሆኑም እስራኤላውያን ተሰባስበው በምጽጳ ሰፈሩ። 18 የጊልያድ ሕዝብና መኳንንት እርስ በርሳቸው እንዲህ ተባባሉ፦ “ከአሞናውያን ጋር የሚደረገውን ውጊያ ግንባር ቀደም ሆኖ የሚመራው ማን ነው?+ ይህ ሰው በጊልያድ ነዋሪዎች ሁሉ ላይ አለቃ ይሁን።”