ዘፍጥረት
39 ዮሴፍም ወደ ግብፅ ተወሰደ፤+ የፈርዖን የቤተ መንግሥት ባለሥልጣንና የዘቦች አለቃ የሆነ ጶጢፋር+ የሚባል አንድ ግብፃዊ ወደዚያ ይዘውት ከወረዱት እስማኤላውያን+ እጅ ዮሴፍን ገዛው። 2 ሆኖም ይሖዋ ከዮሴፍ ጋር ነበር።+ በዚህም የተነሳ ስኬታማ ሆነ፤ በግብፃዊው ጌታው ቤትም ላይ ኃላፊ ሆኖ ተሾመ። 3 ጌታውም ይሖዋ ከዮሴፍ ጋር እንደሆነና የሚሠራውንም ነገር ሁሉ ይሖዋ እንደሚያሳካለት አየ።
4 ዮሴፍም በፊቱ ሞገስ እያገኘ ሄደ፤ የቅርብ አገልጋዩም ሆነ። በመሆኑም በቤቱ ላይ ሾመው፤ የእሱ የሆነውንም ነገር ሁሉ በኃላፊነት ሰጠው። 5 በቤቱና ባለው ነገር ሁሉ ላይ ከሾመው ጊዜ አንስቶ ይሖዋ በዮሴፍ ምክንያት የግብፃዊውን ቤት ባረከ፤ ይሖዋም በቤትና በመስክ ያለውን ነገር ሁሉ ባረከለት።+ 6 ከጊዜ በኋላም ያለውን ነገር ሁሉ ለዮሴፍ በኃላፊነት ሰጠው፤ እሱም ከሚመገበው ምግብ በስተቀር ስለ ሌላው ነገር ምንም አይጨነቅም ነበር። ደግሞም ዮሴፍ ሰውነቱ እየዳበረና መልኩ እያማረ ሄደ።
7 በኋላም የጌታው ሚስት በዮሴፍ ላይ ዓይኗን ጣለችበት፤ እሷም “ከእኔ ጋር ተኛ” ትለው ጀመር። 8 እሱ ግን ፈቃደኛ አለመሆኑን በመግለጽ የጌታውን ሚስት እንዲህ አላት፦ “ጌታዬ በዚህ ቤት በእኔ እጅ ስላለው ነገር ምንም የሚያውቀው ነገር የለም፤ ያለውንም ነገር ሁሉ በአደራ ሰጥቶኛል። 9 በዚህ ቤት ውስጥ ከእኔ የሚበልጥ ሰው የለም፤ ጌታዬ ከአንቺ በስተቀር ምንም ያልሰጠኝ ነገር የለም፤ ይህን ያደረገውም ሚስቱ ስለሆንሽ ነው። ታዲያ እንዲህ ያለውን እጅግ መጥፎ ድርጊት በመፈጸም በአምላክ ላይ እንዴት ኃጢአት እሠራለሁ?”+
10 እሷም ዮሴፍን በየቀኑ ትወተውተው ነበር፤ እሱ ግን ከእሷ ጋር ለመተኛትም ሆነ አብሯት ለመሆን ፈጽሞ ፈቃደኛ አልሆነም። 11 ይሁንና አንድ ቀን ዮሴፍ ሥራውን ለማከናወን ወደ ቤት ሲገባ ከቤቱ አገልጋዮች መካከል አንዳቸውም በዚያ አልነበሩም። 12 እሷም ልብሱን አፈፍ አድርጋ ይዛ “አብረኸኝ ተኛ!” አለችው። እሱ ግን ልብሱን እጇ ላይ ጥሎ ወደ ውጭ ሸሽቶ ወጣ። 13 እሷም ልብሱን እጇ ላይ ጥሎ ወደ ውጭ እንደሸሸ ባየች ጊዜ 14 የቤቷን ሰዎች ጮኻ በመጣራት እንዲህ አለቻቸው፦ “አያችሁ! ባለቤቴ ያመጣው ይህ ዕብራዊ መሳለቂያ ሊያደርገን ነው። መጥቶ አብሬሽ ካልተኛሁ አለኝ፤ እኔ ግን ጩኸቴን አቀለጥኩት። 15 ድምፄን ከፍ አድርጌ ስጮኽ ልብሱን አጠገቤ ጥሎ ወደ ውጭ ሸሽቶ ወጣ።” 16 ከዚያም ጌታው ወደ ቤቱ እስኪመለስ ድረስ ልብሱን አጠገቧ አቆየችው።
17 ከዚያም እንዲህ ስትል ያንኑ ነገር ነገረችው፦ “ይህ ያመጣህብን ዕብራዊ አገልጋይ እኔ ወዳለሁበት ገብቶ መሳለቂያ ሊያደርገኝ ነበር። 18 ሆኖም ድምፄን ከፍ አድርጌ ስጮኽ ልብሱን አጠገቤ ጥሎ ወደ ውጭ ሸሽቶ ወጣ።” 19 ጌታውም “ይኸውልህ፣ አገልጋይህ እንዲህ አደረገኝ” ብላ ሚስቱ የነገረችውን ሲሰማ ቁጣው ነደደ። 20 በመሆኑም የዮሴፍ ጌታ ዮሴፍን ወስዶ የንጉሡ እስረኞች የታሰሩበት እስር ቤት አስገባው፤ ዮሴፍም እዚያው እስር ቤት ውስጥ ቆየ።+
21 ይሁን እንጂ ይሖዋ ከዮሴፍ አልተለየም፤ እንደወትሮው ሁሉ ለእሱ ታማኝ ፍቅር ከማሳየት ወደኋላ አላለም፤ በእስር ቤቱ አለቃም ፊት ሞገስ ሰጠው።+ 22 በመሆኑም የእስር ቤቱ አለቃ ዮሴፍን በእስር ቤቱ ውስጥ ባሉት እስረኞች ሁሉ ላይ ኃላፊ አደረገው፤ በእስር ቤቱ ውስጥ እስረኞቹ የሚያከናውኑትን ማንኛውንም ሥራ የሚቆጣጠረው እሱ ነበር።+ 23 ይሖዋ ከዮሴፍ ጋር ስለነበርና የሚያደርገውን ነገር ሁሉ ይሖዋ ስለሚያሳካለት የእስር ቤቱ አለቃ በዮሴፍ ኃላፊነት ሥር ስላለው ስለ ማንኛውም ነገር ምንም አይጨነቅም ነበር።+