ሩት
3 ከዚያም አማቷ ናኦሚ እንዲህ አለቻት፦ “ልጄ ሆይ፣ መልካም ይሆንልሽ ዘንድ ቤት* ልፈልግልሽ አይገባም?+ 2 ቦዔዝ ዘመዳችን አይደለም?+ አብረሻቸው የነበርሽው ወጣት ሴቶች የእሱ ናቸው። ዛሬ ማታ በአውድማው ላይ ገብስ ያዘራል። 3 ስለዚህ ተነስተሽ ተጣጠቢና ሰውነትሽን ጥሩ መዓዛ ያለው ዘይት ተቀቢ፤ ከዚያም ልብስሽን ለባብሰሽ* ወደ አውድማው ውረጂ። ሰውየው በልቶና ጠጥቶ እስኪጨርስ ድረስ እዚያ መኖርሽን እንዲያውቅ ማድረግ የለብሽም። 4 ሲተኛም የሚተኛበትን ቦታ ልብ ብለሽ እዪ፤ ከዚያም ሄደሽ እግሩን ገልጠሽ ተኚ። እሱም ምን ማድረግ እንዳለብሽ ይነግርሻል።”
5 እሷም “ያልሽኝን ሁሉ አደርጋለሁ” አለቻት። 6 ስለዚህ ሩት ወደ አውድማው በመውረድ ሁሉንም ነገር ልክ አማቷ እንዳዘዘቻት አደረገች። 7 ቦዔዝም ከበላና ከጠጣ በኋላ ልቡ በደስታ ተሞላ። ከዚያም ሄዶ የተቆለለው እህል አጠገብ ተኛ። ሩትም በቀስታ መጥታ እግሩን ገልጣ ተኛች። 8 እኩለ ሌሊትም ሲሆን ቦዔዝ እየተንቀጠቀጠ ከእንቅልፉ ባነነ፤ ቀና ሲልም አንዲት ሴት እግሩ ሥር ተኝታ ተመለከተ። 9 እሱም “ለመሆኑ አንቺ ማን ነሽ?” አላት። እሷም መልሳ “እኔ አገልጋይህ ሩት ነኝ። መቤዠት+ የሚገባህ አንተ ስለሆንክ መጎናጸፊያህን በአገልጋይህ ላይ ጣል” አለችው። 10 በዚህ ጊዜ እንዲህ አላት፦ “ልጄ ሆይ፣ ይሖዋ ይባርክሽ። ሀብታምም ሆኑ ድሃ፣ ወጣት ወንዶችን ተከትለሽ ባለመሄድሽ ከበፊቱ ይልቅ+ አሁን ያሳየሽው ታማኝ ፍቅር በለጠ። 11 ስለዚህ የእኔ ልጅ፣ አትፍሪ። አንቺ ምግባረ መልካም ሴት መሆንሽን የከተማው* ሰው ሁሉ ስለሚያውቅ ያልሽውን ሁሉ አደርግልሻለሁ።+ 12 እኔ መቤዠት+ እንዳለብኝ የማይካድ ቢሆንም ከእኔ ይልቅ የቅርብ ዘመድ የሆነ መቤዠት የሚችል ሰው አለ።+ 13 ዛሬ እዚሁ እደሪ፤ ሲነጋም ሰውዬው የሚቤዥሽ ከሆነ፣ መልካም! እሱ ይቤዥሽ።+ ሊቤዥሽ የማይፈልግ ከሆነ ግን ሕያው በሆነው በይሖዋ እምላለሁ እኔው ራሴ እቤዥሻለሁ። እስከ ማለዳ ድረስ ግን እዚሁ ተኚ።”
14 በመሆኑም እስኪነጋ ድረስ እግሩ ሥር ተኛች፤ ከዚያም ጎህ ቀዶ ሰውን በውል መለየት የሚያስችል ብርሃን ከመውጣቱ በፊት ተነሳች። እሱም “አንዲት ሴት ወደ አውድማው መጥታ እንደነበር ማንም አይወቅ” አለ። 15 በተጨማሪም “የለበስሽውን ኩታ ዘርግተሽ ያዢው” አላት። ስትዘረጋለትም ስድስት መስፈሪያ* ገብስ ሰፈረላትና አሸከማት፤ በኋላም ወደ ከተማ ሄደ።
16 እሷም ወደ አማቷ ሄደች፤ አማቷም “ልጄ ሆይ፣ እንዴት ሆነልሽ?”* አለቻት። ሩትም ሰውየው ያደረገላትን ሁሉ አንድ በአንድ ነገረቻት። 17 እንዲሁም “‘ወደ አማትሽ ባዶ እጅሽን አትሂጂ’ ብሎ ይህን ስድስት መስፈሪያ ገብስ ሰጠኝ” አለቻት። 18 በዚህ ጊዜ ናኦሚ እንዲህ አለቻት፦ “ልጄ ሆይ፣ ከዚህ በኋላ ቁርጡ እስኪታወቅ ድረስ ዝም ብለሽ ተቀመጪ፤ ምክንያቱም ሰውየው ዛሬውኑ ለጉዳዩ እልባት ሳያበጅ ዝም ብሎ አይቀመጥም።”