ለቲቶ የተጻፈ ደብዳቤ
3 ለመንግሥታትና ለባለሥልጣናት እንዲገዙና እንዲታዘዙ+ እንዲሁም ለመልካም ሥራ ሁሉ ዝግጁ እንዲሆኑ አሳስባቸው፤ 2 ደግሞም ስለ ማንም ክፉ ነገር እንዳይናገሩ፣ ጠበኞች እንዳይሆኑ ከዚህ ይልቅ ምክንያታዊ እንዲሆኑና+ ለሰው ሁሉ ገርነትን በተሟላ ሁኔታ እንዲያንጸባርቁ አሳስባቸው።+ 3 እኛም በአንድ ወቅት የማናመዛዝን፣ የማንታዘዝ፣ የምንስት፣ ለተለያየ ምኞትና ሥጋዊ ደስታ የምንገዛ፣ በክፋትና በቅናት የምንኖር፣ በሰዎች ዘንድ የምንጠላና እርስ በርስ የማንዋደድ ነበርን።
4 ይሁን እንጂ አዳኛችን የሆነው አምላክ ደግነትና+ ለሰው ልጆች ያለው ፍቅር በተገለጠ ጊዜ 5 (እኛ በሠራነው የጽድቅ ሥራ ሳይሆን+ በምሕረቱ)+ እኛን አጥቦ ሕያው በማድረግና በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት በማደስ+ አዳነን።+ 6 ይህን መንፈስ አዳኛችን በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት በእኛ ላይ አትረፍርፎ* አፈሰሰው፤+ 7 ይህን ያደረገው በእሱ ጸጋ አማካኝነት ከጸደቅን+ በኋላ ከተስፋችን ጋር በሚስማማ ሁኔታ የዘላለም ሕይወትን+ እንድንወርስ ነው።+
8 እነዚህ ቃላት እምነት የሚጣልባቸው ናቸው፤ ደግሞም በአምላክ ያመኑ ሁሉ መልካም ሥራዎችን በመሥራት ላይ እንዲያተኩሩ እነዚህን ጉዳዮች በተመለከተ ዘወትር አስረግጠህ እንድትናገር እፈልጋለሁ። እነዚህ ነገሮች መልካምና ለሰዎች ጠቃሚ ናቸው።
9 ሆኖም ሞኝነት ከሚንጸባረቅበት ክርክር፣ ከትውልድ ሐረግ ቆጠራ፣ ከጭቅጭቅና ሕጉን በተመለከተ ከሚነሳ ጠብ ራቅ፤ እነዚህ ነገሮች ምንም የማይጠቅሙና ከንቱ ናቸው።+ 10 ኑፋቄ+ የሚያስፋፋን ሰው ከአንዴም ሁለቴ አጥብቀህ ምከረው።*+ ካልሰማህ ግን ከእሱ ራቅ፤+ 11 እንዲህ ዓይነቱ ሰው ከትክክለኛው መንገድ የወጣና ኃጢአት እየሠራ ያለ ከመሆኑም ሌላ በራሱ ላይ እንደፈረደ እወቅ።
12 አርጤማስን ወይም ቲኪቆስን+ ወደ አንተ ስልክ፣ እኔ ወዳለሁበት ወደ ኒቆጶሊስ ለመምጣት የተቻለህን ሁሉ አድርግ፤ ክረምቱን በዚያ ለማሳለፍ ወስኛለሁና። 13 ሕጉን ጠንቅቆ የሚያውቀው ዜናስም ሆነ አጵሎስ ለጉዟቸው የሚያስፈልጋቸው ነገር ሁሉ እንዲሟላላቸው የተቻለህን ሁሉ ጥረት አድርግ።+ 14 ይሁን እንጂ አሳሳቢ ችግር ሲፈጠር መርዳት እንዲችሉና+ ፍሬ ቢሶች እንዳይሆኑ የእኛም ሰዎች በመልካም ሥራ መጠመድን ይማሩ።+
15 አብረውኝ ያሉት ሁሉ ሰላምታ ያቀርቡልሃል። ለሚወዱን የእምነት ባልንጀሮቻችን ሰላምታ አቅርብልኝ።
የአምላክ ጸጋ ከሁላችሁ ጋር ይሁን።