ዘኁልቁ
15 በተጨማሪም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ 2 “እስራኤላውያንን እንዲህ በላቸው፦ ‘እንድትኖሩባት ወደምሰጣችሁ ምድር በምትገቡበትና+ 3 ይሖዋን ደስ የሚያሰኝ* መዓዛ+ እንዲሆን የሚቃጠል መባም+ ሆነ ለየት ያለ ስእለት ለመሳል የሚቀርብ መሥዋዕት ወይም የፈቃደኝነት መባ+ አሊያም በየወቅቱ በምታከብሯቸው በዓላት+ ላይ የሚቀርብ መባ፣ ከከብታችሁ ወይም ከመንጋችሁ በመውሰድ ለይሖዋ በእሳት የሚቃጠል መባ በምታቀርቡበት ጊዜ 4 መባውን የሚያቀርበው ሰው በአንድ አራተኛ ሂን* ዘይት የተለወሰ አንድ አሥረኛ ኢፍ* የላመ ዱቄትም+ የእህል መባ አድርጎ ለይሖዋ ማቅረብ ይኖርበታል። 5 እንዲሁም ከሚቃጠለው መባ ወይም ከተባዕት የበግ ጠቦት መሥዋዕቱ ጋር አንድ አራተኛ ሂን የወይን ጠጅ የመጠጥ መባ አድርገህ ማቅረብ አለብህ።+ 6 ወይም ከአውራ በግ ጋር በአንድ ሦስተኛ ሂን ዘይት የተለወሰ ሁለት አሥረኛ የኢፍ መስፈሪያ የላመ ዱቄት የእህል መባ አድርገህ አቅርብ። 7 እንዲሁም አንድ ሦስተኛ ሂን የወይን ጠጅ ይሖዋን ደስ የሚያሰኝ* መዓዛ ያለው የመጠጥ መባ አድርገህ ማቅረብ አለብህ።
8 “‘ሆኖም ከመንጋው መካከል አንድ ወይፈን የሚቃጠል መባ+ ወይም ለየት ያለ ስእለት+ ለመሳል የሚቀርብ መሥዋዕት አሊያም የኅብረት መሥዋዕት አድርገህ ለይሖዋ የምታቀርብ+ ከሆነ 9 ከወይፈኑ ጋር በግማሽ ሂን ዘይት የተለወሰ ሦስት አሥረኛ የኢፍ መስፈሪያ የላመ ዱቄት የእህል መባ+ አድርገህ ማቅረብ ይኖርብሃል። 10 እንዲሁም ይሖዋን ደስ የሚያሰኝ* መዓዛ ያለው የመጠጥ መባ+ እንዲሆን ግማሽ ሂን የወይን ጠጅ በእሳት የሚቃጠል መባ አድርገህ ማቅረብ አለብህ። 11 ለእያንዳንዱ በሬ ወይም ለእያንዳንዱ አውራ በግ ወይም ለእያንዳንዱ ተባዕት የበግ ጠቦት ወይም ለእያንዳንዱ ፍየል እንዲሁ መደረግ አለበት። 12 የምታቀርቡት ብዛቱ ምንም ያህል ይሁን ምን ለእያንዳንዱ እንደየብዛቱ እንዲህ ማድረግ ይኖርባችኋል። 13 የአገሩ ተወላጅ የሆነ እያንዳንዱ እስራኤላዊ ይሖዋን ደስ የሚያሰኝ* መዓዛ ያለው በእሳት የሚቃጠል መባ የሚያቀርበው በዚህ መንገድ ነው።
14 “‘ከእናንተ ጋር እየኖረ ያለ ወይም ለብዙ ትውልድ በመካከላችሁ ሲኖር የነበረ የባዕድ አገር ሰው ይሖዋን ደስ የሚያሰኝ* መዓዛ ያለው በእሳት የሚቃጠል መባ ቢያቀርብ ልክ እናንተ እንደምታደርጉት ያድርግ።+ 15 የጉባኤው ክፍል የሆናችሁት እናንተም ሆናችሁ አብሯችሁ የሚኖር የባዕድ አገር ሰው አንድ ዓይነት ደንብ ይኖራችኋል። ይህም በትውልዶቻችሁ ሁሉ ዘላቂ ደንብ ይሆናል። የባዕድ አገሩ ሰው በይሖዋ ፊት ልክ እንደ እናንተ ይታያል።+ 16 ለእናንተም ሆነ ከእናንተ ጋር ለሚኖር የባዕድ አገር ሰው አንድ ዓይነት ሕግና አንድ ዓይነት ድንጋጌ ይኑር።’”
17 ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ 18 “እስራኤላውያንን አናግራቸው፤ እንዲህም በላቸው፦ ‘ወደማመጣችሁ ምድር በምትገቡበትና 19 ከምድሪቱ ማንኛውንም ምግብ በምትበሉበት+ ጊዜ ለይሖዋ መዋጮ ማድረግ አለባችሁ። 20 ከተፈጨው የእህላችሁ በኩር+ ላይ የቀለበት ቅርጽ ያለው ዳቦ በማዘጋጀት መዋጮ ማድረግ ይኖርባችኋል። ይህን ማዋጣት የሚኖርባችሁ ከአውድማ ላይ የሚገኘውን መዋጮ በምታዋጡበት መንገድ ነው። 21 በትውልዶቻችሁ ሁሉ፣ ከተፈጨው የእህላችሁ በኩር ላይ የተወሰነውን ለይሖዋ መዋጮ አድርጋችሁ መስጠት ይኖርባችኋል።
22 “‘ምናልባት ስህተት ብትሠሩና ይሖዋ ለሙሴ የተናገራቸውን እነዚህን ትእዛዛት ሁሉ ሳትፈጽሙ ብትቀሩ 23 ይኸውም ይሖዋ ትእዛዙን ከሰጠበት ዕለት አንስቶ ሥራ ላይ የዋለውንና በትውልዶቻችሁ ሁሉ ጸንቶ የሚኖረውን ይሖዋ በሙሴ በኩል ያስተላለፈላችሁን ትእዛዝ ሁሉ ባትፈጽሙና 24 ይህን ያደረጋችሁት ደግሞ በስህተትና ማኅበረሰቡ ሳያውቅ ቢሆን መላው ማኅበረሰብ አንድ ወይፈን ይሖዋን ደስ የሚያሰኝ* መዓዛ ያለው የሚቃጠል መባ አድርጎ ያቅርብ፤ ከእሱም ጋር በተለመደው አሠራር መሠረት+ የእህል መባውንና የመጠጥ መባውን እንዲሁም አንድ የፍየል ጠቦት የኃጢአት መባ አድርጎ ያቅርብ።+ 25 ካህኑም ለመላው የእስራኤል ማኅበረሰብ ያስተሰርያል፤ ኃጢአቱም ባለማወቅ የተፈጸመ ስለሆነና ለሠሩትም ስህተት መባቸውን ለይሖዋ በእሳት የሚቃጠል መባ አድርገው ስላቀረቡ እንዲሁም በይሖዋ ፊት የኃጢአት መባቸውን ስላቀረቡ ይቅር ይባልላቸዋል።+ 26 ይህም ሕዝቡ ሁሉ ባለማወቅ የፈጸመው ስለሆነ መላው የእስራኤል ማኅበረሰብም ሆነ በመካከላቸው የሚኖር የባዕድ አገር ሰው ይቅር ይባላል።
27 “‘ማንኛውም ሰው* ባለማወቅ ኃጢአት ቢሠራ አንድ ዓመት ገደማ የሆናት አንዲት ፍየል የኃጢአት መባ አድርጎ ያቅርብ።+ 28 ከዚያም ባለማወቅ በይሖዋ ፊት ኃጢአት በመሥራት የተሳሳተው ሰው* ኃጢአቱ ይሰረይለት ዘንድ ካህኑ ማስተሰረያ ያቀርብለታል፤ ኃጢአቱም ይቅር ይባልለታል።+ 29 ባለማወቅ ከሚፈጸም ነገር ጋር በተያያዘ በእስራኤላውያን መካከል ለሚገኝ የአገሬው ተወላጅም ሆነ በመካከላቸው ለሚኖር የባዕድ አገር ሰው አንድ ዓይነት ሕግ ይኑራችሁ።+
30 “‘ይሁን እንጂ ሆን ብሎ ኃጢአት የሚሠራ ሰው*+ የአገሬው ተወላጅም ይሁን የባዕድ አገር ሰው ይሖዋን እንደተሳደበ ስለሚቆጠር ከሕዝቡ ተለይቶ እንዲጠፋ መደረግ አለበት። 31 የይሖዋን ቃል ስላቃለለና የእሱን ትእዛዝ ስለጣሰ ያ ሰው* ያለምንም ጥርጥር ተለይቶ እንዲጠፋ መደረግ አለበት።+ ጥፋቱ የራሱ ነው።’”+
32 እስራኤላውያን በምድረ በዳ ሳሉ አንድ ሰው በሰንበት ቀን እንጨት ሲለቅም አገኙ።+ 33 ሰዎቹም እንጨት ሲለቅም ያገኙትን ሰው ወደ ሙሴ፣ ወደ አሮንና ወደ መላው ማኅበረሰብ አመጡት። 34 ሰውየው ምን መደረግ እንዳለበት በግልጽ የተቀመጠ ነገር ስላልነበረ በጥበቃ ሥር እንዲቆይ አደረጉ።+
35 ይሖዋም ሙሴን “ሰውየው ያለምንም ጥርጥር መገደል አለበት፤+ መላው ማኅበረሰብም ከሰፈሩ ውጭ በድንጋይ ይውገረው”+ አለው። 36 ስለዚህ ይሖዋ ሙሴን ባዘዘው መሠረት መላው ማኅበረሰብ ሰውየውን ከሰፈሩ ውጭ አውጥቶ እስኪሞት ድረስ በድንጋይ ወገረው።
37 ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ 38 “እስራኤላውያን በትውልዶቻቸው ሁሉ በልብሳቸው ጫፍ ላይ ዘርፍ እንዲያደርጉ ንገራቸው፤ ልብሳቸውም ከዘርፉ በላይ ሰማያዊ ጥለት ይኑረው።+ 39 ‘ይህን ዘርፍ በልብሳችሁ ላይ አድርጉ፤ ምክንያቱም እሱን ስታዩ የይሖዋን ትእዛዛት ሁሉ ታስታውሳላችሁ፤ እንዲሁም ትፈጽማላችሁ።+ ወደ መንፈሳዊ ምንዝር የሚመራችሁን የገዛ ልባችሁንና ዓይናችሁን አትከተሉ።+ 40 ይህን መመሪያ የሰጠኋችሁ ትእዛዛቴን በሙሉ እንድታስታውሱና እንድትፈጽሙ ነው፤ ለአምላካችሁም የተቀደሳችሁ ትሆናላችሁ።+ 41 አምላካችሁ መሆኔን ለማስመሥከር ከግብፅ ምድር ያወጣኋችሁ እኔ አምላካችሁ ይሖዋ ነኝ።+ አዎ፣ እኔ አምላካችሁ ይሖዋ ነኝ።’”+