የዮሐንስ ወንጌል
14 “ልባችሁ አይረበሽ።+ በአምላክ እመኑ፤+ በእኔም ደግሞ እመኑ። 2 በአባቴ ቤት ብዙ መኖሪያ ቦታ አለ። ይህ ባይሆን ኖሮ በግልጽ እነግራችሁ ነበር፤ ለእናንተ ቦታ ለማዘጋጀት እሄዳለሁና።+ 3 ደግሞም ሄጄ ቦታ ባዘጋጀሁላችሁ ጊዜ እኔ ባለሁበት እናንተም እንድትሆኑ እንደገና መጥቼ እኔ ወዳለሁበት እወስዳችኋለሁ።*+ 4 እኔ ወደምሄድበትም ቦታ የሚወስደውን መንገድ ታውቃላችሁ።”
5 ቶማስም+ “ጌታ ሆይ፣ ወዴት እንደምትሄድ አናውቅም። ታዲያ መንገዱን እንዴት ማወቅ እንችላለን?” አለው።
6 ኢየሱስም እንዲህ አለው፦ “እኔ መንገድ፣+ እውነትና+ ሕይወት+ ነኝ። በእኔ በኩል ካልሆነ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም።+ 7 እኔን ብታውቁኝ ኖሮ አባቴንም ታውቁት ነበር፤ ከዚህ ጊዜ አንስቶ ታውቁታላችሁ፤ ደግሞም አይታችሁታል።”+
8 ፊልጶስም “ጌታ ሆይ፣ አብን አሳየንና ይበቃናል” አለው።
9 ኢየሱስም እንዲህ አለው፦ “ፊልጶስ፣ ከእናንተ ጋር ይህን ያህል ረጅም ጊዜ ኖሬም እንኳ አላወቅከኝም? እኔን ያየ ሁሉ አብንም አይቷል።+ ታዲያ እንዴት ‘አብን አሳየን’ ትላለህ? 10 እኔ ከአብ ጋር አንድነት እንዳለኝና አብ ከእኔ ጋር አንድነት እንዳለው አታምንም?+ የምነግራችሁን ነገር የምናገረው ከራሴ አመንጭቼ አይደለም፤+ ሆኖም ሥራውን እየሠራ ያለው ከእኔ ጋር አንድነት ያለው አብ ነው። 11 እኔ ከአብ ጋር አንድነት እንዳለኝ አብም ከእኔ ጋር አንድነት እንዳለው እመኑኝ፤ ካልሆነ ደግሞ ከተሠሩት ሥራዎች የተነሳ እመኑ።+ 12 እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ በእኔ የሚያምን ሁሉ እኔ የምሠራቸውን ሥራዎች ይሠራል፤ እንዲያውም እኔ ወደ አብ ስለምሄድ+ እሱ ከእነዚህ የበለጡ ሥራዎች ይሠራል።+ 13 በተጨማሪም አብ በወልድ አማካኝነት እንዲከበር በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ አደርገዋለሁ።+ 14 ማንኛውንም ነገር በስሜ ከለመናችሁ እኔ አደርገዋለሁ።
15 “የምትወዱኝ ከሆነ ትእዛዛቴን ትጠብቃላችሁ።+ 16 እኔም አብን እጠይቃለሁ፤ እሱም ለዘላለም ከእናንተ ጋር የሚሆን ሌላ ረዳት* ይሰጣችኋል፤+ 17 እሱም የእውነት መንፈስ ነው፤+ ዓለም ስለማያየውና ስለማያውቀው ሊቀበለው አይችልም።+ እናንተ ግን አብሯችሁ ስለሚኖርና በውስጣችሁ ስላለ ታውቁታላችሁ። 18 ሐዘን ላይ* ትቻችሁ አልሄድም። ወደ እናንተ እመጣለሁ።+ 19 ከጥቂት ጊዜ በኋላ ዓለም ከቶ አያየኝም፤ እናንተ ግን ታዩኛላችሁ፤+ ምክንያቱም እኔ እኖራለሁ፤ እናንተም ትኖራላችሁ። 20 እኔ ከአባቴ ጋር አንድነት እንዳለኝ፣ እናንተ ከእኔ ጋር አንድነት እንዳላችሁና እኔም ከእናንተ ጋር አንድነት እንዳለኝ በዚያን ቀን ታውቃላችሁ።+ 21 እኔን የሚወደኝ ትእዛዛቴን የሚቀበልና የሚጠብቅ ነው። እኔን የሚወደኝን ሁሉ ደግሞ አባቴ ይወደዋል፤ እኔም እወደዋለሁ፤ ራሴንም እገልጥለታለሁ።”
22 የአስቆሮቱ ሳይሆን ሌላው ይሁዳ+ “ጌታ ሆይ፣ ለዓለም ሳይሆን ለእኛ ራስህን ለመግለጥ ያሰብከው ለምንድን ነው?” አለው።
23 ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “ማንም ሰው እኔን የሚወደኝ ከሆነ ቃሌን ይጠብቃል፤+ አባቴም ይወደዋል፣ እኛም ወደ እሱ መጥተን መኖሪያችንን ከእሱ ጋር እናደርጋለን።+ 24 እኔን የማይወደኝ ሁሉ ቃሌን አይጠብቅም። ይህ እየሰማችሁት ያለው ቃል ደግሞ የላከኝ የአብ ነው እንጂ የእኔ አይደለም።+
25 “አሁን ከእናንተ ጋር እያለሁ እነዚህን ነገሮች ነግሬአችኋለሁ። 26 ሆኖም አብ በስሜ የሚልከው ረዳት* ይኸውም መንፈስ ቅዱስ ሁሉንም ነገር ያስተምራችኋል እንዲሁም የነገርኳችሁን ነገር ሁሉ እንድታስታውሱ ያደርጋችኋል።+ 27 ሰላምን እተውላችኋለሁ፤ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ።+ እኔ ሰላም የምሰጣችሁ ዓለም በሚሰጥበት መንገድ አይደለም። ልባችሁ አይረበሽ፤ በፍርሃትም አይዋጥ። 28 ‘እሄዳለሁ ወደ እናንተም ተመልሼ እመጣለሁ’ እንዳልኳችሁ ሰምታችኋል። ብትወዱኝስ ወደ አብ በመሄዴ ደስ ባላችሁ ነበር፤ ከእኔ አብ ይበልጣልና።+ 29 በመሆኑም በሚፈጸምበት ጊዜ እንድታምኑ ከመፈጸሙ በፊት አሁን ነግሬአችኋለሁ።+ 30 የዚህ ዓለም ገዢ+ እየመጣ ስለሆነ ከዚህ በኋላ ከእናንተ ጋር ብዙ አልነጋገርም፤ እሱም በእኔ ላይ ምንም ኃይል የለውም።+ 31 ይሁን እንጂ እኔ አብን እንደምወድ ዓለም እንዲያውቅ አብ ባዘዘኝ መሠረት+ እየሠራሁ ነው። ተነሱ ከዚህ እንሂድ።