13 የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ+ በራእይ ያየው በባቢሎን ላይ የተላለፈ ፍርድ፦+
2 “በተራቆተ ዓለታማ ተራራ ላይ ምልክት አቁሙ።+
ታላላቅ ሰዎች ወደሚገቡባቸው በሮች እንዲመጡ
ድምፃችሁን ከፍ አድርጋችሁ ጥሯቸው፤ እጃችሁንም አውለብልቡ።
3 እኔ ለሾምኳቸው ትእዛዝ ሰጥቻለሁ።+
ቁጣዬን ለመግለጥ
በኩራት ሐሴት የሚያደርጉትን ተዋጊዎቼን ጠርቻለሁ።
4 ስሙ! በተራሮች ላይ እንደ ታላቅ ሕዝብ ድምፅ ያለ
የብዙ ሰዎች ድምፅ ይሰማል!
አዳምጡ! አንድ ላይ የተሰበሰቡ መንግሥታትና
ብሔራት+ ሁካታ ይሰማል!
የሠራዊት ጌታ ይሖዋ ሠራዊቱን ለጦርነት አሰልፏል።+
5 ይሖዋና የቁጣው መሣሪያዎች
መላ ምድሪቱን ለመደምሰስ+
ከሩቅ አገር፣+
ከሰማያትም ዳርቻ እየመጡ ነው።
6 የይሖዋ ቀን ቀርቧልና ዋይ ዋይ በሉ!
በዚያ ቀን ሁሉን ቻይ ከሆነው አምላክ ዘንድ ጥፋት ይመጣል።+
7 ከዚህም የተነሳ እጆች ሁሉ ይዝላሉ፤
የሰዎችም ልብ ሁሉ በፍርሃት ይቀልጣል።+
8 ሰዎቹ እጅግ ተሸብረዋል።+
ምጥ እንደያዛት ሴት
ብርክና ሥቃይ ይዟቸዋል።
እርስ በርሳቸው በታላቅ ድንጋጤ ይተያያሉ፤
ፊታቸው በጭንቀት ቀልቷል።
9 እነሆ፣ የይሖዋ ቀን ምድሪቱን አስፈሪ ቦታ ለማድረግና
በምድሪቱ ላይ ያሉትን ኃጢአተኞች ለማጥፋት
በንዴትና በታላቅ ቁጣ
ጨካኝ ሆኖ እየመጣ ነው።+
10 የሰማያት ከዋክብትና የኅብረ ከዋክብት ስብስቦቻቸው+
ብርሃን አይሰጡም፤
ፀሐይ ስትወጣ ትጨልማለች፤
ጨረቃም ብርሃኗን አትሰጥም።
11 ምድሪቱን ስለ ክፋቷ፣+
ክፉዎችንም ስለ በደላቸው እቀጣለሁ።
የእብሪተኞችን ኩራት አጠፋለሁ፤
የጨቋኞችንም ትዕቢት አዋርዳለሁ።+
12 ሟች የሆነውን ሰው ከጠራ ወርቅ፣
ሰዎችንም ከኦፊር ወርቅ+ ይበልጥ ብርቅ አደርጋለሁ።+
13 ስለዚህ የሠራዊት ጌታ የይሖዋ ቁጣ በሚነድበት ቀን፣
በታላቅ ቁጣ ሰማይን አናውጣለሁ፤
ምድርንም ከቦታዋ አናጋለሁ።+
14 እንደሚታደን የሜዳ ፍየል፣ እረኛም እንደሌለው መንጋ
እያንዳንዱ ወደ ወገኑ ይመለሳል፤
እያንዳንዱም ወደ አገሩ ይሸሻል።+
15 የተገኘ ሁሉ ይወጋል፤
የተያዘም ሁሉ በሰይፍ ይወድቃል።+
16 ልጆቻቸው ዓይናቸው እያየ ይጨፈጨፋሉ፤+
ቤታቸው ይዘረፋል፤
ሚስቶቻቸውም ተገደው ይደፈራሉ።
17 እነሆ፣ ለብር ደንታ የሌላቸውን፣
በወርቅም ደስ የማይሰኙትን
ሜዶናውያንን አስነሳባቸዋለሁ።+
18 ቀስታቸው ወጣቶችን ይፈጃል፤+
ለማህፀን ፍሬ አያዝኑም፤
ለልጆችም አይራሩም።
19 ከመንግሥታትም ሁሉ እጅግ የከበረችው፣+
የከለዳውያን ውበትና ኩራት የሆነችው ባቢሎን፣+
አምላክ እንደገለበጣቸው እንደ ሰዶምና እንደ ገሞራ ትሆናለች።+
20 ከዚያ በኋላ የሚቀመጥባት አይኖርም፤
እንዲሁም ከትውልድ እስከ ትውልድ ድረስ የመኖሪያ ቦታ አትሆንም።+
በዚያም ዓረብ ድንኳኑን አይተክልም፤
እረኞችም መንጎቻቸውን በዚያ አያሳርፉም።
21 የበረሃ ፍጥረታት በዚያ ይተኛሉ፤
ቤቶቻቸው በጉጉቶች ይሞላሉ።
ሰጎኖች በዚያ ይኖራሉ፤+
የዱር ፍየሎችም በዚያ ይፈነጫሉ።
22 የሚያላዝኑ ፍጥረታት በማማዎቿ፣
ቀበሮዎችም በሚያማምሩ ቤተ መንግሥቶቿ ውስጥ ሆነው ይጮኻሉ።
ጊዜዋ ቀርቧል፤ ቀኖቿም አይራዘሙም።”+