ዳንኤል
6 ዳርዮስ በመላው ንጉሣዊ ግዛቱ ላይ 120 የአውራጃ ገዢዎችን ለመሾም ወሰነ።+ 2 በእነሱ ላይ ሦስት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ሾመ፤ ከእነዚህም አንዱ ዳንኤል ነበር፤+ ንጉሡ ለኪሳራ እንዳይዳረግ እነዚህ የአውራጃ ገዢዎች+ ተጠሪነታቸው ለባለሥልጣናቱ እንዲሆን ተደረገ። 3 ዳንኤልም በዓይነቱ ልዩ የሆነ መንፈስ ስለነበረው ከከፍተኛ ባለሥልጣናቱና ከአውራጃ ገዢዎቹ ይበልጥ ብቃት እንዳለው አስመሠከረ፤+ ንጉሡም በመላው ንጉሣዊ ግዛቱ ላይ ከፍ ያለ ቦታ ሊሰጠው አሰበ።
4 በዚህ ጊዜ ከፍተኛ ባለሥልጣናቱና የአውራጃ ገዢዎቹ ከመንግሥት ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ዳንኤልን ለመክሰስ የሚያስችል ሰበብ ለማግኘት ይከታተሉት ነበር፤ ሆኖም ዳንኤል እምነት የሚጣልበት ስለነበርና ምንም ዓይነት እንከንና ጉድለት ስላልነበረበት በእሱ ላይ አንዳች ሰበብ ወይም ጉድለት ሊያገኙ አልቻሉም። 5 በመሆኑም “ከአምላኩ ሕግ ጋር በተያያዘ ካልሆነ በቀር ዳንኤልን ለመክሰስ ምንም ዓይነት ሰበብ ልናገኝ አንችልም” አሉ።+
6 ስለዚህ ከፍተኛ ባለሥልጣናቱና የአውራጃ ገዢዎቹ ተሰብስበው ወደ ንጉሡ በመግባት እንዲህ አሉት፦ “ንጉሥ ዳርዮስ ሆይ፣ ለዘላለም ኑር። 7 ንጉሥ ሆይ፣ ለ30 ቀናት ያህል ለአንተ ካልሆነ በስተቀር ለአምላክም ሆነ ለሰው ልመና የሚያቀርብ ማንኛውም ግለሰብ ወደ አንበሶች ጉድጓድ እንዲወረወር+ የሚያዝዝ ንጉሣዊ ድንጋጌ እንዲወጣና እገዳ እንዲጣል የመንግሥት ባለሥልጣናቱ፣ አስተዳዳሪዎቹ፣ የአውራጃ ገዢዎቹ፣ የንጉሡ አማካሪዎችና አገረ ገዢዎቹ ሁሉ በአንድነት ተስማምተዋል። 8 አሁንም ንጉሥ ሆይ፣ ሊሻር በማይችለው የሜዶናውያንና የፋርሳውያን ሕግ+ መሠረት ድንጋጌው እንዳይለወጥ አጽናው፤ በጽሑፉም ላይ ፈርምበት።”+
9 ስለዚህ ንጉሥ ዳርዮስ እገዳውን በያዘው ድንጋጌ ላይ ፈረመ።
10 ዳንኤል ግን ድንጋጌው በፊርማ መጽደቁን እንዳወቀ ወደ ቤቱ ገባ፤ በሰገነት ላይ ባለው ክፍሉ ውስጥ በኢየሩሳሌም አቅጣጫ ያሉት መስኮቶች ተከፍተው ነበር።+ ከዚህ በፊት አዘውትሮ ያደርግ እንደነበረውም በቀን ሦስት ጊዜ በጉልበቱ ተንበርክኮ ጸለየ፤ ለአምላኩም ውዳሴ አቀረበ። 11 ሰዎቹ በሩን በርግደው በገቡ ጊዜ ዳንኤል በአምላኩ ፊት ሞገስ ለማግኘት ልመና ሲያቀርብና ሲማጸን አገኙት።
12 በመሆኑም ወደ ንጉሡ ቀርበው “ንጉሥ ሆይ፣ ለ30 ቀናት ያህል ለአንተ ካልሆነ በስተቀር ለአምላክም ሆነ ለሰው ልመና የሚያቀርብ ማንኛውም ግለሰብ ወደ አንበሶች ጉድጓድ እንዲወረወር የሚደነግገውን እገዳ በፊርማህ አጽድቀህ አልነበረም?” በማለት ንጉሡ የጣለውን እገዳ አስታወሱት። ንጉሡም “ጉዳዩ ሊሻር በማይችለው በሜዶናውያንና በፋርሳውያን ሕግ መሠረት በሚገባ የጸና ነው” ሲል መለሰላቸው።+ 13 እነሱም ቀበል አድርገው ንጉሡን እንዲህ አሉት፦ “ንጉሥ ሆይ፣ ከይሁዳ ግዞተኞች አንዱ የሆነው ዳንኤል፣+ ለአንተም ሆነ በፊርማህ ላጸደቅከው እገዳ አክብሮት የለውም፤ ይልቁንም በቀን ሦስት ጊዜ ይጸልያል።”+ 14 ንጉሡም ይህን በሰማ ጊዜ እጅግ ተጨነቀ፤ ዳንኤልንም መታደግ የሚችልበትን መንገድ ያወጣና ያወርድ ጀመር፤ ፀሐይ እስክትጠልቅም ድረስ እሱን ለማዳን የተቻለውን ሁሉ ጥረት ሲያደርግ ቆየ። 15 በመጨረሻም እነዚህ ሰዎች አንድ ላይ ሆነው ወደ ንጉሡ በመግባት ንጉሡን እንዲህ አሉት፦ “ንጉሥ ሆይ፣ በሜዶናውያንና በፋርሳውያን ሕግ መሠረት ንጉሡ ያጸናው ማንኛውም እገዳ ወይም ድንጋጌ ሊለወጥ እንደማይችል አትርሳ።”+
16 ስለዚህ ንጉሡ ትእዛዝ አስተላለፈ፤ እነሱም ዳንኤልን አምጥተው አንበሶች ጉድጓድ ውስጥ ጣሉት።+ ንጉሡም ዳንኤልን “ሁልጊዜ የምታገለግለው አምላክህ ይታደግሃል” አለው። 17 ከዚያም ድንጋይ አምጥተው በጉድጓዱ አፍ* ላይ ገጠሙት፤ ንጉሡም በዳንኤል ላይ የተወሰደው እርምጃ እንዳይለወጥ፣ በራሱ የማኅተም ቀለበትና በመኳንንቱ የማኅተም ቀለበት በድንጋዩ ላይ አተመበት።
18 ከዚያም ንጉሡ ወደ ቤተ መንግሥቱ ሄደ። ጾሙንም አደረ፤ በምንም ነገር መዝናናት አልፈለገም፤* እንቅልፍም በዓይኑ አልዞረም።* 19 በመጨረሻም ንጉሡ ገና ጎህ ሲቀድ ተነስቶ እየተጣደፈ ወደ አንበሶቹ ጉድጓድ ሄደ። 20 ወደ ጉድጓዱ በቀረበ ጊዜ ሐዘን በተቀላቀለበት ድምፅ ጮክ ብሎ ዳንኤልን ተጣራ። ንጉሡም ዳንኤልን “የሕያው አምላክ አገልጋይ ዳንኤል ሆይ፣ ሁልጊዜ የምታገለግለው አምላክህ ከአንበሶቹ ሊታደግህ ችሏል?” አለው። 21 ዳንኤልም ንጉሡን እንዲህ አለው፦ “ንጉሥ ሆይ፣ ለዘላለም ኑር። 22 አምላኬ መልአኩን ልኮ የአንበሶቹን አፍ ዘጋ፤+ እነሱም አልጎዱኝም፤+ በፊቱ ንጹሕ ሆኜ ተገኝቻለሁና፤ ንጉሥ ሆይ፣ በአንተም ላይ የሠራሁት በደል የለም።”
23 ንጉሡ እጅግ ተደሰተ፤ ዳንኤልንም ከጉድጓዱ እንዲያወጡት አዘዘ። እነሱም ከጉድጓዱ አወጡት፤ ዳንኤል በአምላኩ ታምኖ ስለነበር ምንም ጉዳት አልደረሰበትም።+
24 ከዚያም በንጉሡ ትእዛዝ መሠረት፣ የዳንኤልን ከሳሾች* አምጥተው ከነልጆቻቸውና ከነሚስቶቻቸው ወደ አንበሶቹ ጉድጓድ ጣሏቸው። ገና ወደ ጉድጓዱ መጨረሻ ሳይደርሱ አንበሶቹ ተቀራመቷቸው፤ አጥንቶቻቸውንም ሁሉ አደቀቁ።+
25 ከዚያም ንጉሥ ዳርዮስ በመላው ምድር ለሚኖሩ ከተለያዩ ብሔራትና ቋንቋዎች ለተውጣጡ ሕዝቦች ሁሉ እንዲህ ሲል ጻፈ፦+ “ሰላም ይብዛላችሁ! 26 በየትኛውም የመንግሥቴ ግዛት የሚኖሩ ሰዎች የዳንኤልን አምላክ ፈርተው እንዲንቀጠቀጡ ትእዛዝ አስተላልፌአለሁ።+ እሱ ለዘላለም የሚኖር ሕያው አምላክ ነውና። መንግሥቱ ፈጽሞ አይጠፋም፤ የመግዛት ሥልጣኑም* ዘላለማዊ ነው።+ 27 እሱ ይታደጋል፤+ ደግሞም ያድናል፤ በሰማያትና በምድርም ተአምራዊ ምልክቶችንና ድንቅ ነገሮችን ያደርጋል፤+ ዳንኤልን ከአንበሶች መዳፍ ታድጎታልና።”
28 ስለዚህ ዳንኤል በዳርዮስ+ መንግሥት እንዲሁም በፋርሳዊው በቂሮስ+ መንግሥት ሁሉ ነገር ተሳካለት።