የማቴዎስ ወንጌል
23 ከዚያም ኢየሱስ ሕዝቡንና ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ አላቸው፦ 2 “ጸሐፍትና ፈሪሳውያን በገዛ ሥልጣናቸው የሙሴን ቦታ ወስደዋል። 3 ስለዚህ የሚነግሯችሁን ነገር ሁሉ አድርጉ፤ ጠብቁትም፤ ሆኖም የሚናገሩትን በተግባር ስለማያውሉ እነሱ የሚያደርጉትን አታድርጉ።+ 4 ከባድ ሸክም አስረው በሰዎች ትከሻ ላይ ይጭናሉ፤+ እነሱ ግን በጣታቸው እንኳ ለመንካት* ፈቃደኞች አይደሉም።+ 5 ማንኛውንም ነገር የሚያደርጉት በሰዎች ለመታየት ብለው ነው፤+ ለምሳሌ ትልቅ ክታብ* ያስራሉ፤+ የልብሳቸውንም ዘርፍ ያስረዝማሉ።+ 6 በራት ግብዣ ላይ የክብር ቦታ ማግኘት፣ በምኩራብ ደግሞ ከፊት መቀመጥ* ይወዳሉ፤+ 7 በገበያ ቦታም ሰዎች እጅ እንዲነሷቸው ይፈልጋሉ እንዲሁም ረቢ* ተብለው መጠራት ይሻሉ። 8 እናንተ ግን መምህራችሁ+ አንድ ስለሆነ ረቢ ተብላችሁ አትጠሩ፤ እናንተ ሁላችሁም ወንድማማቾች ናችሁ። 9 በተጨማሪም አባታችሁ+ አንድ እሱም በሰማይ ያለው ብቻ ስለሆነ በምድር ላይ ማንንም አባት ብላችሁ አትጥሩ። 10 እንዲሁም መሪያችሁ አንድ እሱም ክርስቶስ ስለሆነ መሪ ተብላችሁ አትጠሩ። 11 ይልቁንም ከመካከላችሁ ታላቅ የሆነው የእናንተ አገልጋይ መሆን ይገባዋል።+ 12 ራሱን ከፍ ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ዝቅ ይደረጋል፤+ ራሱን ዝቅ የሚያደርግ ሁሉ ደግሞ ከፍ ይደረጋል።+
13 “እናንተ ግብዞች ጸሐፍትና ፈሪሳውያን፣ ሰዎች ወደ መንግሥተ ሰማያት እንዳይገቡ በሩን ስለምትዘጉ ወዮላችሁ! እናንተ ራሳችሁ አትገቡም፤ ለመግባት የሚመጡትንም እንዳይገቡ ትከለክላላችሁ።+ 14 *——
15 “እናንተ ግብዞች+ ጸሐፍትና ፈሪሳውያን፣ አንድን ሰው ወደ ይሁዲነት ለመለወጥ በባሕርና በየብስ ስለምትጓዙና ሰውየው በተለወጠ ጊዜ ከእናንተ ይባስ ሁለት እጥፍ ለገሃነም* የተገባ እንዲሆን ስለምታደርጉት ወዮላችሁ!
16 “‘አንድ ሰው በቤተ መቅደሱ ቢምል ምንም አይደለም፤ በቤተ መቅደሱ ውስጥ ባለው ወርቅ ቢምል ግን መሐላውን የመጠበቅ ግዴታ አለበት’+ የምትሉ እናንተ ዕውር መሪዎች+ ወዮላችሁ! 17 እናንተ ሞኞችና ዕውሮች! ለመሆኑ ከወርቁና ወርቁ እንዲቀደስ ካደረገው ቤተ መቅደስ የትኛው ይበልጣል? 18 ደግሞም ‘አንድ ሰው በመሠዊያው ቢምል ምንም አይደለም፤ በመሠዊያው ላይ ባለው መባ ቢምል ግን መሐላውን የመጠበቅ ግዴታ አለበት’ ትላላችሁ። 19 እናንተ ዕውሮች! ለመሆኑ ከመባውና መባው እንዲቀደስ ካደረገው መሠዊያ የትኛው ይበልጣል? 20 ስለዚህ በመሠዊያው የሚምል ሁሉ በመሠዊያውና በላዩ ላይ ባለው ነገር ሁሉ ይምላል፤ 21 እንዲሁም በቤተ መቅደሱ የሚምል ሁሉ በቤተ መቅደሱና በዚያ በሚኖረው+ ይምላል፤ 22 በሰማይ የሚምል ሁሉ ደግሞ በአምላክ ዙፋንና በዙፋኑ ላይ በተቀመጠው ይምላል።
23 “እናንተ ግብዞች ጸሐፍትና ፈሪሳውያን ወዮላችሁ! ከኮሰረት፣ ከእንስላልና ከከሙን አሥራት ትሰጣላችሁ፤+ ነገር ግን በሕጉ ውስጥ የሚገኙትን እንደ ፍትሕ፣+ ምሕረትና+ ታማኝነት ያሉ ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች ችላ ትላላችሁ። እነዚያን ችላ ማለት ባይኖርባችሁም እነዚህን ነገሮች ማድረጋችሁ አስፈላጊ ነው።+ 24 እናንተ ዕውር መሪዎች!+ ትንኝን+ አጥልላችሁ ታወጣላችሁ፤ ግመልን+ ግን ትውጣላችሁ!
25 “እናንተ ግብዞች ጸሐፍትና ፈሪሳውያን ወዮላችሁ! ጽዋውንና ሳህኑን ከውጭ በኩል ታጸዳላችሁ፤+ ውስጡ ግን ስግብግብነትና*+ ራስ ወዳድነት የሞላበት ነው።+ 26 አንተ ዕውር ፈሪሳዊ፣ በመጀመሪያ ጽዋውንና ሳህኑን ከውስጥ በኩል አጽዳ፤ ከዚያ በኋላ ከውጭ በኩልም ንጹሕ ይሆናል።
27 “እናንተ ግብዞች+ ጸሐፍትና ፈሪሳውያን፣ ከውጭ አምረው የሚታዩ ከውስጥ ግን በሙታን አፅምና በብዙ ዓይነት ርኩሰት የተሞሉ በኖራ የተቀቡ መቃብሮችን ስለምትመስሉ ወዮላችሁ!+ 28 እናንተም ከውጭ ስትታዩ ጻድቅ ትመስላላችሁ፤ ውስጣችሁ ግን በግብዝነትና በዓመፅ የተሞላ ነው።+
29 “እናንተ ግብዞች+ ጸሐፍትና ፈሪሳውያን፣ የነቢያትን መቃብር ስለምትገነቡና የጻድቃንን መቃብር ስለምታስጌጡ ወዮላችሁ!+ 30 ደግሞም ‘በአባቶቻችን ዘመን ኖረን ቢሆን ኖሮ የነቢያትን ደም በማፍሰስ አንተባበራቸውም ነበር’ ትላላችሁ። 31 በመሆኑም የነቢያት ገዳዮች ልጆች እንደሆናችሁ በራሳችሁ ላይ ትመሠክራላችሁ።+ 32 እንግዲያው አባቶቻችሁ የጀመሩትን ተግባር ዳር አድርሱ።
33 “እናንተ እባቦች፣ የእፉኝት ልጆች፣+ ከገሃነም* ፍርድ እንዴት ታመልጣላችሁ?+ 34 ስለዚህ ነቢያትን፣+ ጥበበኞችንና የሕዝብ አስተማሪዎችን+ ወደ እናንተ እልካለሁ። ከእነሱም መካከል አንዳንዶቹን ትገድላላችሁ+ እንዲሁም በእንጨት ላይ ትሰቅላላችሁ፤ አንዳንዶቹን ደግሞ በምኩራቦቻችሁ ትገርፋላችሁ፤+ ከከተማ ወደ ከተማም ታሳድዷቸዋላችሁ፤+ 35 በዚህም ምክንያት ከጻድቁ ከአቤል ደም+ ጀምሮ በመቅደሱና በመሠዊያው መካከል እስከገደላችሁት እስከ በራክዩ ልጅ እስከ ዘካርያስ ደም ድረስ በምድር ላይ ለፈሰሰው የጻድቃን ደም ሁሉ ተጠያቂ ትሆናላችሁ።+ 36 እውነት እላችኋለሁ፣ እነዚህ ነገሮች ሁሉ በዚህ ትውልድ ላይ ይደርሳሉ።
37 “ኢየሩሳሌም፣ ኢየሩሳሌም፣ ነቢያትን የምትገድል! ወደ እሷ የተላኩትንም በድንጋይ የምትወግር!+ ዶሮ ጫጩቶቿን በክንፎቿ ሥር እንደምትሰበስብ እኔም ልጆችሽን ለመሰብሰብ ስንት ጊዜ ፈለግኩ! እናንተ ግን አልፈለጋችሁም።+ 38 እነሆ፣ ቤታችሁ* ለእናንተ የተተወ ይሆናል።*+ 39 ስለዚህ እላችኋለሁ፣ ‘በይሖዋ* ስም የሚመጣ የተባረከ ነው!’+ እስክትሉ ድረስ ከእንግዲህ ወዲህ ፈጽሞ አታዩኝም።”