ረቢ ተብሎ ሊጠራ የሚገባው ማን ነው?
የተሽከርካሪዎች መጨናነቅ ይኖራል ብሎ ያልጠበቀ ጎብኚ በዚህ ዕለት በሰዓቱ የመድረሱ ጉዳይ ፈጽሞ የማይታሰብ ነበር። በመቶ የሚቆጠሩ ፖሊሶች የኢየሩሳሌምን ጎዳናዎች ያጨናነቁትን ከ300,000 የሚበልጡ ሐዘንተኞች ለመጠበቅና የተሽከርካሪዎችን ዝውውር ለማስተናገድ ሞክረዋል። ዘ ጀሩሳሌም ፖስት “በፕሬዚዳንቶች፣ በነገሥታት ወይም ፈላጭ ቆራጭ መሪዎች ሥርዓተ ቀብር ላይ የሚታየውን ያክል ብዙ ሕዝብ የተገኘበት የቀብር ሥነ ሥርዓት ነበር” ሲል ገልጾታል። የእስራኤል ዋና ከተማ እንቅስቃሴ ለሰዓታት እስኪተጓጎል ድረስ ይህን ያህል ልዩ ግምት የተሰጣቸው ሰው ማን ነበሩ? አንድ የተከበሩ ረቢ ናቸው። ረቢዎች በአይሁዳውያን ዘንድ ይህን ያህል ክብርና ልዩ ግምት የሚሰጣቸው ለምንድን ነው? “ረቢ” የሚለውን ቃል መጠቀም የተጀመረው መቼ ነው? ረቢ ተብሎ በትክክል ሊጠራ የሚገባው ማን ነው?
ሙሴ ረቢ ነበርን?
የእስራኤል የሕግ ቃል ኪዳን መካከለኛ ሆኖ ያገለገለው ሙሴ ስሙ በአይሁድ እምነት ዘንድ ከማንኛውም ስም ይበልጥ የተከበረ ነው። ሃይማኖተኛ አይሁዳውያን “‘ረቢያችን’ ሙሴ” ብለው ይጠሩታል። ይሁን እንጂ ሙሴ በየትኛውም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ውስጥ “ረቢ” በሚለው የማዕረግ ስም ተጠርቶ አያውቅም። እንዲያውም “ረቢ” የሚለው ቃል በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ጨርሶ አይገኝም። ታዲያ አይሁዳውያን ሙሴን እንዲህ ብለው መጥራት የጀመሩት እንዴት ነው?
በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ እንደተገለጸው የማስተማሩ እንዲሁም ሕጉን የማብራራቱ ኃላፊነትና ሥልጣን ለአሮን ልጆች ማለትም ከሌዊ ነገድ ለሆኑት ካህናት የተሰጠ ነበር። (ዘሌዋውያን 10:8-11፤ ዘዳግም 24:8፤ ሚልክያስ 2:7) ይሁን እንጂ ከሁለተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ አንስቶ በአይሁዳውያን አስተሳሰብ ላይ ከፍተኛ ለውጥ ያስከተለ እንቅስቃሴ በአይሁድ እምነት መካከል ተቀሰቀሰ።
ይህን ከፍተኛ ለውጥ በተመለከተ ዳንኤል ጀርሜ ሲልቨር፣ ኤ ሂስትሪ ኦቭ ጁዳይዝም በተባለው መጽሐፍ ውስጥ እንደሚከተለው በማለት አስፍረዋል፦ “በዚያ ጊዜ ከካህናት ወገን ያልሆኑ ጻፎችንና ምሁራንን ያቀፈ አንድ ቡድን የቶራህን [የሙሴን ሕግ] ትርጓሜ የማብራራቱ መብት የካህናት ብቻ መሆን የለበትም የሚል ግድድር አስነሣ። ካህናት የቤተ መቅደሱን አስተዳደር መያዝ እንደሚገባቸው ሁሉም ተስማምተው የነበረ ቢሆንም ከቶራህ ጋር ግንኙነት ባላቸው ጉዳዮች ሁሉ ላይ እነርሱ የመጨረሻ ባለ ሥልጣን የሚሆኑት ለምንድን ነው? ብለው ተከራክረዋል።” የካህናቱ ክፍል ባለው ሥልጣን ላይ ይህ ግድድር እንዲነሣ የቆሰቆሱት እነማን ናቸው? በዚያው በአይሁድ እምነት መካከል የበቀለ ፈሪሳውያን ተብሎ የሚጠራ አንድ ቡድን ነው። ሲልቨር ሐሳባቸውን በመቀጠል “ፈሪሳውያን ወደ ትምህርት ቤቶቻቸው ለመግባት ፈቃድ የሰጡት በውልደት [የካህናት ዝርያ ለሆኑት] ሳይሆን ብቃቱን ላሟሉት ነበር፤ በመሆኑም አንድ አዲስ የአይሁዳውያን ቡድን ሃይማኖታዊ አመራሩን እንዲጨብጥ አደረጉ” ብለዋል።
በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ ከእነዚህ የፈሪሳውያን ትምህርት ቤቶች የተመረቁ ሁሉ የአይሁዳውያን ሕግ አስተማሪዎች ወይም መምህራን በመባል ይታወቁ ጀመር። ሌሎች አይሁዳውያን ደግሞ አክብሮታቸውን ለማሳየት “አስተማሪዬ” ወይም “መምህሬ” ብለው መጥራት ጀመሩ፤ በዕብራይስጥ ረቢ ማለት ነው።
ይህ አዲስ የማዕረግ ስም ተቀባይነት እንዲያገኝ ለማድረግ በአይሁዳውያን ታሪክ ውስጥ ከተነሡት አስተማሪዎች ሁሉ የሚበልጥ ታላቅ አስተማሪ ተደርጎ የሚታየውን ሙሴን በዚህ የማዕረግ ስም ከመሰየም የተሻለ ዘዴ አልነበረም። ይህም ለክህንነት ይሰጥ የነበረውን ትኩረት የሚያመናምንና የበላይነቱ እየገነነ የመጣውን የፈሪሳውያንን አመራር በሕዝቡ መካከል ይበልጥ የሚያሰርጽ ነበር። በዚህ መንገድ ሙሴ ከሞተ ከ1,500 ከሚበልጡ ዓመታት በኋላ “ረቢ” የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል።
መምህሩን መምሰል
ብዙሐኑ አይሁዳውያን “ረቢ” (“መምህሬ”) የሚለውን ቃል የሚጠቀሙበት የሚያከብሯቸውን አስተማሪዎች ሁሉ ለመጥራት ቢሆንም ቃሉ ብዙውን ጊዜ የሚሠራበት በፈሪሳውያን መካከል ያሉትን የላቀ ቦታ የሚሰጣቸው አስተማሪዎች ማለትም “ጠቢባኑን” ለማመልከት ነበር። በ70 እዘአ ቤተ መቅደሱ ሲደመሰስ የክህንነቱ ሥልጣን ስላከተመለት ፈሪሳውያን ረቢዎች ተቀናቃኝ የሌለባቸው የአይሁድ እምነት መሪዎች ሆኑ። ተቀናቃኝ የሌለበት ሥልጣናቸው የረቢ ጠቢባንን በዋነኝነት ያቀፈ የመናፍቃን ቡድን እንዲፈጠር በር ከፍቷል።
ፕሮፌሰር ዶቭ ዝሎትኒክ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ስለነበረው ስለዚህ የሽግግር ዘመን ሲተርኩ እንዲህ ብለዋል፦ “ቶራህን ከማጥናት ይልቅ ‘ጠቢባኑ የሚያደርጉትን በትኩረት መከታተል’ የላቀ ግምት የሚሰጠው ነገር ሆኖ ነበር።” የአይሁድ ምሁር የሆኑት ጃኮብ ኖይስነር እንደሚከተለው በማለት ተጨማሪ ማብራሪያ ሰተዋል፦ “‘የጠቢባኑ ደቀ መዝሙር’ ከአንድ ረቢ ጋር ተጣብቆ የሚኖር ተማሪ ነው። ይህን የሚያደርገው ‘ቶራህን’ ለመማር ሲል ነው። . . . ቶራህን የሚማረው ከሕጉ ሳይሆን ሕያዋን የሆኑት ጠቢባን በሚያሳዩት እንቅስቃሴና በሚፈጽሙት ድርጊት ሕጉ ሲተገበር በመመልከት ነው። ሕጉን የሚያስተምሩት በቃላቸው ብቻ ሳይሆን በድርጊታቸውም ጭምር ነው።”
የታልሙድ ምሁር የሆኑት አደን ሰቴንሳልትዝ እንደሚከተለው በማለት ይህን ሐሳብ የሚያጠናክር ነገር ፈዋል፦ “‘አፋቸው እንዳመጣላቸው የሚናገሩት ነገር፣ ቀልዶቻቸው ወይም ማንኛውም የዕለት ተዕለት ንግግራቸው መጠናት እንዳለበት’ ራሳቸው ጠቢባኑ ይናገራሉ።” ይህ አባባል እስከምን ድረስ ይሠራበታል? ስቴንሳልትዝ እንዲህ ብለዋል፦ “አንድ ተማሪ አስተማሪው ከሚስቱ ጋር የጾታ ግንኙነት የሚፈጽምበትን ሁኔታ ለመከታተል ሲል አልጋ ሥር ተደብቆ መገኘቱ ለዚህ ዓይነተኛ ምሳሌ ነው። ለምን ይህን ለማወቅ እንደፈለገ ሲጠየቅ ወጣቱ ደቀ መዝሙር ‘ቶራህ ስለሆነ ሊጠና ይገባዋል ’ ሲል መልስ ሰጥቷል፤ ይህ መልስ በረቢዎችም ሆነ በተማሪዎች ዘንድ ተቀባይነት አግኝቷል።”
ቶራህን በረቢዎች አማካኝነት ሲማሩ በትምህርቱ ውስጥ ከቶራህ ይበልጥ ተጋንኖ የሚገለጸው ነገር የረቢዎች አቋም በመሆኑ የአይሁድ እምነት ከመጀመሪያው መቶ ዘመን አንስቶ የረቢዎች የበላይነት የሰፈነበት ሃይማኖት ሆኗል። አንድ ሰው ወደ አምላክ የሚቀርበው የአምላክ መንፈስ ባለበት በጽሑፍ በሰፈረው ቃል አማካኝነት ሳይሆን አንድ መምህር ማለትም ረቢ በሚያሳየው ምሳሌነት አማካኝነት ነበር። በዚህም ምክንያት የሰዎቹ ትኩረት ያረፈው በመንፈስ አነሳሽነት በተጻፉት ቅዱሳን ጽሑፎች ላይ ሳይሆን ከእነዚህ ረቢዎች በቃል በሚነገረው ሕግና ወግ ላይ ነበር። ከዚያ ወዲህ ያሉት እንደ ታልሙድ የመሳሰሉት የአይሁዳውያን የጽሑፍ ሥራዎች ይበልጥ ያተኮሩት አምላክ በተናገራቸው ነገሮች ላይ ሳይሆን በረቢዎች ውይይት፣ በአንዳንድ ገጠመኞቻቸውና ጠባያቸው ላይ ነው።
ረቢዎች በእነዚህ ሁሉ ዘመናት የተጫወቱት ሚና
የጥንቶቹ ረቢዎች ከፍተኛ ሥልጣንና ተሰሚነት የነበራቸው ቢሆንም ከሃይማኖታዊ ሥራቸው የሚያገኙት ገቢ አልነበረም። ዘ ኢንሳይክሎፔድያ ጁዳይካ እንዲህ ይላል፦ “የታልሙዱ ረቢ . . . ዛሬ ይህን የማዕረግ ስም ከተሸከሙት ሰዎች ፈጽሞ የተለየ ነበር። የታልሙዱ ረቢ የመጽሐፍ ቅዱስንና በቃል የሚነገረውን ሕግ ትርጓሜ የሚያስረዳና የሚያብራራ ሲሆን ሁልጊዜ ማለት ይቻላል ኑሮውን ለማሸነፍ የሚያስችል ገቢ የሚያገኝበት ሥራ ይኖረዋል። ረቢዎች . . . አስተማሪ፣ ሰባኪና የአይሁዳውያን ጉባኤ ወይም ማኅበረሰብ መንፈሳዊ መሪ የሆኑት ከመካከለኛው ዘመን ወዲህ ነው።”
ረቢዎች ለሥራቸው ደሞዝ እንዲከፈላቸው ማድረግ ሲጀምሩ አንዳንዶች ተቃውሟቸውን አሰምተዋል። በሐኪምነት ሥራ ይተዳደር የነበረው የ12ኛው መቶ ዘመን የታወቀ ረቢ ማይሞኒደስ እንደነዚህ ያሉትን ረቢዎች አጥብቆ አውግዟቸዋል። “ከግለሰቦችና ከማኅበረሰቦች የገንዘብ ድጋፍ የሚደረግበትን መንገድ ከማመቻቸታቸውም በላይ ሕዝቡ ጠቢባኑን፣ ምሁራኑንና ቶራህን የሚያጠኑ ሰዎችን በገንዘብ የመደገፍ ግዴታ አለብን በሚል የሞኝነት አስተሳሰብ ቀንበር ውስጥ እንዲገባ አድርገውታል፤ በዚህ መንገድ ቶራህ መተዳደሪያቸው ሆነ። ይሁን እንጂ ይህ ስህተት ነው። በቶራህም ሆነ በጠቢባኑ ቃል ውስጥ ይህን ሐሳብ የሚደግፍ አንድም ቃል አይገኝም።” (ኮሜንታሪ ኦን ዘ ሚሽናህ፣ አቮት 4:5) ይሁን እንጂ ከዚያ በኋላ የመጡት የረቢ ትውልዶች የማይሞኒደስን ውግዘት ከቁብ አልቆጠሩትም።
አሁን ባለንበት የሥልጣኔ ዘመን ውስጥ የአይሁድ እምነት በተኃድሶ ቡድኖች፣ በአክራሪዎችና በኦርቶዶክስ እምነት ተከፋፍሏል። ለብዙዎቹ አይሁዳውያን ሃይማኖታዊ እምነትና ድርጊት ከሌሎች ጭንቀቶቻቸው ቀጥሎ ሁለተኛ ደረጃ የሚሰጣቸው ነገሮች ሆነዋል። ይህም ለረቢዎች የሚሰጠው ግምት እንዲቀንስ አድርጓል። በአመዛኙ ረቢዎች እየተከፈላቸው የሙያ ግዴታቸውን እንደሚወጡ አስተማሪዎችና ላሉበት ቡድን አባላት ምክር ሰጪ ሆነው እንደሚያገለግሉ የተሾሙ የጉባኤ ራስ ሆነዋል። ይሁን እንጂ አክራሪ ኦርቶዶክስ በሆኑት የሐሲዳውያን ቡድን መካከል ረቢዎች መምህርና ምሳሌ ናቸው የሚለው ጽንሰ ሐሳብ አድማሱን እያሰፋ ቀጥሏል።
ኤድዋርድ ሆፍማን ሐሲዳውያን ስላደረጉት ቻባድ ሉባቪቸር የተባለ እንቅስቃሴ በሚገልጸው መጽሐፋቸው ውስጥ ምን ብለው አስተያየት እንደሰጡ ልብ በል፦ “ከዚህ በተጨማሪ የጥንቱ ሄሲድዝም በእያንዳንዱ ትውልድ መካከል ዛዲክ [ጻድቅ]፣ የዘመኑ ‘ሙሴ’ የሚሆን፣ በምሁርነቱና ለሌሎች ባለው ፍቅር ማንም የማይተካከለው አንድ አይሁዳዊ መሪ እንደሚነሣ ጠበቅ አድርጎ ይገልጻል። እያንዳንዱ የሐሲድስም እምነት ቡድን የእነርሱ ሬቤ [በይዲሽ ቋንቋ “ረቢ” ማለት ነው] ከቅድስና ግርማው የተነሣ ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ካወጣቸው ድንጋጌዎች እንኳን ይበልጥ ተሰሚነት እንዳለው ያምናሉ። ምሳሌ እንደሆነ ተደርጎ ጥልቅ አክብሮት የሚቸረው በራእይ ቀመስ ንግግሮቹ ብቻ ሳይሆን አኗኗሩም (እንደነርሱ አገላለጽ፣ ‘ጫማ አስተሳሰሩ’) ስብዕናን የሚያስከብርና ወደ አምላክ የሚያደርሰውን መንገድ የሚያመላክት ጥበብ በመሆኑ ጭምር ነው።”
“እናንተ ግን ረቢ ተብላችሁ አትጠሩ”
ክርስትናን የመሠረተው የመጀመሪያው መቶ ዘመን አይሁዳዊ ኢየሱስ በምድር ላይ የኖረው ፈሪሳውያን ስለ ረቢዎች ያስፋፉት ጽንሰ ሐሳብ የአይሁድን እምነት ባጥለቀለቀበት ዘመን ላይ ነበር። እርሱ ፈሪሳዊ አልነበረም ወይም ደግሞ በእነርሱ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ገብቶ ሥልጠና አልተቀበለም፤ ይሁን እንጂ እርሱም ረቢ ተብሎ ተጠርቷል።—ማርቆስ 9:5፤ ዮሐንስ 1:38፤ 3:2
ኢየሱስ እንደሚከተለው በማለት በአይሁድ እምነት ውስጥ የነበረውን የፈሪሳውያን ዝንባሌ አውግዟል፦ “ጻፎችና ፈሪሳውያን በሙሴ ወንበር ተቀምጠዋል [“ራሳቸውን አስቀምጠዋል፣” አዓት]። በምሳም የከበሬታ ሥፍራ፣ በምኩራብም የከበሬታ ወንበር፣ በገበያም ሰላምታና፦ መምህር ሆይ መምህር ሆይ [“ረቢ፣” አዓት] ተብለው እንዲጠሩ ይወዳሉ እናንተ ግን መምህር [“ረቢ፣” አዓት] ተብላችሁ አትጠሩ፤ መምህራችሁ አንድ ስለሆነ እናንተም ሁላችሁ ወንድማማች ናችሁ።”—ማቴዎስ 23:2, 6-8
ኢየሱስ በአይሁድ እምነት ውስጥ እያቆጠቆጠ ከነበረው የቀሳውስትና የምዕመናን ክፍል ከሚለው የመከፋፈል ዝንባሌ እንዲቆጠቡ አስጠንቅቋል። ለሰዎች የማይገባቸውን ይህን መሰል ክብር መስጠትን አውግዟል። ‘መምህራችሁ አንድ ነው’ በማለት በልበ ሙሉነት ተናግሯል። ይህ አንዱ መምህር ማን ነበር?
“እግዚአብሔርን ፊት ለፊት ያወቀው” እና ጠቢባኑ ራሳቸው “የእኛ ረቢ” ብለው የሚጠሩት ሙሴ ፍጹም ሰው አልነበረም። አልፎ ተርፎም ስህተቶችን ፈጽሟል። (ዘዳግም 32:48-51፤ 34:10፤ መክብብ 7:20) የመጨረሻው ታላቅ ምሳሌ ሙሴ እንደሆነ አድርጎ ከማጋነን ይልቅ ይሖዋ እንደሚከተለው በማለት ነግሮታል፦ “ከወንድሞቻቸው መካከል እንደ አንተ ያለ ነቢይ አስነሣላቸዋለሁ፤ ቃሌንም በአፉ አደርጋለሁ፣ ያዘዝሁትንም ቃል ሁሉ ይነግራቸዋል፤ በስሜም የሚናገረውን ቃሌን የማይሰማውን ሰው እኔ እበቀልለታለሁ።”—ዘዳግም 18:18, 19
የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች እነዚህ ቃላት በመሲሑ በኢየሱስ ላይ ፍጻሜያቸውን እንዳገኙ ያረጋግጣሉ።a ኢየሱስ “እንደ” ሙሴ ከመሆንም አልፎ ከእርሱ የሚበልጥ ነበር። (ዕብራውያን 3:1-3) ቅዱሳን ጽሑፎች ኢየሱስ ፍጹም ሆኖ እንደተወለደና ከሙሴ በተለየ መልኩ አምላክን ‘ያለ አንዳች ኃጢአት’ እንዳገለገለ ይገልጻሉ።—ዕብራውያን 4:15
ምሳሌ የሆነውን ተከተሉ
አይሁዳውያን አንድ ረቢ የሚያደርገውንና የሚናገረውን ነገር ሁሉ በጥልቀት ማጥናታቸው ከአምላክ ጋር አላቀራረባቸውም። አንድ ፍጹም ያልሆነ ሰው የታመነ ትእዛዝ አክባሪ በመሆን ረገድ ምሳሌ ሊሆን ቢችልም እያንዳንዱን ድርጊቱን ካጠናንና ከኮረጅነው እንደ መልካም ጎኑ ሁሉ ስሕተቶቹንና አለፍጽምናውንም እንኮርጃለን። በፈጣሪ ፋንታ ለፍጡሩ የማይገባውን ክብር እንሰጣለን።—ሮሜ 1:25
ይሁን እንጂ ይሖዋ ለሰው ልጅ ምሳሌ የሚሆን አዘጋጅቷል። በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ እንደተገለጸው ኢየሱስ ሰው ከመሆኑም በፊት ሕልውና ነበረው። እንዲያውም “የማይታይ አምላክ ምሳሌ . . . ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኩር” ተብሎ ተጠርቷል። (ቆላስይስ 1:15) ኢየሱስ ቁጥር ስፍር ለሌላቸው ብዙ ሺህ ዓመታት በሰማይ የአምላክ “ዋና ሠራተኛ” ሆኖ ያገለገለ እንደመሆኑ መጠን ከማንም በተሻለ መንገድ ይሖዋን እንድናውቅ ሊረዳን ይችላል።—ምሳሌ 8:22-30፤ ዮሐንስ 14:9, 10
በመሆኑም ጴጥሮስ “ክርስቶስ ደግሞ ፍለጋውን [“በቅርብ፣” አዓት] እንድትከተሉ ምሳሌ ትቶላችሁ ስለ እናንተ መከራን ተቀብሎአልና” በማለት ጽፏል። (1 ጴጥሮስ 2:21) ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቲያኖች ‘የእምነታቸውን ራስና ፈጻሚ የሆነውን ኢየሱስን በትኩረት እንዲመለከቱ’ አበረታቷል። በተጨማሪም “የተሰወረ የጥበብና የእውቀት መዝገብ ሁሉ በእርሱ” እንደሆነ ገልጿል። (ዕብራውያን 12:2፤ ቆላስይስ 2:3) ሙሴም ሆነ የትኛውም የረቢ ጠቢብ ወይም ሌላ ሰው ይህን ያህል ክብር የሚገባው ማንም የለም። በቅርብ ምሳሌውን ልንኮርጀው የሚገባ አለ ቢባል ኢየሱስ ብቻ ነው። የአምላክ አገልጋዮች ረቢ የሚለውን የማዕረግ ስም በተለይ ደግሞ ዛሬ ከሚሰጠው ትርጉም አንጻር ለራሳቸው መጠቀም አያስፈልጋቸውም፤ ነገር ግን ረቢ ተብሎ ሊጠራ የሚገባው አለ ከተባለ ኢየሱስ ብቻ ነው።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ይመጣል ተብሎ የተነገረለት መሲሕ ኢየሱስ መሆኑን የሚያሳዩ ተጨማሪ ማስረጃዎችን ለማግኘት ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማሕበር የታተመውን ጦርነት የሌለበት ዓለም ይመጣ ይሆን? (የእንግሊዝኛ) የሚለውን ብሮሹር ገጽ 24-30 ተመልከት።
[ምንጭ]
© Brian Hendler 1995. የባለቤቱ መብት የተጠበቀ ነው።