አስቴር
3 ከዚህ በኋላ ንጉሥ አሐሽዌሮስ የአጋጋዊውን+ የሃመዳታን ልጅ የሃማን+ ዙፋን አብረውት ካሉት ከሌሎቹ መኳንንት ሁሉ በላይ በማድረግ ላቅ ያለ ሹመት ሰጠው፤ ደግሞም ከፍ ከፍ አደረገው።+ 2 በንጉሡ በር የነበሩት የንጉሡ አገልጋዮች በሙሉ ሃማን እጅ ይነሱትና ለእሱ ይሰግዱለት ነበር፤ ንጉሡ እንዲህ እንዲደረግለት አዝዞ ነበርና። መርዶክዮስ ግን እጅ ለመንሳትም ሆነ ለመስገድ ፈቃደኛ አልሆነም። 3 በመሆኑም በንጉሡ በር የነበሩት የንጉሡ አገልጋዮች መርዶክዮስን “የንጉሡን ትእዛዝ የማታከብረው ለምንድን ነው?” አሉት። 4 በየቀኑ ይህን ጉዳይ ቢያነሱበትም እሱ ግን ሊሰማቸው ፈቃደኛ አልሆነም። ከዚያም የመርዶክዮስ አድራጎት በቸልታ የሚታለፍ እንደሆነና+ እንዳልሆነ ለማየት ጉዳዩን ለሃማ ነገሩት፤ መርዶክዮስ አይሁዳዊ መሆኑን ነግሯቸው ነበርና።+
5 ሃማም መርዶክዮስ እሱን እጅ ለመንሳትና ለእሱ ለመስገድ ፈቃደኛ አለመሆኑን ባስተዋለ ጊዜ እጅግ ተቆጣ።+ 6 ሆኖም ስለ መርዶክዮስ ወገኖች ነግረውት ስለነበር መርዶክዮስን ብቻ ማስገደሉ* ተራ ነገር እንደሆነ ተሰማው። ስለዚህ ሃማ በመላው የአሐሽዌሮስ ግዛት የሚገኙትን አይሁዳውያን በሙሉ ማለትም የመርዶክዮስን ወገኖች በአጠቃላይ ለማጥፋት ዘዴ ይፈልግ ጀመር።
7 ንጉሥ አሐሽዌሮስ በነገሠ በ12ኛው ዓመት+ ኒሳን* በተባለው የመጀመሪያ ወር ላይ፣ ቀኑንና ወሩን ለመወሰን በሃማ ፊት ፑር+ (ዕጣ ማለት ነው) ጣሉ፤ ዕጣውም በ12ኛው ወር ማለትም በአዳር*+ ወር ላይ ወደቀ። 8 ከዚያም ሃማ ንጉሥ አሐሽዌሮስን እንዲህ አለው፦ “በግዛትህ ውስጥ ባሉት አውራጃዎች ሁሉ+ ተበታትኖና ተሰራጭቶ የሚገኝ፣+ የሚመራበትም ሕግ ከሌሎቹ ሕዝቦች ሁሉ የተለየ አንድ ሕዝብ አለ፤ የንጉሡንም ሕጎች አያከብርም፤ ንጉሡም ይህን ሕዝብ ዝም ብሎ መመልከቱ ይጎዳዋል። 9 ለንጉሡ መልካም መስሎ ከታየው እነዚህ ሰዎች እንዲጠፉ የሚያዝዝ ድንጋጌ በጽሑፍ ይውጣ። እኔም ወደ ንጉሡ ግምጃ ቤት እንዲያስገቡ ለባለሥልጣናቱ 10,000 የብር ታላንት* እከፍላለሁ።”*
10 በዚህ ጊዜ ንጉሡ የማኅተም ቀለበቱን ከእጁ አውልቆ+ የአይሁዳውያን ጠላት ለነበረው ለአጋጋዊው+ ለሃመዳታ ልጅ ለሃማ ሰጠው።+ 11 ንጉሡም ሃማን “ተገቢ መስሎ የታየህን እንድታደርግበት ብሩም ሆነ ሕዝቡ ለአንተ ተሰጥቷል” አለው። 12 ከዚያም በመጀመሪያው ወር 13ኛ ቀን የንጉሡ ጸሐፊዎች+ ተጠሩ። የሃማን ትእዛዝ ሁሉ በተለያዩ አውራጃዎች ላይ ለተሾሙት የንጉሡ አስተዳዳሪዎችና ገዢዎች እንዲሁም ለተለያዩ ሕዝቦች መኳንንት ጻፉ፤+ ለእያንዳንዱ አውራጃ በራሱ ጽሑፍ፣* ለእያንዳንዱም ሕዝብ በራሱ ቋንቋ ተጻፈ። ደብዳቤው የተጻፈው በንጉሥ አሐሽዌሮስ ስም ሲሆን በንጉሡ የማኅተም ቀለበትም ታተመ።+
13 ወጣት ሽማግሌ፣ ሕፃንም ሆነ ሴት ሳይባል አይሁዳውያን በጠቅላላ በአንድ ቀን ይኸውም አዳር+ በተባለው በ12ኛው ወር 13ኛ ቀን ላይ እንዲጠፉ፣ እንዲገደሉ፣ እንዲደመሰሱና ንብረታቸው እንዲወረስ+ የሚያዝዙ ደብዳቤዎች በመልእክተኞች አማካኝነት ወደ ንጉሡ አውራጃዎች ሁሉ ተላኩ። 14 ሕዝቡም ሁሉ ለዚያ ቀን ዝግጁ እንዲሆን ሲባል በደብዳቤዎቹ ላይ የሰፈረው ሐሳብ በሁሉም አውራጃዎች ውስጥ ሕግ ሆኖ እንዲደነገግና ለሕዝቡ ሁሉ እንዲታወጅ መመሪያ ተላለፈ። 15 መልእክተኞቹም ከንጉሡ ትእዛዝ የተነሳ ተጣድፈው ወጡ፤+ ሕጉም በሹሻን* ግንብ*+ ታወጀ። ከዚያም ንጉሡና ሃማ ሊጠጡ ተቀመጡ፤ የሹሻን* ከተማ ግን ግራ ተጋባች።