ለተሰሎንቄ ሰዎች የተጻፈ የመጀመሪያው ደብዳቤ
5 እንግዲህ ወንድሞች፣ ጊዜያትንና ወቅቶችን በተመለከተ ምንም ነገር እንዲጻፍላችሁ አያስፈልግም። 2 የይሖዋ* ቀን+ የሚመጣው ሌባ በሌሊት በሚመጣበት መንገድ+ መሆኑን እናንተ ራሳችሁ በሚገባ ታውቃላችሁና። 3 “ሰላምና ደህንነት ሆነ!” ሲሉ ምጥ እርጉዝ ሴትን እንደሚይዛት ያልታሰበ ጥፋት ድንገት ይመጣባቸዋል፤+ ደግሞም በምንም ዓይነት አያመልጡም። 4 እናንተ ግን ወንድሞች፣ በጨለማ ውስጥ ስላልሆናችሁ ሌሊቱ ድንገት እንደሚነጋበት ሌባ፣ ያ ቀን ድንገት አይደርስባችሁም፤ 5 እናንተ ሁላችሁ የብርሃን ልጆችና የቀን ልጆች ናችሁና።+ እኛ የሌሊት ወይም የጨለማ ልጆች አይደለንም።+
6 ስለዚህ ነቅተን እንኑር+ እንዲሁም የማስተዋል ስሜታችንን እንጠብቅ+ እንጂ እንደ ሌሎቹ አናንቀላፋ።+ 7 የሚያንቀላፉ ሰዎች፣ የሚያንቀላፉት በሌሊት ነው፤ የሚሰክሩም ቢሆኑ የሚሰክሩት በሌሊት ነው።+ 8 የቀን ልጆች የሆንነው እኛ ግን የማስተዋል ስሜታችንን እንጠብቅ፤ ደግሞም የእምነትንና የፍቅርን ጥሩር እንልበስ፤ የመዳንንም ተስፋ እንደ ራስ ቁር እንድፋ፤+ 9 ምክንያቱም አምላክ የመረጠን በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በኩል መዳን እንድናገኝ+ ነው እንጂ ለቁጣ አይደለም። 10 እሱ በሕይወት ብንኖርም ሆነ ብናንቀላፋ* አብረነው እንድንኖር+ ለእኛ ሞቶልናል።+ 11 ስለዚህ አሁን እያደረጋችሁት እንዳለው እርስ በርስ ተበረታቱ* እንዲሁም እርስ በርስ ተናነጹ።+
12 እንግዲህ ወንድሞች፣ በመካከላችሁ በትጋት እየሠሩና በጌታ ሥራ አመራር እየሰጧችሁ ያሉትን እንዲሁም ምክር እየለገሷችሁ ያሉትን እንድታከብሯቸው እንለምናችኋለን፤ 13 በተጨማሪም በሚያከናውኑት ሥራ የተነሳ በፍቅር ለየት ያለ አሳቢነት እንድታሳዩአቸው እንለምናችኋለን።+ እርስ በርሳችሁ ሰላማዊ ግንኙነት ይኑራችሁ።+ 14 በሌላ በኩል ደግሞ ወንድሞች፣ ይህን እናሳስባችኋለን፦ በሥርዓት የማይሄዱትን አስጠንቅቋቸው፤*+ የተጨነቁትን* አጽናኗቸው፤ ደካሞችን ደግፏቸው፤ ሁሉንም በትዕግሥት ያዙ።+ 15 ማንም ሰው በማንም ላይ በክፉ ፋንታ ክፉ እንዳይመልስ ተጠንቀቁ፤+ ከዚህ ይልቅ እርስ በርሳችሁም ሆነ ለሌሎች ሰዎች ሁሉ ምንጊዜም መልካም የሆነውን ነገር ለማድረግ ተጣጣሩ።+
16 ሁልጊዜ ደስ ይበላችሁ።+ 17 ዘወትር ጸልዩ።+ 18 ለሁሉም ነገር አመስግኑ።+ አምላክ በክርስቶስ ኢየሱስ ለእናንተ ያለው ፈቃድ ይህ ነው። 19 የመንፈስን እሳት አታጥፉ።+ 20 ትንቢቶችን አትናቁ።+ 21 ሁሉንም ነገር መርምሩ፤+ መልካም የሆነውን አጥብቃችሁ ያዙ። 22 ከማንኛውም ዓይነት ክፋት ራቁ።+
23 የሰላም አምላክ ራሱ ሙሉ በሙሉ ይቀድሳችሁ። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሚገኝበት ጊዜ መንፈሳችሁ፣ ነፍሳችሁና* አካላችሁ በማንኛውም ረገድ ጤናማ ይሁን፤ ደግሞም ነቀፋ አይገኝበት።+ 24 የጠራችሁ ታማኝ ነው፤ ይህን በእርግጥ ያደርገዋል።
25 ወንድሞች፣ ስለ እኛ መጸለያችሁን አታቋርጡ።+
26 ወንድሞችን ሁሉ በተቀደሰ አሳሳም ሰላም በሏቸው።
27 ይህ ደብዳቤ ለወንድሞች ሁሉ እንዲነበብ በጌታ አደራ እላችኋለሁ።+
28 የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን።