ዘዳግም
9 “እስራኤል ሆይ፣ ስማ፤ እንግዲህ ዛሬ ከአንተ ይልቅ ታላቅና ኃያል የሆኑ ብሔራትን+ እንዲሁም ታላላቅና እስከ ሰማያት የሚደርስ ቅጥር ያላቸውን ከተሞች+ በማስለቀቅ ወደ ምድሪቱ ለመግባት ዮርዳኖስን ልትሻገር ነው፤+ 2 ‘የኤናቅን ልጆች ማን ሊቋቋማቸው ይችላል?’ ሲባልላቸው የሰማኸውን፣ አንተ ራስህ የምታውቃቸውን ብርቱና ቁመተ ረጃጅም ሕዝብ የሆኑትን የኤናቅን ልጆችም+ ልታስለቅቅ ነው። 3 ስለሆነም አምላክህ ይሖዋ ዛሬ ከአንተ ቀድሞ እንደሚሻገር እወቅ።+ እሱ የሚባላ እሳት ነው፤+ ደግሞም ያጠፋቸዋል። ልክ ይሖዋ ቃል በገባልህ መሠረት በፍጥነት ታባርራቸውና* ታጠፋቸው ዘንድ ዓይንህ እያየ ድል ያደርጋቸዋል።+
4 “አምላክህ ይሖዋ እነሱን ከፊትህ በሚያባርራቸው ጊዜ በልብህ ‘ይሖዋ ይህችን ምድር እንድወርስ ወደዚህ ያመጣኝ እኮ በራሴ ጽድቅ ነው’ አትበል፤+ ይሖዋ እነዚህን ብሔራት ከፊትህ የሚያባርራቸው በራሳቸው ክፋት የተነሳ ነው።+ 5 የእነሱን ምድር ገብተህ የምትወርሰው ከጽድቅህ ወይም ከልብህ ቅንነት የተነሳ አይደለም። ከዚህ ይልቅ አምላክህ ይሖዋ እነዚህን ብሔራት ከፊትህ የሚያባርራቸው ከራሳቸው ክፋት የተነሳ ነው፤+ እንዲሁም ይሖዋ ለአባቶችህ ለአብርሃም፣+ ለይስሐቅና+ ለያዕቆብ+ የማለላቸውን ቃል ለመፈጸም ሲል ነው። 6 ስለዚህ አምላክህ ይሖዋ ይህችን መልካም ምድር እንድትወርሳት የሚሰጥህ ከጽድቅህ የተነሳ እንዳልሆነ እወቅ፤ ምክንያቱም አንተ ግትር* ሕዝብ ነህ።+
7 “በምድረ በዳ አምላክህን ይሖዋን እንዴት እንዳስቆጣኸው+ አስታውስ፤ ፈጽሞም አትርሳ። ከግብፅ ምድር ከወጣችሁበት ጊዜ አንስቶ እዚህ ቦታ እስክትደርሱ ድረስ በይሖዋ ላይ ዓምፃችኋል።+ 8 በኮሬብም እንኳ ይሖዋን አስቆጥታችሁት ነበር፤ ይሖዋም በእናንተ ላይ እጅግ ከመቆጣቱ የተነሳ እናንተን ለማጥፋት አስቦ ነበር።+ 9 እኔም የድንጋይ ጽላቶቹን+ ይኸውም ይሖዋ ከእናንተ ጋር የገባው ቃል ኪዳን የተጻፈባቸውን ጽላቶች+ ለመቀበል ወደ ተራራው በወጣሁ ጊዜ እህል ሳልበላና ውኃ ሳልጠጣ በተራራው ላይ 40 ቀንና 40 ሌሊት ቆይቼ ነበር።+ 10 ከዚያም ይሖዋ በአምላክ ጣት የተጻፈባቸውን ሁለቱን የድንጋይ ጽላቶች ሰጠኝ፤ በእነሱም ላይ ይሖዋ እዚያ ተሰብስባችሁ በነበረበት ቀን በተራራው ላይ በእሳት ውስጥ ሆኖ ለእናንተ የነገራችሁ ነገር ሁሉ ተጽፎባቸው ነበር።+ 11 ከ40 ቀንና ከ40 ሌሊት በኋላ ይሖዋ ሁለቱን የድንጋይ ጽላቶች ይኸውም የቃል ኪዳኑን ጽላቶች ሰጠኝ፤ 12 ይሖዋም እንዲህ አለኝ፦ ‘ተነስ፤ ቶሎ ብለህ ውረድ፤ ምክንያቱም ከግብፅ ያወጣኸው ሕዝብህ የጥፋት ጎዳና እየተከተለ ነው።+ እንዲከተሉት ካዘዝኳቸው መንገድ ፈጥነው ዞር ብለዋል። ከብረት የተሠራ ምስልም* ለራሳቸው አበጅተዋል።’+ 13 ከዚያም ይሖዋ እንዲህ አለኝ፦ ‘ይህን ሕዝብ አይቼዋለሁ፤ በእርግጥም ግትር* ሕዝብ ነው።+ 14 አጠፋቸውና ስማቸውን ከሰማይ በታች እደመስሰው ዘንድ ተወኝ፤ አንተን ግን ከእነሱ ይልቅ ኃያልና ብዙ ሕዝብ ያቀፈ ብሔር አደርግሃለሁ።’+
15 “እኔም ተራራው በእሳት እየተቀጣጠለ+ እያለ ተመልሼ ከተራራው ወረድኩ፤ ሁለቱን የቃል ኪዳን ጽላቶችም በእጆቼ ይዤ ነበር።+ 16 ከዚያም ስመለከት በአምላካችሁ በይሖዋ ላይ ኃጢአት እንደፈጸማችሁ አየሁ! ለራሳችሁም የብረት* ጥጃ ሠርታችሁ ነበር። ይሖዋ እንድትከተሉት ካዘዛችሁ መንገድ ፈጥናችሁ ዞር ብላችሁ ነበር።+ 17 ስለዚህ ሁለቱን ጽላቶች አሽቀንጥሬ በመወርወር ዓይናችሁ እያየ ሰባበርኳቸው።+ 18 ከዚያም እንደ መጀመሪያው ጊዜ ሁሉ ለ40 ቀንና ለ40 ሌሊት በይሖዋ ፊት ተደፋሁ። በይሖዋ ፊት መጥፎ የሆነውን ነገር በማድረግና እሱን በማስቆጣት በፈጸማችሁት ኃጢአት ሁሉ የተነሳ እህል አልቀመስኩም፤ ውኃም አልጠጣሁም።+ 19 ምክንያቱም ይሖዋ በእናንተ ላይ እጅግ ከመቆጣቱ የተነሳ ሊያጠፋችሁ ስለተዘጋጀ+ ፈርቼ ነበር። ይሁንና ይሖዋ በዚያን ጊዜም ሰማኝ።+
20 “ይሖዋ አሮንን ለማጥፋት እስኪያስብ ድረስ በእሱ ላይ ተቆጥቶ ነበር፤+ ሆኖም በዚያን ጊዜ ስለ አሮንም ምልጃ አቀረብኩ። 21 ከዚያም የኃጢአት ሥራችሁን ይኸውም ጥጃውን+ ወስጄ በእሳት አቃጠልኩት፤ ሰባበርኩት፤ እንደ አቧራ ብናኝ እስኪሆንም ድረስ ፈጨሁት፤ ብናኙንም ከተራራው በሚወርደው ጅረት ውስጥ በተንኩት።+
22 “በተጨማሪም በታበራ፣+ በማሳህ+ እና በቂብሮትሃታባ+ ይሖዋን አስቆጣችሁት። 23 ይሖዋ ከቃዴስበርኔ+ በላካችሁና ‘ውጡ፤ የምሰጣችሁንም ምድር ውረሱ!’ ባላችሁ ጊዜ በአምላካችሁ በይሖዋ ትእዛዝ ላይ በድጋሚ ዓመፃችሁ፤+ በእሱ አልታመናችሁም፤+ እንዲሁም አልታዘዛችሁትም። 24 እኔ እናንተን ካወቅኩበት ጊዜ አንስቶ በይሖዋ ላይ እንዳመፃችሁ ነው።
25 “በመሆኑም 40 ቀንና 40 ሌሊት በይሖዋ ፊት ተደፋሁ፤+ እንዲህ በፊቱ የተደፋሁት፣ ይሖዋ እንደሚያጠፋችሁ ተናግሮ ስለነበር ነው። 26 ከዚያም እንዲህ በማለት ይሖዋን መማጸን ጀመርኩ፦ ‘ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ ሆይ፣ ሕዝብህን አታጥፋ። እነሱ በታላቅነትህ የታደግካቸውና በኃያል ክንድህ ከግብፅ ያወጣሃቸው+ የግል ንብረቶችህ*+ ናቸው። 27 አገልጋዮችህን አብርሃምን፣ ይስሐቅንና ያዕቆብን አስብ።+ የዚህን ሕዝብ ግትርነት፣ ክፋትና ኃጢአት አትመልከት።+ 28 አለዚያ እኛን ባወጣህበት ምድር የሚገኙ ሰዎች “ይሖዋ ቃል ወደገባላቸው ምድር ሊያስገባቸው ስላልቻለና ስለጠላቸው በምድረ በዳ ሊገድላቸው አወጣቸው” ሊሉ ይችላሉ።+ 29 እነሱ በታላቅ ኃይልህና በተዘረጋ ክንድህ ያወጣሃቸው+ ሕዝቦችህና የግል ንብረቶችህ*+ ናቸው።’