8 ጥበብ እየተጣራች አይደለም?
ማስተዋልስ ድምፅዋን ከፍ አድርጋ እያሰማች አይደለም?+
2 በጎዳና አጠገብ በሚገኙ ከፍታ ቦታዎች፣+
መንገዶች በሚገናኙበት ቦታ ላይ ቆማለች።
3 ወደ ከተማዋ በሚያስገቡት በሮች አጠገብ፣
በደጆቹ መግቢያዎች ላይ
ድምፅዋን ከፍ አድርጋ ትጮኻለች፦+
4 “ሰዎች ሆይ፣ የምጣራው እናንተን ነው፤
ድምፄን ከፍ አድርጌ የማሰማው ለሁሉም ነው።
5 እናንተ ተሞክሮ የሌላችሁ፣ ብልሃትን ተማሩ፤+
እናንተ ሞኞች፣ አስተዋይ ልብ ይኑራችሁ።
6 የምናገረው ነገር በጣም አስፈላጊ ስለሆነ አዳምጡኝ፤
ከንፈሮቼ ትክክል የሆነውን ይናገራሉ፤
7 አንደበቴ በለሰለሰ ድምፅ እውነትን ይናገራልና፤
ከንፈሮቼም ክፋትን ይጸየፋሉ።
8 ከአፌ የሚወጡት ቃላት ሁሉ ጽድቅ ናቸው።
የተጣመመ ወይም የተወላገደ ነገር አይገኝባቸውም።
9 ጥልቅ ግንዛቤ ላለው፣ ሁሉም ቀና ናቸው፤
እውቀት ላላቸውም ትክክል ናቸው።
10 ከብር ይልቅ ተግሣጼን፣
ጥራት ካለውም ወርቅ ይልቅ እውቀትን ተቀበሉ፤+
11 ጥበብ ከዛጎል ትበልጣለችና፤
ተፈላጊ የሆኑ ሌሎች ነገሮች ሁሉ ከእሷ ጋር ሊወዳደሩ አይችሉም።
12 እኔ ጥበብ፣ ከብልሃት ጋር አብሬ እኖራለሁ፤
እውቀትና የማመዛዘን ችሎታ አግኝቻለሁ።+
13 ይሖዋን መፍራት ማለት ክፉ ነገርን መጥላት ነው።+
ትዕቢትን፣ ኩራትን፣+ ክፉ መንገድንና ጠማማ ንግግርን እጠላለሁ።+
14 ጥሩ ምክር መስጠት እችላለሁ፤ ማስተዋል የታከለበት ጥበብም አለኝ፤+
ማስተዋልና+ ኃይል+ የእኔ ናቸው።
15 ነገሥታት የሚገዙት በእኔ ነው፤
ከፍተኛ ባለሥልጣናትም የጽድቅ ድንጋጌ የሚያወጡት በእኔ ነው።+
16 መኳንንት የሚገዙት በእኔ ነው፤
ታላላቅ ሰዎችም በጽድቅ የሚፈርዱት በእኔ ነው።
17 የሚወዱኝን እወዳቸዋለሁ፤
የሚፈልጉኝም ያገኙኛል።+
18 ሀብትና ክብር፣
ዘላቂ ብልጽግናና ጽድቅ በእኔ ዘንድ አሉ።
19 ፍሬዬ ከወርቅ፣ አልፎ ተርፎም ከጠራ ወርቅ ይሻላል፤
ከእኔ የምታገኙት ስጦታም ጥራት ካለው ብር ይበልጣል።+
20 በጽድቅ መንገድ፣
በፍትሕ ጎዳና መካከል እጓዛለሁ፤
21 ለሚወዱኝ ውድ የሆኑ ነገሮችን አወርሳለሁ፤
ግምጃ ቤቶቻቸውንም እሞላለሁ።
22 ይሖዋ የመንገዱ መጀመሪያ አድርጎ ፈጠረኝ፤+
ከብዙ ዘመን በፊት ካከናወናቸው ሥራዎች ቀዳሚው አደረገኝ።+
23 ከጥንት፣ ከመጀመሪያው አንስቶ፣
ምድርም ከመፈጠሯ አስቀድሞ+ ከፍ ያለ ቦታ ተሰጠኝ።+
24 ጥልቅ ውኃዎች ባልነበሩበት ጊዜ፣+
ምንጮች ከመፍለቃቸው በፊት ተወለድኩ።
25 ተራሮች ገና ሳይመሠረቱ፣
ከኮረብቶች በፊት ተወለድኩ፤
26 ምድርንም ሆነ ሜዳዎቹን እንዲሁም
የመጀመሪያዎቹን የአፈር ጓሎች ከመሥራቱ በፊት ተወለድኩ።
27 ሰማያትን ባዘጋጀ ጊዜ+ በዚያ ነበርኩ፤
በውኃዎች ላይ የአድማስን ምልክት ባደረገ ጊዜ፣+
28 ደመናትን በላይ ባዘጋጀ ጊዜ፣
የጥልቅ ውኃ ምንጮችን በመሠረተ ጊዜ፣
29 የባሕሩ ውኃ
ከትእዛዙ አልፎ እንዳይሄድ በደነገገ ጊዜ፣+
የምድርን መሠረቶች ባቆመ ጊዜ፣
30 በዚያን ወቅት የተዋጣለት ሠራተኛ ሆኜ ከጎኑ ነበርኩ።+
በየዕለቱ በእኔ የተነሳ ልዩ ደስታ ይሰማው ነበር፤+
እኔም በፊቱ ሁልጊዜ ሐሴት አደርግ ነበር፤+
31 እሱ በፈጠረው፣ ሰው በሚኖርበት ምድር ሐሴት አደረግኩ፤
በተለይ ደግሞ በሰው ልጆች እጅግ እደሰት ነበር።
32 እንግዲህ ልጆቼ ሆይ፣ አዳምጡኝ፤
አዎ፣ መንገዴን የሚጠብቁ ደስተኞች ናቸው።
33 ተግሣጽን ስሙ፤+ ጥበበኞችም ሁኑ፤
ፈጽሞም ቸል አትበሉት።
34 በየዕለቱ በማለዳ በራፌ ላይ መጥቶ፣
በበሬ መቃን አጠገብ ቆሞ በመጠባበቅ
የሚያዳምጠኝ ሰው ደስተኛ ነው፤
35 እኔን የሚያገኝ ሕይወትን ያገኛልና፤+
በይሖዋም ዘንድ ሞገስ ያገኛል።
36 እኔን ችላ የሚል ግን ራሱን ይጎዳል፤
የሚጠሉኝ ሁሉ ሞትን ይወዳሉ።”+