11 አባይ ሚዛን በይሖዋ ዘንድ አስጸያፊ ነው፤
ትክክለኛ መለኪያ ግን ደስ ያሰኘዋል።+
2 እብሪት ከመጣ ውርደት ይከተላል፤+
ልካቸውን በሚያውቁ ዘንድ ግን ጥበብ ትገኛለች።+
3 ቅኖችን ንጹሕ አቋማቸው ይመራቸዋል፤+
ከዳተኞችን ግን ተንኮላቸው ያጠፋቸዋል።+
4 በቁጣ ቀን ሀብት ፋይዳ አይኖረውም፤+
ጽድቅ ግን ከሞት ይታደጋል።+
5 ነቀፋ የሌለበት ሰው የሚሠራው ጽድቅ መንገዱን ቀና ያደርግለታል፤
ክፉ ሰው ግን በገዛ ክፋቱ ይወድቃል።+
6 ቅኖችን ጽድቃቸው ያድናቸዋል፤+
ከዳተኞች ግን በገዛ ምኞታቸው ይጠመዳሉ።+
7 ክፉ ሰው ሲሞት ተስፋው መና ይቀራል፤
በኃይሉ ተመክቶ ተስፋ የሚያደርገው ነገርም ይጠፋል።+
8 ጻድቅ ከመከራ ይድናል፤
ክፉ ሰው ደግሞ በእሱ ቦታ ይተካል።+
9 ከሃዲ ሰው በአፉ ባልንጀራውን ያጠፋል፤
ጻድቃን ግን በእውቀት ይድናሉ።+
10 በጻድቃን ጥሩነት ከተማ ሐሴት ታደርጋለች፤
ክፉዎች ሲጠፉም እልልታ ይሆናል።+
11 በቅኖች በረከት ከተማ ከፍ ከፍ ትላለች፤+
የክፉዎች አፍ ግን ያፈራርሳታል።+
12 ማስተዋል የጎደለው ሰው ባልንጀራውን ይንቃል፤
ጥልቅ ግንዛቤ ያለው ሰው ግን ዝም ይላል።+
13 ስም የሚያጠፋ ሰው እየዞረ የሌሎችን ሚስጥር ይገልጣል፤+
እምነት የሚጣልበት ሰው ግን ሚስጥር ይጠብቃል።
14 ጥበብ ያለበት አመራር ሲጓደል ሕዝብ ይጎዳል፤
ብዙ አማካሪዎች ባሉበት ግን ስኬት ይገኛል።+
15 የማያውቀው ሰው ለወሰደው ብድር ዋስ የሚሆን ጉዳት ላይ መውደቁ አይቀርም፤+
እጅ በመምታት ቃል ከመግባት የሚቆጠብ ግን ምንም አይደርስበትም።
16 ሞገስ ያላት ሴት ክብር ታገኛለች፤+
ጨካኞች ግን ሀብት ያካብታሉ።
17 ደግ ሰው ራሱን ይጠቅማል፤+
ጨካኝ ሰው ግን በራሱ ላይ መከራ ያመጣል።+
18 ክፉ ሰው የሚያገኘው ደሞዝ እርባና የለውም፤+
ጽድቅን የሚዘራ ግን እውነተኛ ብድራት ያገኛል።+
19 ለጽድቅ ጽኑ አቋም ያለው ሰው ሕይወት የማግኘት ተስፋ አለው፤+
ክፋትን የሚያሳድድ ግን ለሞት መዳረጉ አይቀርም።
20 ይሖዋ ጠማማ ልብ ያላቸውን ሰዎች ይጸየፋል፤+
ነቀፋ በሌለበት ጎዳና የሚመላለሱ ግን ደስ ያሰኙታል።+
21 ይህን አትጠራጠር፦ ክፉ ሰው ከቅጣት አያመልጥም፤+
የጻድቃን ልጆች ግን ይድናሉ።
22 ማስተዋልን የምትንቅ ቆንጆ ሴት፣
በአሳማ አፍንጫ ላይ እንዳለ የወርቅ ቀለበት ናት።
23 የጻድቅ ምኞት መልካም ነገር ያስገኛል፤+
የክፉ ሰው ተስፋ ግን ወደ ቁጣ ይመራል።
24 አንዱ በልግስና ይሰጣል፤ ሆኖም ተጨማሪ ያገኛል፤+
ሌላው ደግሞ ለመስጠት ይሰስታል፤ ነገር ግን ለድህነት ይዳረጋል።+
25 ለጋስ ሰው ይበለጽጋል፤+
ሌሎችን የሚያረካም እሱ ራሱ ይረካል።+
26 እህል ለመሸጥ ፈቃደኛ ያልሆነውን ሕዝቡ ይረግመዋል፤
የሚሸጠውን ግን ይባርከዋል።
27 መልካም ነገር ለማድረግ የሚተጋ ሞገስ ለማግኘት ይጥራል፤+
መጥፎ ነገር ለማድረግ የሚፈልግ ግን ክፋቱ በራሱ ላይ እንደሚመጣ የተረጋገጠ ነው።+
28 በሀብቱ የሚታመን ሰው ይወድቃል፤+
ጻድቅ ግን እንዳማረ ቅጠል ይለመልማል።+
29 ቤተሰቡ ላይ ችግር የሚያመጣ ሰው ሁሉ ነፋስን ይወርሳል፤+
ሞኝ ሰውም ጥበበኛ ልብ ላለው ሰው አገልጋይ ይሆናል።
30 የጻድቅ ፍሬ የሕይወት ዛፍ ነው፤+
ነፍሳትንም የሚማርክ ጥበበኛ ነው።+
31 በእርግጥ ጻድቅ በምድር ላይ የሚገባውን ብድራት የሚቀበል ከሆነ
ክፉውና ኃጢአተኛው የሚቀበሉት ብድራትማ ምንኛ የከፋ ይሆን!+