16 ኢዮብ እንዲህ ሲል መለሰ፦
2 “ከዚህ በፊት እንዲህ ያሉ ብዙ ነገሮች ሰምቻለሁ።
ሁላችሁም የምታስጨንቁ አጽናኞች ናችሁ!+
3 ከንቱ ቃላት ማብቂያ የላቸውም?
እንዲህ ብለህ እንድትመልስ ያነሳሳህ ምንድን ነው?
4 እኔም እንደ እናንተ መናገር እችል ነበር።
እናንተ በእኔ ቦታ ብትሆኑ ኖሮ፣
አሳማኝ በሆነ መንገድ ልናገራችሁ እችል ነበር፤
በእናንተም ላይ ራሴን መነቅነቅ እችል ነበር።+
5 እንዲህ ከማድረግ ይልቅ በአፌ ቃል አበረታችሁ ነበር፤
የከንፈሮቼም ማጽናኛ ባሳረፋችሁ ነበር።+
6 ብናገር ከሥቃዬ አልገላገልም፤+
ዝም ብልስ ሥቃዬ ምን ያህል ይቀንስልኛል?
7 አሁን ግን አምላክ እንድዝል አድርጎኛል፤+
መላ ቤተሰቤን አጥፍቷል።
8 ደግሞም ያዝከኝ፤ ይህም ምሥክር ሆኖብኛል፤
በመሆኑም ክሳቴ ተነስቶ በፊቴ ይመሠክራል።
9 ቁጣው ቦጫጨቀኝ፤ በጥላቻ ተመለከተኝ።+
ጥርሱን አፋጨብኝ።
ባላጋራዬ በዓይኑ ወጋኝ።+
10 እነሱ አፋቸውን በሰፊው ከፈቱብኝ፤+
በንቀትም ጉንጬን አጮሉኝ፤
ብዙ ሆነው በእኔ ላይ ተሰበሰቡ።+
11 አምላክ ለልጆች አሳልፎ ሰጠኝ፤
በክፉዎችም እጅ ላይ ገፍትሮ ጣለኝ።+
12 ያለምንም ችግር እኖር ነበር፤ እሱ ግን ሰባበረኝ፤+
ማጅራቴን ይዞ አደቀቀኝ፤
ከዚያም ዒላማው አደረገኝ።
13 ቀስተኞቹ ከበቡኝ፤+
ኩላሊቴን ወጋ፤+ ምንም ርኅራኄ አላሳየኝም፤
ሐሞቴን መሬት ላይ አፈሰሰ።
14 እንደ ግንብ ሰንጥቆ ሰነጣጥቆ አፈራረሰኝ፤
እንደ ተዋጊ ተንደርድሮ መጣብኝ።
15 ቆዳዬን ለመሸፈን ማቅ ሰፍቻለሁ፤+
ክብሬንም አፈር ውስጥ ቀብሬአለሁ።+
16 ከለቅሶ የተነሳ ፊቴ ቀልቷል፤+
ድቅድቅ ጨለማም በዓይኖቼ ቆብ ላይ አጥልቷል፤
17 ይሁንና እጆቼ ምንም ዓመፅ አልሠሩም፤
ጸሎቴም ንጹሕ ነው።
18 ምድር ሆይ፣ ደሜን አትሸፍኚ!+
ጩኸቴም ማረፊያ ስፍራ አያግኝ!
19 አሁንም እንኳ ምሥክሬ በሰማያት አለ፤
ስለ እኔ መመሥከር የሚችል በከፍታ ቦታዎች ላይ ይገኛል።
20 ጓደኞቼ በእኔ ላይ ያፌዛሉ፤+
ዓይኔም ወደ አምላክ ያነባል።+
21 በሰውና በባልንጀራው መካከል የሚዳኝ እንደሚኖር፣
በሰውና በአምላክ መካከልም የሚዳኝ ይኑር።+
22 የሚቀሩት ዓመታት ጥቂት ናቸውና፤
እኔም በማልመለስበት መንገድ እሄዳለሁ።+