ዘዳግም
24 “አንድ ሰው አንዲት ሴት ቢያገባ ሆኖም ነውር የሆነ ነገር አግኝቶባት ቅር ቢሰኝ የፍቺ የምሥክር ወረቀት ጽፎ በመስጠት+ ከቤቱ ያሰናብታት።+ 2 እሷም ከእሱ ቤት ከወጣች በኋላ የሌላ ሰው ሚስት መሆን ትችላለች።+ 3 በኋላ ያገባትም ሰው ቢጠላትና የፍቺ የምሥክር ወረቀት ጽፎ በመስጠት ከቤቱ ቢያሰናብታት ወይም አግብቷት የነበረው ሁለተኛው ሰው ቢሞት 4 ከቤቱ አሰናብቷት የነበረው የመጀመሪያው ባለቤቷ ከረከሰች በኋላ እንደገና ሚስቱ አድርጎ እንዲወስዳት አይፈቀድለትም፤ ምክንያቱም ይህ በይሖዋ ፊት አስጸያፊ ነው። አምላክህ ይሖዋ ርስት አድርጎ በሚሰጥህ ምድር ላይ ኃጢአት አታምጣ።
5 “አንድ ሰው አዲስ ሙሽራ ከሆነ በሠራዊቱ ውስጥ ማገልገል የለበትም፤ ወይም ምንም ዓይነት ሌላ ሥራ ሊሰጠው አይገባም። ለአንድ ዓመት ያህል ከምንም ነገር ነፃ ሆኖ ይቆይ፤ በቤቱም ተቀምጦ ሚስቱን ያስደስታት።+
6 “ማንም ሰው ወፍጮን ወይም መጅን የብድር መያዣ አድርጎ መውሰድ የለበትም፤ ምክንያቱም የሰውየውን መተዳደሪያ* መያዣ አድርጎ መውሰድ ይሆንበታል።+
7 “አንድ ሰው ከእስራኤላውያን ወንድሞቹ መካከል አንዱን አፍኖ በመውሰድ በደል ሲፈጽምበትና ሲሸጠው+ ቢገኝ አፍኖ የወሰደው ሰው ይገደል።+ ክፉ የሆነውን ከመካከልህ አስወግድ።+
8 “የሥጋ ደዌ* ቢከሰት ሌዋውያን ካህናት የሚሰጧችሁን መመሪያዎች ሁሉ በጥንቃቄ ተከተሉ።+ እኔ የሰጠኋቸውንም ትእዛዝ በጥንቃቄ ፈጽሙ። 9 ከግብፅ በወጣችሁ ጊዜ መንገድ ላይ ሳላችሁ አምላካችሁ ይሖዋ በሚርያም ላይ ያደረገውን አስታውሱ።+
10 “ለባልንጀራህ ማንኛውንም ነገር ብታበድር+ መያዣ አድርጎ የሚሰጥህን ነገር ለመውሰድ ወደ ቤቱ አትግባ። 11 ውጭ ቆመህ ጠብቅ፤ ያበደርከውም ሰው መያዣ አድርጎ የሚሰጥህን ነገር ውጭ ድረስ ያምጣልህ። 12 ሰውየው ከተቸገረ መያዣ አድርጎ የሰጠህን ነገር አንተ ጋ አታሳድር።+ 13 ልክ ፀሐይ ስትጠልቅ መያዣውን ልትመልስለት ይገባል፤ እሱም ለብሶት ይተኛል፤+ ደግሞም ይባርክሃል፤ በአምላክህም በይሖዋ ፊት እንደ ጽድቅ ይቆጠርልሃል።
14 “ከወንድሞችህም ሆነ በምድርህ ይኸውም በከተሞችህ* ውስጥ ከሚኖሩ የባዕድ አገር ሰዎች መካከል የተቸገረውንና ድሃ የሆነውን ቅጥር ሠራተኛ አታታል።+ 15 ደሞዙን በዕለቱ ስጠው፤+ ችግረኛ በመሆኑና ሕይወቱ* የተመካው በደሞዙ ላይ ስለሆነ ፀሐይ ከመጥለቋ በፊት ስጠው። አለዚያ በአንተ የተነሳ ወደ ይሖዋ ይጮኻል፤ አንተም በኃጢአት ትጠየቃለህ።+
16 “አባቶች ልጆቻቸው በሠሩት ነገር መገደል የለባቸውም፤ ልጆችም አባቶቻቸው በሠሩት ነገር መገደል የለባቸውም።+ አንድ ሰው መገደል ያለበት በገዛ ኃጢአቱ ብቻ ነው።+
17 “የባዕድ አገሩን ሰው ወይም አባት የሌለውን* ልጅ ፍርድ አታዛባ፤+ የመበለቲቱን ልብስ የብድር መያዣ አድርገህ አትውሰድ።+ 18 አንተም በግብፅ ባሪያ እንደነበርክና አምላክህ ይሖዋ ከዚያ እንደተቤዠህ አስታውስ።+ እኔም ይህን እንድታደርግ የማዝህ ለዚህ ነው።
19 “በማሳህ ላይ ያለውን እህል በምታጭድበት ጊዜ በማሳው ላይ ነዶ ብትረሳ ያን ለመውሰድ አትመለስ። አምላክህ ይሖዋ የእጅህን ሥራ ሁሉ እንዲባርክልህ+ ለባዕድ አገሩ ሰው፣ አባት ለሌለው ልጅና ለመበለቲቱ እንዲሆን እዚያው ተወው።+
20 “የወይራ ዛፍህን በምታራግፍበት ጊዜ በየቅርንጫፉ ላይ የቀረውን ሙልጭ አድርገህ አታራግፈው። የቀረው ለባዕድ አገሩ ሰው፣ አባት ለሌለው ልጅና ለመበለቲቱ ይሁን።+
21 “ከወይን እርሻህ ላይ የወይን ፍሬህን በምትሰበስብበት ጊዜ ተመልሰህ ቃርሚያውን አትልቀም። ለባዕድ አገሩ ሰው፣ አባት ለሌለው ልጅና ለመበለቲቱ መተው አለበት። 22 አንተም በግብፅ ምድር ባሪያ እንደነበርክ አስታውስ። እኔም ይህን እንድታደርግ የማዝህ ለዚህ ነው።