የጋብቻን ማሰሪያ እንዴት ማጠንከር ይቻላል?
ታላቁ አስተማሪ ኢየሱስ ክርስቶስን ሊያጠምዱት ይሞክሩ የነበሩት ፈሪሳውያን “ሰው በሆነው ምክንያት ሁሉ ሚስቱን ሊፈታ ተፈቅዶለታልን?” ሲሉ ጠየቁት። እሱም የመጀመሪያዎቹን ሰዎች ጋብቻ በመጥቀስና “እግዚአብሔር ያጣመረውን እንግዲህ ሰው አይለየውም” በማለት ስለጉዳዩ አንድ የአቋም ደረጃ በማውጣት መለሰላቸው።
ፈሪሳውያንም ሙሴ “የፍችዋን ጽሕፈት ሰጥተው እንዲፈቱአት” ፈቅዷል ሲሉ ተከራከሩ። ኢየሱስም “ሙሴስ ስለ ልባችሁ ጥንካሬ ሚስቶቻችሁን ትፈቱ ዘንድ ፈቀደላችሁ ከጥንት ግን እንዲህ አልነበረም። እኔ ግን እላችኋለሁ፣ ያለ ዝሙት ምክንያት ሚስቱን ፈትቶ ሌላዪቱን የሚያገባ ሁሉ ያመነዝራል፣ የተፈታችውንም የሚያገባ ያመነዝራል” ሲል መለሰላቸው። — ማቴዎስ 19:3–9
በመጀመሪያ ላይ ጋብቻ ቋሚ ማሰሪያ እንዲሆን ታስቦ ነበር። የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት ለዘላለም የሚኖሩ ፍጹም ሰብአዊ ሰዎች ሆነው ስለተፈጠሩ ሞት እንኳን አይለያቸውም ነበር። ይሁን እንጂ ኃጢአት ሠሩ። የሠሩት ኃጢአት ሰብአዊውን ጋብቻ አበላሸው። ሞት የተባለው ጠላት የተጋቡ ባልና ሚስቶችን መለያየት ጀመረ። “ሴት ባልዋ በሕይወት ሳለ የታሰረች ናት፤ ባልዋ ቢሞት ግን በጌታ ይሁን እንጂ የወደደችውን ልታገባ ነጻነት አላት” የሚለውን ሐሳብ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደምናነበው አምላክ ሞትን የጋብቻ ፍጻሜ አድርጎ ይመለከተዋል። (1 ቆሮንቶስ 7:39) ከሞቱም በኋላ ጋብቻቸው በሌላ ዓይነት ሕይወት ይቀጥላል በሚል እምነት አንዲት ሚስት ባሏ በሚሞትበት ጊዜ ራሷን በእሳት አቃጥላ እንድትሞት ለማግባባት ከሚሞክረው ወይም ከሚያስገድደው ሃይማኖታዊ አስተሳሰብ ይህ እንዴት የተለየ ነው።
በሙሴ ሕግ ውስጥ የነበረው ዝግጅት
የሙሴ ሕግ በተሰጠበት ጊዜ ከእስራኤላውያን ልበ ደንዳናነት የተነሳ ይሖዋ ፍቺን የሚፈቅድ ዝግጅት እስኪያደርግ ድረስ የጋብቻ ግንኙነት በጣም ተዳክሞ ነበር። (ዘዳግም 24:1) ይሖዋ ባልንጀሮቻቸውን እንደራሳቸው እንዲወዱ ከሰጠው ትዕዛዝ ለመረዳት እንደሚቻለው በጥቃቅን ስሕተቶች ሚስቶቻቸውን በመፍታት እስራኤላውያን በዚህ ሕግ አለአግባብ እንዲጠቀሙበት የአምላክ ዓላማ አልነበረም። (ዘሌዋውያን 19:18) የፍቺዋን ጽሕፈት መስጠቱ እንኳ ፍቺን ለመከላከል የሚያገለግል ነበር። ምክንያቱም ፍቺውን የሚፈልገው ባል የፍቺዋን ጽሕፈት ለመስጠት ከሚያደርጋቸው ነገሮች አንዱ ምናልባትም በእርቅ እንዲያልቅ ሊያደርጉ የሚችሉትን በወቅቱ የተሾሙ ሰዎች የግድ ማማከር አለበት። አምላክ ይህን ሕግ ያወጣው አንድ ሰው “በሆነው ምክንያት ሁሉ ሚስቱን” እንዲፈታት መብት ለመስጠት አልነበረም። — ማቴዎስ 19:3
ይሁን እንጂ እስራኤላውያን ከጊዜ በኋላ የሕጉን ትክክለኛ መንፈስ ችላ በማለት ይህን አንቀጽ እንደፈለጉ ለመፍታት ተጠቅመውበታል። በአምስተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ እስራኤላውያን በሆነ ባልሆነው ምክንያት ሚስቶቻቸውን በመፍታት የወጣትነት ሚስቶቻቸውን አለአግባብ ይይዟቸው ነበር። ይሖዋም ፍቺን እንደሚጠላ አጥብቆ ነግሯቸው ነበር። (ሚልክያስ 2:14–16) ኢየሱስ ከዚህ በመነሳት ነበር በእሱ ዘመን የነበሩት እስራኤላውያን ያደርጉት የነበረውን ፍቺ ያወገዘው።
ለፍቺ የሚያበቃው ተቀባይነት ያለው ብቸኛው መሠረት
ኢየሱስ ለፍቺ የሚያበቃ ተቀባይነት ያለውን አንድ መሠረት ጠቅሷል፤ እሱም ዝሙት ነው። (ማቴዎስ 5:31, 32፤ 19:8, 9) እዚህ ላይ “ዝሙት” ተብሎ የተተረጎመው ቃል ቅዱስ ጽሑፋዊ ከሆነው ጋብቻ ውጭ የሚደረገውን ማንኛውንም ተገቢ ያልሆነ የጾታ ግንኙነት ይጨምራል። ይህም ከተመሳሳይ ጾታ ጋር ወይም ከተቃራኒ ጾታ ወይም ከእንሰሳ ጋር ሊሆን ይችላል።
ያም ሆኖ ግን ኢየሱስ ታማኝነትን ያጎደሉ የትዳር ጓደኞችን መፍታት ጥሩ ነው ብሎ ምክር መስጠቱ አልነበረም። ነገሩ የሚያስከትለውን ልዩ ልዩ መዘዝ በማመዛዘን ለመፍታት ወይም ላለመፍታት የመወሰን መብት ያለው ታማኝ የሆነው የትዳር ጓደኛ ነው። በዚህ ቅዱስ ጽሑፋዊ ድጋፍ መሠረት ባላቸውን ለመፍታት የሚያስቡ ሚስቶች አምላክ የመጀመሪያዋ ሴት ለሠራችው ኃጢአት ፍርዷን በነገራት ጊዜ የተናገረውን ነገር ጭምር ግምት ውስጥ ለማስገባት ይፈልጉ ይሆናል። ከሞት ፍርድ በተጨማሪ አምላክ ለሔዋን ለይቶ “ፈቃድሽም ወደ ባልሽ ይሆናል፣ እርሱም ገዥሽ ይሆናል” ሲል ነግሯታል። (ዘፍጥረት 3:16) በካርል ኤፍ ኬይል እና በፍራንዝ ዴልትሽ የተዘጋጀው ኮሜንታሪ ኦን ዘ ኦልድ ቴስታመንት የተባለው መጽሐፍ “ፈቃድሽ” ወይም በእንግሊዝኛው “ክሬቪንግ” የሚለውን ቃል “የበሽታ ያክል የሆነ ምኞት” በማለት ይገልጸዋል። እርግጥ ነው ይህ ምኞት በሁሉም ሚስቶች ላይ ይህን ያህል ጠንካራ አይደለም። ይሁን እንጂ አንዲት ንጹህ የሆነች ሚስት ባሏን ለመፍታት ስታስብ ሴቶች ከሔዋን የወረሱትን ስሜታዊ ፍላጎቶች በሚገባ ብታጤናቸው ጥበበኛ ትሆናለች። ሆኖም ጥፋተኛው የትዳር ጓደኛ ከጋብቻ ውጭ የፈጸመው የጾታ ግንኙነት ንጹህ የሆነችው የትዳር ጓደኛ ኤድስን ጨምሮ በጾታ በሚተላለፉ በሽታዎች እንድትበከል ሊያደርጋት ይችላል። ስለዚህ አንዳንዶች ኢየሱስ በገለጸው መሠረት ለመፋታት ወስነዋል።
የቤተሰብ ችግር መነሾዎች
የሰዎች ልበ ደንዳናነት በመጀመሪያ የመጣው የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት በአምላክ ላይ ከሠሩት ኃጢአት ነው። (ሮሜ 5:12) የመጀመሪያዎቹ ሰብአዊ ባልና ሚስት በሰማያዊ አባታቸው ላይ ኃጢአት ሲሠሩ ለቤተሰብ ጥል መሠረት የሚሆን ነገር ተጣለ። እንዴት? የመጀመሪያዋ ሴት ሔዋን ከተከለከለው የዛፍ ፍሬ እንድትበላ በእባብ በተፈተነችበት ጊዜ በቀጥታ ሄደችና ከፍሬው በላች። ይህን ከባድ ውሳኔ ካደረገች በኋላ ነበር እባቡ ስለነገራት ነገር ለባሏ የነገረችው። (ዘፍጥረት 3:6) አዎ፣ ባሏን ሳታማክር እርምጃ ወሰደች። ዛሬም ቢሆን ብዙ ቤተሰቦች ልክ ይህን የሚመስል ችግር ያጋጥማቸዋል። ልብ ለልብ የሐሳብ ግንኙነት አያደርጉም።
አዳምም ሆነ ሔዋን የሠሩት ኃጢአት ያስከተለባቸውን ውጤቶች ሲመለከቱ ዛሬ ያሉ ብዙ ባልና ሚስቶች ችግር ውስጥ በሚወድቁበት ጊዜ በሚጠቀሙበት ዘዴ ነው የተጠቀሙት። ይኸውም ጥፋትን በሌላው ላይ ማላከክ ነው። የመጀመሪያው ሰው አዳም “ከእኔ ጋር እንድትሆን የሰጠኸኝ ሴት እርስዋ ከዛፉ ሰጠችኝና በላሁ” በማለት ያደረገውን ነገር ሁሉ በሚስቱና በይሖዋ ላይ ደፈደፈ። ሴቲቱም በበኩሏ “እባብ አሳተኝና በላሁ” አለች። — ዘፍጥረት 3:12, 13
ይሖዋ በአዳምና በሔዋን ላይ ያስተላለፈው ፍርድ ወደፊት የሚፈጠሩ ሌሎች ችግሮችንም የሚጠቁሙ ነበሩ። ይሖዋ ሔዋን ከባሏ ጋር የሚኖራትን ግንኙነት በተመለከተ “እርሱም ገዥሽ ይሆናል” ሲል ነገራት። በመጀመሪያው ርዕሳችን ላይ እንደተጠቀሰው ኢሶኦ ዛሬ ብዙ ባሎች ለሚስቶቻቸው ስሜት ምንም ሳይጨነቁ ሚስቶቻቸውን በጭካኔ ይገዟቸዋል። ያም ሆኖ ብዙ ሚስቶች የባሎቻቸውን ትኩረት ለማግኘት በጣም ይጓጓሉ። ይህን ምኞታቸውን ባሎቻቸው ሳያሟሉላቸው ሲቀሩ ሚስቶች የባሎቻቸውን ትኩረት በግድ ለማግኘት ሊሞክሩና የራስ ወዳድነት እርምጃ ሊወስዱ ይችላሉ። ብዙ ባሎች ጨቋኝ ስለሚሆኑና ብዙ ሚስቶች ደግሞ ለባሎቻቸው ጠንካራ ፍላጎት ስላላቸው ራስ ወዳድነት ያሸንፍና ሰላም ይጠፋል። ሸንስክ ሰሬዛው “ሀው ቱ አናላይዝ ቱዴይስ ዲቮርስስ” በሚል ርዕስ ስር በጻፉት ጽሑፍ “ሰዎች ያላቸውን ለራሳቸው ፍላጎት ቅድሚያ የመስጠት ዝንባሌ ችላ ካልነው ዛሬ ያለውን የፍቺ ሁኔታ ለመመርመር ድንገት የማይቻል ሆኖ እናገኘዋለን” ሲሉ ተናግረዋል።
ታዛዥ የሆኑ ባልና ሚስቶች ፍጽምና በጎደለው ሁኔታቸው እንኳን ከጋብቻ የተወሰነ ደስታ ማግኘት እንዲችሉ ይሖዋ በቃሉ ውስጥ መመሪያ ሰጥቷል። ኢሶኦ የአምላክን መመሪያ በመከተሉ አሁን አስደሳች የቤተሰብ ኑሮ አግኝቷል። የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች የጋብቻን ማሰሪያ በማጠንከር ረገድ ሰዎችን እንዴት ሊረዱ እንደሚችሉ እስቲ እንመልከት።
ነገሮችን በግልጽ መነጋገር
በብዙ ጋብቻዎች ውስጥ የሐሳብ ግንኙነት አለመኖሩ፣ ጥፋትን በሌሎች ላይ የማላከክና የራስ ወዳድነት ዝንባሌ መኖሩ ባልና ሚስት እርስ በርስ በስሜት መግባባት አዳጋች እንዲሆንባቸው ያደርጋል። ተመራማሪው ካሪል ኤስ አቨሪ “በጣም ለመቀራረብ መጀመሪያ ስሜትን ማካፈል ስለሚጠይቅ በጣም መቀራረብ ሙሉ በሙሉ መተማመንን ይጠይቃል። ዛሬ ደግሞ መተማመን የለም” ሲሉ ተናግረዋል። ዘወትር የውስጥ ስሜቶችን ማካፈል እንዲህ ዓይነቱን መተማመን ይገነባል። ይህም በባልና በሚስት መካከል ልብ ለልብ የሐሳብ ግንኙነት ማድረግን ይጠይቃል።
የምሳሌ መጽሐፍ ሚስጥራዊ ሐሳቦችን ማካፈልን ለማበረታታት “ምክር በሰው ልብ ውስጥ እንደ ጠሊቅ ውኃ ነው፤ አእምሮ ያለው ሰው ግን ይቀዳዋል” በማለት በምሳሌ ይጠቀማል። (ምሳሌ 20:5) የትዳር ጓደኛሞች አስተዋይ መሆንና በትዳር ጓደኛቸው ልብ ውስጥ ያሉትን ጥልቅ ሐሳቦች መቅዳት አለባቸው። የትዳር ጓደኛህ ወይም የትዳር ጓደኛሽ ተናድዷል እንበል። “ዛሬ እኔ ራሴ ደህና አልዋልኩም” ብሎ ከመመለስ ይልቅ “ዛሬ ደህና አልዋልሽም እንዴ? ምን ሆንሽ?” ብለህ ለምን በደግነት አትጠይቃትም። የትዳር ጓደኛን ለመስማት ጊዜንና ጥረትን ሊጠይቅ ይችላል። ይሁን እንጂ እንደዚያ ማድረግህ የሚያረካና ይበልጥ የሚያስደስት ነው። ደግሞም የትዳር ጓደኛን ችላ በማለትና በኋላ ታምቆ የቆየው ስሜት ገንፍሎ ሲወጣ ነገሩን ለማስተካከል ከሚፈጀው ጊዜ ያነሰ ነው።
እርስ በርስ መተማመን እንዲኖር እያንዳንዱ የትዳር ጓደኛ ሐቀኛ መሆንና ስሜቱን ሌላው የትዳር ጓደኛ ሊረዳው በሚችለው መንገድ ለመግለጽ መሞከር አለበት። የአምላክ ቃል “እርስ በርስ ብልቶች ሆነናልና . . . እውነትን ተነጋገሩ” ሲል አጥብቆ ያሳስበናል። (ኤፌሶን 4:25) እውነትን መናገር አስተዋይነትን ይጠይቃል። ለምሳሌ ሚስት የሚሰማት እንደሌለ ሆኖ ይሰማታል እንበል። ከመናገሯ በፊት የሚከተለውን ምሳሌ ማጤን ይኖርባታል:- “ጥቂት ቃልን የሚናገር አዋቂ ነው፣ መንፈሱም ቀዝቃዛ የሆነ አስተዋይ ነው።” (ምሳሌ 17:27) “በፍጹም አትሰማኝም!” ብላ ባሏን ከመክሰስ ይልቅ በውጧ ብስጭትና ተስፋ መቁረጥ ከማደጉ በፊት ረጋ ባለ ሁኔታ ስሜቷን ብትገልጽለት በጣም የተሻለ ይሆናል። ምናልባትም እንደሚከተለው በማለት እንዴት እንደሚሰማት ልትገልጽለት ትችላለች:- “ሥራ እንደሚበዛብህ አውቃለሁ፤ ይሁን እንጂ ለጥቂት ጊዜ ከአንተ ጋር መጫወት ብችል በጣም ደስ ይለኛል።”
እውነት ነው “ምክር ከሌለች ዘንድ የታሰበው ሳይሳካ ይቀራል።” (ምሳሌ 15:22) የትዳር ጓደኛህ ትወድሃለች፤ ይህን ማለት ግን በአእምሮህ ውስጥ ያለውን ማንበብ ትችላለች ማለት አይደለም። ለትዳር ጓደኛህ እንዴት እንደሚሰማህ ቅር በማያሰኝ መንገድ ማሳወቅ አለብህ። ክርስቲያን ባልና ሚስቶች እንደመሆናችሁ መጠን “በሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ” እንድትተጉ ፍቅራዊ ማስተካከያዎችን እንድታደርጉ ይህ ይረዳችኋል። — ኤፌሶን 4:2, 3
ለምሳሌ ያህል ካዙዎ የሚባለውን ከፍተኛ የቁማር ሱስ ያለበትን ባል እንውሰድ። ውሎ አድሮ በብዙ መቶ ሺህ ዶላር እዳ ውስጥ ተዘፈቀ። እዳውን ለመክፈል ገንዘብ እየተበደረ የባሰ ማጥ ውስጥ እየሰመጠ ሄደ። ከዚያም መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረና ስላለበት ችግር ለሚስቱ ለመንገር ድፍረት አገኘ። የምታመጣውን ክስ ሁሉ ለመጋፈጥ ዝግጁ ነበር። ነገር ግን ከእሱ ረዘም ላለ ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስን ታጠና የነበረችው ሚስቱ ረጋ ብላ “እዳውን እንዴት እንደምንከፍለው ዘዴ እንፈልግ” ብላ ስትመልስለት በጣም ተገረመ።
ከሚቀጥለው ቀን ጀምረው ቤታቸውን እንኳ ሳይቀር በመሸጥ ወደተበደሯቸው ሰዎች በመሄድ እዳቸውን መክፈል ጀመሩ። እዳውን ለማስተካከል ወደ አንድ ዓመት ገደማ ፈጀባቸው። ሚስቱን ኪሚን የለወጣት ምን ነበር? እንዲህ ትላለች:- “በፊልጵስዩስ ምዕራፍ 4 ቁጥር 6 እና 7 ላይ ያሉት ቃላት በእርግጥ እውነት ናቸው። ‘በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችሁን አስታውቁ እንጂ በአንዳች አትጨነቁ። አእምሮን ሁሉ የሚያልፍ የእግዚአብሔር ሰላም ልባችሁንና አሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል።’” አክላም እንዲህ ብላለች:- “አንዲት ወዳጄ ይህ ሁሉ ችግር ቢደርስብኝም እንዴት ደስተኛ እንደሆንኩ አይታ በመገረሟ ከእኔ ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀምራለች።” ካዙዎና ሚስቱ አሁን ተጠምቀው ደስተኛ የቤተሰብ ኑሮ እየመሩ ነው።
ከላይ ያለው ተሞክሮ የነበራቸው ባልና ሚስት እውነቱን በመነጋገር እርስ በርስ ከመተማመን በተጨማሪ የጋብቻ ችግሮቻቸውን ለመፍታት የሚረዷቸው አንዳንድ ነገሮችን አድርገዋል። የጋብቻ ዝግጅት መሥራች ከሆነው ከይሖዋ አምላክ ጋር የሐሳብ ግንኙነት አድርገው ነበር። ባልና ሚስቶች የይሖዋን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሥራ ላይ ለማዋል የተቻላቸውን ያህል ከጣሩና የቀረውን ለእሱ ከተውት ምንም እንኳ ተጽእኖዎችና አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢገጥሟቸውም አእምሮን ሁሉ በሚያልፈው የአምላክ ሰላም ሊባርካቸው ይችላል። በተለይ አብሮ መጸለይ በጣም ጠቃሚ ነው። ባልየው እሱና ሚስቱ ለሚያጋጥማቸው ማንኛውም ችግር የአምላክን መመሪያ በመፈለግ በአምላክ ፊት ‘ልቡን በማፍሰስ’ ቀዳሚ መሆን ይኖርበታል። (መዝሙር 62:8) ይሖዋ እንዲህ ዓይነቱን ጸሎት እንደሚሰማ የተረጋገጠ ነው።
አዎ፣ የጋብቻን ማሰሪያ ማጠንከር ይቻላል። በዚህ ብጥብጥ በበዛበት ዓለም ውስጥ ፍጽምና በጎደለው ሁኔታ እየኖሩም እንኳ የተጋቡ ባልና ሚስት ባላቸው ግንኙነት ብዙ ደስታ ማግኘት ይችላሉ። በመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር ከተዘጋጀው የቤተሰብህን ኑሮ አስደሳች አድርገው ከተባለው መጽሐፍ ተጨማሪ ተግባራዊ የሆኑ ሐሳቦችንና አምላካዊ ምክሮችን ልታገኝ ትችላለህ። ከዚህም በላይ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሥራ ላይ ለማዋል ከልብ የሚጥሩ ባልና ሚስቶች በቅርቡ አምላክ በሚያመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ ፍጹም በሆነ ፍቅር የመተሳሰር ተስፋ አላቸው።