ለዘመናዊው ኑሮ ተግባራዊ ጥቅም የሚሰጥ መጽሐፍ
በዛሬው ዓለም በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ምክር የሚሰጡ መጻሕፍት በጣም ተወዳጅ ሆነዋል። ይሁን እንጂ እነዚህ መጻሕፍት ብዙ ሳይቆዩ ጊዜ ያለፈባቸው ይሆኑና በሌላ መጻሕፍት ይተካሉ። መጽሐፍ ቅዱስስ? መጽሐፍ ቅዱስ ተጽፎ ያለቀው ወደ 2,000 ከሚጠጉ ዓመታት በፊት ነው። ቢሆንም የያዘው ጥንታዊ መልእክት ተሻሽሎ ወይም ዘመናዊ ይዘት እንዲኖረው ተደርጎ አያውቅም። ታዲያ እንዲህ ያለው መጽሐፍ ለዘመናችን ተግባራዊ የሆነ መመሪያ ሊሰጥ ይችላልን?
አንዳንዶች ፈጽሞ አይችልም ይላሉ። ዶክተር ኤላይ ኤስ ቼሰን “በአንድ የኬሚስትሪ መማሪያ ክፍል ውስጥ በ1924 በተጻፈ የኬሚስትሪ መማሪያ [መጽሐፍ] መጠቀም አለብን ብሎ ሊሟገት የሚደፍር ሰው ሊኖር አይችልም” ሲሉ ጽፈዋል። ይህን የጻፉት መጽሐፍ ቅዱስ ጊዜ ያለፈበት መጽሐፍ ነው ብለው ያመኑበትን ምክንያት ሲያስረዱ ነበር።1 ይህ የመከራከሪያ ሐሳብ ትክክል መስሎ ሊታይ ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ ከተጻፈ ወዲህ የሰው ልጅ ስለ አእምሮ ጤንነትና ስለ ሰብዓዊ ተፈጥሮ ብዙ እውቀት እንዳካበተ የሚካድ ነገር አይደለም። ታዲያ እንዲህ ያለ ጥንታዊ መጽሐፍ እንዴት ለዘመናዊው ኑሮ ሊጠቅም ይችላል?
ዘመን ያልሻራቸው መሠረታዊ ሥርዓቶች
ዘመናት የተለዋወጡ ቢሆንም መሠረታዊ የሆኑ የሰው ልጅ ፍላጎቶች ግን አልተለወጡም። በየትኛውም ዘመን የኖሩ ሰዎች ቢሆኑ ለመፈቀርና ለመወደድ ይፈልጉ እንደነበረ ግልጽ ነው። ደስተኛ ለመሆንና ትርጉም ያለው ኑሮ ለመኖር ይፈልጉ ነበር። ኢኮኖሚያዊ ተጽእኖዎችን እንዴት እንደሚቋቋሙ፣ ትዳራቸውን እንዴት ለማሳካት እንደሚችሉና ልጆቻቸውን በመልካም ሥነ ምግባር እንዴት ቀርጸው እንደሚያሳድጉ የሚጠቁሙ ምክሮች ማግኘት አስፈልጓቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ እነዚህን በጣም አስፈላጊ የሆኑ መሠረታዊ ነገሮች በተመለከተ ምክር ይሰጣል።—መክብብ 3:12, 13፤ ሮሜ 12:10፤ ቆላስይስ 3:18-21፤ 1 ጢሞቴዎስ 6:6-10
መጽሐፍ ቅዱስ የያዛቸው ምክሮች የሰውን ተፈጥሮና ባሕርይ በጥልቅ የተገነዘቡ መሆናቸውን ማስተዋል ይቻላል። ለዘመናዊው ኑሮ ተግባራዊ መመሪያ ከሚሰጡት ጊዜ የማይሽራቸው ግልጽ መሠረታዊ ሥርዓቶች መካከል ጥቂት ምሳሌዎችን ተመልከት።
ስለ ጋብቻ የተሰጠ ተግባራዊ መመሪያ
ቤተሰብ ይላል ዩ ኤን ክሮኒክል የተባለው ጽሑፍ “በጣም ረዥም ዕድሜ ያለውና እጅግ መሠረታዊ የሆነ፣ ትውልዶችን እርስ በርስ የሚያያይዝ ወሳኝ ሰንሰለት ነው።” ይሁን እንጂ ይህ “ወሳኝ ሰንሰለት” በሚያስደነግጥ ሁኔታ በመበጣጠስ ላይ ይገኛል። ክሮኒክል አክሎ እንደተናገረው “በዛሬው ጊዜ ባለው ዓለም ውስጥ በርካታ ቤተሰቦች ሕልውናቸውንና እንቅስቃሴያቸውን የሚፈታተኑ በርካታ ችግሮች ተደቅነውባቸዋል።”2 መጽሐፍ ቅዱስ ቤተሰብ ጸንቶ እንዲኖር የሚረዳ ምን ምክር ይሰጣል?
በመጀመሪያ ደረጃ መጽሐፍ ቅዱስ ባልና ሚስት አንዳቸው ለሌላው ማድረግ ስለሚገቧቸው ነገሮች ብዙ ምክር ይሰጣል። ለምሳሌ ያህል ባሎችን በተመለከተ እንዲህ ይላል:- “ባሎች ደግሞ እንደ ገዛ ሥጋቸው አድርገው የገዛ ሚስቶቻቸውን ሊወዱአቸው ይገባቸዋል። የገዛ ሚስቱን የሚወድ ራሱን ይወዳል፤ ማንም የገዛ ሥጋውን የሚጠላ ከቶ የለምና፣ ነገር ግን . . . ይመግበዋል ይከባከበውማል።” (ኤፌሶን 5:28, 29፤ ጋደል አድርገን የጻፍነው እኛ ነን።) ሚስት ደግሞ “ለባልዋ ጥልቅ አክብሮት እንዲኖራት” ተመክራለች።—ኤፌሶን 5:33 NW
እንደነዚህ ያሉትን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክሮች ሥራ ላይ ማዋል ምን ማለት እንደሚሆን እንመልከት። ሚስቱን ‘እንደ ገዛ አካሉ’ የሚወድ ባል ሚስቱን አይጠላም ወይም ጨካኝ አይሆንባትም። አይመታትም ወይም በቃልም ሆነ በስሜት አይበድላትም። ከዚህ ይልቅ ለገዛ ራሱ የሚያሳየውን አክብሮትና አሳቢነት ያሳያታል። (1 ጴጥሮስ 3:7) በዚህ ምክንያት ሚስቲቱ የምትወደድ መሆኗ ተሰምቷት በትዳርዋ ተማምና ትኖራለች። ይህን በማድረጉም ሴቶችን እንዴት መያዝ እንደሚገባ ለልጆቹ ጥሩ ምሳሌ ይተዋል። በሌላው በኩል ደግሞ ባልዋን ‘በጥልቅ የምታከብር’ ሚስት እርሱን ዘወትር በማዋረድና በመተቸት ክብሩን አትገፍም። ስለምታከብረው እምነት የሚጣልበት፣ ተቀባይነት ያለው፣ የሚወደድና የሚደነቅ ባል እንደሆነ ይሰማዋል።
ታዲያ እንዲህ ያለው ምክር በዚህ ዘመናዊ ዓለም ተግባራዊ ጥቅም ሊሰጥ ይችላልን? በቤተሰብ ሕይወት ላይ በርካታ ጥናት ያደረጉ ሊቃውንት ከዚህ ጋር ተመሳሳይ ወደሆነ መደምደሚያ ደርሰዋል። አንድ የቤተሰብ ምክር መስጫ ፕሮግራም አስተዳዳሪ እንዲህ ብለዋል:- “በጣም ጤናማ ሆነው ያገኘኋቸው ቤተሰቦች ጠንካራና ፍቅራዊ ዝምድና ያላቸው እናትና አባት ያሉባቸው ቤተሰቦች ናቸው። . . . በእናትና አባት መካከል ጠንካራ ዝምድና መኖሩ በልጆች ላይ የመተማመንና የመረጋጋት መንፈስ የሚያሳድር ይመስላል።”3
ባለፉት ዘመናት በሙሉ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ጋብቻ የሚሰጠው ምክር ቁጥር ስፍር የሌላቸው የቤተሰብ አማካሪዎች ጠቃሚ ናቸው ብለው ከሰጧቸው ምክሮች በሙሉ ይበልጥ አስተማማኝ ሆኖ ተገኝቷል። በርካታ ሊቃውንት ከቅርብ ጊዜ በፊት ፍቺ ጥሩ ካልሆነ ጋብቻ በቀላሉ የሚገላግል መፍትሔ እንደሆነ አድርገው ይመክሩ ነበር። ዛሬ ግን ብዙዎቹ ሊቃውንት ሰዎች በተቻላቸው መጠን ትዳራቸው ዘላቂ እንዲሆን ጥረት እንዲያደርጉ ይመክራሉ። ይሁን እንጂ እንዲህ ያለ ለውጥ የተደረገው በቀላሉ የማይገመት ጉዳት ከደረሰ በኋላ ነው።
መጽሐፍ ቅዱስ ግን ስለ ጋብቻ ሚዛኑን የጠበቀና አስተማማኝ የሆነ ምክር ሲሰጥ ቆይቷል። በአንዳንድ ከበድ ያሉ ሁኔታዎች መፋታት እንደሚፈቀድ ይናገራል። (ማቴዎስ 19:9) ቢሆንም በየጥቃቅኑ ምክንያት መፋታትን ያወግዛል። (ሚልክያስ 2:14-16) በተጨማሪም በጋብቻ ላይ መወስለትን ያወግዛል። (ዕብራውያን 13:4) ጋብቻ የእርስ በርስ መተሳሰር እንደሆነ ይናገራል። “ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፣ በሚስቱም ይጣበቃል፤ ሁለቱም አንድ ይሆናሉ” ይላል።a—ዘፍጥረት 2:24፤ ጋደል አድርገን የጻፍነው እኛ ነን፤ ማቴዎስ 19:5, 6
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ጋብቻ የሚሰጠው ምክር ዛሬም መጽሐፉ ከተጻፈበት ዘመን ባላነሰ መጠን ጠቃሚ ነው። ባልና ሚስት እርስ በርሳቸው ሲዋደዱና ሲከባበሩ እንዲሁም ትዳራቸው በሁለቱ መካከል ብቻ የተወሰነ ዝምድና እንደሆነ አድርገው ሲመለከቱ የትዳራቸው ሕልውና ይበልጥ አስተማማኝ ይሆናል። ቤተሰባቸውም ዘላቂ ይሆናል።
ለወላጆች የተሰጡ ተግባራዊ መመሪያዎች
ከበርካታ አሥርተ ዓመታት በፊት ወላጆች ስለ ልጆች አስተዳደግ በተሰጡ “አዳዲስ ሐሳቦች” በመመራት “ልጆችን መከልከል ክልክል ነው” ብለው ያስቡ ነበር።8 ልጆች በሚያደርጓቸው ነገሮች ላይ ገደብ ማድረግ ልጆችን ሊጎዳና ሊያበሳጭ ይችላል የሚል ሥጋት ነበራቸው። ስለ ልጆች አስተዳደግ ምክር የሚሰጡ ሊቃውንት ወላጆች ልጆችን በለዘብተኝነት ከማረም የበለጠ ነገር ከማድረግ እንዲታቀቡ ይመክሩ ነበር። ይሁን እንጂ በአሁኑ ጊዜ ከነዚህ ሊቃውንት ብዙዎቹ ልጆችን መገሠጽ ያለውን ጠቀሜታ እንደገና በማጤን የነበራቸውን አስተሳሰብ ማስተካከል ጀምረዋል። ጉዳዩ ያሳሰባቸው ወላጆችም ተጨማሪ ማብራሪያ በመፈለግ ላይ ናቸው።
መጽሐፍ ቅዱስ ግን በዚህ ሁሉ ጊዜ በልጆች አስተዳደግ ረገድ ግልጽና ምክንያታዊ የሆነ ምክር ሲሰጥ ቆይቷል። 2,000 ከሚያክሉ ዓመታት በፊት “እናንተም አባቶች ሆይ፣ ልጆቻችሁን በጌታ ምክርና በተግሣጽ [“ዲስፕሊን፣” NW] አሳድጉአቸው እንጂ አታስቆጡአቸው” ብሏል። (ኤፌሶን 6:4) ተግሳጽ ወይም “ዲስፕሊን” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል “ማሳደግ፣ ማሰልጠን፣ መመሪያ መስጠት” የሚል ትርጉም አለው።9 ይህ ዓይነቱ ዲስፕሊን ወይም መመሪያ ወላጆች ለልጆቻቸው ያላቸውን ፍቅር የሚያሳይ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ምሳሌ 13:24) ልጆች ግልጽ የሆነ የሥነ ምግባር መመሪያና ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር የመለየት ችሎታ ሲያገኙ በጥሩ ሁኔታ ያድጋሉ። የሚያገኙት ዲስፕሊን ወላጆቻቸው ወደ ፊት ስለሚኖራቸው ስብዕናና ስለ ማንነታቸው አጥብቀው እንደሚያስቡ እንዲገነዘቡ ያደርጋቸዋል።
ይሁን እንጂ የወላጅነትን ሥልጣን የሚያመለክተው “የተግሣጽ በትር” ከመጠን ያለፈ መሆን የለበትም።b (ምሳሌ 22:15፤ 29:15) መጽሐፍ ቅዱስ ወላጆችን ሲያስጠነቅቅ “ተስፋ እንዳይቆርጡ ልጆቻችሁን በቁጣ አታስመርሩአቸው” ይላል። (ቆላስይስ 3:21 የ1980 ትርጉም) በተጨማሪም አካላዊ ቅጣት መስጠት አብዛኛውን ጊዜ በጣም ውጤታማ የሆነ የማስተማር ዘዴ እንዳልሆነ ይናገራል። ምሳሌ 17:10 (የ1980 ትርጉም) “ሰነፍ መቶ ጊዜ ተገርፎ ከሚማረው ይልቅ አስተዋይ ሰው ከአንድ ጊዜ በማይበልጥ ተግሣጽ የሚማረው ይበልጣል” ይላል። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ጥፋት ከመፈጸሙ በፊት የመከላከያ ዲስፕሊን መስጠት አስፈላጊ እንደሆነ ይናገራል። በዘዳግም 11:19 ላይ ወላጆች ሌሎች ነገሮችን በሚያደርጉባቸው ጊዜያት ሳይቀር በልጆቻቸው ውስጥ መልካም ሥነ ምግባር እንዲቀርጹ ይመክራል።—በተጨማሪም ዘዳግም 6:6, 7ን ተመልከት።
መጽሐፍ ቅዱስ ለወላጆች የሚሰጠው በዘመን ርዝመት የማይሻር ምክር በጣም ግልጽ ነው። ልጆች ተከታታይና ፍቅራዊ የሆነ ዲስፕሊን ያስፈልጋቸዋል። እንዲህ ያለው ምክር ጥሩ ውጤት እንደሚያስገኝ ከተሞክሮ ታይቷል።c
ሰዎችን የሚከፋፍሉ ነገሮችን ማሸነፍ
በዛሬው ጊዜ ሰዎች በዘር፣ በብሔርና በጎሳ ድንበሮች ተከፋፍለዋል። እንዲህ ያለው ሰው ሠራሽ አጥር በመላው ዓለም ለበርካታ ንጹሐን ሰዎች መጨፍጨፍ ምክንያት ሆኗል። የሰው ልጅ ያሳለፈውን ታሪክ ስንመለከት የተለያየ ዘርና ብሔር ያላቸው ሰዎች በእኩልነት ተያይተው አብረው የመኖራቸው ተስፋ በእጅጉ የጨለመ እንደሆነ እንገነዘባለን። “መፍትሔው” አሉ አንድ አፍሪካዊ የፖለቲካ ሰው “በልባችን ውስጥ ነው።”11 ይሁን እንጂ የሰው ልጆችን ልብ መለወጥ ቀላል ነገር አይደለም። ሆኖም የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት እንዴት የሰዎችን ልብ እንደሚነካና የእኩልነት ዝንባሌ እንደሚያሳድር ተመልከት።
እግዚአብሔር “የሰውን ዘር ሁሉ ከአንድ ሰው ፈጠረ” የሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ማንኛውም ዘር የበላይነት ስሜት ሊኖረው እንደማይገባ ያመለክታል። (ሥራ 17:26 የ1980 ትርጉም) አንድ የሰው ዘር ብቻ እንዳለ ያመለክታል። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ‘አምላክን የምንመስል እንድንሆን’ ይመክረናል። አምላክ ደግሞ “ለሰው ፊት እንዳያደላ፣ ነገር ግን በአሕዛብ ሁሉ እርሱን የሚፈራና ጽድቅን የሚያደርግ በእርሱ የተወደደ እንደሆነ” ተገልጿል። (ኤፌሶን 5:1፤ ሥራ 10:34, 35) መጽሐፍ ቅዱስን አጥብቀው ለሚከተሉና የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርቶች የኑሯቸው መመሪያ ለማድረግ ለሚፈልጉ ሁሉ ይህ እውቀት በመካከላቸው አንድነት እንዲኖር አስችሏል። ወደ ሰዎች ልብ ጠልቆ በመግባት ሰዎችን ከሰዎች የሚያለያዩትን ሰው ሠራሽ አጥሮች አስወግዷል። አንድ ምሳሌ ተመልከት።
ሂትለር በመላው አውሮፓ ጦርነት ባቀጣጠለበት ጊዜ ንጹሐን ሰዎችን በመጨፍጨፍ ተግባር ለመካፈል አሻፈረኝ ያሉት የይሖዋ ምስክሮች ብቻ ነበሩ። በሌሎች ሰዎች ላይ ‘ሠይፍ ለማንሳት’ ፈቃደኛ አልሆኑም። ይህን አቋም የያዙት አምላክን የማስደሰት ፍላጎት ስለነበራቸው ነው። (ኢሳይያስ 2:3, 4፤ ሚክያስ 4:3, 5) ማንም ብሔር ወይም ዘር ከሌላው የበለጠ ወይም የተሻለ አይደለም የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ከልብ ያምኑበታል። (ገላትያ 3:28) በወሰዱት የሰላም ወዳድነት አቋም ምክንያት የይሖዋ ምሥክሮች በሂትለር ማጎሪያ ካምፖች ውስጥ ከታሰሩት የመጀመሪያዎቹ እስረኞች መካከል ሆነው ነበር።—ሮሜ 12:18
ይሁን እንጂ ይህን የመሰለ አቋም ይዘው የተገኙት መጽሐፍ ቅዱስን እንከተላለን የሚሉት ሁሉ አልነበሩም። ጀርመናዊው የፕሮቴስታንት ቄስ ማርቲን ኒሞለር ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት ጥቂት ቆየት ብሎ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “[ጦርነት] አመጣ ብሎ አምላክን የሚወነጅል ሰው የአምላክን ቃል አያውቅም ወይም ለማወቅ አይፈልግም። . . . አብያተ ክርስቲያናት ባለፉት ዘመናት በሙሉ ጦርነቶችን፣ ጦር ሠራዊቶችንና የጦር መሣሪያዎችን ባርከዋል . . . ጠላቶቻቸው በጦርነት እንዲጠፉላቸው ከክርስትና በጣም በራቀ መንገድ ጸልየዋል። ይህ ሁሉ የደረሰው በእኛና በአባቶቻችን ጥፋት እንጂ በአምላክ ምክንያት አይደለም። እኛ የዛሬዎቹ ክርስቲያኖች የውትድርና አገልግሎት አንሰጥም ወይም በሰብዓዊ ፍጡር ላይ ጥይት አንተኩስም በማለታቸው ምክንያት ወደ ማጎሪያ ካምፖች በተወረወሩትና [አልፎ ተርፎም] በሞቱት በሺህ የሚቆጠሩ እውነተኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች [የይሖዋ ምሥክሮች] ተብሎ የሚጠራው ሃይማኖታዊ ቡድን አባላት ፊት ስንቆም እፍረት ሊሰማን ይገባል።”12
የይሖዋ ምሥክሮች እስከ ዛሬ ድረስ አረቦችንና አይሁዶችን፣ ክሮኤሽያውያንንና ሰርቦችን፣ ሁቱዎችንና ቱትሲዎችን ሳይቀር ባዛመደው ወንድማማችነታቸው በሚገባ የታወቁ ሆነዋል። ይሁን እንጂ ምሥክሮቹ እንዲህ ያለ አንድነት በመካከላቸው ሊኖር የቻለው ከሌሎች የተሻሉ ሰዎች ስለሆኑ ሳይሆን የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ባመጣላቸው ለውጥ ምክንያት እንደሆነ በግልጽ ይናገራሉ።—1 ተሰሎንቄ 2:13
ሰዎች ጥሩ የአእምሮ ጤንነት እንዲኖራቸው የሚያስችል ተግባራዊ መመሪያ
ብዙ ጊዜ የአንድ ሰው አእምሮአዊና ስሜታዊ ጤና በአካላዊ ጤንነቱ ላይ የሚያስከትለው ውጤት ይኖራል። ለምሳሌ ያህል ቁጣ ጉዳት እንደሚያስከትል በሳይንሳዊ ጥናቶች ተረጋግጧል። በዱክ ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ማዕከል የሥነ ባሕርይ ምርምር ዳይሬክተር የሆኑት ዶክተር ሬድፎርድ ዊልያምስና ባለቤታቸው ቨርጅንያ ዊልያምስ አንገር ኪልስ በተባለው መጽሐፋቸው እንዲህ ብለዋል:- “እስካሁን ከተገኙት ማስረጃዎች አብዛኞቹ ግልፍተኛ ሰዎች ብዙ ወዳጆች ስለማይኖሩአቸው፣ በሚቆጡበት ጊዜ ሕዋሶቻቸው ከልክ በላይ ስለሚሠሩ፣ ቁጣቸውን ለማብረድ ከመጠን በላይ ስለሚበሉ ወይም ደግሞ ስለሚጠጡ ወይም ስለሚያጨሱና በሌሎች በርካታ ምክንያቶች የተነሣ በልብ በሽታና (በሌሎች በሽታዎች) የመያዛቸው ዕድል በጣም ከፍተኛ ነው።”13
እነዚህን የመሰሉ ሳይንሳዊ ጥናቶች ከመደረጋቸው በሺህ የሚቆጠሩ ዓመታት በፊት መጽሐፍ ቅዱስ ቀላልና ግልጽ በሆነ አነጋገር በአካላዊ ጤንነትና በስሜት መካከል ዝምድና መኖሩን አመልክቷል። “ትሑት ልብ የሥጋ ሕይወት ነው፣ ቅንዓት ግን አጥንትን ያነቅዛል።” (ምሳሌ 14:30፤ 17:22) መጽሐፍ ቅዱስ “አትቆጣ፣ አትናደድም” በተጨማሪም “ለቁጣ ችኩል አትሁን” በማለት የጥበብ ምክር ይሰጣል።—መዝሙር 37:8 የ1980 ትርጉም፤ መክብብ 7:9
በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ቁጣን ለመቆጣጠር የሚያስችል ጥሩ ምክር ይሰጣል። ለምሳሌ ያህል ምሳሌ 19:11 [የ1980 ትርጉም] እንዲህ ይላል:- “የቁጣን ስሜት መቆጣጠር አስተዋይነት ነው፤ ለበደለም ይቅርታ ማድረግ ጨዋነት ነው።” “አስተዋይነት” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል የአንድን ነገር “ምክንያት ማወቅ” የሚል ትርጉም ካለው ቃል የተወሰደ ነው።14 “ምንም ነገር ከማድረግህ በፊት አስብ” የሚለው ምክር በእርግጥም ጥበብ ያለበት ምክር ነው። አንድ ሰው ሌሎች ከሚናገሩት ወይም ከሚያደርጉት ነገር በስተጀርባ ያለውን ምክንያት ለመረዳት ጥረት ካደረገ ለቁጣ የዘገየና ቻይ ይሆናል።—ምሳሌ 14:29
በቆላስይስ 3:13 ላይ ደግሞ ሌላ ተግባራዊ የሆነ ምክር ይገኛል:- “እርስ በርሳችሁ ትዕግሥትን አድርጉ፣ ማንም በባልንጀራው ላይ የሚነቅፈው ነገር ካለው፣ ይቅር ተባባሉ።” የሚያስቆጡ ጥቃቅን ነገሮች ዘወትር ያጋጥማሉ። “እርስ በርሳችሁ ትዕግሥትን አድርጉ” የሚለው አነጋገር በሌሎች ላይ የምንጠላውን ነገር መቻልን ያመለክታል። “ይቅር መባባል” ቅሬታን መተው ማለት ነው። አንዳንድ ጊዜ ቅያሜን ቋጥሮ ከመያዝ ይልቅ መርሳትና መተው ጥበብ ይሆናል። ምክንያቱም ቂም መያዝ በሸክማችን ላይ ሸክም ከመጨመር ሌላ የሚፈይድልን ነገር አይኖርም።—“በሰዎች መካከል ለሚኖሩ ግንኙነቶች የሚጠቅም ተግባራዊ መመሪያ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።
በዛሬው ጊዜ ምክርና መመሪያ የሚገኝባቸው ምንጮች በጣም በርካታ ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው ምክር ግን ከእነዚህ ሁሉ የተለየ ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ ምክሮች በንድፈ ሐሳብ ላይ ብቻ የተመሠረቱ አይደሉም። እነዚህን ምክሮች ሥራ ላይ ማዋል ምንም ዓይነት ጉዳት አያስከትልብንም። ከዚህ ይልቅ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው ጥበብ ‘እጅግ የታመነ ነው።’ (መዝሙር 93:5) ከዚህም በላይ የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ዘመን የማይሽረው ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ተጽፎ ያለቀው ከ2,000 ዓመታት በፊት ቢሆንም ቃሎቹ አሁንም ተግባራዊ ጠቀሜታ ያላቸው ናቸው። ምንም ዓይነት የቆዳ ቀለም ቢኖረን ወይም ደግሞ በየትኛውም አገር የምንኖር ብንሆን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ለሁላችንም እኩል ይሠራል። በተጨማሪም የመጽሐፍ ቅዱስ ቃሎች ኃይል አላቸው፤ ሰዎች ለውጥ እንዲያደርጉና የተሻሉ ሰዎች እንዲሆኑ ያስችላሉ። (ዕብራውያን 4:12) ስለዚህ ይህን መጽሐፍ ማንበብና መሠረታዊ ሥርዓቶቹን ሥራ ላይ ማዋል የተሻለ ሕይወት እንድትኖር ያስችልሃል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a እዚህ ላይ ‘መጣበቅ’ ተብሎ የተተረጎመው ዳቫቅ የተባለ የዕብራይስጥ ቃል “ከአንድ ሰው ጋር በፍቅርና በታማኝነት መጣበቅን ያመለክታል።”4 ማቴዎስ 19:5 ላይ “ይጣበቃል” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል “በሙጫ ወይም በሲሚንቶ ማጣበቅን” ወይም ደግሞ “አንድ ላይ አጥብቆ ማያያዝን” ከሚያመለክት ቃል ጋር ይዛመዳል።5
b በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን “በትር” (በዕብራይስጥ ሸቨት) የሚለው ቃል አንድ እረኛ እንደሚይዘው ያለውን “በትር” ያመለክታል።10 በዚህ አገባብ የሥልጣን በትር የሚያመለክተው ጭካኔን ሳይሆን ፍቅራዊ አመራርን ነው።—ከመዝሙር 23:4 ጋር አወዳድር።
c ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ እና ትራክት ማኅበር የታተመው የቤተሰብ ደስታ የሚገኝበት ምሥጢር በተባለው (የእንግሊዝኛ) መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙትን “ልጅህን ከሕፃንነቱ ጀምረህ አሰልጥን፣” “በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ የሚገኘው ልጅህ በጥሩ ሁኔታ እንዲያድግ እርዳ፣” “በቤት ውስጥ ዓመፀኛ አለን?” እና “ቤተሰብህን ጉዳት ከሚያስከትሉ ተጽእኖዎች ጠብቅ” የሚሉትን ምዕራፎች ተመልከት።
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ቤተሰብ ኑሮ ምክንያታዊና ግልጽ የሆነ ምክር ይሰጣል
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የጤነኛ ቤተሰብ መለያ ባሕርያት
ከበርካታ ዓመታት በፊት አንዲት የትምህርትና የቤተሰብ ጉዳዮች ባለሞያ ከ500 የሚበልጡ የቤተሰብ አማካሪዎች “በጤናማ” ቤተሰቦች ላይ ስለተመለከቷቸው የተለዩ ባሕርያት ሐሳብ እንዲሰጡ የተጠየቁበት ሰፊ ጥናት አድርገው ነበር።
እነዚህ አማካሪዎች ካስተዋሏቸው ባሕርያት ብዙዎቹ ከረዥም ዘመናት በፊት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ ናቸው። አለመግባባቶችን ማስወገድ የሚቻልባቸውን ውጤታማ መንገዶች ጨምሮ ሐሳብ ለሐሳብ የመለዋወጥ ልማድ ከባሕርያቱ ዝርዝር ውስጥ የመጀመሪያውን ደረጃ ይዞ ተገኝቷል። የጥናቱ ጸሐፊ እንደተናገሩት ጤነኛ ቤተሰቦች አብዛኛውን ጊዜ “በመካከላቸው የተፈጠረውን ቁጣ ሳያስወግዱ አይተኙም።”6 መጽሐፍ ቅዱስም ከ1,900 ዓመታት በፊት “ተቆጡ ኃጢአትንም አታድርጉ፣ በቁጣችሁ ላይ ፀሐይ አይግባ” ሲል መክሯል። (ኤፌሶን 4:26) በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመናት አንድ ቀን የሚባለው ፀሐይ ከጠለቀችበት ጊዜ አንስቶ እንደገና እስከምትጠልቅበት ጊዜ ድረስ ያለው ሰዓት ነው። ስለዚህ ዘመናዊ ሊቃውንት ስለ ቤተሰብ ኑሮ ጥናት ከማድረጋቸው ከረዥም ዘመን በፊት መጽሐፍ ቅዱስ በመካከላችሁ የሚፈጠረውን ልዩነት ቶሎ ብላችሁ ቀኑ ከማለቁና ሌላ ቀን ከመጀመሩ በፊት አስወግዱ በማለት የጥበብ ምክር ሰጥቷል።
ጤነኛ ቤተሰቦች “ጭቅጭቅ ሊያስነሱ የሚችሉ ጉዳዮችን ከቤት ሊወጡ ሲሉ ወይም ሊተኙ ሲሉ” እንደማያነሱ ጸሐፊዋ ተገንዝበዋል። “‘በተገቢው ሰዓት’ የሚለውን ሐረግ ደግሜ ደጋግሜ እሰማለሁ” ብለዋል።7 እንደነዚህ ያሉት ቤተሰቦች ሳይታወቃቸው ከ2,700 ዓመታት በፊት የተጻፈውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ እውነተኝነት አስተጋብተዋል። “በተገቢው ጊዜ የተነገረ ቃል ከብር በተሠራ ዕቃ ላይ እንደተቀመጠ የወርቅ ፖም ነው።” (ምሳሌ 15:23፤ 25:11 NW) ይህ ምሳሌያዊ አነጋገር በፖም ቅርጽ የተሠራ የወርቅ ጌጥ በብር ጻህል ላይ ስለመቀመጡ ይናገራል። እነዚህ በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ከፍተኛ ዋጋ የሚሰጣቸው ጌጦች ናቸው። በተገቢው ጊዜ የተነገረ ቃል ያለውን ጠቀሜታና ማራኪነት የሚያመለክት ጥሩ ምሳሌ ነው። በጣም አስጨናቂ በሆኑ ሁኔታዎች ትክክለኛ ቃላት በትክክለኛው ጊዜ መናገር በዋጋ ሊተመን የማይችል ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው።—ምሳሌ 10:19
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
በሰዎች መካከል ለሚኖሩ ግንኙነቶች የሚጠቅም ተግባራዊ መመሪያ
“ተቆጡ፣ ነገር ግን ኃጢአትን አታድርጉ። በመኝታችሁ ሳላችሁ በልባችሁ አስቡ፣ ዝም በሉ።” (መዝሙር 4:4) አብዛኛውን ጊዜ ጥቃቅን ቅሬታዎች ሲኖሩ ጭቅጭቅ ከመፍጠር ይልቅ ዝም ማለት የተሻለ ሊሆን ይችላል።
“እንደሚዋጋ ሠይፍ የሚለፈልፍ ሰው አለ፣ የጠቢባን ምላስ ግን ጤና ነው።” (ምሳሌ 12:18) ከመናገርህ በፊት አስብ። ሳይታሰብባቸው የሚነገሩ ቃላት ሌሎችን ሊያቆስሉና ከወዳጅ ሊያቆራርጡ ይችላሉ።
“የለዘበች መልስ ቁጣን ትመልሳለች፣ ሸካራ ቃል ግን ቁጣን ታስነሣለች።” (ምሳሌ 15:1) የለዘበ መልስ ለመስጠት ራስን መግዛት ያስፈልጋል። ይሁን እንጂ እንዲህ ያለው መልስ ችግሮችን አስወግዶ ሰላማዊ ሁኔታ እንዲሰፍን ያደርጋል።
“የጠብ መጀመሪያ እንደ ውኃ አፈሳሰስ ነው። ስለዚህ ጠብ ሳይበረታ አንተ ክርክርን ተው።” (ምሳሌ 17:14) ቁጣህ ገንፍሎ ራስህን መግዛት ሳያቅትህ በፊት በቀላሉ ቁጣህን ሊቀሰቅስ ከሚችል ሁኔታ ራቅ።
“ቅሬታህን ለመግለጽ አትቸኩል፣ ቅሬታቸውን የሚያስታምሙ ሞኞች ናቸውና።” (መክብብ 7:9፤ ዘ ኒው ኢንግሊሽ ባይብል) አብዛኛውን ጊዜ የስሜት ግንፋሎት ከድርጊት ይቀድማል። ለመቆጣት የሚቸኩል ወይም ግልፍተኛ የሆነ ሰው ይህ ጠባዩ በኋላ የሚጸጸትበት ነገር እንዲያደርግ ወይም እንዲናገር ስለሚያደርገው ሞኝ ነው።
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የይሖዋ ምሥክሮች ወደ ማጎሪያ ካምፕ ከተወሰዱት የመጀመሪያዎቹ እስረኞች መካከል ሆነው ነበር