ለዮሐንስ የተገለጠለት ራእይ
21 እኔም አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር አየሁ፤+ የቀድሞው ሰማይና የቀድሞው ምድር አልፈዋልና፤+ ባሕሩም+ ከእንግዲህ ወዲህ የለም። 2 ደግሞም ቅድስቲቱ ከተማ፣ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ከሰማይ ከአምላክ ዘንድ ስትወርድ አየሁ፤+ እሷም ለባሏ እንዳጌጠች ሙሽራ ተዘጋጅታ ነበር።+ 3 በዚህ ጊዜ ከዙፋኑ አንድ ታላቅ ድምፅ እንዲህ ሲል ሰማሁ፦ “እነሆ፣ የአምላክ ድንኳን ከሰዎች ጋር ነው፤ እሱም ከእነሱ ጋር ይኖራል፤ እነሱም ሕዝቡ ይሆናሉ። አምላክ ራሱም ከእነሱ ጋር ይሆናል።+ 4 እሱም እንባን ሁሉ ከዓይናቸው ያብሳል፤*+ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም፤+ ሐዘንም ሆነ ጩኸት እንዲሁም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም።+ ቀድሞ የነበሩት ነገሮች አልፈዋል።”
5 በዙፋኑም ላይ የተቀመጠው+ “እነሆ፣ ሁሉንም ነገር አዲስ አደርጋለሁ” አለ።+ ደግሞም “እነዚህ ቃላት አስተማማኝና* እውነት ስለሆኑ ጻፍ” አለኝ። 6 እንዲህም አለኝ፦ “እነዚህ ነገሮች ተፈጽመዋል! እኔ አልፋና ኦሜጋ፣* የመጀመሪያውና የመጨረሻው ነኝ።+ ለተጠማ ሁሉ ከሕይወት ውኃ ምንጭ በነፃ* እሰጣለሁ።+ 7 ድል የሚነሳ ሁሉ እነዚህን ነገሮች ይወርሳል፤ እኔ አምላክ እሆነዋለሁ፤ እሱም ልጄ ይሆናል። 8 ይሁን እንጂ የፈሪዎች፣ የእምነት የለሾች፣+ ርኩስና አስጸያፊ የሆኑ ሰዎች፣ የነፍሰ ገዳዮች፣+ የሴሰኞች፣*+ መናፍስታዊ ድርጊት የሚፈጽሙ፣ የጣዖት አምላኪዎችና የውሸታሞች+ ሁሉ ዕጣ ፋንታቸው በእሳትና በድኝ በሚቃጠል ሐይቅ ውስጥ መጣል ነው።+ ይህ ሁለተኛውን ሞት ያመለክታል።”+
9 በሰባቱ የመጨረሻ መቅሰፍቶች የተሞሉትን ሰባቱን ሳህኖች ይዘው ከነበሩት ሰባት መላእክት+ አንዱ መጥቶ “ና፣ የበጉን ሚስት፣ ሙሽራይቱን+ አሳይሃለሁ” አለኝ። 10 ከዚያም በመንፈስ ኃይል ወደ አንድ ትልቅና ረጅም ተራራ ወሰደኝና ቅድስቲቱ ከተማ ኢየሩሳሌም ከሰማይ ከአምላክ ዘንድ ስትወርድ አሳየኝ፤+ 11 እሷም የአምላክን ክብር ተላብሳ ነበር።+ የብርሃኗም ድምቀት እጅግ እንደከበረ ድንጋይ ይኸውም እንደ ኢያስጲድ ነበር፤ ደግሞም እንደ ክሪስታል ጥርት ብሎ ያንጸባርቅ ነበር።+ 12 ትልቅና ረጅም የግንብ አጥር እንዲሁም 12 በሮች ነበሯት፤ በበሮቹም ላይ 12 መላእክት ነበሩ፤ የ12ቱም የእስራኤል ልጆች ነገዶች ስም በበሮቹ ላይ ተቀርጾ ነበር። 13 በምሥራቅ ሦስት በሮች፣ በሰሜን ሦስት በሮች፣ በደቡብ ሦስት በሮችና በምዕራብ ሦስት በሮች ነበሩ።+ 14 በተጨማሪም የከተማዋ የግንብ አጥር 12 የመሠረት ድንጋዮች ነበሩት፤ በእነሱም ላይ የ12ቱ የበጉ ሐዋርያት 12 ስሞች+ ተጽፈው ነበር።
15 እያነጋገረኝ የነበረው መልአክም ከተማዋን፣ በሮቿንና የግንብ አጥሯን ለመለካት የሚያገለግል የወርቅ ዘንግ ይዞ ነበር።+ 16 ከተማዋ አራት ማዕዘን ቅርጽ ያላት ሲሆን ርዝመቷ ከወርዷ ጋር እኩል ነው። እሱም ከተማዋን በዘንጉ ሲለካት 12,000 ስታዲዮን* ሆና ተገኘች፤ ርዝመቷ፣ ወርዷና ከፍታዋ እኩል ነው። 17 በተጨማሪም የግንብ አጥሯን ለካ፤ አጥሩም በሰው መለኪያ፣ በመልአክም መለኪያ 144 ክንድ* ሆኖ ተገኘ። 18 የከተማዋ የግንብ አጥር የተገነባው ከኢያስጲድ ነበር፤+ ከተማዋም የጠራ መስተዋት የሚመስል ንጹሕ ወርቅ ነበረች። 19 የከተማዋ የግንብ አጥር መሠረቶች በተለያዩ የከበሩ ድንጋዮች* ያጌጡ ነበሩ፦ የመጀመሪያው መሠረት ኢያስጲድ፣ ሁለተኛው ሰንፔር፣ ሦስተኛው ኬልቄዶን፣ አራተኛው መረግድ፣ 20 አምስተኛው ሰርዶንክስ፣ ስድስተኛው ሰርድዮን፣ ሰባተኛው ክርስቲሎቤ፣ ስምንተኛው ቢረሌ፣ ዘጠነኛው ቶጳዝዮን፣ አሥረኛው ክርስጵራስስ፣ አሥራ አንደኛው ያክንትና አሥራ ሁለተኛው አሜቴስጢኖስ ነበር። 21 በተጨማሪም 12ቱ በሮች 12 ዕንቁዎች ነበሩ፤ እያንዳንዱ በር ከአንድ ዕንቁ የተሠራ ነበር። የከተማዋ አውራ ጎዳናም ብርሃን እንደሚያስተላልፍ መስተዋት ንጹሕ ወርቅ ነበር።
22 በከተማዋ ውስጥ ቤተ መቅደስ አላየሁም፤ ሁሉን ቻይ የሆነው ይሖዋ* አምላክና+ በጉ ቤተ መቅደሷ ናቸውና። 23 ከተማዋ የፀሐይም ሆነ የጨረቃ ብርሃን አላስፈለጋትም፤ የአምላክ ክብር ብርሃን ሰጥቷታልና፤+ በጉም መብራቷ ነበር።+ 24 ብሔራትም በእሷ ብርሃን ይጓዛሉ፤+ የምድር ነገሥታትም ክብራቸውን ወደ እሷ ያመጣሉ። 25 በሮቿ በቀን አይዘጉም፤ በዚያም ሌሊት ፈጽሞ አይኖርም።+ 26 የብሔራትን ግርማና ክብርም ወደ እሷ ያመጣሉ።+ 27 ሆኖም የረከሰ ማንኛውም ነገር እንዲሁም አስጸያፊ ነገር የሚያደርግና የሚያታልል ማንኛውም ሰው በምንም ዓይነት ወደ እሷ አይገባም፤+ ወደ እሷ የሚገቡት በበጉ የሕይወት መጽሐፍ ጥቅልል ላይ የተጻፉ ብቻ ናቸው።+