ዳንኤል
11 “እኔም ሜዶናዊው ዳርዮስ+ በነገሠ በመጀመሪያው ዓመት፣ እሱን ለማበረታታትና ለማጠናከር* ቆሜ ነበር። 2 አሁን የምነግርህ ነገር እውነት ነው፦
“እነሆ፣ ሦስት ተጨማሪ ነገሥታት በፋርስ ምድር ይነሳሉ፤* አራተኛውም ከሌሎቹ ሁሉ ይበልጥ ብዙ ሀብት ያከማቻል። በሀብቱም በበረታ ጊዜ፣ ሁሉንም ነገር በግሪክ መንግሥት ላይ ያስነሳል።+
3 “አንድ ኃያል ንጉሥ ይነሳል፤ በታላቅ ኃይልም ይገዛል፤+ የፈለገውንም ያደርጋል። 4 ሆኖም በተነሳ ጊዜ መንግሥቱ ይፈራርሳል፤ ወደ አራቱ የሰማይ ነፋሳት አቅጣጫ ይከፋፈላል፤+ ለልጆቹ* ግን አይተላለፍም፤ ግዛታቸው እንደ እሱ ግዛት አይሆንም፤ መንግሥቱ ይነቀላልና፤ ከእነሱም ለሌሎች ይተላለፋል።
5 “የደቡቡ ንጉሥ ይኸውም ከገዢዎቹ አንዱ ብርቱ ይሆናል፤ ይሁንና አንዱ በእሱ ላይ ያይላል፤ ከዚያኛው የገዢነት ሥልጣንም በላቀ ኃይል ይገዛል።
6 “ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ኅብረት ይፈጥራሉ፤ የደቡቡ ንጉሥ ሴት ልጅ ስምምነት ለማድረግ ወደ ሰሜኑ ንጉሥ ትመጣለች። ሆኖም የክንዷ ኃይል አይጸናም፤ ደግሞም እሱም ሆነ ክንዱ አይጸናም፤ እሷም አልፋ ትሰጣለች፤ እሷና ያመጧት ሰዎች፣ የወለዳትና በዚያ ዘመን ብርቱ እንድትሆን ያደረጋት አልፈው ይሰጣሉ። 7 ከሥሮቿም ከሚበቅለው ቀንበጥ አንዱ በእሱ ቦታ ይነሳል፤ እሱም ወደ ሠራዊቱ ይመጣል፤ በሰሜኑ ንጉሥ ምሽግም ላይ ይዘምታል፤ በእነሱም ላይ እርምጃ ይወስዳል፤ ያሸንፋቸዋልም። 8 በተጨማሪም አማልክታቸውን፣ ከብረት የተሠሩ ምስሎቻቸውን፣* ከብርና ከወርቅ የተሠሩ ጠቃሚ* ዕቃዎቻቸውንና ምርኮኞቹን ይዞ ወደ ግብፅ ይመጣል። ለተወሰኑ ዓመታት ከሰሜኑ ንጉሥ ርቆ ይቆማል፤ 9 የሰሜኑም ንጉሥ የደቡቡን ንጉሥ መንግሥት ይወርራል፤ ሆኖም ወደ ገዛ ምድሩ ይመለሳል።
10 “ወንዶች ልጆቹም ለጦርነት ይዘጋጃሉ፤ እጅግ ታላቅ ሠራዊትም ያሰባስባሉ። እሱ በእርግጥ ይገሰግሳል፤ እንደ ጎርፍም ምድሪቱን እያጥለቀለቀ ያልፋል። ሆኖም ይመለሳል፤ ወደ ምሽጉም እስከሚደርስ ድረስ ይዋጋል።
11 “የደቡቡም ንጉሥ በምሬት ተሞልቶ ይወጣል፤ ደግሞም ከእሱ ይኸውም ከሰሜኑ ንጉሥ ጋር ይዋጋል፤ ይሄኛውም ታላቅ ሠራዊት ያሰልፋል፤ ይሁንና ሠራዊቱ ለዚያኛው እጅ አልፎ ይሰጣል። 12 ሠራዊቱም ተጠራርጎ ይወሰዳል። ልቡም ይታበያል፤ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ያጠፋል፤ ሆኖም ያገኘውን ጥሩ አጋጣሚ አይጠቀምበትም።
13 “የሰሜኑም ንጉሥ ይመለሳል፤ ከመጀመሪያውም የሚበልጥ ሠራዊት ያሰባስባል፤ ከተወሰነ ጊዜ ይኸውም ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ በሚገባ የታጠቀ ታላቅ ሠራዊት ይዞ ይመጣል። 14 በዚያ ዘመን ብዙዎች በደቡቡ ንጉሥ ላይ ይነሳሉ።
“በሕዝብህ መካከል ያሉ ዓመፀኛ ሰዎች* ይነሳሉ፤ ደግሞም ራእይን ለመፈጸም ይጥራሉ፤ ሆኖም አይሳካላቸውም።
15 “የሰሜኑም ንጉሥ ይመጣል፤ የአፈር ቁልልም ይደለድላል፤ የተመሸገችንም ከተማ ይይዛል። የደቡቡ ክንዶችም ሆኑ* የተመረጡት ተዋጊዎቹ አይቋቋሙትም፤ ለመቋቋም የሚያስችል ኃይልም አይኖራቸውም። 16 በእሱ ላይ የሚመጣው እንደፈለገው ያደርጋል፤ በፊቱም የሚቆም አይኖርም። ውብ በሆነችው* ምድር+ ላይ ይቆማል፤ የማጥፋትም ኃይል ይኖረዋል። 17 የመንግሥቱን ወታደራዊ ኃይል በሙሉ አሰባስቦ ለመምጣት ፊቱን ያቀናል፤* ከእሱም ጋር ስምምነት ያደርጋል፤ እርምጃም ይወስዳል። የሴቶችንም ሴት ልጅ እንዲያጠፋ ይፈቀድለታል። እሷም አትጸናም፤ የእሱም ሆና አትቀጥልም። 18 እሱም ፊቱን ወደ ባሕር ዳርቻዎች በመመለስ ብዙ ቦታዎችን ይይዛል። አንድ አዛዥ ከእሱ የደረሰበትን ነቀፋ ያስቀራል፤ ከዚያ በኋላ የሚሰነዘርበት ነቀፋ ይቆማል። ነቀፋውንም በራሱ ላይ ይመልስበታል። 19 ከዚያም ፊቱን በገዛ ምድሩ ወደሚገኙት ምሽጎች ይመልሳል፤ ተሰናክሎም ይወድቃል፤ ደግሞም አይገኝም።
20 “በእሱም ቦታ የሚነሳው ዕፁብ ድንቅ በሆነው ግዛቱ የሚያልፍ አስገባሪ* ይልካል፤ ይሁንና በቁጣ ወይም በጦርነት ባይሆንም እንኳ በጥቂት ቀናት ውስጥ ይሰበራል።
21 “በእሱም ቦታ የተናቀ* ሰው ይነሳል፤ እነሱም ንጉሣዊ ክብር አይሰጡትም፤ እሱም ሰዎች ተረጋግተው በሚኖሩበት ጊዜ* ይመጣል፤ መንግሥቱንም በብልጠት* ይይዛል። 22 የጎርፉም ክንዶች* በእሱ የተነሳ ተጠራርገው ይወሰዳሉ፤ ደግሞም ይሰበራሉ፤ የቃል ኪዳኑም+ መሪ+ ይሰበራል። 23 እነሱም ከእሱ ጋር በማበራቸው ማታለሉን ይቀጥላል፤ ደግሞም ይነሳል፤ በጥቂት ሕዝብ አማካኝነትም ኃያል ይሆናል። 24 ሰዎች ተረጋግተው በሚኖሩበት ጊዜ* ወደበለጸገው* የአውራጃው ክፍል ይገባል፤ አባቶቹና የአባቶቹ አባቶች ያላደረጉትን ነገር ያደርጋል። ብዝበዛን፣ ምርኮንና ንብረትን በሕዝቡ መካከል ያከፋፍላል፤ በተመሸጉት ቦታዎችም ላይ ሴራ ይጠነስሳል፤ ይህን የሚያደርገው ግን ለጊዜው ብቻ ነው።
25 “እሱም ታላቅ ሠራዊት አሰባስቦ ኃይሉንና ልቡን በደቡቡ ንጉሥ ላይ ያነሳሳል፤ የደቡቡም ንጉሥ እጅግ ታላቅና ኃያል የሆነ ሠራዊት አሰባስቦ ለጦርነቱ ይዘጋጃል። ሴራ ስለሚጠነስሱበትም መቋቋም አይችልም። 26 የእሱን ምርጥ ምግብ የሚበሉም ለውድቀት ይዳርጉታል።
“ሠራዊቱ ተጠራርጎ* ይወሰዳል፤ ብዙዎችም ተገድለው ይወድቃሉ።
27 “እነዚህ ሁለት ነገሥታት ልባቸው መጥፎ ነገር ለመሥራት ይነሳሳል፤ በአንድ ጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠው እርስ በርስ ውሸት ይነጋገራሉ። ሆኖም ፍጻሜው እስከተወሰነው ጊዜ+ ድረስ ስለሚቆይ ምንም ነገር አይሳካላቸውም።
28 “እሱም በጣም ብዙ ንብረት ሰብስቦ ወደ አገሩ ይመለሳል፤ ልቡም በቅዱሱ ቃል ኪዳን ላይ ይነሳል። እርምጃ ይወስዳል፤ ወደ አገሩም ይመለሳል።
29 “በተወሰነው ጊዜ ይመለሳል፤ በደቡቡ ላይም ይነሳል። በዚህ ጊዜ ግን ቀድሞ እንደነበረው አይሆንም፤ 30 የኪቲም+ መርከቦች በእሱ ላይ ይመጡበታልና፤ ይዋረዳልም።
“ወደ ኋላ ይመለሳል፤ በቅዱሱ ቃል ኪዳንም ላይ የውግዘት ቃል* ይሰነዝራል፤+ እርምጃም ይወስዳል፤ ተመልሶም ትኩረቱን ቅዱስ ቃል ኪዳኑን በተዉት ላይ ያደርጋል። 31 ከእሱ የሚወጡ ክንዶች ይቆማሉ፤* እነሱም ምሽጉን ይኸውም መቅደሱን ያረክሳሉ፤+ የዘወትሩንም መሥዋዕት ያስቀራሉ።+
“ጥፋት የሚያመጣውንም ርኩስ ነገር በዚያ ያኖራሉ።+
32 “ክፋት የሚሠሩትንና ቃል ኪዳኑን የሚያፈርሱትን በማታለል* ወደ ክህደት ጎዳና ይመራቸዋል። አምላካቸውን የሚያውቁት ሰዎች ግን ይበረታሉ፤ እርምጃም ይወስዳሉ። 33 በሕዝቡም መካከል ያሉ ጥልቅ ማስተዋል ያላቸው ሰዎች+ ብዙዎች ማስተዋል እንዲኖራቸው ያደርጋሉ። እነሱም ለተወሰነ ጊዜ የሰይፍ፣ የእሳት፣ የምርኮና የብዝበዛ ሰለባ በመሆን ይወድቃሉ። 34 ሆኖም በሚወድቁበት ጊዜ መጠነኛ እርዳታ ያገኛሉ፤ ብዙዎችም አታላይ በሆነ አንደበት* ከእነሱ ጋር ይተባበራሉ። 35 እስከ ፍጻሜው ዘመን ድረስ በእነሱ የተነሳ የማጥራት፣ የማጽዳትና የማንጻት ሥራ+ ይከናወን ዘንድ ጥልቅ ማስተዋል ካላቸው ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ እንዲወድቁ ይደረጋል፤ ምክንያቱም ይህ እስከተወሰነው ጊዜ ድረስ ይቆያል።
36 “ንጉሡ እንደፈለገው ያደርጋል፤ ከአማልክትም ሁሉ በላይ ራሱን ከፍ ከፍ ያደርጋል፤ እጅግም ይኩራራል፤ በአማልክትም አምላክ+ ላይ አስደንጋጭ ነገር ይናገራል። ቁጣው እስኪፈጸም ድረስ ይሳካለታል፤ ምክንያቱም የተወሰነው ነገር መፈጸም አለበት። 37 ለአባቶቹ አምላክ ምንም ቦታ አይሰጥም፤ ደግሞም ለሴቶች ፍላጎትም ሆነ ለሌላ ለማንኛውም አምላክ ምንም ቦታ አይሰጥም፤ ራሱን ግን በሁሉም ላይ ከፍ ከፍ ያደርጋል። 38 ይልቁንም* ለምሽጎች አምላክ ክብር ይሰጣል፤ አባቶቹም ለማያውቁት አምላክ በወርቅ፣ በብር፣ በከበሩ ድንጋዮችና ተፈላጊ* በሆኑ ነገሮች ክብር ይሰጣል። 39 ከባዕድ አምላክ ጋር ሆኖ* እጅግ ጠንካራ በሆኑት ምሽጎች ላይ እርምጃ ይወስዳል። ለእሱ እውቅና የሚሰጡትን ሁሉ* ከፍተኛ ክብር ያጎናጽፋቸዋል፤ በብዙዎችም መካከል እንዲገዙ ያደርጋል፤ ምድሩንም በዋጋ ያከፋፍላል።*
40 “በፍጻሜው ዘመን የደቡቡ ንጉሥ ከእሱ ጋር ይጋፋል፤* የሰሜኑም ንጉሥ ከሠረገሎች፣ ከፈረሰኞችና ከብዙ መርከቦች ጋር እንደ አውሎ ነፋስ ይመጣበታል፤ ወደ ብዙ አገሮችም ይገባል፤ እንደ ጎርፍም እያጥለቀለቀ ያልፋል። 41 ውብ* ወደሆነችውም ምድር+ ይገባል፤ ብዙ አገሮችም ይወድቃሉ። ሆኖም ኤዶም፣ ሞዓብና የአሞናውያን ዋነኛ ክፍል ከእጁ ያመልጣሉ። 42 እጁንም በብዙ አገሮች ላይ ይዘረጋል፤ የግብፅም ምድር አታመልጥም። 43 እሱም በተደበቁ ውድ ሀብቶች፣ በወርቅና በብር እንዲሁም በግብፅ የከበሩ* ነገሮች ሁሉ ላይ ይሠለጥናል። ሊቢያውያንና ኢትዮጵያውያንም ይከተሉታል።
44 “ሆኖም ከምሥራቅና* ከሰሜን የሚመጣ ወሬ ይረብሸዋል፤ እሱም ለማጥፋትና ብዙዎችን ለመደምሰስ በታላቅ ቁጣ ይወጣል። 45 ንጉሣዊ* ድንኳኖቹንም በታላቁ ባሕርና ቅዱስ በሆነው ውብ* ተራራ+ መካከል ይተክላል፤ እሱም ወደ ፍጻሜው ይመጣል፤ የሚረዳውም አይኖርም።