ለዮሐንስ የተገለጠለት ራእይ
6 እኔም በጉ+ ከሰባቱ ማኅተሞች አንዱን ሲከፍት አየሁ፤+ ከአራቱ ሕያዋን ፍጥረታትም+ አንዱ እንደ ነጎድጓድ ባለ ድምፅ “ና!” ሲል ሰማሁ። 2 እኔም አየሁ፣ እነሆ ነጭ ፈረስ ነበር፤+ በእሱም ላይ የተቀመጠው ቀስት ነበረው፤ አክሊልም ተሰጠው፤+ እሱም ድል እያደረገ ወጣ፤ ድሉንም ለማጠናቀቅ ወደ ፊት ገሰገሰ።+
3 ሁለተኛውን ማኅተም በከፈተ ጊዜ ሁለተኛው ሕያው ፍጡር+ “ና!” ሲል ሰማሁ። 4 ደማቅ ቀይ ቀለም ያለው ሌላ ፈረስ ወጣ፤ በእሱም ላይ ለተቀመጠው ሰዎች እርስ በርሳቸው ይተራረዱ ዘንድ ሰላምን ከምድር እንዲወስድ ተፈቀደለት፤ እንዲሁም ትልቅ ሰይፍ ተሰጠው።+
5 ሦስተኛውን ማኅተም በከፈተ ጊዜ+ ሦስተኛው ሕያው ፍጡር+ “ና!” ሲል ሰማሁ። እኔም አየሁ፣ እነሆ ጥቁር ፈረስ ነበር፤ በእሱም ላይ የተቀመጠው በእጁ ሚዛን ይዞ ነበር። 6 ከአራቱ ሕያዋን ፍጥረታት መካከል እንደ ድምፅ ያለ ነገር “አንድ እርቦ* ስንዴ በዲናር፣*+ ሦስት እርቦ ገብስም በዲናር፤ ደግሞም የወይራ ዘይቱንና የወይን ጠጁን አትጉዳ” ሲል ሰማሁ።+
7 አራተኛውን ማኅተም በከፈተ ጊዜ አራተኛው ሕያው ፍጡር+ “ና!” ሲል ሰማሁ። 8 እኔም አየሁ፣ እነሆ ግራጫ ፈረስ ነበር፤ በእሱም ላይ የተቀመጠው ስሙ ሞት ነበር። መቃብርም* በቅርብ ይከተለው ነበር። ሞትና መቃብርም በረጅም ሰይፍ፣ በምግብ እጥረት፣+ በገዳይ መቅሰፍትና በምድር አራዊት እንዲገድሉ በምድር አንድ አራተኛ ላይ ሥልጣን ተሰጣቸው።+
9 አምስተኛውን ማኅተም በከፈተ ጊዜ በአምላክ ቃል የተነሳና በሰጡት ምሥክርነት የተነሳ የታረዱትን ሰዎች ነፍሳት*+ ከመሠዊያው በታች+ አየሁ።+ 10 እነሱም “ቅዱስና እውነተኛ የሆንከው ሉዓላዊ ጌታ ሆይ፣+ በምድር በሚኖሩት ላይ የማትፈርደውና ደማችንን የማትበቀለው እስከ መቼ ነው?”+ ብለው በታላቅ ድምፅ ጮኹ። 11 ለእያንዳንዳቸውም ነጭ ልብስ ተሰጣቸው፤+ እንዲሁም ወደፊት እንደ እነሱ የሚገደሉት ባልንጀሮቻቸው የሆኑ ባሪያዎችና የወንድሞቻቸው ቁጥር እስኪሞላ ድረስ ለጥቂት ጊዜ እንዲጠብቁ ተነገራቸው።+
12 ስድስተኛውንም ማኅተም ሲከፍት አየሁ፤ ታላቅ የምድር ነውጥም ተከሰተ፤ ፀሐይም ከፀጉር* እንደተሠራ ማቅ ጠቆረች፤ ጨረቃም ሙሉ በሙሉ ደም መሰለች፤+ 13 ኃይለኛ ነፋስ የበለስን ዛፍ ሲያወዛውዝ ያልበሰሉት ፍሬዎች ከዛፉ ላይ እንደሚረግፉ፣ የሰማይ ከዋክብትም ወደ ምድር ወደቁ። 14 ሰማይም እየተጠቀለለ እንዳለ የመጽሐፍ ጥቅልል ከቦታው ተነሳ፤+ እንዲሁም ተራሮች ሁሉና ደሴቶች ሁሉ ከቦታቸው ተወገዱ።+ 15 ከዚያም የምድር ነገሥታት፣ ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣ የጦር አዛዦች፣ ሀብታሞች፣ ብርቱዎች፣ ባሪያዎች ሁሉና ነፃ ሰዎች ሁሉ በዋሻዎች ውስጥና ተራራ ላይ ባሉ ዓለቶች መካከል ተደበቁ።+ 16 ተራሮቹንና ዓለቶቹንም እንዲህ እያሉ ተማጸኑ፦ “በላያችን ውደቁና+ በዙፋኑ ላይ ከተቀመጠው+ ፊትና ከበጉ+ ቁጣ ሰውሩን፤ 17 ምክንያቱም ቁጣቸውን የሚገልጹበት ታላቁ ቀን መጥቷል፤+ ማንስ ሊቆም ይችላል?”+