የማቴዎስ ወንጌል
18 በዚያን ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ወደ ኢየሱስ ቀርበው “በመንግሥተ ሰማያት ከሁሉ የሚበልጠው ማን ነው?” አሉት።+ 2 ኢየሱስም አንድ ትንሽ ልጅ ጠርቶ በመካከላቸው በማቆም 3 እንዲህ አለ፦ “እውነት እላችኋለሁ፣ ካልተመለሳችሁና* እንደ ልጆች ካልሆናችሁ+ በምንም ዓይነት ወደ መንግሥተ ሰማያት አትገቡም።+ 4 ስለዚህ በመንግሥተ ሰማያት ከሁሉ የሚበልጠው እንደዚህ ትንሽ ልጅ ራሱን ዝቅ የሚያደርግ ነው፤+ 5 እንዲሁም እንደዚህ ያለውን ትንሽ ልጅ በስሜ የሚቀበል ሁሉ እኔንም ይቀበላል። 6 ሆኖም በእኔ ከሚያምኑት ከእነዚህ ከትናንሾቹ አንዱን የሚያሰናክል ሁሉ የወፍጮ ድንጋይ* በአንገቱ ታስሮ ጥልቅ ባሕር ውስጥ ቢሰጥም ይሻለዋል።+
7 “ይህ ዓለም ሰዎችን የሚያሰናክል ነገር ስለሚያስቀምጥ ወዮለት! እርግጥ ማሰናከያ መምጣቱ የማይቀር ነው፤ ነገር ግን በእሱ ጠንቅ ሌሎች እንዲሰናከሉ ለሚያደርግ ሰው ወዮለት! 8 እንግዲያው እጅህ ወይም እግርህ ቢያሰናክልህ ቆርጠህ ጣለው።+ ሁለት እጅ ወይም ሁለት እግር ኖሮህ ወደ ዘላለማዊ እሳት+ ከምትወረወር ጉንድሽ ወይም አንካሳ ሆነህ ሕይወት ብታገኝ ይሻልሃል። 9 እንዲሁም ዓይንህ ቢያሰናክልህ አውጥተህ ጣለው። ሁለት ዓይን ኖሮህ ወደ እሳታማ ገሃነም* ከምትወረወር አንድ ዓይን ኖሮህ ሕይወት ብታገኝ ይሻልሃል።+ 10 በሰማይ ያሉት መልአኮቻቸው በሰማይ ባለው አባቴ ፊት ዘወትር ስለሚቀርቡ ከእነዚህ ከትናንሾቹ መካከል አንዱንም እንዳትንቁ ተጠንቀቁ።+ 11 *——
12 “ምን ይመስላችኋል? አንድ ሰው 100 በጎች ቢኖሩትና ከእነሱ አንዷ ብትጠፋ+ 99ኙን በተራራ ላይ ትቶ የጠፋችውን ለመፈለግ አይሄድም?+ 13 እውነት እላችኋለሁ፣ የጠፋችውን በግ ካገኛት፣ ካልጠፉት ከ99ኙ ይልቅ በእሷ ይበልጥ ይደሰታል። 14 በተመሳሳይም በሰማይ ያለው አባቴ* ከእነዚህ ከትናንሾቹ መካከል አንዱም እንኳ እንዲጠፋ አይፈልግም።+
15 “በተጨማሪም ወንድምህ ቢበድልህ አንተና እሱ ብቻችሁን ሆናችሁ ጥፋቱን በግልጽ ንገረው።*+ ከሰማህ ወንድምህን ታተርፋለህ።+ 16 የማይሰማህ ከሆነ ግን ማንኛውም ጉዳይ ሁለት ወይም ሦስት ምሥክሮች በሚሰጡት የምሥክርነት ቃል* ስለሚጸና አንድ ወይም ሁለት ሰው ይዘህ ሂድ።+ 17 እነሱንም ካልሰማ ለጉባኤ ተናገር። ጉባኤውንም እንኳ የማይሰማ ከሆነ እንደ አሕዛብና+ እንደ ቀረጥ ሰብሳቢ+ አድርገህ ቁጠረው።
18 “እውነት እላችኋለሁ፣ በምድር የምታስሩት ነገር ሁሉ ቀድሞውኑ በሰማያት የታሰረ ይሆናል፤ እንዲሁም በምድር የምትፈቱት ነገር ሁሉ ቀድሞውኑ በሰማያት የተፈታ ይሆናል። 19 ደግሞም እውነት እላችኋለሁ፣ በምድር ላይ ከእናንተ መካከል ሁለታችሁ አንድ አስፈላጊ የሆነ ነገር ለመለመን ብትስማሙ በሰማይ ያለው አባቴ ያደርግላችኋል።+ 20 ሁለት ወይም ሦስት ሆነው በስሜ በሚሰበሰቡበት+ በዚያ በመካከላቸው እገኛለሁና።”
21 ከዚያም ጴጥሮስ ወደ ኢየሱስ ቀርቦ “ጌታ ሆይ፣ ወንድሜ ቢበድለኝ ስንት ጊዜ ይቅር ልበለው? እስከ ሰባት ጊዜ ይቅር ልበለው?” አለው። 22 ኢየሱስም እንዲህ አለው፦ “እስከ 77 ጊዜ* እንጂ እስከ ሰባት ጊዜ ብቻ አልልህም።+
23 “ስለዚህ መንግሥተ ሰማያት ከባሪያዎቹ ጋር ሒሳብ መተሳሰብ ከፈለገ አንድ ንጉሥ ጋር ይመሳሰላል። 24 ሒሳቡን መተሳሰብ በጀመረ ጊዜም 10,000 ታላንት* ዕዳ ያለበትን አንድ ሰው አቀረቡለት። 25 ሆኖም ሰውየው ዕዳውን የሚከፍልበት ምንም መንገድ ስላልነበረው ጌታው እሱም ሆነ ሚስቱ እንዲሁም ልጆቹና ያለው ንብረት ሁሉ ተሸጠው ዕዳው እንዲከፈል አዘዘ።+ 26 ባሪያውም ወድቆ በመስገድ* ‘ጌታዬ ሆይ፣ እባክህ ታገሠኝ፤ ያለብኝን ዕዳ ሁሉ እከፍልሃለሁ’ ሲል ለመነው። 27 ጌታውም እጅግ አዘነለትና ለቀቀው፤ ዕዳውንም ሰረዘለት።+ 28 ሆኖም ይህ ባሪያ ወጥቶ ከሄደ በኋላ 100 ዲናር* ያበደረውን እንደ እሱ ያለ ባሪያ አግኝቶ ያዘውና አንገቱን አንቆ ‘ያለብህን ዕዳ ክፈለኝ’ አለው። 29 ባልንጀራው የሆነው ያ ባሪያም እግሩ ላይ ወድቆ ‘ወንድሜ ሆይ፣ እባክህ ታገሠኝ፤ እከፍልሃለሁ’ ብሎ ይለምነው ጀመር። 30 እሱ ግን ፈቃደኛ አልሆነም፤ ከዚህ ይልቅ ሄዶ ያለበትን ዕዳ እስኪከፍል ድረስ ወህኒ ቤት አሳሰረው። 31 ባልንጀሮቹ የሆኑ ባሪያዎች የሆነውን ነገር ባዩ ጊዜ እጅግ አዘኑ፤ ሄደውም የሆነውን ነገር ሁሉ ለጌታቸው ነገሩት። 32 በዚህ ጊዜ ጌታው አስጠራውና እንዲህ አለው፦ ‘አንተ ክፉ ባሪያ፣ ስለተማጸንከኝ ያን ሁሉ ዕዳ ተውኩልህ። 33 ታዲያ እኔ ምሕረት እንዳደረግኩልህ ሁሉ አንተስ ባልንጀራህ ለሆነው ባሪያ ምሕረት ልታደርግለት አይገባም ነበር?’+ 34 ጌታውም በዚህ እጅግ ተቆጥቶ ያለበትን ዕዳ ሁሉ እስኪከፍል ድረስ ለወህኒ ቤት ጠባቂዎቹ አሳልፎ ሰጠው። 35 እናንተም እያንዳንዳችሁ ወንድማችሁን ከልባችሁ ይቅር ካላላችሁ+ በሰማይ ያለው አባቴ እንደዚሁ ያደርግባችኋል።”+