የሐዋርያት ሥራ
28 እኛም በደህና ወደ የብስ ደረስን፤ ደሴቲቱም ማልታ ተብላ እንደምትጠራ አወቅን።+ 2 የአካባቢው ነዋሪዎችም* የተለየ ደግነት* አሳዩን። ዝናብ መዝነብ ጀምሮ ስለነበረና ብርድ ስለነበር እሳት በማቀጣጠል ሁላችንንም በደግነት አስተናገዱን። 3 ይሁን እንጂ ጳውሎስ ጭራሮ ሰብስቦ እሳቱ ውስጥ ሲጨምር ከሙቀቱ የተነሳ እፉኝት ወጥታ እጁ ላይ ተጣበቀች። 4 ባዕድ ቋንቋ የሚናገሩትም ሰዎች እፉኝቷ እጁ ላይ ተንጠልጥላ ባዩ ጊዜ እርስ በርሳቸው “ይህ ሰው ነፍሰ ገዳይ መሆን አለበት፤ ከባሕሩ ተርፎ በደህና ቢወጣም እንኳ ፍትሕ* በሕይወት እንዲኖር አልፈቀደለትም” ይባባሉ ጀመር። 5 እሱ ግን እፉኝቷን እሳቱ ላይ አራገፋት፤ አንዳችም ጉዳት አልደረሰበትም። 6 ሆኖም ሰዎቹ ከአሁን አሁን ሰውነቱ ያብጣል ወይም ድንገት ወድቆ ይሞታል ብለው ይጠባበቁ ነበር። ብዙ ጠብቀው ምንም ጉዳት እንዳልደረሰበት ባዩ ጊዜ ሐሳባቸውን ለውጠው ይህ ሰው አምላክ ነው ይሉ ጀመር።
7 በዚያ አካባቢ፣ ፑፕልዮስ የተባለ የደሴቲቱ አስተዳዳሪ ርስት ነበረው፤ እሱም በእንግድነት ተቀብሎን ሦስት ቀን በደግነት አስተናገደን። 8 የፑፕልዮስ አባት ትኩሳትና ተቅማጥ ይዞት ተኝቶ ነበር፤ ጳውሎስም ወደ እሱ ገብቶ ጸለየለት፤ እጁንም ጫነበትና ፈወሰው።+ 9 ይህ ከሆነ በኋላ በደሴቲቱ የሚኖሩ የታመሙ ሌሎች ሰዎችም ወደ እሱ እየመጡ ይፈወሱ ጀመር።+ 10 በተጨማሪም ብዙ ስጦታ በመስጠት አክብሮታቸውን ገለጹልን፤ በመርከብ ለመሄድ በተዘጋጀን ጊዜም የሚያስፈልጉንን ነገሮች ሁሉ ጫኑልን።
11 ከሦስት ወር በኋላም “የዙስ ልጆች” የሚል ዓርማ ባለው መርከብ ጉዞ ጀመርን። ይህ መርከብ ከእስክንድርያ የመጣ ሲሆን ክረምቱን ያሳለፈው በዚህች ደሴት ነበር። 12 በስራኩስ ወደሚገኘው ወደብ ከደረስን በኋላ በዚያ ሦስት ቀን ቆየን፤ 13 ከዚያም ተነስተን በመጓዝ ሬጊዩም ደረስን። ከአንድ ቀን በኋላም የደቡብ ነፋስ ስለተነሳ በሁለተኛው ቀን ፑቲዮሉስ ደረስን። 14 በዚያም ወንድሞችን አገኘን፤ እነሱም ሰባት ቀን አብረናቸው እንድንቆይ ለመኑን፤ እነሱ ጋር ከቆየን በኋላ ወደ ሮም አመራን። 15 በዚያ የነበሩ ወንድሞች ስለ እኛ በሰሙ ጊዜ እስከ አፍዩስ የገበያ ስፍራና ሦስት ማደሪያ* እስከሚባለው ቦታ ድረስ ሊቀበሉን መጡ። ጳውሎስም ባያቸው ጊዜ አምላክን አመሰገነ፤ እንዲሁም ተበረታታ።+ 16 በመጨረሻም ሮም በደረስን ጊዜ ጳውሎስ አንድ ወታደር እየጠበቀው ብቻውን እንዲኖር ተፈቀደለት።
17 ይሁን እንጂ ከሦስት ቀን በኋላ የአይሁዳውያንን ታላላቅ ሰዎች አንድ ላይ ጠራ። ሰዎቹም በተሰበሰቡ ጊዜ እንዲህ አላቸው፦ “ወንድሞች፣ ምንም እንኳ ሕዝቡን ወይም የአባቶቻችንን ልማድ የሚጻረር ነገር ያልፈጸምኩ+ ቢሆንም በኢየሩሳሌም አስረው ለሮማውያን አሳልፈው ሰጥተውኛል።+ 18 እነሱም ከመረመሩኝ+ በኋላ ለሞት የሚያበቃ ምንም ጥፋት ስላላገኙብኝ ሊፈቱኝ ፈልገው ነበር።+ 19 ሆኖም አይሁዳውያን ይህን በተቃወሙ ጊዜ ለቄሳር ይግባኝ ለማለት ተገደድኩ፤+ ይህን ያደረግኩት ግን ሕዝቤን የምከስበት ነገር ኖሮኝ አይደለም። 20 እናንተንም ለማየትና ለማነጋገር ጥያቄ ያቀረብኩት ለዚህ ነው፤ በዚህ ሰንሰለት የታሰርኩትም ለእስራኤል በተሰጠው ተስፋ ምክንያት ነው።”+ 21 እነሱም እንዲህ አሉት፦ “ስለ አንተ የተጻፈ ከይሁዳ የመጣ ምንም ደብዳቤ አልደረሰንም፤ ከዚያ ከመጡት ወንድሞች መካከልም ስለ አንተ ክፉ ነገር የተናገረ ወይም ያወራ አንድም ሰው የለም። 22 ሆኖም ስለዚህ ኑፋቄ+ በየቦታው መጥፎ ነገር እንደሚወራ ስለምናውቅ+ የአንተን ሐሳብ ደግሞ መስማት ተገቢ ይመስለናል።”
23 በጉዳዩ ላይ ለመነጋገር ከእሱ ጋር ቀን ከወሰኑ በኋላ ብዙ ሆነው ወደ መኖሪያ ስፍራው መጡ። እሱም በኢየሱስ እንዲያምኑ ለማድረግ+ ከሙሴ ሕግና+ ከነቢያት+ እየጠቀሰ ከጠዋት ጀምሮ እስከ ማታ ድረስ ስለ አምላክ መንግሥት በሚገባ* በመመሥከር ጉዳዩን አብራራላቸው። 24 አንዳንዶቹ የተናገረውን ነገር ሲያምኑ ሌሎቹ ግን አላመኑም። 25 እርስ በርስ ሊስማሙ ስላልቻሉም ለመሄድ ተነሱ፤ በዚህ ጊዜ ጳውሎስ የሚከተለውን የመጨረሻ ሐሳብ ተናገረ፦
“መንፈስ ቅዱስ በነቢዩ ኢሳይያስ በኩል ለአባቶቻችሁ እንዲህ ሲል የተናገረው ቃል ትክክል ነበር፦ 26 ‘ወደዚህ ሕዝብ ሄደህ እንዲህ በላቸው፦ “መስማቱን ትሰማላችሁ፤ ግን በፍጹም አታስተውሉም፤ ማየቱን ታያላችሁ፤ ግን በፍጹም ልብ አትሉም።+ 27 ምክንያቱም በዓይናቸው አይተው፣ በጆሯቸው ሰምተው እንዲሁም በልባቸው አስተውለው ወደ እኔ እንዳይመለሱና እንዳልፈውሳቸው የዚህ ሕዝብ ልብ ደንድኗል፤ በጆሯቸው ሰምተው ምላሽ አልሰጡም፤ ዓይናቸውንም ጨፍነዋል።”’+ 28 ስለዚህ አምላክ ሰዎችን ስለሚያድንበት መንገድ የሚናገረው ይህ መልእክት ለአሕዛብ እንደተላከ እንድታውቁ እፈልጋለሁ፤+ እነሱም በእርግጥ ይሰሙታል።”+ 29 *——
30 ጳውሎስም በተከራየው ቤት ሁለት ዓመት ሙሉ ኖረ፤+ ወደ እሱ የሚመጡትንም ሁሉ በደግነት ያስተናግዳቸው ነበር፤ 31 ያለምንም እንቅፋት በታላቅ የመናገር ነፃነት* ስለ አምላክ መንግሥት ይሰብክላቸው የነበረ ከመሆኑም በላይ ስለ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተምራቸው ነበር።+