ለኤፌሶን ሰዎች የተጻፈ ደብዳቤ
6 ልጆች ሆይ፣ ከጌታ ፈቃድ ጋር በሚስማማ መንገድ ለወላጆቻችሁ ታዘዙ፤+ ይህ የጽድቅ ተግባር ነውና። 2 “አባትህንና እናትህን አክብር”+ የሚለው ትእዛዝ የሚከተለውን የተስፋ ቃል የያዘ የመጀመሪያው ትእዛዝ ነው፦ 3 “ይህም መልካም እንዲሆንልህና* ዕድሜህ በምድር ላይ እንዲረዝም ነው።” 4 አባቶች ሆይ፣ ልጆቻችሁን አታስመርሯቸው፤+ ከዚህ ይልቅ በይሖዋ* ተግሣጽና+ ምክር* አሳድጓቸው።+
5 እናንተ ባሪያዎች ሆይ፣ ለክርስቶስ እንደምትታዘዙ ሁሉ ለሰብዓዊ ጌቶቻችሁ ከልብ በመነጨ ቅንነት፣ በአክብሮትና በፍርሃት ታዘዙ፤+ 6 ሰዎችን ለማስደሰት+ እንዲሁ ለታይታ ሳይሆን እንደ ክርስቶስ ባሪያዎች የአምላክን ፈቃድ በሙሉ ነፍስ*+ በመፈጸም ታዘዟቸው። 7 ሰዎችን ሳይሆን ይሖዋን* እንደምታገለግሉ አድርጋችሁ በማሰብ በፈቃደኝነት አገልግሉ፤+ 8 ባሪያም ሆነ ነፃ ሰው፣ እያንዳንዱ ለሚያደርገው ማንኛውም መልካም ነገር ከይሖዋ* ወሮታ እንደሚቀበል ታውቃላችሁና።+ 9 እናንተም ጌቶች ሆይ፣ ለእነሱ እንዲሁ ዓይነት አመለካከት ይኑራችሁ፤ የእነሱም ሆነ የእናንተ ጌታ በሰማያት እንዳለና+ እሱ ደግሞ እንደማያዳላ ስለምታውቁ አታስፈራሯቸው።
10 በተረፈ ከጌታና ከታላቅ ብርታቱ ኃይል+ ማግኘታችሁን እንድትቀጥሉ አሳስባችኋለሁ። 11 የዲያብሎስን መሠሪ ዘዴዎች* መቋቋም እንድትችሉ ከአምላክ የሚገኘውን ሙሉ የጦር ትጥቅ ልበሱ፤+ 12 ምክንያቱም የምንታገለው+ ከደምና ከሥጋ ጋር ሳይሆን ከመንግሥታት፣ ከሥልጣናት፣ ይህን ጨለማ ከሚቆጣጠሩ የዓለም ገዢዎች እንዲሁም በሰማያዊ ስፍራ ካሉ ከክፉ መንፈሳዊ ኃይሎች ጋር ነው።+ 13 ስለሆነም ክፉው ቀን በሚመጣበት ጊዜ መቋቋም እንድትችሉና ሁሉንም ነገር ከፈጸማችሁ በኋላ ጸንታችሁ መቆም እንድትችሉ ከአምላክ የሚገኘውን ሙሉ የጦር ትጥቅ አንሱ።+
14 እንግዲህ ወገባችሁን በእውነት ቀበቶ ታጥቃችሁና+ የጽድቅን ጥሩር ለብሳችሁ+ ጸንታችሁ ቁሙ፤ 15 እንዲሁም የሰላምን ምሥራች ለማወጅ ዝግጁ በመሆን እግሮቻችሁ ተጫምተው ቁሙ።*+ 16 ከዚህ ሁሉ በተጨማሪ የሚንበለበሉትን የክፉውን ፍላጻዎች* ሁሉ ማምከን የምትችሉበትን ትልቅ የእምነት ጋሻ አንሱ።+ 17 በተጨማሪም የመዳንን የራስ ቁር አድርጉ፤+ እንዲሁም የመንፈስን ሰይፍ ይኸውም የአምላክን ቃል ያዙ፤+ 18 ከዚህም በተጨማሪ በሁሉም ዓይነት ጸሎትና+ ምልጃ በማንኛውም ጊዜ በመንፈስ መጸለያችሁን ቀጥሉ።+ ለዚህም ሲባል ዘወትር ንቁ ሁኑ፤ እንዲሁም ስለ ቅዱሳን ሁሉ ምልጃ አቅርቡ። 19 የምሥራቹን ቅዱስ ሚስጥር በድፍረት ለሌሎች ማሳወቅ እንድችል አፌን በምከፍትበት ጊዜ የምናገረው ቃል እንዲሰጠኝ ለእኔም ጸልዩልኝ፤+ 20 በሰንሰለት የታሰረ አምባሳደር ሆኜ እያገለገልኩ+ ያለሁት ለዚሁ ምሥራች ነው፤ ስለ ምሥራቹ የሚገባኝን ያህል በድፍረት መናገር እንድችል ጸልዩልኝ።
21 እንግዲህ ስለ እኔ እንዲሁም እያከናወንኩ ስላለሁት ነገር እናንተም እንድታውቁ የተወደደ ወንድማችንና በጌታ ታማኝ አገልጋይ የሆነው ቲኪቆስ+ ሁሉንም ነገር ይነግራችኋል።+ 22 በምን ዓይነት ሁኔታ ላይ እንዳለን እንድታውቁና ልባችሁን እንዲያጽናና ለዚሁ ዓላማ ስል ወደ እናንተ እልከዋለሁ።
23 አባታችን ከሆነው አምላክና ከጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰላምና ፍቅር ከእምነት ጋር ለወንድሞች ይድረስ። 24 ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የማይከስም ፍቅር ካላቸው ሁሉ ጋር የአምላክ ጸጋ ይሁን።