ስለ አምላክ ጸጋ የሚገልጸውን ምሥራች አውጁ
“ስለ አምላክ ጸጋ የሚገልጸውን ምሥራች በተሟላ ሁኔታ [መሥክሩ]።”—ሥራ 20:24
1, 2. ሐዋርያው ጳውሎስ ለአምላክ ጸጋ አመስጋኝ መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው?
ሐዋርያው ጳውሎስ “አምላክ ለእኔ ያሳየው [ጸጋ] ከንቱ ሆኖ አልቀረም” በማለት አፉን ሞልቶ መናገር ችሏል። (1 ቆሮንቶስ 15:9, 10ን አንብብ።) ጳውሎስ ቀደም ሲል ክርስቲያኖችን ያሳድድ ስለነበር፣ አምላክ ለእሱ ያሳየው ታላቅ ምሕረት ይገባኛል የሚለው ነገር እንዳልሆነ አሳምሮ ያውቅ ነበር።
2 ጳውሎስ በሕይወቱ መገባደጃ ላይ አብሮት ለሚያገለግለው ለጢሞቴዎስ እንደሚከተለው በማለት ጽፎለታል፦ “ለአገልግሎቱ በመሾም ታማኝ አድርጎ ስለቆጠረኝ ኃይል የሰጠኝን ጌታችን ክርስቶስ ኢየሱስን አመሰግናለሁ።” (1 ጢሞ. 1:12-14) ይህ አገልግሎት ምን ነበር? ጳውሎስ በኤፌሶን ጉባኤ ለነበሩት ሽማግሌዎች ይህ አገልግሎት ምን እንደሚያካትት ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “ሩጫዬን እስካጠናቀቅኩ እንዲሁም ስለ አምላክ ጸጋ የሚገልጸውን ምሥራች በተሟላ ሁኔታ በመመሥከር ከጌታ ኢየሱስ የተቀበልኩትን አገልግሎት እስከፈጸምኩ ድረስ ሕይወቴ ምንም አያሳሳኝም።”—ሥራ 20:24
3. ጳውሎስ ምን ልዩ አገልግሎት ተሰጥቶት ነበር? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)
3 ጳውሎስ የሰበከውና የይሖዋን ጸጋ አጉልቶ የሚያሳየው “ምሥራች” ምንድን ነው? ለኤፌሶን ክርስቲያኖች “ለእናንተ ጥቅም ሲባል ስለተሰጠኝ የአምላክ ጸጋ መጋቢነት በእርግጥ ሰምታችኋል” በማለት ነግሯቸዋል። (ኤፌ. 3:1, 2) ጳውሎስ፣ አይሁዳውያን ያልሆኑ ሰዎችም በመሲሐዊው መንግሥት ውስጥ ከክርስቶስ ጋር አብረው የመግዛት መብት እንደተዘረጋላቸው የሚገልጸውን ምሥራች ለአሕዛብ እንዲያውጅ ተልእኮ ተሰጥቶት ነበር። (ኤፌሶን 3:5-8ን አንብብ።) ጳውሎስ አገልግሎቱን ሲያከናውን የነበረው ቅንዓት በአሁኑ ጊዜ ላለን ክርስቲያኖች ግሩም አርዓያ ከመሆኑም ሌላ አምላክ ለእሱ ያሳየው ጸጋ “ከንቱ” ሆኖ እንዳልቀረ አሳይቷል።
የአምላክ ጸጋ ለሥራ ያነሳሳሃል?
4, 5. “የመንግሥቱ ምሥራች” እና ‘ስለ አምላክ ጸጋ የሚገልጸው ምሥራች’ ተመሳሳይ ናቸው የምንለው ለምንድን ነው?
4 በዚህ የፍጻሜ ዘመን የይሖዋ ሕዝቦች ‘ለብሔራት ሁሉ ምሥክር እንዲሆን የመንግሥቱን ምሥራች በመላው ምድር’ የመስበክ ተልእኮ ተሰጥቷቸዋል። (ማቴ. 24:14) የምናውጀው መልእክት “ስለ አምላክ ጸጋ [የሚገልጽ] ምሥራች” እንደሆነም ተገልጿል። እንዲህ የተባለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር በረከቶች እንደምናገኝ ተስፋ ሊኖረን የቻለው፣ በክርስቶስ በኩል በተገለጸው የይሖዋ ጸጋ አማካኝነት ነው። (ኤፌ. 1:3) እኛስ በአገልግሎት በቅንዓት በመካፈል ልክ እንደ ጳውሎስ ይሖዋ ላሳየን ጸጋ አመስጋኝነታችንን እንገልጻለን?—ሮም 1:14-16ን አንብብ።
5 ኃጢአተኞች የሆንነው የሰው ልጆች፣ በተለያዩ መንገዶች ከተገለጸው የይሖዋ ጸጋ ምን ጥቅም እንዳገኘን ቀደም ባለው የጥናት ርዕስ ላይ ተመልክተን ነበር። በመሆኑም ይሖዋ ፍቅሩን የገለጸባቸውን መንገዶች እንዲሁም ሰዎች በግለሰብ ደረጃ ከዚህ ጥቅም ማግኘት የሚችሉት እንዴት እንደሆነ ለሰው ሁሉ ለማሳወቅ አቅማችን የፈቀደውን በሙሉ የማድረግ ኃላፊነት አለብን። ለሰዎች ማሳወቅ ካለብን የአምላክ ጸጋ መገለጫዎች አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው?
ስለ ቤዛው የሚገልጸውን ምሥራች አውጁ
6, 7. ለሰዎች ስለ ቤዛው ስንናገር ስለ አምላክ ጸጋ የሚገልጸውን ምሥራች እያወጅን ነው ሊባል የሚችለው እንዴት ነው?
6 በሥነ ምግባር ልቅ በሆነው በዚህ ዓለም ውስጥ ኃጢአት አስነዋሪ ነገር መሆኑ እየቀረ ነው፤ በመሆኑም ብዙዎች ለኃጢአታቸው ቤዛ እንደሚያስፈልጋቸው አይገነዘቡም። በሌላ በኩል ደግሞ ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣ ሰዎች፣ ልቅ የሆነ አኗኗር እውነተኛ ደስታ እንደማያስገኝ እያስተዋሉ ነው። ብዙዎች ኃጢአት ምን እንደሆነ፣ በእኛ ላይ ምን ተጽዕኖ እንደሚያሳድር እንዲሁም ከኃጢአት ባርነት ነፃ ለመውጣት ምን ማድረግ እንዳለብን የሚያውቁት ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ሲወያዩ ነው። ልበ ቅን የሆኑ ሰዎች ኃጢአት ምን እንደሆነ ሲገነዘቡ እንዲሁም ይሖዋ በታላቅ ፍቅሩና በጸጋው ተነሳስቶ ልጁን ወደ ምድር በመላክ ከኃጢአትና የኃጢአት ውጤት ከሆነው ከሞት እንደዋጀን ሲያውቁ በጣም ይደሰታሉ።—1 ዮሐ. 4:9, 10
7 ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “[ይሖዋ] በተትረፈረፈ ጸጋው መሠረት በልጁ ደም አማካኝነት ቤዛውን በመክፈሉ ነፃ ወጥተናል፤ አዎ፣ ለበደላችን ይቅርታ አግኝተናል።” (ኤፌ. 1:7) የክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት፣ አምላክ ለእኛ ያለውን ፍቅር የገለጸበት ከሁሉ የላቀ ስጦታ ከመሆኑም ሌላ የይሖዋ ጸጋ የተትረፈረፈ መሆኑን በግልጽ ያሳያል። በፈሰሰው የኢየሱስ ደም ላይ እምነት ካሳደርን፣ የኃጢአት ይቅርታ እንዲሁም ንጹሕ ሕሊና እንደምናገኝ ማወቃችን ምንኛ የሚያጽናና ነው! (ዕብ. 9:14) ይህ በእርግጥም ለሌሎች ልናካፍለው የሚገባ ምሥራች ነው!
ሰዎች ከአምላክ ጋር ወዳጅነት እንዲመሠርቱ እርዷቸው
8. ኃጢአተኛ የሆኑት የሰው ልጆች ከአምላክ ጋር መታረቅ የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው?
8 ሰዎች ከፈጣሪያቸው ጋር ወዳጅነት መመሥረት እንደሚችሉ የማሳወቅ ኃላፊነት አለብን። የሰው ልጆች በኢየሱስ መሥዋዕት ላይ እምነት ከሌላቸው አምላክ እንደ ጠላቶቹ ይመለከታቸዋል። ሐዋርያው ዮሐንስ እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “በወልድ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፤ ወልድን የማይታዘዝ ግን የአምላክ ቁጣ በላዩ ይኖራል እንጂ ሕይወትን አያይም።” (ዮሐ. 3:36) ደስ የሚለው ነገር፣ የክርስቶስ መሥዋዕት ከአምላክ ጋር እርቅ ለመፍጠር የሚያስችል መንገድ ከፍቷል። ጳውሎስ እንዲህ ብሏል፦ “እናንተ በአንድ ወቅት አእምሯችሁ በክፉ ሥራዎች ላይ ያተኮረ ስለነበር ከአምላክ የራቃችሁና ጠላቶች ነበራችሁ፤ አሁን ግን እሱ . . . ራሱን ለሞት አሳልፎ በሰጠው ሰው ሥጋዊ አካል አማካኝነት ከራሱ ጋር አስታርቋችኋል።”—ቆላ. 1:21, 22
9, 10. (ሀ) ክርስቶስ ለቅቡዓን ወንድሞቹ ምን ኃላፊነት ሰጥቷቸዋል? (ለ) “ሌሎች በጎች” ቅቡዓን ወንድሞቻቸውን የሚያግዟቸው እንዴት ነው?
9 ክርስቶስ በምድር ላሉት ቅቡዓን ወንድሞቹ ተልእኮ የሰጣቸው ሲሆን ጳውሎስ ይህንን ተልእኮ “የማስታረቅ አገልግሎት” ብሎ ጠርቶታል። ይህን በተመለከተ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለነበሩት ቅቡዓን ክርስቲያኖች እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ሁሉም ነገሮች የተገኙት በክርስቶስ አማካኝነት ከራሱ ጋር ካስታረቀንና የማስታረቅ አገልግሎት ከሰጠን አምላክ ነው። ይህም፣ አምላክ በክርስቶስ አማካኝነት ዓለምን ከራሱ ጋር ከማስታረቁም በላይ በደላቸውን አልቆጠረባቸውም ማለት ነው፤ ለእኛ ደግሞ የእርቁን መልእክት በአደራ ሰጥቶናል። ስለዚህ እኛ ክርስቶስን ተክተን የምንሠራ አምባሳደሮች ነን፤ አምላክ በእኛ አማካኝነት እየተማጸነ ያለ ያህል ነው። ክርስቶስን ተክተን የምንሠራ እንደመሆናችን መጠን ‘ከአምላክ ጋር ታረቁ’ ብለን እንለምናለን።”—2 ቆሮ. 5:18-20
10 “ሌሎች በጎች” በዚህ አገልግሎት በመካፈል ቅቡዓን ወንድሞቻቸውን የሚያግዟቸው ሲሆን ይህንንም እንደ ትልቅ መብት ይቆጥሩታል። (ዮሐ. 10:16) ሌሎች በጎች፣ የክርስቶስ መልእክተኞች በመሆን ለሰዎች መንፈሳዊውን እውነት በማስተማርና ሰዎች በግለሰብ ደረጃ ከይሖዋ ጋር ወዳጅነት እንዲመሠርቱ በመርዳት ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው። ይህም ስለ አምላክ ጸጋ የሚገልጸውን ምሥራች በተሟላ ሁኔታ የመመሥከሩ ሥራ አብይ ገጽታ ነው።
አምላክ ጸሎት ሰሚ እንደሆነ የሚገልጸውን ምሥራች ተናገሩ
11, 12. ሰዎች ወደ ይሖዋ መጸለይ እንደሚችሉ የሚገልጸው መልእክት ምሥራች ነው የምንለው ለምንድን ነው?
11 ብዙ ሰዎች የሚጸልዩት፣ እንዲሁ የአእምሮ እረፍት ለማግኘት እንጂ አምላክ ጸሎታቸውን እንደሚሰማ ስለሚያምኑ አይደለም። በመሆኑም ይሖዋ “ጸሎት ሰሚ” መሆኑን ማወቅ ያስፈልጋቸዋል። መዝሙራዊው ዳዊት እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ጸሎት ሰሚ የሆንከው አምላክ ሆይ፣ ሁሉም ዓይነት ሰው ወደ አንተ ይመጣል። የፈጸምኳቸው በደሎች አሸንፈውኛል፤ አንተ ግን መተላለፋችንን ይቅር አልክ።”—መዝ. 65:2, 3
12 ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ “ማንኛውንም ነገር በስሜ ከለመናችሁ እኔ አደርገዋለሁ” ብሏቸዋል። (ዮሐ. 14:14) “ማንኛውንም ነገር” ሲል ከይሖዋ ፈቃድ ጋር የሚስማማ ማንኛውንም ነገር ማለቱ እንደሆነ ግልጽ ነው። ዮሐንስ “በእሱ ላይ ያለን ትምክህት ይህ ነው፤ የምንጠይቀው ነገር ምንም ይሁን ምን ከፈቃዱ ጋር በሚስማማ ሁኔታ እስከለመንን ድረስ ይሰማናል” የሚል ማረጋገጫ ሰጥቶናል። (1 ዮሐ. 5:14) ጸሎት አእምሮን ከማረጋጋት ያለፈ ጥቅም እንዳለውና ወደ ይሖዋ ‘የጸጋ ዙፋን’ ለመቅረብ የሚያስችል ግሩም መንገድ እንደሆነ ሌሎች እንዲያውቁ መርዳት ትልቅ ነገር ነው! (ዕብ. 4:16) ሰዎች በትክክለኛው መንገድ፣ ወደ ትክክለኛው አካል እንዲሁም ተገቢ ስለሆኑ ነገሮች እንዲጸልዩ ስናስተምራቸው ወደ ይሖዋ እንዲቀርቡና በተጨነቁበት ወቅት መጽናኛ እንዲያገኙ እንረዳቸዋለን።—መዝ. 4:1፤ 145:18
የአምላክ ጸጋ በአዲሱ ሥርዓት
13, 14. (ሀ) ቅቡዓን ምን አስደናቂ መብት ይጠብቃቸዋል? (ለ) ቅቡዓኑ ከሰው ልጆች ጋር በተያያዘ ወደፊት ምን ግሩም ሥራ ያከናውናሉ?
13 የይሖዋ ጸጋ በዚህ ክፉ ሥርዓት ብቻ ተወስኖ አይቀርም። ጳውሎስ፣ ከክርስቶስ ጋር በሰማይ እንዲገዙ ለተጠሩት 144,000 ክርስቲያኖች አምላክ ስለሰጣቸው አስደናቂ መብት ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “አምላክ ምሕረቱ ብዙ ነው፤ እኛን ከወደደበት ታላቅ ፍቅሩ የተነሳ በበደላችን ሙታን በነበርንበት ጊዜም እንኳ ሕያዋን አድርጎ ከክርስቶስ ጋር አንድ አደረገን፤ እንደ እውነቱ ከሆነ የዳናችሁት በጸጋ ነው። ደግሞም ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድነት ስላለን ከእሱ ጋር አስነሳን፤ እንዲሁም ከእሱ ጋር በሰማያዊ ስፍራ አስቀመጠን፤ ይህን ያደረገው ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድነት ላለን ለእኛ በቸርነቱ የገለጠውን ወደር የሌለውን የጸጋውን ብልጽግና በመጪዎቹ ሥርዓቶች ያሳይ ዘንድ ነው።”—ኤፌ. 2:4-7
14 ቅቡዓን ክርስቲያኖች በሰማይ ከክርስቶስ ጋር ዙፋን ላይ ተቀምጠው በሚገዙበት ጊዜ ይሖዋ ምን ዓይነት አስደናቂ ነገሮች እንደሚሰጣቸው መገመት ያዳግታል። (ሉቃስ 22:28-30፤ ፊልጵ. 3:20, 21፤ 1 ዮሐ. 3:2) ይሖዋ በተለይ ለእነዚህ ክርስቲያኖች “ወደር የሌለውን የጸጋውን ብልጽግና” ያሳያል። ቅቡዓኑ “አዲሲቱ ኢየሩሳሌም” ይኸውም የክርስቶስ ሙሽራ ይሆናሉ። (ራእይ 3:12፤ 17:14፤ 21:2, 9, 10) እነዚህ ቅቡዓን፣ ታዛዥ የሆኑ የሰው ልጆች ከኃጢአትና ከሞት ባርነት ነፃ ወጥተው ወደ ፍጽምና እንዲደርሱ በመርዳት ከኢየሱስ ጋር ሆነው ‘ሕዝቦችን ይፈውሳሉ።’—ራእይ 22:1, 2, 17ን አንብብ።
15, 16. ይሖዋ ወደፊት ‘ለሌሎች በጎች’ ጸጋውን የሚያሳየው በየትኞቹ መንገዶች ነው?
15 ኤፌሶን 2:7 አምላክ “በመጪዎቹ ሥርዓቶች” ጸጋውን እንደሚያሳይ ይናገራል። ይሖዋ በምድር ላይ በሚያመጣው አዲስ ሥርዓት ውስጥ የሚኖሩ ሁሉ “ወደር የሌለውን የጸጋውን ብልጽግና” ይመለከታሉ። (ሉቃስ 18:29, 30) የይሖዋ ጸጋ በምድር ላይ ከሚገለጽባቸው አስደናቂ መንገዶች አንዱ ‘በመቃብር’ ያሉ ሰዎች ከሞት መነሳታቸው ይሆናል። (ኢዮብ 14:13-15፤ ዮሐ. 5:28, 29) ክርስቶስ መሥዋዕት ሆኖ ከመሞቱ በፊት በነበሩት ዘመናት የሞቱ ታማኝ ወንዶችና ሴቶች እንዲሁም በመጨረሻዎቹ ቀናት በታማኝነት የሚያንቀላፉ “ሌሎች በጎች” ሁሉ ትንሣኤ አግኝተው ይሖዋን ማገልገላቸውን ይቀጥላሉ።
16 አምላክን ሳያውቁ የሞቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችም ይነሳሉ። እነዚህ ሰዎች የይሖዋን ሉዓላዊነት የመደገፍ አጋጣሚ ይሰጣቸዋል። ዮሐንስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ሙታንን፣ ታላላቆችንና ታናናሾችን በዙፋኑ ፊት ቆመው አየሁ፤ የመጽሐፍ ጥቅልሎችም ተከፈቱ። ሌላም ጥቅልል ተከፈተ፤ ይህም የሕይወት መጽሐፍ ጥቅልል ነው። ሙታን በጥቅልሎቹ ውስጥ በተጻፉት ነገሮች መሠረት እንደየሥራቸው ፍርድ ተሰጣቸው። ባሕርም በውስጡ ያሉትን ሙታን ሰጠ፤ ሞትና መቃብርም በውስጣቸው ያሉትን ሙታን ሰጡ፤ እነሱም እያንዳንዳቸው እንደየሥራቸው ፍርድ ተሰጣቸው።” (ራእይ 20:12, 13) እርግጥ ነው፣ ከሞት የሚነሱት ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን የአምላክ መሥፈርቶች በሕይወታቸው ውስጥ እንዴት ተግባራዊ እንደሚያደርጉ መማር ያስፈልጋቸዋል። ከዚህም ሌላ በአዲሱ ሥርዓት ውስጥ ይሖዋ የሚጠብቅብንን ብቃቶች በያዙት ‘ጥቅልሎች’ ውስጥ የሰፈሩትን ጠቃሚ የሆኑ አዳዲስ መመሪያዎች መታዘዝ ይኖርባቸዋል። ይሖዋ፣ የእነዚህን ጥቅልሎች ይዘት እንድናውቅ በማድረግም ጸጋውን ይገልጻል።
ምሥራቹን ማወጃችሁን ቀጥሉ
17. በምሥክርነቱ ሥራ ስንካፈል ምን ነገር ማስታወስ ይኖርብናል?
17 መጨረሻው እየቀረበ ሲመጣ የመንግሥቱን ምሥራች የመስበክ ተልእኳችንን ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ትኩረት ልንሰጠው ይገባል! (ማር. 13:10) ምሥራቹ የይሖዋን ጸጋ አጉልቶ እንደሚያሳይ ምንም ጥርጥር የለውም። በምሥክርነቱ ሥራ ስንካፈል ይህን ልናስታውስ ይገባል። የምንሰብክበት ዋና ዓላማ ለይሖዋ ክብር ማምጣት ነው። ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? በአዲሱ ዓለም ውስጥ እንደምናገኛቸው ቃል የተገቡልን በረከቶች በሙሉ የይሖዋ ጸጋ ግሩም መገለጫዎች እንደሆኑ ለሰዎች በማሳወቅ ነው።
18, 19. የይሖዋ ጸጋ ጎልቶ እንዲታይ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
18 ለሌሎች በምንሰብክበት ጊዜ በክርስቶስ አገዛዝ ሥር የሰው ልጆች፣ ከቤዛዊ መሥዋዕቱ የተሟላ ጥቅም እንደሚያገኙና ቀስ በቀስ ወደ ፍጽምና እንደሚደርሱ ልናስረዳቸው እንችላለን። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ተስፋውም ፍጥረት ራሱ ደግሞ ከመበስበስ ባርነት ነፃ ወጥቶ የአምላክ ልጆች የሚያገኙት ዓይነት ክብራማ ነፃነት ማግኘት ነው።” (ሮም 8:21) ይህ ሊሆን የሚችለው በይሖዋ ጸጋ አማካኝነት ብቻ ነው።
19 መልእክቱን ለመስማት ፈቃደኛ ለሆኑ ሁሉ በራእይ 21:4, 5 ላይ የሚገኘውን አስደሳች ተስፋ የማካፈል መብት አግኝተናል፤ ጥቅሱ እንዲህ ይላል፦ “[አምላክ] እንባን ሁሉ ከዓይናቸው ያብሳል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም፤ ሐዘንም ሆነ ጩኸት እንዲሁም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም። ቀድሞ የነበሩት ነገሮች አልፈዋል።” በዙፋኑ ላይ የተቀመጠው ይሖዋም “እነሆ፣ ሁሉንም ነገር አዲስ አደርጋለሁ” ብሏል። አክሎም “እነዚህ ቃላት አስተማማኝና እውነት ስለሆኑ ጻፍ” በማለት ተናግሯል። ይህን ምሥራች በቅንዓት ስንሰብክ የይሖዋ ጸጋ ይበልጥ ጎልቶ እንዲታይ እናደርጋለን!