የዓለም መንፈስ እንዳይጋባባችሁ እየተከላከላችሁት ነውን?
“ከእግዚአብሔር የሆነውን መንፈስ እንጂ የዓለምን መንፈስ አልተቀበልንም።” —1 ቆሮንቶስ 2:12
1, 2. በህንድ አገር በቮፓል ከተማ መርዛማ ጋዝን የተመለከተ ምን አሳዛኝ አደጋ ደርሶ ነበር? ነገር ግን ሰዎች በዓለም ዙሪያ ከዚያ የከፋ ምን የሚገድል “ጋዝ” ወደ ውስጥ እየሳቡ ነው?
በ1984 በአንድ ቀዝቃዛ የታኅሣሥ ሌሊት በህንድ ውስጥ በሚገኘው የቮፓል ከተማ አንድ አስደንጋጭ ነገር ደረሰ። በዚያ ከተማ ውስጥ የኬሚካል ማምረቻ ፋብሪካ ነበረ። በዚያ የታኅሣሥ ሌሊት በጋዝ ማጠራቀሚያው በርሜሎች ውስጥ የሚገኝ አንድ መክደኛ በደንብ አልገጥም አለ። በድንገት ብዙ ኪሎ ግራም መጠን ያለው ሜቲል አይሶሲያኔት የተባለው ጋዝ አየር ውስጥ መደባለቅ ጀመረ። ይህ የሚገድል መርዘኛ ጋዝ በነፋስ እየተወሰደ ቤቶችንና ተኝተው የነበሩ ቤተሰቦችን አጥለቀለቀ። በዚህ ሳቢያ የሞቱት በሺዎች ሲቆጠሩ ብዙዎች ደግሞ አካለ ጐደሎ ሆኑ። እስከዚያ ድረስ ከደረሱት የኢንዱስትሪ አደጋዎች ሁሉ የከፋ ነበር።
2 ስለ ቮፓል ሲሰሙ ብዙ ሰዎች በጣም አዘኑ። ነገር ግን በዓለም ዙሪያ በመንፈሳዊ ገዳይ የሆነ መርዘኛ “ጋዝ” በመሳባቸው በየቀኑ ከሚሞቱት ሰዎች ቁጥር ጋር ሲወዳደር በቮፓል የፈነዳው ጋዝ የገደላቸው ሰዎች ቁጥር በጣም ጥቂት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “የዓለም መንፈስ” በማለት ይጠራዋል። ይህም ሐዋርያው ጳውሎስ “እኛ ግን ከእግዚአብሔር እንዲያው የተሰጠንን እናውቅ ዘንድ ከእግዚአብሔር የሆነውን መንፈስ እንጂ የዓለምን መንፈስ አልተቀበልንም” በማለት ከአምላክ መንፈስ ጋር እያነጻጸረ የተናገረለት የሚገድል ከባቢ አየር ነው።—1 ቆሮንቶስ 2:12
3. “የዓለም መንፈስ” ምንድን ነው?
3 ታዲያ “የዓለም መንፈስ” ምንድን ነው? ዘ ኒው ታየርስ ግሪክ ኢንግሊሽ ሌክሲከን ኦቭ ዘ ኒው ቴስታመንት እንደሚለው “መንፈስ” (በግሪክኛ ፕኒውማ) ለሚለው ቃል ብዙ ጊዜ የሚሠራበት ትርጉም “የማንኛውንም ሰው ነፍስ የሚሞላና የሚቆጣጠር ዝንባሌ ወይም ግፊት” ነው። አንድ ሰው ጥሩ ወይም መጥፎ መንፈስ ወይም ዝንባሌ ሊኖረው ይችላል። (መዝሙር 51:10፤ 2 ጢሞቴዎስ 4:22) አንድ የሰዎች ቡድንም እንዲሁ አንድ መንፈስ ወይም ጎላ ብሎ የሚታይ ዝንባሌ ሊኖረው ይችላል። ሐዋርያው ጳውሎስ ለወዳጁ ለፊልሞና “የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከመንፈሳችሁ ጋር ይሁን” በማለት ጽፎለታል። (ፊልሞና 25) በተመሳሳይም ዓለም በአጠቃላይ ሰፋ ባለ መጠን የሚታይ ጎላ ያለ ዝንባሌ አለው። ጳውሎስ “የዓለም መንፈስ” ብሎ የጠቀሰው ይህንን ነው። በቫንሳን በተዘጋጀው ወርድ ስተዲስ ኢን ዘ ኒው ቴስታመንት መሠረት “የሐረጉ ትርጉም ብልሹውን ዓለም የሚያንቀሳቅሰው የክፋት ባሕርይ ማለት ነው።” በዚህ ዓለም አስተሳሰብ የተሞላና የሰዎችን ድርጊት በኃይል የሚለውጥ ኃጢያተኛ ዝንባሌ ነው።
4. የዓለም መንፈስ ምንጭ ማን ነው? ይህስ መንፈስ በሰዎች ላይ ምን ጉዳት ያደርሳል?
4 ይህ መንፈስ መርዘኛ ነው። ለምን? ምክንያቱም ምንጩ “የዚህ ዓለም ገዥ” የሆነው ሰይጣን ስለሆነ ነው። እንዲያውም ሰይጣን “በማይታዘዙትም ልጆች ላይ አሁን ለሚሠራው መንፈስ አለቃ እንደ ሆነው በአየር ላይ ሥልጣን እንዳለው አለቃ” ተብሎ ተጠርቷል። (ዮሐንስ 12:31፤ ኤፌሶን 2:2) ይህን “አየር” ወይም “በማይታዘዙትም ልጆች ላይ አሁን ለሚሠራው መንፈስ” ከተባለው መሸሽ አስቸጋሪ ነው። በሰብዓዊው ኅብረተሰብ ውስጥ የትም ቦታ ይገኛል። ወደ ውስጥ ከሳብነው ዝንባሌዎቹንና ዓላማዎቹን ያጋባብናል። የዓለም መንፈስ ‘እንደ ሥጋ ፈቃድ መኖርን’ ማለትም ከኃጢአተኛው አለፍጽምናችን ጋር በሚስማማ መንገድ መኖርን ያበረታታል። እንዲህ ማድረግ ይገድላል፤ “እንደ ሥጋ ፈቃድ ብትኖሩ ትሞቱ ዘንድ አላችሁና” ስለተባለ ይህ መንፈስ ገዳይ ነው።—ሮሜ 8:13
የዚህን ዓለም መንፈስ መሸሽ
5. በቮፓል አደጋ በደረሰበት ወቅት አንድ ምስክር የጥበብ እርምጃ የወሰደው እንዴት ነበር?
5 በቮፓል አደጋው በደረሰበት ወቅት አንድ የይሖዋ ምስክር የአደጋ ማስጠንቀቂያ በሚያሰሙ መኪኖችና አፍንጫን በሚከረክረው የመርዘኛው ጋዝ ጭስ አማካኝነት ከእንቅልፉ ነቃ። ሳይዘገይ ቤተሰቡን ከእንቅልፍ ቀስቅሶ ወደ መንገድ ይዟቸው ወጣ። የንፋሱን አቅጣጫ ለመለየት ትንሽ ቆም ካለ በኋላ ግራ በተጋባው ሕዝብ መካከል እንደምንም ብሎ ታግሎ ቤተሰቡን ከከተማው ውጭ ወደሚገኝ አንድ ጋራ ጫፍ ላይ ይዞ ወጣ። እዚያም በአቅራቢያቸው ካለው ሐይቅ ከሚነፍሰው ንጹሕና ትኩስ አየር ሳንባዎቻቸውን ለመሙላት ቻሉ።
6. ከዓለም መንፈስ ለማምለጥ ወደ የት መሄድ እንችላለን?
6 ከዚህ ዓለም መርዘኛ “አየር” ሸሽተን የምናመልጥበት ከፍ ያለ ቦታ ይኖራልን? መጽሐፍ ቅዱስ አለ ይላል። ነቢዩ ኢሳይያስ ዘመናችንን አርቆ በመመልከት እንደሚከተለው ጽፏል፦ “በዘመኑም ፍጻሜ የእግዚአብሔር ቤት ተራራ በተራሮች ራስ ላይ ጸንቶ ይቆማል፣ ከኮረብቶችም በላይ ከፍ ከፍ ይላል፣ አሕዛብም ሁሉ ወደ እርሱ ይሰበሰባሉ። ሕግ ከጽዮን የእግዚአብሔርም ቃል ከኢየሩሳሌም ይወጣልና ብዙዎች አሕዛብ ሄደው፦ ኑ፣ ወደ እግዚአብሔር ተራራ፣ ወደ ያዕቆብ አምላክ ቤት እንውጣ፤ እርሱም መንገዱን ያስተምረናል፣ በጎዳናውም እንሄዳለን ይላሉ።” (ኢሳይያስ 2:2, 3) በዚህች ፕላኔት ላይ ከዚህ ዓለም የተበላሸና የተመረዘ መንፈስ ነፃ የሆነው ቦታ ከፍ ያለው ‘የይሖዋ ተራራ’ ማለትም የአምልኮ ስፍራ ብቻ ነው። በታማኝ ክርስቲያኖች መካከል የይሖዋ መንፈስ በነፃነት የሚፈስበት ቦታ ይህ ብቻ ነው።
7. ከዓለም መንፈስ ብዙዎች የዳኑት እንዴት ነው?
7 ከዚህ በፊት የዚህን ዓለም መንፈስ ወደ ውስጥ ሲስቡ የነበሩ ብዙ ሰዎች በቮፓል ያለው ምስክር ያጋጠመው ዓይነት እፎይታ አግኝተዋል። የዚህን ዓለም አየር ወይም መንፈስ ስለሚስቡት ‘የማይታዘዙ ልጆች’ ከተናገረ በኋላ ሐዋርያው ጳውሎስ “በእነዚህም ልጆች መካከል እኛ ሁላችን ደግሞ፣ የሥጋችንንና የልቡናችንን ፈቃድ እያደረግን፣ በሥጋችን ምኞት በፊት እንኖር ነበርን፤ እንደ ሌሎቹም ደግሞ ከፍጥረታችን የቁጣ ልጆች ነበርን። ነገር ግን እግዚአብሔር በምሕረቱ ባለጠጋ ስለ ሆነ፣ ከወደደን ከትልቅ ፍቅሩ የተነሣ በበደላችን ሙታን እንኳ በሆንን ጊዜ ከክርስቶስ ጋር ሕይወት ሰጠን” ብሏል። (ኤፌሶን 2:3–5) የዚህን የነገሮች ሥርዓት መርዛማ አየር ወደ ውስጥ የሚስቡ ሁሉ በመንፈሳዊ የሞቱ ናቸው። ይሁን እንጂ ለይሖዋ ምስጋና ይድረሰውና በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ለሞት ከሚያደርሰው ሁኔታ እያመለጡ በመንፈሳዊ ከፍ ወዳለው ቦታ እየሸሹ ነው።
“የዓለም መንፈስ” የሚገለጥባቸው መንገዶች
8, 9. (ሀ) የዓለም መንፈስ እንዳይጋባብን ዘወትር ንቁ መሆን እንዳለብን የሚያሳየው ምንድን ነው? (ለ) የሰይጣን መንፈስ ሊበክለን የሚችለው እንዴት ነው?
8 ሞት የሚያስከትለው የሰይጣን አየር አካባቢያችንን አሁንም አጥለቅልቆታል። ከፍ ካለው የንጹሕ አምልኮ ስፍራ ተንሸራትተን ወደ ታች በመውረድ ዓለም ውስጥ ገብተን በመንፈሳዊ ታፍነን እንዳንሞት ልንጠነቀቅ ይገባል። ለዚህም የማያቋርጥ ንቃት ያስፈልጋል። (ሉቃስ 21:36፤ 1 ቆሮንቶስ 16:13) ለምሳሌ ያህል የሚከተለውን ሐቅ እንመልከት። ሁሉም ክርስቲያኖች ይሖዋ ካወጣቸው የአቋም ደረጃዎች ጋር ይተዋወቃሉ፣ እንዲሁም እንደ ዝሙት፣ ምንዝር እና ግብረ ሰዶም የመሳሰሉ ንጹሕ ያልሆኑ ልማዶች ተቀባይነት አላቸው ብለውም አይስማሙም። ሆኖም በየዓመቱ 40,000 የሚያህሉ ግለሰቦች ከይሖዋ ድርጅት ይወገዳሉ። ለምን? ብዙውን ጊዜ ከላይ በተገለጹት ንጹሕ ያልሆኑ ልማዶች ምክንያት ነው። ይህ እንዴት ሊደርስባቸው ቻለ?
9 ሁላችንም ፍጹም አለመሆናችን አንዱ ምክንያት ነው። ሥጋ ደካማ ነው። በልባችን ውስጥ ከሚፈጠረው መጥፎ ዝንባሌ ጋር የማያቋርጥ ትግል አለብን። (መክብብ 7:20፤ ኤርምያስ 17:9) ይሁን እንጂ እነዚህ መጥፎ ዝንባሌዎች በዓለም መንፈስ አማካኝነት ይጠናከራሉ። በዚህ ዓለም ውስጥ ያሉ ብዙ ሰዎች የጾታ ብልግናን እንደ ስሕተት ስለማይቆጥሩት የፈለግኸውን አድርግ የሚለው ዝንባሌ የሰይጣን የነገሮች ሥርዓት ክፍል ነው። እንደዚህ ለመሰለው አስተሳሰብ ራሳችንን ካጋለጥን እንደ ዓለም ማሰብ መጀመራችን የማይቀር ነው። ብዙም ሳይቆይ እንደዚህ ያለው ንጹሕ ያልሆነ አስተሳሰብ መጥፎ ምኞቶችን ይፈጥርና መጨረሻው ከባድ ኃጢአት መሥራት ይመጣል። (ያዕቆብ 1:14, 15) ከዚያ በኋላ ከይሖዋ የንጹሕ አምልኮ ተራራ ወጥተን እየተንከባለልን ወደ ተበከሉ የሰይጣን ዓለም ዝቅተኛ ቦታዎች እንወርዳለን። በዚህ ቦታ በውዴታው የሚቆይ ማንኛውም ሰው የዘላለም ሕይወት አይወርስም።—ኤፌሶን 5:3–5, 7
10. የሰይጣን አየር የሚገለጽበት አንዱ መንገድ ምንድን ነው? ክርስቲያኖችስ ይህንን መሸሽ ያለባቸው ለምንድን ነው?
10 የዓለም መንፈስ በዙሪያችን በየትም ስፍራ ይታያል። ለምሳሌ ያህል ብዙ ሰዎች አክብሮት የጎደለውን የቀልድ አነጋገር ወይም ተረብ የኑሮአቸው ክፍል አድርገውታል። ብልሹ በሆኑ የፖለቲካ ሰዎችና ሥነ ምግባር በጎደላቸው ስግብግብ የሃይማኖት መሪዎች ግራ በመጋባት ከፍተኛ ቁም ነገር ባላቸው ነገሮች እንኳ ሳይቀር አክብሮት በጎደለው መንገድ ይናገራሉ። ክርስቲያኖች እንደዚህ ያለው አዝማሚያ እንዳይጋባባቸው ይከላከላሉ። ጤናማ በሆነ ቀልድ ሌሎችን ማሳቅ ብንችልም ወደ ጉባኤው ውስጥ አክብሮት የጎደለው የቀልድ አነጋገር ይዘን እንዳንገባ እንጠነቀቃለን። የአንድ ክርስቲያን አነጋገር ይሖዋን እንደሚፈራና የልብ ንጽሕና እንዳለው ያንጸባርቃል። (ያዕቆብ 3:10, 11፤ ከምሳሌ 6:14 ጋር አወዳድር።) ወጣቶችም ሆንን ሽማግሌዎች ‘ለእያንዳንዱ እንዴት እንደምንመልስ እንደሚገባን እናውቅ ዘንድ ንግግራችን ሁልጊዜ በጨው እንደ ተቀመመ፣ በጸጋ መሆን’ ይገባዋል።—ቆላስይስ 4:6
11. (ሀ) ሁለተኛው የዓለም መንፈስ ገጽታ ምንድን ነው? (ለ) ክርስቲያኖች ይህንን ነገር ከሚያንጸባርቁት ሰዎች የተለዩ የሆኑት ለምንድን ነው?
11 ሌላው የዚህን ዓለም መንፈስ የሚያንጸባርቀው ዝንባሌ ጥላቻ ነው። ዓለም በዘር፣ በጎሳ፣ በብሔርና በግለሰብ ግጭቶች ላይ በተመሠረተ ጥላቻና ቂም በቀል ተከፋፍሏል። የአምላክ መንፈስ ሙሉ በሙሉ በሚንቀሳቀስበት ቦታ ላይ ሁኔታዎች ምንኛ የተሻሉ ናቸው! ሐዋርያው ጳውሎስ እንደሚከተለው በማለት ጽፏል። “ለማንም ስለ ክፉ ፈንታ ክፉን አትመልሱ፤ በሰው ሁሉ ፊት መልካም የሆነውን አስቡ። ቢቻላችሁስ በእናንተ በኩል ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ። ተወዳጆች ሆይ፣ ራሳችሁ አትበቀሉ፣ ለቁጣው ፈንታ ስጡ እንጂ፤ በቀል የእኔ ነው፣ እኔ ብድራቱን እመልሳለሁ ይላል ጌታ ተብሎ ተጽፎአልና። ጠላትህ ግን ቢራብ አብላው፤ ቢጠማ አጠጣው፤ ይህን በማድረግህ በራሱ ላይ የእሳት ፍም ትከምራለህና። ክፉውን በመልካም አሸንፍ እንጂ በክፉ አትሸነፍ።”—ሮሜ 12:17–21
12. ክርስቲያኖች ፍቅረ ንዋይን የሚሸሹት ለምንድን ነው?
12 በተጨማሪም የዚህ ዓለም መንፈስ ፍቅረ ንዋይን ያበረታታል። በንግዱ ዓለም በመገፋፋት ብዙ ሰዎች በቅርብ ቀን በወጡ ዕቃዎች፣ ፋሽኖችና የመኪና ሞዴሎች ፍቅር የተለከፉ ሆነዋል። የ“ዓይን አምሮት” ባሪያ ሆነዋል። (1 ዮሐንስ 2:16) አብዛኞቹ ሰዎች የተሳካ ኑሮ ለማግኘታቸው መለኪያ አድርገው የሚቆጥሩት የቤታቸውን ትልቅነት ወይም በባንክ ያስቀመጡትን ገንዘብ ብዛት ነው። ከፍ ባለው የይሖዋ ንጹሕ አምልኮ ላይ የሚገኘውን መንፈሳዊ አየር የሚስቡት ክርስቲያኖች ግን ይህ ዝንባሌ እንዳይጋባባቸው ይከላከሉታል። ቁሳዊ ነገሮችን ለማግኘት ቆርጦ መነሣት አጥፊ ሊሆን እንደሚችል ያውቃሉ። (1 ጢሞቴዎስ 6:9, 10) ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን “የሰው ሕይወት በገንዘቡ ብዛት አይደለም” በማለት አሳስቧቸዋል።—ሉቃስ 12:15
13. አንዳንድ ተጨማሪ የዚህ ዓለም መንፈስ መግለጫዎች ምንድን ናቸው?
13 ጤናማ ያልሆነው የዚህ ዓለም “አየር” መግለጫ የሆኑ ሌሎች ነገሮችም አሉ። ከእነዚህም አንዱ የዓመፀኝነት መንፈስ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:1–3) ብዙ ሰዎች በሥልጣን ላይ ካሉት ጋር ፈጽሞ መተባበርን እንዳቆሙ ልብ ብለሃልን? ዓለማዊ ሥራ በምትሠራበት ቦታ አንድ የሚመለከት ሰው እስከሌለ ድረስ ብዙዎች መሥራት እንደማይፈልጉ ተመልክተሃልን? ግብር ሲከፍሉ በማጭበርበራቸው ወይም በሥራ ቦታ በመስረቃቸው ሕግ አፍራሽ የሆኑ ስንት ሰዎች ታውቃለህ? ተማሪ ከሆንክ የክፍል ጓደኞችህ በትምህርትህ ጥሩ ውጤት በማምጣትህ ስለሚንቁህ በደንብ ለመማርና የምትችለውን ሁሉ ከማድረግ ተስፋ ቆርጠህ ታውቃለህን? እነዚህ ሁሉ ክርስቲያኖች ሊቋቋሟቸው የሚገቡ የዓለም መንፈስ መግለጫዎች ናቸው።
የዚህን ዓለም መንፈስ እንዴት መከላከል ይቻላል?
14. ክርስቲያኖች ክርስቲያን ካልሆኑት ሰዎች የሚለዩት በምን መንገዶች ነው?
14 ታዲያ በዚህ ዓለም ውስጥ እየኖርን የዓለምን መንፈስ መከላከል የምንችለው እንዴት ነው? በአካል የትም ቦታ ብንገኝ በመንፈሳዊ ግን የዓለም ክፍል አለመሆናችንን ፈጽሞ መርሳት የለብንም። (ዮሐንስ 17:15, 16) ግቦቻችን የዚህ ዓለም ግቦች አይደሉም። ለነገሮች ያለን አመለካከት የተለየ ነው። እኛ መንፈሳዊ ሰዎች ነን። የምንናገረውና የምናስበው “መንፈሳዊውን ነገር ከመንፈሳዊው ነገር ጋር አስተያይተን መንፈስ በሚያስተምረን ቃል . . . እንጂ የሰው ጥበብ በሚያስተምረን ቃል አይደለም።”—1 ቆሮንቶስ 2:13
15. የዓለምን መንፈስ መቋቋም የምንችለው እንዴት ነው?
15 አንድ ሰው መርዛማ ጋዝ ባለበት አካባቢ መቆሙን ቢያውቅ ምን ማድረግ ይችላል? ከንጹሕ አየር ጋር የተያያዘ ጭምብል ያደርጋል ወይም ከአካባቢው ይሸሻል። የሰይጣንን አየር መሸሽም እነዚህን ዘዴዎች አጣምሮ ይይዛል። በተቻለ መጠን አስተሳሰባችን በዓለም መንፈስ እንዳይበከል ከሚያደርግ ከማንኛውም ነገር በአካል ራሳችንን ለማራቅ እንሞክራለን። ከዚህ የተነሣ ከመጥፎ ባልንጀርነት እንርቃለን፤ ረብሻን፣ ብልግናን፣ መናፍስትነትን፣ ዓመፅን ወይም ማንኛውንም የሥጋ ሥራ ለሚያስፋፋ የመዝናኛ ዓይነት ራሳችንን አጋልጠን አንሰጥም። (ገላትያ 5:19–21) ይሁን እንጂ በዓለም ውስጥ ስለምንኖር ለእነዚህ ነገሮች የመጋለጡን ሁኔታ ሙሉ በሙሉ ልናስቀረው አንችልም። ስለዚህ መንፈሳዊ ንጹሕ አየር ሊሰጠን ከሚችል ነገር ጋር ብንጣበቅ ጥበብ ያለበት እርምጃ እንወስዳለን። አዘውትሮ በመሰብሰብ፣ በግል ጥናት፣ በክርስቲያናዊ እንቅስቃሴዎችና ከክርስቲያኖች ጋር ተገናኝተን በመጫወት እንዲሁም በጸሎት መንፈሳዊ ሳንባዎቻችንን እንሞላቸዋለን። በዚህ መንገድ ማንኛውም ዓይነት የሰይጣን አየር ወደ ሳንባዎቻችን ሰርጎ ቢገባ የአምላክ መንፈስ ገፍትረን እንድናስወጣው ሊያበረታን ይችላል።—መዝሙር 17:1–3፤ ምሳሌ 9:9፤ 13:20፤ 19:20፤ 22:17
16. የአምላክ መንፈስ እንዳለን የምናሳየው እንዴት ነው?
16 የአምላክ መንፈስ አንድን ክርስቲያን የዚህ ዓለም ክፍል ከሆኑ ሰዎች የተለየ ሆኖ እንዲታይ አድርጎ ይለውጠዋል። (ሮሜ 12:1, 2) ጳውሎስ “የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ቸርነት፣ በጎነት፣ እምነት፣ የውሃት፣ ራስን መግዛት ነው። እንደዚህ ያሉትን የሚከለክል ሕግ የለም” ብሏል። (ገላትያ 5:22, 23) የአምላክ መንፈስ አንድ ክርስቲያን ጠለቅ ያለ ማስተዋል እንዲኖረውም ይረዳዋል። ጳውሎስ “ከእግዚአብሔር መንፈስ በቀር ለእግዚአብሔር ያለውን ማንም አያውቅም” ብሏል። (1 ቆሮንቶስ 2:11) በአጠቃላይ “ለእግዚአብሔር ያለው” የተባለው ስለ ቤዛዊ መሥዋዕቱ፣ በኢየሱስ ክርስቶስ ስለምትመራው የአምላክ መንግሥት፣ ስለ ዘላለም ሕይወት ተስፋና በቅርቡ ይህ ክፉ ዓለም የሚጠፋ ስለ መሆኑ የሚገልጹትን እውነቶች ይጨምራል። በአምላክ መንፈስ እርዳታ ክርስቲያኖች እንደነዚህ ያሉትን ነገሮች እንደ እውነት አድርገው ለመቀበል ችለዋል። ይህም እውቀት ለሕይወት ያላቸውን አመለካከት የዓለም ሰዎች ካላቸው አመለካከት የተለየ እንዲሆን አድርጎታል። በፊታቸው ይሖዋን ለዘላለም የማገልገልን ተስፋ አስቀምጠው በአሁኑ ጊዜ እርሱን በማገልገል በሚያገኙት ደስታ ይረካሉ።
17. የዓለምን መንፈስ በመቋቋም ረገድ የላቀውን ምሳሌ ያሳየው ማን ነው? እንዴትስ?
17 ኢየሱስ የዚህን ዓለም መንፈስ ለሚከላከሉት ሁሉ የላቀ ምሳሌ ነው። ኢየሱስ ብዙም ሳይቆይ ሰይጣን ሦስት ፈተናዎችን በማቅረብ ከይሖዋ አገልግሎት እርሱን ለማራቅ ሙከራ አድርጎ ነበር። (ማቴዎስ 4:1–11) የመጨረሻው ፈተና ኢየሱስ አንዴ ብቻ ለሰይጣን ቢሰግድ የመላው ዓለም ገዥ የመሆን አጋጣሚ ሊያገኝ እንደሚችል የሚገልጽ ነበር። ኢየሱስ ‘እሺ፣ ልስገድና አንዴ የዓለም ገዥ ከሆንኩ በኋላ ንስሐ ገብቼ ወደ ይሖዋ አምልኮ እመለሳለሁ። የዓለም ገዥ ብሆን የናዝሬቱ አናጢ በመሆን የሰውን ዘር ከምጠቅመው የበለጠ መጥቀም የምችልበት ደረጃ ላይ ልሆን እችላለሁ’ ብሎ ሊያስብ ይችል ነበር። ኢየሱስ እንደዚህ ብሎ አላሰበም። ይሖዋ የዓለም ገዥነቱን ሥልጣን እስኪሰጠው ድረስ ለመጠበቅ ፈቃደኛ ነበር። (መዝሙር 2:8) በዚያ ወቅትና በሌሎቹ አጋጣሚዎች ሁሉ የሰይጣንን አየር መርዛማ ግፊት ተቋቁሟል። ከዚህም የተነሣ ይህንን በመንፈሳዊ የተበከለ ዓለም አሸንፏል።—ዮሐንስ 16:33
18. የዓለምን መንፈስ መቋቋማችን ለአምላክ ምስጋና የሚያመጣለት እንዴት ነው?
18 ሐዋርያው ጴጥሮስ የኢየሱስን ፈለግ በጥብቅ መከተል እንዳለብን ተናግሯል። (1 ጴጥሮስ 2:21) ከዚህ የሚበልጥ ምን ምሳሌ ይኖረናል? በእነዚህ የመጨረሻ ቀኖች ሰዎች በዚህ ዓለም መንፈስ በመገፋፋት በየጊዜው እያዘቀጠ በሚሄድ ነውር ውስጥ ተዘፍቀዋል። እንደዚህ ባለ ዓለም ውስጥ ከፍ ያለው የይሖዋ አምልኮ ስፍራ የጠራና ንጹሕ ሆኖ መቆሙ እንዴት ያለ አስደናቂ ነገር ነው! (ሚክያስ 4:1, 2) በእርግጥም፣ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በየስፍራው የተንሰራፋውን የዚህን ዓለም መንፈስ ተቋቁመው በሁሉም ፊት ለይሖዋ ክብርና ምስጋና በማምጣት ወደ ይሖዋ የአምልኮ ስፍራ መጉረፋቸው የአምላክ መንፈስ ኃይል ያለው መሆኑን ያሳያል። (2 ጴጥሮስ 2:11, 12) የይሖዋ ቅቡዕ ንጉሥ ይህንን ክፉ ዓለም እስኪያስወግደውና ሰይጣን ዲያብሎስንና አጋንንቱን በጥልቁ ውስጥ እስኪያስራቸው ድረስ በዚያ ከፍ ያለ ስፍራ ላይ መቆየት የሁላችንም ቁርጥ ውሳኔ ይሁን። (ራእይ 19:19 እስከ 20:3) ከዚያ በኋላ የዚህ ዓለም መንፈስ አይኖርም። ያ ጊዜ እንዴት የተባረከ ጊዜ ይሆናል!
ልታብራራ ትችላለህን?
◻ የዓለም መንፈስ ምንድን ነው?
◻ የዚህ ዓለም መንፈስ በግለሰቦች ላይ ምን ጉዳት ያስከትላል?
◻ የዓለም መንፈስ መግለጫ የሆኑ አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው? እንዴትስ ልንሸሻቸው እንችላለን?
◻ የአምላክ መንፈስ እንዳለን እንዴት እናሳያለን?
◻ የዓለምን መንፈስ ለሚቋቋሙት ምን በረከቶች ይመጡላቸዋል?
[በገጽ 16, 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የዓለም መንፈስ ምንጩ ሰይጣን ነው
ከዓለም መንፈስ ለመራቅ ከፍ ወዳለው የይሖዋ የአምልኮ ስፍራ ሽሽ