ጥናት በረከት ያስገኛል
ሰዎች ፍራፍሬ ሲመርጡ አስተውለህ ታውቃለህ? አብዛኞቹ ሰዎች መብሰል አለመብሰሉን ለመለየት ቀለሙንና መጠኑን ይመለከታሉ። አንዳንዶች ያሸቱታል። ሌሎች በእጃቸው ያገላብጡታል፣ አልፎ ተርፎም በጣታቸው ጫን ጫን ያደርጉታል። ሌሎች ደግሞ የትኛው የበለጠ ውኃ እንዳለው ለማወቅ በሁለት እጃቸው አንድ አንድ ይዘው ያወዳድራሉ። አእምሮአቸው ምን እያሰበ ይሆን? እያንዳንዱን ነገር እያጤኑ፣ ልዩነቱን እያነጻጸሩ፣ ከዚህ በፊት ያደረጉትን ምርጫ እያስታወሱና አሁን የሚያዩትን ቀደም ሲል ከሚያውቁት ነገር ጋር እያወዳደሩ ነው። እንዲህ በማድረጋቸው የመረጡትን ጣፋጭ ፍሬ በመብላት ይደሰታሉ።
እርግጥ የአምላክን ቃል ማጥናት የሚያስገኘው በረከት ከዚህ እጅግ የላቀ ነው። እንዲህ ያለውን ጥናት በሕይወታችን ውስጥ ጉልህ ስፍራ ከሰጠነው እምነታችን ይጠነክራል፣ ፍቅራችን ያድጋል፣ አገልግሎታችን ይበልጥ ውጤታማ ይሆናል እንዲሁም የምናደርጋቸው ውሳኔዎች ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ማስተዋልና መለኮታዊ ጥበብ የተንጸባረቀባቸው ይሆናሉ። ምሳሌ 3:15 የአምላክን ቃል ማጥናት ስለሚያስገኘው በረከት ሲገልጽ “የተከበረም ነገር ሁሉ አይተካከላትም” ይላል። አንተ ይህን በረከት እያገኘህ ነውን? የአጠናን ዘዴህ በዚህ ረገድ ትልቅ ድርሻ ሊኖረው ይችላል።—ቆላ. 1:9, 10
ለመሆኑ ጥናት ምንድን ነው? እንዲሁ ላይ ላዩን ማንበብ ሳይሆን የማሰብ ችሎታን ተጠቅሞ አንድን ርዕሰ ጉዳይ በጥልቀትና በጥሞና መመርመር ማለት ነው። የምታነበውን ነገር ማጤንን፣ ከአሁን ቀደም ከምታውቀው ጉዳይ ጋር ማገናዘብንና የቀረቡትን ማስረጃዎች ማስተዋልን ይጨምራል። በጥናትህ ወቅት አዲስ ሆኖ ያገኘኸውን ነጥብ ለማጤን ሞክር። እንዲሁም ቅዱስ ጽሑፋዊውን ምክር ይበልጥ በተሟላ ሁኔታ ልትሠራበት የምትችለው እንዴት እንደሆነ አስብ። የይሖዋ አገልጋይ እንደመሆንህ መጠን ይህን ትምህርት ሌሎችን ለመርዳት መጠቀም ስለምትችልበት አጋጣሚ ማሰብህ አይቀርም። ጥናት ማሰላሰልን እንደሚጨምር ምንም ጥርጥር የለውም።
አእምሮን ማዘጋጀት
ለማጥናት በምትሰናዳበት ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስህን፣ የምታጠናውን ጽሑፍ፣ እርሳስ ወይም ብዕር፣ ማስታወሻ ደብተርና የመሳሰሉትን ነገሮች እንደምታዘጋጅ የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ ልብህንስ ታዘጋጃለህ? መጽሐፍ ቅዱስ ዕዝራ “የእግዚአብሔርን ሕግ ይፈልግና ያደርግ ዘንድ፣ ለእስራኤልም ሥርዓትንና ፍርድን ያስተምር ዘንድ ልቡን አዘጋጅቶ” እንደነበር ይነግረናል። (ዕዝራ 7:10) በዚህ መንገድ ልብን ማዘጋጀት ምንን ይጨምራል?
ጸሎት የአምላክን ቃል በትክክለኛ ዝንባሌ እንድናጠና ይረዳናል። ልባችን ይሖዋ የሚሰጠንን ትምህርት የሚቀበል እንዲሆን እንፈልጋለን። ምን ጊዜም ጥናቱን ከመጀመርህ በፊት ይሖዋ በመንፈሱ አማካኝነት እንዲረዳህ ለምነው። (ሉቃስ 11:13) የምታጠናው ነገር ትርጉም ምን እንደሆነ፣ ከይሖዋ ዓላማ ጋር እንዴት እንደሚዛመድ፣ መልካምና ክፉ የሆነውን በመለየት ረገድ እንዴት እንደሚረዳህ፣ መሠረታዊ ሥርዓቱን እንዴት በሕይወትህ ውስጥ ልትሠራበት እንደሚገባና ትምህርቱ ከአምላክ ጋር ያለህን ዝምድና የሚነካው እንዴት እንደሆነ ማስተዋል ትችል ዘንድ እንዲረዳህ ጸልይ። (ምሳሌ 9:10) በጥናትህ ወቅትም ቢሆን አምላክ ‘ጥበብ እንዲሰጥህ ከመለመን ወደኋላ አትበል።’ (ያዕ. 1:5) የተሳሳቱ ሐሳቦችን ወይም መጥፎ ምኞቶችን ለማስወገድ ይሖዋ እንዲረዳህ ከፈለግህ ባገኘኸው ትምህርት መሠረት ራስህን በሐቀኝነት መርምር። ይሖዋን ለሚሰጥህ ትምህርት ‘ዘወትር አመስግነው።’ (መዝ. 147:7) በዚህ መልኩ በጸሎት የተደገፈ ጥናት ይሖዋ በቃሉ አማካኝነት የሚያስተላልፈውን መልእክት አዳምጠን ተግባራዊ ምላሽ እንድንሰጥ ስለሚረዳን ከእርሱ ጋር ያለን ዝምድና እንዲጠናከር ያደርጋል።—መዝ. 145:18
የይሖዋን ሕዝቦች ከሌሎች የሚለያቸው የተማሩትን ተግባራዊ ማድረጋቸው ነው። ለአምላክ የማደር ባሕርይ የሚጎድላቸው ሰዎች ብዙውን ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስንና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን የመጠራጠርና የመቃወም ዝንባሌ አላቸው። እኛ ግን እንዲህ ዓይነት አመለካከት የለንም። በይሖዋ እንታመናለን። (ምሳሌ 3:5-7) አንድ ነገር ካልገባን በድፍረት ስህተት መሆን አለበት ወደሚል መደምደሚያ አናመራም። መልሱን ለማግኘት ምርምር ማድረጋችንንና መቆፈራችንን በመቀጠል ይሖዋን በትዕግሥት እንጠባበቃለን። (ሚክ. 7:7) እኛም ግባችን እንደ ዕዝራ የተማርነውን በሥራ ላይ ማዋልና ለሌሎች ማስተማር ነው። እንዲህ ያለ የልብ ዝንባሌ ካለን ከጥናታችን ብዙ በረከት እናጭዳለን።
የአጠናን ዘዴ
በቀጥታ ከአንቀጽ 1 ከመጀመርና እስከ መጨረሻው ድረስ ከመውጣት ይልቅ በመጀመሪያ የርዕሰ ጉዳዩን ወይም የምዕራፉን አጠቃላይ ይዘት ለመቃኘት ሞክር። በቅድሚያ ርዕሱ ምን እንደሚል አጢን። የምታጠናው ትምህርት ጭብጥ ይህ ነው። ከዚያም ንዑስ ርዕሶቹ ከጭብጡ ጋር እንዴት እንደሚዛመዱ ለማስተዋል ሞክር። በመቀጠል ደግሞ ከትምህርቱ ጋር ተያይዘው የቀረቡ ሥዕላዊ መግለጫዎች፣ ሰንጠረዦች ወይም የክለሳ ጥያቄዎች ካሉ እነሱን ተመልከት። ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ:- ‘በዚህ አጠቃላይ ግምገማ መሠረት ከዚህ ርዕስ የማገኘው ትምህርት ምን ሊሆን ይችላል? የሚጠቅመኝስ እንዴት ነው?’ ይህም ጥናትህ በምን ላይ ያተኮረ እንደሚሆን ከወዲሁ ፍንጭ ይሰጥሃል።
ከዚያ ነጥቦቹን አንድ በአንድ መርምር። የመጠበቂያ ግንብ የጥናት ርዕሶች እንዲሁም አንዳንድ መጻሕፍት ለየአንቀጾቹ የተዘጋጀ ጥያቄ አላቸው። እያንዳንዱን አንቀጽ በምታነብበት ጊዜ የጥያቄውን መልስ ማስመር ጠቃሚ ነው። ጥያቄዎች ባይኖሩ እንኳ ልታስታውሳቸው በምትፈልጋቸው ዋና ዋና ነጥቦች ላይ አስምር። ከዚህ ቀደም የማታውቀው አዲስ ሐሳብ ካጋጠመህ በደንብ ለመረዳት ሞክር። ለአገልግሎት የሚጠቅሙህን ወይም በሚቀጥለው ጊዜ በምታቀርበው ክፍል ውስጥ ልታካትታቸው የምትችላቸውን ምሳሌዎች ወይም አሳማኝ ነጥቦች ልብ በል። እያጠናኸው ያለውን ትምህርት ብትነግራቸው እምነታቸው ይጠናከራል የምትላቸውን ሰዎች አስብ። ልትጠቀምባቸው የምትፈልጋቸውን ነጥቦች አስምርባቸውና ጥናትህን ስትጨርስ ከልሳቸው።
ትምህርቱን በምታጠናበት ጊዜ ጥቅሶቹን አውጥተህ አንብብ። እያንዳንዱ ጥቅስ ከአንቀጹ ፍሬ ነገር ጋር እንዴት እንደሚዛመድ አጢን።
ያልገቡህ ወይም ይበልጥ ልትመረምራቸው የምትፈልጋቸው ነጥቦች ታገኝ ይሆናል። በእነዚህ ነጥቦች ከመዘናጋት ይልቅ ሌላ ጊዜ ቀስ ብለህ ልታያቸው እንድትችል በማስታወሻ ጽፈሃቸው እለፍ። አብዛኛውን ጊዜ ትምህርቱን እየመረመርክ ስትሄድ ነጥቦቹም ግልጽ እየሆኑልህ ይመጣሉ። ካልሆነ ተጨማሪ ምርምር ልታደርግ ትችላለህ። እንዲህ ዓይነት ምርምር የሚጠይቁት ነገሮች ምን ሊሆኑ ይችላሉ? ምናልባት በግልጽ ያልተረዳኸው ጥቅስ ይኖር ይሆናል። ወይም ደግሞ ጥቅሱ እየተብራራ ካለው ነጥብ ጋር እንዴት እንደሚዛመድ መረዳት ተቸግረህ ይሆናል። ወይም በትምህርቱ ውስጥ ያለ አንድ ሐሳብ ለራስህ ቢገባህም ለሌሎች ግልጽ አድርገህ ለማስረዳት ሊከብድህ ይችላል። እነዚህን ነጥቦች እንዲሁ ከማለፍ ይልቅ የጀመርከውን ጥናት ስትጨርስ በእነርሱ ላይ ምርምር ማድረጉ ጥበብ ሊሆን ይችላል።
ሐዋርያው ጳውሎስ ብዙ ዝርዝር የያዘውን መልእክቱን ለዕብራውያን ክርስቲያኖች ሲጽፍ በመልእክቱ መሃል “ከተናገርነውም ዋና ነገሩ ይህ ነው” ሲል ጠቅሷል። (ዕብ. 8:1) አንተስ አለፍ አለፍ እያልክ ዋናውን ነጥብ ትከልሳለህ? ጳውሎስ እንዲህ ያደረገበት ምክንያት ምን እንደሆነ ተመልከት። በዚሁ መልእክቱ ፊተኛ ምዕራፎች ውስጥ ታላቁ የአምላክ ሊቀ ካህናት ክርስቶስ ወደ ሰማይ እንደገባ ገልጾ ነበር። (ዕብ. 4:14–5:10፤ 6:20) ይሁንና ጳውሎስ በምዕራፍ ዕብ. 8:1 መጀመሪያ ላይ ይህንኑ ዋና ነጥብ ነጥሎ በመጥቀስና በማጉላት አንባቢዎቹ ትምህርቱ እነርሱን እንዴት እንደሚመለከታቸው በጥሞና እንዲያስቡበት አድርጓል። ክርስቶስ ስለ እነርሱ ይታይ ዘንድ በአምላክ ፊት እንደቀረበና እነርሱም ወደ ሰማያዊቷ “ቅድስት” ይገቡ ዘንድ መንገድ እንደከፈተላቸው ገልጿል። (ዕብ. 9:24፤ 10:19-22) ተስፋቸው እርግጠኛ መሆኑ በቀረው የመልእክቱ ክፍል ውስጥ ስለ እምነት፣ ጽናትና ክርስቲያናዊ አኗኗር የተሰጠውን ምክር ተግባራዊ እንዲያደርጉ የሚያነሳሳ ነበር። እኛም በተመሳሳይ በምናጠናበት ጊዜ በዋና ዋናዎቹ ነጥቦች ላይ የምናተኩር ከሆነ ጭብጡ እንዴት እንደዳበረ ከማስተዋላችንም ሌላ ከዚያ ምክር ጋር በሚስማማ መንገድ ለመመላለስ የሚያበቁ አሳማኝ ምክንያቶችን በአእምሮአችን መቅረጽ እንችላለን።
የግል ጥናትህ ለተግባር ያነሳሳህ ይሆን? ይህ በጣም ወሳኝ ጥያቄ ነው። አንድ ነገር ስትማር እንደሚከተለው እያልክ ራስህን ጠይቅ:- ‘ይህ ትምህርት አመለካከቴንና በሕይወቴ ውስጥ የማወጣውን ግብ እንዴት ሊነካው ይገባል? የሚገጥሙኝን ችግሮች ለመፍታት፣ ውሳኔ ለማድረግ ወይም አንድ ግብ ላይ ለመድረስ ልጠቀምበት የምችለው እንዴት ነው? በቤተሰቤ ውስጥ፣ በመስክ አገልግሎትና በጉባኤ እንዴት ልሠራበት እችላለሁ?’ እውቀትህን ሥራ ላይ ማዋል የምትችልባቸውን ተጨባጭ ሁኔታዎች ወደ አእምሮህ በማምጣት እነዚህን ጥያቄዎች በጸሎት አስብባቸው።
አንድን ምዕራፍ ወይም ርዕሰ ትምህርት ከጨረስህ በኋላ በአጭሩ ከልሰው። ዋና ዋናዎቹን ነጥቦችና እነርሱን የሚደግፉትን አሳማኝ ነጥቦች ማስታወስ ትችል እንደሆነና እንዳልሆነ ራስህን ፈትሽ። ይህን ማድረግህ ሐሳቡን ወደፊት ልትጠቀምበት በምትችለው መልኩ በአእምሮህ ለመቅረጽ ይረዳሃል።
የምናጠናቸው ጽሑፎች
የይሖዋ ሕዝብ እንደመሆናችን መጠን ብዙ የምናጠናቸው ጽሑፎች አሉን። ይሁን እንጂ ከየትኛው እንጀምር? ቅዱሳን ጽሑፎችን በየዕለቱ መመርመር ከተባለው ቡክሌት ጥቅሱንና የተሰጠውን ሐሳብ በየዕለቱ ማጥናታችን የተገባ ይሆናል። በየሳምንቱ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ስለምንገኝ ለእነዚህ ስብሰባዎች ለመዘጋጀት አስቀድመን የምናደርገው ጥናት የሚኖረው ጠቀሜታ የላቀ ነው። ከዚህም በተጨማሪ አንዳንዶች እነርሱ እውነትን ከመስማታቸው በፊት የወጡትን ክርስቲያናዊ ጽሑፎች ለማጥናት ጊዜ መድበዋል። ሌሎች ደግሞ በመረጡት የሳምንታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባባቸው ክፍል ላይ ጥልቀት ያለው ጥናት ያካሂዳሉ።
በሳምንታዊ የጉባኤ ስብሰባዎች ላይ የሚቀርቡትን ትምህርቶች በሙሉ በጥልቀት ለማጥናት ሁኔታህ ባይፈቅድልህስ? እንዲሁ ተዘጋጅቻለሁ ለማለት ያህል ብቻ በጥድፊያ ትምህርቱን ለመሸፈን አትሞክር። ሁሉንም ተዘጋጅቼ ልጨርሰው አልችልም በሚል አንዱንም ሳይጀምሩ መቅረት ደግሞ ከዚህ የከፋ ነው። ከዚህ ይልቅ ምን ያህሉን ልታጠና እንደምትችል ወስንና ያንኑ ጥሩ አድርገህ ተዘጋጅ። በየሳምንቱ እንደዚያ አድርግ። ቀስ በቀስ ሌሎች ስብሰባዎችንም በዝግጅትህ ለማካተት ጥረት አድርግ።
“ቤትህን ሥራ”
ይሖዋ የቤተሰብ ራሶች ቤተሰባቸው የሚያስፈልገውን ነገር ለማሟላት ጠንክረው መሥራት እንዳለባቸው ያውቃል። ምሳሌ 24:27 “በስተ ሜዳ ሥራህን አሰናዳ፣ ስለ አንተ በእርሻ አዘጋጃት” ይላል። ይሁንና የቤተሰብህ አባላት መንፈሳዊ ፍላጎትም ቢሆን ችላ ሊባል አይገባም። በመሆኑም ጥቅሱ “ከዚያም በኋላ ቤትህን ሥራ” በማለት ይቀጥላል። የቤተሰብ ራሶች ይህንን ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው? ምሳሌ 24:3 እንዲህ ይላል:- “ቤት በጥበብ ይሠራል፣ በማስተዋልም ይጸናል።”
ማስተዋል ቤተሰብህን የሚጠቅመው እንዴት ነው? ማስተዋል በግልጽ ከሚታየው ነገር ባሻገር ያለውን ለመመልከት የሚረዳ የአእምሮ ችሎታ ነው። ውጤታማ የቤተሰብ ጥናት የሚጀምረው የቤተሰብህን ሁኔታ በማጥናት ነው ሊባል ይችላል። የቤተሰብህ አባላት መንፈሳዊ እድገት ምን ይመስላል? ከእነርሱ ጋር ውይይት ስታደርግ ልብ ብለህ አዳምጣቸው። የማጉረምረም ወይም የቅሬታ መንፈስ ይታይባቸዋል? ለቁሳዊ ነገሮች ትልቅ ቦታ ይሰጣሉ? ከልጆችህ ጋር በአገልግሎት ስትካፈል ምን አስተውለሃል? በእኩዮቻቸው ፊት የይሖዋ ምሥክሮች ሆነው በመታወቃቸው አይሸማቀቁም? በቤተሰብ መልክ መጽሐፍ ቅዱስ ለማንበብና ለማጥናት ባወጣችሁት ፕሮግራም ደስ ብሏቸው ይካፈላሉ? በእርግጥ በይሖዋ መንገድ እየተመላለሱ ነውን? እነዚህን ነገሮች ልብ ብለህ መከታተልህ የቤተሰብ ራስ እንደመሆንህ መጠን በእያንዳንዱ የቤተሰብ አባል ውስጥ መንፈሳዊ ባሕርያትን ለመገንባት ምን እንደሚያስፈልግ ለመገንዘብ ይረዳሃል።
ከመጠበቂያ ግንብ ወይም ከንቁ! መጽሔት ለቤተሰቡ የሚያስፈልገውን ርዕስ ምረጥ። ከዚያም የቤተሰቡ አባላት አስቀድመው ሊዘጋጁበት ይችሉ ዘንድ የሚጠናው ርዕስ ምን እንደሆነ ንገራቸው። በጥናቱ ወቅት ፍቅራዊ መንፈስ እንዲሰፍን አድርግ። የትኛውንም የቤተሰብ አባል መገሰጽ ወይም ማሸማቀቅ ሳያስፈልግ ነጥቦቹ ለቤተሰባችሁ የሚሠሩት እንዴት እንደሆነ ለይተህ በመጥቀስ እያጠናችሁት ያለው ትምህርት ዋና ነጥብ ጎላ ብሎ እንዲታይ አድርግ። እያንዳንዱን የቤተሰብ አባል እንዲሳተፍ አበረታታ። የይሖዋ ቃል ለኑሯችን የሚያስፈልገንን ምክር በመስጠት ረገድ እንዴት “ፍጹም” እንደሆነ እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል እንዲያስተውል እርዳ።—መዝ. 19:7
የሚያስገኘው በረከት
አንዳንድ አስተዋይ ሰዎች ምንም መንፈሳዊ ግንዛቤ ሳይኖራቸውም ስለ አጽናፈ ዓለማችን፣ በዓለም ላይ ስለሚከናወኑት ነገሮችና ስለ ራሳቸውም ጥናት ሊያካሂዱ ይችላሉ። ይሁን እንጂ የዚህ ሁሉ ትርጉም ምን እንደሆነ አይገነዘቡም። በሌላ በኩል ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስን አዘውትረው የሚያጠኑ ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ እየታገዙ በእነዚህ ነገሮች አማካኝነት የተገለጡትን የአምላክን የእጅ ሥራዎች፣ የመጽሐፍ ቅዱስን ትንቢት ፍጻሜዎችና ለታዛዥ የሰው ዘሮች በረከት የሚሆነውን የአምላክ ዓላማ አፈጻጸም ያስተውላሉ።—ማር. 13:4-29፤ ሮሜ 1:20፤ ራእይ 12:12
ይህ ትልቅ ነገር ቢሆንም ለመኩራራት ምክንያት ሊሆነን አይገባም። ይልቁንም የአምላክን ቃል በየዕለቱ መመርመራችን በትሕትና መመላለሳችንን እንድንቀጥል ይረዳናል። (ዘዳ. 17:18-20) እንዲሁም ‘ከኃጢአት መታለል’ ይጠብቀናል። ምክንያቱም የአምላክ ቃል በልባችን ውስጥ ሕያው ከሆነ ከኃጢአት ለመራቅ ያለን ቁርጥ አቋም የሚላላበትና በኃጢአት ማባበያዎች የምንሸነፍበት አጋጣሚ አይኖርም። (ዕብ. 2:1፤ 3:13፤ ቆላ. 3:5-10) በዚህ መንገድ ‘በበጎ ሥራ ሁሉ ፍሬ እያፈራን በነገር ሁሉ ደስ ልናሰኝ ለጌታ እንደሚገባ መመላለስ’ እንችላለን። (ቆላ. 1:10) የአምላክን ቃል ስናጠና ዓላማችን ይኸው ነው። ይህንን ዓላማ ዳር ማድረስ መቻል ደግሞ ከሁሉ የላቀ ታላቅ በረከት ነው።