‘ከሁሉ በላይ ከልብ ተዋደዱ’
“የሁሉ ነገር መጨረሻ ተቃርቦአል፤ . . . ከሁሉ በላይ እርስ በርሳችሁ ከልብ ተዋደዱ።”—1 ጴጥሮስ 4:7, 8
ኢየሱስ ከሐዋርያቱ ጋር የሚያሳልፋቸው የመጨረሻ ሰዓታት ውድ እንደሆኑ ያውቅ ነበር። ከፊታቸው ምን እንደሚጠብቃቸው ተገንዝቦ ነበር። ብዙ ሥራ የሚጠብቃቸው ቢሆንም እንደ ኢየሱስ እነሱም ጥላቻና ስደት ያጋጥማቸዋል። (ዮሐንስ 15:18-20) አብረው ባሳለፉት የመጨረሻ ምሽት ‘እርስ በርስ የመዋደድን’ አስፈላጊነት በተደጋጋሚ አሳስቧቸዋል።—ዮሐንስ 13:34, 35፤ 15:12, 13, 17
2 በዚያ ምሽት አብሮ የነበረው ሐዋርያው ጴጥሮስ ኢየሱስ የሰጠው ማሳሰቢያ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ተገንዝቦ ነበር። ዓመታት ካለፉ በኋላ ኢየሩሳሌም ከመጥፋቷ ጥቂት ቀደም ብሎ በጻፈው ደብዳቤ ላይ የፍቅርን አስፈላጊነት አበክሮ ገልጿል። ክርስቲያኖችን “የሁሉ ነገር መጨረሻ ተቃርቦአል፤ . . . ከሁሉ በላይ እርስ በርሳችሁ ከልብ ተዋደዱ” ሲል መክሯቸዋል። (1 ጴጥሮስ 4:7, 8) ጴጥሮስ የተናገራቸው ቃላት በዚህ ሥርዓት ‘የመጨረሻ ዘመን’ ለሚኖሩ ሰዎች ልዩ ትርጉም አላቸው። (2 ጢሞቴዎስ 3:1) ‘ከልብ መዋደድ’ ሲባል ምን ማለት ነው? ሌሎችን ከልብ መውደዳችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? እንዲህ ዓይነት ፍቅር እንዳለን ልናሳይ የምንችለውስ እንዴት ነው?
‘ከልብ መዋደድ’ ሲባል ምን ማለት ነው?
3 ብዙዎች ፍቅር በተፈጥሮ የሚመጣ ስሜት መሆን አለበት ብለው ያስባሉ። ይሁን እንጂ ጴጥሮስ እዚህ ላይ የጠቀሰው ማንኛውንም ዓይነት ፍቅር ሳይሆን ከሁሉ የላቀውን የፍቅር ዓይነት ነው። በ1 ጴጥሮስ 4:8 ላይ ፍቅርን ለማመልከት የገባው የግሪክኛ ቃል አጋፔ የተባለው ነው። ይህ ቃል በመሠረታዊ ሥርዓት የሚመራን ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር ያመለክታል። አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ እንደገለጸው “አጋፔ የተባለው ፍቅር እንዲሁ በስሜት በመመራት የሚገለጽ ሳይሆን አስበንበትና ራሳችንን ገፋፍተን የምናሳየው የፍቅር ዓይነት ነው።” የራስ ወዳድነትን ዝንባሌ የወረስን በመሆናችን በአምላክ መሠረታዊ ሥርዓቶች በመመራት አንዳችን ለሌላው ፍቅር እንድናሳይ በየጊዜው ማሳሰቢያ ያስፈልገናል።—ዘፍጥረት 8:21፤ ሮሜ 5:12
4 እንዲህ ሲባል ግን እርስ በርስ የምንዋደደው እንዲሁ ግዴታ ስለሆነብን ብቻ ነው ማለት አይደለም። አጋፔ በመሠረታዊ ሥርዓት የሚመራ ነው ሲባል ምንም ዓይነት ስሜት የማይንጸባረቅበት የፍቅር ዓይነት እንደሆነ አድርገን ማሰብ የለብንም። ጴጥሮስ ‘እርስ በርሳችን ከልብ መዋደድ’ እንዳለብን ተናግሯል።a ያም ሆኖ እንዲህ ዓይነቱ ፍቅር ጥረት ማድረግ ይጠይቃል። አንድ ምሁር “ከልብ” ተብሎ የተተረጎመውን የግሪክኛ ቃል አስመልክተው ሲናገሩ “ቃሉ አንድ አትሌት በውድድሩ መጨረሻ ላይ ያለ የሌለ ኃይሉን ተጠቅሞ ለማሸነፍ የሚያደርገውን ጥረት በዓይነ ህሊናችን እንድንመለከት ያደርገናል” ብለዋል።
5 እንግዲያው እንዲህ ያለ ፍቅር ካለን ቀላል ሆኖ ያገኘነውን ነገር ብቻ በማድረግ ወይም ፍቅራችንን ለተወሰኑ ሰዎች ብቻ በመግለጽ አንወሰንም። ከዚህ ይልቅ ክርስቲያናዊ ፍቅር ሌሎችን መውደድ በሚያስቸግረን ጊዜም እንኳ ሳይቀር ፍቅራችንን እንድናሳይ ይገፋፋናል። (2 ቆሮንቶስ 6:11-13) ከዚህ በግልጽ መረዳት እንደሚቻለው አንድ አትሌት ችሎታውን ለማሻሻል ሌት ተቀን መሥራትና መለማመድ እንደሚያስፈልገው ሁሉ እኛም ይህን ፍቅር ለማዳበር ጥረት ይጠይቅብናል። አንዳችን ለሌላው እንዲህ ያለ ፍቅር ማሳየታችን በጣም አስፈላጊ ነው። ለምን? ቢያንስ ሦስት ምክንያቶች መጥቀስ ይቻላል።
እርስ በርስ መዋደድ ያለብን ለምንድን ነው?
6 በመጀመሪያ ደረጃ “ፍቅር ከእግዚአብሔር ስለሆነ” ነው። (1 ዮሐንስ 4:7) የዚህ ተወዳጅ ባሕርይ ምንጭ የሆነው ይሖዋ ቀድሞ ፍቅሩን አሳይቶናል። ሐዋርያው ዮሐንስ “እግዚአብሔር ፍቅሩን በመካከላችን የገለጠው እንዲህ ነው፤ እኛ በእርሱ አማካይነት በሕይወት እንኖር ዘንድ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን ወደ ዓለም ላከ” ሲል ተናግሯል። (1 ዮሐንስ 4:9) የአምላክ ልጅ ሰው ሆኖ ወደ ምድር ‘የተላከው’፣ አገልግሎቱን ያከናወነውና በእንጨት ላይ የተሰቀለው “በሕይወት እንኖር ዘንድ” ነው። አምላክ ላሳየን ከሁሉ የላቀ ፍቅር ምን ምላሽ መስጠት አለብን? ዮሐንስ “እግዚአብሔር እንዲህ ከወደደን እኛም እርስ በእርሳችን መዋደድ ይገባናል” በማለት ተናግሯል። (1 ዮሐንስ 4:11) ዮሐንስ “እግዚአብሔር እንዲህ ከወደደን” አለ እንጂ ከወደደህ አላለም። ነጥቡ ግልጽ ነው፤ አምላክ አንተን ብቻ ሳይሆን የእምነት ባልንጀሮችህንም የሚወድ ከሆነ አንተም ልትወዳቸው ይገባል።
7 በሁለተኛ ደረጃ ‘የሁሉ ነገር መጨረሻ ስለተቃረበ’ የተቸገሩ ወንድሞቻችንን ለመርዳት ከምንጊዜውም በበለጠ ዛሬ እርስ በርስ መዋደዳችን በጣም አስፈላጊ ነው። (1 ጴጥሮስ 4:7) የምንኖርበት ዘመን “የሚያስጨንቅ ጊዜ” ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:1) የዓለም ሁኔታዎች፣ የተፈጥሮ አደጋዎችና ተቃውሞ የተለያዩ ችግሮች ሊያስከትሉብን ይችላሉ። እንዲህ ያሉ ፈታኝ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን ከምንጊዜውም ይበልጥ እርስ በርስ መቀራረብና መረዳዳት አለብን። ከልብ የመነጨ ፍቅር እርስ በርስ የሚያስተሳስረን ከመሆኑም በላይ ‘እንድንተሳሰብ’ ያደርገናል።—1 ቆሮንቶስ 12:25, 26
8 በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ ‘ዲያብሎስ ስፍራ’ እንዳያገኝና እንዳያጠቃን እርስ በርስ መዋደዳችን በጣም አስፈላጊ ነው። (ኤፌሶን 4:27) ሰይጣን የእምነት አጋሮቻችንን አለፍጽምና ማለትም ያለባቸውን ድክመትና የሚፈጽሟቸውን ስህተቶች እንደ ማሰናከያ አድርጎ ለመጠቀም ፈጣን ነው። አንድ የእምነት ባልንጀራችን አሳቢነት የጎደለው ቃል ቢናገረን ወይም አግባብ ያልሆነ ድርጊት ቢፈጽምብን በዚህ ሳቢያ ከጉባኤ እንርቃለን? (ምሳሌ 12:18) እርስ በርስ ከልብ የምንዋደድ ከሆነ እንዲህ አናደርግም። እንዲህ ያለው ፍቅር በመካከላችን ያለውን ሰላም እንድንጠብቅና እጅ ለእጅ ተያይዘን አምላክን በአንድነት እንድናገለግል ይረዳናል።—ሶፎንያስ 3:9
ለሌሎች ፍቅር እንዳለህ ማሳየት የምትችልበት መንገድ
9 ፍቅር መጀመር ያለበት ከቤተሰብ ነው። ኢየሱስ እውነተኛ ተከታዮቹ እርስ በርስ ባላቸው ፍቅር ተለይተው እንደሚታወቁ ተናግሯል። (ዮሐንስ 13:34, 35) ፍቅር መታየት ያለበት በጉባኤ ብቻ ሳይሆን በቤተሰብም ውስጥ ነው። በትዳር ጓደኛሞች መካከልም ሆነ በወላጆችና በልጆች መካከል ፍቅር መታየት ይኖርበታል። የቤተሰብ አባሎቻችንን ማፍቀር ብቻ ሳይሆን ፍቅራችንን በተግባር መግለጽ ይኖርብናል።
10 የትዳር ጓደኛሞች አንዳቸው ለሌላው ፍቅራቸውን መግለጽ የሚችሉት እንዴት ነው? ሚስቱን ከልቡ የሚወድ ባል ለእሷ ልዩ አድናቆት እንዳለው በግልም ሆነ በሰው ፊት በቃልም ሆነ በተግባር ይገልጽላታል። ክብሯን የሚጠብቅላት ከመሆኑም በላይ ለስሜቷ ያስባል እንዲሁም የምትሰጠውን ሐሳብና አስተያየት ከፍ አድርጎ ይመለከታል። (1 ጴጥሮስ 3:7) ከራሱ ይልቅ ለእሷ ደኅንነት ይጨነቃል፤ በተጨማሪም ቁሳዊ፣ መንፈሳዊና ስሜታዊ ፍላጎቶቿን ለማሟላት የተቻለውን ሁሉ ጥረት ያደርጋል። (ኤፌሶን 5:25, 28) ባሏን ከልቧ የምትወድ ሚስት አንዳንድ ጊዜ እንዳሰበችው ሆኖ ባይገኝ እንኳ በጥልቅ ‘ታከብረዋለች።’ (ኤፌሶን 5:22, 33) ከአቅሙ በላይ የሆነ ነገር እንዲያደርግላት ከመጠበቅ ይልቅ ሕይወታቸው በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ያተኮረ እንዲሆን በማድረግ የባሏ ደጋፊና ተገዢ መሆኗን ታሳያለች።—ዘፍጥረት 2:18፤ ማቴዎስ 6:33
11 ወላጆች የሆናችሁ ለልጆቻችሁ ፍቅር ማሳየት የምትችሉት እንዴት ነው? ተግታችሁ በመሥራት ቁሳዊ ፍላጎቶቻቸውን ለማሟላት የምታደርጉት ጥረት አንዱ የፍቅራችሁ መግለጫ ነው። (1 ጢሞቴዎስ 5:8) ሆኖም ልጆች የሚያስፈልጋቸው ምግብ፣ ልብስና መጠለያ ብቻ አይደለም። እውነተኛውን አምላክ እንዲወዱና እንዲያገለግሉ መንፈሳዊ ማሠልጠኛ ማግኘት ያስፈልጋቸዋል። (ምሳሌ 22:6) ይህም በቤተሰብ ደረጃ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት፣ በአገልግሎት ለመካፈልና በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት ጊዜ መመደብ ይጠይቃል። (ዘዳግም 6:4-7) እንዲህ ባሉ መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች አዘውትሮ ለመካፈል በተለይ በዚህ ባለንበት አስጨናቂ ዘመን ውስጥ ከፍተኛ መሥዋዕትነት መክፈል ይጠይቃል። ለልጆችህ ዘላለማዊ ደኅንነት በማሰብ መንፈሳዊ ፍላጎታቸውን ለማሟላት መጣርህ ለእነሱ ያለህን ፍቅር የሚያሳይ ነው።—ዮሐንስ 17:3
12 በተጨማሪም ወላጆች የልጆቻቸውን ስሜታዊ ፍላጎት በማሟላት ፍቅራቸውን ማሳየታቸው በጣም አስፈላጊ ነው። ልጆች ስሜታቸው በቀላሉ ሊጎዳ ይችላል፤ ከልብ እንደምትወዷቸው ማወቅ ይፈልጋሉ። ምን ያህል እንደምትወዷቸው በተለያዩ መንገዶች ግለጹላቸው፤ እንዲህ ያሉት የፍቅር መግለጫዎች እንደሚወደዱና እንደሚፈለጉ እንዲሰማቸው ያደርጓቸዋል። ከልብ በመነጨ ስሜት አመስግኗቸው፤ እንዲህ ማድረጋችሁ የሚያደርጉትን ጥረት እንደምታስተውሉና እንደምታደንቁ እንዲገነዘቡ ያደርጋቸዋል። በተጨማሪም ምን ዓይነት ልጅ ሆነው እንዲያድጉ እንደምትፈልጉ እንዲገነዘቡ ስለሚያደርጋቸው በፍቅር ገስጿቸው። (ኤፌሶን 6:4) እንዲህ ያሉት የፍቅር መግለጫዎች በእነዚህ መጨረሻ ቀኖች ያሉትን ተጽዕኖዎች መቋቋም የሚችል ደስተኛና እርስ በርስ የሚደጋገፍ ቤተሰብ ለመገንባት ይረዳሉ።
13 ፍቅር የሌሎችን ድክመት ችላ ብለን እንድናልፍ ያደርገናል። ጴጥሮስ “ከልብ ተዋደዱ” የሚል ምክር በሰጠበት ጊዜ ይህን ማድረግ በጣም አስፈላጊ የሆነበትን ምክንያት ሲገልጽ “ፍቅር ብዙ ኀጢአትን ይሸፍናልና” ብሏል። (1 ጴጥሮስ 4:8) ይሁንና ኃጢአትን ‘መሸፈን’ ሲባል ከባድ የሆኑ ኃጢአቶችንም መደበቅ ማለት አይደለም። ከባድ ኃጢአቶች በጉባኤ ውስጥ በኃላፊነት ቦታ ለሚያገለግሉ ወንድሞች መነገር ያለባቸው ጉዳዮች ናቸው። (ዘሌዋውያን 5:1፤ ምሳሌ 29:24) ከባድ ኃጢአት የሠሩ ሰዎች በመጥፎ ድርጊታቸው ንጹሕ የሆኑ ሰዎችን ሲጎዱ ዝም ብሎ መመልከት ፍቅር የጎደለው ከመሆኑም በላይ ቅዱስ ጽሑፋዊ ድጋፍ የለውም።—1 ቆሮንቶስ 5:9-13
14 አብዛኛውን ጊዜ የእምነት ባልንጀሮቻችን የሚፈጽሟቸው ስህተቶች ያን ያህል የሚጋነኑ አይደሉም። ሁላችንም ብንሆን በቃል ወይም በድርጊት የምንሰናከል ሲሆን በዚህም ሌሎችን ቅር ልናሰኝ አልፎ ተርፎም ልንጎዳ እንችላለን። (ያዕቆብ 3:2) የእምነት ባልንጀሮቻችን የሚፈጽሙትን ስህተት ለሌሎች ለመንዛት እንቸኩላለን? እንዲህ ያለው ድርጊት በጉባኤ ውስጥ አለመግባባት እንዲፈጠር ከማድረግ ሌላ የሚፈይደው ነገር የለም። (ኤፌሶን 4:1-3) በፍቅር የምንመራ ከሆነ የእምነት ባልንጀራችንን ‘አናማም።’ (መዝሙር 50:20) ልስን ወይም ቀለም በአንድ ግድግዳ ላይ የሚታዩ እንከኖችን እንደሚሸፍን ሁሉ ፍቅርም የሌሎችን አለፍጽምና ይሸፍናል።—ምሳሌ 17:9
15 ፍቅር ችግር ላይ ለወደቁ ወንድሞቻችን እንድንደርስላቸው ያደርገናል። በእነዚህ መጨረሻ ቀኖች ያሉት ሁኔታዎች እየከፉ በሄዱ መጠን አንዳንድ ጊዜ የእምነት ባልንጀሮቻችን ችግር ላይ ሊወድቁና ቁሳዊ እርዳታ ማግኘት ሊያስፈልጋቸው ይችላል። (1 ዮሐንስ 3:17, 18) ለምሳሌ ያህል ከጉባኤያችን አባላት መካከል ከፍተኛ የኢኮኖሚ ችግር ላይ የወደቀ ወይም ሥራ አጥቶ የተቸገረ ይኖር ይሆን? ካለ አቅማችን በፈቀደ መጠን ቁሳዊ እርዳታ ልናደርግለት እንችላለን። (ምሳሌ 3:27, 28፤ ያዕቆብ 2:14-17) ቤታቸው ጥገና የሚያስፈልገው አንዲት አረጋዊት መበለት ይኖሩ ይሆን? ካሉ በራሳችን ተነሳሽነት የበኩላችንን አስተዋጽኦ ልናበረክት እንችላለን።—ያዕቆብ 1:27
16 ፍቅራችንን የምናሳየው በአካባቢያችን ላሉት የእምነት ባልንጀሮቻችን ብቻ አይደለም። አንዳንድ ጊዜ በሌሎች አገሮች ያሉ የአምላክ አገልጋዮች በጎርፍ መጥለቅለቅ፣ በመሬት መንቀጥቀጥ ወይም በእርስ በርስ ብጥብጥ ሳቢያ ችግር እንደደረሰባቸው የሚገልጽ ሪፖርት ልንሰማ እንችላለን። እነዚህ ወንድሞች ምግብ፣ ልብስና ሌሎች ቁሳቁሶች በአስቸኳይ ያስፈልጓቸው ይሆናል። ጎሳቸው ወይም ዘራቸው ምንም ይሁን ምን ለውጥ አያመጣም። በዓለም ዙሪያ ያሉ ‘ወንድሞቻችንን በሙሉ እንወዳቸዋለን።’ (1 ጴጥሮስ 2:17) ስለዚህ በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደነበሩት ጉባኤዎች ሁሉ እኛም ሌሎችን ለመርዳት በሚደረጉ ዝግጅቶች የበኩላችንን ድርሻ ለማበርከት የቻልነውን ሁሉ ጥረት እናደርጋለን። (የሐዋርያት ሥራ 11:27-30፤ ሮሜ 15:26) በእነዚህ ሁሉ መንገዶች ፍቅራችንን ስናሳይ በዚህ የመጨረሻ ዘመን አንድ ላይ የሚያስተሳስረንን ሰንሰለት ይበልጥ እናጠናክረዋለን።—ቆላስይስ 3:14
17 ፍቅር የአምላክን መንግሥት ምሥራች ለሌሎች እንድንናገር ይገፋፋናል። ኢየሱስን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። የሰበከውና ያስተማረው ለምንድን ነው? ሕዝቡ የነበረበት መንፈሳዊ ሁኔታ በእጅጉ ‘ስላሳዘነው’ ነው። (ማርቆስ 6:34) ለሕዝቡ መንፈሳዊ እውነት ማስተማርና የተስፋ ብርሃን መፈንጠቅ ይጠበቅባቸው የነበሩት ሐሰተኛ እረኞች መንጎቻቸውን ችላ ብለዋቸው ነበር። በመሆኑም ኢየሱስ ከልብ በመነጨ ፍቅርና ርኅራኄ ተገፋፍቶ “የእግዚአብሔርን መንግሥት ወንጌል” በመስበክ አጽናናቸው።—ሉቃስ 4:16-21, 43
18 በዛሬው ጊዜም ብዙ ሰዎች መንፈሳዊ ረሃባቸውን የሚያስታግስላቸው ከማጣታቸውም በላይ ተስፋ ቢሶች ሆነዋል። ልክ እንደ ኢየሱስ እኛም እውነተኛውን አምላክ የማያውቁ ሰዎች ያሉበትን መንፈሳዊ ሁኔታ የምናስተውል ከሆነ በፍቅርና በርኅራኄ ተገፋፍተን የአምላክን መንግሥት ምሥራች እንነግራቸዋለን። (ማቴዎስ 6:9, 10፤ 24:14) የቀረው ጊዜ አጭር ከመሆኑ አንጻር ሲታይ ይህን ሕይወት አድን መልእክት መስበክ የአሁኑን ያህል አጣዳፊ የሆነበት ዘመን የለም።—1 ጢሞቴዎስ 4:16
“የሁሉ ነገር መጨረሻ ተቃርቦአል”
19 ጴጥሮስ እርስ በርስ ተዋደዱ የሚለውን ምክር ከመስጠቱ በፊት “የሁሉ ነገር መጨረሻ ተቃርቦአል” ሲል ተናግሯል። (1 ጴጥሮስ 4:7) በቅርቡ ይህ ክፉ ዓለም ይጠፋና አምላክ በሚያመጣው ጽድቅ የሚሰፍንበት አዲስ ዓለም ይተካል። (2 ጴጥሮስ 3:13) እንግዲያው ዛሬ ቸልተኞች የምንሆንበት ጊዜ አይደለም። ኢየሱስ “በገደብ የለሽ ሕይወት፣ በመጠጥ ብዛትና ስለ ኑሮ በመጨነቅ ልባችሁ እንዳይዝልና ያ ቀን እንደ ወጥመድ ድንገት እንዳይደርስባችሁ ተጠንቀቁ” በማለት አሳስቧል።—ሉቃስ 21:34, 35
20 በመሆኑም በጊዜ ሂደት ውስጥ በምን ወቅት ላይ እንደምንገኝ ለይተን በማወቅ ‘ነቅተን መጠበቅ’ አለብን። (ማቴዎስ 24:42) ሊያዘናጉን ከሚችሉ የተለያዩ የሰይጣን ፈተናዎች ራሳችንን እንጠብቅ። ይህ ጨካኝና ፍቅር የለሽ ዓለም ለሌሎች ፍቅር እንዳናሳይ ተጽዕኖ እንዲያሳድርብን አንፍቀድ። ከሁሉ በላይ ደግሞ በቅርቡ በመሲሐዊ መንግሥቱ አማካኝነት ለዚህች ምድር ያለውን ታላቅ ዓላማ ወደሚያስፈጽመው እውነተኛ አምላክ ማለትም ወደ ይሖዋ ከምንጊዜውም ይበልጥ እንቅረብ።—ራእይ 21:4, 5
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች 1 ጴጥሮስ 4:8 ላይ የሚገኘውን ሐሳብ “አጥብቃችሁ ተዋደዱ” ወይም “የጠለቀ ፍቅር ይኑራችሁ” ሲሉ ተርጉመውታል።
ለጥናት የሚረዱ ጥያቄዎች
• ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ምን የስንብት ምክር ሰጠ? ጴጥሮስ የኢየሱስን ምክር እንደተገነዘበ የሚያሳየውስ ምንድን ነው? (አንቀጽ 1-2)
• ‘ከልብ መዋደድ’ ሲባል ምን ማለት ነው? (አንቀጽ 3-5)
• እርስ በርስ መዋደድ ያለብን ለምንድን ነው? (አንቀጽ 6-8)
• ለሌሎች ያለህን ፍቅር ማሳየት የምትችለው እንዴት ነው? (አንቀጽ 9-18)
• ያለንበት ዘመን ቸልተኞች የምንሆንበት ጊዜ አይደለም የምንለው ለምንድን ነው? ቁርጥ ውሳኔያችንስ ምን መሆን አለበት? (አንቀጽ 19-20)
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በፍቅር የተሳሰረ ቤተሰብ በእነዚህ መጨረሻ ቀኖች የሚያጋጥሙትን ተጽዕኖዎች በተሻለ ሁኔታ መቋቋም ይችላል
[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ፍቅር ችግር ላይ ለወደቁት እንድንደርስ ያነሳሳናል
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የአምላክን መንግሥት ምሥራች ለሌሎች መንገር የፍቅር መግለጫ ነው