ምዕራፍ 12
ሐሜት መጥፎ የሆነው ለምንድን ነው?
“በአንድ ወቅት የሆነ ፓርቲ ላይ ተገኝቼ ነበር። በማግስቱ፣ በዚያ ከነበሩት ወንዶች ከአንዱ ጋር የፆታ ግንኙነት እንደፈጸምኩ ተወራ። ይህ ጨርሶ ከእውነት የራቀ ነበር!”—ሊንዳ
“ከአንዲት ልጅ ጋር የፍቅር ጓደኝነት እንደጀመርኩ ሲወራ የምሰማበት ጊዜ አለ፤ እውነቱን ለመናገር ግን እንዲህ ዓይነት ግንኙነት ልጀምር ይቅርና ልጅቷን እንኳ ጭራሽ አላውቃትም! ሐሜተኛ የሆኑ ብዙ ሰዎች የሚያወሩት ነገር እውነት ይሁን አይሁን ብዙም አይጨነቁም።”—ማይክ
ሐሜት ልክ በፊልም ላይ እንደምታያቸው ሰዎች ሕይወትህ የተመሰቃቀለ ሆኖ እንዲሰማህ ሊያደርግህ ይችላል። የ19 ዓመቷ አምበር ያጋጠማት ሁኔታ ለዚህ ምሥክር ነው፤ “ብዙ ጊዜ መጥፎ ነገር ይወራብኛል” ብላለች። “እንዳረገዝኩና በተደጋጋሚ እንዳስወረድኩ እንዲሁም ዕፅ እንደምወስድና እንደማዘዋውር ተወርቶብኝ ያውቃል። ሰዎች እንዲህ ያለ ነገር የሚያወሩብኝ ለምንድን ነው? እውነቱን ለመናገር ምክንያቱ አይገባኝም!”
ሊጎዳህ የሚያስብ አንድ ልጅ አንዲት ቃል መተንፈስ ሳያስፈልገው በኢንተርኔትና በሞባይል መልእክት በመላክ ብቻ ስምህን ሊያጠፋው ይችላል። እንዲህ ያለውን ሐሜት፣ ወሬ ለመስማት አሰፍስፈው ለሚጠብቁ በርካታ ሰዎች ለማድረስ የሚያስፈልገው ነገር በኮምፒውተሩ ወይም በሞባይሉ ላይ የሚገኙ የተወሰኑ ፊደሎችን መንካት ብቻ ነው! እንዲያውም አንዳንዶች አንድን ሰው ለማዋረድ ሲሉ ራሱን የቻለ ድረ ገጽ የሚከፍቱበት ጊዜ አለ። አብዛኛውን ጊዜ ማለት ይቻላል የግል መረጃዎችን ለማሰራጨት ተብለው የሚዘጋጁ ድረ ገጾች (ዌብሎግ) ፊት ለፊት ቢሆን ኖሮ በማይነገሩ ወሬዎች የተሞሉ ናቸው።
ስለ ሌሎች ማውራት ሁልጊዜ መጥፎ ነው?
የሚከተለው ዓረፍተ ነገር እውነት ነው ወይስ ሐሰት?
ስለ ሌሎች ማውራት ምንጊዜም መጥፎ ነው። □ እውነት □ ሐሰት
ለዚህ ጥያቄ ትክክለኛው መልስ ምንድን ነው? በጨዋታ መሃል ስለ ሌሎች ማንሳታችን ተገቢ የሚሆንበት ጊዜ ሊኖር ይችላል። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ “ለሌሎች ሰዎች ጉዳይም ትኩረት ስጡ” በማለት ይመክረናል። (ፊልጵስዩስ 2:4) ይህ ሲባል ግን በማይመለከተን ጉዳይ ጣልቃ እንገባለን ማለት አይደለም። (1 ጴጥሮስ 4:15) ይሁንና በጭውውት መሃል ስለ ሌሎች የምንሰማቸው ወሬዎች ማን ሊያገባ እንደሆነ፣ ማን እንደወለደ ወይም እንደነዚህ ያሉ ሌሎች ነገሮችን ለማወቅ ስለሚያስችሉን አብዛኛውን ጊዜ ጠቃሚ ሊሆኑ ይችላሉ። ደግሞስ ስለ ሌሎች ሰዎች አንስተን ካላወራን ስለ እነሱ እናስባለን ማለት እንዴት እንችላለን?
ይሁን እንጂ እንዲህ ያለው ጭውውት በቀላሉ ወደ ሐሜት ሊቀየር ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ “ቶማስና ሊዲያ ቢጋቡ ጥሩ ባልና ሚስት ይወጣቸዋል” የሚለው በቅንነት የተሰነዘረ አስተያየት መልኩን ቀይሮ “ቶማስና ሊዲያ ለመጋባት እያሰቡ ነው” ተብሎ ይወራ ይሆናል። ይሁንና በእነዚህ ሁለት ሰዎች መካከል ምንም ዓይነት ግንኙነት ላይኖር ይችላል። ‘ታዲያ ምን ችግር አለው’ ትል ይሆናል፤ በአንተ ላይ ቢደርስ ግን እንዲህ አትልም ነበር!
የ18 ዓመቷ ጁሊ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ያጋጠማት ሲሆን በወቅቱ ስሜቷ ተጎድቶ ነበር። “በጣም ተናድጄ ነበር። ከዚያ ወዲህ ማንንም ማመን አቃተኝ” በማለት ተናግራለች። የ19 ዓመቷ ጄንም ተመሳሳይ ሁኔታ አጋጥሟታል። “አንድ ልጅ የፍቅር ጓደኛዬ እንደሆነ ተደርጎ ስለተወራ ልጁን ለመራቅ ተገደድኩ። ይሁንና ከልጁ ጋር የነበረን ወዳጅነት በሰው ወሬ መቋረጥ አልነበረበትም፤ ሌላ ዓይነት ግንኙነት እንዳለን ሳይወራብን በነፃነት ጓደኛሞች መሆን አንችልም?”
በዘዴ የጭውውቱን አቅጣጫ ቀይር
አንድን ሰው ለማማት ቢከጅልህ አንደበትህን ለመግታት ምን ማድረግ ትችላለህ? ይህን ጥያቄ ለመመለስ መኪና በሚበዛበት መንገድ ላይ ማሽከርከር ምን ዓይነት ችሎታ እንደሚጠይቅ ለማሰብ ሞክር። አንድ አሽከርካሪ እንዲህ ባለ መንገድ ላይ ሲነዳ መስመሩን እንዲቀይር፣ ሌላ መኪና ለማሳለፍ ሲል ፍጥነቱን እንዲቀንስ አሊያም ከናካቴው እንዲያቆም የሚያስገድድ ድንገተኛ ሁኔታ ያጋጥመው ይሆናል። አሽከርካሪው ንቁ ከሆነ ምን ሊከሰት እንደሚችል አስቀድሞ በማስተዋል አስፈላጊውን እርምጃ ይወስዳል።
ከሰዎች ጋር በምትጨዋወትበት ጊዜም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ብዙውን ጊዜ ጭውውቱ መልኩን ለውጦ ወደ ሐሜት እየተቀየረ መሆኑ በቀላሉ ሊታወቅህ ይችላል። እንዲህ ያለ ሁኔታ ሲያጋጥም ከላይ እንዳየነው አሽከርካሪ ‘መስመርህን መቀየር’ ትችላለህ? እንዲህ ያለ እርምጃ ካልወሰድህ ሐሜት ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል መገንዘብ ይኖርብሃል። ማይክ እንዲህ ብሏል፦ “ስለ አንዲት ልጅ ሲወራ ‘እሷ ያየሁት ወንድ ሁሉ አይለፈኝ የምትል ናት’ በማለት መጥፎ ነገር ተናግሬ ነበር፤ ይህ ወሬ ዞሮ ዞሮ ልጅቷ ጆሮ ደረሰ። ልጅቷ ስለ ጉዳዩ መጥታ ስታነጋግረኝ የነበረውን ሁኔታ ፈጽሞ አልረሳውም፤ ደግነት በጎደለው አነጋገሬ ምን ያህል እንደተጎዳች ንግግሯ ያስታውቅ ነበር። በወቅቱ ችግሩን የፈታነው ቢሆንም በዚህ መንገድ ሰውን በመጉዳቴ በጣም አዝኛለሁ!”
ቃላት የሌሎችን ስሜት ሊጎዱ እንደሚችሉ ምንም ጥርጥር የለውም። መጽሐፍ ቅዱስም ቢሆን “ግድ የለሽ ቃል እንደ ሰይፍ ይወጋል” ይላል። (ምሳሌ 12:18) ከመናገርህ በፊት ቆም ብለህ ማሰብህ አስፈላጊ የሆነው ለዚህ ነው! ስለ አንድ ሰው የግል ጉዳይ ተነስቶ ሞቅ ያለ ወሬ እየተወራ ሳለ ጭውውቱን ማቆም ራስን መግዛት ይጠይቃል። የ17 ዓመቷ ካሮሊን እንደገለጸችው “ስለምትናገረው ነገር መጠንቀቅ ይኖርብሃል። ወሬውን የሰማኸው ከታመነ ምንጭ ካልሆነ ውሸት ልታዛምት ትችላለህ።” እንግዲያው ሌሎችን ሊጎዳ የሚችል ወሬ በምትሰማበት ጊዜ የሐዋርያው ጳውሎስን ምክር በመከተል ‘በጸጥታ ለመኖርና በሌሎች ሰዎች ጉዳይ ጣልቃ ላለመግባት’ ጥረት አድርግ።—1 ተሰሎንቄ 4:11
በሌሎች ጉዳይ ጣልቃ ሳትገባ ለእነሱ እንደምታስብ ማሳየት የምትችለው እንዴት ነው? ስለ አንድ ሰው ከማውራትህ በፊት እንዲህ እያልክ ራስህን ጠይቅ፦ ‘ጉዳዩን በትክክል አውቀዋለሁ? ይህን ጉዳይ ለማውራት የተነሳሳሁት ለምንድን ነው? የማወራው ነገር ሰዎች ስለ እኔ ምን አመለካከት እንዲኖራቸው ያደርጋል?’ በተለይ የመጨረሻውን ጥያቄ ልታስብበት ይገባል፤ ምክንያቱም ሐሜተኛ በመሆንህ የምትታወቅ ከሆነ ከምታማው ሰው ይልቅ ትዝብት ውስጥ የምትወድቀው አንተ ነህ።
ሐሜቱ የተወራብህ አንተ ብትሆንስ?
ሐሜቱ የተወራው ስለ አንተ ቢሆን ምን ማድረግ ትችላለህ? መክብብ 7:9 “በመንፈስህ ለቍጣ አትቸኵል” በማለት ያስጠነቅቃል። ነገሩን በጣም አክብደህ ላለማየት ጥረት አድርግ። መጽሐፍ ቅዱስ “የሚነገረውን ቃል ሁሉ ለማዳመጥ አትሞክር፤ . . . ብዙ ጊዜ አንተ ራስህ፣ ሌሎችን እንደረገምህ ልብህ ያውቃልና” ይላል።—መክብብ 7:21, 22
እርግጥ ነው፣ ምንጊዜም ቢሆን ለሐሜት ምንም ማስተባበያ ሊቀርብ አይገባም። ያም ሆኖ ከመጠን በላይ መቆጣትህ የከፋ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል፤ ስምህ በሐሜት መጥፋቱ ሳያንስ ሌሎች ስለ አንተ ያላቸው ግምት ይባስ ዝቅ እንዲል ሊያደርግ ይችላል! ታዲያ ረኔ እንደተባለችው ወጣት ዓይነት አስተሳሰብ ለምን አታዳብርም? ረኔ እንዲህ ብላለች፦ “ስለ እኔ መጥፎ ነገር ሲወራ ብዙውን ጊዜ በጣም አዝናለሁ፤ ሆኖም ሁኔታውን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ለመመልከት እሞክራለሁ። እነዚህ ሰዎች በሚቀጥለው ጊዜ ስለ ሌላ ሰው ወይም ስለ ሌላ ነገር ማውራታቸው አይቀርም።”a
እንግዲያው ከሰዎች ጋር ስትጫወት ወሬው ወደ ሐሜት የሚያመራ ከመሰለህ አስተዋይ በመሆን የጭውውቱን አቅጣጫ ለመቀየር ጥረት አድርግ። ሐሜት የተወራብህ አንተ ከሆንክ ደግሞ ነገሩን ከመጠን በላይ አክብደህ ባለማየት መብሰልህን ማሳየት ትችላለህ። ማንነትህን በመልካም ሥራህ አሳይ። (1 ጴጥሮስ 2:12) እንዲህ የምታደርግ ከሆነ ከሌሎች ጋር ያለህ ጥሩ ግንኙነት እንዳይበላሽ ማድረግ የምትችል ከመሆኑም በላይ በአምላክ ፊት ጥሩ አቋም ይዘህ ትኖራለህ።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a አንዳንድ ጊዜ ሐሜተኛውን በዘዴ ማነጋገሩ ጥሩ ሊሆን ይችላል። አብዛኛውን ጊዜ ግን ‘ፍቅር የኃጢአትን ብዛት ስለሚሸፍን’ እንዲህ ማድረጉ አስፈላጊ አይደለም።—1 ጴጥሮስ 4:8
ቁልፍ ጥቅስ
“አንደበቱን የሚጠብቅ ሕይወቱን ይጠብቃል፤ አፉ እንዳመጣለት የሚናገር ግን ይጠፋል።”—ምሳሌ 13:3
ጠቃሚ ምክር
ሐሜት ሲወራልሽ ምን ማለት ትችያለሽ? “ስለዚህ ጉዳይ ማውራት አልፈልግም። ደግሞም በሌለችበት ስለ እሷ ማውራቱ ተገቢ አይደለም።”
ይህን ታውቅ ነበር?
ሐሜት ሲወራ መስማትህ በራሱ በተወሰነ መጠን ጥፋተኛ ያደርግሃል። ሐሜተኛው ሲያወራልህ ጆሮህን ሰጥተህ ማዳመጥህ ወሬው በፍጥነት እንዲዛመት መንገድ ይከፍታል!
ላደርጋቸው ያሰብኳቸው ነገሮች
አንድ ወሬ ለማናፈስ ቢከጅለኝ እንዲህ አደርጋለሁ፦ ․․․․․
ስለ እኔ መጥፎ ነገር ቢወራ ችግሩን ለመፍታት እንዲህ አደርጋለሁ፦ ․․․․․
ከዚህ ርዕሰ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ወላጆቼን ልጠይቃቸው የምፈልገው ነገር ․․․․․
ምን ይመስልሃል?
● ስለ ሌሎች ጉዳይ ማውራት ተገቢ የሚሆነው መቼ ነው?
● በሐሜት ምክንያት ስሜትህ ተጎድቶ ያውቃል? ከሆነ ከሁኔታው ምን ትምህርት አገኘህ?
● ሰዎችን ማማትህ ሌሎች ለአንተ ያላቸው አመለካከት ዝቅ እንዲል የሚያደርገው እንዴት ነው?
[በገጽ 107 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
ያማሁት ሰው ስለ ጉዳዩ ሰምቶ ባነጋገረኝ ጊዜ ሁለተኛ ሰው ማማት እንደሌለብኝ ተማርኩ። ነገሩን አድበስብሼ ማለፍ የምችልበት መንገድ አልነበረም! አንድን ሰው ከጀርባው ከማማት ይልቅ ግለሰቡን በግልጽ ማነጋገሩ በጣም የተሻለ መሆኑን ጥሩ ትምህርት አግኝቻለሁ!”—ፖላ
[በገጽ 108 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሐሜት የሰውን ስም የሚያጠፋ አደገኛ መሣሪያ ነው