ምዕራፍ ስምንት
ተስፋ የሚያስቆርጡ ነገሮች ቢያጋጥሙትም ጸንቷል
1. የሴሎ ነዋሪዎች በሐዘን የተዋጡት ለምንድን ነው?
ሳሙኤል የሴሎ ነዋሪዎች ባጋጠማቸው ሐዘን ልቡ ተነክቷል። ከተማይቱ በእንባ የታጠበች ያህል ነበር። አባታቸው፣ የትዳር ጓደኛቸው፣ ልጃቸው ወይም ወንድማቸው ከቤት እንደወጣ በመቅረቱ ምክንያት የማያለቅሱ ሴቶችና ልጆች አልነበሩም ማለት ይቻላል። እስራኤላውያን ከፍልስጤማውያን ጋር ባደረጉት ጦርነት ክፉኛ ተሸንፈው ወደ 30,000 የሚጠጉ ወታደሮቻቸውን አጥተዋል፤ ይህ እልቂት የደረሰው ደግሞ በዚያው ሰሞን አድርገውት በነበረው ሌላ ጦርነት 4,000 ወታደሮቻቸው መገደላቸው ያስከተለው ሐዘን ሳይረሳ ነው።—1 ሳሙ. 4:1, 2, 10
2, 3. ሴሎ ለኀፍረት እንድትዳረግና ክብሯን እንድታጣ ያደረጓት በተከታታይ የደረሱባት አሳዛኝ ክስተቶች ምንድን ናቸው?
2 ይህ ሁኔታ እስራኤላውያን በተከታታይ ካጋጠሟቸው አሳዛኝ ክስተቶች አንዱ ብቻ ነበር። መጥፎ የነበሩት የሊቀ ካህኑ የዔሊ ልጆች አፍኒንና ፊንሐስ ቅዱስ የሆነው የቃል ኪዳኑ ታቦት ከሴሎ በተወሰደ ጊዜ እነሱም አብረው ሄደው ነበር። ለወትሮው በመገናኛው ድንኳን ቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ ይቀመጥ የነበረው ይህ ክቡር ታቦት አምላክ በመካከላቸው እንዳለ የሚያመለክት ነበር። ይህ ታቦት ምትሃታዊ ኃይል ያለው ይመስል ሕዝቡ ድል ያስገኝልናል በሚል የተሳሳተ አመለካከት ታቦቱን ወደ ጦርነቱ ስፍራ ይዞት ሄደ። ሆኖም ፍልስጤማውያን አፍኒንን እና ፊንሐስን ከገደሉ በኋላ ታቦቱን ማርከው ወሰዱ።—1 ሳሙ. 4:3-11
3 ታቦቱ ለብዙ መቶ ዓመታት ሴሎ በሚገኘው የማደሪያ ድንኳን ውስጥ መቀመጡ ማደሪያውን ክብር አጎናጽፎት ነበር። አሁን ግን ታቦቱ ተማረከ። የ98 ዓመቱ ዔሊ ይህን ሲሰማ ከተቀመጠበት ወንበር ላይ ወደ ኋላ ወድቆ ሞተ። ባሏን በሞት ያጣችው የልጁ ሚስትም በዚያኑ ዕለት በወሊድ ምክንያት አረፈች። እሷም ልትሞት እያጣጣረች ሳለ “ክብር ከእስራኤል ተለይቶአል” በማለት ተናግራ ነበር። በእርግጥም፣ ሴሎ ፈጽሞ እንደ ቀድሞዋ ልትሆን አልቻለችም።—1 ሳሙ. 4:12-22
4. በዚህ ምዕራፍ ላይ ስለ ምን ጉዳይ ይብራራል?
4 ታዲያ ሳሙኤል እነዚህን ሁሉ አሳዛኝ ሁኔታዎች እንዴት ይወጣቸው ይሆን? እምነቱ፣ የይሖዋን ጥበቃና ሞገስ ያጣውን ሕዝብ የመርዳቱን ተፈታታኝ ኃላፊነት እንዲወጣ ያስችለው ይሆን? በዛሬው ጊዜ፣ ሁላችንም እምነታችንን የሚፈታተን መከራ ብሎም ተስፋ የሚያስቆርጥ ሁኔታ አልፎ አልፎ ያጋጥመን ይሆናል፤ ስለሆነም ከሳሙኤል ምን ትምህርት ማግኘት እንደምንችል እስቲ እንመልከት።
“ጽድቅ እንዲፈጸም የሚያደርግ ተግባር” አከናውኗል
5, 6. የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ የሳሙኤልን ታሪክ መተረኩን ተወት በማድረግ በ20 ዓመቱ ጊዜ ውስጥ በተከናወኑት በየትኞቹ ጉዳዮች ላይ ያተኩራል?
5 አሁን ደግሞ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ የሳሙኤልን ታሪክ ተወት ያደርግና ፍልስጤማውያን ቅዱሱን ታቦት በመውሰዳቸው ምክንያት ምን ችግር እንደደረሰባቸውና ታቦቱን ለመመለስ የተገደዱት እንዴት እንደሆነ ይተርካል። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሳሙኤል እንደገና መተረክ የሚጀምረው 20 ዓመታት ገደማ ካለፉ በኋላ ስለተፈጸሙ ነገሮች በመናገር ነው። (1 ሳሙ. 7:2) ሳሙኤል በእነዚያ 20 ዓመታት ምን ሲያደርግ ነበር? መልሱን መገመት አያስፈልገንም።
6 መጽሐፍ ቅዱስ ይህ የ20 ዓመት ጊዜ ከመጀመሩ በፊት ስለነበረው ሁኔታ ሲናገር “የሳሙኤልም ቃል ወደ እስራኤል ሁሉ ደረሰ” ይላል። (1 ሳሙ. 4:1) በተጨማሪም ይህ የ20 ዓመት ጊዜ ከተጠናቀቀ በኋላ ሳሙኤል አለመግባባቶችን ለመፍታትና ለጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት በየዓመቱ በሦስት የእስራኤል ከተሞች ውስጥ እየተዘዋወረ ይሠራ እንደነበር ይናገራል። ከዚያም ወደ ትውልድ ከተማው ወደ አርማቴም ይመለስ ነበር። (1 ሳሙ. 7:15-17) ከዚህ በግልጽ መረዳት እንደምንችለው ሳሙኤል ምንጊዜም በሥራ የተጠመደ ሰው ነበር፤ በእነዚያ 20 ዓመታት ውስጥም የሚያከናውነው በርካታ ሥራ ነበረው።
መጽሐፍ ቅዱስ ሳሙኤል በ20 ዓመት ጊዜ ውስጥ ስላከናወነው ተግባር የሚጠቅሰው ነገር ባይኖርም በይሖዋ አገልግሎት ተጠምዶ እንደነበር እርግጠኞች መሆን እንችላለን
7, 8. (ሀ) ሳሙኤል ለሁለት አሥርተ ዓመታት ጠንክሮ ሲሠራ ከቆየ በኋላ ለሕዝቡ ምን መልእክት አስተላለፈ? (ለ) ሕዝቡ ሳሙኤል ለሰጠው ማረጋገጫ ምን ምላሽ ሰጠ?
7 የዔሊ ልጆች ብልሹ ምግባር የሕዝቡን እምነት ሸርሽሮት ነበር። እንዲያውም ብዙዎች በዚህ ምክንያት ወደ ጣዖት አምልኮ ፊታቸውን ሳያዞሩ አልቀሩም። ሳሙኤል ለሁለት አሥርተ ዓመታት ጠንክሮ ሲሠራ ከቆየ በኋላ ለሕዝቡ እንዲህ የሚል መልእክት አስተላለፈ፦ “በፍጹም ልባችሁ ወደ እግዚአብሔር የምትመለሱ ከሆነ፣ ሌሎችን አማልክትና አስታሮትን ከመካከላችሁ አስወግዱ፤ ራሳችሁንም ለእግዚአብሔር አሳልፋችሁ ስጡ፤ እርሱንም ብቻ አምልኩ፤ እርሱም ከፍልስጥኤማውያን እጅ ይታደጋችኋል።”—1 ሳሙ. 7:3
8 ‘የፍልስጥኤማውያን እጅ’ በሕዝቡ ላይ አይሎ ነበር። ፍልስጤማውያን፣ የእስራኤልን ጦር በቀላሉ ስለደመሰሱ የአምላክን ሕዝቦች በማንአለብኝነት መጨቆን እንደሚችሉ ተሰምቷቸው ነበር። ይሁንና ሳሙኤል፣ ሕዝቡ ወደ ይሖዋ ቢመለስ ሁኔታው እንደሚለወጥ ማረጋገጫ ሰጣቸው። ታዲያ ሕዝቡ ፈቃደኛ ነበር? ሕዝቡ ጣዖቶቻቸውን አስወግደው ይሖዋን ብቻ ማምለክ ጀመሩ፤ ይህ ሁኔታ ሳሙኤልን በጣም አስደስቶታል። ከዚያ በኋላ ሳሙኤል ከኢየሩሳሌም በስተ ሰሜን በሚገኘው ተራራማ አካባቢ በነበረችው ምጽጳ በተባለች ከተማ ሕዝቡን ሰበሰበ። ሕዝቡም በዚያ ሲጾም ዋለ፤ ከጣዖት አምልኮ ጋር በተያያዘ ለፈጸመውም በርካታ ኃጢአት ንስሐ ገባ።—1 ሳሙኤል 7:4-6ን አንብብ።
ፍልስጤማውያን፣ ንስሐ የገቡት የይሖዋ ሕዝቦች አንድ ላይ መሰብሰባቸው እነሱን ለማጥቃት ጥሩ አጋጣሚ እንደሆነ ተሰምቷቸው ነበር
9. ፍልስጤማውያን ምን ጥሩ አጋጣሚ እንዳገኙ ተሰማቸው? የአምላክ ሕዝቦችስ አደጋ እንዳንዣበበባቸው ሲያውቁ ምን አደረጉ?
9 ይሁንና ፍልስጤማውያን ሕዝቡ በአንድነት እንደተሰበሰበ ሲያውቁ ይህ ለእነሱ ጥሩ አጋጣሚ እንደሆነ አሰቡ። በመሆኑም በዚያ የተሰበሰበውን የአምላክን ሕዝብ ለማጥፋት ሠራዊታቸውን ወደ ምጽጳ ላኩ። በዚህ ጊዜ እስራኤላውያን አደጋ እንዳንዣበበባቸው ሰሙ። በጣም ስለተሸበሩም ሳሙኤልን እንዲጸልይላቸው ጠየቁት። ሳሙኤል መጸለይ ብቻ ሳይሆን መሥዋዕት ጭምር አቀረበ። ይህ ቅዱስ ሥነ ሥርዓት እየተካሄደ እያለ የፍልስጤማውያን ሠራዊት ምጽጳን ለመውጋት ወጣ። በዚህ ጊዜ ይሖዋ የሳሙኤልን ጸሎት ሰማ። ይሖዋም በፍልስጤማውያን ላይ እጅግ ከመቆጣቱ የተነሳ “ከባድ የነጐድጓድ ድምፅ [አንጐደጐደባቸው]።”—1 ሳሙ. 7:7-10
10, 11. (ሀ) ይሖዋ በፍልስጤማውያን ሠራዊት ላይ ያሰማው የነጎድጓድ ድምፅ የተለየ መሆን አለበት የምንለው ለምንድን ነው? (ለ) ምጽጳ ላይ የተጀመረው ጦርነት ምን ውጤት አስገኘ?
10 እነዚህን ፍልስጤማውያን፣ የነጐድጓድ ድምፅ ሲሰማ በጣም ከመፍራቱ የተነሳ እናቱ ሥር እንደሚሸጎጥ ትንሽ ልጅ አድርገን ልናስባቸው ይገባል? በፍጹም፣ እነዚህ ሰዎች ጦርነት ምንም የማይመስላቸው ኃይለኛ ተዋጊዎች ነበሩ። ስለዚህ ይህ የነጐድጓድ ድምፅ እነሱ ሰምተውት ከሚያውቁት ፈጽሞ የተለየ መሆን አለበት። ምናልባት ይህ የሆነው የድምፁ መጠን ኃይለኛ ስለነበረ ይሆን? ወይስ ድምፁ ጥርት ካለው ሰማይ ስለመጣ አሊያም በተራራዎቹ መሃል እንግዳ በሆነ ሁኔታ ስላስተጋባ ይሆን? ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን ድምፁ እነዚህን ፍልስጤማውያን በጣም አሸብሯቸዋል። ፈጽሞ ግራ የተጋቡት እነዚህ ፍልስጤማውያን ኃያል ተዋጊዎች መሆናቸው ቀርቶ ጭራሽ የጥቃት ዒላማ ሆኑ። እስራኤላውያን ከምጽጳ ግልብጥ ብለው በመውጣት ድል ያደረጓቸው ሲሆን ከኢየሩሳሌም በስተ ደቡብ ምዕራብ እስከሚገኝ ስፍራ ድረስ ረጅም ርቀት አሳደዷቸው።—1 ሳሙ. 7:11
11 ይህ ጦርነት አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ክንውን ነበር። ሳሙኤል ፈራጅ ሆኖ ባገለገለባቸው ከዚያ በኋላ ባሉት ዓመታት ሁሉ ፍልስጤማውያን ከእስራኤላውያን ፊት ሲሸሹ ኖረዋል። የአምላክ ሕዝቦችም ተወስደውባቸው የነበሩትን ከተሞች አንድ በአንድ አስመልሰዋል።—1 ሳሙ. 7:13, 14
12. ሳሙኤል “ጽድቅ እንዲፈጸም የሚያደርግ ተግባር” አከናውኗል ሲባል ምን ማለት ነው? ውጤታማ እንዲሆን የረዱትስ የትኞቹ ባሕርያት ናቸው?
12 ከብዙ መቶ ዓመታት በኋላ ሐዋርያው ጳውሎስ “ጽድቅ እንዲፈጸም የሚያደርግ ተግባር ፈጽመዋል” ብሎ ከጠቀሳቸው ታማኝ መሳፍንትና ነቢያት መካከል ሳሙኤልም ይገኝበታል። (ዕብ. 11:32, 33) በእርግጥም ሳሙኤል በአምላክ ፊት መልካምና ትክክል የሆነውን ነገር አድርጓል፤ ሌሎችም እንዲህ እንዲያደርጉ አበረታቷል። ሳሙኤል ውጤታማ ሊሆን የቻለው ተስፋ የሚያስቆርጡ ነገሮች ቢያጋጥሙትም ሥራውን በታማኝነት ማከናወኑን በመቀጠል ይሖዋን በትዕግሥት ስለተጠባበቀ ነው። በተጨማሪም ሳሙኤል አመስጋኝ ነበር። በምጽጳ ከተገኘው ድል በኋላ ሳሙኤል ይሖዋ ሕዝቡን ለመርዳት ሲል ለወሰደው እርምጃ መታሰቢያ እንዲሆን አንድ ሐውልት አቆመ።—1 ሳሙ. 7:12
13. (ሀ) ሳሙኤል የተወውን ምሳሌ መከተል ከፈለግን የትኞቹን ባሕርያት ማዳበር ይኖርብናል? (ለ) ሳሙኤል የነበሩትን ዓይነት ባሕርያት ለማዳበር ከሁሉ የተሻለው ጊዜ የትኛው ነው?
13 አንተስ ‘ጽድቅ እንዲፈጸም የሚያደርግ ተግባር’ ማከናወን ትፈልጋለህ? ከሆነ ሳሙኤል ካሳየው ትዕግሥትና ትሕትና እንዲሁም የአመስጋኝነት መንፈስ ትምህርት ማግኘት ይኖርብሃል። (1 ጴጥሮስ 5:6ን አንብብ።) ከመካከላችን እነዚህ ባሕርያት እንዲኖሩት የማይፈልግ ማን አለ? ሳሙኤል ልጅ ሳለ እነዚህን ባሕርያት ማዳበሩ በኋለኞቹ ዓመታት ያጋጠሙትን ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታዎች ለመቋቋም ረድቶታል።
“ልጆችህ ያንተን ፈለግ አይከተሉም”
14, 15. (ሀ) ሳሙኤል ‘ከሸመገለ’ በኋላ ምን አሳዛኝ ሁኔታ አጋጥሞታል? (ለ) ሳሙኤል ልክ እንደ ዔሊ ቸልተኛ አባት ነበር? አብራራ።
14 መጽሐፍ ቅዱስ ከዚህ በኋላ የሚተርከው ሳሙኤል ‘ከሸመገለ’ በኋላ ስላከናወነው ነገር ነው። በዚህ ጊዜ ሳሙኤል ኢዮኤል እና አብያ የተባሉ ሁለት ትላልቅ ልጆች ያደረሰ ሲሆን ፈራጆች ሆነው እንዲረዱት ኃላፊነት ሰጥቷቸው ነበር። የሚያሳዝነው ግን ልጆቹ እሱ እንደሚጠብቀው ሆነው አልተገኙም። ሳሙኤል ሐቀኛና ጻድቅ ሰው የነበረ ቢሆንም ልጆቹ ፍትሕ በማጣመምና ጉቦ በመቀበል የተሰጣቸውን ኃላፊነት የግል ጥቅማቸውን ለማሳደድ ተጠቅመውበታል።—1 ሳሙ. 8:1-3
15 አንድ ቀን የእስራኤል ሽማግሌዎች ወደ አረጋዊው ነቢይ ቀርበው “ልጆችህ ያንተን ፈለግ አይከተሉም” በማለት ምሬታቸውን ገለጹ። (1 ሳሙ. 8:4, 5) ሳሙኤል ይህን ችግር ያውቅ ነበር? ዘገባው ስለዚህ ጉዳይ ምንም የሚናገረው ነገር የለም። ይሁንና ሳሙኤል እንደ ዔሊ ቸልተኛ አባት እንዳልነበር እርግጠኞች ነን። ዔሊ ከአምላክ ይልቅ ልጆቹን በማክበሩና ለፈጸሙት ኃጢአት ተግሣጽ ሳይሰጣቸው በመቅረቱ ይሖዋ ገሥጾታል እንዲሁም ቀጥቶታል። (1 ሳሙ. 2:27-29) ይሖዋ በሳሙኤል ላይ እንዲህ ያለ ስህተት አላገኘበትም።
16. ዓመፀኛ ልጆች ያሏቸው ወላጆች ምን ስሜት ሊያሠቃያቸው ይችላል? ሳሙኤል ከተወው ምሳሌስ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ምን መጽናኛና መመሪያ ሊያገኙ ይችላሉ?
16 መጽሐፍ ቅዱስ ሳሙኤል ልጆቹ መጥፎ ተግባር እንደፈጸሙ ባወቀበት ጊዜ ስለተሰማው ከባድ ኀፍረት፣ ጭንቀት ወይም የተስፋ መቁረጥ ስሜት የሚናገረው ነገር የለም። ሆኖም በርካታ ወላጆች፣ በዚያ ጊዜ ምን ተሰምቶት ሊሆን እንደሚችል መረዳት አይከብዳቸውም። በዚህ መጥፎ ዘመን በወላጆች ሥልጣን ላይ ማመፅና እነሱ የሚሰጡትን ተግሣጽ አለመቀበል እንደወረርሽኝ ተስፋፍቶ ይገኛል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5ን አንብብ።) እንዲህ ያለው አሳዛኝ ሁኔታ ያጋጠማቸው ወላጆች ሳሙኤል ከተወው ምሳሌ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን መጽናኛና መመሪያ ማግኘት ይችላሉ። ሳሙኤል ልጆቹ የፈጸሙት ታማኝነት የጎደለው ድርጊት በጥቂቱም ቢሆን እርምጃውን እንዲያዛባበት አልፈቀደም። ወላጆች የሚሰጡት ምክርና ተግሣጽ ተቀባይነት ሳያገኝ ቢቀርም እንኳ ምንጊዜም ለልጆቻቸው ምሳሌ መሆናቸው ትልቅ ለውጥ ሊያመጣ እንደሚችል አትዘንጋ። እንዲሁም ወላጆች ልክ እንደ ሳሙኤል፣ ምንጊዜም የአባታቸውን የይሖዋ አምላክን ልብ ደስ የማሰኘት አጋጣሚ አላቸው።
“የሚመራን ንጉሥ አንግሥልን”
17. የእስራኤል ሽማግሌዎች ሳሙኤልን ምን እንዲያደርግላቸው ጠየቁት? እሱስ ምን ተሰማው?
17 የሳሙኤል ልጆች ስግብግብና ራስ ወዳድ መሆናቸው ምን ያህል መጥፎ ውጤት እንዳስከተለ ሊረዱት አይችሉም። የእስራኤል ሽማግሌዎች በመቀጠል “ሌሎች ሕዝቦች እንደሚያደርጉት ሁሉ የሚመራን ንጉሥ አንግሥልን” አሉት። ይህን ጥያቄ ያቀረቡት ከዚያ በኋላ ሳሙኤልን እንደማይፈልጉት ለማሳየት ይሆን? ያም ሆነ ይህ ሳሙኤል ይሖዋን በመወከል በሕዝቡ ላይ ለብዙ አሥርተ ዓመታት ፈራጅ ሆኖ ሲያገለግል ቆይቷል። አሁን ግን እስራኤላውያን እንደ ሳሙኤል ያለ ተራ ነቢይ ሳይሆን ንጉሥ እንዲያስተዳድራቸው ፈልገዋል። በዙሪያቸው ያሉት ብሔራት የየራሳቸው ንጉሥ ነበራቸው፤ ስለሆነም እነሱም ንጉሥ እንዲኖራቸው ፈለጉ! ታዲያ ሳሙኤል ምን ተሰማው? ዘገባው ይህ ሐሳብ ሳሙኤልን ‘እንዳላስደሰተው’ ይናገራል።—1 ሳሙ. 8:5, 6
18. ይሖዋ ሳሙኤልን ያጽናናው እንዴት ነው? የእስራኤላውያን ኃጢአት ከባድ መሆኑን ይፋ ያወጣውስ እንዴት ነው?
18 ሳሙኤል ጉዳዩን በጸሎት ለይሖዋ ባቀረበ ጊዜ ይሖዋ ምን እንደተናገረ ልብ በል፦ “ንጉሣቸው እንዳልሆን የናቁት እኔን እንጂ አንተን አይደለምና ሕዝቡ የሚሉህን ሁሉ አድምጥ።” ይህ አባባል ሳሙኤልን ምንኛ አጽናንቶት ይሆን! ይሁንና ሕዝቡ የተናገረው ይህ ሐሳብ ሁሉን ቻይ የሆነውን አምላክ እንደመሳደብ የሚቆጠር ነበር። ይሖዋ፣ እስራኤላውያን ሰብዓዊ ንጉሥ ማንገሣቸው ከፍተኛ ዋጋ እንደሚያስከፍላቸው በመንገር ሕዝቡን እንዲያስጠነቅቅ ለነቢዩ ነገረው። ሳሙኤል የይሖዋን ሐሳብ ሲነግራቸው ሕዝቡ “አይሆንም፤ ንጉሥ እንዲነግሥልን እንፈልጋለን” በማለት አሻፈረኝ አሉ። ምንጊዜም ለአምላኩ ታዛዥ የነበረው ሳሙኤል ሄዶ ይሖዋ የመረጠውን ንጉሥ ቀባው።—1 ሳሙ. 8:7-19
19, 20. (ሀ) ሳሙኤል፣ ይሖዋ ሳኦልን የእስራኤል ንጉሥ አድርጎ እንዲቀባው የሰጠውን መመሪያ የታዘዘው እንዴት ነው? (ለ) ሳሙኤል የይሖዋን ሕዝቦች መርዳቱን የቀጠለው እንዴት ነው?
19 ሆኖም ሳሙኤል የታዘዘው በምን ዓይነት መንፈስ ነበር? እንደው ቅር እያለው ከአንገት በላይ በሆነ ስሜት ነበር? የደረሰበት አሳዛኝ ሁኔታ ያሳደረበት ምሬት በውስጡ ሥር ሰዶ ልቡን እንዲመርዘው ፈቅዷል? ብዙ ሰዎች እንዲህ ያደርጉ ይሆናል፤ ሳሙኤል ግን እንዲህ አላደረገም። ሳኦልን ንጉሥ አድርጎ የቀባው ከመሆኑም ሌላ ይሖዋ የመረጠው ሰው መሆኑንም አምኖ ተቀብሏል። ሳሙኤል ሳኦልን የሳመው ሲሆን ይህም አዲሱን ንጉሥ እንደተቀበለና ለእሱ ለመገዛት ፈቃደኛ እንደሆነ የሚያሳይ ድርጊት ነበር። ከዚያም ለሕዝቡ “እግዚአብሔር የመረጠውን ሰው አያችሁን? ከሕዝቡ ሁሉ የሚስተካከለው ማንም የለም” በማለት ተናገረ።—1 ሳሙ. 10:1, 24
20 ሳሙኤል ሕዝቡ በሠራው ስህተት ላይ ሳይሆን ይሖዋ የመረጠው ሰው ባሉት መልካም ጎኖች ላይ ትኩረት አድርጓል። ከራሱ ጋር በተያያዘም ቢሆን እንደ እስስት በሚለዋወጠው ሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት ከማሰብ ይልቅ ንጹሕ አቋሙን በመጠበቅ ባስመዘገበው ታሪክ ላይ አተኩሯል። (1 ሳሙ. 12:1-4) በተጨማሪም የአምላክ ሕዝብ ወደፊት ሊያጋጥመው ስለሚችለው መንፈሳዊ አደጋ ምክር በመስጠትና ለይሖዋ ያላቸውን ታማኝነት እንዲጠብቁ በማበረታታት ኃላፊነቱን በታማኝነት ተወጥቷል። ሰዎቹም በሳሙኤል ምክር ልባቸው ስለተነካ ወደ ይሖዋ እንዲጸልይላቸው ተማጸኑት። በዚህ ጊዜ ሳሙኤል “ለእናንተ ከመጸለይ ወደ ኋላ በማለት እግዚአብሔርን መበደል ከእኔ ይራቅ፤ እኔ መልካምና ቅን የሆነውን መንገድ አስተምራችኋለሁ” የሚል ግሩም መልስ ሰጥቷቸዋል።—1 ሳሙ. 12:21-24
ሳሙኤል የተወው ምሳሌ ቅናት ወይም ምሬት በልባችን ውስጥ ሥር እንዲሰድ ፈጽሞ መፍቀድ እንደሌለብን ያስተምረናል
21. ከአንተ ይልቅ ሌላ ሰው ኃላፊነት ወይም መብት ስለተሰጠው ቅር ተሰኝተህ ከሆነ ሳሙኤል የተወው ምሳሌ ሊያበረታታህ የሚችለው እንዴት ነው?
21 ከአንተ ይልቅ ሌላ ሰው ኃላፊነት ወይም መብት ስለተሰጠው ቅር የተሰኘህበት ጊዜ አለ? ሳሙኤል የተወልን ምሳሌ ቅናት ወይም ምሬት በልባችን ውስጥ ሥር እንዲሰድ መፍቀድ እንደማይኖርብን ግሩም ማሳሰቢያ ይሆነናል። (ምሳሌ 14:30ን አንብብ።) አምላክ ለሁሉም ታማኝ አገልጋዮቹ የሚሆን የሚክስና እርካታ የሚያስገኝ ሥራ አለው።
“ለሳኦል የምታለቅስለት እስከ መቼ ነው?”
22. መጀመሪያ ላይ ሳሙኤል የሳኦልን መልካም ጎን መመልከቱ ተገቢ የነበረው ለምንድን ነው?
22 ሳሙኤል የሳኦልን መልካም ጎን መመልከቱ ተገቢ ነበር፤ ምክንያቱም ሳኦል አስደናቂ ሰው ነበር። ረጅምና ጥሩ ቁመና የነበረው ከመሆኑም ሌላ ደፋርና ብልህ ነበር፤ ደግሞም በኋላ ላይ ተለወጠ እንጂ ልኩን የሚያውቅና ልታይ ልታይ የማይል ሰው ነበር። (1 ሳሙ. 10:22, 23, 27) ሳኦል ካሉት ጥሩ ተሰጥኦዎች በተጨማሪ ሌላም ውድ ስጦታ ይኸውም የፈለገውን የሕይወት ጎዳና የመምረጥና የራሱን ውሳኔ የማድረግ ነፃ ምርጫ ነበረው። (ዘዳ. 30:19) ታዲያ ይህን ስጦታ በጥሩ ሁኔታ ተጠቅሞበታል?
23. ሳኦል መጀመሪያ ላይ ያጣው ግሩም ባሕርይ የትኛው ነው? ከዕለት ወደ ዕለት ትዕቢተኛ እየሆነ የሄደውስ እንዴት ነው?
23 የሚያሳዝነው ነገር፣ አንድ ሰው ሥልጣን አግኝቶ ከፍ ከፍ ሲል እንደ ጉም በንኖ የሚጠፋው የመጀመሪያው ባሕርይ ልክን ማወቅ ነው። ሳኦልም ብዙ ሳይቆይ መታበይ ጀመረ። በሳሙኤል በኩል የተሰጠውን የይሖዋን ትእዛዝ ለመፈጸም ፈቃደኛ ሳይሆን ቀረ። በአንድ ወቅት ሳኦል ትዕግሥት በማጣቱ የተነሳ ሳሙኤል ሊያቀርበው ያሰበውን መሥዋዕት እሱ ራሱ አቀረበ። በዚህ ጊዜ ሳሙኤል ጠንከር ያለ ተግሣጽ ለመስጠት የተገደደ ሲሆን የሳኦል ቤተሰብ ከዚያ በኋላ የንግሥና መብት እንደማይኖረው ትንቢት ተናግሯል። ሳኦል የተሰጠውን ተግሣጽ ተቀብሎ መስተካከል ሲገባው እምቢተኛ መሆኑን የሚያሳዩ የከፉ ድርጊቶችን መፈጸሙን ቀጠለ።—1 ሳሙ. 13:8, 9, 13, 14
24. (ሀ) ሳኦል ከአማሌቃውያን ጋር በተዋጋበት ወቅት ይሖዋን ሳይታዘዝ የቀረው እንዴት ነው? (ለ) ሳኦል ለተሰጠው ተግሣጽ ምን ምላሽ ሰጠ? ይሖዋስ ምን ውሳኔ አስተላለፈ?
24 በአንድ ወቅት ይሖዋ፣ ሳኦል አማሌቃውያንን እንዲወጋ በሳሙኤል አማካኝነት ነገረው። ይሖዋ የሰጠው ትእዛዝ ክፉ የሆነውን የአማሌቃውያንን ንጉሥ አጋግን መግደልን ይጨምር ነበር። ይሁን እንጂ ሳኦል፣ አጋግን ሳይገድለው የተወው ከመሆኑም በላይ መጥፋት ከሚገባቸው ነገሮች መካከል ምርጥ ምርጡን አስቀረ። ሳሙኤል ሊገሥጸው በመጣ ጊዜ ሳኦል ያደረገው ነገር ባሕርይው ፈጽሞ እንደተለወጠ የሚያሳይ ነበር። የተሰጠውን ተግሣጽ በትሕትና ከመቀበል ይልቅ ሰበብ አስባብ ለማቅረብ፣ ያደረገው ነገር ትክክል እንደሆነ ለማስመሰል፣ ጥፋቱ ያን ያህል ከባድ እንዳልሆነ ለማሳመን እንዲያውም ጥፋቱን በሕዝቡ ላይ ለማላከክ ሞከረ። ሳኦል በምርኮ የያዛቸውን አንዳንድ እንስሳት ሳያጠፋ የቀረው ለይሖዋ መሥዋዕት አድርጎ ለማቅረብ አስቦ እንደሆነ በመናገር የፈጸመው ስህተት ያን ያህል ከባድ እንዳልሆነ ለማስተባበል በሞከረ ጊዜ ሳሙኤል “እነሆ! መታዘዝ ከመሥዋዕት . . . ይበልጣል” የሚለውን በብዙዎች ዘንድ የሚታወቀውን ሐሳብ ተናገረ። ሳሙኤል ሳኦልን በድፍረት ከገሠጸው በኋላ ይሖዋ ያሳለፈውን ውሳኔ ይኸውም ንጉሣዊ አገዛዙ ከሳኦል እንደተቀደደና ከእሱ ለተሻለ ሰው እንደተሰጠ ነገረው።a—1 ሳሙ. 15:1-33
25, 26. (ሀ) ሳሙኤል ለሳኦል ያለቀሰው ለምንድን ነው? ይሖዋ ነቢዩን ደግነት በሚንጸባረቅበት ሁኔታ የገሠጸው እንዴት ነው? (ለ) ሳሙኤል ወደ እሴይ ቤት በሄደበት ወቅት ምን ትምህርት አገኘ?
25 ሳሙኤል፣ ሳኦል በፈጸማቸው ስህተቶች በጣም ተበሳጭቶ ነበር። ጉዳዩ ስላሳሰበው ሌሊቱን ሙሉ ወደ ይሖዋ ሲጮኽ አደረ። ለሳኦልም ጭምር አለቀሰለት። ሳሙኤል፣ ሳኦል ብዙ ጥሩ ነገሮችን ሊያከናውን እንደሚችል ተሰምቶት ነበር፤ አሁን ግን በእሱ ላይ የነበረው ተስፋ ሁሉ በንኖ ጠፍቷል። ከዚህ በፊት የሚያውቀው ሰው ሊሆንለት አልቻለም፤ እነዚያ ሁሉ ግሩም ባሕርያቱ ጠፍተው አሁን የይሖዋ ጠላት ሆኗል። በዚህ ምክንያት ሳሙኤል ከዚያ በኋላ ሳኦልን ለማየት ፈቃደኛ አልሆነም። ከጊዜ በኋላ ይሖዋ ደግነት በሚንጸባረቅበት ሁኔታ ለሳሙኤል እንዲህ የሚል ተግሣጽ ሰጠው፦ “በእስራኤል ላይ እንዳይነግሥ ለናቅሁት ለሳኦል የምታለቅስለት እስከ መቼ ነው? ወደ ቤተ ልሔሙ ሰው ወደ እሴይ ስለምልክህ፣ ዘይት በቀንድ ሞልተህ ሂድ፤ ከልጆቹ አንዱ ንጉሥ ይሆን ዘንድ መርጬዋለሁ።”—1 ሳሙ. 15:34, 35፤ 16:1
26 የይሖዋ ዓላማ፣ ፍጻሜ ማግኘቱ የተመካው የሚዋዥቅ አቋም ባላቸው ፍጽምና የጎደላቸው ሰዎች ታማኝነት ላይ አይደለም። አንድ ሰው ታማኝነቱን ካጓደለ ይሖዋ ፈቃዱን ለማስፈጸም ሌላ ሰው ይጠቀማል። በመሆኑም አረጋዊው ሳሙኤል በሳኦል ምክንያት ማዘን የለበትም። ስለዚህ ሳሙኤል ይሖዋ በሰጠው መመሪያ መሠረት በቤተልሔም ወደሚገኘው ወደ እሴይ ቤት ሄደ፤ እዚያም ግርማ ሞገስ ያላቸውን የእሴይን ወንዶች ልጆች አገኘ። ሆኖም ይሖዋ ገና ከጅምሩ ለሳሙኤል ውጫዊ ገጽታን ብቻ እንዳያይ ማሳሰቢያ ሰጠው። (1 ሳሙኤል 16:7ን አንብብ።) በመጨረሻም ሳሙኤል የሁሉም ታናሽ የሆነውን የእሴይን ልጅ አስጠራ፤ ይህ ልጅ በይሖዋ የተመረጠው ዳዊት ነበር!
ሳሙኤል፣ ይሖዋ ሊያስተካክለው፣ መፍትሔ ሊያገኝለት ወይም ወደ በረከት ሊለውጠው የማይችል ምንም ዓይነት ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ እንደሌለ ተገንዝቧል
27. (ሀ) ሳሙኤል እምነቱ ይበልጥ እየጠነከረ እንዲሄድ የረዳው ምንድን ነው? (ለ) ሳሙኤል የተወውን ምሳሌ መመርመርህ ምን ስሜት አሳድሮብሃል?
27 ሳሙኤል በሕይወቱ የመጨረሻ ዓመታት፣ ይሖዋ በሳኦል ፋንታ ዳዊትን መተካቱ በእርግጥ ትክክለኛ ውሳኔ እንደነበር ይበልጥ ማስተዋል ችሏል። ውሎ አድሮ ሳኦል ቀናተኛ፣ ነፍሰ ገዳይና ከሃዲ ሆነ። ዳዊት ግን እንደ ድፍረት፣ እምነትና ታማኝነት ያሉ ግሩም ባሕርያት የነበሩት ሲሆን ንጹሕ አቋሙንም የሚጠብቅ ሰው ነበር። ሳሙኤል በሕይወቱ መገባደጃ ላይ እምነቱ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ጠንካራ ሆኖ ነበር። ሳሙኤል፣ ይሖዋ ሊያስተካክለው፣ መፍትሔ ሊያገኝለት ወይም ወደ በረከት ሊለውጠው የማይችል ምንም ዓይነት ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ እንደሌለ ተገንዝቧል። በመጨረሻም ሳሙኤል ወደ አንድ ክፍለ ዘመን በሚጠጋ ዕድሜው አስደናቂ የሕይወት ታሪክ አስመዝግቦ አለፈ። እስራኤላውያን በሙሉ ይህን ታማኝ ሰው በሞት ሲያጡ በእጅጉ ማዘናቸው ምንም አያስደንቅም! በአሁኑ ጊዜ ያሉ የይሖዋ አገልጋዮች ‘ሳሙኤል እምነት በማሳየት ረገድ የተወውን ምሳሌ እየተከተልኩ ነው?’ ብለው ራሳቸውን መጠየቃቸው ተገቢ ነው።
a ሳሙኤል ራሱ አጋግን ገደለው። ይህ ክፉ ንጉሥም ሆነ ቤተሰቡ ምሕረት የሚገባቸው አልነበሩም። ከበርካታ መቶ ዓመታት በኋላ ይኖር የነበረውና የአምላክን ሕዝቦች ጠራርጎ ለማጥፋት የሞከረው “አጋጋዊው ሐማ” ከአጋግ ዘሮች መካከል አንዱ እንደነበር ከሁኔታው መረዳት ይቻላል።—አስቴር 8:3፤ የዚህን መጽሐፍ ምዕራፍ 15 እና 16ን ተመልከት።