ምዕራፍ ዘጠኝ
የዓለም መጨረሻ ቀርቧል?
1. ስለወደፊቱ ጊዜ ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው?
ዜና ስታዳምጥ፣ ‘አሁንስ ጊዜው በጣም ከፋ’ ብለህ አስበህ ታውቃለህ? በዓለማችን ላይ ጭካኔ የተሞላባቸው በርካታ አሳዛኝ ድርጊቶች ስለሚፈጸሙ አንዳንድ ሰዎች የዓለም መጨረሻ እንደቀረበ ይሰማቸዋል። በእርግጥ መጨረሻው ቀርቧል? ወደፊት ስለሚሆነው ነገር ማወቅ የምንችልበት መንገድ አለ? አዎ፣ አለ። የሰው ልጆች ወደፊት የሚሆነውን ነገር ማወቅ አይችሉም፤ ይሖዋ ግን ይችላል። ይሖዋ፣ የሰው ልጆችም ሆኑ ምድር ወደፊት ምን እንደሚጠብቃቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ገልጾልናል።—ኢሳይያስ 46:10፤ ያዕቆብ 4:14
2, 3. የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ምን ማወቅ ፈልገው ነበር? ኢየሱስ ምን መልስ ሰጣቸው?
2 መጽሐፍ ቅዱስ የዓለም መጨረሻ ሲል ምድር የምትጠፋበትን ጊዜ ሳይሆን ክፋት የሚያበቃበትን ጊዜ ማመልከቱ ነው። ኢየሱስ፣ የአምላክ መንግሥት ምድርን እንደሚገዛ አስተምሯል። (ሉቃስ 4:43) ደቀ መዛሙርቱ የአምላክ መንግሥት የሚመጣው መቼ እንደሆነ ማወቅ ፈልገው ነበር፤ በመሆኑም ኢየሱስን “እነዚህ ነገሮች የሚፈጸሙት መቼ ነው? የመገኘትህና የዚህ ሥርዓት መደምደሚያ ምልክትስ ምንድን ነው?” ሲሉ ጠይቀውት ነበር። (ማቴዎስ 24:3) ኢየሱስ የመጨረሻውን ቀን ለይቶ ባይነግራቸውም የዓለም መጨረሻ ሲቃረብ የሚከናወኑትን ነገሮች ነግሯቸዋል። ኢየሱስ የተናገራቸው ነገሮች አሁን እየተፈጸሙ ነው።
3 በዚህ ምዕራፍ ላይ፣ አሁን ያለነው የዓለም መጨረሻ በቀረበበት ዘመን ላይ እንደሆነ የሚያሳዩ ማስረጃዎችን እንመረምራለን። በመጀመሪያ፣ በምድር ላይ ያለው ሁኔታ ይህን ያህል አስከፊ የሆነበትን ምክንያት መረዳት እንድንችል በሰማይ ስለተደረገ አንድ ጦርነት የሚገልጸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ እንመልከት።
በሰማይ የተደረገ ጦርነት
4, 5. (ሀ) ኢየሱስ ንጉሥ ሆኖ እንደተሾመ በሰማይ ምን ተከናውኗል? (ለ) በራእይ 12:12 ላይ በተገለጸው መሠረት ሰይጣን መወርወሩ በምድር ላይ ምን አስከትሏል?
4 በምዕራፍ 8 ላይ፣ ኢየሱስ በ1914 በሰማይ ንጉሥ ሆኖ እንደተሾመ ተመልክተናል። (ዳንኤል 7:13, 14) የራእይ መጽሐፍ የተከናወነውን ነገር እንዲህ በማለት ይገልጻል፦ “በሰማይም ጦርነት ተነሳ፦ ሚካኤልና [ማለትም ኢየሱስና] መላእክቱ ከዘንዶው [ከሰይጣን] ጋር ተዋጉ፤ ዘንዶውና መላእክቱም ተዋጓቸው።”a ሰይጣንና አጋንንቱ በጦርነቱ ስለተሸነፉ ወደ ምድር ተወረወሩ። በዚህ ወቅት መላእክት ምን ያህል ተደስተው ሊሆን እንደሚችል አስበው! ይሁንና ይህ በምድር ላይ ምን አስከተለ? መጽሐፍ ቅዱስ፣ ሰይጣን ወደ ምድር መወርወሩ በሰዎች ላይ መከራ እንደሚያስከትል ተናግሯል። ለምን? ምክንያቱም “ዲያብሎስ ጥቂት ጊዜ እንደቀረው ስላወቀ” በጣም ተቆጥቷል።—ራእይ 12:7, 9, 12
5 ዲያብሎስ በምድር ላይ ብዙ መከራ እያደረሰ ነው። አምላክ በቅርቡ እንደሚያስወግደው ስለሚያውቅ ዲያብሎስ በጣም ተቆጥቷል። ኢየሱስ በመጨረሻዎቹ ቀናት ስለሚከናወኑት ነገሮች የተናገረውን እስቲ እንመልከት።—ተጨማሪ ሐሳብ 24ን ተመልከት።
የመጨረሻዎቹ ቀናት
6, 7. ኢየሱስ ስለ ጦርነትና ስለ ረሃብ የተናገረው ትንቢት በዛሬው ጊዜ እየተፈጸመ ያለው እንዴት ነው?
6 ጦርነት። ኢየሱስ “ሕዝብ በሕዝብ ላይ፣ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሳል” በማለት ተናግሯል። (ማቴዎስ 24:7) ከየትኛውም ዘመን ይበልጥ በርካታ ሰዎች በጦርነት የተገደሉት በአሁኑ ዘመን ነው። በዓለም ላይ የሚከናወኑትን ነገሮች የሚያጠና አንድ ድርጅት ያቀረበው ሪፖርት እንደሚያሳየው ከ1914 ወዲህ ከ100 ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎች በጦርነት ሞተዋል። ከ1900 እስከ 2000 ባሉት 100 ዓመታት በጦርነት የተገደሉት ሰዎች ቁጥር፣ ከ1900 ዓ.ም. በፊት ከተገደሉት ሰዎች ቁጥር በሦስት እጥፍ ይበልጣል። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በጦርነት ምክንያት ምን ያህል ሥቃይና መከራ እንደደረሰባቸው አስበው!
7 ረሃብ። ኢየሱስ “የምግብ እጥረት . . . ይከሰታል” በማለት ተናግሯል። (ማቴዎስ 24:7) በዘመናችን ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ብዙ እህል እየተመረተ ቢሆንም ብዙ ሰዎች በቂ ምግብ አያገኙም። ለምን? ምግብ ለመግዛትም ሆነ እህል የሚዘሩበት መሬት ለመግዛት የሚያስችል በቂ ገንዘብ ስለሌላቸው ነው። ከአንድ ቢሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች የዕለት ገቢያቸው በጣም አነስተኛ ነው። የዓለም የጤና ድርጅት እንደገለጸው በየዓመቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ልጆች የተመጣጠነ ምግብ ባለማግኘታቸው የተነሳ ይሞታሉ።
8, 9. ኢየሱስ ስለ ምድር ነውጥና በሽታ የተናገረው ትንቢት እየተፈጸመ ያለው እንዴት ነው?
8 የምድር ነውጥ። ኢየሱስ “ታላላቅ የምድር ነውጦች ይከሰታሉ” በማለት አስቀድሞ ተናግሯል። (ሉቃስ 21:11) በአሁኑ ጊዜ በየዓመቱ ኃይለኛ የምድር ነውጦች እንደሚከሰቱ ይታመናል። ከ1900 ዓ.ም. ወዲህ ከሁለት ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎች በምድር ነውጥ የተነሳ ሞተዋል። በአሁኑ ጊዜ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመጠቀም የምድር ነውጥ እንደሚከሰት አስቀድሞ ማወቅ የተቻለ ቢሆንም አሁንም ብዙ ሰዎች በምድር ነውጥ የተነሳ እየሞቱ ነው።
9 በሽታ። ኢየሱስ “ቸነፈር” እንደሚኖር አስቀድሞ ተናግሯል። አደገኛ የሆኑ በሽታዎች በፍጥነት የሚሰራጩ ሲሆን ብዙ ሰዎችን ይገድላሉ። (ሉቃስ 21:11) ሐኪሞች ብዙ በሽታዎችን ማከም የቻሉ ቢሆንም እስካሁን መድኃኒት ያልተገኘላቸው በሽታዎች አሉ። እንዲያውም አንድ ሪፖርት እንደገለጸው በየዓመቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች እንደ ሳንባ ነቀርሳ፣ ወባና ኮሌራ ባሉ በሽታዎች የተነሳ ይሞታሉ። በተጨማሪም ባለፉት 40 ዓመታት ሐኪሞች 30 አዳዲስ በሽታዎችን ያገኙ ሲሆን አንዳንዶቹ መድኃኒት የሌላቸው ናቸው።
በመጨረሻዎቹ ቀናት የሚኖሩ ሰዎች የሚያሳዩት ባሕርይ
10. በ2 ጢሞቴዎስ 3:1-5 ላይ የሚገኘው ትንቢት በዛሬው ጊዜ እየተፈጸመ ያለው እንዴት ነው?
10 መጽሐፍ ቅዱስ በ2 ጢሞቴዎስ 3:1-5 ላይ “በመጨረሻዎቹ ቀናት ለመቋቋም የሚያስቸግር በዓይነቱ ልዩ የሆነ ዘመን እንደሚመጣ” ይናገራል። ሐዋርያው ጳውሎስ በመጨረሻዎቹ ቀናት ብዙ ሰዎች የሚከተሉትን ባሕርያት እንደሚያሳዩ ገልጿል፦
ራሳቸውን የሚወዱ
ገንዘብ የሚወዱ
ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ
ታማኝ ያልሆኑ
ለቤተሰባቸው ፍቅር የሌላቸው
ራሳቸውን የማይገዙ
ዓመፀኞችና ጠበኞች
ከአምላክ ይልቅ ሥጋዊ ደስታን የሚወዱ
አምላክን የሚወዱ ይመስላሉ፤ እሱን ለመታዘዝ ግን ፈቃደኞች አይደሉም
11. በመዝሙር 92:7 ላይ እንደተገለጸው ክፉዎች ምን ይደርስባቸዋል?
11 አንተ በምትኖርበት አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች እንዲህ ያለ ባሕርይ ያሳያሉ? በዓለም ዙሪያ የሚኖሩ ብዙ ሰዎች እንዲህ ዓይነት ባሕርይ አላቸው። ይሁንና አምላክ በቅርቡ እርምጃ ይወስዳል። አምላክ እንዲህ ሲል ቃል ገብቷል፦ “ክፉዎች እንደ አረም ቢበቅሉ፣ ክፉ አድራጊዎች ሁሉ ቢያብቡ እንኳ፣ ለዘላለም መጥፋታቸው የማይቀር ነው።”—መዝሙር 92:7
በመጨረሻዎቹ ቀናት እየተከናወኑ ያሉ መልካም ነገሮች
12, 13. ይሖዋ በመጨረሻዎቹ ቀናት ምን አስተምሮናል?
12 መጽሐፍ ቅዱስ፣ በመጨረሻዎቹ ቀናት በዓለም ላይ ሥቃይና መከራ እንደሚበዛ ትንቢት ተናግሯል። ይሁን እንጂ በመጨረሻዎቹ ቀናት የሚከናወኑ መልካም ነገሮች እንዳሉም ይናገራል።
13 መጽሐፍ ቅዱስን መረዳት። ነቢዩ ዳንኤል ስለ መጨረሻዎቹ ቀናት ሲጽፍ ‘እውነተኛው እውቀት ይበዛል’ ብሏል። (ዳንኤል 12:4) ይሖዋ በተለይ ከ1914 ወዲህ አገልጋዮቹ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ መጽሐፍ ቅዱስን መረዳት እንዲችሉ የማስተዋል ችሎታ ሰጥቷቸዋል። ለምሳሌ ስለ ስሙ፣ ለምድር ስላለው ዓላማና ስለ ቤዛው አስተምሮናል፤ በተጨማሪም ስንሞት ምን እንደምንሆን እንዲሁም ስለ ትንሣኤ ተምረናል። ችግሮቻችንን ሊፈታልን የሚችለው የአምላክ መንግሥት ብቻ እንደሆነም ተገንዝበናል። ከዚህም ሌላ ደስተኛ መሆን እንዲሁም አምላክን በሚያስደስት መንገድ መኖር የምንችለው እንዴት እንደሆነ ተምረናል። ታዲያ የአምላክ አገልጋዮች ይህን እውቀት ማግኘታቸው ምን እንዲያደርጉ ያነሳሳቸዋል? ሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ለዚህ ጥያቄ መልስ ይሰጠናል።—ተጨማሪ ሐሳብ 21 እና 25ን ተመልከት።
14. የመንግሥቱ ምሥራች በስፋት እየተሰበከ እንዳለ የሚያሳየው ምንድን ነው? ይህን ምሥራች የሚሰብኩትስ እነማን ናቸው?
14 ዓለም አቀፉ የስብከት ሥራ። ኢየሱስ ስለ መጨረሻዎቹ ቀናት ሲናገር “ይህ የመንግሥቱ ምሥራች . . . በመላው ምድር ይሰበካል” ብሏል። (ማቴዎስ 24:3, 14) ስለ አምላክ መንግሥት የሚገልጸው ምሥራች ከ230 በሚበልጡ አገሮች፣ ከ700 በላይ በሚሆኑ ቋንቋዎች እየተሰበከ ነው። ‘ከሁሉም ብሔራትና ነገዶች የተውጣጡ’ የይሖዋ ምሥክሮች በዓለም ዙሪያ ይሰብካሉ፤ ስለ አምላክ መንግሥት ምንነት እንዲሁም ይህ መንግሥት ለሰው ልጆች ስለሚያመጣው በረከት ለሰዎች ይናገራሉ። (ራእይ 7:9) ይህን የሚያደርጉት ደግሞ ያለምንም ክፍያ ነው። ኢየሱስ አስቀድሞ እንደተናገረው ብዙዎች የሚጠሏቸውና ስደት የሚያደርሱባቸው ቢሆንም ይህን ሥራ ሊያስቆም የሚችል ምንም ነገር የለም።—ሉቃስ 21:17
ምን ማድረግ ይኖርብሃል?
15. (ሀ) የምንኖረው በመጨረሻዎቹ ቀናት ውስጥ እንደሆነ ታምናለህ? እንዲህ ብለህ እንድታምን ያደረገህስ ምንድን ነው? (ለ) ይሖዋን የሚታዘዙ ሰዎች ምን በረከት ያገኛሉ? የማይታዘዙ ሰዎችስ ምን ይደርስባቸዋል?
15 የምንኖረው በመጨረሻዎቹ ቀናት ውስጥ እንደሆነ ታምናለህ? ስለ መጨረሻዎቹ ቀናት የሚናገሩት በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች እየተፈጸሙ ነው። በቅርቡ ይሖዋ የስብከቱ ሥራ እንዲቆም ያደርጋል፤ ከዚያም “መጨረሻው” ይመጣል። (ማቴዎስ 24:14) መጨረሻው የተባለው ምንድን ነው? የአርማጌዶን ጦርነት ነው፤ ያን ጊዜ አምላክ ክፋትን ሁሉ ከምድር ላይ ያስወግዳል። ይሖዋ፣ እሱንም ሆነ ልጁን ለመታዘዝ ፈቃደኛ ያልሆኑትን ሁሉ በኢየሱስና በኃያላን መላእክቱ አማካኝነት ያጠፋቸዋል። (2 ተሰሎንቄ 1:6-9) ከዚያ በኋላ ሰይጣንና አጋንንቱ ዳግመኛ ሰዎችን አያስቱም። በተጨማሪም አምላክን የሚታዘዙና የእሱን መንግሥት የሚደግፉ ሰዎች በሙሉ አምላክ ቃል የገባቸው ተስፋዎች አንድ በአንድ ሲፈጸሙ ይመለከታሉ።—ራእይ 20:1-3፤ 21:3-5
16. መጨረሻው በጣም እንደቀረበ ማወቅህ ምን እንድታደርግ ሊያነሳሳህ ይገባል?
16 ሰይጣን የሚገዛው ይህ ዓለም በቅርቡ ይጠፋል። በመሆኑም ‘ምን ማድረግ ይኖርብኛል?’ ብለን ራሳችንን መጠየቃችን በጣም አስፈላጊ ነው። ይሖዋ፣ መጽሐፍ ቅዱስን ለመማር የተቻለህን ሁሉ ጥረት እንድታደርግ ይፈልጋል። መጽሐፍ ቅዱስን በቁም ነገር ማጥናት ይኖርብሃል። (ዮሐንስ 17:3) የይሖዋ ምሥክሮች፣ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን እንዲማሩ ለመርዳት በየሳምንቱ ስብሰባ ያደርጋሉ። በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ አዘውትረህ ለመገኘት ጥረት አድርግ። (ዕብራውያን 10:24, 25ን አንብብ።) በሕይወትህ ውስጥ አንዳንድ ለውጦች ማድረግ እንዳለብህ ከተሰማህ ወዲያውኑ እርምጃ ውሰድ። እንዲህ ካደረግህ ከይሖዋ ጋር ያለህ ወዳጅነት እየጠነከረ ይሄዳል።—ያዕቆብ 4:8
17. አብዛኞቹ ሰዎች ጥፋቱ ድንገተኛ የሚሆንባቸው ለምንድን ነው?
17 ሐዋርያው ጳውሎስ በክፉዎች ላይ የሚደርሰው ጥፋት የሚመጣው “ሌባ በሌሊት በሚመጣበት መንገድ” እንደሆነ ገልጿል፤ ይህም ጥፋቱ አብዛኞቹ ሰዎች ባልጠበቁት ወቅት እንደሚመጣ ያሳያል። (1 ተሰሎንቄ 5:2) ኢየሱስ፣ ብዙዎች በመጨረሻዎቹ ቀናት ውስጥ እንደምንኖር የሚያሳየውን ማስረጃ ችላ እንደሚሉ አስቀድሞ ተናግሯል። እንዲህ ብሏል፦ “በኖኅ ዘመን እንደነበረው ሁሉ የሰው ልጅ መገኘትም [ወይም የመጨረሻዎቹ ቀናትም] እንደዚሁ ይሆናል። ከጥፋት ውኃ በፊት በነበረው ዘመን ኖኅ ወደ መርከቡ እስከገባበት ቀን ድረስ ሰዎች ይበሉና ይጠጡ እንዲሁም ወንዶች ያገቡ፣ ሴቶችም ይዳሩ ነበር፤ የጥፋት ውኃ መጥቶ ሁሉንም ጠራርጎ እስከወሰዳቸው ጊዜ ድረስ ምንም አላስተዋሉም፤ የሰው ልጅ መገኘትም እንደዚሁ ይሆናል።”—ማቴዎስ 24:37-39
18. ኢየሱስ ምን ማስጠንቀቂያ ሰጥቶናል?
18 ኢየሱስ “ከልክ በላይ በመብላትና በመጠጣት እንዲሁም ስለ ኑሮ በመጨነቅ” ትኩረታችን እንዳይከፋፈል ማስጠንቀቂያ ሰጥቶናል። መጨረሻው ድንገት “እንደ ወጥመድ” እንደሚመጣ ተናግሯል። በተጨማሪም ጥፋቱ “በመላው ምድር በሚኖሩ ሁሉ ላይ” እንደሚደርስባቸው ገልጿል። ቀጥሎም “መፈጸማቸው ከማይቀረው ከእነዚህ ሁሉ ነገሮች ማምለጥና በሰው ልጅ ፊት መቆም እንድትችሉ ሁልጊዜ ምልጃ እያቀረባችሁ [ወይም አጥብቃችሁ በመጸለይ] ዘወትር ነቅታችሁ ጠብቁ” ብሏል። (ሉቃስ 21:34-36) ኢየሱስ የሰጠውን ማስጠንቀቂያ መስማት በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? የሰይጣን ክፉ ዓለም በቅርቡ ስለሚጠፋ ነው። ከሚመጣው ጥፋት መትረፍና በአዲሱ ዓለም ውስጥ ለዘላለም መኖር የሚችሉት በይሖዋና በኢየሱስ ፊት ጥሩ ስም ያተረፉ ሰዎች ብቻ ናቸው።—ዮሐንስ 3:16፤ 2 ጴጥሮስ 3:13
a ሚካኤል የኢየሱስ ክርስቶስ ሌላ መጠሪያ ነው። ስለዚህ ርዕሰ ጉዳይ ይበልጥ ለማወቅ ተጨማሪ ሐሳብ 23ን ልትመለከት ትችላለህ።