ምዕራፍ 18
“ታላቅ ቁጣዬ ይነድዳል”
ፍሬ ሐሳብ፦ ጎግ የሚሰነዝረው ጥቃት ይሖዋን ያስቆጣዋል፤ ይሖዋ በአርማጌዶን ጦርነት ወቅት ሕዝቡን ይታደጋል
1-3. (ሀ) የይሖዋ “ታላቅ ቁጣ” ምን ያስከትላል? (ለ) በዚህ ምዕራፍ ውስጥ ምን እንመለከታለን?
ወንዶች፣ ሴቶችና ልጆች በአንድነት ቆመው መዝሙር እየዘመሩ ነው። ከዚያም አንድ ሽማግሌ ይሖዋ ጥበቃ እንዲያደርግላቸው በመለመን ልባዊ ጸሎት አቀረበ። የጉባኤው ወንድሞችና እህቶች በሙሉ ይሖዋ አስፈላጊውን እንክብካቤ እንደሚያደርግላቸው እርግጠኛ ናቸው፤ ያም ቢሆን ማጽናኛና ማበረታቻ ያስፈልጋቸዋል። ከውጭ የጦርነት ሁካታ ይሰማል። አርማጌዶን ጀምሯል!—ራእይ 16:14, 16
2 በአርማጌዶን ጦርነት ወቅት ይሖዋ ‘በታላቅ ቁጣ’ ተነስቶ ሰዎችን ያጠፋል። (ሕዝቅኤል 38:18ን አንብብ።) ቁጣው የሚነደው በአንድ ሠራዊት ወይም በአንድ አገር ላይ ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም በሚኖሩ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሰዎች ላይ ነው። በዚያ ቀን “ይሖዋ የገደላቸው ከምድር ዳር እስከ ምድር ዳር ድረስ ይሆናሉ።”—ኤር. 25:29, 33
3 “መሐሪና ሩኅሩኅ፣ . . . ለቁጣ የዘገየ” ተብሎ የተገለጸውና የፍቅር አምላክ የሆነው ይሖዋ ‘በታላቅ ቁጣ’ ተነስቶ እርምጃ እንዲወስድ የሚያደርገው ነገር ምንድን ነው? (ዘፀ. 34:6፤ 1 ዮሐ. 4:16) የዚህን ጥያቄ መልስ ማወቃችን ማጽናኛ የሚሰጠን፣ በድፍረት እንድንሞላ የሚያደርገንና በአሁኑ ጊዜ ለምናከናውነው የስብከት ሥራ ብርታት የሚሆነን እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።
የይሖዋን “ታላቅ ቁጣ” የሚያነሳሳው ምንድን ነው?
4, 5. የአምላክ ቁጣ ፍጹማን ካልሆኑ ሰዎች ቁጣ የሚለየው በምን መንገድ ነው?
4 በመጀመሪያ የይሖዋ ቁጣ ፍጹማን ካልሆኑ ሰዎች ቁጣ የተለየ መሆኑን መገንዘብ ይኖርብናል። ሰዎች በቁጣ ገንፍለው እርምጃ ሲወስዱ አብዛኛውን ጊዜ ሁኔታው ከቁጥጥር ውጭ ይሆናል፤ ውጤቱም ያማረ አይሆንም። ለምሳሌ የአዳም የበኩር ልጅ የሆነው ቃየን፣ ይሖዋ እሱ ያቀረበውን መሥዋዕት ሳይቀበል የአቤልን በመቀበሉ ‘በጣም ተናዶ’ ነበር። ውጤቱስ ምን ሆነ? ጻድቅ የሆነውን ወንድሙን አቤልን ገደለው። (ዘፍ. 4:3-8፤ ዕብ. 11:4) ይሖዋ “እንደ ልቤ የሆነ” ብሎ የተናገረለት ዳዊት ያጋጠመውን ነገርም እንመልከት። (ሥራ 13:22) ጥሩ ሰው የነበረው ዳዊትም እንኳ ናባል የተባለው ባለጸጋ ሰው እሱንና ከእሱ ጋር የነበሩትን ሰዎች እንደተሳደበ ሲሰማ ከባድ ጥፋት ሊሠራ ተቃርቦ ነበር። ዳዊትና ወታደሮቹ በቁጣ ገንፍለው ውለታ ቢስ የሆነውን ናባልን ብቻ ሳይሆን በቤቱ ውስጥ ያሉትን ወንዶች በሙሉ ለመግደል “ሰይፋቸውን ታጠቁ።” ደስ የሚለው ግን፣ የናባል ሚስት የሆነችው አቢጋኤል ዳዊትንና ወታደሮቹን በማግባባት የበቀል እርምጃ እንዳይወስዱ ልታስቆማቸው ችላለች። (1 ሳሙ. 25:9-14, 32, 33) ይሖዋ ያዕቆብን በመንፈሱ በመምራት “የሰው ቁጣ የአምላክ ጽድቅ እንዲፈጸም አያደርግም” ብሎ እንዲጽፍ ማድረጉ በእርግጥም ተገቢ ነው።—ያዕ. 1:20
ይሖዋ ምንጊዜም ቁጣውን መቆጣጠር የሚችል ሲሆን የሚያስቆጣው ነገር ምን እንደሆነም በግልጽ ይታወቃል
5 ከሰዎች በተለየ መልኩ ይሖዋ ምንጊዜም ቁጣውን መቆጣጠር የሚችል ሲሆን የሚያስቆጣው ነገር ምን እንደሆነም በግልጽ ይታወቃል። ይሖዋ በታላቅ ቁጣ በሚነሳበት ጊዜም እንኳ የሚወስደው እርምጃ የጽድቅ እርምጃ ነው። ከጠላት ጋር በሚዋጋበት ጊዜ ፈጽሞ “ጻድቁን ከኃጢአተኛው ጋር” አያጠፋም። (ዘፍ. 18:22-25) በተጨማሪም ይሖዋ ምንጊዜም የሚቆጣው የጽድቅ ቁጣ ነው። የጽድቅ ቁጣውን የሚያነሳሱትን ሁለት ምክንያቶች እንዲሁም ከዚህ የምናገኘውን ትምህርት እስቲ እንመልከት።
6. ይሖዋ ስሙ ሲረክስ ምን ይሰማዋል?
6 ምክንያት፦ ይሖዋ ስሙ ሲረክስ ቁጣው ይነሳሳል። ይሖዋን እንወክላለን እያሉ የክፋት ድርጊት የሚፈጽሙ ሰዎች ስሙን ያሰድባሉ፤ ይህ ደግሞ ይሖዋን ያስቆጣዋል። (ሕዝ. 36:23) ቀደም ባሉት ምዕራፎች ላይ እንደተመለከትነው የእስራኤል ብሔር የይሖዋን ስም በእጅጉ አሰድቦ ነበር። ይሖዋ በእስራኤላውያን ዝንባሌና ድርጊት መቆጣቱ አያስገርምም። ሆኖም ምንጊዜም ቁጣውን ይቆጣጠር ነበር፤ ሕዝቡን በተገቢው መጠን እንጂ ከተገቢው መጠን በላይ ቀጥቷቸው አያውቅም። (ኤር. 30:11) ይሖዋ ተቆጥቶ እርምጃ ከወሰደ በኋላ ደግሞ ፈጽሞ ቂም አይዝም።—መዝ. 103:9
7, 8. ይሖዋ ከእስራኤላውያን ጋር ከነበረው ግንኙነት ምን ትምህርት እናገኛለን?
7 የምናገኘው ትምህርት፦ ይሖዋ ከእስራኤላውያን ጋር የነበረው ግንኙነት ትልቅ የማስጠንቀቂያ ትምህርት ይዟል። እንደ እስራኤላውያን ሁሉ እኛም በይሖዋ ስም የመጠራት መብት አግኝተናል። የይሖዋ ምሥክሮች ነን። (ኢሳ. 43:10) ንግግራችንም ሆነ ድርጊታችን የምናመልከውን አምላክ ሊያስመሰግን ወይም ሊያሰድብ ይችላል። ያለአንዳች ኀፍረት ክፉ ድርጊት በመፈጸም በይሖዋ ስም ላይ ነቀፌታ ማምጣት በፍጹም አንፈልግም። እንዲህ ያለው አካሄድ የይሖዋን ቁጣ ይቀሰቅሰዋል፤ እንዲሁም ይዋል ይደር እንጂ ስሙን ለማስከበር እርምጃ ይወስዳል።—ዕብ. 3:13, 15፤ 2 ጴጥ. 2:1, 2
8 ይሖዋ “ታላቅ ቁጣ” ሊቆጣ እንደሚችል ማወቃችን ወደ እሱ እንዳንቀርብ ሊያግደን ይገባል? በፍጹም። ይሖዋ ታጋሽና ይቅር ባይ እንደሆነ እናውቃለን። (ኢሳ. 55:7፤ ሮም 2:4) ይሁን እንጂ አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ተገቢውን ተግሣጽ እንደሚሰጥም እንገነዘባለን። እንዲያውም ሆን ብለው በኃጢአት ጎዳና በሚመላለሱ ሰዎች ላይ ቁጣው እንደሚነድና እነዚህ ሰዎች በሕዝቦቹ መካከል ሆነው እንዲቀጥሉ እንደማይፈቅድ ማወቃችን ለእሱ ጤናማ የሆነ ፍርሃት እንዲያድርብን ያደርጋል። (1 ቆሮ. 5:11-13) ይሖዋ፣ የሚያስቆጡት ነገሮች ምን እንደሆኑ በግልጽ ነግሮናል። ስለዚህ እሱን የሚያስቆጡትን ዝንባሌዎችና ድርጊቶች ማስወገድ የእኛ ፋንታ ነው።—ዮሐ. 3:36፤ ሮም 1:26-32፤ ያዕ. 4:8
9, 10. ይሖዋ ታማኝ ሕዝቦቹ ለአደጋ ሲጋለጡ ምን ያደርጋል? ምሳሌ ስጥ።
9 ምክንያት፦ ይሖዋ ታማኝ ሕዝቦቹ ለአደጋ ሲጋለጡ ቁጣው ይነሳሳል። ይሖዋ በእሱ ጥበቃ ሥር መኖር በሚፈልጉ ታማኝ ሕዝቦቹ ላይ ጥቃት ሲሰነዘር ይቆጣል። ለምሳሌ፣ እስራኤላውያን ከግብፅ ከወጡ በኋላ ፈርዖንና ኃያል ሠራዊቱ በቀይ ባሕር ዳርቻ ሰፍረው የነበሩትን አንዳች ረዳት የሌላቸው የሚመስሉ ምስኪን ሕዝቦች ማሳደድ ጀመሩ። ሆኖም ኃያላኑ የግብፅ ወታደሮች እስራኤላውያንን ተከትለው ደረቅ ወደሆነው የባሕር ወለል ሲገቡ፣ ይሖዋ የጦር ሠረገሎቻቸውን መንኮራኩሮች በማወላለቅ ባሕሩ ውስጥ ጣላቸው። “ከእነሱም መካከል አንድም የተረፈ የለም።” (ዘፀ. 14:25-28) የይሖዋ ቁጣ በግብፃውያን ላይ የነደደው ለሕዝቦቹ ባለው “ታማኝ ፍቅር” የተነሳ ነው።—ዘፀአት 15:9-13ን አንብብ።
10 በንጉሥ ሕዝቅያስ ዘመንም ይሖዋ ለሕዝቦቹ ያለው ፍቅር እርምጃ እንዲወስድ አነሳስቶታል። በዘመኑ እጅግ ኃያልና ጨካኝ የነበረው የአሦር ሠራዊት በኢየሩሳሌም ላይ ዘመተ። የይሖዋ ታማኝ አገልጋዮች በአሦራውያን የመከበብ አደጋ ተጋረጠባቸው፤ ይህ ከበባ አሰቃቂ በሆነ ሁኔታ ቀስ በቀስ ሞተው እንዲያልቁ የሚያደርግ ነበር። (2 ነገ. 18:27) በዚህም ምክንያት ይሖዋ አንድ መልአክ ላከ፤ ይህ መልአክ ብቻውን በአንድ ሌሊት 185,000 የጠላት ወታደሮችን ገደለ! (2 ነገ. 19:34, 35) በማግስቱ ጠዋት በአሦራውያን ጦር ሰፈር የነበረውን ሁኔታ በዓይነ ሕሊናህ ለመሣል ሞክር። የወታደሮቹ ጦር፣ ጋሻና ሰይፍ ካለበት ቦታ አልተንቀሳቀሰም። ተዋጊዎቹን የሚቀሰቅስ የመለከት ድምፅ የለም። ወታደሮቹ እንዲሰለፉ የሚያዝዝ ድምፅም አይሰማም። በድንኳኖቹ ውስጥ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ አይታይም፤ የጦር ሰፈሩ ጸጥ ረጭ ብሏል። ሜዳው ሁሉ በሬሳ ተሞልቷል።
11. ይሖዋ ሕዝቦቹ ለአደጋ ሲጋለጡ ምን እንደሚያደርግ የሚያሳዩት የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎች ማጽናኛና ማበረታቻ የሚሰጡን እንዴት ነው?
11 የምናገኘው ትምህርት፦ ይሖዋ ሕዝቦቹ ለአደጋ ሲጋለጡ ምን እንደሚያደርግ የሚያሳዩት እነዚህ ምሳሌዎች ለጠላቶቻችን የሚከተለውን ኃይለኛ ማስጠንቀቂያ ያስተላልፋሉ፦ አምላክ በሚቆጣበት ጊዜ በእሱ “እጅ መውደቅ የሚያስፈራ ነገር ነው።” (ዕብ. 10:31) እነዚህ ምሳሌዎች ለእኛ ደግሞ ማጽናኛና ድፍረት ይሰጡናል። ዋነኛው ጠላታችን የሆነው ሰይጣን እንደማይሳካለት ማወቃችን ያጽናናናል። ሰይጣን ዓለምን እየገዛ ያለበት “ጥቂት ጊዜ” በቅርቡ ያበቃል! (ራእይ 12:12) እስከዚያ ድረስ ግን ማንም ግለሰብ፣ ድርጅት ወይም መንግሥት የአምላክን ፈቃድ ከማድረግ ሊያግደን እንደማይችል በመተማመን ይሖዋን በልበ ሙሉነት ማገልገል እንችላለን። (መዝሙር 118:6-9ን አንብብ።) ሐዋርያው ጳውሎስ “አምላክ ከእኛ ጋር ከሆነ ማን ሊቃወመን ይችላል?” በማለት በመንፈስ መሪነት የጻፋቸው ቃላት ያለንን የመተማመን ስሜት በሚገባ ይገልጻሉ።—ሮም 8:31
12. በታላቁ መከራ ወቅት የይሖዋ ቁጣ እንዲነድ የሚያደርገው ምንድን ነው?
12 ይሖዋ ግብፃውያን እያሳደዷቸው ለነበሩት እስራኤላውያንና በአሦራውያን ከበባ ውስጥ ለወደቁት የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች እንዳደረገው ሁሉ በመጪው ታላቅ መከራ ወቅት እኛን ለመታደግ እርምጃ ይወስዳል። ይሖዋ ለእኛ ያለው ጥልቅ ፍቅር ጠላቶቻችን ሊያጠፉን በሚሞክሩበት ጊዜ ቁጣው እንዲነድ ያደርገዋል። እኛን ለማጥቃት በመነሳት የሞኝነት ድርጊት የሚፈጽሙት ሰዎች የይሖዋን ዓይን ብሌን እንደነኩ ይቆጠራል። በዚህ ጊዜ ይሖዋ የሚወስደው እርምጃ ፈጣንና የማያዳግም ይሆናል። (ዘካ. 2:8, 9) በዚያ ወቅት በታሪክ ዘመናት ሁሉ ታይቶ የማይታወቅ ከፍተኛ እልቂት ይከሰታል። ይሁን እንጂ የአምላክ ጠላቶች ይሖዋ የሚያወርድባቸው ቁጣ እንግዳ ነገር ሊሆንባቸው አይገባም። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው?
ይሖዋ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል
13. ይሖዋ ምን ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል?
13 ይሖዋ “ለቁጣ የዘገየ” አምላክ በመሆኑ፣ እሱን የሚቃወሙትንና በሕዝቦቹ ላይ ጉዳት ለማድረስ የሚሞክሩትን እንደሚያጠፋ በተደጋጋሚ አስጠንቅቋል። (ዘፀ. 34:6, 7) ይሖዋ እንደ ኤርምያስ፣ ሕዝቅኤልና ዳንኤል ያሉትን ነቢያት፣ ክርስቶስ ኢየሱስን እንዲሁም ሐዋርያቱን ጴጥሮስን፣ ጳውሎስንና ዮሐንስን በመጠቀም አንድ ታላቅ ጦርነት እንደሚመጣ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል።—“ይሖዋ ስለ መጪው ታላቅ ጦርነት የሰጠው ማስጠንቀቂያ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።
14, 15. ይሖዋ ምን ሥራ አከናውኗል? ለምንስ?
14 ይሖዋ እነዚህ ማስጠንቀቂያዎች በቃሉ ውስጥ እንዲሰፍሩ አድርጓል። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ከየትኛውም መጽሐፍ ይበልጥ በብዛት እንዲተረጎምና እንዲሰራጭ አድርጓል። ከዚህም ሌላ፣ ሰዎች ከአምላክ ጋር ጥሩ ዝምድና እንዲመሠርቱ ለመርዳትና ስለ መጪው ‘ታላቅ የይሖዋ ቀን’ ለማስጠንቀቅ የተቻላቸውን ጥረት የሚያደርጉ ፈቃደኛ ሠራተኞችን ያቀፈ ሠራዊት በመላው ምድር አሰልፏል። (ሶፎ. 1:14፤ መዝ. 2:10-12፤ 110:3) አገልጋዮቹ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የሚረዱ ጽሑፎችን በመቶዎች በሚቆጠሩ ቋንቋዎች እንዲተረጉሙ እንዲሁም በቃሉ ውስጥ የሚገኙትን ተስፋዎችና ማስጠንቀቂያዎች ለሰዎች በመናገር በየዓመቱ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ሰዓት እንዲያሳልፉ አነሳስቷቸዋል።
15 ይሖዋ ይህ ሁሉ ሥራ እንዲከናወን ያደረገው “ሁሉ ለንስሐ እንዲበቃ እንጂ ማንም እንዲጠፋ ስለማይፈልግ ነው።” (2 ጴጥ. 3:9) አፍቃሪና ታጋሽ የሆነውን አምላካችንን መወከልና መልእክቱን በማዳረሱ ሥራ አነስተኛ ድርሻ ማበርከት መቻላችን እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው! ይሁን እንጂ ለማስጠንቀቂያው ጆሯቸውን የማይሰጡ ሰዎች እርምጃ መውሰድ የሚችሉበት ጊዜ እያለቀባቸው ነው።
የይሖዋ ቁጣ ‘የሚነደው’ መቼ ነው?
16, 17. ይሖዋ የመጨረሻው ጦርነት የሚካሄድበትን ጊዜ አስቀድሞ ወስኗል? አብራራ።
16 ይሖዋ የመጨረሻው ጦርነት የሚካሄድበትን ጊዜ አስቀድሞ ወስኗል። በሕዝቦቹ ላይ ጥቃት የሚሰነዘረው መቼ እንደሆነ ያውቃል። (ማቴ. 24:36) ይሖዋ ጠላቶቹ ጥቃት የሚሰነዝሩት መቼ እንደሆነ የሚያውቀው እንዴት ነው?
17 ከዚህ በፊት በነበረው ምዕራፍ ላይ እንደተመለከትነው ይሖዋ ጎግን “[በመንጋጋህ] መንጠቆ አስገባለሁ” ብሎታል። ይሖዋ ግንባር የፈጠሩትን ብሔራት ወሳኝ ወደሆነ ግጭት ይመራቸዋል። (ሕዝ. 38:4) ይህ ሲባል ግን የጦርነቱ ጠንሳሽ እሱ ይሆናል ወይም ተቃዋሚዎቹን የመምረጥ ነፃነት ይነፍጋቸዋል ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ይሖዋ የሰውን ልብ ማንበብ ስለሚችል ጠላቶቹ አንድ ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥማቸው ምን ምላሽ እንደሚሰጡ ያውቃል፤ በመሆኑም እንዲህ ዓይነት እርምጃ እንዲወስዱ ሁኔታዎችን ያመቻቻል።—መዝ. 94:11፤ ኢሳ. 46:9, 10፤ ኤር. 17:10
18. ሰዎች፣ ሁሉን ቻይ ከሆነው አምላክ ጋር ጦርነት እንዲገጥሙ የሚያደርግ ነገር የሚፈጽሙት ለምንድን ነው?
18 ታዲያ ይሖዋ ራሱ ጦርነቱን ካላስጀመረ ወይም ተቃዋሚዎቹ ለጦርነት እንዲዘምቱ የማያስገድዳቸው ከሆነ ሥጋ ለባሽ የሆኑ ሰዎች፣ ሁሉን ቻይ ከሆነው አምላክ ጋር ጦርነት እንዲገጥሙ የሚያደርግ ነገር የሚፈጽሙት ለምንድን ነው? ምናልባት በዚህ ወቅት፣ አምላክ እንደሌለ አሊያም ደግሞ በሰዎች ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ እንደማይገባ አድርገው ማሰብ ይጀምሩ ይሆናል። የሐሰት ሃይማኖት ድርጅቶችን በሙሉ ከምድር ላይ ማጥፋት መቻላቸው እንዲህ ብለው እንዲያስቡ ሊያደርጋቸው ይችላል። ‘በእርግጥ አምላክ ቢኖር ኖሮ እሱን እንወክላለን የሚሉትን ድርጅቶች ይጠብቃቸው ነበር’ ብለው ሊያስቡ ይችላሉ። እሱን እንደሚያመልኩ እየተናገሩ መጥፎ ድርጊት በመፈጸም ስሙን ያሰደቡትን ሃይማኖቶች እንዲያጠፉ ሐሳቡን በልባቸው ያኖረው አምላክ ራሱ እንደሆነ አይገነዘቡም።—ራእይ 17:16, 17
19. የሐሰት ሃይማኖት ከጠፋ በኋላ ምን ሊከናወን ይችላል?
19 የሐሰት ሃይማኖት ከጠፋ በኋላ ይሖዋ ሕዝቦቹ ኃይለኛ የፍርድ መልእክት እንዲያውጁ ያደርግ ይሆናል፤ ይህ መልእክት በራእይ መጽሐፍ ላይ እያንዳንዱ 20 ኪሎ ግራም በሚመዝን የበረዶ ድንጋይ ውርጅብኝ ተመስሏል። (ራእይ 16:21 ግርጌ) ምናልባት መልእክቱ የፖለቲካውና የንግዱ ሥርዓት መጥፊያው እንደቀረበ የሚገልጽ ሊሆን ይችላል፤ ሰዎች ይህ መልእክት በጣም ስለሚያሠቃያቸው አምላክን እስከመሳደብ ይደርሳሉ። ብሔራት መጠነ ሰፊ ጥቃት በመሰንዘር የአምላክ ሕዝቦችን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ጸጥ ለማሰኘት የሚያነሳሳቸው ይህ መልእክት ሊሆን ይችላል። ለጥቃት የተጋለጥን እንደሆንንና በቀላሉ ልንጠፋ እንደምንችል አድርገው ያስባሉ። ይህ እንዴት ያለ ስህተት ነው!
ይሖዋ ቁጣውን የሚገልጸው እንዴት ነው?
20, 21. ጎግ ማን ነው? ምንስ ይደርስበታል?
20 በዚህ መጽሐፍ ምዕራፍ 17 ላይ እንደተመለከትነው ሕዝቅኤል እኛን ለማጥቃት የሚነሱትን ግንባር የፈጠሩ ብሔራት ‘በማጎግ ምድር የሚገኘው ጎግ’ በሚል ትንቢታዊ ስያሜ ጠርቷቸዋል። (ሕዝ. 38:2) ይሁን እንጂ የእነዚህ ብሔራት ጥምረት በቀላሉ ሊበጠስ የሚችል ነው። ላይ ላዩን ሲታዩ እርስ በርስ የሚተባበሩ ቢመስሉም የፉክክርና የኩራት መንፈስ እንዲሁም ከፍተኛ ብሔራዊ ስሜት ይንጸባረቅባቸዋል። በመሆኑም “የእያንዳንዱ ሰው ሰይፍ በገዛ ወንድሙ ላይ” እንዲሆን ማድረግ ለይሖዋ በጣም ቀላል ነገር ነው። (ሕዝ. 38:21) ይሁን እንጂ በብሔራቱ ላይ የሚደርሰው ጥፋት ከሰብዓዊ ኃይል በላይ የሆነ ምንጭ እንዳለው በግልጽ መታየቱ አይቀርም።
21 ጠላቶቻችን ከመጥፋታቸው በፊት የሰውን ልጅ ምልክት ያያሉ፤ ይህም የይሖዋና የኢየሱስ ኃይል የሚታይበትን ተአምራዊ መግለጫ የሚያመለክት ሳይሆን አይቀርም። (ማቴ. 24:30) ተቃዋሚዎቹ በሚያዩት ነገር የተነሳ በከፍተኛ ጭንቀት ይዋጣሉ። ኢየሱስ እንደተናገረው “ሰዎች ከፍርሃትና በዓለም ላይ የሚመጡትን ነገሮች ከመጠበቅ የተነሳ ይዝለፈለፋሉ።” (ሉቃስ 21:25-27) ብሔራት፣ የይሖዋን ሕዝቦች ለማጥቃት መነሳታቸው ትልቅ ስህተት እንደነበረ ይገነዘባሉ። በዚያ ወቅት፣ ኃያል የጦር አዛዥ የሆነውን የሠራዊት ጌታ ይሖዋን ለማወቅ ይገደዳሉ። (መዝ. 46:6-11፤ ሕዝ. 38:23) ይሖዋ ታማኝ አገልጋዮቹን ለመጠበቅና ጠላቶቹን ለማስወገድ ሰማያዊ ሠራዊቱንና የተፈጥሮ ኃይሎችን እንደሚጠቀም ጥያቄ የለውም።—2 ጴጥሮስ 2:9ን አንብብ።
22, 23. የአምላክን ሕዝቦች የሚጠብቁት እነማን ናቸው? ይህን ኃላፊነታቸውን በተመለከተስ ምን እንደሚሰማቸው መጠበቅ እንችላለን?
ስለ ይሖዋ ቀን ያለን እውቀት ምን እንድናደርግ ሊያነሳሳን ይገባል?
22 ኢየሱስ ሠራዊቱን እየመራ በአምላክ ጠላቶች ላይ ለመዝመት እንዲሁም አባቱን የሚወዱትንና የሚያገለግሉትን ሰዎች ለመታደግ ምን ያህል እንደሚጓጓ ለማሰብ ሞክር። በተጨማሪም በዚያ ጊዜ ቅቡዓኑ ምን ሊሰማቸው እንደሚችል መገመት ትችላለህ። በምድር ላይ የቀሩት ሁሉም ቅቡዓን አርማጌዶን ከመጀመሩ በፊት ወደ ሰማይ ስለሚሄዱ 144,000ዎቹ በሙሉ ከኢየሱስ ጎን ተሰልፈው ይዋጋሉ። (ራእይ 17:12-14) ብዙዎቹ ቅቡዓን በመጨረሻዎቹ ቀናት ከሌሎች በጎች አባላት ጋር አብረው በማገልገላቸው ከእነሱ ጋር የቅርብ ወዳጅነት መሥርተው እንደሚሆን የታወቀ ነው። በአርማጌዶን ጦርነት ወቅት፣ ቅቡዓኑ በፈተናዎቻቸው ሁሉ በታማኝነት የደገፏቸውን የሌሎች በጎች አባላት መታደግ የሚችሉበት ሥልጣንም ሆነ ኃይል ይኖራቸዋል።—ማቴ. 25:31-40
23 ኢየሱስ በሚመራው ሰማያዊ ሠራዊት ውስጥ መላእክትም ይገኙበታል። (2 ተሰ. 1:7፤ ራእይ 19:14) መላእክት ቀደም ሲልም ቢሆን ኢየሱስ ሰይጣንንና አጋንንቱን ከሰማይ ባባረረበት ወቅት ከእሱ ጎን ተሰልፈው ነበር። (ራእይ 12:7-9) በተጨማሪም ይሖዋን ማምለክ የሚፈልጉ ሰዎችን በመሰብሰቡ ሥራ ተካፍለዋል። (ራእይ 14:6, 7) በመሆኑም ይሖዋ ለእነዚህ ታማኝ አገልጋዮቹ ጥበቃ ለማድረግ መላእክትን መጠቀሙ ተገቢ ነው። ከሁሉ በላይ ደግሞ የይሖዋ ሠራዊት አባላት ሆነው የተሰለፉ በሙሉ የእሱን ጠላቶች በማጥፋት ስሙ እንዲቀደስና ከነቀፋ ነፃ እንዲሆን ማድረግ በመቻላቸው ታላቅ ክብር ይሰማቸዋል።—ማቴ. 6:9, 10
24. የሌሎች በጎች ክፍል የሆኑት እጅግ ብዙ ሕዝብ በአርማጌዶን ጦርነት ወቅት ምን ይሰማቸዋል?
24 የሌሎች በጎች ክፍል የሆኑት እጅግ ብዙ ሕዝብ፣ እነሱን ለመርዳት ከፍተኛ ጉጉት ያለው ይህ ኃያል ሠራዊት ጥበቃ ስለሚያደርግላቸው በፍርሃት የሚርበተበቱበት ምንም ምክንያት አይኖርም። እንዲያውም ‘መዳናቸው እየቀረበ ስለሆነ ቀጥ ብለው ይቆማሉ፤ ራሳቸውንም ቀና ያደርጋሉ።’ (ሉቃስ 21:28) የይሖዋ ቀን ከመምጣቱ በፊት በተቻለ መጠን ብዙ ሰዎች መሐሪና አዳኝ የሆነውን አባታችንን ማወቅና መውደድ እንዲችሉ መርዳታችን ምንኛ አስፈላጊ ነው!—ሶፎንያስ 2:2, 3ን አንብብ።
25. በሚቀጥለው ምዕራፍ ላይ ምን እንመለከታለን?
25 ብዙውን ጊዜ ሰብዓዊ ጦርነቶች፣ ካበቁ በኋላም እንኳ ከፍተኛ ሥቃይና ትርምስ ያስከትላሉ። በአንጻሩ ግን የአርማጌዶን ጦርነት ሥርዓት እንዲነግሥና ደስታ እንዲሰፍን ያደርጋል። የይሖዋ ቁጣ ከበረደ፣ ተዋጊዎቹ ሰይፋቸውን ወደ ሰገባው ከመለሱና የታላቁ ጦርነት ሁካታ ካበቃ በኋላ የሚኖረው ሁኔታ ምን ይመስላል? በሚቀጥለው ምዕራፍ በዚያን ጊዜ የሚኖረው አስደሳች ሕይወት ምን እንደሚመስል እንመረምራለን።