ብዙ ሥራ እያለብህ ደስተኛ ልትሆን ትችላለህን?
ብዙዎቻችን ሥራ በጣም ይበዛብናል፤ እንዲያውም ብዙ ጊዜ የውጥረት ኑሮ እንኖራለን። ዘመናዊው ኑሮ የሚያስከትላቸው አስቸጋሪ ተጽዕኖዎች ከፕሮግራማችን ወደኋላ እንዳንቀር የማያቋርጥ ጥረት እንድናደርግ ይጠይቁብናል። ባሎችና አባቶች ለቤተሰባቸው፣ ለአሠሪዎቻቸውና ለሌሎች ያሉባቸውን አስጨናቂ ግዴታዎች ማሟላት ይኖርባቸዋል። ሚስቶችና እናቶችም ለቤተሰባቸው የሚያስፈልጉትን ነገሮች ለማሟላት ይባክናሉ፤ ብዙዎቹም ሰብዓዊ ሥራ ይሠራሉ። ወጣቶችም በኅብረተሰቡ ውስጥ ፍሬያማ ሥራ መሥራት የሚያስችላቸውን ትምህርት ለመከታተል ሲጣጣሩ አንዳንድ የቤተሰብ ግዴታዎችን ለማሟላት ሲሠሩ ጭንቀት ይሰማቸዋል።
ይሁን እንጂ እኛ ሕይወታችንን ለይሖዋ አምላክ የወሰንና የእርሱ የተጠመቅን ምስክሮች የሆንነውስ እንዴት ነን? እንድናሟላቸው ከምንጠየቃቸው ነገሮች በተጨማሪ ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ያሳስበናል፦ “የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፣ ድካማችሁ በጌታ ከንቱ እንዳይሆን አውቃችኋልና የምትደላደሉ፣ የማትነቃነቁም፣ የጌታም ሥራ ሁልጊዜ የሚበዛላችሁ ሁኑ።” (1 ቆሮንቶስ 15:58) አዎን፣ እውነተኛው አምልኮ የሚጠይቃቸው ብዙ የሆኑ ሌሎች ኃላፊነቶችን ይጨምራል። እነዚህን ሁሉ ግዴታዎች ልናሟላና የአእምሮ ሰላምና ደስተኛ አመለካከት ሊኖረን የሚችለው እንዴት ነው?
ሥራን አሟልቶ መፈጸም ደስታን ያመጣል
የደኅንነት ወይም የእርካታ ስሜት የሆነው ደስታ የሕይወትን ኃላፊነቶች በተሳካ ሁኔታ ከማሟላት ጋር በቅርብ የሚዛመድ ነው። ዕለታዊ ግዴታዎቻችንን ምክንያታዊ በሆነ መንገድና በተሟላ ሁኔታ ለማሟላት ከቻልን፣ ነገሮች በጊዜያቸውና ሥርዓታማ በሆነ መንገድ ከተሠሩ አንድ ነገር እንዳከናወን ይሰማናል፤ እርካታም ይኖረናል። መሆንም የሚገባው እንደዚህ ነው፤ ውጤቱም ደስታን ያመጣልናል።
ይሖዋ አምላክ ኃላፊነታችንን መወጣቱ የሚያስጨንቀን ሸክም እንዲሆንብን ፈጽሞ አላሰበም። ከዚህ ይልቅ ምን ጊዜም የእርሱ ምኞት ‘በድካማችን ሁሉ ደስ እንዲለንና መልካሙንም እንድናይ’ ነው። (መክብብ 3:12, 13) በሥራችን ስንደሰት ብዙውን ጊዜ ፍሬያማ እንሆናለን። መመሪያ ቶሎ የምንቀበል እንሆናለን፤ ከሌሎችም ጋር በሰላም እንኖራለን። በሌላው በኩል ግን ደስታ ከሌለን ሥራችን የሚያስጠላ፣ አሰልቺና የማይጥም እንዲያውም ስሜትንም የሚያቃውስ ይሆንብናል። ይህም ውጤት አልባ ወደሆኑ ልማዶችና አፍራሽ ወደሆነ የአእምሮ ዝንባሌ ይመራል። የሚፈለግብንን ነገር ሁሉ ለማሟላት ስንሞክር ሕይወት ዕለታዊ ትግል የሚጠይቅ ይሆንብናል። ይሁን እንጂ በምንሠራው ሥራ ደስተኞች ሆነን ለመቀጠል የሚያስችለን መንገድ ካገኘን አስደሳችና የተሟላ የአኗኗር መንገድ ማግኘታችን የማይቀር ነው።
ሚዛናዊ ሁኑ
ብዙ የምንሠራው ሥራ እያለን ደስተኞች ለመሆን ከፈለግን ሚዛናዊ መሆን አለብን። ሚዛን ምንድን ነው? “የአእምሮና የስሜት መረጋጋት” ነው። ሚዛናዊ የሆነ ሰው በሥራዎቹ ሥርዓታማ ለመሆን ይጣጣራል። አስቀድሞ ያቅዳል፣ ነገ ከነገ ወዲያ ይደርሳል የሚለውን ዝንባሌ ያስወግዳል፣ በልማዶቹም ልከኛ ነው። በምግብ፣ በመጠጥ፣ በመዝናኛ፣ በጊዜ ማሳለፊያዎችና በጭውውቶች ራሱን ይቆጣጠራል። እንዲያውም ‘በሁሉም ነገር ራሱን የሚገዛ’ መሆኑን ያሳያል።—1 ቆሮንቶስ 9:24-27፤ ከቲቶ 2:2 ጋር አወዳድር
ክርስቲያናዊ ሚዛንን በመጠበቅ ረገድ ጸሎት ከፍተኛ ቦታ አለው። አንድ የይሖዋ አገልጋይ የአምላክን ቅዱስ መንፈስ እንዲያገኝና የመንፈሱን ፍሬ (ራስን መግዛትንም ጭምር) ለመኮትኮት የሰማያዊ አባቱን እርዳታ ለማግኘት ሊጸልይ ይችላል። (ሉቃስ 11:13፤ ገላትያ 5:22, 23) በተለይ አንድ ክርስቲያን ሚዛኑን በሚያዛቡ ችግሮች ሲጠቃ ወደ አምላክ ጸሎት ማቅረብ ይኖርበታል። መዝሙራዊው ዳዊት “መንገድህን [ለይሖዋ (አዓት)] አደራ ስጥ፣ በእርሱም ታመን፣ እርሱም ያደርግልሃል” ብሏል። (መዝሙር 37:5) አንዳንድ ጊዜ ዳዊት እንደሚከተለው በማለት እንደለመነው ብለን መጸለይ ሊያስፈልገን ይችላል፦ “አምላኬ ሆይ በቶሎ እርዳኝ። አንተ ረዳቴና ማምለጫ መንገድ የምታዘጋጅልኝ ነህ። ይሖዋ ሆይ፣ በጣም አትዘግይ።” (መዝሙር 70:5 አዓት) በጸሎት ሚዛንን ለመጠበቅና ‘ልባችንንና የማሰብ ኃይላችንን ሊጠብቅልን የሚችለውን አእምሮን ሁሉ የሚያልፍ የአምላክ ሰላም’ ለማግኘት እንደሚቻል በፍጹም አትርሱ።—ፊልጵስዩስ 4:6, 7
ሚዛናዊ የሆነ ክርስቲያን በይሖዋ ስለሚመካና የአምላክን ሰላም ስለሚያገኝ የተረጋጋ አእምሮ አለው። (ቲቶ 2:11, 12) ይህም የሚመጣው የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ጥሩ አድርጎ ከመረዳትና በሕይወቱ ላይ ተግባራዊ ከማድረግ ነው። እንደዚህ ያለው ሰው ግብዝ አይደለም፤ ወይም ቸኩሎ አይፈርድም። ምክንያታዊ መሆኑ ሐሳበ ግትር ወይም እልኸኛ ከመሆን ይጠብቀዋል። ስለ ራሱና ስለ ችሎታዎቹ ልከኛ አመለካከት ይኖረዋል፤ ይህም ከሌሎች ጋር እንዲተባበር ይረዳዋል። (ሚክያስ 6:8) አንድን ሰው ሚዛናዊ ለመሆን የሚረዱት ጠባዮች በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የበላይ ተመልካቾች ሆነው ለማገልገል የሚሾሙት ከሚፈለጉባቸው ብቃቶች መካከል ናቸው።—1 ጢሞቴዎስ 3:2, 3
በዕለታዊ የሥራ እንቅስቃሴያችን ይበልጥ ሚዛናዊ ለመሆን በመጣር ደስታችንን ለመጨመር እንችላለን። ከጥሩ ሚዛን ጋር ግንኙነት ያላቸውን ጠባዮች በማሳየት ከባድ የሆነ አካላዊ ወይም ስሜታዊ ጭንቀት ሳያጋጥመን አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ለማከናወን እንችላለን። አኗኗራችን ከፍተኛ መረጋጋት ያለበት ይሆናል፤ ብዙ ለማከናወንም እንችላለን። ሌሎችም ከእኛ ጋር በመቀራረባቸው ተጨማሪ ደስታ ያገኛሉ፤ እኛም ከፍተኛ እርካታና ደስታ እናገኛለን። ይሁን እንጂ ሚዛንን ለመጠበቅ የሚረዱን አንዳንድ ተግባራዊ መንገዶች ምንድን ናቸው?
ሚዛንን ለመጠበቅ የሚረዱ ተግባራዊ መንገዶች
ሚዛንን ለመጠበቅ ከፈለግን የግል ጉዳዮቻችንን በወቅቱ ቶሎ ማከናወንና የተደራጀን መሆን ይገባናል። ቀደም ብለን ዕቅድ ማውጣት፣ ነገሮችን በሥርዓትና ዘዴ በተሞላበት ሁኔታ መያዝ ያስፈልገናል። ጉዳዮቻቸውን በጥሩ ሁኔታ ያላደራጁትና ዛሬ ነገ በማለት ሥራ የሚያቆዩት ግን ሕይወታቸውን በተጨማሪ ውጥረትና ጭንቀት ያወሳስቡታል። በዚህ የሕይወት ክልል ውስጥ የተሳካ ውጤት ማግኘታችን ምንም ዋጋ የሌለን የመጥፎ አጋጣሚዎች ተጠቂዎች እንደሆንን ሳይሆን ነገሮችን በቁጥጥራችን ሥር እንዳደረግን ሆኖ እንዲሰማን ያደርጋል።
ሁሉንም ነገር ራሳችን ለማድረግ መሞከር የለብንም። ከሌሎች እርዳታ ለመቀበል ፈቃደኞች የማይሆኑት ብዙውን ጊዜ ኃይላቸው ተሟጦ ተስፋ በመቁረጥ ዋጋቸውን ሲከፍሉ ይታያሉ። ሌሎች ሊይዟቸው የሚችሉ የተለያዩ ሥራዎች አሉ። ስለዚህ የእርዳታ እጃቸውን ለመዘርጋት ፈቃደኛ ከሆኑት ሰዎች ችሎታ መጠቀሙ ጥበብ ነው። ይህ ሸክማችንን ከማቃለሉም በተጨማሪ ወደ እኛ ለመቅረብ የሚፈልጉትን የሚያበረታታ ይሆናል።
ራሳችንን ከእኛ የበለጠ መሥራት ከሚችሉት ጋር ማወዳደሩ ጥበብ አይደለም። ከእኛ በላይ ለመሥራት እንደቻሉት ሰዎች ለመሆን መሞከሩ ተስፋ የሚያስቆርጥ ነው፤ ዝቅተኞችና የማንረባ እንደሆንን እንዲሰማንም ያደርጋል። እንደዚህ ያለው አስተሳሰብ አፍራሽ ነው፣ ቁርጥ ውሳኔያችንና በራስ የመተማመን መንፈሳችንን የሚያዳክም ነው። ጳውሎስ “እያንዳንዱ የራሱን ሥራ ይፈትን፣ ከዚያም በኋላ ስለ ሌላው ሰው ያልሆነ ስለ ራሱ ብቻ የሚመካበትን ያገኛል” ሲል ጽፏል። (ገላትያ 6:4) ከሁሉም ሠራተኞች የበለጠ ከፍ ተደርጎ የሚታየው ሠራተኛ መመሪያን የሚከተል፣ የማይወላውልና ትምክህት የሚጣልበት፣ ጥራት ያለው ሥራ የሚሠራ መሆኑን አስታውስ። እንደዚያ ከሆንን አገልግሎታችን የሚደነቅና የሚፈለግ ይሆናል።—ምሳሌ 22:29
ለጤንነታችን ጥሩ እንክብካቤ ማድረግ ያስፈልገናል። ካሉን ውድ ሀብቶች አንዱ እርሱ ነው፤ ምክንያቱም ያለ እርሱ ምንም ያህል መሥራት አንችልም። ስለዚህ ጤንነትን ለመጠበቅ የሚረዳ ምግብ መመገብ ይኖርብናል። በቂ እረፍት ማግኘት ያስፈልገናል፤ ማታም በጊዜ መተኛት ይኖርብናል። በጣም ሲደክመን ወይም የሕመም ስሜት ሲሰማን ራሳችንን አስገድደን ማሠራት የለብንም፤ እንደዚያ ካደረግን ከባድ ዋጋ እንከፍላለን።
የአጉረምራሚነት መንፈስ ከማሳደግ መጠበቁ አስፈላጊ ነው። አፍራሽ አስተሳሰብ እንዲያድግ ከለቀቅነው በማንኛውም ነገር ወይም በማንኛውም ሰው ላይ አንድ ዓይነት ስህተት ልናገኝ እንችላለን። ይህ የራሳችንንም ሆነ የሌሎችን ደስታ ለማጥፋት የተረጋገጠው መንገድ ነው። ሌላውን ከማማት ወይም ትክክል እንዳልሆነ ስለተሰማን ጉዳይ ከማጉረምረም ይልቅ ነገሩን እንዲመለከቱት ኃላፊነት ላላቸው መንገርና ነገሮችን እንዲያስተካክሉ ለእነርሱ መተው ይገባናል። (ከ1 ቆሮንቶስ 1:10-12 ጋር አወዳድር) ብሩህና ገንቢ አመለካከት ብንይዝ፣ ሁልጊዜ በሌሎች ላይና ሕይወታችንን በሚቀርጹት ነገሮች ላይ ጥሩ ነገር ለማግኘት ብንፈልግና ብንጠብቅ ጥበበኞች ነን።—ከይሁዳ 3, 4, 16 ጋር አወዳድር።
ለምንሠራቸው ሥራዎች ዕቅድ ስናወጣ በጥድፊያ በመሥራት አንዳንድ ከፍተኛ ነገሮችን ለማከናወን እንችል ይሆናል፤ ይሁን እንጂ በዚህ ዓይነቱ ጥድፊያ ለረጅም ጊዜ መቆየት አይቻልም። በተደጋጋሚ ከአቅም በላይ መሥራት ወደ መሰልቸት የሚመራ ብቻ ሳይሆን በሥራው ለመቀጠል ያለንንም ቁርጥ ውሳኔ ሊያዳክም የሚችል ተስፋ የመቁረጥ ሁኔታን ሊያስከትል ይችላል። እንግዲያው ለሁል ጊዜ ይዘነው ለመቀጠል በምንችለው ፍጥነት እንሥራ። ለምሳሌ ያህል ዘወትር ከቤት ወደ ቤት ለሚደረገው የስብከቱ ሥራና ለሌሎቹ የክርስቲያን አገልግሎት ገጽታዎች ሊሠራ የሚችል ፕሮግራም ማውጣቱ ጥሩ ነው። ለመዝናናትና ገንቢ ለሆነ የሚያንጽ ጊዜ ማሳለፊያ ጊዜ መመደብ ያስፈልገናል። በዕድሜ ከሸመገሉ የብዙ ዓመታት ተሞክሮ ካላቸው ሰዎች ጋር መነጋገሩንም ጠቃሚ ሆኖ እናገኘዋለን፤ ምክንያቱም እነርሱ በአካል ወይም በአእምሮ ራሳቸውን ሳያስጨንቁ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን እንዴት ማከናወን እንደሚችሉ ተምረዋል።
ስትወስኑ ጥሩ ግምት ይኑራችሁ
ግዴታ እንዳለብን ቢሰማንና የተሰጡንን ኃላፊነቶች (በይሖዋ ሕዝቦች ጉባኤ ውስጥ የተሰጡንንም ኃላፊነቶች ጭምር) ለመፈጸም ፍላጎት ቢኖረን ተገቢ ነው። አምላክ በትጉህና ትምክህት በሚጣልባቸው ሠራተኞች ይደሰታል። (ከማቴዎስ 25:21፤ ከቲቶ 2:11-14 ጋር አወዳድር) ሆኖም ቅዱሳን ጽሑፎች “መልካም ጥበብንና ጥንቃቄን ጠብቅ” በማለት ያስጠነቅቃሉ። (ምሳሌ 3:21) የመጽሐፍ ቅዱስን ጥበብ ተግባራዊ ማድረጉ ይጠቅመናል። ስንወስን ምክንያታዊ የሆነ ጥሩ ግምት ሊኖረን፣ በጥንቃቄ ዕቅዶችን ማውጣትና ምን ጊዜም የአቅማችንን ወሰን ሳናልፍ መሥራት ያስፈልገናል።
የጌታ ሥራ የበዛልን እንድንሆን የተሰጠን ማሳሰቢያ በመክብብ 9:4 ላይ ከሚገኘው ማስጠንቀቂያ ጋር መመዛዘን ይኖርበታል። እዚህ ላይ “ያልሞተ ውሻ ከሞተ አንበሳ ይሻላልና” የሚል ማስጠንቀቂያ እናነባለን። አዎን፣ በሕይወት ያለ ውሻ አንዳንድ ሰዎች ቢንቁትም ብዙዎች እንደ አራዊት ንጉሥ አድርገው ከሚመለከቱት የሞተ አንበሳ ይሻላል። ሚዛናችንን ከጠበቅንና ለጤንነታችን ተገቢውን እንክብካቤ ካደረግን በሕይወት ለመኖርና ነገሮችን በማከናወን ለመቀጠል እንችላለን። ሙታን በምንም ዓይነት እንቅስቃሴ ለመካፈል አይችሉም። ስንወስን ጥሩ ግምት ቢኖረን ደስታችንን ሳናጣ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን ለመሥራት የሚያስችለን ምክንያታዊ የሆነ ሚዛን እንዲኖረን ሊረዳን ይችላል።
ስለዚህ ብዙ የሚሠራ ሥራ ስላለን ደስተኞች ልንሆን አንችልም ማለት አይደለም። ሥራ እጅግ የሚበዛባቸው ሰዎች ምክንያታዊ ከሆኑ፣ ጥሩ አመለካከት ካላቸው፣ የተስተካከለ ሚዛናቸውን ለመጠበቅ በጥሩ ግምት የሚጠቀሙ ከሆኑ በጣም ከሚደሰቱት መካከል ለመሆን ይችላሉ። ጥበብን ካሳየን፣ ጥሩ ሥራዎችን ካከናወንንና ተስፋችንን በይሖዋ አምላክ ላይ ካደረግን ወደር የማይገኝለት ደስታ ማግኘት እንችላለን።—1 ጢሞቴዎስ 6:17-19