የአንባብያን ጥያቄዎች
◼ ኢየሱስ በማቴዎስ 10:21 ላይ በጉባኤ ውስጥ የሚገኙ ብዙ ወንድሞች በመንፈሳዊ ወንድሞቻቸው ላይ እንደሚነሡ ማስጠንቀቁ ነበርን?
አልነበረም፤ ኢየሱስ “ወንድምም ወንድሙን አባትም ልጁን ለሞት አሳልፎ ይሰጣል፣ ልጆችም በወላጆቻቸው ላይ ይነሣሉ ይገድሉአቸውማል” የሚል ማስጠንቀቂያ በሰጠ ጊዜ ለመግለጽ የፈለገው ነጥብ ያ አልነበረም።—ማቴዎስ 10:21
ከላይና ከታች ያለው አሳብ ኢየሱስ ይህን የተናገረው 12 ሐዋርያቱን በእስራኤል ውስጥ እንዲሰብኩ በላካቸው ጊዜ እንደነበር ያሳያል። ከተናገራቸው ነገሮች ውስጥ አብዛኛው በመጀመሪያ ደረጃ የሚያመለክተው ለሐዋርያቱ ነው። ለምሳሌ ያህል ተዓምራታዊ ፈውሶችን ለማድረግ፣ ርኩሳን መናፍስትን ለማውጣት፣ ሙታንን ለማስነሳት ኃይል እንደተሰጣቸው ተናግሯል። (ማቴዎስ 10:1, 8፤ 11:1) ሁሉም ክርስትያኖች እንደነዚህ ያሉትን ተዓምራታዊ ኃይሎች እንዳልተቀበሉ ታሪክ ያረጋግጣል። ይህም ኢየሱስ እዚህ ላይ እየተናገረ ያለው ለአንድ የተወሰነ የአድማጮች ቡድን ይኸውም ለሐዋርያቱ እንደነበረ ያረጋግጣል።
ቢሆንም ኢየሱስ ከተናገራቸው ነገሮች ውስጥ አንዳንዱ ከሐዋርያቱ የስብከት ጉዞም አልፎ የሚሄዱ ነበሩ። “ከሰዎች ተጠበቁ፤ ለእነርሱና ለአሕዛብም ምስክር እንዲሆን፣ ስለ እኔ ወደ ገዥዎች ወደ ነገሥታትም ትወሰዳላችሁ” ብሎአቸው ነበር። (ማቴዎስ 10:17, 18) በዚህ ጉዞ ላይ 12ቱ ተቃውሞ ሳያጋጥማቸው አይቀርም፤ ነገር ግን “ለአሕዛብም”a ምሥክርነቱን ለመስጠት “በገዥዎችና በነገሥታት ፊት” ስለመወሰዳቸው የሚገልጽ ምንም ማስረጃ የለም። ከዚያ በኋላ ባሉት ዓመታት ሐዋርያት እንደ ሄሮድስ አግሪጳ ቀዳማዊና ዳግማዊ፣ ሰርጊየስ ጳውሎስ፣ ጋሊዮና ንጉሠ ነገሥት ኔሮ በመሳሰሉት ገዥዎች ፊት ቀርበው ነበር። (ሥራ 12:1, 2፤ 13:6, 7፤ 18:12፤ 25:8-12, 21፤ 26:1-3) ስለዚህ የኢየሱስ ቃላት ከጊዜ በኋላ ተፈጽመዋል።
የኢየሱስ ምክር “ወንድምም ወንድሙን . . . ለሞት አሳልፎ ይሰጣል” የሚለውን ማስጠንቀቂያ በመስጠት ቀጠለ። በሚቀጥለው በቁጥር 21 ላይ “አባትም ልጁን ለሞት አሳልፎ ይሰጣል፣ ልጆችም በወላጆቻቸው ላይ ይነሣሉ ይገድሉአቸውማል” ሲል በተናገራቸው ቃላት መንፈሳዊ አባቶችን ወይም ልጆችን መጥቀሱ እንዳልነበረ ሁሉ እዚህም ላይ መንፈሳዊ ወንድሞችን መጥቀሱ አልነበረም። ኢየሱስ ሐዋርያቱ ከገዛ ዘመዶቻቸውም ቢሆን የመረረ ጥላቻ ወይም ተቃውሞ እንደሚመጣ ሊጠብቁ እንደሚችሉ መናገሩ ነበር።—ማቴዎስ 10:35, 36
ሐዋርያቱ በዚያ የስብከት ጉዞአቸው መጽናት ያስፈልጋቸው ነበር። ኢየሱስ ቀጥሎ እንዲህ አለ፦ “በሁሉም ስለ ስሜ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ፤ እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል።”—ማቴዎስ 10:22
ኢየሱስ በዚህ ጊዜ ከተናገራቸው ነገሮች ውስጥ አንዳንዱ በዛሬ ጊዜ ለምንገኘው የይሖዋ ምስክሮች የሚያገለግል ነው። በስብከታችን የምናጐላው መንግሥቲቱን ነው። አገልግሎታችንን ያለ ክፍያ እናከናውናለን። ለምሥራቹ ፍላጎት የሚያሳዩትን ወይም የሚገባቸውን ሰዎች ለማግኘት ፍለጋ እናካሂዳለን። ጥንቃቄ ማድረግ አስፈላጊ ነው። ተቃዋሚዎች ብዙ ናቸው። አንዳንድ ጊዜ ዘመዶች፣ ጎረቤቶች፣ ወይም የሥራ ጓደኞች በተለይ እውነተኛውን ክርስትና መከተል ገና በጀመሩት ቅን ሰዎች ላይ ከባድ ችግሮችን ሊፈጥሩ ይችላሉ። ኢየሱስ የመገኘቱን “ምልክት” በሚገልጽበት ጊዜ ማስጠንቀቂያውን ደግሞታል። (ማቴዎስ 24:3, 9, 10፤ ሉቃስ 21:16, 17) በተጨማሪም ለመዳን ከፈለግን ‘እስከ መጨረሻው ድረስ የመጽናትን’ አስፈላጊነት በድጋሚ ተናግሮአል። አዎን፣ እስከ አሁኑ ሕይወታችን ፍጻሜ ወይም ይህ የነገሮች ሥርዓት እስከሚያበቃና ወደ አዲስ ምድር ለመግባት እስከምንችል ድረስ መጽናት ያስፈልገናል።—ማቴዎስ 24:13
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ሌሎች ትርጉሞች ይህን ቃል “አረመኔዎች” (ዘ ጀሩሳሌም ባይብል) “አሕዛብ” (ኒው ኢንተርናሺናል ቨርሺን እና የሞፋትና የላምሳ ትርጉሞች) እንዲሁም “የተጠሉት አረመኔዎች” (ዘ ኒው ኢንግሊሽ ባይብል) ብለው ይተረጉሙታል።