መጽሐፍ ቅዱስ—በእርግጥ ቅዱስ ነውን?
ባሁኑ ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስን ቅዱስ እንደሆነ የአምላክ ቃል አድርገው የሚመለከቱት ስንት ሰዎች ናቸው? በዚህ የጥርጣሬ ዘመን ብዙ ሰዎች መጽሐፉ በእውነት ቅዱስ መሆኑን በመጠራጠር ጊዜ እንዳለፈበትና እንደማይረባ አድርገው ይመለከቱታል። ከሕዝበ ክርስትና የሃይማኖት መሪዎችም እንኳን ሳይቀር አንዳንዶቹ መጽሐፍ ቅዱስ በአፈ ታሪክና በተረት የተሞላ ነው ብለው ያስተምራሉ። ‘መጽሐፍ ቅዱሳዊውን የታሪክ አቀራረብ አንድ አዋቂ ሰው ሊቀበለው የሚችል ስለመሆኑ’ ይጠራጠራሉ።—የተርጓሚዎች የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ጥራዝ 2 ገጽ 611
ታዋቂ የሆኑ ምሁራን መጽሐፍ ቅዱስን እንደ አምላክ ቃል አድርጎ የመጥቀስን ተገቢነት በሚመለከት የጥርጣሬ ዘር እየዘሩ ነው። አንዱ ምሁር “አንድ ሰው የአምላክ ቃል በሚለው ዓይነት አነጋገር ለመጠቀም ከፈለገ ለመጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው ተገቢ ስያሜ የእስራኤል ቃል፣ የጥንቶቹን ክርስቲያኖች ይመሩ የነበሩ የአንዳንዶች ቃል የሚል ይሆናል” በማለት ተናግረዋል። (መጽሐፍ ቅዱስ በዘመናዊው ዓለም ውስጥ—በጄምስ ባር) አንተስ ምን ብለህ ታስባለህ? መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል ነውን? በእርግጥ ቅዱስ ነውን?
መጽሐፍ ቅዱስን ማን ጻፈው?
የመጀመሪያውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የዘፍጥረትን መጽሐፍ የጻፈው ከ3,500 ዓመታት በፊት ይኖር የነበረው ዕብራዊው ሙሴ እንደሆነ በዘልማድም ይታመናል። ራሱ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚገልጸው ሌሎቹን ቅዱሳን ጽሑፎች በመጻፍ የተካፈሉት ከተለያየ የኑሮ መስክ የመጡ 40 የሚያህሉ ሰዎች ናቸው። በውጤቱም የመጽሐፍ ቅዱስ 66 መጻሕፍት ወይም ክፍሎች ስብስብ ሊገኝ ተችሏል። ይሁን እንጂ እነዚህ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች እኛ ነን ብለው አልተናገሩም። አንዱ ጸሐፊ እንዲህ አለ፦ “ቅዱስ ጽሑፍ ሁሉ በአምላክ መንፈስ መሪነትና አነሳሽነት የተጻፈ ነው።” (2 ጢሞቴዎስ 3:16 አዓት) ሌላውም ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች “በእግዚአብሔር ተልከው ቅዱሳን ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ተናገሩ” በማለት ጽፎአል።—2 ጴጥሮስ 1:21
ይህም ጸሐፊዎቹን በአምላክ ቁጥጥርና መሪነት ሥር የሠሩ የግል ጸሐፊዎቹ ያደርጋቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚገልጸው ብዙውን ጊዜ ጸሐፊው ከአምላክ ያገኘውን መልዕክት ለማስተላለፍ የራሱን ቃላት እንዲመርጥ ተፈቅዶለታል። (ዕንባቆም 2:2) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ብዙ ዓይነት የአፃፃፍ ዘይቤዎች ሊኖሩ የቻሉት በዚህ ምክንያት ነው። ይሁን እንጂ በሚጻፍበት ጊዜ ሁሉ የአምላክ አመራር ነበረበት።
እርግጥ እነዚህ ጸሐፊዎች በመለኮታዊ ኃይል እየተመራን ጽፈናል ብለው መናገራቸው ብቻ መጽሐፍ ቅዱስ ፈጣሪ ለሰው ዘር የሰጠው መልዕክት መሆኑን የሚያረጋግጥ አይደለም። ሆኖም ራሱን መጽሐፉን ጥንቃቄ በተሞላበትና አድልዎ በሌለበት መንገድ በመመርመር ልዑሉ አምላክ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ መሆኑንና አለመሆኑ በግልጽ መታየት ይኖርበታል። ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስ መለኮታዊ ባለቤትነት እንዳለው ማስረጃ ይሰጣልን? መጽሐፍ ቅዱስ በእርግጥ ቅዱስ ነው ብለን በትምክህት ለመናገር እንችላለንን?