የይሖዋን ውድ በጎች በጥንቃቄ መጠበቅ
ሽማግሌዎቹ በተመስጦ እያዳመጡ ነበር። ከሐዋርያው ጳውሎስ መመሪያዎችን ለመቀበል ከኤፌሶን እስከ ሚሊጢን 50 ኪሎ ሜትር ያህል ተጉዘዋል። እርሱን ከዚህ በኋላ እንደማያዩት በመስማታቸው አዝነዋል። ቀጥሎ ያሉት ቃላት በከፍተኛ ሁኔታ ሊታሰብባቸው እንደሚገባ ያውቁ ነበር:- “አምላክ በገዛ ልጁ ደም የዋጀውን ጉባኤ እንድትጠብቁ በመንፈስ ቅዱስ የበላይ ተመልካቾች ሆናችሁ ለተሾማችሁለት መንጋ ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ።” — ሥራ 20:25, 28, 38 አዓት
ጳውሎስ ለእረኞች የሰጠው አጭር መግለጫ ለእነዚህ የኤፌሶን ሽማግሌዎች ብዙ እውቀት አስገኝቶላቸዋል። በአካባቢያቸው በሚገኘው ገጠር ውስጥ ያለውን የእረኝነት ሥራ ያውቁ ነበር። በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ስለ እረኞች የሚናገሩት ብዙ መግለጫዎችም ለእነርሱ እንግዳ አልነበሩም። በተጨማሪም ይሖዋ ራሱን የሕዝቡ እረኛ አድርጎ እንደገለጸ አውቀው ነበር። — ኢሳይያስ 40:10, 11
ጳውሎስ ‘በመንጋው’ መካከል “የበላይ ተመልካቾች” ሆናችሁ እንዲሁም ‘የጉባኤው’ እረኞች ሆናችሁ በማለት ስለ እነርሱ ተናግሯል። “የበላይ ተመልካቾች” የሚለው ቃል ሥራቸው ምን እንደሆነ ሲያመለክት ‘እረኛ’ የሚለው ቃል ግን በበላይነት የማስተዳደር ሥራቸውን እንዴት እንደሚያከናውኑ ይገልጻል። አዎ፣ አንድ እረኛ የበጎቹን መንጋ ፍቅራዊ በሆነ መንገድ እንደሚጠብቅ ሁሉ የበላይ ተመልካቾችም እያንዳንዱን የጉባኤ አባል ተመሳሳይ በሆነ መንገድ መጠበቅ ይገባቸዋል።
በአሁኑ ጊዜ ቃል በቃል በጎችን ጠብቀው የሚያውቁ ሽማግሌዎች እምብዛም አይገኙም። ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ በተለይም ምሳሌያዊ በሆነ መንገድ ስለ በጎችም ሆነ ስለ እረኞች በጣም ብዙ መግለጫዎችን ይሰጣል። ይህም የጳውሎስ ቃላት ምንጊዜም የሚሠሩ መሆናቸውን ያሳያል። እንዲሁም በጥንት ዘመን አምላክ ሞገሱን ስላሳያቸው እረኞች ከሚናገረው ዘገባ ብዙ መማር ይቻላል። የእነርሱ ግሩም ምሳሌዎች በአሁኑ ጊዜ ያሉት ሽማግሌዎች የአምላክን ጉባኤ ለመጠበቅ በውስጣቸው ምን ምን ባሕርያትን ማዳበር እንደሚያስፈልጋቸው እንዲያውቁ ሊረዷቸው ይችላሉ።
ፍርሃት የለሹ እረኛ ዳዊት
በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ስለነበሩ እረኞች ስናስብ ቀደም ሲል የበጎች እረኛ የነበረውን ዳዊትን ማስታወሳችን አይቀርም። ከዳዊት ሕይወት ከምንማራቸው የመጀመሪያ ትምህርቶች አንዱ እረኛ መሆን የክብር ቦታ አለመሆኑን ነው። እንዲያውም ነቢዩ ሳሙኤል የእሴይን ልጅ የወደፊቱ የእስራኤል ንጉሥ አድርጎ ለመቀባት በሄደ ጊዜ ወጣቱ ዳዊት መጀመሪያ ላይ ፈጽሞ ተረስቶ ነበር። በመስክ ላይ “በጎችን ይጠብቅ” የነበረው ዳዊት ስሙ የተነሣው ይሖዋ ሰባቱን ታላላቅ ወንድሞቹን እንዳልተቀበላቸው ከገለጸ በኋላ ብቻ ነበር። (1 ሳሙኤል 16:10, 11) የሆነው ሆኖ ዳዊት በእረኝነት ያሳለፋቸው ዓመታት ትዕግስትን ለሚፈታተነው የእስራኤልን ሕዝብ እንደ እረኛ ሆኖ ለመምራቱ ሥራ ለሚጠይቅበት ነገር አዘጋጅተውታል። “[ይሖዋ] ዳዊትንም ባሪያውን መረጠው፣ ከበጎቹም መንጋ ውስጥ ወሰደው፤ . . . ርስቱንም እስራኤልን ይጠብቅ ዘንድ ወሰደው” በማለት መዝሙር 78:70, 71 ይናገራል። ዳዊት “ይሖዋ እረኛዬ ነው” በሚሉት ቃላት በመጀመር ውብ የሆነውንና በስፋት የሚታወቀውን 23ኛውን መዝሙር መጻፉ ተስማሚ ነበር።
በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ያሉ ሽማግሌዎች ልክ እንደ ዳዊት ትሑት የበታች እረኞች ሆነው ማገልገል እንጂ የማይገባቸውን ክብር መፈላለግ የለባቸውም። ሐዋርያው ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ እንደጻፈው ለዚህ የእረኝነት ኃላፊነት የሚጣጣሩ የክብርን ቦታ ሳይሆን ‘መልካምን ሥራ ይመኛሉ።’ — 1 ጢሞቴዎስ 3:1
ምንም እንኳ ዳዊት ቃል በቃል እረኛ ሆኖ መሥራቱ ዝቅተኛ ሥራ የነበረ ቢሆንም አንዳንድ ጊዜ ከፍተኛ ድፍረትን የሚጠይቅበት ነበር። ለምሳሌ ከአባቱ መንጋ በአንድ ወቅት አንበሳ በሌላ ጊዜ ደግሞ ድብ መጥቶ በግ ሲወስድ ዳዊት ያለፍርሃት እነዚህን ለማደን የመጡ አውሬዎችን ፊት ለፊት በመግጠም ገድሏቸዋል። (1 ሳሙኤል 17:34–36) አንበሳ ከእርሱ በጣም የበለጠ ግዙፍ የሆኑ እንስሳትን መግደል እንደሚችል ስናስብ ዳዊት አስደናቂ ድፍረት እንዳሳየ ልንገነዘብ እንችላለን። 140 ኪሎ ግራም ያህል የሚመዝነው በጳለስቲና ምድር ይኖር የነበረው ቡናማው የሶርያው ድብም ኃይለኛ በሆነው መዳፉ አንድን አጋዘን በአንድ ምት ሊገድለው ይችላል።
ዳዊት ለአባቱ በጎች ያሳየው ድፍረት የተሞላበት አሳቢነት በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ለሚገኙት እረኞች ጥሩ ምሳሌ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ የኤፌሶን ሽማግሌዎችን ‘ለመንጋው ከማይራሩ ጨካኝ ተኩላዎች’ እንዲጠነቀቁ አሳስቧቸዋል። (ሥራ 20:29) በዘመናችንም ክርስቲያን እረኞች የይሖዋን በጎች መንፈሳዊ ደኅንነት ለመጠበቅ ሲሉ ድፍረት ማሳየት የሚኖርባቸው ጊዜያት ሊከሰቱ ይችላሉ።
በጎቹን በድፍረት መጠበቅ የሚያስፈልግ ቢሆንም አፍቃሪውን እረኛ ዳዊትንና መልካሙን እረኛ ኢየሱስ ክርስቶስን በመምሰል በከፍተኛ ጥንቃቄ ሊያዙ ይገባል። (ዮሐንስ 10:11) ሽማግሌዎች መንጋው የይሖዋ መሆኑን በመረዳት በጎቹን ‘በኃይል በመግዛት’ ሊጫኑአቸው አይገባም። — 1 ጴጥሮስ 5:2, 3፤ ማቴዎስ 11:28–30፤ 20:25–27
ስሌትን መስጠት
ሌላው በደንብ የሚታወቀው እረኛ የእስራኤላውያን አባት ያዕቆብ ነው። እንዲጠብቅ በአደራ ለተሰጠው ለእያንዳንዱ በግ ኃላፊነት እንዳለበት ሆኖ ይሰማው ነበር። የአማቹን የላባን መንጎች ለአደራው የታመነ ሆኖ በመጠበቁ ለ20 ዓመታት ካገለገለ በኋላ እንዲህ ለማለት ችሏል:- “በጎችህና ፍየሎችህ አልጨነገፉም፤ የመንጎችህንም ጠቦቶች አልበላሁም፤ አውሬ የሰበረውን አላመጣሁልህም ነበር፤ እኔ ስለ እርሱ እከፍልህ ነበርሁ፤ በቀንም በሌሊትም ከእጄ ትሻው ነበርህ።” — ዘፍጥረት 31:38, 39
ክርስቲያን የበላይ ተመልካቾች የነፍሳችን እረኛ የሆነው ይሖዋ አምላክ ‘በገዛ ልጁ ደም ለዋጃቸው’ በጎች ከዚህ የላቀ አሳቢነት ያሳያሉ። (ሥራ 20:28 አዓት፤ 1 ጴጥሮስ 2:25፤ 5:4) ጳውሎስ በጉባኤ ውስጥ የመምራት ኃላፊነት ያላቸው ሰዎች “ስሌትን እንደሚሰጡ አድርገው፣ . . . ስለ ነፍሳችሁ ይተጋሉ” ብሎ የዕብራውያን ክርስቲያኖችን ባስታወሳቸው ጊዜ ይህን ከባድ ኃላፊነት ጐላ አድርጎ ገልጾታል። — ዕብራውያን 13:17
በተጨማሪም የያዕቆብ ምሳሌ የእረኛን ሥራ ጊዜ እንደማይወስነው ያሳያል። ሌት ተቀን መሥራትን አንዳንድ ጊዜም የራስን ጥቅም መሥዋዕት ማድረግን የሚጠይቅ ሥራ ነው። ያዕቆብ ለላባ “የቀን ሀሩር የሌሊት ቁር ይበላኝ ነበር፣ እንቅልፍም ከዓይኔ ጠፋ” ብሎት ነበር። — ዘፍጥረት 31:40
የሚከተለው ተሞክሮ እንደሚያሳየው ይህ ሁኔታ በዛሬው ጊዜ በብዙዎቹ አፍቃሪ ክርስቲያን ሽማግሌዎች ላይ ታይቷል። የአንጎሉ ውስጥ እባጭ (ብሬይን ቱመር) የወጣበት አንድ ወንድም ለምርመራ ሲባል ከእባጩ ጥቂት ክፍል መወሰዱ በሽታውን ስላባባሰበት ለሕሙማን ከፍተኛ ክትትል ወደሚደረግበት የአንድ ሆስፒታል ክፍል እንዲገባ ተደረገ። ቤተሰቦቹ በሆስፒታሉ ውስጥ ሌት ተቀን ከእርሱ ላለመለየት ሁኔታዎችን አመቻቹ። ከጉባኤው ሽማግሌዎች አንዱ አስፈላጊውን የሞራል ድጋፍና ማበረታቻ ለመስጠት በየዕለቱ የታመመውን ሰውና ቤተሰቡን መጠየቅ እንዲችል የተጣበበውን ፕሮግራሙን አስተካከለ። ነገር ግን ሆስፒታሉ ከፍተኛ ሕክምና ለመስጠት በሚያደርገው ክትትል የተነሣ ሁልጊዜ ቀን ቀን መጠየቅ አዳጋች ሆነበት። በዚህም ምክንያት ሽማግሌው አብዛኛውን ጊዜ ወደ ሆስፒታሉ መሸት ካለ በኋላ ለመሄድ ተገደደ። ሆኖም በየዕለቱ ማታ ማታ ደስ እያለው ይሄድ ነበር። “ለእኔ ምቹ በሆነ ጊዜ ሳይሆን ለበሽተኛው ተስማሚ በሆነ ጊዜ መጠየቅ እንዳለብኝ ተገንዝቤ ነበር” ሲል ሽማግሌው ተናገረ። ወንድም ወደ ሆስፒታሉ ሌላ ክፍል መዛወር በሚችልበት አስተማማኝ ሁኔታ ሲያገግምም ሽማግሌው በየዕለቱ በመጠየቅ ማበረታታቱን ቀጠለ።
ሙሴ ከእረኝነቱ ያገኘው ትምህርት
መጽሐፍ ቅዱስ ሙሴን “በምድር ላይ ካሉት ሰዎች ሁሉ ይልቅ እጅግ ትሑት [ገር አዓት] ነበር” ሲል ይገልጸዋል። (ዘኁልቁ 12:3) ይሁን እንጂ ተመዝግቦ የሚገኘው ታሪክ እንደሚያሳየው ይህ ከመጀመሪያው የነበረው ባሕሪው አልነበረም። በጉብዝናው ጊዜ መሰሉን እስራኤላዊ አንድ ግብጻዊ ሲመታው አይቶ ገድሎታል። (ዘጸአት 2:11, 12) ገር ሰው የወሰደው እርምጃ ነው ለማለት ያዳግታል! ይህም ሆኖ አምላክ ከጊዜ በኋላ ሙሴን በሚልዮን የሚቆጠርን ሕዝብ በምድረበዳ በኩል ወደ ተስፋይቱ ምድር ለመምራት ሊጠቀምበት ይፈልጋል። ስለሆነም ሙሴ ተጨማሪ ማሠልጠኛ ያስፈልገው እንደነበር በግልጽ መረዳት ይቻላል።
ምንም እንኳ ሙሴ “የግብጾችን ጥበብ ሁሉ” በመማር ዓለማዊ ማሠልጠኛ ያገኘ ቢሆንም የይሖዋን መንጋ እንደ እረኛ ሆኖ ለመምራት ከዚህ የበለጠ ነገር ያስፈልገው ነበር። (ሥራ 7:22) ይህ ተጨማሪ ማሠልጠኛ ምን ዓይነት መልክ ይኖረው ይሆን? አምላክ ሙሴ ለ40 ዓመታት በምድያም ምድር ዝቅተኛ እረኛ ሆኖ እንዲያገለግል አደረገ። ሙሴ የአማቹን የየትሮን መንጎች ይጠብቅ በነበረበት ጊዜ እንደ ትዕግሥት፣ ገርነት፣ ትሕትና፣ ሌላውን ችሎ መኖር፣ የዋህነትና ራስን መግዛት ያሉትን መልካም ባሕርያት አዳብሯል። ይሖዋን በተስፋ መጠባበቅንም ተምሯል። አዎ፣ ሙሴ ቃል በቃል በጎችን መጠበቁ ብቁ ችሎታ ያለው የእስራኤል ሕዝብ እረኛ እንዲሆን አስችሎታል። — ዘጸአት 2:15 እስከ 3:1፤ ሥራ 7:29, 30
በአሁኑ ጊዜ አንድ ሽማግሌ የአምላክን ሕዝብ ለመጠበቅ የሚያስፈልጉት ባሕርያት እነዚህ አይደሉምን? አዎን፣ ጳውሎስ ጢሞቴዎስን እንዲህ ሲል አሳስቦታል:- “የጌታም ባሪያ ለሰው ሁሉ ገር ለማስተማርም የሚበቃ ለትዕግሥትም የሚጸና ሊሆን ይገባዋል . . . የሚቃወሙትን በየዋህነት ይቅጣ።” — 2 ጢሞቴዎስ 2:24, 25
አንድ ሽማግሌ እነዚህን ባሕርያት ሙሉ በሙሉ ማሟላት ተስኖት በራሱ የሚያዝንበት ጊዜ ሊኖር ይችላል። ቢሆንም ተስፋ ቆርጦ ጥረቱን ማቆም አይገባውም። ልክ እንደ ሙሴ ሁሉ አንድ ሰው ጥሩ እረኛ ለመሆን እነዚህን ባሕርያት ሙሉ በሙሉ ማዳበር እንዲችል ረጅም ጊዜ ሊወስድበት ይችላል። ይሁን እንጂ እንዲህ ዓይነቱ በጽኑ መንፈስ የሚደረግ ጥረት ከጊዜ በኋላ የሚክስ ይሆናል። — 1 ጴጥሮስ 5:10
እንደሌሎቹ ሽማግሌዎች በብዙ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ተመድበህ አትሠራ ይሆናል። ልክ እንደ ሙሴ ይሖዋ አንዳንድ አስፈላጊ የሆኑ ባሕርያትን እንድታዳብር እያደረገ ሊሆን አይችልምን? ይሖዋ ‘እንደሚያስብልህ’ ፍጽሞ አትርሳ። ይሁን እንጂ ‘አምላክ ትዕቢተኞችን ስለሚቃወም ለትሑታን ግን የማይገባ ደግነት ስለሚያሳይ ትሕትናን የመልበሱን’ አስፈላጊነት በአእምሮአችን መያዝ ይኖርብናል። (1 ጴጥሮስ 5:5–7) በርትተህ ከሠራህና ይሖዋ የሚሰጥህን ማሠልጠኛ ከተቀበልክ ልክ እንደ ሙሴ ይበልጥ ሊጠቀምብህ ይችላል።
ሁሉም የይሖዋ በጎች ውድ ናቸው
በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የነበሩ ትምክህት የሚጣልባቸው አፍቃሪ እረኞች ለእያንዳንዱ በግ ኃላፊነት እንዳለባቸው ይሰማቸው ነበር። የመንፈሳዊ እረኞችም ሁኔታ ከዚህ የተለየ መሆን አይኖርበትም። ይህም “ለመንጋው ሁሉ . . . ተጠንቀቁ” ከሚሉት የጳውሎስ ቃላት በግልጽ መረዳት ይቻላል። (ሥራ 20:28) “ለመንጋው ሁሉ” በሚለው አነጋገር የሚጠቃለሉት እነማን ናቸው?
ኢየሱስ መቶ በጎች ሰላሉት ነገር ግን የባዘነበትን አንድ በግ ከመንጋው ጋር ለመቀላቀል ፍለጋ ስለሄደ ሰው አንድ ምሳሌ ሰጥቷል። (ማቴዎስ 18:12–14፤ ሉቃስ 15:3–7) በተመሳሳይም አንድ የበላይ ተመልካች ለእያንዳንዱ የጉባኤ አባል ማሰብ ይኖርበታል። አገልግሎትን ወይም በክርስቲያን ስብሰባዎች መገኘትን ማቆሙ በጉ የመንጋው አካል መሆኑ ቀርቷል ማለት አይደለም። ሽማግሌዎቹ ለይሖዋ ‘ስሌት የሚሰጡበት’ ‘የመንጋው ሁሉ’ አካል ሆኖ ይቀጥላል።
አንድ የሽማግሌዎች አካል ቀደም ሲል ከጉባኤው ጋር ግንኙነት የነበራቸው ከጊዜ በኋላ ግን የቀዘቀዙ ሰዎችን ጉዳይ አሰበበት። የእነዚህን ግለሰቦች ስም ዝርዝር ካዘጋጁ በኋላ እነርሱን ለማነጋገርና ወደ ይሖዋ በጎች በረት እንዲመለሱ ለመርዳት ልዩ ጥረት ተደረገ። ከሁለት ዓመት ተኩል በኋላ እነዚህ ሽማግሌዎች ከ30 በላይ የሚሆኑ ሰዎች በይሖዋ አገልግሎት እንደገና የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉ መርዳት በመቻላቸው አምላክን በጣም አመሰገኑት። በእዚህ መንገድ እርዳታ ከተደረገላቸው ከእነዚህ ሰዎች መካከል አንዱ ለ17 ዓመታት ያህል ቀዝቅዞ ነበር!
በጎቹ ‘በገዛ [በአምላክ] ልጁ ደም የተዋጁ’ መሆናቸው የበላይ ተመልካቾች ያለባቸውን ይህን ኃላፊነት የበለጠ ከባድ ያደርገዋል። (ሥራ 20:28 አዓት) ለእነዚህ ውድ በጎች ከዚህ የበለጠ ዋጋ ሊከፈል አይችልም። እያንዳንዱን በግ መሰል ሰው ፈልጎ ለማግኘት የሚጠፋውን ጊዜና ጉልበትም እስቲ አስብ! ሁሉም አምላክ ባዘጋጀው በረት ውስጥ መኖራቸውን እንዲቀጥሉ ተመሳሳይ ጥረት ማድረግ አይገባምን? በእርግጥም በጉባኤ ውስጥ ያለው እያንዳንዱ በግ በጣም ውድ ንብረት ነው።
አንድ የመንጋው አባል ከባድ ኃጢአት በሚፈጽምበት ጊዜም እንኳ የሽማግሌዎቹ ኃላፊነት አይለወጥም። አሳቢ እረኞች በመሆን ኃጢአተኛውን ለማዳን በጥንቃቄና በየውሃት የተቻላቸውን ያህል ጥረት ያደርጋሉ። (ገላትያ 6:1, 2) አንዳንድ ጊዜ እንደሚታየው አንድ የጉባኤ አባል ለሠራቸው ከባድ ኃጢአቶች አምላካዊ የሆነ ጸጸት አለማሳየቱ የሚያሳዝን ነው። እንግዲያው አፍቃሪ እረኞች የተቀረውን መንጋ ሊበክል ከሚችል ከዚህ ግፊት የመከላከል ቅዱስ ጽሑፋዊ ኃላፊነት አለባቸው። — 1 ቆሮንቶስ 5:3–7, 11–13
ሆኖም ይሖዋ አምላክ ለባዘኑ በጎች የምሕረት እጁን በመዘርጋት ፍጹም የሆነ ምሳሌ ትቶልናል። ሩህሩህ የሆነው እረኛችን እንዲህ ይላል:- “የጠፋውንም እፈልጋለሁ የባዘነውንም እመልሳለሁ የተሰበረውንም እጠግናለሁ የደከመውንም አጸናለሁ።” (ሕዝቅኤል 34:15, 16፤ ኤርምያስ 31:10) ይህን ግሩም ምሳሌ በመከተል በዘመናችን የሚገኙት መንፈሳዊ እረኞች ለሚያደርጉላቸው እርዳታ ጥሩ ምላሽ ሊያሳዩ የሚችሉ የተወገዱ ሰዎችን እንዲያነጋግሩ ፍቅራዊ የሆነ ዝግጅት ተደርጓል። እንዲህ የመሰሉትን የጠፉ በጎች ለመመለስ የሚደረጉት እነዚህ ምሕረት የተሞላባቸው ጥረቶች ጥሩ ፍሬ አፍርተዋል። ከውገዳ የተመለሰች አንዲት እኅት:- “ሽማግሌዎች መጥተው አነጋገሩኝ። ለመመለስም ያስፈልገኝ የነበረው አይዞሽ ባይነትም ይኸው ነበር” በማለት ተናግራለች።
ጳውሎስ በሚሊጢን ለኤፌሶን ሽማግሌዎች የተናገራቸው ቃላት ለእነርሱም ሆነ ዛሬ ላሉት የበላይ ተመልካቾች ብዙ ትርጉም የተሞሉ መሆናቸው ምንም አያጠራጥርም። እረኞችን በተመለከተ የተናገራቸው ቃላት በእረኛው ንጉሥ ዳዊት የታዩትን ትሕትናና ድፍረት፣ በያዕቆብ ሌት ተቀን አገልግሎት የተንጸባረቁትን በግል ኃላፊነት የመሰማትንና ከጥቃት የመከላከል ባሕርዮች እንዲሁም በሙሴ የታየውን ተጨማሪ ማሠልጠኛ በትዕግሥት ለመቀበል ፈቃደኛ መሆንን የመሰሉ የበላይ ተመልካቾች ሊያሳዩአቸው የሚገቡ ግሩም ባሕርያትን የሚያስታውሱ ናቸው። በእርግጥም እነዚህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምሳሌዎች የጉባኤ ሽማግሌዎች አስፈላጊ የሆኑትን ባሕርያት በማዳበርና በማሳየት “አምላክ በገዛ ልጁ ደም የዋጀውን ጉባኤ” በጥንቃቄ መጠበቅ እንዲችሉ ይረዷቸዋል።