በአቅኚነት አገልግሎት ጽኑ
በዓለም ዙሪያ 4,500,000 የሚያህሉ የይሖዋ ምስክሮች ምስራቹን እያወጁ ናቸው። ከእነዚህ መካከል ከ600,000 በላይ የሚሆኑት አቅኚዎች ወይም የሙሉ ጊዜ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ናቸው። በዚህ የአቅኚዎች ሠራዊት ውስጥ በአሥራዎቹ ዕድሜ መጀመሪያ ከሚገኙት አንስቶ በ90ዎቹ የጡረታ ዓመታት ውስጥ ያሉ የተለያዩ ሰዎች ይገኙበታል። ከሁሉም ዓይነት ሁኔታና የኑሮ ደረጃ የመጡ ናቸው።
እነዚህ ሁሉ የሙሉ ጊዜ ሰባኪዎች በአቅኚነት አገልግሎት ስኬታማ ለመሆን እንደሚፈልጉ አያጠራጥርም። ብዙዎቹ የዕድሜ ልክ ሥራቸው እንዲሆን ይመኛሉ። አንዳንዶች በተወሰኑ ምክንያቶች የተነሳ እንደዚያ ለማድረግ አልቻሉም። ሌሎች ደግሞ ገንዘብ ነክ የሆኑ ችግሮች፣ የጤና መታወክ፣ ተስፋ መቁረጥና ሌሎች ችግሮች ቢኖሩባቸውም በአቅኚነት መቀጠል ችለዋል። ታዲያ የሙሉ ጊዜ ሰባኪዎች እንዲህ ዓይነቶቹን ችግሮች መቋቋምና በአቅኚነት አገልግሎት ጸንተው መቀጠል የሚችሉት እንዴት ነው?
የሚያስፈልጋቸውን ገንዘብ ማግኘት
በጥቅሉ፣ አቅኚዎች ጳውሎስ ያደርግ እንደነበረው ወጪዎቻቸውን ለመሸፈን ሰብአዊ ሥራ ይሠራሉ። (1 ተሰሎንቄ 2:9) በአብዛኛው የዓለም ክፍል እየጨመረ የሄደው የምግብ፣ የልብስ፣ የመጠለያና የመጓጓዣ ዋጋ ንረት ያጋጥማቸዋል። የሚያስፈልጋቸውን የትርፍ ጊዜ ሰብአዊ ሥራ ማግኘቱ አስቸጋሪ ነው። እንዲህ ዓይነቶች ሥራዎች አይገኙም፤ ቢገኙም ብዙ ጊዜ ክፍያቸው በጣም አነስተኛ ከመሆኑም ሌላ የሕክምና ወጪን ለመሸፈን ምንም እርዳታ የማይሰጡ ናቸው።
‘ከሁሉ አስቀድመን የአምላክን መንግሥትና ጽድቁን ሳናቋርጥ የምንፈልግ’ ከሆነ ይሖዋ ቁሳዊ ፍላጎቶቻችንን እንደሚያሟላልን ልንተማመን እንችላለን። እንግዲያው አቅኚዎች ገንዘብ ነክ የሆኑ ችግሮች ሲደርሱባቸው ‘ለነገ መጨነቅ’ የለባቸውም። (ማቴዎስ 6:25–34) እንዲህ የመሰሉትን ችግሮች ለመፍታት ልባዊ የሆነ ጥረት ሲያደርጉ በይሖዋ ላይ ያላቸው እምነት ጭንቀቱን ያስወግደዋል።
አንድ ሰው ገንዘብ ነክ የሆኑ ችግሮች ሲያጋጥሙት ወጪዎችን መቀነስ ይችል ይሆናል። የፈለጉትን ሁሉ መግዛት ባይቻልም አንዳንድ የባጀት ለውጦችን በማድረግ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ማሟላት ይቻላል። አንዳንድ አቅኚዎች ወጪዎችን ለመቀነስ ከሌሎች ክርስቲያኖች ጋር ቤት ይከራያሉ። አንዳንድ ጊዜ ወላጆች ልጆቻቸው አቅኚ ሆነው እንዲሠሩ እቤታቸው ውስጥ በነፃ እንዲኖሩ ወይም በጣም ዝቅተኛ ገንዘብ እንዲከፍሉ በመጠየቅ አብረዋቸው እንዲኖሩ ይፈቅዱላቸዋል። ሌሎች ደግሞ በምግብና በመጓጓዣ ወጪዎች አቅኚዎችን ይረዷቸዋል። ሆኖም አቅኚዎች ራሳቸውን የመርዳት ቅዱስ ጽሑፋዊ ግዴታ ስላለባቸው የሌሎች ሸክም ለመሆን መፈለግ የለባቸውም። — 2 ተሰሎንቄ 3:10–12
ወጪዎችን ከሌሎች አቅኚዎች ጋር በመተጋገዝ ለመጓጓዣ የሚወጣውን ወጪ መቀነስ ይቻላል። ሁለት አቅኚዎች የየራሳቸው መኪና ቢኖራቸው አንድ መኪና ተጠቅመው በአንድ ቦታ ላይ የስብከቱን ሥራ በአንድነት በማከናወን ሁለት መኪናዎችን በመጠቀም ይወጣ የነበረውን ወጪ ማስቀረት ይችላሉ። መኪና የሌላቸው አቅኚዎች የመጓጓዣ ወጪዎችን በቡድን ከሚሸፍኑት ጋር መቀናጀት ይችሉ ይሆናል። በአቅራቢያ በሚገኙ ክልሎች አብዛኛውን ጊዜ በእግር በመጓዝ የጉዞ ወጪዎችን የበለጠ መቀነስ ይቻላል። በብዙ አገሮች አቅኚዎች ቀላል ክፍያ በሚጠይቁ የሕዝብ መጓጓዣዎች ይጠቀማሉ።
ገንዘብ ነክ ችግሮችን ከተቋቋሙትና በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ከጸኑት መካከል ኒውተን ካንትዌልና ሚስቱ ይገኙበታል። ኢኮኖሚው በደቀቀበትና ሥራ አጥነትና ድህነት በተስፋፋበት በ1932 የእርሻ መሬታቸውን ሸጡና ከሰባቱ ልጆቻቸው መካከል ከስድስቱ ጋር አቅኚ ሆነው ማገልገል ጀመሩ። “የእርሻ መሬታችንን ሸጠን ያገኘነው በሙሉ ብዙም ሳይቆይ በአብዛኛው ለሐኪሞች በሰጠነው ክፍያ አለቀ” በማለት ወንድም ካንትዌል ጽፏል። “ወደሚቀጥለው የሥራ ምድባችን ስንዛወር የሁለት ሳምንት የቤት ኪራይ በቅድሚያ ለመክፈል የሚበቃ ገንዘብ አውጥተን አምስት ዶላር ብቻ ቀርቶን እንደነበረ እናስታውሳለን። የሆነ ሆኖ አገልግሎታችንን በትጋት እስከፈጸምን ድረስ ይሖዋ የሚያስፈልገንን እንደሚሰጠን እናውቅ ነበር . . . በተለያዩ መንገዶች እየቆጠቡ መኖር ተምረናል። ለምሳሌ ወደ አዲስ ክልል ስንዛወር የተወሰኑ የነዳጅ ማደያ ባለቤቶችን በማነጋገር ከክርስቲያናዊ ሥራ ጋር በተያያዘ ሁኔታ በየቀኑ ሦስት መኪና እንደምንጠቀም ገልጬላቸዋለሁ። ይህም አብዛኛውን ጊዜ ቤንዚን በቅናሽ ዋጋ እንድናገኝ አስችሎናል። ወንዶች ልጆቻችን መኪና መጠገንን ተማሩ፤ ይህም ለመኪና ጥገና ብዙ ወጪ ከማውጣት አድኖናል።” በዚህ መንገድ የካንትዌል ቤተሰቦች ገንዘብ ነክ የሆኑ ችግሮችን ስኬታማ በሆነ መንገድ ተቋቁመዋል፤ እንዲሁም በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ጸንተዋል። ወንድም ካንትዌል በ103 ዓመቱ እስከሞተበት ጊዜ ድረስ አቅኚ ሆኖ ያገለግል ነበር።
የከፊል ጊዜ ሥራ ማግኘት
ብዙ አቅኚዎች የከፊል ጊዜ ሥራ በመሥራት ገንዘብ ነክ በሆኑ ጉዳዮች ራሳቸውን ይችላሉ። ጳውሎስ በቆሮንቶስ አገልግሎቱ ራሱን ለመቻል መሰል አማኞች ከሆኑት ከአቂላና ከጵርስቅላ ጋር ድንኳን ሰፊ ሆኖ ይሥራ ነበር። (ሥራ 18:1–11) በጊዜያችን ብዙውን ጊዜ መንፈሳዊ ወንድሞች ለአቅኚዎች የከፊል ጊዜ ሰብአዊ ሥራ ቢሰጧቸው ደስ ይላቸዋል። ሌሎች አቅኚዎች ጊዜያዊ ሥራ በሚያስገኙ አስቀጣሪ ድርጅቶች በኩል እንዲህ ዓይነቱን ሥራ ያገኛሉ። በአምላክ መተማመንና ሥራን በተመለከተ ለምናደርጋቸው ውሳኔዎች የእርሱን መመሪያ ለማግኘት ከልብ መጸለይ በጣም አስፈላጊ ነው። — ምሳሌ 15:29
አንድ አቅኚ እንዲህ ብሏል:- “በጸሎት አስቤበት ከፍተኛ ብርታት ካገኘሁ በኋላ የአገልጋይነት ሥራ ከባድ የግል ኃላፊነት ስለሆነ የሙሉ ቀን ሥራውን ልቀበለው እንደማልችል ለአለቃዬ ነገርኩት። በሚቀጥለው ረቡዕ ሥራውን ከከፊል ጊዜ ሥራ አንጻር እንደገና እንዳስብበት የቀረበልኝን ጥያቄ በደስታ ተቀበልኩት።” የጸሎትን ኃይል አቅልላችሁ አትመልከቱት፤ እንዲሁም ከጸሎታችሁ ጋር የሚስማማ ሥራ ሥሩ።
አቅኚዎች ሊቀጥሯቸው ላሰቡት ሰዎች የከፊል ጊዜ ሥራ የፈለጉበት ዓላማ በአገልግሎት ራሳቸውን ለመደገፍ እንደሆነ ቢነግሯቸው የተሻለ ሆኖ ሊያገኙት ይችላሉ። የሚሰሩባቸውን ቀኖችና በሳምንት በሥራው ላይ ምን ያህል ሰዓት ማሳለፍ እንደሚችሉ ሊጠቅሱ ይችሉ ይሆናል። ሁለት ሥጋዊ እህትማማቾች በአንድ የጠበቆች መሥሪያ ቤት እያንዳንዳቸው በሳምንት ውስጥ ሁለት ቀን ተኩል መሥራት በሚችሉበት ሁኔታ ሥራውን ተካፈሉት። ይህም የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስ የጊሊያድ ትምህርት ቤት ውስጥ እስከገቡና የሚስዮናዊ ምድብ ሥራቸውን እስከተቀበሉበት ጊዜ ድረስ አቅኚ ሆነው እንዲቀጥሉ ረድቷቸዋል።
ከመሰል አማኞችና ከሌሎች ጋር በመነጋገር ወይም የጋዜጣ ማስታወቂያዎችን በመመልከት ቅዱስ ጽሑፋዊ ተቀባይነት ያላቸው የተለያዩ ዓይነት ሥራዎች ማግኘት ይቻላል። አቅኚዎች የሚሠሩትን ሥራ በተመለከተ ከመጠን በላይ መራጮች እንዳይሆኑ ትህትና ሊረዳቸው ይችላል። (ከያዕቆብ 4:10 ጋር አወዳድር።) በአቅኚነት ለመቀጠል አንዳንድ ሰዎች ዝቅተኛ ወይም ተራ አድርገው የሚመለከቱአቸውን ሰብአዊ ሥራዎች መሥራት ሊያስፈልጋቸው ይችላል። እንዲህ ዓይነቱን ሥራ መቀበል ብትችሉም ሌላ ሥራ መለወጥ ካስፈለገ ግን ከጊዜ በኋላ የሥራ ለውጥ ማድረግ ይቻል ይሆናል።
የጤና መታወክና ተስፋ መቁረጥ
አንዳንዶች ከባድ በሆኑ የጤና እክሎች ምክንያት የአቅኚነት አገልግሎታቸውን ለማቋረጥ ተገደዋል። ሆኖም አቅኚዎች በዚህ ረገድ ካልተቻኮሉ በሽታው ፈውስ ሊያገኝ ወይም ጤንነታቸው ተሻሽሎ በአቅኚነት መቀጠል የሚቻል ሆኖ ሊያገኙት ይችላሉ። ብዙዎች የጤና እክሎች ቢኖሩባቸውም ሕክምና በማግኘታቸው፣ የሚስማማቸውን ምግብ እየመረጡ ዘወትር በመመገባቸውና አስፈላጊውን አካላዊ እንቅስቃሴ በማድረጋቸውና እረፍት በመውሰዳቸው አቅኚ ሆነው መቀጠል ችለዋል። አንድ ተጓዥ የበላይ ተመልካች በአርትራይትስ በሽታ በጣም የምትሰቃይና ለአገልግሎት ከቤት ወደ ቤት ለመሄድ እርዳታ ያስፈለጋትን አንዲት እህት ተመልክቶ ነበር። (ሥራ 20:20) ያም ሆኖ እርሷና ባልዋ 33 የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን መርተዋል፤ 83 ሰዎች የአምላክን እውነት እንዲቀበሉ ረድተዋል። ውሎ አድሮ ግን ጤንነቷ ተሻሻለና ከ11 ዓመት በኋላ የአቅኚነት አገልግሎት ትምህርት ቤት ተካፈለች።
አንዳንዶች የአቅኚነት አገልግሎትን እንዲተዉ ተስፋ መቁረጥ ምክንያት ሊሆናቸው ይችላል። (ምሳሌ 24:10) አንድ አቅኚ ለአንድ ተጓዥ የበላይ ተመልካች “መክፈል ያለብኝ ዕዳ ስላለ አቅኜ ሆኜ ማገልገሌን ላቆም ነው።” ብሎ ነገረው። 20 ዶላር የሚያወጣ መነጽር አስፈልጎት ነበር። “20 ዶላር ስላስፈለገህ አቅኚ ሆነህ ማገልገልህን ልታቋርጥ ነው?” ሲል የበላይ ተመልካቹ ጠየቀው። በአካባቢው በሚገኝ የቡና እርሻ ውስጥ ለአንድ ቀን በመሥራት 20 ዶላር አግኝቶ መነጽሩን እንዲገዛና በአቅኚነት እንዲቀጥል ሐሳብ ቀረበለት። በተደረገው ተጨማሪ የሐሳብ ልውውጥ ለተስፋ መቁረጡ ዋነኛው መንስኤ መኪናውን ለማሠራት ብዙ ገንዘብ ማውጣቱ እንደነበረ ታወቀ። ረጅም ጉዞ ከሚያደርግ ይልቅ በቀኑ የተወሰኑ ኪሎ ሜትሮችን በመጓዝ ወጪውን መቀነስ እንደሚችል አቅኚው ሐሳብ ቀረበለት። መንፈሳዊነቱንም በሚገባ እንዲጠብቅ ምክር ተሰጠው። አቅኚው ምክሩን በሥራ አዋለና ከስድስት ወራት በኋላ በጊሊያድ ትምህርት ቤት እንዲካፈል ጥሪ ቀረበለትና ሄደ። ከምረቃ በኋላ ወደ ውጪ አገር ተመድቦ እስከሞተበት ጊዜ ድረስ ለብዙ ዓመታት የታመነ ሆኖ አገልግሏል። አዎን፤ ለተስፋ መቁረጥ እጃችንን ከመስጠት ይልቅ ይሖዋ ከእኛ ጋር መሆኑን በአእምሮአችን ከያዝን ብዙውን ጊዜ በውጤቱ ታላላቅ በረከቶች ይገኛሉ።
የአገልግሎት መብታችሁን እንደ ውድ ሀብት አድርጋችሁ ያዙ
ጳውሎስ ማጣትንና ራብን በመሰሉ ሁኔታዎች ቢፈተንም አገልግሎቱን እንደ ውድ ሀብት አድርጎ ተመልክቷል። (2 ቆሮንቶስ 4:7፤ 6:3–6) በጊዜያችን በአፍሪካ፣ በእስያ፣ በምስራቅ አውሮፓና በሌሎችም ቦታዎች የሚገኙ ብዙ የይሖዋ አገልጋዮች መከራና ስደት ቢያጋጥማቸውም አቅኚ ሆኖ የማገልገል መብታቸውን አጥብቀው ይዘዋል። ስለዚህ ፈተናዎች ሲያጋጥሟችሁ ለይሖዋ ምስጋና የሚያመጣ እንዲሆን በዚህ ውድ አገልግሎት ለመጽናት ማንኛውንም ጥረት አድርጉ።
አብዛኛዎቹ አቅኚዎች አኗኗራቸውን ቀላል በማድረጋቸው ብቻ ወደ ሙሉ ጊዜ የስብከት ሥራ መግባት ችለዋል። ልክ እንደ ጳውሎስ በቁሳዊ ማባበያዎች ባለመታለል ‘በምግብና በልብስ’ የመርካትን ጠባይ ኮትኩተዋል። በአቅኚነት አገልግሎት መጽናት እንዲችሉ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች በማግኘታቸው ረክተው መኖር ያስፈልጋቸዋል። (1 ጢሞቴዎስ 6:8) ደስታ የሚገኘው አምላክ የሰጠንን መብቶች ከቁሳዊ ሀብቶች አስበልጠን እንደ ውድ ሀብት በመያዝ ነው።
በምሳሌ ለማስረዳት:- አንቶን ኮርበር በዋሽንግተን ዲ ሲ ውስጥ በመንግሥት ባለ ሥልጣኖች ፊት የመንግሥቱን ጥቅሞች የሚያራምድ ሆኖ ለመቅረብ ልዩ አጋጣሚ አግኝቶ ነበር። ለተወሰነ ጊዜ አቅኚ ሆኖ ያገለገለ ሲሆን በ1950ዎቹ ደግሞ የክልል የበላይ ተመልካች ነበር። ከቀድሞ የሥራ ባልደረቦቹ መካከል አንዳንዶቹ አንድ ሚሊዩን ዶላር የተጣራ ገንዘብ ሊያስገኝለት የሚችል ሥራ እንዲሠራ ሐሳብ አቅርበውለት ነበር። ይሁን እንጂ ይህ እንዲሆን ለአንድ ዓመት ያህል ጊዜውን በሙሉ ለሥራ ጉዳዮች ማዋል ያስፈልገው ነበር። መመሪያንና የጤናማ አእምሮን መንፈስ ለማግኘት ከጸለየ በኋላ እንዲህ ብሏል:- “በዚህ ቦታ ይሖዋን የማገልገል ግሩም የሆኑ መብቶች ለአንድ ዓመት ብቻም እንኳን ማጣት አይቻለኝም፤ በፍጹም አላደርገውም፤ በዓለም ውስጥ በሚገኘው ገንዘብም እንኳን አልለውጠውም። እዚህ ዋሽንግተን ያሉትን ወንድሞቼን ማገልገል ይበልጥብኛል፤ የይሖዋ በረከትም ከእኔ ጋር እንደሆነ አውቃለሁ። አንድ ሚሊዮን ዶላር ማግኘት እንደምችል ምንም አልጠራጠርም፤ ሆኖም ይህን ዓይነቱን ሕይወት ካሳለፍኩ በኋላ በዓመቱ መጨረሻ ላይ በአካላዊም ሆነ በመንፈሳዊ ምን ዓይነት ሁኔታ ላይ እገኝ ይሆን?” ስለዚህ የቀረበለትን ሐሳብ ሳይቀበለው ቀረ። ብዙዎች ያገኟቸውን መብቶች ተመሳሳይ በሆነ መንገድ እንደ ውድ ሀብት አድርገው በመያዛቸው በአቅኚነት አገልግሎት መጽናት እንዲችሉ ረድቷቸዋል።
አቅኚዎች እንዴት ያሉ ታላላቅ በረከቶች ያገኛሉ! ስለ ክብራማው የይሖዋ ንግሥና በመናገር ብዙ ሰዓታት ማሳለፍ በረከት ነው። (መዝሙር 145:11–13) አቅኚዎች በአገልግሎት ረጅም ጊዜ ለማሳለፍ ስለሚችሉ ለድሆች፣ ለተጨቆኑት፤ ለታመሙት ወይም ዘመድ ለሞተባቸው እንዲሁም ከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ ላሉትና አስተማማኝ ተስፋ ለሚሹት መንፈሳዊ መጽናኛ የመስጠት ልዩ አጋጣሚ አላቸው። ስለዚህም በሙሉ ጊዜ የስብከቱ ሥራ ለመካፈል ሁኔታዎች የሚፈቅዱልን ከሆነ በእርግጥም ብዙ በረከቶች እናገኛለን። ‘ባለጠጋ የሚያደርግ የይሖዋ በረከት ነው።’ (ምሳሌ 10:22) ቁጥራቸው የበዛው የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎችም በአቅኚነት አገልግሎት እየተደሰቱ መጽናት የቻሉት በእርሱ እርዳታና በረከት ነው።