የአንባብያን ጥያቄዎች
ሐዋርያው ጳውሎስ በሮሜ 9:3 ላይ:- “በሥጋ ዘመዶቼ ስለሆኑ ስለ ወንድሞቼ ከክርስቶስ ተለይቼ እኔ ራሴ የተረገምሁ እንድሆን እጸልይ ነበርና” ሲል ጽፏል። መሰል አይሁዳውያንን ለማዳን ሕይወቱን ለመሰዋት ፈቃደኛ ይሆን ነበር ማለቱ ነውን?
ኢየሱስ ከሁሉ የላቀውን የፍቅር ምሳሌ ትቶልናል። ለኃጢአተኛው የሰው ዘር ነፍሱን ወይም ሕይወቱን አሳልፎ ለመስጠት ፈቃደኛ ነበር። ለሕዝብ ባደረገው አገልግሎቱ ብዙዎቹ ከእርሱ ቤዛዊ መሥዋዕት እንዲጠቀሙ ሲል የአገሩ ሰዎች ለሆኑት አይሁዳውያን በጣም ደክሟል። (ማርቆስ 6:30–34) መዳንን ለሚያስገኘው መልዕክት ያሳዩት ቸልተኝነትና ተቃውሞ ኢየሱስ ለአይሁዶች ያለውን ፍቅራዊ አሳቢነት አልቀነሰበትም። (ማቴዎስ 23:37) ‘ፍለጋውንም እንድንከተል ምሳሌ ትቶልናል።’ — 1 ጴጥሮስ 2:21
ፍጹማን ያልሆኑ ሰዎች የኢየሱስን የፍቅር ምሳሌ መከተል ይችላሉን? አዎን፤ የሐዋርያው ጳውሎስን ሁኔታ እንደ ማስረጃ አድርገን መጥቀስ እንችላለን። ለመሰል አይሁዳውያን በጣም ያስብላቸው ስለነበር ለእነርሱ ካለው ፍቅር የተነሳ ስለ እነርሱ “ከክርስቶስ ተለይቼ እኔ ራሴ የተረገምሁ እንድሆን” እፈልጋለሁ ሲል ተናግሯል።
ጳውሎስ እዚህ ቦታ ላይ ነጥቡን በግልጽ ለማስቀመጥ በአድናቆት ወይም በማጋነን አነጋገር ተጠቅሟል። ኢየሱስ ተመሳሳይ በሆነ የማጋነን አነጋገር ተጠቅሞ በማቴዎስ 5:18 ላይ:- “እውነት እላችኋለሁ፣ ሰማይና ምድር እስኪያልፍ ድረስ፣ ከሕግ አንዲት የውጣ ወይም አንዲት ነጥብ ከቶ አታልፍም፣ ሁሉ እስኪፈጸም ድረስ” ብሏል። ኢየሱስ ሰማይና ምድር እንደማያልፉ ያውቅ ነበር። ጳውሎስም የተረገመ አይሆንም፤ ሁሉም አይሁዳውያንም ክርስትናን እንደማይቀበሉ የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ ጳውሎስ ለመግለጽ የፈለገው ነጥብ አይሁዳውያን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በአምላክ በሚገኘው መዳን እንዲጠቀሙ ለመርዳት ማንኛውንም ነገር ከማድረግ ወደ ኋላ አልልም የሚል ነው። ሐዋርያው መሰል ክርስቲያኖችን:- “እኔ ክርስቶስን እንደምመስል እኔን ምሰሉ” በማለት ሊያበረታታቸው መቻሉ ምንም አያስደንቅም። — 1 ቆሮንቶስ 11:1
ዛሬም ክርስቲያኖች ኢየሱስና ጳውሎስ ለማያምኑ ሰዎች የነበራቸው ዓይነት አሳቢነት ሊኖራቸው ይገባል። ምስክርነት በምንሰጥበት የአገልግሎት ክልላችን ውስጥ ያሉት ሰዎች ፍላጎት የሌላቸው መሆኑ ወይም ቀጥተኛ ተቃውሞ ማሳየታቸው ለጎረቤቶቻቸን ያለንን ፍቅርና የመዳንን መንገድ እንዲያውቁ ለመርዳት ያለንን ቅንዓት እንዲቀንስብን በፍጹም መፍቀድ አይገባንም። — ማቴዎስ 22:39