“በመማፀኛው ከተማ” ውስጥ ቆይተህ ሕይወትህን አድን!
‘ሊቀ ካህኑ እስኪሞት ድረስ በመማፀኛው ከተማ ውስጥ መቀመጥ ይኖርበታል።’—ዘኁልቁ 35:28 አዓት
1. ደም ተበቃዩ ማን ነው? በቅርቡ ምን እርምጃ ይወስዳል?
ይሖዋ የሾመው ደም ተበቃይ ማለትም ኢየሱስ ክርስቶስ እርምጃ ሊወስድ ነው። በቅርቡ ይህ ተበቃይ ከመላእክታዊ ኃይሎች ጋር በመሆን ንስሐ በማይገቡ የደም ባለ ዕዳዎች ላይ እርምጃ ይወስዳል። አዎን፣ ኢየሱስ በፍጥነት እየቀረበ ባለው “ታላቅ መከራ” ወቅት የአምላክ ፍርድ አስፈጻሚ ሆኖ ያገለግላል። (ማቴዎስ 24:21, 22፤ ኢሳይያስ 26:21) በዚያን ጊዜ የሰው ልጆች ያለባቸው የደም ዕዳ ከሚያስከትልባቸው መዘዝ አያመልጡም።
2. ብቸኛው እውነተኛ የመማፀኛ ቦታ የትኛው ነው? ምላሽ ማግኘት የሚያስፈልጋቸው ጥያቄዎች የትኞቹ ናቸው?
2 መዳን የሚቻለው ወደ ታላቁ የመማፀኛ ከተማ የሚወስደውን መንገድ ይዞ ሕይወትን ለማዳን በመሸሽ ነው! አንድ ስደተኛ ወደ ከተማው እንዲገባ ከተፈቀደለት እዚያው መቆየት ይኖርበታል፤ እውነተኛ የመማፀኛ ከተማ ይኸው ብቻ ነው። ይሁን እንጂ ‘አብዛኞቻችን ሰው ገድለን ስለማናውቅ እንዴት የደም ዕዳ ሊኖርብን ይችላል? ኢየሱስ ደም ተበቃይ የሆነው ለምንድን ነው? ዘመናዊው የመማፀኛ ከተማ ምንድን ነው? አንድ ሰው ይህን ከተማ ለቆ መውጣቱ የሚያስከትልበት ችግር ይኖራልን?’ በማለት ትጠይቅ ይሆናል።
በእርግጥ የደም ዕዳ አለብንን?
3. በምድር ላይ የሚኖሩ በቢልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በደም ዕዳ ተጠያቂ እንደ ሆኑ የሚያሳይ በሙሴ የተጠቀሰ ምን ነገር አለ?
3 በምድር ላይ የሚኖሩ በቢልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በደም ዕዳ ተጠያቂ መሆናቸውን የሚያሳይ በሙሴ ሕግ ውስጥ የተጠቀሰ አንድ ነገር አለ። እስራኤላውያን በጋራ በአምላክ ፊት በደም ዕዳ ተጠያቂ የሚሆኑበት ጊዜ ነበር። አንድ ሰው ተገድሎ ከተገኘና ገዳዩ ካልታወቀ ዳኞች ግድያው ለተፈጸመበት አካባቢ ቅርብ የሆነውን ከተማ ለማወቅ በአካባቢው የሚገኙትን ከተሞች ርቀት ይለካሉ። በደም ዕዳ ተጠያቂ ናት የተባለችው የዚህች ከተማ ሽማግሌዎች ከደም ዕዳ ነፃ ለመሆን የአንዲትን ለሥራ ያልደረሰች ጊደር አንገት ባልታረሰ ሸለቆ ውስጥ ይሰብራሉ። ‘ይሖዋ በእነርሱ ቃል ክርክር ሁሉ ጉዳትም እንዲቆረጥ ስለመረጣቸው’ ይህ የሚደረገው በሌዋውያን ካህናት ፊት ነው። የከተማዋ ሽማግሌዎች እጃቸውን በጊደሪቱ ላይ ከታጠቡ በኋላ እንዲህ ይላሉ፦ “እጃችን ይህን ደም አላፈሰሰችም፣ ዓይናችንም አላየችም፤ አቤቱ፣ የተቤዠኸውን ሕዝብህን እስራኤልን ይቅር በል፤ በሕዝብህም በእስራኤል ላይ የንጹሑን ደም በደል አትቁጠር።” (ዘዳግም 21:1–9) ይሖዋ አምላክ የእስራኤል ምድር በደም እንዲበከል ወይም ሕዝቦቿ በጋራ በደም ዕዳ ተጠያቂዎች እንዲሆኑ አልፈለገም።
4. ታላቂቱ ባቢሎን በደም ዕዳ ተጠያቂ የሚያደርጋት ምን ነገር ፈጽማለች?
4 አዎን፣ በጋራ ወይም በማኅበረሰብ ደረጃ የደም ባለ ዕዳ የመሆን ጉዳይም አለ። የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ግዛት በሆነችው በታላቂቱ ባቢሎን ላይ የተከመረባትን የደም ዕዳ እንውሰድ። በይሖዋ አገልጋዮች ደም ሰክራለች! (ራእይ 17:5, 6፤ 18:24) የሕዝበ ክርስትና ሃይማኖቶች የሰላሙን መስፍን እንከተላለን ቢሉም ጦርነቶች፣ ሃይማኖታዊ ኢንኩዊዚሽኖችና ብዙ ሕዝብ ያለቁባቸው የመስቀል ጦርነቶች በአምላክ ፊት በደም ዕዳ እንዲጠየቁ አድርጓቸዋል። (ኢሳይያስ 9:6፤ ኤርምያስ 2:34) እንዲያውም ሕዝበ ክርስትና በዚህ መቶ ዘመን በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ላለቁባቸው ሁለት የዓለም ጦርነቶች ዋነኛ ተጠያቂ ናት። ስለዚህ የሐሰት ሃይማኖት ተከታዮችም ሆኑ ሰብዓዊ ጦርነቶችን የሚደግፉና በእነዚህ ጦርነቶች የሚሳተፉ ሰዎች በአምላክ ፊት በደም ዕዳ ይጠየቃሉ።
5. አንዳንድ ሰዎች በእስራኤል ውስጥ እንደ ነበሩት በስሕተት ነፍስ የገደሉ ሰዎች የሆኑት እንዴት ነው?
5 አንዳንድ ሰዎች ሆን ብለው ወይም በጥንቃቄ ጉድለት ሰዎችን ለሞት ዳርገዋል። ሌሎች የጅምላ ጭፍጨፋ ፈጽመዋል፤ ምናልባት ይህን ያደረጉት ሃይማኖታዊ መሪዎች ይህ የአምላክ ፈቃድ ነው ብለው ስላሳመኗቸው ሊሆን ይችላል። ሌሎች ደግሞ የአምላክ አገልጋዮችን አሳደዋል እንዲሁም ገድለዋል። እኛ እነዚህን ነገሮች ባንፈጽምም እንኳ ቀደም ሲል የአምላክን ሕግና ፈቃድ የማናውቅ ሰዎች ስለ ነበርን ለጠፋው የሰው ሕይወት ማኅበረሰባዊ ተጠያቂነት አለብን። ‘ጠላቱ ሳይሆን ባልንጀራውን ሳያስበው እንደ ገደለው’ ነፍሰ ገዳይ እንሆናለን። (ዘዳግም 19:4) እንደነዚህ ያሉት ግለሰቦች የአምላክን ምሕረት አጥብቀው መለመንና ወደ ታላቁ መማፀኛ ከተማ መሸሽ ይኖርባቸዋል። ይህን ካላደረጉ ደም ተበቃዩ አግኝቶ ይገድላቸዋል።
ኢየሱስ የሚጫወታቸው ወሳኝ ሚናዎች
6. ኢየሱስ የሰው ልጆች የቅርብ ዘመድ ነው ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው?
6 በእስራኤል ውስጥ ደም ተበቃዩ የሟቹ የቅርብ ዘመድ ነበር። በምድር ላይ የተገደሉትን ሰዎች በሙሉ በተለይም የተገደሉትን የይሖዋ አገልጋዮች ደም የሚበቀለው የዘመናችን ደም ተበቃይ የመላው የሰው ልጆች ዘመድ መሆን ይኖርበታል። ይህን ሚና የሚጫወተው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ፍጹም ሰው ሆኖ ተወልዷል። ኢየሱስ ኃጢአት የሌለበት ሕይወቱን በሞት ቤዛዊ መሥዋዕት አድርጎ ሰጥቷል። ከትንሣኤው በኋላም ወደ ሰማይ አርጎ ሟች ለሆኑት የአዳም ኃጢአተኛ ዘሮች የከፈለውን የቤዛዊ መሥዋዕቱን ዋጋ ለአምላክ አቅርቧል። በዚህ መንገድ የቅርብ ዘመዳችን የሆነው ክርስቶስ የሰውን ዘር በመቤዠት ደም ተበቃይ የመሆን መብት አግኝቷል። (ሮሜ 5:12፤ 6:23፤ ዕብራውያን 10:12) ኢየሱስ ኮቴውን ለሚከተሉት ቅቡዓን ወንድም እንደሆነ ተገልጿል። (ማቴዎስ 25:40, 45፤ ዕብራውያን 2:11–17) ሰማያዊ ንጉሥ እንደ መሆኑ መጠን ከመሥዋዕቱ ለሚጠቀሙ ምድራዊ ተገዢዎቹ “የዘላለም አባት” ይሆንላቸዋል። እነዚህ ሰዎች ለዘላለም ይኖራሉ። (ኢሳይያስ 9:6, 7) ስለዚህ ይሖዋ ይህን የሰው ልጆች ዘመድ ደም ተበቃይ አድርጎ መሾሙ ተገቢ ነው።
7. ኢየሱስ ታላቅ ሊቀ ካህን እንደ መሆኑ መጠን ለሰው ልጆች ምን ያደርግላቸዋል?
7 በተጨማሪም ኢየሱስ ኃጢአት የሌለበት፣ የተፈተነና ሩኅሩኅ ሊቀ ካህን ነው። (ዕብራውያን 4:15) በዚህ ሥልጣኑ የሰው ልጆች ኃጢአት ከሚያስተሰርየው መሥዋዕቱ ጥቅም እንዲያገኙ ያደርጋል። የመማፀኛ ከተሞች የተቋቋሙት “ለእስራኤል ልጆች በመካከላቸው ለሚቀመጡ እንግዶችና መጻተኞች” ነው። (ዘኁልቁ 35:15) ስለዚህ ታላቁ ሊቀ ካህን በመጀመሪያ “የእስራኤል ልጆች” የሆኑት ቅቡዓን ተከታዮቹ ከመሥዋዕቱ ዋጋ እንዲጠቀሙ አድርጓል። በአሁኑ ጊዜ ደግሞ በታላቁ የመማፀኛ ከተማ ውስጥ ያሉት “እንግዶችና መጻተኞች” በመሥዋዕቱ ዋጋ እንዲጠቀሙ እያደረገ ነው። እነዚህ የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ “ሌሎች በጎች” በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ አላቸው።—ዮሐንስ 10:16፤ መዝሙር 37:29, 34
በአሁኑ ጊዜ ያለው የመማፀኛ ከተማ
8. ታላቁ የመማፀኛ ከተማ ምንድን ነው?
8 ታላቁ የመማፀኛ ከተማ ምንድን ነው? ከስድስቱ የሌዋውያን የመማፀኛ ከተሞች አንዷ የሆነችውንና የእስራኤል ሊቀ ካህን መኖሪያ የነበረችው ኬብሮንን የመሰለ በአንድ አካባቢ የሚገኝ ቦታ አይደለም። በአሁኑ ጊዜ ያለው የመማፀኛ ከተማ አምላክ ስለ ደም ቅድስና ያወጣውን ትእዛዝ በመጣሳችን ምክንያት ከሚመጣብን ሞት የሚጠብቀን የአምላክ ዝግጅት ነው። (ዘፍጥረት 9:6) ሆን ብሎም ሆነ ሳያውቅ ይህን ትእዛዝ የጣሰ ግለሰብ ሁሉ የአምላክን ይቅርታ መለመንና በሊቀ ካህኑ በኢየሱስ ክርስቶስ ደም በማመን ኃጢአቱ እንዲደመሰስለት ማድረግ ይኖርበታል። ሰማያዊ ተስፋ ያላቸው ቅቡዓን ክርስቲያኖችና ምድራዊ በረከቶች የሚያገኙት “እጅግ ብዙ ሰዎች” ኃጢአት የሚያስተሰርየው የኢየሱስ መሥዋዕት ከሚያስገኛቸው ጥቅሞች ለመቋደስ ራሳቸውን ዝግጁ አድርገው ስላቀረቡ በታላቁ የመማፀኛ ከተማ ውስጥ ይገኛሉ።—ራእይ 7:9, 14፤ 1 ዮሐንስ 1:7፤ 2:1, 2
9. የጠርሴሱ ሳውል አምላክ ስለ ደም የሰጠውን ሕግ የጣሰው እንዴት ነበር? ሆኖም አመለካከቱን እንደለወጠ ያሳየው እንዴት ነው?
9 ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቲያን ከመሆኑ በፊት ስለ ደም የወጣውን ትእዛዝ ጥሶ ነበር። የጠርሴሱ ሳውል ይባል በነበረበት ወቅት የኢየሱስን ተከታዮች ከማሳደዱም በላይ እነርሱ ሲገደሉ ተባባሪ ሆኖ ነበር። ጳውሎስ “ነገር ግን ሳላውቅ ባለማመን ስላደረግሁት ምሕረትን አገኘሁ” ብሏል። (1 ጢሞቴዎስ 1:13፤ ሥራ 9:1–19) ሳውል በኋላ ባደረጋቸው የእምነት ሥራዎች እንደ ተረጋገጠው የንስሐ ዝንባሌ ነበረው። ይሁን እንጂ ወደ ታላቁ የመማፀኛ ከተማ ለመግባት በቤዛው ከማመንም በተጨማሪ የሚያስፈልግ ነገር አለ።
10. በጎ ሕሊና ማግኘት የሚቻለው እንዴት ነው? በጎ ሕሊና ይዞ ለመኖር ምን ማድረግ ያስፈልጋል?
10 በስሕተት ነፍስ የገደለ አንድ ግለሰብ ከእስራኤል የመማፀኛ ከተሞች በአንዱ ውስጥ መቆየት ይችል የነበረው የሰውን ደም በማፍሰስ ረገድ በአምላክ ፊት በጎ ሕሊና እንዳለው ማስመስከር ከቻለ ብቻ ነበር። በጎ ሕሊና ለማግኘት በኢየሱስ መሥዋዕት ማመን፣ ከኃጢአቶቻችን ንስሐ መግባትና አካሄዳችንን መለወጥ ይኖርብናል። በክርስቶስ በኩል ራሳችንን ለአምላክ በጸሎት በመወሰንና ይህንን በውኃ ጥምቀት በማሳየት በጎ ሕሊና ለማግኘት መለመን ያስፈልገናል። (1 ጴጥሮስ 3:20, 21) ይህ በጎ ሕሊና ከይሖዋ ጋር ጥሩ ዝምድና እንዲኖረን ያስችለናል። በጥንት የመማፀኛ ከተሞች ውስጥ ይኖሩ የነበሩት ስደተኞች ሕጉን መታዘዝና የተሰጣቸውን ሥራ መሥራት እንደ ነበረባቸው ሁሉ በጎ ሕሊና ይዞ መኖር የሚቻለው ከአምላክ ብቃቶች ጋር በመስማማትና በታላቁ የመማፀኛ ከተማ ውስጥ እንድንሠራው የተሰጠንን ሥራ በመሥራት ብቻ ነው። የይሖዋ ሕዝቦች በአሁኑ ጊዜ የሚሠሩት ዋነኛ ሥራ የመንግሥቱን መልእክት ማወጅ ነው። (ማቴዎስ 24:14፤ 28:19, 20) ይህን ሥራ መሥራታችን በአሁኑ ጊዜ ባለው የመማፀኛ ከተማ ውስጥ አስተዋጽኦ የምናደርግ ጠቃሚ ነዋሪዎች እንድንሆን ያስችለናል።
11. በአሁኑ ጊዜ በሚገኘው የመማፀኛ ከተማ ውስጥ ደኅንነታችን ተጠብቆ ለመቆየት ከፈለግን ከምን ነገር መቆጠብ ይኖርብናል?
11 በቅርቡ ደም ተበቃዩ የደም ዕዳ ባለባቸው ሰዎች ሁሉ ላይ እርምጃ ስለሚወስድ በዛሬው ጊዜ ያለውን የመማፀኛ ከተማ ለቀን መውጣታችን ራሳችንን ለጥፋት እንድንዳርግ ያደርገናል። ዛሬ ጥበቃ ከምናገኝበት ከዚህ ከተማ የምንወጣበት ወይም ከከተማዋ የግጦሽ ሥፍራዎች ወሰን አለፍ ብለን ወደ አደገኛው ክልል የምንገባበት ጊዜ አይደለም። ኃጢአት በሚያስተሰርየው በሊቀ ካህኑ መሥዋዕት ላይ እምነት ከጎደለን ከታላቁ የመማፀኛ ከተማ ወጥተን ለጥፋት እንዳረጋለን። (ዕብራውያን 2:1፤ 6:4–6) በተጨማሪም በዓለማዊ መንገዶች መመላለስ ከጀመርን፣ በይሖዋ ድርጅት ውስጥ ዳር ዳር የምንል ከሆነ ወይም ከሰማያዊው አባታችን የጽድቅ ደረጃዎች ፈቀቅ ካልን ደኅንነት አናገኝም።—1 ቆሮንቶስ 4:4
ከመማፀኛ ከተማ መውጣት
12. ቀደም ሲል የደም ዕዳ የነበረባቸው ሰዎች በታላቁ የመማፀኛ ከተማ ውስጥ መቆየት የሚኖርባቸው ምን ያህል ጊዜ ነው?
12 በእስራኤል ውስጥ በስሕተት ነፍስ የገደለ ግለሰብ ‘ሊቀ ካህኑ እስኪሞት ድረስ’ በመማፀኛ ከተማ ውስጥ መቆየት ነበረበት። (ዘኁልቁ 35:28) ታዲያ ቀደም ሲል የደም ዕዳ የነበረባቸው ሰዎች በታላቁ የመማፀኛ ከተማ ውስጥ መቆየት የሚኖርባቸው ለምን ያህል ጊዜ ነው? ሊቀ ካህኑ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚሰጠው አገልግሎት ወደማያስፈልጋቸው ደረጃ እስኪደርሱ ድረስ ነው። ጳውሎስ “በእርሱ ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ፈጽሞ ሊያድናቸው ይችላል” ብሏል። (ዕብራውያን 7:25) የደም ዕዳ እስካለ ድረስ ፍጹም ያልሆኑ ሰዎች በአምላክ ፊት ትክክለኛ አቋም እንዲኖራቸው ሊቀ ካህኑ የሚሰጣቸው አገልግሎቶች ያስፈልጋሉ።
13. በዘመናችን “የእስራኤል ልጆች” እነማን ናቸው? “በመማፀኛ ከተማ” ውስጥስ ምን ያህል ጊዜ መቆየት አለባቸው?
13 የጥንት የመማፀኛ ከተሞች “ለእስራኤል ልጆች፣” ለእንግዶችና ለመጻተኞች ተብለው እንደ ተቋቋሙ አስታውስ። “የእስራኤል ልጆች” መንፈሳዊ እስራኤላውያን ናቸው። (ገላትያ 6:16) በምድር ላይ እስካሉ ድረስ በታላቁ የመማፀኛ ከተማ ውስጥ መቆየት ይኖርባቸዋል። ለምን? አሁንም ቢሆን ያላቸው ሰብዓዊ አካል ፍጽምና የጎደለው ስለሆነ የሰማያዊ ሊቀ ካህናቸው ኃጢአት የሚያስተሰርይ ዋጋ ያስፈልጋቸዋል። ይሁን እንጂ እነዚህ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ከሞቱ በኋላ መንፈሳዊ ሕይወት ለማግኘት ሲነሡ ሊቀ ካህኑ የሚሰጠው የስርየት አገልግሎት አያስፈልጋቸውም፤ ለዘላለም ሥጋዊ አካላቸውን በመተው ካለባቸው የደም ዕዳ ነፃ ይሆናሉ። የሊቀ ካህኑ ምሳሌያዊ ሞት ትንሣኤ ያገኙ ቅቡዓንን ከደም ዕዳ ነፃ እንዲሆኑ በማድረግ አስተማማኝ ደኅንነት ያስገኝላቸዋል።
14. ሰማያዊ ተስፋ ያላቸው ክርስቲያኖች በአሁኑ ጊዜ ባሉት የመማፀኛ ከተሞች ውስጥ መቆየት የሚኖርባቸው ለምንድን ነው?
14 በሰማይ ‘ከክርስቶስ ጋር አብረው የሚወርሱት’ ታማኝ ሆነው ምድራዊ ሕይወታቸውን በሞት እስኪጨርሱ ድረስ በታላቁ የመማፀኛ ከተማ ውስጥ መቆየታቸው አስፈላጊ የሚሆንበት ሌላ ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክንያት አለ። በሚሞቱበት ወቅት ሰብዓዊ ተፈጥሯቸውን ለዘላለም ይሠዋሉ። (ሮሜ 8:17፤ ራእይ 2:10) የኢየሱስ መሥዋዕት የሚሠራው ሰብዓዊ ተፈጥሮ ላላቸው ሰዎች ብቻ ነው። ስለዚህ ሊቀ ካህኑ ለመንፈሳዊ እስራኤላውያን እንደ ሞተ የሚቆጠረው “የመለኮት ባሕርይ ተካፋዮች” በመሆን በሰማይ ለዘላለም የሚኖሩ መንፈሳዊ ፍጥረታት ሆነው ከሞት ሲነሡ ነው።—2 ጴጥሮስ 1:4
15. ዘመናዊዎቹ “እንግዶችና መጻተኞች” እነማን ናቸው? ታላቁ ሊቀ ካህን ምን ያደርግላቸዋል?
15 ሊቀ ካህኑ ታላቁን የመማፀኛ ከተማ ለቀው ለመውጣት እንዲችሉ ለዘመናዊዎቹ “እንግዶችና መጻተኞች” በምሳሌያዊ ሁኔታ ‘የሚሞተው’ መቼ ነው? እነዚህ የእጅግ ብዙ ሰዎች አባላት ከታላቁ መከራ በኋላ ወዲያውኑ ከዚህ የመማፀኛ ከተማ ሊወጡ አይችሉም። ይህ የሚሆነው ለምንድን ነው? ምክንያቱም በዚያን ጊዜም ቢሆን ፍጽምና የጎደለውና ኃጢአተኛ ሥጋ ስለሚኖራቸው በሊቀ ካህኑ ጥበቃ ሥር መቆየት ያስፈልጋቸዋል። በሺህ ዓመት የክህነትና የንግሥና ዘመኑ በሚሰጠው ኃጢአትን የማስተሰረይ አገልግሎት በመጠቀም ወደ ሰብዓዊ ፍጽምና ይደርሳሉ። ወደ ፍጽምና ከደረሱ በኋላ ኢየሱስ ለአምላክ ያስረክባቸዋል። ከዚያም ሰይጣንና አጋንንቱ ለጥቂት ጊዜ ተፈትተው ዘላለማዊ ዕጣ ፈንታቸው የሚወሰንበትና የአቋማቸው ጽናት የሚታይበት የመጨረሻ ፈተና ይቀርብላቸዋል። መለኮታዊ ተቀባይነት በማግኘት ይህን ፈተና ስለሚያልፉ ይሖዋ ጻድቃን ናችሁ ይላቸዋል። በዚህ መንገድ የተሟላ ሰብዓዊ ፍጽምና ያገኛሉ።—1 ቆሮንቶስ 15:28፤ ራእይ 20:7–10a
16. ከታላቁ መከራ በሕይወት የሚተርፉ ሰዎች ሊቀ ካህኑ የሚሰጠው ኃጢአትን የማስተሰረይ አገልግሎት የማያስፈልጋቸው መቼ ነው?
16 ስለዚህ ከታላቁ መከራ በሕይወት የሚተርፉት ሰዎች እስከ የሺህ ዓመቱ የክርስቶስ ግዛት መጨረሻ ድረስ በታላቁ የመማፀኛ ከተማ ውስጥ በመቆየት በጎ ሕሊና እንደያዙ መኖር ይኖርባቸዋል። ፍጹማን ሰዎች ስለሚሆኑ የሊቀ ካህኑ የማስተሰርያ አገልግሎት ከዚያ በኋላ አያስፈልጋቸውም። በዚያን ጊዜ ከጥበቃው ነፃ ይሆናሉ። ከኃጢአት የሚያነጻው የኢየሱስ መሥዋዕታዊ ደም ስለማያስፈልጋቸው ኢየሱስ በሊቀ ካህንነት ደረጃ እንደ ሞተላቸው ተደርጎ ይቆጠራል። በዚያን ጊዜ የመማፀኛ ከተማውን ለቀው ይወጣሉ።
17. በክርስቶስ የሺህ ዓመት የግዛት ዘመን ትንሣኤ የሚያገኙት ሰዎች በታላቁ የመማፀኛ ከተማ ውስጥ መግባትና እዚያ መቆየት የማያስፈልጋቸው ለምንድን ነው?
17 በሺው ዓመት የኢየሱስ የግዛት ዘመን ወቅት ከሞት የሚነሡት ሰዎች በመማፀኛው ከተማ ውስጥ ገብተው ሊቀ ካህኑ እስኪሞት ድረስ እዚያ መቆየት ያስፈልጋቸዋልን? አያስፈልጋቸውም፣ ምክንያቱም በሚሞቱበት ወቅት ለሠሩት ኃጢአት የሚገባውን ዋጋ ከፍለዋል። (ሮሜ 6:7፤ ዕብራውያን 9:27) ሆኖም ሊቀ ካህኑ ወደ ፍጽምና እንዲደርሱ ይረዳቸዋል። ከሺው ዓመት በኋላ የሚመጣውን የመጨረሻ ፈተና በተሳካ ሁኔታ ካለፉም አምላክ በምድር ላይ የዘላላም ሕይወት በመስጠት ጻድቃን ናችሁ ይላቸዋል። እርግጥ የአምላክን ብቃቶች የማያሟሉና በአቋማቸው ጸንተው የመጨረሻውን ፈተና የማያልፉ ሰዎች የጥፋት ፍርድ ይበየንባቸዋል።
18. የኢየሱስ ንግሥና እና ክህነት ለሰው ልጆች ምን ዘላቂ ጥቅም ያስገኝላቸዋል?
18 እስራኤላውያን ሊቀ ካህናት በመጨረሻ ሞተዋል። ይሁን እንጂ ኢየሱስ “እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ለዘላለም ሊቀ ካህናት” ይሆናል። (ዕብራውያን 6:19, 20፤ 7:3 ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።) ስለዚህ ኢየሱስ ለሰው ልጆች እንደ መካከለኛ ሆኖ በሊቀ ካህንነት ማገልገሉን ማቆሙ ሕይወቱን እንዲያጣ አያደርገውም። እንደ ንጉሥና ሊቀ ካህን ሆኖ በማገልገል ያስገኛቸው መልካም ውጤቶች በሰዎች ዘንድ ለዘላለም ሲታወሱ ይኖራሉ። ኢየሱስ በንግሥና እና በክህነት አገልግሎቱ ለዋለላቸው ውለታ የሰው ልጆች ምን ጊዜም ሲያመሰግኑት ይኖራሉ። ከዚህም በላይ ኢየሱስ በይሖዋ ንጹሕ አምልኮ ለዘላለም ግምባር ቀደም ሆኖ ይሠራል።—ፊልጵስዩስ 2:5–11
ለእኛ የሚሆኑ ጠቃሚ ትምህርቶች
19. የመማፀኛ ከተሞችን በማቋቋም ከተደረገው ዝግጅት ጥላቻንና ፍቅርን በተመለከተ ምን ትምህርት ሊገኝ ይችላል?
19 የመማፀኛ ከተሞችን በማቋቋም ከተደረገው ዝግጅት ብዙ ትምህርቶችን ልናገኝ እንችላለን። ለምሳሌ ያህል በጥላቻ ነፍስ የገደለ ግለሰብ በመማፀኛ ከተማ ውስጥ እንዲኖር አይፈቀድለትም ነበር። (ዘኁልቁ 35:20, 21) ታዲያ በታላቁ የመማፀኛ ከተማ ውስጥ የሚኖር ሰው በልቡ ውስጥ ለወንድሙ ጥላቻ እንዲያድግ እንዴት ሊፈቅድ ይችላል? ሐዋርያው ዮሐንስ “ወንድሙን የሚጠላ ሁሉ ነፍሰ ገዳይ ነው፣ ነፍሰ ገዳይም የሆነ ሁሉ የዘላለም ሕይወት በእርሱ እንዳይኖር ታውቃላችሁ” ብሏል። እንግዲያው ‘ፍቅር ከእግዚአብሔር ስለ ሆነ እርስ በርሳችን መዋደዳችንን እንቀጥል።’—1 ዮሐንስ 3:15፤ 4:7
20. በታላቁ የመማፀኛ ከተማ ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ከደም ተበቃዩ ለመዳን ምን ማድረግ ይኖርባቸዋል?
20 በስሕተት ነፍስ የገደለ ግለሰብ ከደም ተበቃዩ ለመዳን በመማፀኛ ከተማው ውስጥ መቆየት ነበረበት። ከግጦሽ ሥፍራዎቹ ርቆ መሄድ አልነበረበትም። በታላቁ የመማፀኛ ከተማ ውስጥ ስለሚኖሩ ሰዎችስ ምን ለማለት ይቻላል? ከታላቁ ደም ተበቃይ እንዲድኑ ከተማውን ለቅቀው መውጣት የለባቸውም። በምሳሌያዊ አነጋገር ወደ ግጦሽ ስፍራዎቹ ወሰን እንዲሄዱ ከሚያደርጓቸው ማታለያዎች መጠንቀቅ ያስፈልጋቸዋል። ልባቸው ለሰይጣን ዓለም ፍቅር እንዳያድርበት ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርባቸዋል። ይህ ጸሎትንና ጥረትን የሚጠይቅ ሊሆን ቢችልም ሕይወታቸው የተመካው በዚህ ላይ ነው።—1 ዮሐንስ 2:15–17፤ 5:19
21. በአሁኑ ጊዜ ባለው የመማፀኛ ከተማ ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ምን ዘለቄታዊ ጥቅም የሚያስገኝ ሥራ በመሥራት ላይ ናቸው?
21 በጥንቶቹ የመማፀኛ ከተማዎች ውስጥ የነበሩ በስሕተት ነፍስ የገደሉ ሰዎች ምርታማ ሠራተኞች እንዲሆኑ ይጠበቅባቸው ነበር። በተመሳሳይም “የእስራኤል ልጆች” የሆኑት ቅቡዓን የመከሩ ሠራተኞችና የመንግሥት አዋጅ ነጋሪዎች በመሆን ጥሩ ምሳሌ ትተዋል። (ማቴዎስ 937, 38፤ ማርቆስ 13:10) ምድራዊ ተስፋ ያላቸው ክርስቲያኖች በአሁኑ ጊዜ ባሉት የመማፀኛ ከተሞች ውስጥ “እንግዶችና መጻተኞች” ሆነው የሚኖሩ እንደ መሆናቸው መጠን በዚህ ነፍስ አድን ሥራ በምድር ላይ ከሚገኙት ቅቡዓን ጋር የመሥራት መብት አግኝተዋል። ይህ ዘለቄታዊ ጥቅም የሚያስገኝ ሥራ ነው! በታላቁ የመማፀኛ ከተማ ውስጥ በታማኝነት የሚሠሩ ሁሉ በደም ተበቃዩ እጅ ለዘላለማዊ ሞት ከመዳረግ ይድናሉ። ከዚህ ይልቅ የአምላክ ታላቅ ሊቀ ካህን በመሆን ከሚሰጠው አገልግሎት ዘላለማዊ ጥቅሞችን ያገኛሉ። በመማፀኛው ከተማ ውስጥ ቆይተህ ለዘላለም ትኖር ይሆን?
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ታኅሣሥ 15, 1991 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 12 አንቀጽ 15 እና 16ን ተመልከት።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
◻ በምድር ላይ የሚኖሩ በቢልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የደም ዕዳ አለባቸው ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው?
◻ ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጆችን በተመለከተ ምን ሚናዎችን በመጫወት ላይ ነው?
◻ ታላቁ የመማፀኛ ከተማ ምንድን ነው? አንድ ሰው ወደዚህ ከተማ መግባት የሚችለው እንዴት ነው?
◻ ሰዎች ከታላቁ የመማፀኛ ከተማ የሚወጡት መቼ ነው?
◻ የመማፀኛ ከተሞችን በማቋቋም ከተደረገው ዝግጅት ምን ጠቃሚ ትምህርቶችን ልናገኝ እንችላለን?
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ ክርስቶስ ምን ወሳኝ ሚናዎች በመጫወት ላይ እንዳለ ታውቃለህን?