የመማፀኛ ከተሞች የአምላክ የምሕረት ዝግጅት ናቸው
“በስሕተት ነፍስ የገደለ [“ማንኛውም ሰው” አዓት] ይሸሽበት ዘንድ እነዚህ ስድስት ከተሞች ለእስራኤል ልጆች በመካከላቸው ለሚቀመጡ እንግዶችና መጻተኞች መማፀኛ ይሆናሉ።”—ዘኁልቁ 35:15
1. አምላክ ስለ ሕይወትና ስለ ደም ዕዳ ያለው አመለካከት ምንድን ነው?
በይሖዋ አምላክ ፊት የሰው ሕይወት ቅዱስ ነው። ሕይወት ደግሞ ያለው በደም ውስጥ ነው። (ዘሌዋውያን 17:11, 14) ስለዚህ በምድር ላይ ከተወለዱት ሰዎች የመጀመሪያው የሆነው ቃየን ወንድሙን አቤልን በገደለበት ወቅት በራሱ ላይ የደም ዕዳ አምጥቶ ነበር። በዚህ ምክንያት አምላክ ቃየንን “የወንድምህ የደሙ ድምፅ ከምድር ወደ እኔ ይጮኻል” ብሎታል። ግድያው በተፈጸመበት ቦታ መሬቱን የበከለው ደም ድምፅ አውጥቶ ባይናገርም እንኳ በጭካኔ ለተቀጠፈ ሕይወት ግልጽ ምሥክር ነበር። የአቤል ደም አምላክ እንዲበቀልለት ጮኾዋል።—ዘፍጥረት 4:4–11
2. ከጥፋት ውኃ በኋላ ይሖዋ ለሕይወት ያለው አክብሮት ጎላ ተደርጎ የተገለጸው እንዴት ነው?
2 ጻድቁ ኖኅና ቤተሰቡ ከዓለም አቀፉ የጥፋት ውኃ በሕይወት ተርፈው ከመርከቡ ከወጡ በኋላ አምላክ ለሰው ሕይወት ያለው አክብሮት ጎላ ተደርጎ ተገልጿል። በዚያን ጊዜ ይሖዋ የእንስሳንም ሥጋ እንዲበሉ በመፍቀድ ሰዎች የሚመገቧቸውን የምግብ ዓይነቶች አበራክቶላቸዋል፤ ሆኖም ይህ ደምን አይጨምርም። ከዚህም በላይ እንዲህ በማለት ደንግጓል፦ “ነፍሳችሁ ያለችበትን ደማችሁን በእርግጥ እሻዋለሁ፤ ከሰውም እጅ፣ ከሰው ወንድም እጅ፣ የሰውን ነፍስ እሻለሁ። የሰውን ደም የሚያፈስስ ሁሉ ደሙ ይፈስሳል፤ ሰውን በእግዚአብሔር መልክ ፈጥሮታልና።” (ዘፍጥረት 9:5, 6) ነፍሰ ገዳዩን ባገኘው ጊዜ መግደል እንዲችል ይሖዋ ለሟቹ የቅርብ ዘመድ መብት ሰጥቶት ነበር።—ዘኁልቁ 35:19
3. የሙሴ ሕግ የሕይወት ቅድስናን ጠበቅ አድርጎ የገለጸው እንዴት ነው?
3 በነቢዩ ሙሴ አማካኝነት ለእስራኤላውያን በተሰጠው ሕግ ላይ የሕይወት ቅድስና በተደጋጋሚ ጊዜያት ጎላ ተደርጎ ተገልጿል። ለምሳሌ ያህል አምላክ “አትግደል” የሚል ትእዛዝ ሰጥቶ ነበር። (ዘጸአት 20:13) የሙሴ ሕግ በእርጉዝ ሴት ላይ የሚደርሰውን ሞት የሚያስከትል አደጋ አስመልክቶ የሚናገረውም ነገር ለሕይወት አክብሮትን የሚያሳይ ነው። ሕጉ በሁለት ሰዎች ጥል ምክንያት በእሷ ወይም በማኅፀኗ ውስጥ ባለው ልጅ ላይ ሞት የሚያስከትል ጉዳት ቢደርስ ዳኞች ሁኔታውንና ነገሩ ሆን ተብሎ የተደረገ መሆኑንና አለመሆኑን ማመዛዘን እንዳለባቸው ይገልጻል። ሆኖም ቅጣቱ “ነፍስ በነፍስ” ወይም ሕይወት በሕይወት ሊሆን ይችላል። (ዘጸአት 21:22–25) ይሁን እንጂ ሰው የገደለ እስራኤላዊ የፈጸመው መጥፎ ድርጊት ከሚያስከትለው መዘዝ መዳን የሚችልበት ሁኔታ ይኖራልን?
ነፍሰ ገዳዮች ጥገኝነት የሚጠይቁበት ቦታ ነበርን?
4. በጥንት ዘመን ከእስራኤል ውጪ ጥገኝነት ማግኘት የሚቻልባቸው ቦታዎች የትኞቹ ነበሩ?
4 እስራኤላውያን ያልሆኑ ሌሎች ብሔራት ነፍሰ ገዳዮችና ሌሎች ወንጀለኞች ጥገኝነት የሚጠይቁባቸው ቦታዎች ነበሯቸው። በጥንቷ የኤፌሶን ከተማ የሚገኘውን አርጤምስ የተባለችው ሴት አምላክ ቤተ መቅደስን የመሰሉ ቦታዎች ለዚህ ዓላማ ያገለግሉ ነበር። እነዚህን የመሰሉ ቦታዎችን በተመለከተ የሚከተለው ዘገባ ቀርቧል፦ “አንዳንድ ቅዱሳን ስፍራዎች የወንጀለኞች ቁጥር እየጨመረ እንዲሄድ አስተዋጽኦ አድርገዋል፤ ጥገኝነት ማግኘት የሚቻልባቸውን ቦታዎች ብዛት በየጊዜው መገደብ አስፈላጊ ሆኖ ነበር። በአቴንስ ውስጥ ሕጋዊ እውቅና ያገኙ ጥገኝነት ማግኘት የሚቻልባቸው ቦታዎች የተወሰኑ ነበሩ (ለባሪያዎች ጥገኝነት ይሰጥ የነበረውን ቲሰስ የተባለውን ቤተ መቅደስ ለአብነት መጥቀስ ይቻላል)፤ በጢባርዮስ ዘመን ጥገኝነት ማግኘት የሚቻልባቸው ከተሞች ውስን ስለ ነበሩ ወንጀለኞች በቅዱሳን ስፍራዎች ውስጥ መከማቸታቸው በጣም አደገኛ እየሆነ መጥቶ ነበር (በ22ኛው ዓመት።)” (ዘ ጁዊሽ ኢንሳይክሎፔድያ፣ 1909 ጥራዝ 2 ገጽ 256) ከዚያ በኋላ የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት ጥገኞች ማግኘት የሚቻልባቸው ቦታዎች ሆኑ። ሆኖም ይህ ሁኔታ ሥልጣን ከሕዝብ ባለ ሥልጣናት ወደ ቀሳውስት እንዲዛወር ስላደረገ ትክክለኛውን የፍትሕ አሠራር አዛብቶታል። ውሎ አድሮ ጥገኝነት ማግኘት የሚቻልባቸውን ቤተ ክርስቲያኖች አለአግባብ መጠቀም ስለ ተጀመረ ይህ ዝግጅት እንዲቀር ተደረገ።
5. ጥንቃቄ ሳይደረግ ቀርቶ ሰው ቢሞት ሕጉ ለምሕረት ቦታ እንደማይሰጥ የሚያሳይ ምን ማስረጃ አለ?
5 በእስራኤላውያን መካከል ሆን ብለው ነፍስ የገደሉ ሰዎች ጥገኝነት አይሰጣቸውም ነበር። በአምላክ መሠዊያ አጠገብ የሚያገለግለው ሌዋዊ ካህን እንኳ ሰውን በተንኮል ቢገድል ከመሠዊያው አጠገብ ተወስዶ ይገደል ነበር። (ዘጸአት 21:12–14) ከዚህም በላይ አንድ ግለሰብ ጥንቃቄ ሳያደርግ ቀርቶ ሰው ቢገድል ሕጉ ለምሕረት ቦታ አይሰጥም። ለምሳሌ ያህል አንድ ሰው አዲስ ቤት ሲሠራ በጣሪያው ዙሪያ መከታ ማበጀት ነበረበት። አለበለዚያ አንድ ሰው ከጣሪያው ወድቆ ቢሞት በዚያ ቤት ላይ የደም ዕዳ ይሆንበታል። (ዘዳግም 22:8) ከዚህም በላይ ተዋጊ ያለው ወይፈን ባለቤት ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶት ከነበረና እንስሳውን ሳይጠብቅ ቀርቶ እንስሳው አንድ ሰው ቢገድል የወይፈኑ ባለቤት በደም ዕዳ ተጠያቂ ስለሚሆን ሊገደል ይችላል። (ዘጸአት 21:28–32) በተጨማሪም አንድ ሰው አንድን ሌባ መትቶ ቢገድለውና ይህን ያደረገው ሌባው ሊታይና ተለይቶ ሊታወቅ በሚችልበት በቀን ከሆነ በደም ዕዳ የሚጠየቅ መሆኑ አምላክ ሕይወትን ከፍ አድርጎ እንደሚመለከት ያሳያል። (ዘጸአት 22:2, 3) በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው አምላክ ያወጣቸው ፍጹም ሚዛናዊ የሆኑ ሕግጋት ሆን ብለው ሰው የገደሉ ሰዎች በሞት እንዲቀጡ የሚያደርጉ ነበሩ።
6. በጥንቷ እስራኤል ውስጥ ‘ሕይወት በሕይወት’ የሚለው ሕግ ይፈጸም የነበረው እንዴት ነው?
6 በጥንቷ እስራኤል ውስጥ የነፍስ ግድያ ተግባር ከተፈጸመ የድርጊቱ ሰለባ የሆነው ሰው ደሙ ደመ ከልብ ሆኖ አይቀርም። ነፍሰ ገዳዩ “በደም ተበቃዩ” ሲገደል ‘ሕይወት በሕይወት’ የተባለው ሕግ ይፈጸማል። (ዘኁልቁ 35:19) ደም ተበቃዩ የሟቹ የቅርብ ዘመድ ነው። ይሁን እንጂ በስሕተት ሰው የገደሉ ሰዎች ምን ይሆናሉ?
የይሖዋ የምሕረት ዝግጅት
7. አምላክ በስሕተት ነፍስ ለገደሉ ሰዎች ምን ዝግጅት አድርጎላቸው ነበር?
7 አምላክ በድንገት ወይም ሳያስቡት ሰው ለገደሉ ግለሰቦች በፍቅር ተነሣስቶ የመማፀኛ ከተሞች አዘጋጅቶላቸዋል። እነዚህን ከተሞች በተመለከተ ሙሴ እንዲህ የሚል ትእዛዝ ተሰጥቶት ነበር፦ “ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ ወደ ከነዓን ምድር ዮርዳኖስን በተሻገራችሁ ጊዜ፣ በስሕተት ነፍስ የገደለ ወደዚያ ይሸሽ ዘንድ የመማፀኛ ከተሞች እንዲሆኑላችሁ ከተሞችን ለእናንት ለዩ። ነፍሰ ገዳዩ በማኅበሩ ፊት ለፍርድ እስኪቆም ድረስ እንዳይሞት፣ ከተሞቹ ከደም ተበቃይ የመማፀኛ ከተሞች ይሁኑላችሁ። የምትሰጡአቸውም ስድስቱ ከተሞች የመማፀኛ ከተሞች ይሁኑላችሁ። በዮርዳኖስ ማዶ ሦስት ከተሞች ትሰጣላችሁ፣ በከነዓንም ምድር ሦስት ከተሞች ትሰጣላችሁ፤ . . . በስሕተት ነፍስ የገደለ [“ማንኛውም ሰው” አዓት] ይሸሽበት ዘንድ . . . የመማፀኛ ከተሞች ይሆናሉ።”—ዘኁልቁ 35:9–15
8. የመማፀኛ ከተሞች የሚገኙት የት ነበር? በስሕተት ነፍስ የገደሉ ሰዎች እነዚህን ከተሞች በቀላሉ ማግኘት እንዲችሉ ምን ተደርጎ ነበር?
8 እስራኤላውያን ተስፋ ወደ ተሰጠበት ምድር ሲገቡ በታዛዥነት ስድስት የመማፀኛ ከተሞች አቋቋሙ። ከእነዚህ ከተሞች መካከል ሦስቱ ማለትም ቃዴስ፣ ሴኬምና ኬብሮን ከዮርዳኖስ ወንዝ በስተ ምዕራብ የሚገኙ ነበሩ። ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ ደግሞ ጎላን፣ ራሞትና ቦሶር የተባሉ የመማፀኛ ከተሞች ነበሩ። ስድስቱ የመማፀኛ ከተሞች ጥሩ መንገዶች ባሉባቸው አመቺ ሥፍራዎች ይገኙ ነበር። በእነዚህ መንገዶች አስፈላጊ በሆኑ ቦታዎች ላይ “የመማፀኛ ከተማ” የሚል ጽሑፍ የሰፈሩባቸው ቅስቶች ነበሩ። እነዚህ ቅስቶች ወደ መማፀኛ ከተማ የሚወስደውን አቅጣጫ ያመለክታሉ። በስሕተት ነፍስ የገደለ ግለሰብ ሕይወቱን ለማዳን ወደሚቀርበው የመማፀኛ ከተማ ይሸሽ ነበር። እዚያም ሆኖ ከደም ተበቃዩ ሊድን ይችል ነበር።—ኢያሱ 20:2–9
9. ይሖዋ የመማፀኛ ከተሞችን ያዘጋጀው ለምን ነበር? እነዚህ ከተሞች የተዘጋጁት እነማንን ለመጥቀም ሲባል ነው?
9 አምላክ የመማፀኛ ከተሞች ያዘጋጀው ለምን ነበር? እነዚህ ከተሞች የተዘጋጁት ምድሪቱ በንጹሕ ደም እንዳትበከልና በሕዝቡ ላይ የደም ዕዳ እንዳይመጣበት ነበር። (ዘዳግም 19:10) የመማፀኛ ከተሞች የተዘጋጁት እነማንን ለመጥቀም ሲባል ነው? ሕጉ “በስሕተት ነፍስ የገደለ [“ማንኛውም ሰው” አዓት] ይሸሽበት ዘንድ እነዚህ ስድስት ከተሞች ለእስራኤል ልጆች በመካከላቸው ለሚቀመጡ እንግዶችና መጻተኞች መማፀኛ ይሆናሉ” ይላል። (ዘኁልቁ 35:15፤ ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።) ስለዚህ ይሖዋ ያለ አድልዎ ምሕረት የተሞላበት ትክክለኛ ፍርድ እንዲሰጥ ብሎ በስሕተት ነፍስ ለገደሉ (1) የአገሩ ተወላጅ ለሆኑ እስራኤላውያን፣ (2) በእስራኤል ውስጥ መጻተኞች ለሆኑ ሰዎች ወይም (3) በአገሪቱ ውስጥ ለሚኖሩ ከሌሎች አገሮች ለመጡ ሰዎች የመማፀኛ ከተሞች እንዲለዩ እስራኤላውያንን አዘዛቸው።
10. የመማፀኛ ከተሞች የአምላክ የምሕረት ዝግጅት ናቸው ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው?
10 አምላክ “የሰውን ደም የሚያፈስ ሁሉ ደሙ ይፈስሳል” በማለት በደነገገው ሕግ መሠረት በስሕተት ነፍስ የገደለ ግለሰብም ቢሆን መገደል እንደ ነበረበት ሊስተዋል ይገባል። ስለዚህ በስሕተት ነፍስ የገደለ ግለሰብ በወቅቱ ከነበሩት የመማፀኛ ከተሞች ወደ አንዱ መሸሽ የሚችለው በይሖዋ አምላክ የምሕረት ዝግጅት ነበር። ሕዝቡ ከደም ተበቃዩ ለሚሸሽ ሰው ይራሩ እንደ ነበር አያጠራጥርም። ምክንያቱም እነሱም በስሕተት ተመሳሳይ ጥፋት ሊፈጽሙና መማፀኛ ከተማና ምሕረት ሊያስፈልጋቸው እንደሚችል ያውቁ ነበር።
ወደ መማፀኛ ከተማ መሸሽ
11. በጥንቷ እስራኤል ውስጥ አንድ ሰው አብሮት የሚሠራውን ግለሰብ ሳያስበው ቢገድል ምን ሊያደርግ ይችል ነበር?
11 የሚከተለው ምሳሌ አምላክ ላዘጋጀው ጥበቃ ማግኘት የሚቻልበት የምሕረት ዝግጅት ያለህን አድናቆት ከፍ ሊያደርገው ይችላል። በጥንቷ እስራኤል ውስጥ እንጨት እየቆረጥክ እንዳለህ አድርገህ አስብ። በድንገት የመጥረቢያው አናት ከእጀታው ወለቀና ከአንተ ጋር ይሠራ የነበረውን ሰው መትቶ ገደለው እንበል። በዚህ ወቅት ምን ታደርጋለህ? ሕጉ ለዚህ ሁኔታ ዝግጅት አድርጓል። በዚህ የአምላክ ዝግጅት እንደምትጠቀም አያጠራጥርም፦ “የነፍሰ ገዳይ ወግ ይህ ነው፤ አስቀድሞ ጠላቱ ሳይሆን ባልንጀራውን ሳያስብ የገደለ ወደዚያ [ወደ መማፀኛ ከተማ] ሸሽቶ በሕይወት ይኑር። ሰው ከባልንጀራው ጋር እንጨት ሊቆርጥ ወደ ዱር ቢሄድ፣ ዛፉንም ሊቆርጥ ምሳሩን ሲያነሣ ብረቱ ከእጀታው ቢወልቅ፣ ባልንጀራውንም እስኪሞት ድረስ ቢመታው፣ . . . ከእነዚህ ከተሞች ወደ አንዲቱ ሸሽቶ በሕይወት ይኖራል።” (ዘዳግም 19:4, 5) ሆኖም ወደ መማፀኛ ከተማ ከገባህ በኋላም እንኳ ለተፈጸመው ነገር ከኃላፊነት ነፃ አትሆንም።
12. በስሕተት ነፍስ የገደለ ሰው ወደ መማፀኛ ከተማ ከገባ በኋላ ምን ነገሮች ይደረጋሉ?
12 ምንም እንኳ ጥሩ አቀባበል ቢደረግልህም በመማፀኛው ከተማ በር ላይ ለሚቀመጡት ሽማግሌዎች ሙሉ በሙሉ ስለ ሁኔታው ማስረዳት ይኖርብሃል። ወደ ከተማው ከገባህ በኋላ ግድያው በተፈጸመበት አካባቢ በከተማው በሮች ላይ የእስራኤልን ጉባኤ ወክለው የፍርድ ጉዳዮችን በሚመለከቱ ሽማግሌዎች ፊት ለፍርድ እንድትቀርብ እንደገና ወደዚያ ትላካለህ። በዚያም ግድያውን የፈጸምከው ሆን ብለህ እንዳልሆነ ለማስረዳት የምትችልበት አጋጣሚ ታገኛለህ።
ነፍሰ ገዳዮች ለፍርድ ሲቀርቡ
13, 14. ሽማግሌዎች ነፍሰ ገዳዩን በሚመረምሩበት ወቅት ማረጋገጥ የሚፈልጓቸው አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው?
13 በከተማው መግቢያ ለዳኝነት በተቀመጡት ሽማግሌዎች ፊት ለፍርድ በምትቀርብበት ወቅት ቀደም ሲል የነበራችሁ ግንኙነት ግምት ውስጥ የሚገባ መሆኑን ማወቅህ አመስጋኝ እንድትሆን እንደሚገፋፋህ አያጠራጥርም። ሽማግሌዎች ከሟቹ ጋር የነበረህን ግንኙነት በጥንቃቄ ይመረምራሉ። ሰውዬውን የገደልከው ባደረብህ ጥላቻ ምክንያት ሆን ብለህ አድፍጠህ ጠብቀህ ነውን? እንዲህ ካደረግህ ሽማግሌዎቹ ለደም ተበቃዩ አሳልፈው ይሰጡህና ትገደላለህ። እነዚህ ኃላፊነት የተሰጣቸው ሰዎች ሕጉ ‘ንጹሕ ደም ያፈሰሰ ከእስራኤል መወገድ እንዳለበት’ እንደሚናገር ያውቃሉ። (ዘዳግም 19:11–13) በተመሳሳይም ክርስቲያን ሽማግሌዎች በዛሬው ጊዜ በሚወስዱት የፍርድ እርምጃ ረገድ ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠንቅቀው የሚያውቁና ከእነሱ ጋር በመስማማት የኃጢአተኛውን የቀድሞ ዝንባሌና አኗኗር ግምት ውስጥ የሚያስገቡ መሆን ይኖርባቸዋል።
14 የከተማው ሽማግሌዎች ሟቹን አድፍጠህ የገደልከው መሆኑንና አለመሆኑን ለማረጋገጥ በቀና መንፈስ አንዳንድ ጥያቄዎችን ያቀርቡልሃል። (ዘጸአት 21:12, 13) ሰውዬውን የመታኸው አሳቻ ቦታ ላይ ጠብቀህ ነውን? (ዘዳግም 27:24) ሰውዬው በጣም ስላናደደኽ እሱን ለመግደል አንድ የተንኮል ዘዴ ሸርበሃልን? እንደዚህ ካደረግህ መሞት ይገባሃል። (ዘጸአት 21:14) በተለይ ሽማግሌዎቹ በአንተ እና በሟቹ መካከል ጠላትነት ወይም ጥላቻ ስለ መኖሩ ማወቅ ያስፈልጋቸዋል። (ዘዳግም 19:4, 6, 7፤ ኢያሱ 20:5) ሽማግሌዎቹ ግድያውን ሆን ብለህ እንዳልፈጸምከው አረጋገጡና ወደ መማፀኛ ከተማ መለሱህ እንበል። ምሕረት በማግኘትህ ምንኛ አመስጋኝ ትሆን ነበር!
በመማፀኛ ከተማ ውስጥ ያለው የአኗኗር ሁኔታ
15. በስሕተት ነፍስ የገደለ ግለሰብ ምን ብቃቶችን እንዲያሟላ ይጠበቅበት ነበር?
15 በስሕተት ነፍስ የገደለ ሰው በመማፀኛ ከተማ ውስጥ ወይም ከወሰኑ ከ1,000 ክንድ (ከ445 ሜትር ገደማ) በላይ ሳይርቅ የመቆየት ግዴታ ነበረበት። (ዘኁልቁ 35:2–4) ከዚያ አካባቢ ርቆ ከሄደ ደም ተበቃዩ ሊያገኘው ይችላል። በእንደዚህ ዓይነቶቹ ሁኔታዎች ተበቃዩ ነፍሰ ገዳዩን ቢገድለው ሊጠየቅ አይችልም ነበር። ይሁን እንጂ ነፍሰ ገዳዩ በካቴና አይታሰርም ወይም እስር ቤት አይገባም። የመማፀኛ ከተማው ነዋሪ እንደመሆኑ መጠን አንድ ሙያ የመማር፣ የመሥራትና የኅብረተሰቡ ጠቃሚ አባል ሆኖ የማገልገል ግዴታ ነበረበት።
16. (ሀ) በስሕተት ነፍስ የገደለ ግለሰብ በመማፀኛ ከተማ ውስጥ መቆየት የሚኖርበት ለምን ያህል ጊዜ ነው? (ለ) የሊቀ ካህኑ ሞት ነፍሰ ገዳዩ ከመማፀኛ ከተማ እንዲወጣ የሚያስችለው ለምንድን ነው?
16 በስሕተት ነፍስ የገደለ ግለሰብ በመማፀኛ ከተማ ውስጥ መቆየት የሚኖርበት ምን ያህል ጊዜ ነው? ምናልባት ቀሪ ሕይወቱን በሙሉ እዚያ ማሳለፍ ሊያስፈልገው ይችላል። ያም ሆነ ይህ ሕጉ እንዲህ በማለት ይገልጻል፦ “ዋነኛው ካህን እስኪሞት ድረስ በመማፀኛው ከተማ ውስጥ መቀመጥ ይገባው ነበርና። ዋነኛው ካህን ከሞተ በኋላ ግን ነፍሰ ገዳዩ ወደ ርስቱ ምድር ይመለሳል።” (ዘኁልቁ 35:26–28) ሊቀ ካህኑ መሞቱ በስሕተት ነፍስ የገደለው ግለሰብ የመማፀኛውን ከተማ ለቆ እንዲወጣ የሚያስችለው ለምንድን ነው? ሊቀ ካህኑ በብሔሩ ውስጥ ካሉት ታላላቅ ሰዎች አንዱ ነበር። ስለዚህ የእሱ ሞት በቀላሉ የሚታይ ባለመሆኑ የእስራኤል ነገዶች በሙሉ የእሱን ሞት ይሰሙ ነበር። በዚህ ጊዜ ወደ መማፀኛ ከተሞች የሸሹት ስደተኞች በሙሉ ደም ተበቃዮች ይገድሉናል የሚል ስጋት ሳይኖርባቸው ወደ ቤታቸው መመለስ ይችሉ ነበር። ለምን? የአምላክ ሕግ ተበቃዩ ነፍሰ ገዳዩን ለመግደል ያለው አጋጣሚ ሊቀ ካህኑ ሲሞት እንደሚያበቃ ስለሚናገር ነው። ይህን ደግሞ ማንም ያውቃል። ከዚህ በኋላ የቅርብ ዘመዱ ለሟቹ ቢበቀልለት ተበቃዩ ራሱ ነፍሰ ገዳይ ስለሚሆን ለነፍሰ ገዳይ የሚገባውን ቅጣት መቀበሉ አይቀርም።
ዘላቂ ጥቅሞች
17. በስሕተት ነፍስ በገደለ ግለሰብ ላይ የሚጣሉበት እገዳዎች ምን ውጤቶች ሊያስከትሉ ይችላሉ?
17 በስሕተት ነፍስ በገደለ ግለሰብ ላይ የሚጣሉበት እገዳዎች ምን ጥቅም ሊያስገኙ ይችሉ ነበር? እነዚህ እገዳዎች ሰው መግደሉን እንዲያስታውስ ያደርጉታል። ከዚያ በኋላ ከመቼውም ጊዜ በላይ ሰብዓዊ ሕይወትን እንደ ቅዱስ ነገር አድርጎ ሊመለከተው ይችላል። ከዚህም በላይ የተደረገለትን ምሕረት ፈጽሞ ሊረሳ አይችልም። ምሕረት ስለ ተደረገለት ለሌሎች ምሕረት ለማድረግ እንደሚፈልግ አያጠራጥርም። የመማፀኛ ከተሞች መቋቋማቸውና እዚያ በሚገቡት ሰዎች ላይ አንዳንድ እገዳዎቹ መጣላቸው ለመላው ሕዝብ ጥቅም አስገኝቷል። ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? ለሰው ሕይወት ጥንቃቄ የማያደርጉ ወይም ግዴለሾች መሆን እንደሌለባቸው እንደሚያስገነዝባቸው የተረጋገጠ ነው። ክርስቲያኖችም የሞት አደጋ ሊያስከትል የሚችል ጥንቃቄ የጎደለው ተግባር ከመፈጸም መቆጠብ እንደሚያስፈልጋቸው ማስታወስ ይኖርባቸዋል። ከዚህም በላይ አምላክ የመማፀኛ ከተሞችን በማቋቋም ያደረገው የምሕረት ዝግጅት አስፈላጊ ሆኖ በሚገኝበት ወቅት ምሕረት እንድናሳይ ሊገፋፋን ይገባል።—ያዕቆብ 2:13
18. አምላክ የመማፀኛ ከተሞችን በማቋቋም ያደረገው ዝግጅት ጠቃሚ የሆነው በምን መንገዶች ነው?
18 ይሖዋ አምላክ የመማፀኛ ከተሞችን በማቋቋም ያደረገው ዝግጅት በሌሎች መንገዶችም ይጠቅማል። ሕዝቡ አንድን ነፍሰ ገዳይ ለፍርድ ቀርቦ ጥፋተኛነቱ ከመረጋገጡ በፊት አድነው ለመያዝና ለመቅጣት የተደራጁ ቡድኖችን አያቋቁሙም። ከዚህ ይልቅ ግድያውን የፈጸመው ሆን ብሎ እንዳልሆነ አድርገው በማሰብ ከአደጋ ወደሚያመልጥበት ቦታ እንዲደርስ ይረዱታል። ከዚህም በላይ የመማፀኛ ከተሞችን በማቋቋም የተደረገው ዝግጅት በአሁኑ ጊዜ ካለው ነፍሰ ገዳዮችን በእስር ቤት ከማጎር ተግባር በጣም የተለየ ነው። እነዚህ ነፍሰ ገዳዮች በእስር ቤት ውስጥ ከሕዝብ የገንዘብ ድጋፍ ከማግኘታቸውም በተጨማሪ ከሌሎች ዓመፀኞች ጋር የቅርብ ግንኙነት ስለሚፈጥሩ ከቀድሞው የከፉ ወንጀለኞች ይሆናሉ። የመማፀኛ ከተሞችን በማቋቋም የተደረገው ዝግጅት ብዙውን ጊዜ እስረኞች ለማምለጥ የሚሞክሩባቸውን ዓይነት ከፍተኛ ወጪ የሚደረግባቸው በብረት የታጠሩ እስር ቤቶችን መሥራት፣ መንከባከብና ዘብ አቁሞ ማስጠበቅ የሚጠይቅ አልነበረም። በዚህም ምክንያት ነፍሰ ገዳዩ ራሱ “እስር ቤቱን” ፈልጎ ይሄድና ከዚያ የሚወጣበት ጊዜ እስኪደርስ እዚያው ይቆያል። በተጨማሪም ሌሎች ሰዎችን በሚጠቅም አንድ ተግባር ላይ በመሠማራት መሥራት ነበረበት።
19. የመማፀኛ ከተሞችን በተመለከተ ምን ጥያቄዎች ይነሣሉ?
19 ይሖዋ በስሕተት ነፍስ የገደሉ ሰዎች ጥበቃ ማግኘት እንዲችሉ በእስራኤል ውስጥ የመማፀኛ ከተሞችን ማዘጋጀቱ በእርግጥም የምሕረት ዝግጅት ነው። ይህ ዝግጅት ለሕይወት አክብሮት እንዲኖራቸው እንዳደረገ ምንም አያጠራጥርም። ይሁን እንጂ የጥንቶቹ የመማፀኛ ከተሞች በ20ኛው መቶ ዘመን ለሚኖሩ ሰዎች ትርጉም አላቸውን? በይሖዋ አምላክ ፊት በደም ዕዳ ተጠያቂዎች ሆነን ሳለ ምሕረቱ እንደሚያስፈልገን ሳንገነዘብ ቀርተን ይሆን? በእስራኤል ውስጥ የነበሩ የመማፀኛ ከተሞች ለእኛ ዘመናዊ ጠቀሜታ ይኖራቸዋልን?
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
◻ ይሖዋ የሰውን ሕይወት የሚመለከተው እንዴት ነው?
◻ አምላክ በስሕተት ነፍስ ለገደሉ ሰዎች ምን ዝግጅት አድርጎላቸው ነበር?
◻ አንድ ነፍሰ ገዳይ ወደ መማፀኛ ከተማ መግባት የሚችለው እንዴት ነበር? እዚያስ ምን ያህል ጊዜ መቆየት ነበረበት?
◻ ሳያስበው ነፍስ በገደለ ግለሰብ ላይ የሚጣሉት እገዳዎች ምን ውጤቶች ሊያስከትሉ ይችሉ ነበር?
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ካርታ]
የእስራኤላውያን የመማፀኛ ከተሞች በአማካይ ቦታዎች ላይ ይገኙ ነበር
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
ቃዴስ የዮርዳኖስ ወንዝ ጎላን
ሴኬም ራሞት
ኬብሮን ቦሶር